Dive into the Ultimate Free Library: Your One-Stop Hub for Entertainment!

FastMereja.com

Description
Advertising
We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated hace 1 día, 17 horas

ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot

🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹

Last updated hace 5 días, 6 horas

Last updated hace 5 días, 19 horas

3 weeks, 2 days ago

በአድዋ ከተማ ባልታወቁ ሰዎች ታግታ ሦስት ሚሊየን ብር የተጠየቀባት ታዳጊ
#FastMereja
በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን አድዋ ከተማ መጋቢት 10/2016 ዓ.ም. ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግታ የተወሰደችው የ16 ዓመቷ ልጅ እስከ አሁን ያለችበት ሁኔታ እና ቦታ እንደማይታወቅ ቤተሰቦቿ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ማኅሌት ተኽላይ ከሦስት ሳምንት በፊት ከሰዓት በኋላ 10፡30 ላይ ወደ ቋንቋ ትምህርት ቤት ብላ በወጣችበት ወቅት ነው ታፍና መወሰዷን ታላቅ እህቷ ሚሊዮን ተኽላይ የገለጸችው።

ሚሊዮን እንደምትለው አጋቾቹ እህቷ እነሱ ጋር እንደሆነች እና እንድትለቀቅ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር እንዲከፈላቸው የሚጠይቁ ግለሰቦች እስከ አሁን ሁለት ጊዜ ወደ አባቷ ስልክ ደውለዋል።

“ድምጿን አልሰማንም፤ ከሁለት ሳምንት በፊት አንድ ጊዜ ደውለው ነበር። አባታችንም ‘ምን እንደሚፈልጉ እና እንዴት እንደሚሰጣቸው ጠይቋቸው ነበር። እነሱም ‘አዘጋጅ የምንልህን ታዘጋጃለህ’ ብለው ስልካቸውን እየጠበቅን ነው” ብላለች።

ተማሪ ማህሌት በአድዋ ከተማ አዲ ማሕለኻ ተብሎ በሚጠራው አካበቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ‘ባስ ሰላም’ ተብሎ ወደ ሚጠራው የቋንቋ ትምህርት ቤት ብላ ወጥታ ሳትመለስ ቀርታለች።

“ረፍዶባት ስለነበረ ተጣድፋ ነው ከቤት የወጣችው። … ነገር ግን ወዳሰበችበት አልደረሰችም፤ ያገቷት ሰዎችም ወደ ቤት ተመልሳ በምትመጣበት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ነበር ወደ ባባ የደወሉት” ስትል እህቷ ታስረዳለች።

የታገተችው ተማሪ ማኅሌት 16 ዓመት ከሆነች ሁለት ወር አልሞላትም።

በዚህ ዓመት ወደ ሁለተኛ ደረጃ የሚያሸጋግራትን የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ለመፈተን እና ጥሩ ውጤት ለማምጣት ከትምህርቷ ጎን ለጎን ሌሎች ማጠናከሪያ ትምህርቶችን በመውሰድና ቋንቋ በመማር ዝግጅት ታደርግ ነበር።

ቤተሰቦቿ ማኅሌትን “ሥነ ምግባር ያላት የቤት ልጅ ናት” ይላሉ። በተጨማሪም ወደ ትምህርት ቤት በባጃጅ ስትሄድ አግተው የወሰዷትን ሰዎች ማንነት ቤተሰቧ አስካሁን አላወቀም።

አጋቾቹ በማኅሌት ስልክ ወደ አባቷ በመደወል ልጃቸውን ማገታቸው እና “በሕይወት እንድታያት የምትፈልግ ከሆነ ሦስት ሚሊዮን ብር አዘጋጅ” ብለው ስልኩን እንደዘጉት ሚሊዮን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ መደወላቸው እና የጠየቁትን ገንዘብ ለመክፈል ቤተሰቡ እየተዘጋጀ እንደሆነ ጠይቀው ነበረ።

አጋቾቹም የማኅሌትን አባት “ከጠየቅነው በላይ ልትሰጠን እንደምትችል እናውቃለን፤ የጠየቅንህን ገንዘብ እኛ ባልነው ታቀርባለህ” ብለው መልዕክት ምልዕክት አስተላልፈው ስልኩን ዘጉት።

የታጋቿ እህት እንደምትለው ማኅሌት ከታገተችበት ቀን ቀደም ብሎ በቤታቸው አካባቢ ያልተለመዱ ሰዎችን ማየቷን ለአባቷ ተናግራ፤ አባትም ወጥተው ምንም ነገር እንዳላዩ እና እድትረጋጋ መክረዋት ነበር።

ማኅሌት ከታገተች በኋላ በነበሩት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ልጃቸው ያለችበትን ቦታ ለማወቅ ጥረት ቢያደርጉም ምንም ፍንጭ ሳያገኙ እስካሁን ቆይተዋል።

ቤተሰብ ስለእገታው ለፖሊስ ያሳወቀ ቢሆንም፣ የአካባቢው ፖሊስ “እንደምንጠብቀው እየተባበረን አይደለም” የምትለው ሚሊዮን፤ ከእገታው ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችም ቢሆኑ ያለችበትን ሁኔታም ሆነ አድራሻን የሚጠቁም ነገር ሊገኝባቸው አለመቻሉን ገልጻለች።

የታገተችውን ልጃቸውን ድምጽ ከሰሙ ወር ሊሆናቸው የተቃረቡት ቤተሰቦች “ድምጿ እንኳን ብንሰማ ትልቅ ተስፋ ይሆነን ነበር። በር ላይ አፍጥጦ መጠባበቅ በጣም ከባድ ነው” ይላሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች በታዳጊዎች ላይ የሚፈጸም እገታ እየተበራከተ ይገኛል። ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በትግራይ ክልል መዲና መቀለ ህጻናት ላይ ያነጣጠረ እገታ መታየቱን የፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

ድርጊቱን የሚፈጽሙ ግለሰቦች ደግሞ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩ ባለ ሦስት ጎማ ተሽከርካሪዎችን እንደሚጠቀሙ ይገለጻል።

ቀደም ብሎ በመቀለ ከተማ በሚገኙ የተለዩ ክፍለ ከተማዎች ከትምህርት ቤት ልጆች አግተው ሲወስዱ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች እንዳሉ የከተማዋ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

ባለፈው ወር መጋቢት አቶ መሃሪ ከበደ የተባሉ ግለሰብ ልጅ የሆነ ህጻን ታግቶ ተወስዶ ቤተሰቦች አራት ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ተጠይቀው ነበር።

ህጻኑ ከአንድ ሳምንት በላይ በእገታ ላይ የቆየ ሲሆን፣ ቤተሰቦች ከከተማዋ ፖሊስ ጋር በመተባበር ባደረጉት ጥረት ህጻኑ መጋቢት 17/2016 ዓ.ም. ተለቆ ከቤተሰቡ ጋር መቀላለቁን ቢቢሲ በወቅቱ ዘግቦ ነበር።

“ይህ የእገታ ወንጀል በክልሉ የተለመደ አይደለም” የሚለው የክልሉ ፖሊስ “ክስተቱ በተደጋጋሚ እየተከሰተበት ያለበት ምክንያት ግን ጥናት ያስፈልገዋል” ብለው ነበር።

በትግራይ ክልል የተካሄደውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ ከፍተኛ የፀጥታ እና ደኅንነት ስጋት መፈጠሩ የሚገለጽ ሲሆን፣ በርካታ የክልሉ ከተሞች ውስጥም የተደራጁ እና በትጥቅ የተጋዙ ወንጀሎች መከሰታቸውን የፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

ዘገባው የቢቢሲ ነው።

3 weeks, 3 days ago

ሙሉቀን መለሰ አረፈ
#FastMereja
በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያለው የቀድሞው ድምፃዊና ዘማሪ ሙሉቀን መለሰ ለረጅም ጊዜ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ70 ዓመቱ ዛሬ ማለዳ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል::

ሙሉቀን የተወለደው በጎጃም ግዛት በሰሜን ኢትዮጵያ አሁን የዞን አስተዳደር በአማራ ክልል ነው። በስድስት ዓመቱ ከአጎቱ ጋር ወደ አዲስ አበባ ሄደ። በ1966 ዓ.ም በ12 አመቱ የሙዚቃ ስራውን በምሽት ክለቦች እና በምሽት ክለብ ባለቤቶች በተቋቋሙ ቡድኖች በመዝፈን የጀመረ ሲሆን የመጀመሪያ ዘፈኑ እናቴ ሳይወልድኝ መቺ አማችኝ በተሰኘው መድረክ ላይ ተጫውቷል።

በ1972 በግርማ ብየኔ (ፒያኖ እና ዝግጅት)፣ ተስፋ ማርያም ኪዳኔ (ቴኖር ሳክስ)፣ ተክለ አድሀኖም (ጊታር)፣ ፈቃደ አምደ መስቀል (ባስ)፣ ተስፋይ መኮንን (ከበሮ) እና በ1972 የተቀረፀው በቪኒል ላይ ሄዴች አሉ ነው። ራሱ መለሰ። በ1975 ዓ.ም ሁለተኛውን ዘፈኑን “ወተእቲ ማሬ እና እቴ እንደነሽ ገዳዎ” ከኢኳቶር ባንድ ጋር ቀርጿል። የቀሩት የባንዱ አባላት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ሲሰደዱ፣ ሙሉቀን በ1980ዎቹ የሙዚቃ ህይወቱን ካጠናቀቀ በኋላ የጴንጤ ቆስጤ ቤተ ክርስቲያንን ለመቀላቀል ቆየ።

ከ1970ዎቹ የኢትዮጵያ ምርጥ ድምጾች አንዱ ሆኖ ሲቀጥል፣ ከዘመኑ ተዋናዮች በተለየ፣ ሙሉቀን በይፋዊው የመንግስት ቴሌቪዥን የተቀዳ አይመስልም። አንዳንድ ጊዜ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሙሉቀን ዳግመኛ የተወለደ ክርስቲያን ሲሆን በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው። ሙሉቀን ወደ ዓለማዊ ሙዚቃ ሥሩ እንዲመለስ በተደጋጋሚ ቀርቦ ነበር ነገርግን እምቢተኝነቱ እስከ ሰኔ 2023 ድረስ ጸንቷል። በቅርቡ በኢትዮጵያ የመጽሔት አዘጋጆች የተሳሳተ ጥቅስ እንደቀረበባቸው በመግለጽ አንዳንድ ቃለመጠይቆች አድርጓል። ሪከርዱን ለማስተካከል በኢቢኤስ ቲቪ ወጣ። ሙሉቀን ባለትዳርና በዋሽንግተን ዲሲ ሜትሮፖሊታን አካባቢ ነዋሪ ነው። በመላው ዓለም እየተዘዋወረ ያገለግላል። ሙሉቀን መለሰ ከታወቁት ዘፈኖች መካከል “ምነው ከረፈደ”፣ “ይረገም ልቤ”፣ “ሌቦ ነይ”፣ “ቁመቲሽ ሎጋ አዲስ”፣ “ወድጄሽ ነበረ” እና “ተነሽ ቀልቤ ላይ” ይገኙበታል። የእሱ ዘፈን "ናኑ ናኑ ነይ" የድሮ ተወዳጅ ነበር።

የሙሉቀን ሙዚቀኛ ብቃቱ አንዱ የዜማ ደራሲዎቹ የሰጧቸውን ግጥሞች መስራት ነው። ለእሱ እንደቀረበው እያንዳንዱን ቃል ፈጽሞ አይወስድም. ብዙ ፅሁፎችን እንደ ስታይል ይለውጣል፣ አንዳንዴም ሙዚቃውን አብሮ የፃፈ እስኪመስል ድረስ። አብዛኞቹ ጸሃፊዎች ለፍላጎቱ መስማማታቸውን በመረዳታቸው እድለኛ ነበር። ተስፋዬ ለሜሳ እና አለምፀሀይ ወዳጆ ስራዎቻቸውን ካበረከቱላቸው ታዋቂ የዜማ ደራሲያን መካከል ይጠቀሳሉ።

የቀድሞው ድምፃዊና ዘማሪ ሙሉቀን መለሰ ለረጅም ጊዜ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ70 ዓመቱ ዛሬ ሚያዝያ 1 ቀን ማለዳ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል::

እግዚአብሔር ነፍስህን ይማር!! ለቤተሰቦቹና ለወዳጆቹ እግዚአብሔር መፅናናትን ይስጥ!!
መረጃው የይትባረክ ዋለልኝ ነው።

3 weeks, 3 days ago

በሰሜናዊ ጅቡቲ በደረሰው የጀልባ መስጠም አደጋ የ38 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ሕይወት ጠፍቷል
#FastMereja
በጅቡቲ የባህር ዳርቻ ፍልሰተኞችን አሳፍራ ወደ የመን በመጓዝ ላይ በነበረች ጀልባ ላይ በደረሰ የመስጠም አደጋ 38 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ሰኞ ኤፕሪል 8 ቀን 2024 እ.ኤአ በጅቡቲ ሰሜን ምስራቅ ጎዶሪያ በሚባል የባህር ዳርቻ አቅራቢያ 60 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን አሳፍራ ወደ የመን ትጓዝ የነበረች ጀልባ ላይ በደረሰው የመገልበጥ አደጋ የ 38 ፍልሰተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በጅቡቲ የኢፌዴሪ ሚሲዮንም አደጋው ከደረሰ በኋላ ወደ ስፍራው በመጓዝ የአደጋውን መንስኤ በማጣራት ላይ ይገኛል።

በየዓመቱ ከ200 ሺ የሚበልጡ ፍልሰተኞች ከጅቡቲ ባህር ዳርቻ የኤደን ባህረ ሰላጤ በመነሳት መካከለኛው ምስራቅ አገራት ለመድረስ በየብስ እና በባህር አደገኛ ጉዞ ያደርጋሉ። ባለፉት አምስት ዓመታት በጀልባ መስመጥ አደጋ ብቻ የ189 ዜጎቻችን ሕይወት አልፏል። በየጊዜው የሚደርሰው አደጋ እንዳለ ቢሆንም የፍልሰተኞቹ ቁጥር ግን አሁንም እየጨመረ ነው። በጅቡቲ በኩል አድርጎ ወደ የመን መስመር የሚደረግ ሕገ ወጥ ጉዞ ከሞት ውጭ ትርፍ የሌለው መሆኑን በየጊዜው ከሚደርሱ አሰቃቂ አደጋዎች መረዳት አያዳግትም።

ሚሲዮኑ በዚህ አሳዛኝ ክስተት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ ከጅቡቲ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚደረገው ህገ ወጥ ጉዞ እጅግ አደገኛ ከመሆኑም በላይ በየጊዜው የዜጎቻችንን ሕይወት እያሳጣን ይገኛል። በዚህም ዜጎቻችን ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ለከፋ አደጋ እየዳረጉ ይገኛሉ። በመሆኑም ዜጎቻችን በህገ ወጥ ደላሎች የሀሰት ስብከት በመታለል ውድ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በዚህ አደገኛ የጉዞ መስመር ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ  እና የፍትህ አካላትም ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ከገጠራማ የአገራችን አካባቢዎች ዜጎቻችን በመመልመል ለስደት በሚዳርጓቸው ግለሰቦች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪውን ያስተላልፋል።

በቴሌግራም መረጃ ማቅረብ ጀምረናል ተከተሉን
https://t.me/fastmereja
https://t.me/fastmereja

1 month ago

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የሚገነቡ ማንኛውም ግንባታዎች 10 ሜትር መራቅ እንዳለባቸው ውሳኔ አሳለፈ
#FastMereja
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ 3ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ በሶስት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል::

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ በ3ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ   ለከተማዋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም ጉልህ ሚና ባላቸው ጉዳዮች ላይ በዛሬው ዕለት ተወያይቶ አጽድቋል:: በዚህም መሰረት:-

1ኛ. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የተሽከርካሪ አስተዳደር ህግ እና ሥርዓት ለማስከበር የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት አሰጣጥ ረቂቅ ደንብን ለአሰራር በሚያመች መልኩ ሀሳብ ተሰጥቶበት ደንቡ ፀድቋል።

2ኛ.  የከተማዋን ስታንዳርድ እና መዋቅራዊ ፕላን ለማስጠበቅ እንዲሁም መልሶ ማፍረስ እንዳይገጥም ፤ ግንባታዎች ከመንገድ ያላቸው ርቀት ከዚህ በኋላ ወጥነት ያለው የከተማ አሰራር አንዲኖር በማሰብ ከመንገድ መራቅ ያለባቸውን 3 ደረጃዎች ለማውጣት በቀረበው  መተዳደሪያ ደንብ ላይ በመወያየት ፤  ከአሁን በኋላ የሚገነቡ ማንኛውም ግንባታዎች  ከዋና ከመንገድ በ10 ሜትር  ርቀት መሆን እንደሚገባው ፤ ከንዑስ ዋና መንገድ 5 ሜትር ርቀት፤ ሰብሳቢ መንገድ ደግሞ 3 ሜትር ርቀት በተጨማሪም የውስጥ ለውስጥ መንገድ 2 ሜትር ርቀት  መጠበቅ እንዳለባቸው ካቢኔው ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

3ኛ. የነገዋ የሴቶች ተሀድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ማቋቋሚያ ደንብ ማዕከሉን በተለይም ለጎዳና ህይወት ፤ ለፆታዊ ጥቃት ሰለባ እና ለወሲብ ንግድ ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች ፣ መጠለያ፣ ማገገሚያ እና የተመሰቃቀለ ህይወታቸውን እንደገና ለማደስ የሚያስችል የሙያ እና ክህሎት ሥልጠናዎች የሚያገኙበትን እና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚያግዝ አቅም ያለዉ ማዕከል እንዲሆን ለማስቻል በሚያግዘው ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ካቢኔው ተወያይቶ አጽድቋል::።

1 month ago
FastMereja.com
1 month ago

ጁምዓና ከተራና ቃና ዘገሊላ ጨምሮ አራት ቀናት ሥራ ዝግ ሆኖ እንዲከበሩ ጥያቄ ቀረበ
#FastMereja
ጁምዓ፣ ከተራና ቃና ዘገሊላ የአደባባይ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች፣ እንዲሁም የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ በዓላት ሥራ ዝግ ሆነው እንዲከበሩ በፓርላማ ጥያቄ ቀረበ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና በተባባሪነት ለሕግና ፍትሕ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ የተመራውን፣ የሕዝብ በዓላትንና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብ ውይይት መድረክ ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲካሄድ፣ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ ምሁራንና ሌሎች ተቋማት ተሳትፈው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን በመወከል የተገኙት ኡስታዝ አህመዲን ጀቢል፣ በእስልምና እምነት አንድ ሰው ሦስት ተከታታይ ጁምዓ ካልተገኘ በመናፍቅነት የሚያስፈርጅ ከባድ ጉዳይ በመሆኑ፣ ዓርብ (ጁምዓ) ቀን ሥራ ዝግ እንዲሆን፣ ወይም ደግሞ አሁን በሥራ ላይ ያለውን ከአምስት ሰዓት ተኩል እስከ ሰባት ሰዓት ተኩል በአዋጁ መካተት አለበት ብለዋል፡፡

ሃይማኖታዊ በዓል የሚለው አገላለጽ በሙስሊሞች ከሆነ ዓመታዊና ሳምንታዊ በዓላት በመኖራቸው፣ ዓመታዊ የሚባሉት በአዋጁ የተጠቀሱት የኢድ አልአድሃ (አረፋ) በዓል፣ የመውሊድና የኢድ አልፈጥር በዓል ሲሆኑ፣ ሳምንታዊው ደግሞ ጁምዓ መሆኑ መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡

አዋጁ የበዓላት አከባበርን ሃይማኖታዊ፣ ብሔራዊና ታስበው የሚውሉ በማለት በዝርዝር የጠቀሰ ቢሆንም፣ በዓላቱ የሚከበሩበትን የተለየ ቀን ገልፆ የሙስሊም በዓላትን ግን አልገለጸም ብለዋል፡፡

‹‹በአዋጁ መስከረም 1 እና 17፣ እንዲሁም ሚያዚያ 27 እየተባለ ሲጠቀስ፣ የእስልምና በዓላትን ለመጥቀስ የተቸገረበት ምክንያት፣ የሙስሊም በዓላት የሚከበሩበት ቀን በኢትዮጵያውያን ካላንደር በጨረቃ ከታየ ወይም ካልታየ በሚል ብዥታ ስለሚፈጥር በመሆኑ፣ አዋጁ መላ ኢትዮጵያውያን የሚገለገሉበት እንዲሆን ከተፈለገ የሂጂራ ካላንደር አቆጣጠርን ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ኡስታዝ አህመዲን አክለውም፣ በአዋጁ የመጀመሪያውና የመጨረሻ ገጽ ላይ የተቀመጠው ቀን ዓመተ ምሕረት (ዓ.ም.) ሙስሊሞችን የማይመለከት በመሆኑ፣ የሙስሊም ካላንደር አብሮ ገብቶ በዓሉ ሲጠቀስ በሂጂራ በተቀመጠው ቀን መሆን አለበት ብለዋል፡፡

በአዋጁ ላይ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትሪያሪክ የሕግ መምርያ ኃላፊ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ጌትነት፣ እየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ባህረ ዮርዳኖስ ሄዶ መጠመቁን የሚያሳየው የቃል ኪዳኑን ታቦት በመያዝ ጥር 10 ቀን የሚከበረው ከተራና ከጥምቀት በኋላ ጥር 12 ቀን የሚከበረው ቃና ዘገሊላ ክብረ በዓላት ከሥራ ዝግ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡

የእምነቱ ተከታይ የሆኑ ሠራተኞች የከተራ በዓል ከሰዓት በኋላ ሲከበር ግልጽ መብት ካልተሰጣቸው በስተቀር፣ ሥራውን ትተው ቢሄዱና በመሥሪያ ቤት ስለሚፈጠረው አለመግባባት ኃላፊነት የሚወስደው አካል በግልጽ መቀመጥ አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም የካቲት 12 የሰማዕታት ቀን ታስቦ ከመዋል ይልቅ ከሥራ ዝግ ሆኖ መከበር ይገባዋል ያሉት ደግሞ፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡

‹‹የካቲት 12 ቀን ከደርግ ዘመነ መንግሥት በፊት ቀኑ ዝግ ሆኖ ይከበር የነበረ ሲሆን፣ በ1967 ዓ.ም. የደርግ መንግሥት ሲቋቋም በዓላትን እንደ አዲስ በረቂቅ በማቅረቡ፣ በወቅቱ የነበሩት የአርበኞች ማኅበር አመራሮች ተጠርተው ቀኑ ከሥራ ዝግ መሆኑ ቀርቶ እየታሰበ እንዲውል ከተነገራቸው በኋላ፣ በወቅቱ ፍርኃትም ስለነበር ወዲያውኑ ታስቦ እንዲውል ተደርጓል፤›› ሲሉ አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዘር፣ ፆታ፣ ዕድሜ ሳይለይ በአዲስ አበባ ጥቁር ማቅ የተለበሰበት በመሆኑ፣ ቀኑን ከሥራ ዝግ በማድረግ ተከብሮ መዋል አለበት ሲሉ አበባው (ረዳት ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ተቋማት የተነሱትን የሥራ ዝግ መደረግ ጥያቄን በተመለከተ በፍትሕ ሚኒስቴር አዋጁን በማርቀቅ ሒደት የተሳተፉት አቶ ጠገነኝ ትርፌ፣ ‹‹ጁምዓ፣ ከተራና ሌሎች አዳዲስ በዓላት ሥራ ተዘግቶ የሚውሉበትን ቀን ባበዛን ቁጥር፣ የሥራ ቀናትን ማጣበብና ድህነትን ለመታገል ችግር ይፈጥራል፤›› ብለው ከኢኮኖሚ፣ ከማኅበራዊና ከባህል አኳያ ሊያመጡት የሚችሉት ፋይዳ ታይቶ ቋሚ ኮሚቴው ይመለከተዋል ብለዋል፡፡

‹‹አዋጁ በዓላትንና አከባበራቸውን ለመወሰን የወጣና የእረፍት ቀናትን በተመለከተ የራሱ ማዕቀፍ ያለው ቢሆንም፣ እንደ አገር የራሳችን መዳረሻ ዓላማ ያለን በመሆኑ በጋራ ሊያስተሳስሩን የሚችሉ እሴቶችን አስጠብቆ፣ አዳዲስም ካሉ የጋራ ዓላማ የሚሰንቅ መሆን አለበት፤›› ሲሉ የፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር አቶ አዲስ ጌትነት ገልጸዋል፡፡

አዋጁ መሠረት ያደረገው በዋናነት በዓላትን ዕውቅና መስጠትና አከባበር ላይ እንጂ፣ የእረፍት ቀን መሰየም አለመሆኑ ታሳቢ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በኡስታዝ አህመዲን የተነሳው አዋጁ ውስጥ ‹ዓ.ም.› የሚለውን በተመለከተ፣ በአዋጁ የተገለጸው የዘመን አቆጣጠር አገሪቱ እየተከተለች ያለውን በመሆኑ ነው እንጂ የእስልምና እምነት አቆጣጠርን ችላ ተብሎ አይደለም ብለዋል፡፡

መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ባቀረቡት ተጨማሪ ሐሳብ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕጎችን ሲያወጣ ቤተ እምነቶችን የማሳተፍ ግዴታ እንዳለበት፣ ቤተ እምነቶችም በሁሉም አዋጆች ላይ ሐሳባቸውን ቢሰጡ ይጠቅማሉ እንጂ አይጎዱም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሕግ ማውጣት ችግር የሌለባት አገር ብትሆንም ሕግ ከወጣ በኋላ ሁሌም እንደሚሻሻል፣ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከዜጎች ግብዓት ስለማይወሰድ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በአደባባይ ለሚከበሩ በዓላት የመንግሥት የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን የፀጥታና የደኅንነት ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው በረቂቅ አዋጁ መኖሩን፣ ነገር ለሌሎች በዓላት ለምን የፀጥታ ጥበቃ አይደረግም በማለትና ማናቸውንም በዓላት የመጠበቅ ኃላፊነት በሚል በረቂቅ አዋጁ መስተካከል አለበት ሲሉ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ አሳስበዋል፡፡

አበባው (ረዳት ፕሮፌሰር) ጥቅምት 15 ቀን የመከላከያ (የሠራዊት) ቀን አዲስ በፀደቀው የኢትዮጵያ አገር መከላከያ አዋጅ የተደነገገ ቢሆንም፣ ቀኑ ታስቦ እንዲውል በማድረግ የጀግኖች ቀን መኖር አለበት ብለዋል፡፡

በተለያዩ ወቅቶች ጀግና የነበሩና ስማቸው የማይታወቁ ያልተዘመረላቸው ሰዎች፣ አካላቸው የጎደለ፣ ሕይወታቸውን የሰጡ፣ በተለያየ መንገድ ለአገር በውትድርና አስተዋጽኦ ያደረጉ የሚታሰቡበት ቀን ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የጤና፣ የማኅበራዊ ልማት፣ የባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቀሰሙ ማሞ፣ ረቂቅ አዋጁ ኢትዮጵያውያንን እንዲመስል ዘላቂነት ያለው ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የተሰጡ አስተያየቶችም ረቂቅ አዋጁን ለማጎልበት እንደሚያግዙ ገልጸው፣ የመንግሥት ተቋማት ገለልተኛ ሆነው የተጣለባቸውን ሕዝብን የማገልገል ኃላፊነት ብቻ እንዲወጡ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

ዘገባው የሪፖርተር ነው።

1 month, 1 week ago

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በፌዴራል መንግስት እና ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) እያለ በሚጠራው ቡድን መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም የተደረገውን ድርድር እና በኋላም የተደረሰውን የሰላም ሥምምነት አስመልክቶ በየጊዜው በአንክሮ እየተከታተለ አቋሙን ይፋ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን በፌዴራል መንግስት እና በትህነግ መካከል የተደረገው ሥምምነትና ትግበራ ላይ እንደ ድርጅት የታዘብናቸው ጉድለቶች ቢኖሩም ለሀገር ሰላምና አብሮነት እድል ይሰጣል፤ ለውይይትና ንግግር በር ይከፍታል በሚል በጎ መሻት የሀገራችንን ብሎም የትግራይን ህዝብ ሰላም መሆን በመፈለግ፤ መንግስት የስምምነቱ አፈጻጸም ላይ የሰራቸውን ስህተቶች ጭምር ለትልቁ ሀገራዊ የጋራ ሰላም ሲባል በትዕግስትና በጥሞና ስንከታተል ቆይተናል፡፡

በፕሪቶሪያው ሥምምነት አንቀጽ 6(F) መሰረት ትሕነግ በሰላሳ ቀናት ውስጥ ቀላል መሳሪያን ጨመሮ ጠቅላላ ትጥቅ እንዲፈታ፤ አንቀጽ 3(5) መሰረት ደግሞ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ገብቶ ጸጥታ የማስከበሩን ሥራ በተሟላ ሁኔታ እንደሚረከብ ሥምምነት የተደረሰ ቢሆንም፣ ወያኔ ትጥቅ ሳይፈታ የሀገር መከላከያ ሠራዊትም ወደ ትግራይ ገብቶ ጸጥታ የማስከበር ሥራውን ሳይረከብ፣ በጦርነት ጉዳትና መልሶ ግንባታ ስም ወያኔ በትግራይ ግዜአዊ አስተዳደር ስም ከፍተኛ የገንዘብ እና የግብዓት ድጋፍ ሲደረግለት የቆየና የፕቶሪያውን የሰላም ሥምምነት አንቀጽ 7(1)(D) በግልፅ እየጣሰ ባለበት ሁኔታ የሰላም ስምምነቱ ይከበር የሚል የምጸት ፕሮፓጋንዳ እና የጦርነት ጉሰማ ላይ በአዲስ መልክ ተጠምዷል፡፡

ትህነግ ወያኔ ሐገራዊ ሀይሉ ተከፋፍሎ የርስበርስ ግጭት ውስጥ ወድቋል ብሎ ባመነ ጊዜ ሁሉ እንደ ሁኔታው እያፈራረቀ አንደኛውን በመጠጋትና ሌላውን በመጋፋት ነጣጥሎ ሁሉንም ለማዳከምና ለማጥቃት ሲያደባና ዝግጅት ሲያደርግ ከርሟል። በተለይም ግልብ የሆነውና ዘወትር በሬ ካራጁ ያደረውን የልሂቅ አካል በደጋፊነት መልምሎ ለማሰለፍ በተለይም ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በጦርነት ያላገኘውን ድል ሀገራዊውን ጥምረት በመከፋፈል፣ እርስበርሱ እንዳይነጋገርና እንዳይግባባ ብሎም የሴራ ፖለቲካ ሰለባ እንዲሆን እና ግጭት ውስጥ ገብቶ የሃይል ሚዛኑ እንዲዛነፍ ለማድረግ የተደራጀና ከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ስራ በቅጥረኞቹ በኩል በሰፊው ሲሰራ ቆይቷል።

የአማራ ህዝብ የግፍና ሰቆቃ ሀተታ ዋና ደራሲ የሆነው ትህነግ ወያኔ ራሱ በቀሰቀሰው ጦርነት ሳይቀር በሀሰት ላይ የተመሰረተ የሞራል የበላይነት እንዲኖረው አንዳንድ የልሂቃን ወገኖችን ሳይቀር የሀይል አሰላለፍ ግምገማና አጠቃላይ ፖለቲካዊ ምልከታቸውን በማዛባት ጭምር "ጅብ በማያውቁት ሀገር" እንደሚባለው ነገ አድሮ በገዛ ህዝባቸው ላይ ለሚፈጸም ወያኔአዊ ጥፋት አጋርነትን ለማበጀት መልምሎ ሲያሰልፋቸው አስተውለናል፡፡ አዲሱ የትህነግ ወያኔ መግለጫና የጦርነት ዛቻም ከዚህ አንፃር መታየት ይኖርበታል።

ሆኖም ግን ትሕነግ ወያኔ በምስረታ ሰነዱ የአማራን ሕዝብ በጠላትነት የፈረጀ እና ማኅበራዊ እረፍት መንሳት የሚል ፋሽስታዊ የፖለቲካ ፕሮግራም ቀርጾ እና ከአማራ ዋና ዋና ግዛቶች ውስጥ ለም እና ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ቦታዎች ወደ "ታላቋ ትግራይ" ለማካተት በማወጅ ደደቢት በርሃ መውረዱን ለአፍታም የምንዘነጋው አይሆንም::

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የህዝባችን የማንነትና ወሰን ጥያቄዎች ከ30 ዓመት በላይ በፈጀ ያልተቋረጠ ትግልና መስዋትነት ታሪካዊና ስነልቦናዊ መፍትሄ አግኝተዋል ብለን እናምናለን፡፡ በዚህም የአማራ ሕዝብ እንኳንስ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ከሚጋራቸው ሕዝቦች ቀርቶ ከጎረቤት ሀገራት ወንድም ሕዝቦች ጋርም በሰላም፣ በፍቅርና በመከባበር መኖር የሁሌጊዜም ምርጫው መሆኑን የሚያረጋግጥበት ከባቢ ፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ የህዝቦች አንድነትና የሀገር ሰላም የማይመቻቸው ቀውስ ጠማቂዎችና ከዳግም ጥፋታቸው ያልተማሩ የደም ነጋዴዎች ለሌላ ዙር ሀገራዊና ቀጠናዊ ቀውስ መዘጋጀታቸውን በግልፅ መለፈፍ ጀምረዋል፡፡

በመሆኑም፡-

የተከበርከው የአማራ ሕዝብ ፤

ምንም እንኳ አሸባሪው እና ተስፋፊው ትሕነግ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጠላት ቢሆንም ፣ በተለይ የአማራ እና የአፋር ሕዝቦች የቡድኑ ወረራ ቀጥተኛ ሰለባ እና ገፈት ቀማሽ በመሆናቸው ጦርነቱን የመመከት ድርብ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በሁሉም አካባቢዎች የሚገኝው ሕዝባችን ካለፈው የጥፋት ግዜ በመማር ለጠላት ፕሮፖጋንዳ ጀሮ ባለመስጠት ራስህን ከታሪካዊ ጠላትህ ለመከላከል ከመቸውም ጊዜ በላይ በአንድነት እንድትቆም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

የተከበርከው የትግራይ ሕዝብ ፤

በስምህ የሚነግደው አሸባሪው እና ተስፋፊው ቡድን ፣ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ያለህን ትስስር ለመበጠስ እና ከኢትዮጵያዊ ማንነትህ ለመንቀል በማያባራ የጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዳስገባህና አምራች ሀይልህን ፍትሀዊ ባልሆነ ጦርነት ማግዶ ማስፈጀቱ ይታወቃል፡፡ ልጆችህን ከጉያህ እየነጠቀ ፣ ጥሪትህን እያሟጠጠ እና አግቶ በመያዝ ከሌሎች ኢትዮጵያውን ጋር በአንድነት እና በሰላም እንዳትኖር ጋሬጣ የሆነብህን ደም-የማይጠግብ የሽብር ቡድን ከራስህ ላይ አሽቀንጥረህ በመጣል ራስህን ነጻ እንድታወጣ ጥሪያችንን እያስተላለፍን ፣ ከሽብር ቡድኑ እገታ ነጻ ለመውጣት በምታደርገው ተጋድሎ ድጋፋችን እንደማይለይህ ከወዲሁ እናስታውቃለን፡፡

የአማራ ክልል መንግስትና የፌዴራል መንግስት፦

ትህነግ ወያኔ ተደጋጋሚ ወረራ በመፈጸም ታሪክ ይቅር የማይለው ሰፊ ጥፋት በሀገርና በህዝብ ላይ የፈጸመ ሆኖ ሳለ ይህ አልበቃው ብሎ አሁንም ሌላ ዙር ጦርነት ቀስቃሽ ፕሮፓጋንዳ ውስጥ የገባ በመሆኑ ይህንን የወያኔን ጠብ አጫሪነት በትኩረት እንዲከታተሉ በጥብቅ እያሳሰብን ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ልዩ ትኩረት ሰጥተው በውይይትና ድርድር ሰላም የማስፈን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሁንም ጥሪ እናቀርባለን።

መጋቢት 17/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ!

1 month, 1 week ago

በቀን ከ350 በላይ የአእምሮ ህመምተኞች እያስተናገደ ያለው አማኑኤል ሆስፒታል የቦታ እጥረት አጋጥሞኛል አለ።
#FastMereja
አዲስ አበባ የሚገኘዉ የቅዱስ አማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለታካሚና አካሚዎች በቂ ቦታ እንደሌለዉ ሐኪሞች አስታወቁ።ከቅርብ ግዜ ወዲሕ ቀላል እና መለስተኛ የሚባሉት የአእምሮ ህመም ህክምና በተለያዩ ሐኪም ቤቶች ቢሰጥም አብዛኛዉ የእዕምሮ ሕሙም አሁንም የሚታከመዉ አማኑኤል ሆስፒታል ነዉ።ሆስፒታሉ ከአገልግሎት መስጠት ከጀመረ 80 አመት ሆኖታል።

በኢትዮጵያ እስካሁን  የአእምሮ ጤና ፓሊሲ አለመኖሩ  በዘርፉ ያለውን ችግር አባብሶታል ዶ/ር ክብሮም ሀይሌ የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስት እና የአማኑኤል ሆስፒታል ሚዲካል ዳይሬክተር ለ DW እንደተናገሩት።በአመት 130ሺ  ማለት  በቀን ከ 350 በላይ የአእምሮ ህመምተኞች ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ። ሀኪሞቹም በሰአት በአማካይ 44 ህመምተኞችን ያክማሉ ማለት ነዉ።80% የሚሆኑት ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡት  ከባድ  የአእምሮ ህክምና  እና ክትትል የሚይስፈልጋቸው ናቸው ።

ይህ ማለት ነባራዊ ሁኔታዎች መገንዘብ የማይችሉ  በእውን የሌሉ ነገሮችን ማየት፣መሰማት፣  እና ዝብርቅርቅ ያሉ ሀሳቦች ማንፀባረቅ የሚታይባቸው ታካሚዎች  እንደሆኑ የገለፁት ዶክተር ክብሮም ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በዚህ በሽታ የተያዙ ሰዎች በመሆናቸው ሰፊና ከተፈጥሮ ጋር የተዋሃደ አካባቢ ይፈልጋሉ። የአእምሮ ህመም በባህሪው ጊዜን የሚፈልግ  ነው  ለታካሚዎች  ሆነ አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሞያዎች ከታካሚው ቁጥር ጋር  የሚመጣጠን  ሰላማዊ  የሆነ ሰፊ  ባታ ያስፈልጋል   ይላሉ ።

እንዲህ በተደራራቢ እና ፋታ በማይሰጥ ስራ በሀገሪቱ በብቸኝነት የሚያገለግለው  የቅዱስ አማኑኤል ሆስፒታልየአእምሮ ህክምና ዶክተሮች ለተጨማሪ ትምህርት እና ስልጠና እንዲሰጣቸው ለሚያቀርቡት ጥያቂ   የ ሚንስትር መስራቤቱ  ምላሽ  የዘገየ እንደሆነ ባለሙያው ተናግረዋል።

ዘገባው የዶቼ ቬለ ነው።

በቴሌግራም መረጃ ማቅረብ ጀምረናል ተከተሉን
https://t.me/fastmereja
https://t.me/fastmereja

1 month, 1 week ago

አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ 18 መምህራኑ እንደጠፉበት አስታወቀ
#FastMereja
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ መክሯል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ክብርት እና የዩንቨርሲቲው አመራር አባላት በጋራ ባደረጉት ውይይት ላይ እንደተገለጸው ለሶስተኛ ድግሪ በሚል ለትምህርት የተላኩ እና የጠፉ የዩንቨርሲቲው መምህራን ጉዳይ ዋነኛው ነው፡፡

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ እና የፌደራል ዋና ኦዲተር አመራሮች ዩንቨርሲቲው ለሶስተኛ ድግሪ ትምህርት ብሎ ስፖንሰር ሆኖ የላካቸው መምህራን በወቅቱ ትምህርታቸውን አጠናቀው እንዳልተመለሱ፣ ዩንቨርሲቲውም ለነዚህ መምህራን የከፈለውን ከ7 ሚሊዮን በላይ ብር ገንዘብ ለምን ተመላሽ አላደረክም? በሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስተኛ ድግሪ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ 18 መምህራን ትምህርታቸውን በተቀመጠላቸው ጊዜ አጠናቀው እንዳልተመለሱ፣ የመመለሻ ጊዜያቸውም እንዳለፈ መናገራቸውን በምክር ቤቱ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ በተላለፈው ላይ የቀጥታ ስርጭት ላይ ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

በዩንቨርሲቲው ህግ መሰረት አንድ የዶክትሬት ወይም የሶስተኛ ድግሪ ትምህርትን ለማጠናቀቅ አራት ዓመት በቂ ሲሆን በተለያዩ አስቸጋሪ ምክንያቶች ትምህርቱን ማጠናቀቅ ላልቻሉ ደግሞ ሁለት ዓመት እንዲጨመርላቸው ይፈቅዳል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል፡፡

ይሁንና እነዚህ የዶክትሬት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በተለያዩ ዩንቨርሲቲዎች ከተላኩ መምህራን መካከል ትምህርታቸውን በስድስት ዓመታት ውስጥ አጠናቀው ባለመምጣታቸው ከስራ መባረራቸው ተገልጿል፡፡

እነዚህ የቀድሞ የዩንቨርሲቲው መምህራን ከስራ በመባረራቸው ምክንያት ለትምህርት ስፖንሰር፣ ደመወዝ እና ትራንስፖርት ወጪ የወሰዱትን ገንዘብ ማስመለስ አለመቻሉን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ከ18ቱ ውስጥ አምስቱ ከሀገር ውጪ መሆናቸውን በማረጋገጣችን ዋሶቻቸው ላይ ክስ መስርተን ውሳኔው ለእኛ ተወስኖልናል ማስመለስ እንጀምራለን ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም 15ቱ ቀሪ የቀድሞ መምህራን ግን በሀገር ውስጥ እንዳሉ እና የትኛውም ተቋም እንዳልተቀጠሩ አረጋግጠናል ነገር ግን ከደመወዛቸው እና ስራቸው ስላገድናቸው ገንዘቡን ተመላሽ ማድረግ አልቻልንም ሲሉ ለጥያቄው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ዘገባው የዐል ዐይን ነው።

በቴሌግራም መረጃ ማቅረብ ጀምረናል ተከተሉን
https://t.me/fastmereja
https://t.me/fastmereja

1 month, 2 weeks ago

ሀሰተኛ ሰነዶችንና ስሞችን በመጠቀም ከ2 ቢሊዮን 951 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት ያደረሰ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ
#FastMereja
ቴዎድሮስ ንጉሴ ሀያርያ እና ቴዎድሮስ ንጉሴ ወልድሀዋሪያ በተባሉ ሀሰተኛ ስሞችን በመጠቀም ከ2 ቢሊዮን 951 ሚሊዮን 053 ሺህ 7 መቶ 49 ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት ያደረሰ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ሊውል የቻለው ሐሰተኛ ስሞቹን በመጠቀም ከሌሎች ግብረ-አባሮቹ ጋር በመሆን ቴዎድሮስ ንጉሴ ሀያርያ በሚለው ስም ንግድ ፍቃድ በማውጣት፣ የወንጀል ድርጊቱ እንዳይደረስበት ለማድረግ እና ከታክስ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ክትትል ለመሰወር በቦሌ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በመቀየር ህጋዊ በመምሰል የዕቃ እና አገልግሎት ግብይት ሳይኖር የተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች የመለያ ቁጥር ርLB 0019300 ከሆነው የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ በ1 ሺህ 2 መቶ 70 ደረሰኞች አማካኝነት ምንም ሽያጭ ሳያካሄድ ደረሰኞችን ብቻ በመሸጥ መጠኑ 2,951,053,749.86 ብር የሚሆን ሽያጭ በማከናወኑ ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ባደረገው ጠንካራ ክትትል በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራባት እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግዥ ፈጽመናል በማለት ሀሰተኛ ደረሰኞቹን ከተጠርጣሪው ላይ የገዙ ግብር ከፋዮች ደግሞ በሀሰተኛ ሰነዶች አማካኝነት ወጪያቸውን በማነር ለመንግሥት የሚከፈለውን ግብርና ታክስ እንዲቀንስና ያልተገባ ተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ተመላሽ ከመንግሥት ካዝና አንዲወስዱ ማድረጉንም ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።

የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኢንተለጀንስ ሥራ ሂደት አስልቶ በላከው መሠረት ተጠርጣሪው ምንም ግብይትና አገልግሎት ሳይሰጥ ደረሰኞችን ብቻ በመሸጥ በመንግስት ላይ ያደረሰው ጉዳት መጠን፦
1. የንግድ ትርፍ ግብር:- 769 ሚሊየን 890 ሺህ 1 መቶ ከ08 ሣንቲም፤
2. የተጨማሪ እሴት ታክስ( VAT) መጠን፦ 384 ሚሊየን 920 ሺህ 054 ብር ከ04 ሣንቲም ሲሆን፤
በአጠቃላይ በድምሩ 1 ቢሊዮን 154 ሚሊዮን 760 ሺህ 1 መቶ 62 ብር ከ12 ሣንቲም በመንግስት ላይ ጉዳት ማድረሱም ተረጋግጧል።

ተጠርጣሪው ቴዎድሮስ ንጉሴ ሀያርያ እና ቴዎድሮስ ንጉሴ ወልድሀዋርያ የተባሉ ሀሰተኛ ስሞችን በመጠቀም በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ እና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ከተለያዩ አራት ወረዳዎች የነዋሪነት መታወቂያ እንዳወጣ በማስመሰል እና አራት ሀሰተኛ የውክልና ሠነዶችን በማዘጋጀትና በመጠቀም፤ በገቢዎች ሚኒስቴር የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ አቅራቢ ድርጅት፣ በተለያዩ ባንኮች፣ በንግድ ፅህፈት ቤቶች እና በሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የግል ድርጅቶችና ግለሰብ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ በመምሰል ወንጀል ሲፈጽም መቆየቱን ፖሊስ ደርሶበታል።

ፖሊስ ከፍርድ ቤት የብርበራ ፈፍቃድ በማውጣት አያት ሆሴ ሪልስቴት በሚገኘው የተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ውስጥ ባደረገው ብርበራ፤ ስምንት ፍላሾችን፣ በተጠርጣሪው ሀሰተኛ ስሞችና በራሱ በተጠርጣሪው ትክከለኛ ፎቶግራፍ የወጡ እና የተዘጋጁ ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችንም መያዙን ፖሊስ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጾ ኅብረተሰቡም ወደ ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ቢሮ በአካል ቀርቦ በተጠርጣሪው ላይ ተጨማሪ መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀርባል።

መረጃው የፌዴራል ፖሊስ ነው።

በቴሌግራም መረጃ ማቅረብ ጀምረናል ተከተሉን
https://t.me/fastmereja
https://t.me/fastmereja

We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated hace 1 día, 17 horas

ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot

🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹

Last updated hace 5 días, 6 horas

Last updated hace 5 días, 19 horas