DW Amharic

Description verified
ይህ የዶይቼ ቬለ ይፋዊ የቴሌግራም ገፅ ነው። ትኩስ ዜና፣ በአበይት ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ትንታኔ ያቀርባል።
Subscribers

We recommend to visit

The official Telegram on Telegram. Much recursion. Very Telegram. Wow.

Last updated 2 months, 1 week ago

Intel slava is a Russian News aggregator who covers Conflicts/Geopolitics and urgent news from around the world.

Last updated 1 week, 3 days ago

Your nation. Your news. #OANN *Official

Last updated 4 weeks, 1 day ago

5 days, 8 hours ago DW Amharic

ጊዜ የማይሰጡ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸው የተባሉ ካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ሰዎችን ወደ ተዘጋጀላቸው ስፍራ የመዘዋወር ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አክለው ተናግረዋል። ምን ያህል ሰው ወደ ተዘጋጀለት ስፍራ እንደተወሰደ ግን የአዲስ አበባ ወኪላችን ሐና ደምሴ በላከችልን ዘገባ አልተጠቀሰም። ኮሚሽነሩ በመግባት ላይ ካለው የክረምት ወቅት ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች ሊፈጥሩ እንሚችል በመግለፅ ወላጆች እና ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ግን አስጠንቅቀዋል። በአዲስ አበባ ከተማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዐሥር በተለምዶ ቀይ አፈር በሚባለው አካባቢ ኲዋስ በመጫወት ላይ ከነበሩ ልጆች መካከል ሁለት ታዳጊዎች ባለፈው እሁድ በጎርፍ አደጋ ሕይወታቸው ማለፉ ተዘግቧል። ልጆቹ ሰኔ 12 ቀን፣ 2014 በአቅራቢያው ከነበረ ወንዝ ኳስ ለማወጣት ሲሞክሩ ሕይወታቸው ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዐስታውቋል። ከሁለት ሳምንት በፊት ከትምህርት ቤት ሲወጣ በጎርፍ ተወስዶ ሕይወቱን ያጣውን ታዳጊ ልጅ ጨምሮ ከተማይቱ ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ ሊወገድ በሚችል አደጋ ሦስት ሕፃናትን አጥታለች።

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በሱዳን የቀይ ባህር ክልል አዲስ ወደብ በ6 ቢሊዮን ዶላር እንደምትገነባ ሮይተርስ የዜና አገልግሎት ዘገበ። አዲስ የወደብ ግንባታን የሚያካትተው የመዋዕለ ንዋይ ጥቅል የነጻ ግብይት ዞንን እንደሚያካትትም ታውቋል። ከዚያ ባሻገር መጠነ ሰፊ የግብርና ፕሮጄክቶች በጥቅሉ መካተታቸው ተገልጧል። ሱዳን በስምምነቱ መሠረት 300 ሚሊዮን ዶላር መአከላዊ ባንኳ ውስጥ ይቀመጥላታል ተብሏል። እንዲህ ያለው የውጪ ምንዛሪ ተቀማጭ ሲደረግ የሱዳን ጦር ኃይል የሐገሪቱን ስልጣን ጠቅልሎ ከያዘ ካለፈዉ ኅዳር ወዲህ የመጀመሪያው ነው።
ፓርቲያቸው በሀገር አቀፍ የምክር ቤት ምርጫ አብላጫ ድምጽ ማግኘት ያልቻለው የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኤማኑዌል ማክሮ ከተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ጋር ዛሬ ተነጋገሩ። በምርጫው ፓርቲያቸዉ አብላጫ ድምፅ ባለማግኘቱ የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ኤሎዛቤጥ ቦርኔ ሥልጣን ለመልቀቅ ያቀረቡትን ጥያቄ ፕሬዚደንቱ ውድቅ አድርገዉታል። ማክሮ ዛሬ ኤሊዜይ ቤተ-መንግስት ያነጋገሩት የቀኝ ክንፍ፤ የሶሻሊስት እና ኮሙኒስት ፓርቲ አመራርን እንደኾነ ተዘግቧል። ፕሬዚደንቱ ሀገሪቱ ከገባችበት የመንግሥት አጣብቂኝ ለማውጣት የቀኝ ጽንፍ ፓርቲ መሪ ለ ፔንንም ለማነጋገር ዝግጁ ነበሩ መባሉ አነጋጋሪ ኾኗል። ፕሬዚደንት ኤማኑዌል ማክሮ አብላጫ ድምፅ ማግኘት ያልቻለው መንግሥታቸው፦ «ገንቢ የኾነ መፍትኄን» ለመሻት «በሥራዎቹ እና ተግባሩ ላይ መቆየት» ይገባዋል ብለዋል። ፕሬዚደንቱ ተቃዋሚዎችን ዛሬ ያነጋገሩት አዲስ የጥምረት ትብብር ለመፍጠር መሆኑን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የዓለም ዜናውን ሙሉ ዘገባ እዚህ 👉🏾 https://p.dw.com/p/4D1wd?maca=amh-RED-Telegram-dwcom ማድመጥ ይቻላል።
አስተያየት ለመስጠት፣ ጥቆማ ለማድረስ ይኽን ቦት ይጠቀሙ 👉🏾 @dwamharicbot

Deutsche Welle

የማክሰኞ ሰኔ 14 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የዓለም ዜና

6 days, 15 hours ago DW Amharic

በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ባለፈው ቅዳሜ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ከ260 እስከ 320 እንደሚደርሱ የአይን ምስክሮችን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ። ከጥቃቱ በኋላ የሟቾችን አስክሬን በጅምላ በመቅበር የተሳተፉ ሁለት ግለሰቦችን እንዳነጋገረ የጠቀሰው ዘገባው አንደኛው የአይን ምስክር የሟቾች ቁጥር 260 እንደሆነ ሲገልጹ ሌላኛው ደግሞ ቁጥሩን 320 ያደርሱታል።
በወቅቱ በተፈጸመው ጉዳት እና በደረሰው የጉዳት መጠን የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሃይሉ አዱኛም ሆኑ የመከላከያ ሰራዊቱ ቃል አቃባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ወዲያው መልስ አለመስጠታቸውን የዜና ምንጩ ጠቅሷል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በኦሮሚያ የተፈጸመውን ጥቃት «በንጹሃን ዜጎች ላይ በህገወጥ እና በኢ-መደበኛ ኃይሎች የሚደርስ ጥቃት እና መተዳደሪያን ማውደም ተቀባይነት የለውም» ብለዋል። ነገር ግን ስለ ጥቃቱ በዝርዝር ያሉት ነገር የለም። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ ትናንት ባወጣው መግለጫ «የኦሮሞ ነጻነት ጦር» የተባለ ታጣቂ ቡድን ጥቃቱን ማድረሱን ገልጾ «በሲቪል ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የመከላከል እርምጃዎችን እንዲወስድ» ጠይቋል።

1 week ago DW Amharic

የሰኔ 12/2014 ሙሉ ሥርጭት

1 week, 1 day ago DW Amharic

የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሕግ አግባብ ውጭ ጋምቤላ ክልል ውስጥ የኃይል እርምጃ መፈፀማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ትናንት በተናጥል ባወጡት መግለጫ አስታወቁ። ኢሰመኮ እንዳለው ከሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ልዩ ኃይል እና መደበኛ ፖሊስ ከሕግ ውጭ ግድያ ተፈፅሟል። በተለይም በጥቃቱ ተሳትፈዋል ወይም ተባብረዋል ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ቤት ለቤት በመሄድ ጭምር ግድያዎች መፈፀማቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ኮሚሽኑ ማሰባሰቡን አስታውቋል።የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ «የፀጥታ ኃይሎች ሕይወት ሊያጠፋ ከሚችል ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ እንዲቆጠቡና በፀጥታ ኃይሎች የተወሰዱ ሕገ ወጥ ተግባራት ላይ በአስቸኳይ ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አሳስበዋል።»
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በበኩሉ በመንግስት ኃይሎች ያለፍርድ የሚካሄዱ ግድያዎች የዜጎችን የመኖር መብት እየፈታተኑ ነው ብሏል። የፓርቲው ቃል አቀባይ ሱልጣን ቃሲም ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ “ ህግን ያልተከተለ የፀጥታ አካላት እርምጃ” ኦፌኮን እንዳሳሰበው ገልፀዋል።
የጋምቤላ ክልል መንግስት ግን « ሲቪልያን የሆኑ አሮሞዎች ላይ ግድያ ተፈፅሟል የሚለው የጠላት ሴራ ነው» ሲል አስተባብሏል። የስነ ምግባር ጉድለት ያሳዩ ሁለት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል።
እንደ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጋምቤላ ከተማ የተሟላ መረጋጋት አልሰፈነም። ጋምቤላ ውስጥ ባለፈው ማክሰኞ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና በጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች መካከል በተካሄደ ውጊያ ከሁለቱም ወገን ቢያንስ 37 ሰዎች መገደላቸውን የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ከሁለት ቀናት በፊት አስታውቋል። የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እስካሁን በከተማው ይገኛል።

1 week, 2 days ago DW Amharic

*የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ እና ሰለሞን ሹምዬን እያንዳንዳቸው በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ዛሬ ሰኔ 10 ቀን፣ 102014 ዓ.ም ትዕዛዝ ሰጠ። ጠቅላይ ፍርድቤቱ ሁለቱንም ወገን ሲያከራርክ ከቆየ በኋላ ዛሬ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት ሰጥቶት የነበረውን የስር ትእዛዝ በመሻር ዋስትናውን አፅንቶ የሁለቱም ጋዜጠኞች መዝገብ እንዲዘጋ መወሰኑን ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ ዛሬ ለዶይቸ ቬለ (DW) ተናግረዋል። በትእዛዙ መሰረት ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ ዛሬ ማለዳ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሺን ተፈቶ መውጣቱን የገለጡት አቶ ሄኖክ ጋዜጠኛ መዓዛ አንዳንድ የዋስትናና የጽሕፈት ሥራዎች ስለሚቀሩ እነዚህን በማሙዋላት ሂደት ላይ መሆንዋን ተናግረዋል።
«እነ መዓዛ ላይ እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም። ፍርድ ቤትም አልቀረበም አቃቤ ሕግ፤ ስለዚህ ይህ የሚያሳየኝ ምናልባት በቀጣዮቹ ቀናት በእነ መዓዛ ጉዳይ ክስ የሚመሰረት አይመስለኝም።»
የጋዜጠኛ ያየህ ሰው ሽመልስ ጉዳይ የፊታችን ሰኞ ሰኔ 13 ቀን፣ 2014 የሚታይ ሲሆን፤ ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው 11 ተጨማሪ ቀን እንደተሰጠበት ጠበቃ ታደለ ገብረመድህን ለDW መግለጻቸውን ሃና ደምሴ ከአዲስ አበባ በላከችው ዜና አመልክታለች።

*መአከላዊ የሶማሊያ ከተማ በኾነችው ባህዶ ውስጥ የአልሸባብ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 30 ሰዎች መገደላቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት(dpa) ዘገበ። የአልሸባብ ታጣቂዎች እንደሆኑ የሚነገርላቸው ታጣቂዎች በመጀመሪያ በተሽከርካሪ ላይ ፈንጂ በማጥመድ ፍንዳታ ከፈጸሙ በኋላ ሰዎች ላይ የተኩስ ሩምታ መክፈታቸውን የከተማው ፖሊስ ቃል አቀባይ እና የዐይን ምስክሮች ተናግረዋል። አልሸባብ ዛሬ ለተወሰደው ጥቃት ኃላፊነት መውሰዱን ደግሞ አናዱሉ የተባለው የዜና ምንጭ ዘግቧል። እንደ ዜና ምንጩ ከኾነ የሶማሊያ ኃይላት ከጋልሙዱግ ክልል የፀጥታ ኃይላት ጋር በመቀናጀት ባደረጉት የመልሶ ጥቃት 47 የአልሸባብ ታጣቂዎችን ገድለዋል። ባህዶ የተሰኘችው አነስተኛ ከተማ ከሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ 632 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

*የአውሮጳ ኮሚሽን ዩክሬን የአውሮጳ ኅብረት አባል ለመሆን የእጩነት ደረጃ ሊሰጣት ይገባል ሲል ዛሬ ዐስታወቀ። ይህ ዕውቅና በጦርነት የተዳቀቀችው ዩክሬን እንደተመኘችው የአውሮጳ ኅብረት አባል ለመሆን መንገድ የሚቀይስላት ነው። ዩክሬን የእጩ አባልነት ዕውቅናው እንዲሰጣት ላለፉት ስምንት ዓመታት ስትወተውት ቆይታለች። የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዚደንት ዑርዙላ ፎን ደር ላየን፦ «ዩክሬናውያን የአውሮጳ ኅብረት አባል ለመሆን ለመሞትም ዝግጁ ናቸው» ሲሉ በትዊተር ይፋዊ ገጻቸው ላይ ዛሬ ጽፈዋል። ይህንኑም ከብራስልስ ኾነው ተናግረዋል።

«ዩክሬናውያን ለአውሮጳ ሲሉ ለመሞትም ዝግጁ መሆናቸውን ሁላችንም ዕናውቃለን። ከእኛ ጋር ኾነው አውሮጳያንን ምኞት እንዲኖሩ እንሻለን።»

ኅብረቱ በሚቀጥለው ሳምንት በሚኖረው ስብሰባ ከዩክሬን ባሻገር ሞልዶቫም የአውሮጳ ኅብረት አባል ለመሆን የእጩነት ደረጃ ቢሰጣት ፍላጎቱ እንደሆነ ይፋ አድርጓል። ጆርጂያ ያቀረበችውን ተመሳሳይ ጥያቄ ግን ተጨማሪ የፖለቲካ ለውጥ ያሻታል በሚል ሳይቀበለው ቀርቷል። ዩክሬንም ሆነች ሌላ ሀገር የአውሮጳ ኅብረት አባል መሆን የሚችሉት በኅብረቱ አባል ሃገራት ያለ አንድም ተቃዋሚ ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት ሲኖራቸው ብቻ ነው። ያም ብቻ አይደለም የዴሞክራሲ መርኆዋቸው የአውሮጳ ኅብረት ደረጃን የጠበቀ ሊሆን ይገባል። ከንግድ አንስቶ የሕግ የበላይነት እና ሌሎች ጉዳዮችን በዝርዝር የያዘው 80,000 ገጽ ደንብንም እንዲያሟሉ ይጠበቅባቸዋል።
የዓለም ዜናውን ሙሉ ዘገባ እዚህ 👉🏾 https://p.dw.com/p/4CsKe?maca=amh-RED-Telegram-dwcom ማድመጥ ይቻላል።
አስተያየት ለመስጠት፣ ጥቆማ ለማድረስ ይኽን ቦት ይጠቀሙ 👉🏾 @dwamharicbot

Deutsche Welle

የሰኔ 10 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የዓለም ዜና

1 week, 2 days ago DW Amharic

የሰኔ 10 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የዓለም ዜና
አርዕስተ ዜና

*በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ታጣቂዎች በመንግስት የፀጥታ አካላት እና አስተዳዳሪዎች ላይ በከፈቱት የጦር መሣሪያ ጥቃት የወረዳው አስተዳዳሪ እና የወረዳው የፖሊስ ምክትል አዛዥ መገደላቸው ተገለጠ።

*ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ማክሰኞ በዳኞች ላይ የሰጡት አስተያየት የአማራ ክልል ዳኞችን እንዳስቆጣ የክልሉ ዳኞች ማኅር ዐስታወቀ። ማኅበሩ የማስተካከያ ንግግር እንዲደረግም ጠይቋል።

*የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፦ አንድ ተማሪን ሲደበድቡ በማኅበራዊ መገናኛዎች በተሰራጨ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ የታዩ አራት የፖሊስ አባላቱን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ዐስታወቀ።

*መአከላዊ የሶማሊያ ከተማ በኾነችው ባህዶ ውስጥ የአልሸባብ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 30 ሰዎች መገደላቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት(dpa) ዘገበ።

ዜናው በዝርዝር

*በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ታጣቂዎች በመንግሥት የፀጥታ አካላት እና አስተዳዳሪዎች ላይ በከፈቱት የጦር መሣሪያ ጥቃት የወረዳው አስተዳዳሪ እና የወረዳው የፖሊስ ምክትል አዛዥ መገደላቸው ተገለጠ። ግድያው ባለፈው እሑድ ሰኔ 05 ቀን፣ 2014 ዓ.ም. በወረዳው ጋሌማ በተባለ ደናማ አከባቢ ጠዋት በግምት ከ3 እስከ 4 ሰዓት ገደማ መፈፀሙን ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ያልገለጡ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ (DW) ተናግረዋል። እንደ ነዋሪው አስተያየት፦ የወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ የፖሊስ ኮሚሽን ምክትል አዛዡ ከወረዳው ከተማ ጎቤሳ የተወሰኑ የፖሊስ አባላትን አስከትለው የአርሲ ብሔራዊ መካነ-አራዊት አካል ወደ ሆነው ጋሌማ ሲያመሩ ነው ጥቃቱ በታጣቂዎች የተከፈተው። በጥቃቱም የወረዳው አስተዳዳሪ፣ የወረዳው ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል አዛዥ እና አንድ የሚሊሻ አባል መገደላቸውን ነው ነዋሪው የገለጹት።
«የወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ የፖሊስ ኮሚሽን ምክትል አዛዡ ባለፈው ከዚህ የሔዱት ዘመቻ ተብሎ ነው። ዝምብ ብሎ ፖሊሶች እና ቀለል ያለ ኃይል ይዘው ነው የኼዱት። ጋሌማ ውስጥ ድንኳን ተጥሏል ተብሎ ከዚህ በፊት መረጃ ደርሷቸዋል።»
ነዋሪው እንዳሉት በዕለቱ ታጣቂዎች ሰዎች አግተዋል፤ የጦር መሣሪያና ገንዘብ ዘርፈዋል። የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ዘመዱ ኃይሉ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ እና የፖሊስ ምክትል አዛዥ በጥቃቱ መገደላቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል፡፡
«በታጣቂዎች እና በሰላም አስከባሪዎች መካከል የሰው ሕይወት አልፏል። ይህ መኾኑ የታወቀ ነው። በሺርካ ወረዳ እና በሳቡሬ ድንበር ላይ ነው። ቦታው ደግሞ አስቸጋሪ ነው። የሌሎችም የወደቁ ሰዎች ሬሳ ይኖራል ብለን እናስባለን።»
የአርሲ ዞን ሺርካ ወረዳ ዋና ከተማ ጎቤሳ ከአዲስ አበባ 264 ኪ.ሜ ገደማ ርቀት ላይ ስትገኝ፤ ከበቆጂ ከተማ ደግሞ 35 ኪ.ሜ. ትርቃለች። ነዋሪዎቹ ከዚህ ቀደም ታጣቂዎች በአከባቢው እንደማይንቀሳቀሱና መሰል የፀጥታ ስጋትም ሲያዩ የመጀመሪያቸው መሆኑን ለአዲስ አበባው ዘጋቢችን ሥዩም ጌቱ ተናግረዋል።

*ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ማክሰኞ በዳኞች ላይ የሰጡት አስተያየት የአማራ ክልል ዳኞችን እንዳስቆጣ የክልሉ ዳኞች ማሕበር ዐስታወቀ። የተሰጠው አስተያየት በኅብረተሰቡ ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲታረም ሲል ማኅበሩ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ማክሰኞ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ ዳኞችን በተመለከተ የሰጡት ጥቅል አስተያየት በርካታ የክልሉን ዳኞች በእጅጉ እንዳበሳጨ በመግለጫው ተመልክቷል። የአማራ ክልል ዳኞች ማሕበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ አሰፋ የጠቅላይ ሚንሥትሩ ንግግር ማስተካከያ እንደሚያሻው ተናግረዋል።
«እንግዲህ ዳኞች አንደኛ ደረጃ ሌቦች በሚል ተገልጠዋል። የዚህ አይነት ደረጃን ለማውጣት ጥናት እና ማስረጃ የሚጠይቅ ነው። ምናልባት በሳቸው በኩል ምን አይነት ጥናት እና ማስረጃ ይዘው እንደሆነ ባናውቅም ይህንን ታሳቢ አድርገው የተነገረው ንግግር ፍርድ ቤቶችም ላይ ዳኞችም ላይ የሚፈጥረው ትልቅ ተጽእኖ አለ። ንፁህ እና ምሥጉን ዳኞች ሞራል የሚነካ ነው፤ የሚያሸማቅቅ ነው። ማስተካከያ ንግግር እንዲያደርጉ ነው ጥያቄ ያቀረብነው።»
አንዳንድ ስነምግባር የጎደላቸው ዳኞች እንደሚኖሩ ያመለከቱት የማሕበሩ ምክትል ፕረዚደንት የተሰጠው አስተያየት በንፅህናና በእውነት ለኅሊናቸው የሚሠሩ ዳኞችን ሞራል የነካ ነው ሲሉም ተችተዋል። ያም ሆኖ ዳኞች በተባለው ነገር ሳይረበሹና ሳይበሳጩ ጉዳዩ በሥራቸው ምንም ተፅዕኖ ሳይፈጥር በተለመደው ሁኔታ ተግባራቸውን እንደሚያከናውኑ መግለጣቸውን የባሕር ዳር ወኪላችን ዓለምነው መኮንን ዘግቧል።

*የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፦ አንድ ተማሪን ሲደበድቡ በማኅበራዊ መገናኛዎች በተሰራጨ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ የታዩ አራት የፖሊስ አባላቱን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ለዶይቸ ቬለ (DW) ገለጠ። ሰኔ 8 ቀን፣ 2014 ዓ.ም በጉለሌ ክ/ከተማ ድል በር 2ኛ ደረጃ ት/ት ቤት ክፍል ውስጥ ለስንብት በተደረገ ዝግጅት አንድ ተማሪ ርችት በመተኮሱና ሌሎች ተማሪዎች ላይ መደናገጥ በመፈጠሩ አራት የፖሊስ አባላት ተማሪውን ተከታትለው በመያዝ የድብደባ ወንጀል እንደፈፀሙበት የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ተናግረዋል።
«ያደረገው ጥፋት ትክክል አይደለም። ተማሪውም ቢሆን ሌሎች ተማሪዎች እየተማሩ የሌሎች ተማሪዎችን ኹኔታ ማደናቀፍ አይጠበቅበትም። ግን [ፖሊሶቹ]የወሰዱት ርምጃ ከህግ ውጪ የኾነ፤ ሁላችንንም ያስከፋ መረጃ ነው። ስለዚህ የፖሊስ አባላቱን በቁጥር ስር የማዋል ሥራ ነው የተሠራው። አራት የፖሊስ አባላት ናቸው እዚያ ቦታ ላይ ሥራውን ሲሠሩ የነበሩት። እና በዚያ በሥራ መሀል ለተፈጠረው ችግር አራቱንም ፖሊሶች በቁጥጥር ስር አድርገን ምርመራ እያደረግን ነው ያለነው።»
በፖሊስ በርካታ ውጤታማ ሥራዎች ቢሰሩም ሕገ ወጥ ተግባር የሚፈፅሙ አንዳንድ ፖሊሶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ሆኖም በአጥፊዎች ላይ ርምጃ እንደሚወሰድ ኃላፊው ገልፀዋል። በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ውስጥ የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊሶች የተማሪ ደንብ ልብስ የለበሰ ተማሪን በቆመጥ ደጋግመው ሲነርቱት፤ በጫማ እየረጡ ሲመቱትም በግላጭ ያሳያል። በከተማዋ መሰል ድርጊቶች በፖሊሶች ሲፈፀሙ ተደጋግሞ ታይቷል።

1 week, 3 days ago DW Amharic

-ጋምቤላ ከተማ ዉስጥ ባለፈዉ ማክሰኞ በመንግስትና በአማፂያን ኃይላት መካከል በተደረገ ዉጊያ 40 ያክል ሰዎች መገደላቸዉና ሌሎች ከ40 በላይ ሰዎች መቁሰላቸዉ ተነገረ።ከተማይቱ መረጋጋትዋ ቢነገርም የመንግስት መስሪያ ቤቶችና አገልግሎት መስጪያ ተቋማት የወትሮ ስራቸዉን በቅጡ አልጀመሩም።

-የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ግጭት ቀስቅሰዋል ወይም በየግጭቱ ተሳትፈዋል ያላቸዉን ከ9 መቶ በላይ ሰዎች አሰረ።ተጠርጣሪዎቹ የገዚዉ ፓርቲ አባላት፣ የፖሊስ መኮንኖችና የመንግስት ሰራተኞችን ይጨምራል።

-በተጋመሰዉ የግሪጎሪያኑ 2022 ዓመት በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ መሰደድና መፈናቀሉን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ኮሚሽነር (UNHCR) አስታወቀ።የኮሚሽነሩ የበላይ ፊሊፖ ግራንዲ ምዕራባዉያን መንግስታት ለዩክሬን ስደተኛ ያሳዩትን ርሕራሔና ደግነት ለሌሎች ችግረኞች መንፈጋቸዉን ተችተዋል።https://p.dw.com/p/4CpGB?maca=amh-RED-Telegram-dwcom @dwamharicbot

Deutsche Welle

ዜና፣ ሰኔ 9፣2014

1 week, 4 days ago DW Amharic

ስለትናንቱ የጋምቤላ እና ምዕራብ ኦሮሚያ ፀጥታ ችግር የመንግስት ምላሽ

ዶ/ር ለገሰ በምእራብ ኦሮሚያም በተመሳሳይ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ መውሰዱን ነው የገለጹት። https://p.dw.com/p/4Ckqh?maca=amh-RED-Telegram-dwcom
👉🏾 @dwamharicbot

Deutsche Welle

ስለትናንቱ የጋምቤላ እና ምዕራብ ኦሮሚያ ፀጥታ ችግር የመንግስት ምላሽ

ዶ/ር ለገሰ በምእራብ ኦሮሚያም በተመሳሳይ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ መውሰዱን ነው የገለጹት፡

1 week, 4 days ago DW Amharic

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ መንግስታቸዉ ከሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጋር የገጠመዉን ጦርነት በድርድር የማስወገድ ፍላጎት እንዳለዉ ትናንት አስታዉቀዋል።ጠቅላይ ሚንስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ገለፃና ማብራሪያ እንዳሉት «ድርድር ማድረግ ቀላል አይደለም፤ ከድርድር በፊት ብዙ መሰራት ያለበቻዉ ጉዳዮች አሉ»።ይሁንና ጠቅላይ ሚንስትሩ ቅድመ-ድርድሩን ወይም ዝግጅቱን የሚያስተባብር በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ኮሚቴ መሰየሙን አስታውቀዋል።ጠቅላይ ሚንስትሩ 19ኝ ወራት ያስቆጠረዉን ጦርነት መንግስታቸዉ በድርድር ለመፍታት እንደሚሻ ሲጠቁሙ የትናንቱ የመጀመሪያቸዉ ነዉ።የጠቅላይ ሚንስትሩ መግለጫ፣ የአፍሪቃ ሕብረት የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛ ኦሌሴጎን ኦባሳንጆ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ድርድሩ «አዝጋሚ ግን በጎ ለወጥት እያሳየ ነዉ» ያሉትን የሚያጠናክር ነዉ።የሕወሓት ባለስልጣናትም ባለፈዉ ሰኞ ተፅፎ ትናንት ባሰራጩት ግልፅ ደብዳቤ ፓርቲያቸዉ «ታማኝ፣ያልወገነና በመርሕ ላይ በተመረሰተ የሰላም ሒደት» ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን አስታዉቀዋል።ከአዲስ አበባና ከመቀሌ የተሰማዉ የሰላም ተስፋ ይሆን?

1 week, 5 days ago DW Amharic

የሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ/ም የዓለም ዜና በድምጽ
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ፤የፌዴራል መንግስት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመደራደር ኮሚቴ ማዋቀሩን ዛሬ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጡ።

በጋምቤላ ከተማ ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ በመንግስትና በታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ነዋሪዎች አመለከቱ። በተመሳሳይ በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ አንዳንድ ከተሞች መንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መቀስቀሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

ብሪታኒያ የጥገኝነት ጠያቂዎችን ዛሬ ወደ ርዋንዳ ለመላክ ዝግጅት እያደረገች ባለችበት ወቅት የጥገኝነት ጠያቂዎች ተቃውሞ እና ከህግ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ተግዳሮቶች ሊገጥማት እንደሚችል እየተነገረ ነው። በርዋንዳ የሚገኙ ተገን ጠያቂዎች ከብሪታንያ ተጉዘው የሚመጡት የእነርሱ ዕጣ ፈንታ እንደሚጠብቃቸው ተናግረዋል ።

የድምጻዊ ዳዊት ነጋ ስርዓት ቀብር ዛሬ በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ፡፡

https://p.dw.com/p/4ChfT?maca=amh-RED-Telegram-dwcom ማድመጥ ይቻላል። አስተያየት ለመስጠት፣ ጥቆማ ለማድረስ ይኽን ቦት ይጠቀሙ 👉🏾 @dwamharicbot

Deutsche Welle

የሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ/ም የዓለም ዜና

We recommend to visit

The official Telegram on Telegram. Much recursion. Very Telegram. Wow.

Last updated 2 months, 1 week ago

Intel slava is a Russian News aggregator who covers Conflicts/Geopolitics and urgent news from around the world.

Last updated 1 week, 3 days ago

Your nation. Your news. #OANN *Official

Last updated 4 weeks, 1 day ago