Melinab Health Hub

Description
Sharing Medical Knowledge
Consult @melakutaye
We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated 2 months, 3 weeks ago

Last updated 2 months, 2 weeks ago

ይህ ስለ Manchester United መረጃዎችን የሚያገኙበት የ Telegram ቻናል ነው 🇪🇹
--------------------------------------------------------------
☞︎| ስለ ማንቸስተር ዩናይትድ ትኩስ መረጃዎች
☞| ቀጥታ ስርጭቶች ከየስታድየሞቹ
☞| የዝውውር ዜናዎች
☞| ስለ ማንችስተር ዩናይትድ ታሪኮች

📩 ለማስታወቂያ ስራ DM :- @Marcoabdu

Last updated 1 month, 2 weeks ago

1 week, 6 days ago

የታይሮይድ ሆርሞን ዕጥረት ( hypothyroidism)

የታይሮይድ ዕጢ ፊት ለፊት ከሚገኘው የአንገታችን ክፍል ከማንቁሪት ግርጌ የሚገኝ ለሰዉነታችን አስፈላጊ ንጥረ ቅመሞችን ( ሆርሞኖችን) የሚያመርት የአካል ክፍላችን ነዉ።

በቅርፁም ቢራቢሮ መሰል ሲሆን ክብደቱ በአማካኝ ከ 20 እሰከ 25 ግራም እንደሚመዝን ባለሙያዎች ይገልፃለ፡፡

በታይሮይድ ሆርሞን እጥረት በአለማችን ላይ ከ5 በመቶ በላይ ሰዎች እንደሚጠቁ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የስኳርና ሆርሞን ሰብ ስፔሻሊስት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር መላኩ ታዬ ናቸዉ።

የታይሮይድ ሆርሞን ዕጥረት( hypothyroidism) ምንድን ነው?

የታይሮይድ ሆርሞን ዕጥረት ታይሮይድ ዕጢ በቂ ሆርሞን ማምረት ሳይችል ሲቀር የሚከሰት ችግር ነው ይላሉ፡፡

መንስኤው ምንድን ነው?

- የአዮዲን እጥረት
- የታይሮይድ ብግነት
- የታይሮይድ እጢ አፈጣጠር ችግር
- በተፈጠሩ ችግሮች እንቅርት በቀዶ ህክምና ሲወገድ በጨረር ህክምና ከተጎዳ ሊከሰት ይችላል፡፡

ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

- ብርድ ብርድ ማለት፣ ቅዝቃዜን አለመቋቋም
- በቀላሉ ክብደት መጨመር፣ ብዙ የምግብ ፍላጎት አለመኖር
- የቆዳ መድረቅና አመዳምነት፣ ማሳከክ፣ የጸጉር መሳሳትና መነቃቀል
- ድባቴ፣ ከፍተኛ የድካም ስሜት
- የድምጽ መጎርነን
- የሰውነት ማበጥ በተለይም በፊታችን ላይ ከአይናችን ዙርያ ማኮፍኮፍና ማበጥ
- የልብ ምት መቀነስ እና የልብ ድካም
- በሴቶች ላይ የወር አበባ መዛባት
- የሆድ ድርቀት ሊታዩ የሚችሉ ምልክቶች ናቸው፡፡

ህክምናዎቹ ምንድን ናቸው?

የታይሮይድ ሆርሞን ዕጥረት የሚታከመው ያነሰውን ሆርሞን በሰውሰራሽ የታይሮይድ ሆርሞን መድሃኒቶች በመተካት ነው። ከአንዳንድ ጊዜያዊ የሆርሞን መዛባት ምክንያቶች በስተቀር የዕድሜ ልክ ህክምና ይፈልጋል። የሆርሞን ህክምናው በትክክል ከተወሰደ ጤናማ ሕይወት መቀጠል እንደሚቻል ባለሙያ ይናገራሉ ፡፡

በመጨረሻም ማንኛውም ሰው ግልጽ ያልሆኑ የህመም ምልክቶች ካለው፣ ያልተለመደ የድካም ስሜት ከበዛ፣ ብዙ ሳንበላ ክብደት ከጨመረ ወይም የማስታወስ ችግር ካጋጠመ የታይሮይድ ሆርሞን ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ዶ/ር መላኩ ተናግረዋል፡፡

ሊዲያ ደሳለኝ
Ethio FM 107.8

የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

3 weeks, 1 day ago

የስኳር ህመም ለሚታከሙ ሴቶች የቅድመ እርግዝና እንክብካቤ

ትክክለኛ ቅድመ እርግዝና የስኳር ህክምና እና ክትትል ማድረግ እርግዝና ጤናማ እንዲሆን ያስችላል፤ ልጅም ደህና እንዲወለድ ይረዳል። ጤናማ እርግዝና የሚጀምረው ከመፀነስሽ በፊት ነው። የቅድመ እርግዝና እንክብካቤ በጣም አስፈላጊ ነው።

የስኳር ህመም ያለባቸው ሴቶች አስቀድመው ማቀድና ማስተካከያ ማድረግ ለተሻለ ውጤት ወሳኝ ነው። የጽንስ ጤና ችግሮች እንዳይከሰቱ ይረዳል። ስለሆነም የእርግዝና ጊዜን በደንብ ማሰብ ያስፈልጋል። የስኳር መጠኑ አሪፍ ቁጥጥር ደረጃ እስኪደርስ ድረስ አስተማማኝ የእርግዝና መከላከያ መጠቀም ይመከራል።

ስለዚህ ለማርገዝ እያሰብሽ ከሆነ እና የስኳር ህመም ካለብሽ ይህን ወሳኝ የቅድመ እርግዝና እንክብካቤ ምክር እናካፍልሽ።

1️⃣ የግሉኮስ ቁጥጥርን ማሻሻል
ከማርገዝ በፊት በተቻለ መጠን የስኳር ቁጥጥር ደረጃ በደንብ ማስተካከል ይገባል። በተቻለ አቅም ስኳሩን ወደ ጤናማ መጠን ማድረስ ይመከራል። ለአብዛኛዎቹ ሴቶች የሶስት ወር ስኳር ክምችት መጠን (A1c) ከ6.5% በታች ቢሆን ይመረጣል። በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህንን የስኳር ግብ ማሳካት በእርግዝና እና ወሊድ ወቅት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮችን፣ ውርጃ እና ሌሎች ችግሮችን በእጅጉ ይቀንሳል።
ይህን ለማድረግ ከሌላው ጊዜ በተለዬ ቶሎ ቶሎ ክትትል ማድረግ ጥሩ ነው። የደም ውስጥ የግሉኮስ መጠንን በየጊዜው መከታተል (በባዶ ሆድ እና ከምግብ በኋላ) ቆንጆ የግላይሴሚክ ቁጥጥር ለማምጣት አስፈላጊ ነው።
መድሃኒቶችን፣ አመጋገብን፣ ክብደትን ወዘተ ማስተካከልና ማሻሻል ግብን በቶሎ ለመድረስ ይረዳል። ከስኳር ባለፈ አጠቃላይ ጤንነት ለማረጋገጥ ከስኳር ሃኪም፣ የማህፀን ሐኪም ወይም ሌሎች ባለሙያዎች ጋር ይወያዩ።

2️⃣ የመድኃኒት ማስተካከያዎች ማድረግ
አንዳንድ መድሃኒቶች ለእርግዝና ላይመጥኑ ይችላሉ። ስለሆነም ሁሉንም የሚወስዷቸውን መድሃኒቶች መቀየር ወይም ማቆም ይፈልግ እንደሆነ ከሃኪም ጋር ይወያዩ።
ለአብነትም የስኳር መድሃኒቶች ለእርግዝና የማይመከሩ ክኒኖች ከሆኑ ወይም ስኳሩን በደንብ እየተቆጣጠሩት ካልሆነ ወደ ኢንሱሊን ሊቀየርልዎት ይችላል።
ጽንስ የሚጎዱ አንዳንድ የግፊት መድሃኒቶች፣ የኮሌስትሮል መድሃኒት፣ ደም ማቅጠኛዎች፣ ማስታገሻዎች፣ የሚጥል ህመም መድሃኒቶች ወዘተ መቋረጥ ወይም ለእርግዝና በሚመጥኑ አቻ መድሃኒቶች መቀየር ሊያስፈልግ ይችላል።

3️⃣ የፎሌት ቫይታሚን መውሰድ (Folic Acid Supplementation)
ይህ ቫይታሚን ለሽል አፈጣጠርና ጽንስ እድገት ይጠቅማል። በተለይም የአንጎልና ህብለ ሰረሰር ቱቦዎች አፈጣጠር እክሎችን ይቀንሳል።

4️⃣ የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻያዎች ማድረግ
ማህጸን ለእርግዝና ዝግጁ እንዲሆን የአኗኗር ዘይቤን አስቀድሞ ማስተካከል ይመከራል። የተመጣጠነ እና ጤናማ አመጋገብ ማዘውተር ለእርግዝና ጤና ወሳኝ ነው። የተረጋጋ እና የማይዋዥቅ ስኳር እንዲኖረን የተሻሻለ አመጋገብ ስርዓት ማዳበር ይገባል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የስኳር ቁጥጥርን እና አጠቃላይ ጤናን ያሻሽላል።
ሌላው ወሳኝ ነገር ከእርግዝና በፊት ክብደት ማስተካከል ነው።
አልኮል፣ ሲጋራ እና ሌላም ጎጂ ሱስ ካለ እርግ አርጎ ማቆም ይመከራል።

5️⃣ የስኳር ተያያዥ ችግሮችን ለመለየት ቅድመ ምርመራዎች ማሰራት
• የአይን ምርመራ ማድረግ፡ እርግዝና ከስኳር ጋር የተያያዘ የአይን ነርቭ ችግርን (Diabetic Retinopathy) ሊያባብሰው ስለሚችል አጠቃላይ የአይን ምርመራ በተለይም የአይን ነርቭ ምርመራ ያድርጉ
• የኩላሊት ምርመራ ማድረግ፡ በሽንትና ደም ናሙና የሚሰራ የኩላሊት ክትትል ያስፈልጋል።
• ሌሎችም እንደ ልብ ህመም ያሉ የደም ሥር ችግሮችን (cardiovascular conditions) መታዬት ጥሩ ነው።

6️⃣ መደበኛ የእርግዝና ክትትል ወዲያውኑ መጀመር
እርግዝና እንደታዎቀ ወዲያዉኑ የእርግዝና ክትትል ጀምሪ። እንደአስፈላጊነቱ የስኳር መድሃኒቱን ቶሎ ቶሎ ማስተካከል ስለሚያስፈልግ ከሃኪምሽ ጋር በቅርብ መመካከር ቀጥይ።
እነዚህን ምክሮችን በመተግበር የስኳር ህመም ያለባቸው ሴቶች ጤናማ እርግዝና እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል። ጤናማ ልጅ መውለድ ያስችላልቸዋል።

@hakimmelaku

3 weeks, 1 day ago

በእርግዝና ወቅት የሚደረግ የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም እናት አስፈላጊነት (Universal gestational diabetes screening)

በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር ህመም ሳይታዎቅ ጽንስ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። የእርግዝና ጊዜ ስኳር በርካታ የእናትና ጽንስ ጤና ችግሮችን ለምሳሌ የጽንስ መፋፋትና መተለቅ ፣ ያለጊዜው መውለድ፣ የእርግዝና ጊዜ የደም ግፊት፣ የጽንስ መታፈን፣ የአራስ ህጻን የመተንፈስ ችግርና የጨቅላው የደም ስኳር ማነስ ወዘተ ያሉ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።

ስለሆነም ለሁሉም ነፍሰ ጡር እናቶች የስኳር ቅድመ ምርመራ ማድረግ ለጤናማ እርግዝና ወሳኝ ነዉ። 

የእርግዝና ጊዜ የስኳር ቅድመ ምርመራ መቼ ይሰራል?

የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም ነፍሰ ጡር እናት የሚሰራው በ24 እና 28 ሳምንታት መካከል ባለው አማካኝ የእርግዝና ወራት ነው። ይህ ጊዜ የተመረጠው ስኳር አምጭ የሆኑት የእርግዝና ሆርሞኖች የሚበዙበት ወቅት ስለሆነ ነው። 

ነገር ግን ከፍተኛ የስኳር ተጋላጭነት ያላቸው ሴቶች (ለምሳሌ ከዚህ በፊት በነበረው እርግዝና ስኳር የታየባቸው፣ ከፍተኛ ውፍረት ያላቸው ወይም ሌላ የሆርሞች መዛባት ችግር ያለባቸው እናቶች) ከ24 ሳምንትም ቀደም ብለው እርግዝና እንደታወቀ ወዲያውኑ መመርመር ይኖርባቸዋል ።

ዛሬዉኑ የእርግዝና ጊዜ ስኳር ምርመራ ለማሰራት ከሐኪምዎ ጋር ይነጋገሩ። 

ስለ የእርግዝና ጊዜ ስኳር ጥያቄዎች አሉዎት? አስተያየትዎትን ይጻፉልን። 

ለተጨማሪ መረጃ https://vm.tiktok.com/ZMkCkmxhP/

2 months, 2 weeks ago
**የቀጣይ አመት (2025) ትልም**

የቀጣይ አመት (2025) ትልም

በተረጋገጠ ሳይንሳዊ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ የጤና መረጃ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ይዳረስ ዘንድ የጤና ምክሮችን በዘርፈ ብዙ መንገዶችና የሚዲያ አማራጮች ማጋራት ከጀመርኩ አንድ አመት ሞላው።

ላበረታታችሁኝ ሁሉ ላቅ ያለ ምስጋና ይድረሳችሁ።

በሚመጣው የፈረንጆች አመት 2025ም በተሻለ ይዘትና አቀራረብ የጤና መረጃን የበለጠ ተደራሽ ማድረግ ምኞቴ ነው።

የጤና መረጃን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ግብረ መልስ በመስጠት፣ ሌሎችን በመጋበዝና በማጋራት ይተባበሩኝ።

Telegram: ቴሌግራም https://t.me/HealthifyEthiopia
YouTube: https://www.youtube.com/@healthifyethiopia
TikTok: https://www.tiktok.com/@hakimmelaku

2 months, 2 weeks ago
**2024 ን በጨረፍታ: ላበረታታችሁኝ ሁሉ ላቅ …

2024 ን በጨረፍታ: ላበረታታችሁኝ ሁሉ ላቅ ያለ ምስጋና ይድረሳችሁ!

በተረጋገጠ ሳይንሳዊ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ የጤና መረጃ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ይዳረስ ዘንድ የጤና ምክሮችን በዘርፈ ብዙ መንገዶችና የሚዲያ አማራጮች ማጋራት ከጀመርኩ አንድ አመት ሞላው።

በአለፈው አንድ አመት ዋና ዋና ስኬቶች መካከል፤

በብሎግና ማህበራዊ ሚዲያ
? >100 ፖስቶች
? >10000 ቤተሰቦች

ከባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ መስራት
✍️ በርካታ ጽሁፎች በብሔራዊ ሚዲያዎች እና በታዋቂ መጽሔቶች ላይ ተደራሽ ማድረግ

ማህበራዊ ሃላፊነት መወጣት
✍️ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአንባቢዎች ግብረ መልስ (የጤና መረጃዎቹ እንደጠቀማቸው የሚገልጹ)

✍️ በርካታ የኦንላይን ነጻ ህክምና እና ምክር አገልግሎት

✍️ በርካታ የተሳሳቱ የጤና መረጃዎችን ማረም

Telegram: https://t.me/HealthifyEthiopia
Youtube: https://www.youtube.com/@healthifyethiopia
TikTok: https://www.tiktok.com/@hakimmelaku

@hakimmelaku

2 months, 2 weeks ago
**ለስኳር ታካሚዎች የፍራፍሬ አመጋገብ መመሪያ**

ለስኳር ታካሚዎች የፍራፍሬ አመጋገብ መመሪያ
የስኳር ታካሚዎች ከሚያነሷቸው መጠይቆች መካከል ‘ፍራፍሬ መመገብ እችላለሁ ወይ?’ የሚለው የተለመደ ጥያቄ ነው።

የስኳር ታካሚዎች ፍራፍሬዎችን እንዴት መመገብ እንደሚችሉ በርካታ እርስ በእርስ የሚጣረሱ መረጃዎች ስለሚሰሙ ግራ መጋባት ይፈጥራሉ። ይህን ፍራፍሬ ብላ፣ ያንን ፍሬ እንዳትነካ፣ ይህ የተፈቀደ ነው፣ ያኛው ግዝት ነው ወዘተ የሚሉ ውዥንብር የሚፈጥሩ ያልተረጋገጡ የአመጋገብ ምክሮች አሉ። አንዱ ሃኪም አዎ ያለውን ሌላኛው አይ ብሎ ሊያወዛግበን ይችላል።

ይህ ጽሁፍ የስኳር ታካሚዎች ፍራፍሬዎችን በማእዳቸው እንዴት ማካተት እንደሚችሉ ያስረዳል። እርስዎ እራስዎ የስኳር ታካሚ ከሆኑ ወይም የሚያውቁት ስኳር ያለበት ሰው ካለ ይህ መረጃ መነበብ አለበት።

ፍራፍሬዎችን በስኳር ህክምና አመጋገብ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ያስፈልጋል?

በስኳር ህመም እና በፍራፍሬ አመጋገብ ላይ በጣም ከተለመዱት ሳይንሳዊ ያልሆኑ መረጃዎች መካከል አንዱ ‘የተወሰኑ ፍራፍሬዎች ሙሉ በሙሉ የተከለከሉ ናቸው’ የሚል ይገኝበታል። ይህንን በሳይንሳዊ ጥናቶች ያልተረጋገጠ መረጃ ከእውነታ መለየት ይገባል። እንደ እውነቱ ከሆነ አብዛኛዎቹ ፍራፍሬዎች በስኳር ህመም አመጋገብ እቅድ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።

የስኳር ህመም ላለባቸው ሰዎች ሙሉ በሙሉ የተገዘተ ምንም አይነት ፍራፍሬ የለም። ዋናው ቁምነገር የፍራፍሬ አጠቃቀም መመጠን እና በቶሎ ስኳር ከፍ የማያደርጉትን አይነቶች መምረጡ ላይ ነው።

ፍራፍሬዎች ለጤና አስፈላጊ የሆኑ ቪታሚኖች፣ ማዕድናት እና ፋይበር ምንጭ ናቸው። በማስተዋል መጥነን ከተጠቀምንባቸው ለስኳር ታካሚዎች ተስማሚ የሆነ ምግብ አንድ አካል ሊሆኑ ይችላሉ።

ለስኳር ታካሚዎች የፍራፍሬ አመጋገብ መመሪያ ምን ይመስላል?

የስኳር ህመም አለብን ማለት ፍራፍሬዎችን ዞር ብለን ማየት የለብንም ማለት አይደለም። ነገር ግን የደም ስኳር መጠን በጣም ከፍ ሳይል እንዴት ፍራፍሬዎችን በጥበብ መመገብ እንዳለብን ማወቅ ይገባል።

ዝቅተኛ የስኳር መጠን ያላቸውን ፍራፍሬዎች መምረጥ
አብዛኛዎቹ ፍራፍሬዎች በውስጣቸው ተፈጥሯዊ ስኳር ቢኖራቸውም ከፍተኛ ፋይበር ይዘት ስላላቸው በተመገብን ከመቅጽበት የደም ስኳር መጠን በድንገት እንዳያሻቅብ ያደርጋል (low glycemic index)።

መጠናችንን መገደብ

ፍራፍሬ ስንመገብ ዋና ቁልፉ ልከኝነት ነው። ምንም እንኳ ፍራፍሬዎች ለጤናችን ጠቃሚ ቢሆኑም ቢሆን አብዝተን ከበላን የስኳር መጠን ከፍ ያደርጋሉ። ስለሆነም ፍራፍሬዎችን በተመጣጣኝ መጠን መጠቀም አስፈላጊ ነው። ሁሌም ቢሆን የምንመገበውን ፍራፍሬ መጠን መመጠን (Portion control) ይገባል።

ከጭማቂ ይልቅ ሳይጨመቅ ሙሉ ፍራፍሬዎችን መብላት

የፍራፍሬ ጭማቂ መጠጣት በጤና እና የደም ስኳር ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ሙሉ ፍሬውን ከመብላት በተቃራኒ ነው። የፍራፍሬ ጭማቂ መጠጣት ሙሉ ፍሬውን ከመብላት በበለጠ ፍጥነት በደም ውስጥ ያለው የግሉኮስ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል።

ማስታወሻ፦ የተለያዩ ፍራፍሬዎች የደም ስኳር መጠን ላይ ያላቸው ተጽእኖ የተለያዬ ስለሆነ የደም ስኳር ልኬትን በቅርበት መከታተል ይመከራል። ከምግብ በኋላ ያለን የደም ግሉኮስ መጠንዎን በመፈተሽ የትኛው ፍራፍሬ እና ምን ያህል መጠን ስኳሬን ከፍ ያደርገዋል የሚለውን መረዳት ይቻላል። ሁልጊዜም የደም ስኳር መጠንን መከታተል እና ከጤና ባለሙያ እና የስነ ምግብ ባለሙያ ጋር በመመካከር ግለሰቡን ያማከለ የምግብ እቅድ ማዘጋጀት ይመከራል።

የዚህን ጽሁፍ ሙሉ መረጃ በዶ/ር መላኩ ታዬ ብሎግ https://melakutaye.com/fruits-in-diabetes-diet/ ማንበብና ለሌሎችም ማጋራት ይችላሉ።

@hakimmelaku
@HealthifyEthiopia

4 months, 1 week ago
Melinab Health Hub
4 months, 1 week ago
**የበለጸጉ ምግቦች (fortified foods)** በኢትዮጵያ የምግብ …

የበለጸጉ ምግቦች (fortified foods) በኢትዮጵያ የምግብ ህግ

ምግቦችን ማበልፀግ (food fortification) ሲባል በምግብ ዝግጅት እና ማሸግ ወቅት ምግቦች ላይ ቪታሚኖችን እና ማዕድኖችን በመጨመር የምግብነት ይዘታቸው ላይ እሴት ለመጨመር የሚደረግ ሂደት ነው። ይህ ተዘውትረው የሚበሉ ዋነኛ ምግቦችን ማበልፀግ ተግባር የምግብ እጥረትን ለመከላከል አንዱ ዉጤታማ ስትራቴጂ ነው። ምግብን ለማሻሻል እና የምግብ እጥረቶችን ለመከላከል አስተማማኝ ዘዴ ሲሆን በርካታ የጤና፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎች አሉት።

በኢትዮጵያ በህግ አስገዳጅነት እንዲበለጽጉ የተደረጉ የምግብ ምርቶች የሚከተሉት ናቸው።

1️⃣ የምግብ ጨው ?? በአዮዲን የበለጸገ መሆን አለበት።

2️⃣ የምግብ ዘይት በቫይታሚን ኤ እና ቫይታሚን ዲ የበለጸገ መሆን አለበት።

3️⃣ የስንዴ ዱቄት ? ?ቫይታሚን ቢ እና ዚንክ የበለጸገ መሆን አለበት።

እነዚህን ምግቦች አምራቾች አበልጽገዉ ምርታቸዉ ላይ ‘የበለፀገ fortified’ የሚል ሎጎ መለጠፍ ግዴታ አለባቸው።

በመሆኑም እነዚህን በአስገዳጅነት እንዲበለፅጉ የተመረጡ ምግቦች ሲገዙ የበለፀገ ምግብ ምልክት የለጠፉ መሆናቸውን ልብ ይበሉ።

ዋቢ: የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን

የዚህን ጽሁፍ ሙሉ መረጃ በዶ/ር መላኩ ታዬ ብሎግ https://melakutaye.com/food-fortification-in-ethiopia/ እንዲያነቡና ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።

ስለአዮዲን ምግብ አስፈላጊነት በዚህ ቪዲዮ ተጨማሪ ይመልከቱ https://vm.tiktok.com/ZMrck1Bo2/

@hakimmelaku

4 months, 1 week ago
**በዘር የሚተላለፍ የኮሌስትሮል ህመም እንዲለዩ የተላለፈ …

በዘር የሚተላለፍ የኮሌስትሮል ህመም እንዲለዩ የተላለፈ ጥሪ - call for community diagnosis and early referral of Familial Hypercholesterolemia

በዘር የሚተላለፍ የኮሌስትሮል ህመም (የፋሚሊያል ሃይፐርኮሌስትሮሌሚያ, Familial Hypercholesterolemia, FH) በጣም ከፍተኛ የኮሌስትሮል መብዛት የሚያመጣና ለልብ ህመም የሚያጋልጥ የተለመደ በዘር የሚወረስ በሽታ ነው። ሮጠው ያልጠገቡ ልጆችን እና ወጣቶችን በልብ ህመም የሚያሰቃይ ህመም ሲሆን በጊዜ ካልታከመ ገዳይ በሽታ ነው።

በአለም አቀፍ ደረጃ ከ300 ሰዎች አንዱን እንደሚያጠቃ የተረጋገጠ ሲሆን በዘር ከሚወረሱ የሜታቦሊክ ህመሞች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።

ይህንን አስከፊ ህመም ለማከም እያንዳንዱ ሰው ማገዝ ይችላል! እንዴት ቢባል የህመሙን ምልክቶች በራስ፣ በቤተሰብ አባላት፣ በጓደኞች ወይም በስራ ቦታ ላይ በመመልከት እና በመለየት ለትክክለኛ ምርመራ እና ህክምና ወደጤና ተቋም እንዲሄዱ በማበረታታት ህይወት አድን ስራ ሊሰሩ ይችላሉ።

ማንም ሰው ሊያያቸው የሚችላቸው የህመሙ ምልክቶች እነዚህ ናቸው

1️⃣ በቆዳና ጅማት ላይ የሚወጡ ቢጫማ እብጠቶች (xanthoma) ዋነኛ የህመሙ ምልክቶች ናቸው። እነዚህ እባጮች በቁርጭምጭሚት አካባቢ የተረከዝ ጅማት (ቋንጃ) ላይ፣ በጉልበት፣ በእጆች ወይም ክርን ላይ ሊወጡ ይችላሉ። በአይን ዙሪያም (xanthelasma) ሊወጡ ይችላሉ። እነዚህ እብጠቶች በቀላሉ የሚታዩ ቀለማቸው ቢጫማ ሲሆን ኮሌስትሮል በቆዳና ጅማት ውስጥ ሲከማች የሚመጡ ናቸው።

2️⃣ የአይን መስታውት ዙሪያ ላይ የሚወጣ ቀለበቶች (arcus cornealis) ሌላኛው የኮሌስትሮል ህመም መገለጫ ሊሆን ይችላል። ይህ ነጭ ወይም ግራጫ ቀለም ያለው ክብ መሰል ሲሆን ኮሌስትሮል በአይን መስታወት ዳርቻ ላይ ሲከማች የሚፈጠር ነው። በአብዛኛው በአረጋውያን ላይ ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚታይ ሲሆን ከ45 ዓመት በታች በሆኑ ሰዎች ላይ ሲታይ የኮለኢስትሮል ህመም ምልክት ነው።

3️⃣ ከቤተሰብ አባላት ውስጥ በወጣትነታቸው ከ50 አመት እድሜ በፊት ድንገተኛ የልብ ድካም (heart attack) ወይም ስትሮክ (stroke) ያጋጠመው ካለም እንዲሁ የዚህ የኮሌስትሮል ህመም ምልክት ሊሆን ይችላል።

4️⃣ ለሌላ አጠቃላይ የጤና ምርመራ ሲሰራ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መብዛት ከተገኘም እንዲሁ የፋሚሊያል ሃይፐርኮሌስትሮሌሚያ ሊሆን ይችላል።

ይህን ህመም ማወቅና ተጠቂዎችን በቶሎ መለየት ለምን አስፈለገ?

በቅድመ ምርመራ፣ ትክክለኛ ህክምና እና የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ይህ በዘር የሚወረስ የኮሌስትሮል ህመም ያለባቸው ሰዎች ረጅም እና ጤናማ ህይወት ሊመሩ ይችላሉ። እነዚህን ቀላል ምልክቶች በማወቅ በማህበረሰባችን ውስጥ የዚህ ህመም ተጠቂዎችን የልብ ድካም ሳይዛቸው አስቀድሞ መታከምና መከላከል ይቻላል።

በዘር የሚተላለፍ የኮሌስትሮል ህመም በመለየት በወጣትነት የሚመጣን የልብ ድካም ለመከላከል የሚደረገውን ሃገራዊ ጥረት እናግዝ።

ይህን ማድረግ እንዲያስችለን በሚኖሩበት፣ በሚሰሩበት ከባቢ ውስጥ የፋሚሊያል ሃይፐርኮሌስትሮልሚያ (FH) ምልክቶችን ይወቁ! ለሌሎችም ያሳውቁ።

Read the full article at https://melakutaye.com/call-for-community-diagnosis-and-early-referral-of-familial-hypercholesterolemia-fh/

@hakimmelaku

4 months, 2 weeks ago
[የልብና ተያያዥ የደም ስር ህመም ስጋትን …

የልብና ተያያዥ የደም ስር ህመም ስጋትን በአስተማማኝነት ለመቀነስ የሚረዳ የኮሌስትሮል ህክምና ግብ (therapeutic targets of cholesterol treatment)

ኮሌስትሮልን በተገቢው ሁኔታ ማከም የልብን እና ተያያዥ የደም ስር ህመሞችን ተጋላጭነት ለመቀነስ ይረዳል። ከፍ ያለ የኮሌስትሮል መጠን በተለይም የጎጂ ኮሌስትሮል የሚፈለገውን ያክል ቁጥጥር ውስጥ አለመሆን ለልብ ድካም፣ ለስትሮክ እና ሌሎችም የደም ስር ህመሞች ተጋላጭነት በእጅጉ እንደሚጨምር ያለጥርጥር የተረጋገጠ ሳይንስ ነው።

ኮሌስትሮልን ለማከም በርካታ ውጤታማ እና ወጭ ቆጣቢ ህክምናዎች ያሉት ቢሆንም በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ተገቢውን ትኩረት ስላልተሰጠው ተላላፊ ያልሆኑ የልብና የደም ስር ህመሞች እንደወረርሽኝ እየተሳፋፉ መጥተዋል።

በዚህ ጽሁፍ በ2019 በታተመው የአውሮፓ የልብ ማህበር የኮሌስትሮል ህክምና መመሪያ ላይ በመመርኮዝ የእያንዳንዱን ሰው የልብ ህመም ተጋላጭነት መሰረት ያደረገ የኮሌስትሮል ሕክምና ግቦችን እናብራራለን። እነዚህን ግቦች በመረዳት የልብዎን ጤንነት ለመጠበቅ ተግባራዊ እርምጃወችን ይውሰዱ።

በዚህ የኮሌስትሮል ህክምና መመሪያ መሰረት ዋናው የኮሌስትሮል ሕክምና ግብ ጎጂ ኮሌስትሮልን (LDL-C) መቀነስ ነው። ምክንያቱም የደም ስር ቧንቧዎችን በመዝጋት ሂደት ዋናው ጠላት ይህ ጎጂ ኮሌስትሮል ስለሆነ ነው። የዚህ ጎጂ ኮሌስትሮል መጠን ምን ያህል መውረድ አለበት የሚለው የሚወሰነው አጠቃላይ የልብ ህመም ተጋላጭነትን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ስለሆነም ለሁሉም ሰው የሚሆን ተመሳሳይ ግብ ሳይሆን እንደየ ግል ተጋላጭነት የኮሌስትሮል የቁጥጥር መጠን ይለያያል።

1️⃣ የልብ ህመም ተጋላጭነትህ/ሽ በጣም ከፍተኛ (very high risk) ከሆነ (ለምሳሌ፡ ቀደም ሲል የልብ ድካም ወይም ስትሮክ አጋጥሞ ከነበር፣ ከስኳር ህመም ጋር የተያያዙ የደም ስር ህመሞች ካሉ) አላማው ጎጂ ኮሌስትሮልን ከ55 mg/dL በታች ማውረድ ነው።

2️⃣ የልብ ህመም ተጋላጭነትህ/ሽ ከፍተኛ (high risk) ከሆነ (ለምሳሌ የደም ግፊት ካለብህ፣ የስኳር ህመም፣ ወይም ሌሎች የልብ ህመም አጋላጭ መንስኤዎች ካሉ) የጎጂ ኮሌስትሮል ኢላማው ከ70 mg/dL በታች ማድረግ ነው።

3️⃣ የልብ ህመም ተጋላጭነትህ/ሽ መጠነኛ (moderate risk) ከሆነ የጎጂ ኮሌስትሮል ግቡ ከ100 mg/dL በታች ማድረግ ነው።

4️⃣ ለተቀሩት የልብ ህመም ተጋላጭነታቸው ዝቅተኛ (low risk) ለሆኑ ግለሰቦች በአጠቃላይ ግቡ ጎጂ ኮሌስትሮልን ከ 116 mg / dL ያነሰ እንዲሆን ማድረግ ነው።

5️⃣ በህክምና ውስንነት ከላይ የጠቀስናቸውን ግቦች ማሳካት ባይቻል እንኳ የኮሌስትሮል መጠንን የተቻለውን ያክል መቀነስ በተለይም ኮሌስትሮልን ከመጀመርያው መጠን ቢያንስ በ50% መቀነስ የልብ ሕመምን አደጋ ለመቀነስ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።

መደበኛ የጤና ምርመራዎች፣ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች (እንደ ጤናማ አመጋገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ) እና እንዳስፈላጊነቱ የኮሌስትሮል መድሃኒት መውሰድ እነዚህን ግቦች ለማሳካት የየራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ።

በተለይም የስኳር ህመም ያላቸው፣ የልብና ተያያዥ የደም ስር ህመም ያላቸው፣ የኮሌስትሮል መጠን በከፍትኛ ሁኒታ የጨመረባቸው እንዲሁም ተደራራቢ አጋላጭ ህመም (multiple risk factors) ያላቸው የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒት ያለማቋረጥ መውሰድ ተገቢ ነው። ዋናዎቹ የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒቶች ስታቲን (statin) በመባል ይታወቃሉ። በርካታ የስታቲን መድሃኒት አይነቶች ቢኖሩም ኮሌስትሮልን በከፍተኛ ሁኔታ በማስተካከል ውጤታማነታቸው የተረጋገጠው ሮሱቫስታቲን (Rosuvastatin) እና አቶርቫስታቲን (Atorvastatin) የተባሉት የስታቲን መድሃኒቶች ናቸው።

እነዚህን የሕክምና ግቦች መረዳት በጤናዎ ላይ የተሻሉ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ እና ለጤናማ ህይወት አስፈላጊ እርምጃዎችን እንዲወስዱ እንደአንድ ግብኣት ይረዳዎታል ብዬ አስባለሁ።

የዚህን ትምህርታዊ ጽሁፍ ሙሉ መረጃ በዶ/ር መላኩ ድህረ ገጽ https://melakutaye.com/therapeutic-targets-of-cholesterol-treatment/ እንዲያነቡና ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።
@hakimmelaku

We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated 2 months, 3 weeks ago

Last updated 2 months, 2 weeks ago

ይህ ስለ Manchester United መረጃዎችን የሚያገኙበት የ Telegram ቻናል ነው 🇪🇹
--------------------------------------------------------------
☞︎| ስለ ማንቸስተር ዩናይትድ ትኩስ መረጃዎች
☞| ቀጥታ ስርጭቶች ከየስታድየሞቹ
☞| የዝውውር ዜናዎች
☞| ስለ ማንችስተር ዩናይትድ ታሪኮች

📩 ለማስታወቂያ ስራ DM :- @Marcoabdu

Last updated 1 month, 2 weeks ago