የአብስራ

Description
እምነት ~ ተስፋ ~ ፍቅር
FAITH HOPE LOVE
الإيمان أمل الحب ~ 🤎

📬 @yeabsra_tsega

በዩቲዩብ
https://www.youtube.com/@Yeabsira_Tsega
Advertising
We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated 6 days, 23 hours ago

Last updated 2 days, 5 hours ago

ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot

🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹

Last updated 2 weeks, 6 days ago

1 month ago

“...ላለማንከስ + ለመመለስ...”

ወንድማችሁ የአብስራ ነኝ...

በዚህች ምድር ስንኖር ሁላችንም የራሳችን ፈተናዎች አሉብን...
የህይወት ጥያቄና ሸክም ፈተናና ችግሮች እንዳሉ ሆነው እኛ ለሁኔታዎች የምንሰጠውም ምላሽ አለ።

እስካሁን የእግዚአብሔር ምህረት በዝቶልኝ በኖርኩበት እድሜ ያሳለፍኩትም ያለፍኩበትም ብዙ እንደሆነ አስባለሁ። ራሴንና ኑሮዬን ስቃኝም የማልክዳቸው ጉዳዮች አሉኝ በበጎም ሆነ በጉድፍነትና በምሰሶነት የምጠቅሳቸው...

ትልቅ ነገር የመስራት፤ በጎ ተፅዕኖ የመፍጠርና ለተፈጠርኩበት መልካም አላማ የመኖር መሻቴና የሰራኝም እግዚአብሔር የሰጠኝ መክሊት ቀላል የማይባል ሆኖ ሳለ በስጋ በዚህች አለም ስመላለስ የደከምኩበት የወደቅሁበት እንዲሁም ተስፋ ሁሉ ያስቆረጠኝ ታሪክም አለኝ...

በምከተለው እምነት እኔ የ“እግዚአብሔር ቤተመቅደስ” ስለመሆኔ የማምን ሳለሁም በ Pornography(የወሲብ ፊልም) እና Masturbation(ራስን በራስ የማርካት) ሱስ ውስጥ በመገኘት ደግሞ በተደጋጋሚ ሃጥያት በቅድስና እንድኖርለት የሚፈልገውን ከሞት ያዳነኝን አምላኬን ብዙ በድያለሁኝ...

በትምህርት በስራና በህልም ደረጃ የሚጠበቅብኝን ያህል አለመትጋቴን ከሁሉ የሚልቅ መንፈሳዊ ህይወቴንም በአምላኬ ፀጋ በታማኝነት አለመያዜን ሳስብ አንካሳነቴ በጉልህና በግልፅ ይታየኛል።

ስለሆነም እግዚአብሔር በህይወቴ ያለውን የመንግስቱንና የፅድቁን ሃሳብ ከትላንቶቼ ይልቅ በሙሉ ልብ እፈልግ ዘንድ እንዲሁም በኑሮዬም ፈቀቅ ስል ለማየት ካለኝም ጉጉት የተነሳ እኔ ደካማና ሃጥያተኛው ወንድም ለተወሰኑ ጊዜያት ከግላዊ ሶሻል ሚዲያዬ ሁሉ ገለል እላለሁ።

ይህን ሁሉ ስፅፍ ድካሜን የሚገልፅልኝ መጣኝ ቃል አገኘሁ በሚል ድፍረት አይደለም ደግሞም ራሴን ብዙ ሰዎች እንደሚከታተሉት የሚዲያ ሰው ቆጥሬም አይደለም ግና እንዲሁ ፅሁፎችና ፖስቶች ሳጋራ ሆነ ብላችሁም ይሁን በአጋጣሚ የምትጋሩኝን ቤተሰቦቼን በማክበር ነው።

እግዚአብሔር ፈቅዶ በምህረቱና በፀጋው ብዛት በጊዜው ወደማህበራዊ ሚዲያ ስመለስ እንደምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ!... ሁላችሁም ለያላችሁበት ሁኔታ እግዚአብሔር መልካም እንደሆነ ዳግም እያስታወስኩ መልካሙንም እመኝላችኋለሁ... እወዳችኋለሁ🖤

“...ዳዊት እጅግ ተጨነቀ፤ ዳዊት ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን አበረታ።”
— 1ኛ ሳሙኤል 30፥6

1 month, 2 weeks ago

<<የነልሳን እናት...>>
ክፍል ፲

(የመጨረሻ ክፍል!)

“ምን ሆነህ ነው?”

አለችኝ ኢቫ እንደሌላ ቀን ፊቴ ባይበራ...

“እ?”

"ምነው?”

ምን ልበላት...

እማዬና አባዬን ያስተከዛቸው የነልሳን እናት ነገር... በጊዜው እኔን እንደዛ ለመግረፋቸው ምክንያት የሆኑት ሴት በአካል ቤታችን መምጣታቸው ነበር።

ያኔ ቤት እንደተመለስኩ እማዬ አረጋግታ ነገረችኝ...

“አቢዬ...”

"አቤት...”

"የነልሳንን እናት አገኘሃቸው?”

“አይ...” አኩርፌ የአልጋዋ ጫፍ ላይ ተቀመጥኩ...

አባቴ ብድግ ብሎ ወደበሩ አመራ ጥቂት በዝምታ ቆመ...

“አቢ እትዬ ማክዳ ልጆቻቸውጋ ጠቅልለው ሄደዋል...”

ማናቸው እትዬ ማክዳ ልል ነበር...

አባዬ ጥርሱን ነክሶ ጭንቅላቱን ላይና ታች በእርጋታ ነቀነቀና እጁን ጃኬቱ ኪስ ውስጥ ከተተ። መልሶ አወጣ... እግሮቹ እየመሩት ከቤት ወጣ።

የነልሳን

“የኔ ውሻ...”

ቸኮሌት ይዘዋል በእጃቸው...

“ደህና ናችሁ?... ቅዳሜ ጠዋት ና ስላሉኝ ነውኮ ይኸው መጣሁ...”

“በቃ ከእዚህ በኋላ እቤት እያስፈቀድክ ቅዳሜ ጠዋት እኔጋ ና እሺ...”

እጄን ካለበት ወደእሳቸው ወሰድ አደርገው ሶስት የተለያየ አይነት ቸኮሌት መዳፌ ላይ አስቀመጡልኝ...

ከዚህ ቀን ጀምሮ ለምላሴም ለነፍሴም የጣፈጠ ጊዜ ሆኖልኛል። ስጋዬ ልዩ ቸኮሌታቸውን ስለሚቀበል፤ ነፍሴ ልዩ ፍቅራቸውን ስለምትሸለም ልጅነቴ ታደሰ።

ምንም ያልጎደለብኝ እንደሆንኩ ይበልጥ የሚሰማኝ የሆንኩት የነልሳን እናት በጥቂት መገናኘት የሚያሳዩኝን ስስት ሳይ ነው...

...ተማሪዎች ሁሉ የሚቀኑበት የእጅ ሰአት አለኝ። ከኢቫ ቀጥሎ እኛ ክፍል አይን የሚጣልበት ነገር የእኔ የእጅ ሰአት ነው። ከየት መጣ? የነልሳን እናት አይደሉ በአንዱ ቅዳሜ እጄ ላይ ያሰሩልኝ።

“ይኸው በቃ አሁን ስትንቀሳቀስ ከበፊት ይበልጥ ጊዜህን በአግባቡ ለመጠቀም ሰአት ታያለህ...” አሉኝ “ጥናት ከስንት ሰአት እስከስንት ሰአት አጠናለሁ?፤ እስከስንት ሰአት እጫወታለሁ?፤ መንገድ ላይ ራሱ ሰው ሲጠይቅህ መልስ ይኖርሃል እሺ...”

“እሺ...”

አንዲት የሰፈራችን ሴትዮ “እትዬ ማክዳ” ብለው ተጣሩ...

ባልጠበኩት መልኩ የነልሳን እናት ናቸው ሰላምታውን የመለሱት።

አዎ! አዎ!

አሁን አባዬ ሄዱ ያለኝ፤ እትዬ ማክዳ ያለኝ፤ የነልሳንን እናት ነው።

እንዴዴዴዴዴዴዴዴ.... ወይኔኔኔኔኔኔኔኔ....

ጉድ ሆኛለሁ...

አይኔ እንባ አቀረረ...

እማዬ ትኩረቷ እኔ ላይ አይደለም። ብድግ ብላ ወደኩሽና ልትሄድ ወደበሩ አመራች። የምታስቀምጠው እቃ እንዳለ ሲገባት መለስ ብላ ወደደረቷ እጇን ከታ የተጣጠፈ ፖስታ አወጣች።

“ቅዳሜ ገበያ እንሄዳለን የምትፈልገውን ጫማ መርጠን እንገዛለን ለእኛም ለአንተም የነልሳን እናት ስጦታ ሰጥተውን ነው የሄዱት...”

እማዬ ብሩን ለማስቀመጥ ጓዳ ገባች።

ከጓዳ ሆና ድምጿ ይሰማኛል...

“እግዚአብሔር ይባርካቸው እንዴት ያሉ አሳቢ ናቸው!...”

እኔ ግን ሁሉ ጥንቅር ብሎ ቀርቶብኝ የነልሳን እናት ቢመለሱልኝ ደስታዬ ነበር... እንባዬ ወረደ።

አብዝቼ ከወደድኩት ሰው በግድ መራራቅን አንድ ብላ ሕይወት አስተማረችኝ...

አጎንብሼ እትዬ ማክዳ የገዙልኝን ሰአት ታስሮ ባለበት - እጄ ላይ አየሁት።

ጊዜ ሆይ ብትበር - ብትከንፍ ጊዜ ሆይ
ወደናፈቀኝ ሰው - ታደርሰኝ ይሆን ወይ?
(ምናለ በቀረ መሄድህ ወደፊት
ይልቅ ተመልሰህ በኖርኩ እንደበፊት...)

እንባዬ የሰአቱ መሃል መስታወት ላይ ጠብ አለ።

ይሄ ሰአት ጊዜን መቁጠሪያ ሳይሆን ማስታወሻ ነው መሆን ያለበት! ከእጄ ላይ ፈትቼ ወደጓዳ ገባሁ።

“እማዬ እስከማድግ ይሄንን ጥሩ ቦታ አስቀምጪልኝ... ሳድግ ትሰጪኛለሽ አደራ!”

~              ~            ~

ተጠናቀቀ
(መልካም ማደግ!...)

✍🏾 በየአብስራ ፀጋ
YOUTUBE  TIKTOK INSTAGRAM

1 month, 3 weeks ago

<<የነልሳን እናት...>>
ክፍል ፱

አስቤ የማላውቀው እየሆነ ነው የማድገው...

ከጥቂት ሰላምታና ጨዋታ በቀር ከቆንጆዋ ልጅ ከኢቫጋ እንዲህ እንቀራረባለን ብዬ አስቤ አላውቅም - ተቀራረብን።

ከሳምንቱ ቀናት ቢያንስ በአንዱ ላላያት ከልሳንጋ እንዲህ እንራራቃለን ብዬ አስቤ አላውቅም - ተራራቅን።

ቅዳሜ የሳምንቱ አንዱ ቀን ሳይሆን ለእኔ ተብሎ ከእግዚአብሔር የተላከ ልዩ ቀን እስኪመስለኝ እንድደሰት የሚያደርጉኝ እናትስ?

እቤት ከትምህርት ቤት ደክሞኝ ስገባ ነው...

እናትና አባቴ ትክዝ ብለው ተቀምጠዋል ሶፋ ላይ...

ዝም ብዬ ዩኒፎርሜን ቀይሬ መክሰስ ካለ ይሰጠኝ እንደሆነ ለማየት አልጋችን ጫፍ ላይ ተቀመጥኩ።

ትካዜ ምን ማለት እንደሆነ እስከጥግ እስኪገባኝ ድረስ ቤተሰቦቼ ተክዘዋል - ቤታችን በዝምታ ተውጧል። አርፎ ቤቱ የማይቀመጠው የጎረቤታችን ድመት በለመደበት የአጥር ቀዳዳ ሾልኮ ይመስለኛል እኛ ግቢም ገብቶ እንደሌሎች ተከራይ ጎረቤቶቻችን በራችንን አነፍንፎ አለፈ።

የሆነች ዝንብ መተከዝ ከብዷት ይመስለኛል በ‛ዝንበኛ’ እየተዋከበች ነው...

“አቢዬ...”

"አቤት...”

"አንተን ፍለጋ ሰው መጥቶ ነበር...”

"ማን?”

"የነልሳን እናት...” አለች እናቴ...

“ከዛስ?”

የልጅ ልቤ በድንገት ተረበሸ... መቆሜን ያወኩት ወደበራችን ስራመድ ነው...

“ባገኘው ደስ ይለኝ ነበር አሁን ትምህርት ቤት ነው የሚሆነው በርግጥ አሉንና...”

እማዬ አውርታ ሳትጨርስ ወደእነልሳን ቤት ተፈተለኩ።

በሩጫዬ ሁሉ የነልሳን እናት ፊቴ ድንቅ እያሉ ገሰገስኩ።

በራቸው ራቀኝ...

ውሻዬ የሚል ጥሪያቸው ናፈቀኝ...

አንድ ቀን ሰፈር ውስጥ ከማልችለው ልጅጋ ተጣልቼ... ጠባችን ወደድብድብ ተቀይሮ እኔን ወደመሬት ለማፍረጥ ሰከንድ ሳይፈጅበት ዘርሮኝ ሲያበቃ ላዬ ላይ ተከምሮ በቡጢ ሊለኝ ሲል ፊቴን በሸፈንኩበት የመኪና ‛ክላክስ’ ሰማን...

ልጁም ጠቡን ረስቶ ወደእኛ የቀረበውን መኪና ሲመለከት በችኮላ ከመኪናው ወጥተው የገላገሉን ነጂ የነልሳን እናት ነበሩ። ልጃቸው ይመታ ይመስል ልጆች ሁሉ ግራ እስኪገባቸው እኔን ወደመኪናቸው ከተው ደብዳቢዬን በአጭሩ መክረው ቤታቸው በር ላይ ወስደው ዩኒፎርሜን አራገፉልኝ

“አትጣላ!”

“ራሱ ነውኮ...” እልህ ወሮኛል...

“ከማንምጋ እንዳትጣላ ከዚህ በኋላ...”

“እ እሺ...”

“ሲሰድቡህ አንተ መልሰህ አትስደባቸው ሲያድጉ ወይ አንድ ቀን ልክ እንዳልሆኑ ይገባቸዋል ቂም ሳትይዝ እለፋቸው... እሺ የእኔ ውሻ...”

ጭንቅላቴን ላይና ታች ወዘወዝኩ።

ሩጫዬን ገትቼ በራቸውጋ ስለደረስኩ ተረጋጋሁ... አተነፋፈሴ እየተዛባም ቢሆን አንኳኳሁ...

ተከፈተልኝ...

ግን ያቺው ሴት ናት ፊቴ ድቅን ያለችው።

አንድ የማታውቀው መንደር ሄዳ ከቆሻሻ ገንዳ ብቅ ብሎ ነጭ ቀሚሷ ስር እንደተገኘ ውሻ የምታየኝ ሴትዮ...

በፍፁም ይህቺማ የነልሳን እናት ዘመድ አይደለችም!

~              ~            ~

ነገ የመጨረሻው ክፍል ይለቀቃል...

✍🏾 በየአብስራ ፀጋ
YOUTUBE  TIKTOK INSTAGRAM

4 months ago

<<...ፀሃይ...>>

“ፀሃይ ትመስለኛለች...”

"እኔን ወንድሜ ሴቶችኮ ያቃጥላሉ ፀሃይ ባትመስልህ ነበር የሚገርመኝ...”

“ቀልድ አንተ...”

"ከልቤ ነው ባክህ ምን እልቀልዳለሁ...”

እሷን እያሰበ ፈገግ አለ...

ጣልቃ ገባበት...

“አሁን ግን የት ናት?”

"ምን አውቄ ብለህ...”

“ታድላ የት እንዳለች ሳያውቅም በፅኑ የሚወዳት ሰው አለላት”

"ተው አትቅናባት... ምናልባት አንተንም እንዲህ የት እንዳለህ ሳታውቅ የምትወድህ ትኖር ይሆናል”

“የለችም... እኔ እድሌን በደንብ አውቀዋለሁ... በዛለይ እኔ የሩቅ ፍቅር ምናምን ብዙ አይመስጠኝም...”

"ሞኝ...”

"አቤት?”

የቢሮው መስኮትጋ ወደተቀመጠው ወዳጁ ተጠጋ...

“አቤት አባባልህ ደስ ይላል... ምንም ሆነ ምን ግን ፍቅር ደስ ይላል እሺ አቤት ባዩ ወንድሜ”

ፈገግ አለ...

“አንተ”

"እ?”

“ለካ ወደህ አይደለም ቦታህን ወደዚህ ቀይረህ እዚህ'ጋ ተቀምጠህ የቀረኸው”

"ማለት”

"በዚህ መስኮት ወደውጪ ሲታይ ደስ ይላል እንደዛሬ አስተውዬው አላውቅም...”

"አዎ ኣ ደስ ይላል በጣም...”

"ኧረ ፀሃዩዋ ስታምር ወገግ ብላ ስትወጣ”

“እንዲህ ነውኮ ያልኩህ... እሷም የጠዋት የክምረት ፀሃይ ትመስላለች።”

~              ~            ~

✍? በየአብስራ ፀጋ
YOUTUBE  TIKTOK INSTAGRAM

4 months, 1 week ago

...

“ካንተጋ ነው መሄድ የምፈልገው...”

"ወዴት?”

ኩርፊያ...

ጥቂት ዝምታ...

ብድግ ያለውን እርሱን ተከትላ ብድግ አለች...

አያት ማንም ምንም ቢላት አርፋ የምትቀመጥ አትመስልም።

እንባ ባቀረሩ አይኖቿ ኮቴውን ተከተለች...

እየሄደ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እየራቀ መሆኑ በተሰማት ቅፅበት ሮጣ በራቸው'ጋ ደረሰች...

እውነትም ገና ካሁኑ እየራቀ ነው...

መከፋት የተጫነው ድምጿን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች።

“ከአንተጋ ነው መሄድ የምፈልገው...”

ዞረ...

“ወዴት እንደምሄድ ታውቂያለሽ?”

"አላውቅም...”

"እና የእኔ ንፁህ ነፍስ?”

“ግን በቃ ከአንተጋ ልሂድ...”

ለማሳዘኗ ፈገግ አለላት።

በሩ ስር የተቀረቀረ ነጠላ ጫማዋን ፈልቅቃ አወጣውችና፤ በችኮላ የልጅ እግሯን አጥልቃበት ሮጣ ተከተለችው። እንባዋ ከአይኖቿ ብቻ ሳይሆን ከትንሽዬ ልቧም መድረቅ ጀመረ...

~              ~            ~

✍? በየአብስራ ፀጋ
YOUTUBE  TIKTOK INSTAGRAM

4 months, 1 week ago

<<...ሰበብ...>>

በእርምጃቸው መሃል...

እጆቿን አጎንብሶ አያቸው...

አላየችውም... አይኖቿ ጎዳናው ላይ በዝግታ መንከራተት አላቆሙም...

እሱም ቀና አለ...

መንገዳቸውን እንደቀጠሉ ነው...

የእጁን ጣቶች በአየሩ ላይ እያራመደ ወደእጇ መራቸው...

አልደከማትም... በጥቂቱ የፈካውን ሰማይ ስታይ ፈገግም አለች።

ይፈራ የለ እጁን ወደራሱ ሰበሰበ።

“ምነው ዝም አልክ?...”

“እ?... አንቺም... አንቺም ዝም ብለሻል”

ጎኗ የሚራመደውን እሱን አየችው...

መራመዱን ቀጠለ...

“ደርሰሻል...”

“እሺ በል ደህና ሁን...”

ሄደች።

በዚህች ብዙ በምታስቀይም፤ በምታስመርርና በምትጠላ አለም ውስጥ ጥቂት የሚያሳሳና ለመኖር የሚያነሳሳ ስውር ሰበብ አለ... ለእሱ ከሰበቦቹ አንዱ ይሄ ቀዝቃዛ ስንብት ነው።

~              ~            ~

✍? በየአብስራ ፀጋ
YOUTUBE  TIKTOK INSTAGRAM

4 months, 1 week ago

...

“ሊሆን ይችላል...”

“ሊሆን ይችላል አትበል ይሆናል በል...”

"እንዴ ገና ምንም የታወቀ ነገር በሌለበት...”

"እኮ የታወቀ ነገር ሳይኖር አንተ ምን አውቀህ ነው ጥርጣሬ ላይ እንዲህ ክችች ያልከው... አርፈህ ይሆናል በል...”

"እህ እኔ እንደዚህ አይነት ነገር ደስ አይለኝም...”

"አየሃ ችግርህን...”

"ምን ልትል?”

"ያንተ ችግር አንተ ራስህ ነህ...”

"እሱን መች ካድኩ የብዙዎቻችን ችግርኮ ራሳችን ነን... አንተ ግን አሁን ከራስህ አልፈህ እኔም ላይ ችግር ለመሆን እየሞከርክ ነው...”

"የራስህ ጉዳይ ለውጥ ካልፈለክ እንዲህ መቀጠል ትችላለህ...”

ዝም ተባባሉ...

እጅግ በስሱ ተኮራረፉ...

"ታያለህ ግን ያኔ ሲሳካ እኔ ብቻ ነኝ ብዬ ነበር ማለት የምችለው... አንተ ሊሆን ይችላል ብቻ ማለትህን እንዳትረሳ...”

"ኣሃ ኣሃ አንተ!... ብለን ነበር እንድንል ፈልገህ ነው እንዴ አሁን የምታደርቀኝ...”

"አፈርኩብህ ወንድሜ... ጨርሶ ብሩህ እይታ እንደሌለህ እንዴት እስካሁን አልተገለጠልኝም...”

"ምናልባትም ሰዎች ሁሌም ሁሉ ነገር ላይ ብሩህ ትንበያ ብቻ ይሰጣሉ ብለህ ስለምትተነብይ ነዋ የሚሆነው...”

“መልካም ቀን እሺ... ዞር በል በቃ ከሱቄ ላይ...”

“ሲጀመር የስራ መግቢያ ሰአቴ እየደረሰ ነው እዚህ ቆሜ ላንተ ደንበኛ ስስብ ልውል አላቀድኩም በል ደህና ዋል...”

"ካንተ'ጋ ለሚሰሩት አዘንኩላቸው ሂድ ሰላም ሁን...”

ዞር ብሎ ስቆ አይቶት መንገዱን ቀጠለ።

~              ~            ~

✍? በየአብስራ ፀጋ
YOUTUBE  TIKTOK INSTAGRAM

4 months, 1 week ago

<<አንድ እልልታ>>

መስሏል ዛሬ ተስፋ መጥፎ
አልቋል መቻል ተንጠፍጥፎ

ሆኗል ዛሬ ተስፋ አሳዛኝ
ባዶነትን የለም መዛኝ

አለመኖር
ባዶ ዲስኩር
ግራ ግብት ነፍስ ጭንቅ
እንደገና ተስፋን እንቅ

በአለመቻል የታሰረ
ያልተጠጋው ቅንጣት ክህደት
ከመኖር'ጋ ጥልቅ ውህደት!

በፈረሰ ጎጆ ያደረ
ከአድማጭ የተሰወረ
አንድ እልልታ ተፈጠረ...

~              ~            ~

✍? በየአብስራ ፀጋ
YOUTUBE  TIKTOK INSTAGRAM

4 months, 3 weeks ago

<<...ላፍቅርሽ?...>>

“አሁን አትጨቃጨቂኝ...”

"ምንም ጭቅጭቅ አይደለም ይሄ”

"ነው እንጂ ከዚህ በላይ መጨቃጨቅ አለ እንዴ...”

ከተቀመጡበት የካፌ በረንዳ ወደ መንገደኞች ተመለከተ...

“እ ልሂድ?”

“አይ ካልሽ ሂጂ ከወሰድሽም ውሰጂኝ ሴትዪት...”

“ቀንስልኝና...”

“ከዚህ በላይ አስተያየት ማድረግ አልችልም 2000 ስልሽ እንዲህማ የለም ስላልሽ እኔም አማራጭ የለኝም ብዬ በአንዴ 1000 አደረኩልሽ...”

"150 ያዋጣሃል?”

"አይ በፍፁም!... ደንበኛን ብቻ ንጉስ ያደረገው ማነው?... እኔም ብሆን ንጉስ ነኝ... ከሺህ ዓመት ውጪ አልሰማሽም ነው ምልሽ... ”

ፈገግ አለች...

"ደረቅ ከእኔ ውጪ ደንበኛ ያለህ አትመስልም...”

"ባይኖረኝስ... በዪ ሂጂ 1000 ቅር ካለሽ...”

"እሺ ግን ታያለህ አንድ ሺህ አመት እኔም አንተም አንኖርም...”

"ባንኖርስ... 150 ዓመት ብቻ ላፈቅርሽ ከተነሳሁማ ዕድሜ ሰጥቶኝ 149 ዓመት ላይ ስደርስ ታታክቺኛለሽ...”

ሳቀ።

"እንቢ እንደውም እሺ... አንድ ሺ'ህ አይደለም መቶ ሺ'ህም ዓመት ላፍቅርሽ ብትለኝ አልፈልግም... እሄዳለሁ...”

“ኧረ ባክሽ የእኔ ጨቅጫቃ...”

እንደልጅ አኮረፈች...

ፈገግ ብሎ አያት...

ፈገግ አለች መልሳ...

"እሺ ንግስት ሆይ...”

"ምን ልትል?”

"አሁን ላፍቅርሽ?”

“መቶ ሃምሳውስ አመት?”

"እንደአሁኑ አፈቅርሽ ዘንድ እ?”

እጆቿን በጠረጴዛው አስታካ ወደእሱ ላከቻቸው...

ተያያዙ።

~              ~            ~

✍? በየአብስራ ፀጋ
YOUTUBE  TIKTOK INSTAGRAM

7 months ago

<<...ከአባቶች ሁሉ በላይ...>>

ልጅ የአሳዳጊ እናቱን ጉልበት ተደግፎ እንደተቀመጠ ነው።

“ዛሬ ምን ተማራችሁ?”

"የት?”

"ትምህርት ቤት ነዋ አቢቲዬ”

"እ ትምህርት ቤት ስለቤተሰብ አባላት... ግን ደስ አይልም ነበር...”

“ለምን ምነው?”

"ተሳቀብኝ...”

“ማን አባቱ ነው አንተ ላይ የሳቀው አቢቲዬ”

“ደሞኮ ሳልሳሳት ነው የተሳቀብኝ”

"ምንድነው እስቲ ንገረኛ?”

ፀጉሩን እየዳሰሱት ሊሰሙት ተሰናዱ...

“አስተማሪያችን አስነስቶኝ አክስት ምንድነው አለኝ”

"እሺ ምን አልክ ከዛ...”

"አላውቅም መምህር አልኩ እውነቴን ነበር አልተሳሳትኩምኮ ነበር ግን ሁሉም ተማሪ ሳቀ... ጓደኛዬ ሳይቀርኮ ስቋል”

“አንተ አላጠፋህም እነሱ መልስህ ስላልገባቸው ነው የሳቁት እሺ... ሳቁብኝ አትበል...”

"አስተማሪያችን ግን ትልቅ ሰው አይደል አትሳቁበት አይላቸውም ነበር? ስቀው እስኪጨርሱ ጠብቆ ነውኮ ተቀመጥ ያለኝ...”

"ተወው እሱም መልስህ አልገባው ይሆናል... ከዛስ ግን አክስት ምን ማለት እንደሆነ አስተማራችሁ?”

ጭንቅላቱን ላይና ታች ነቀነቀ...

“ከእንግዲህ ግን ሁሉንም ከትምህርት ቤት ብቻ እስክትማር አትጠብቅ እኔም የምችለውን እመልስልሃለሁ... ማወቅ ስትፈልግ ይረዱኛል ብለህ ለምታስባቸው ሰዎች ጠይቅ... ደሞ ከምንም በላይ እግዚአብሔርን ከጠየከው መልስ ለታጣለት ጥያቄህ ሁሉ መልስ ይሆንሃል እሺ...”

"እሺ...”

"በል ንፍሮህን ዝገን እንዴት ነው ዛሬ ረሳህኮ ስንዴ ለቀማህን...”

ቆነጠረ... ወደአፉ ላከ...

"ግን ግን እናትአለም?”

"እ...”

"አስተማሪው ይሄን ስለምታውቁት መናገር አይጠበቅብኝም ብሎ በደንብ ሳይነግረን ያለፈው አልገባኝም...”

"ምንድን ነበር እሱ?”

"አባት ግን ምን ማለት ነው?”

ያልጠበቁት ጥያቄ አስደነገጣቸው... ዝም አሉ... ቆዩ... አይናቸው እንባ አቀረረ...

“ይሄንን ሰው አይመልስም ለእግዚአብሔር ነው የምጠይቀው?...”

“እ?”

"የክፍል ጓደኞቼና አስተማሪያችን መልሱን ያወቁት እግዚአብሔርን ጠይቀው ነው?”

"አቢቲዬ መልሱ መላሹ ነው እሺ...”

ስላልገባው በልጅ አይኖቹ ቁልጭ ቁልጭ አለ...

“ከአባቶች ሁሉ በላይ የሆነ አባት እግዚአብሔር ነው ልጄ...”

የተጨበጠ እጃቸውን ዘረጉና መዳፋቸውን እያሳዩት...

"በል ያዝ ላንተ ብዬ የለቀምኩልህን ስንዴ...”

"እንዴ አትልቀም ሁሉንም ብላ ትዪኝ አልነበር ራስሽ ለቅመሽልኝ ነው እናትአለም”

በደስታ ከእጃቸው ላይ ዘገነ።

~              ~            ~

YOUTUBE  TIKTOK INSTAGRAM
✍? የአብስራ ፀጋ
@yeabsira_tsega

We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated 6 days, 23 hours ago

Last updated 2 days, 5 hours ago

ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot

🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹

Last updated 2 weeks, 6 days ago