ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ

Description
This channel is not operated by Deacon Yaregal Abegaz- ይህ ገጽ የሚንቀሳቀሰው በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ አይደለም

https://youtube.com/@yaregalabegaz?si=1f5NHTaQ2l2LbxWQ

“ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።”
— 2ኛ ቆሮ 11፥28
Advertising
We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated hace 3 semanas, 5 días

Last updated hace 3 semanas

ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot

🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹

Last updated hace 1 mes, 1 semana

1 month, 1 week ago

**On Fasting and Feasts

By:Saint Basil the Great**

In this new collection of sermon translations-Basil addresses such issues as drunkenness, hesitations over baptism, community benefits of fasting, how to be thankful when facing loss and disaster, and the mystery of the incarnation. Also included are three sermons on local martyrs Julitta, Mamas, and Barlaam. This small volume of elegant translations will be a vital and valued resource for anyone interested in religion and the body, early Christian spiritual disciplines, and their application to the Church today.

1 month, 1 week ago

መንፈሳዊነት ምንድን ነው ?

፩. መንፈሳዊነት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ኅብረትና አንድነት ነው፡፡

፪. መንፈሳዊነት ስሜትን፣አእምሮንና መንፈስን ሲገዛ ነው፡፡

፫. መንፈሳዊነት ጥረት፣ተጋድሎ፣ ውጣ ውረድ ነው

፬. መንፈሳዊነት ጊዜና ቦታ የማይወስነው ነው፡፡

፭. መንፈሳዊነት የኑሮ ሁኔታ የማይወስነው ነው፡፡

በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ

1 month, 1 week ago

ለካህን መናዘዝና ቀኖና መቀበል ለምን?

  • የተሐድሶዎች ትምህርት ለካህን ስለመናዘዝና ቀኖና ስለመቀበል
  • በዚህ ጉዳይ ላይ የተሐድሶዎች መሠረታዊ ስህተቶች
  • ለንስሐ አባት መናዘዝና ቀኖና መቀበል በመፅሀፍ ቅዱስ ትምህርት
  • ቀኖና የሚሰጥባቸው ምክኒያቶች
  • ንስሐ አባትና ቀኖና በአበው ትምህርት

~~~ +++++ ~~~~

“ነቢዩ ናታን ንጉሥ ዳዊትን ኃጢአቱን ከነገረው በኋላ ወዲያውኑ ኃጢአቱን እንዳመነ አጽናንቶት ነበር፡፡ ሆኖም ብፁዕ ዳዊት ግን ምንም እንኳ እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል፡ ኣትሞትም' (2 ሳሙ. 12፡13) የሚለውን የነቢዩን ቃል የሰማ ቢሆንም ንስሐ ከመግባት ግን አልተመሰለም፡፡ ንጉሥ የነበረ ቢሆንም በልብሰ መንግሥት ፋንታ አመድ ለበሰ በወርቅ ዙፋን ላይ በመቀመጥ ፋንታ በመሬት ላይ፣ ያውም በአመድ ላይ ተቀመጠ፡፡ በአመድ ላይ የተቀመጠ ብቻ ሳይሆን አመድንም ምግቡ አደረገ፤ እርሱ ራሱ “አመድን እንደ እህል ቅሜያለሁና፣ መጠጤንም ከእንባዬ ጋር ቀላቅያለሁና” (መዝ 101፡9) ብሏልና፡፡ ወደ ኃጢአት የተመለከተው ዓይኑ በዕንባ እስኪሟሟ ደረሰ፤ “ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፣ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ፤ ዓይኔ ከቍጡ ዕንባ የተነሣ ታወከች” እንዳለ፡፡ መዝ. 6፡6-7 መኳንንቱ እህል እንዲቀምስ በለመኑት ጊዜ እንኳ አልሰማቸውም፡፡ ጾሙን እስከ ሰባት ሙሉ ቀናት አራዘመ፡፡ ንጉሥ የነበረው እርሱ እንዲያ ባለ ሁኔታ ንስሐ ከገባ ተራ ግለሰብ የሆንከው አንተ ንስሐ ልትገባና ልትናዘዝ አይገባህምን?” (ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም፣ ትምህርት 2 በእንተ ንስሐ ወሥርየተ ኀጢአት፣ ቁ 12)

#መድሎተ_ጽድቅ

#ዲያቆን_ያረጋል_አበጋዝ

1 month, 2 weeks ago

“ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል።” (ሮሜ 3፥27)

በፕሮቴስታንቱ ዓለም ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ንባብ የሚተረጎመው ሕግን መፈጸም ለመጽደቅ አይጠቅምም በሚል ነው። በአብዛኛው የሚሰጠው ምክንያት ሕግ መፈጸም ስላልተቻለ ሕግን ፈጽሞ መጽደቅ አይቻልም ነው። “ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል። በየትኛው ሕግ ነው? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፥ በእምነት ሕግ ነው እንጂ።” የሚለውም በሥራ ሕግ መጽደቅ ስላልተቻለ ትምክህት ቀርቷል፤ በወንጌል የሚጸደቀው በእምነት ብቻ ነው ተብሎ ይደመደማል። (ሮሜ 3፥27)
በጣም ጽንፈኛ የሚባለው ፕሮቴስታንታዊ ትርጉም ደግሞ በጀርመናዊው ሮበርት ቡልትማን (1884-1976) የተቀነቀነው ትርጉም ነው። ይህን አስተምህሮ የሚያቀነቅነው Bultmann School እየተባለ ይጠራል። ቡልትማን እንደሚለው በመልካም ሥራ ለመጽደቅ ማሰብ ኃጢአት የሆነው የሰው ዘር ሕግን መፈጸም ስላልቻለ ብቻ አይደለም። ቢችል ራሱ እግዚአብሔር የሕግ ፈጻሚዎች ባለ እዳ እንዳይሆን በሕግ መጽደቅ አይቻልም። በአዲስ ኪዳን ብቻ ሳይሆን በብሉይ ኪዳን ጭምር ሕግን ፈጽሜ ልጽደቅ ብሎ ማሰብ በራሱ ኃጢአት ነው ይላል። ስለዚህ ሕግን መፈጸም አለመቻል ብቻ ሳይሆን ፈጽሞ ለመጽደቅ መሞከር ራሱ ኃጢአት ነው።
ይህ እይታ ብዙ ችግሮች አሉበት። አንደኛው መጽሐፍ ቅዱስን ያልተከተለ ነው። የትም ቦታ ላይ መጽሐፍ ሕግን የፈጸመ አይጸድቅም አይልም፤ በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚፈጽሙ ይጸድቃሉ ይላል እንጂ። (ሮሜ. 2፥13-16) የእግዚአብሔርን ሕግ ለመፈጸም እና በዚያ ለመጽደቅ ማሰብ ኃጢአት ነው አይልም። ሁለተኛው በመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ከእምነት ተለይቶ የተሰጠበት ጊዜ የለም። የብሉይ ኪዳን ሕግ ራሱ እግዚአብሔር ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ፍቅሩን ከገለጸላቸው በኋላ የተሰጠ የኪዳን ሕግ ነው። (ዘጸ. 20) የሕጉ መጀመሪያ በእግዚአብሔር ማመንን እና ከእርሱ በቀር ሌሎች አማልክትን አለመከተልን የሚያዝ ነው። በመሆኑም እምነትን እና ሕግን መፈጸምን ተጻራሪ (antithetical) አድርጎ መተርጎም በብሉይ ኪዳንም በጥንት ቤተ ክርስቲያንም የሌለ ተሐደሶአዊ እሳቤ ነው። ሁልጊዜም ሕግን መፈጸም ከቸርነቱ የተነሣ ላመኑት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ሆኖ እንጂ የእምነት ተቀናቃኝ ሆኖ ተሰጥቶ አያውቅምና። የእግዚአብሔር ሕግ የእምነት መታዘዝ ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር ራሱ በሰጠው ሕግ ባለ እዳ ሊሆን አይችልም፤ የሕጉ ምንጭ የእርሱ ቸርነት ያለበት ፈቃዱ ነውና።
በአዲስ ኪዳን ቅዱስ ጳውሎስ የተቃወመው በክርስቶስ ከማመን የወጣውን (ወይም እንደ ተጨማሪ ነገር የሚቆጥረውን) እና ከአሕዛብ የመጡ በክርስቶስ እምነት አንድ የሆኑ ክርስቲያኖችን 'አልተገዘራችሁም፤ ስለዚህ ከእኛ ጋር በአንድ ማእድ መቀመጥ አይገባችሁም' የሚል እሥራኤላዊ ትምክህት ያለበትን የሕግ ሥራ የሚሰብኩ አይሁድ ዘመም ክርስቲያኖችን የተመለከተ እሳቤ ነው። ይህ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ዝቅ ብሎ "ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና" ካለ በኋላ "ወይስ እግዚአብሔር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ ደግሞ አምላክ አይደለምን? አዎን፥ የተገረዘን ስለ እምነት ያልተገረዘንም በእምነት የሚያጸድቅ አምላክ አንድ ስለ ሆነ የአሕዛብ ደግሞ አምላክ ነው" በማለት ያስተምራል። ይህ ንግግሩ አጠቃላዩን ሕግን የሚቃወም እንዳይመስልበት ደግሞ "እንግዲህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? አይደለም፤ ሕግን እናጸናለን እንጂ" ብሎ ይደመድማል። (ሮሜ. 3፥27-31)

("ሕግ ከጽዮን ይወጣል" (ኢሳ. 2፥3) የተባለላትን የታቦተ ጽዮን መታሰቢያ በዓል እያደረግን ሕግን በተሳሳተ ትርጉም ለሚያጣጥሉ የበዓሉ በረከት ይደርሳቸው ዘንድ ይህ ተጻፈ።)

1 month, 2 weeks ago

ኅዳር ጽዮን
"ጽዮን" ማለት "ጸወን አምባ፣ መጠጊያ" ማለት ነው:: ጽዮን የሚለው ስም በቁሙ ለቅዱስ ዳዊት ተራራና ለኪዳኑ ጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለዘለዓለማዊት ርስት ያገለግላል፡፡

ኅዳር ፳፩ ቀን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙ ታላላቅ ተአምራት የሚታሰቡበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የታቦተ ጽዮንን ተአምራት እግዚአብሔር ቃል ቅድስት ድንግል ማርያምን ታቦቱ አድርጎ ከፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጋር በማነጻጸር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ድርሻ በስፋት ታስተምራለች፡፡

ነቢዩ ሙሴ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጸልዮና ጹሞ ዐሥርቱ ቃላት የተጻፈበትን ጽላት ከእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑን ታቦት ‹ታቦተ ጽዮንን› እንደተቀበለ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል፡፡

ታቦተ ጽዮን ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸችበት ምክንያት የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ንጽሕና ለማመልከት ነው፡፡ በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ የተለበጠች መሆኗ ደግሞ የእመቤታችን ድንግል ማርያም ቅድስናዋንና በሁለት ወገን ድንግል የመሆኗ ምሳሌ ነው፡፡

ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ጽዮን ከተማ ባስመጣበት ወቅት በታቦቷ ፊት በሙሉ ኃይሉ በደስታ እየዘለለ ለእግዚአብሔር በዝማሬ ምስጋና አቅርቧል፡፡ ‹‹ለንጉሥ ዳዊትም “እግዚአብሔር የአቢዳራ ቤት የነበረውን ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ባረከ” ብለው ነገሩት፡፡

ዳዊትም ሄዶ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ራሱ ከተማ በደስታ አመጣት፡፡ ከእርሱም ጋር የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ ሰባት መሰንቆ የሚመቱ መዘምራን ነበሩ፤ በሬዎችንና በጎችን ይሠዉ ነበር፡፡ ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት በገና ይደረድር ነበር›› እንዲል፤ ነቢዩ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት የተቀኘው ለሰው ልጆች ሁሉ የመዳናችን ምክንያት የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያመስገን ነው፡፡ (፪ሳሙ.፮፥፲፪-፲፬)

ታቦተ ጽዮን እስራኤል የዮርዳኖስን ባሕር ለመሻገር በተቸገሩ ጊዜ ነቢዩ ኢያሱ እግዚአብሔር አምላክ በነገረው መሠረት ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ይዘው በሕዝቡ ፊት ወደ ዮርዳኖስ እንዲሄዱ ነገራቸው፤ እነርሱም እንደታዘዙት አደረጉ፤ ታቦቱን የተሸከሙት የካህናቱ እግሮች በውኃው ዳር ሲጠልቁ ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፤ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ እስራኤል ሁሉ በደረቅ መሬት ተሻገሩ፡፡ (ኢያ. ፫፥፩-፲፯)

እስራኤላውያን በመካከላቸው የቃል ኪዳኑ ታቦት በያዙ ቁጥር በጦርነታቸው ሁል ጊዜ ያሸንፉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔር ሕዝበ እስራኤል ስለበደሉት እንዲሁም የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በደላቸውና ክፋታቸው ስለበዛ ታቦተ ጽዮን ተማርካ ወደ ፍልስጥኤም ሄደች፡፡ በዚያ በአሕዛብ ምድርም ልዩ ልዩ ተአምራትን እያደረገች ፍልስጥኤማውያንን ስለአስጨነቀቻቸው የፍልስጥኤማውያን አለቆች የቃልኪዳኑን ታቦት ልዩ ልዩ ገጸ በረከቶችን አስይዘው ወደመጣችበት በሠረገላ አድርገው በክብር ሸኝተዋታል፡፡ (፩ኛ.ሳሙ. ፭፥፩-፲፭)
ሀገራችን ኢትዮጵያም በንግሥተ ሳባ አማካኝነት ለታቦተ ጽዮን መቀመጫ እንድትሆን የእግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኗል፡፡ ይህም እንዲህ ነበር፤ ንግሥተ ሳባ የንጉሥ ሰሎሞንን ጥበብ ለማድነቅ ምድረ እስራኤል ድረስ መጓዟን ተከትሎ ከንጉሡ ቀዳማዊ ምኒልክን ፀነሰች፡፡

ቀዳማዊ ምኒልክ ከአደገ በኋላ አባቱን ሊጠይቅ ሂዶ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ አብረውት አንድ ሺህ ሁለት መቶ እስራኤላውያን የበኩር ልጆች፣ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት በአዛርያስ የሚመሩ ሌዋውያን ካህናትም አብረውት ለጉዞ ተነሡ፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትንና ሌሎች በርካታ ቁሳቁሶችን ይዘውም ነበር።

ነገር ግን ታቦተ ጽዮንን አዛርያስና ካህናቱ ተማክረው ቀዳማዊ ምኒልክ እንኳን ሳይሰማ በምሥጢር ይዘዋት ሊመጡ ተስማሙ፡፡ ዕቅዳቸውን ለማሳካት በታቦተ ጽዮን አምሳያ ሌላ ታቦት አዘጋጅተው ለመሄድ በሚነሡበት ዕለት ሌሊትም ወደ ቤተ መቅደስ ይዘውት ሄዱ፡፡

ከቤተ መቅደስ ሲደርሱም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበርና የቤተ መቅደሱ በር ተከፍቶ እና ውስጡም በብርሃን ተሞልቶ ታቦተ ጽዮንም ከመንበሯ በመነሣት ከፍ ብላ አገኟት። በዚህም የአምላክን ፈቃድ ተረድተውና እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በፍጥነት ይዘዋት ወጡ፡፡ በአምሳያዋ የሠሩትንም ቅርፅ በመንበሩ ላይ አስቀምጠው ሄዱ።

የንጉሡ ወታደሮች በፍጥነት ቢጓዙም ቀዳማዊ ምኒልክ እና አዛርያስ ታቦተ ጽዮንን ይዘው ሲጓዙ እጅግ ፍጣን ስለበር ሊደርሱባቸው አልቻሉም። መጽሐፈ ክብረ ነገሥት ይህንን ሲጠቅስ ‹‹ከመሬት አንድ ክንድ ያህል ከፍ ብለው ይሄዱ ነበር›› በማለት ይገልጸዋል። ባሕረ ኤርትራን ከተሻገሩና ግብፅ ከደረሱ በኋላ ዕረፍትን ባደረጉ ጊዜ አዛርያስ ለቀዳማዊ ምኒልክ ታቦተ ጽዮንን ይዘዋት እንደመጡ ነገረው፡፡

አያይዞም ‹‹አንተም ብትሻ ታቦቷንም ወደ ሀገሯ ልመልሳት ብትል አትችልም፤ አባትህ ሰሎሞንም ሊወስዳት ቢመጣ አይሆንለትም›› አለው። ከቦታ ቦታ ይዣት እንቀሳቀሳለው ቢልም ያለ ፈቃዷ ምንም እንደማያደርግና ሁሉ ነገር በአምላክ መልካም ፈቃድ እንደሚፈጸም ነገረው። ቀዳማዊው ምኒልክም ይህን ሲሰማ ተደሰተ፤ ሕዝቡና ሠራዊቱ በሙሉ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ከግብፅ ምድር ወጥተው እስከ ኢትዮጵያ በታላቅ እልልታና ሆታ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ።

ኅዳር ፳፩ ቀን አክሱም በደረሱ ጊዜም እናቱ ንግሥተ ሳባ ተቀበለችው፤ ደስታና እልልታውን ተመልክታ ያገኙት ነገር እንዳለ ብትጠይቀው ታቦተ ጽዮንን እንዳመጧት ነገራት፡፡ የእርሷም ደስታ እጥፍ ድርብ ሆነ። ታቦቷንም በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስቀመጡአት፡፡

ከዚያም ዘመን ጀምሮ በየዓመቱ ኅዳር ፳፩ ቀን ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙ ታላላቅ ተአምራትን በማሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታከብራለች፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
ምንጭ፤
ክብረ ነገሥት ተርጓሚ ሥርግው ገላው (1994 ዓ.ም)
መዝገበ ታሪክ ቊጥር 1 (መምህር ኅሩይ ኤርምያስ)

1 month, 2 weeks ago

የዕለቱ ወንጌል
የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ፡23

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነገራቸው፦
ጻፊዎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል።
ስለዚህ ያዘዟችኹን ዅሉ አድርጉ፥ጠብቁትም፤ነገር፡ግን፥እየተናገሩ አያደርጉትምና፥እንደ ሥራቸው
አታድርጉ።
ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።
ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ዅሉ ያደርጋሉ፤ስለዚህ፥ዐሸን ክታባቸውን ያሰፋሉ፥ዘርፉንም ያስረዝማሉ፥
በምሳም የከበሬታ ስፍራ፥በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥
በገበያም ሰላምታና፦መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ።
እናንተ ግን፦መምህር ተብላችኹ አትጠሩ፤መምህራችኹ አንድ ስለ ኾነ እናንተም ዅላችኹ ወንድማማች ናችኹ።
አባታችኹ አንዱ ርሱም የሰማዩ ነውና፥በምድር ላይ ማንንም፦አባት ብላችኹ አትጥሩ።
ሊቃችኹ አንድ ርሱም ክርስቶስ ነውና፦ሊቃውንት ተብላችኹ አትጠሩ።
ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችኹ ይኾናል።
ራሱን ከፍ የሚያደርግ ዅሉ ይዋረዳል፥ራሱንም የሚያዋርድ ዅሉ ከፍ ይላል።
እናንተ ግብዞች ጻፊዎችና ፈሪሳውያን፥መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ወዮላችኹ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችኹ።
እናንተ ግብዞች ጻፊዎችና ፈሪሳውያን፥በጸሎት ርዝመት እያመካኛችኹ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ወዮላችኹ፤ስለዚህ፥የባሰ ፍርድ ትቀበላላችኹ።
እናንተ ግብዞች ጻፊዎችና ፈሪሳውያን፥አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥በኾነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ኹለት ዕጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ወዮላችኹ።
እናንተ፦ማንም በቤተ መቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል የምትሉ፥ዕውሮች መሪዎች፥ወዮላችኹ።
እናንተ ደንቈሮዎችና ዕውሮች፥ማናቸው ይበልጣል ወርቁ ነውን፧ወይስ ወርቁንየቀደሰው ቤተ መቅደስ፧ደግማችኹም፦ማንም በመሠዊያው የሚምል ምንም የለበትም፤ማንም በላዩ ባለው መባ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል ትላላችኹ።
እናንተ,ደንቈሮዎችና ዕውሮች፥ማናቸው ይበልጣል መባው,ነውን ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው፧እንግዲህ በመሠዊያው የሚምለው,በርሱና በርሱላይ ባለው ዅሉ ይምላል፤ በቤተ መቅደስም የሚምለው በርሱና በርሱ በሚኖረው ይምላል፤
በሰማይም የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በርሱ ላይ በተቀመጠው ይምላል።እናንተ ግብዞች ጻፊዎችና ፈሪሳውያን፥ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም ዓሥራት ስለምታወጡ፥ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥በሕግ ያለውን ዋና ነገር፡
ስለምትተዉ፥ወዮላችኹ፤ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገ፟ባ፟ችኹ ነበር።እናንተ፡ዕውሮች፡መሪዎች፥ትንኝን፡የምታጠሩ፡ግመልንም፡የምትውጡ።እናንተ ግብዞች ጻፊዎችና ፈሪሳውያን፥በውስጡ ቅሚያና ሥሥት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ ወዮላችኹ።
አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲኾን አስቀድመኽ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ።
እናንተ ግብዞች ጻፊዎችና ፈሪሳውያን፥በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን ዐጥንት ርኵሰትም ዅሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን
ስለምትመስሉ፥ወዮላችኹ።
እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችኹ፥በውስጣችኹ ግን ግብዝነትና ዐመፀኝነት ሞልቶባችዃል።
እናንተ ግብዞች ጻፊዎችና ፈሪሳውያን፥የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና፦
በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በኾነስ፥በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ወዮላችኹ።
እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደኾናችኹ በራሳችኹ ላይ ትመሰክራላችኹ።
እናንተ ደግሞ የአባቶቻችኹን መስፈሪያ ሙሉ።
እናንተ እባቦች፥የእፍኝት ልጆች፥ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችኹ፧
ስለዚህ፥እንሆ፥ነቢያትንና ጥበበኛዎችን ጻፊዎችንም ወደ እናንተ እልካለኹ፤ከነርሱም ትገድላላችኹ ትሰቅሉማላችኹ፥ከነርሱም በምኵራባችኹ ትገርፋላችኹ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችኹ፤ ከጻድቁ ከአቤል ደም ዠምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከገደላችኹት እስከበራክዩ ልጅ እስከዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ዅሉ ይደርስባችኹ ዘንድ።
እውነት እላችዃለኹ፥ይህ ዅሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።
ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ነቢያትን የምትገድል ወደ ርሷ የተላኩትንም የምትወግር፥ዶሮ ጫጩቶቿን ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድኹ!አልወደዳችኹምም።
እንሆ፥ቤታችኹ የተፈታ ኾኖ ይቀርላችዃል።
እላችዃለኹና፥በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።

1 month, 3 weeks ago

ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)

#ጾመ_ነቢያት በየዓመቱ ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እስከ በዓለ ልደት ዋዜማ ድረስ የሚጾም፤ ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንደኛው ጾም ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ለማዳን ሲል የሰውን ሥጋ ስለ መልበሱ፤ ወደ ግብጽ ስለ መሰደዱ፤ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለ መጠመቁ፤ በትምህርቱ ብርሃንነት ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፤ ለሰው ልጆች ድኅነት ልዩ ልዩ መከራን ስለ መቀበሉ፤ ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱና ዳግም ምጽአቱ በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ትንቢት ተናግረዋል፤ ትንቢቱ ደርሶ፣ ተፈጽሞ ለመመልከትም ‹‹አንሥእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሣ፤ እጅህን ላክ›› እያሉ በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው የሚኾንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት እያሰሉ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡

ይህ ጾም የእግዚአብሔርን ሰው መኾን ሲጠባበቁ የኖሩት የነቢያት ትንቢትና ጸሎት በጌታችን መወለድ ፍጻሜ ያገኘበት ወቅት በመኾኑ ‹‹#ጾመ_ነቢያት (#የነቢያት_ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ለአዳም የተነገረው የድኅት ተስፋ ስለ ተፈጸመበትም ‹‹#ጾመ_አዳም (#የአዳም_ጾም)›› ይባላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ሰው መኾን በስፋት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበት ወቅት በመኾኑም ‹‹#ጾመ_ስብከት (#የስብከት_ጾም)››፤ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመኾኑ ደግሞ ‹‹#ጾመ_ልደት (#የልደት_ጾም)›› በመባል ይታወቃል፡፡ እንደዚሁም ‹‹ጾመ ሐዋርያት›› ይባላል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹በዓለ ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብረዋለን፤ በዓለ ልደትንስ ምን አድርገን እናከብረዋለን?›› በማለት ነቢያት የጾሙትን ከልደተ ክርሰቶስ በፊት ያለውን ጾም ጾመዋልና፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ይህ ጾም ‹‹#ጾመ_ፊልጶስ (#የፊልጶስ_ጾም)›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በአፍራቅያና አውራጃዋ ዅሉ እየተዘዋወረ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወንጌልን በማስተማር፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙዎችን ወደ አሚነ እግዚአብሔር ሲመልስ ቆይቶ ትምህርቱን በማይቀበሉ የአፍራቅያ ሰዎች አማካይነት በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሊቀብሩ ሲሉም ስለ ተሰወረባቸው የሐዋርያውን ሥጋ ይመልስላቸው ዘንድ ሱባዔ ይዘው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በለመኑት ጊዜ እግዚአብሔር ልመናቸውን ተቀብሎ በ፫ኛው ቀን መልሶላቸው ሥጋውን (አስከሬኑን) በክብር አሳርፈውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የሐዋርያውን ሥጋ ካገኙ በኋላ እስከ ጌታችን ልደት ድረስ ጾመዋል፡፡ ስለዚህም ጾመ ነቢያት ‹‹ጾመ ፊልጶስ›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ወልደ አምላክ ክርስቶስን በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደምትፀንሰው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ካበሠራት በኋላ እመቤታችን ‹‹ሰማይና ምድር የማይወስኑትን አምላክ ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ?›› በማለት ጌታችንን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማዋለችና ይህ ጾም ‹‹#ጾመ_ማርያም›› በመባልም ይታወቃል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ በገና ጾም ነቢያትም ሐዋርያትም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም እንደ እነርሱ በረከትን እናገኝ ዘንድ ይህንን ጾም መጾም እንደሚገባን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሥርዐት ሠርተውልናል፡፡ በዚህም መሠረት የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን፤ መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ዅላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል፡፡

ምንጭ፡-

ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፣ አንቀጽ ፲፭፡፡

ጾምና ምጽዋት፣ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ፤ ገጽ ፵፯ -፶፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

#ማኅበረ_ቅዱሳን

1 month, 3 weeks ago

ጾም ሙሽሪትን ትመስላለች፤ ሙሽሪትን በሠርግ አዳራሽ ኾነው የሚቀበሏት ሰዎች ቤቱን ያስጌጡታል፤ ይሸልሙታል፡፡ ወደ ሠርጉ አዳራሽ የሚገባውን ሰው የሠርግ ልብስ ለብሶ እንደኾነ፣ የቆሸሸ እንዳልኾነ አይተው ያስገቡታል፡፡ እኛም እንዲኽ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ልቡናችንን በማንጻት፣ ልል ዘሊል ከመኾን በመራቅ፣ የክፋት እርሾን በማስወገድ፣ ከጾም ጋር አብረው የሚመጡትን የሚያጅቧትን መልካም ምግባራትንም ለመቀበል የልቡናችንን ውሳጤ በመክፈት የምግባር እናት፣ የማስተዋል እንዲኹሉም ለሌሎች ምግባራት ኹሉ ንግሥት የምትኾን ጾምን ልንቀበላት ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ ታላቅ ሐሴት እናደርጋለን፤ ርሷም ቁስለ ነፍሳችንን ትፈውስልናለች፡፡

በሌላ አገላለጽ ብነግራችኹ ሐኪሞች በአንድ ታማሚ ሰውነት ውስጥ ያለውን ቆሻሻ፣ መርዘኛ ፈሳሽን ማስገድ ሲፈልጉ መጀመሪያ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ታማሚው ምግብ ከመውሰድ እንዲቈጠብ ነው፡፡ ታማሚው ለጊዜው ምግብን ከመብላት ካልተከለከለ ሓኪሞቹ የሚሰጡት መድኃኒት እንደተፈለገው ውጤት አይሰጥም፡፡

እኛም ቁስለ ነፍስ ቁስለ ሥጋ የምትፈውሰውን ጾም ስንቀበላት ከዚኽ በላይ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን የምንሻ ከኾነ ልቡናችንን ንጹሕና ንቁ በማድረግ ልንወስዳት ይገባናል፡፡ እንዲኽ ካልኾነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

1 month, 3 weeks ago
  1. ጾም በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት

  2. የጾም አስፈላጊነትና ጠቀሜታ

  3. ጾም የታወቀ ጊዜ ያለው መሆኑ

  4. በጾም ወቅት የማይበሉ ምግቦች ስለ መኖራቸው

  5. ጾም በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ ያለው ስለ መሆኑ

  6. ጾም በቅዱሳን አባቶች ትምህርት

በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ

2 months ago

ደብረ ቁስቋም

ኅዳር ፮ ቀን የአርያም ንግሥት፣ የፍጥረታት ሁሉ እመቤት፣ የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ አረጋዊ ቅዱስ ዮሴፍንና ቅድስት ሰሎሜን አስከትላ ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት የስደት እና የመከራ ዓመታት በኋላ በስተደቡብ የምትገኘው ደብረ ቁስቋም ላይ ያረፉችበት ዕለት ይከበራል፡፡

ደብረ ቁስቋም በደቡብ ግብጽ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ይህ ተራራ የተቀደሰ ተራራ ስለመሆኑ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ታኦፊሎጎስ በድርሳነ ማርያም ‹‹ይህም ከሀገሮቹ ሁሉ ተራሮች የሚበልጥ (የተለየ) ከፍ ያለ ተራራ ነው፡፡ በውስጡ ቅዱስ አግዚአብሔር ያድራል፡፡ ይህንን ተራራ የእግዚአብሔር ልጅ ወዶታል፤ አክብሮታልምና፤ ከዓለም ሀገሮች ሁሉ ከተቀደሰች እናቱ ጋር አድሮባታልና፡፡ ከመላእክት ቤት ያድር ዘንድ አልወደደም፤ ቢታንያንም አልመረጠም፡፡ ከተራራው ላይ ባለች ገዳም ቤት ውስጥ አደረ እንጂ፤ ነቢዩ ዳዊት የጽዮንን ተራራ ወደደ፤ በአርያምም መቅደሱን ሠራ እንዳለ፡፡››

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈ ሄሮድስ ክርስቶስን ለመግደል በፈለገ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለአረጋዊው ዮሴፍ በሕልሙ ‹‹ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ›› ባለው መሠረት የተፈጸመ ነው፡፡ (ማቴ. ፪፥፲፫-፲፭)

በስደቱም ጣዖታተ ግብጽ እየተሰባበሩ ሲወድቁ፤ በእነርሱም አድረው ሰውን ሲያስቱ የነበሩ አጋንንትም ሲሸሹ ታይተዋል፤ ደግሞም ጌታችን ዳግማዊ አዳም ነውና በምክረ ከይሲ (ዲያብሎስ) ምክንያት ተሰዶ የነበረው ቀዳማዊ አዳምን ለመካስ ተሰደደ፤ በዚህም አጋንንትን ከሰው ልቡና አውጥቶ አሳደደ፡፡

እመቤታችን ቅድስት ማርያም ከጌታችን ኢየሱስ ጋር ከመሰደዷ አስቀድሞ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ወይወርድ እግዚእነ ውስተ ምድረ ግብጽ እንዘ ይጼዐን ዲበ ደመና ቀሊል፤ ጌታችን በፈጣን ደመና (በእመቤታችን ጀርባ) ተጭኖ ወደ ግብጽ ይወርዳል›› ተብሎም በተናገረው መሠረት ትንቢቱ ተፈጽሟል፡፡ (ኢሳ. ፲፱፥፩)

ጌታችን ኢየሱስ በደብረ ቁስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቱን ሰበሰባቸው፤ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንንም አክብሮ የቁርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ሰጥቷቸዋል፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከጌታችን ኢየሱስ ጋር በቁስቋም ተራራ ስድስት ወራትን ያረፈች ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር ፮ የእነርሱን ስደትና ወደ ሀገራቸው እስራኤል መመለሳቸውን በማስታወስ ታከብራለች፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!!!

ምንጭ፤ ድርሳነ ማርያም (ትርጉም ፳፻፫ ዓ.ም)
ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር

We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated hace 3 semanas, 5 días

Last updated hace 3 semanas

ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot

🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹

Last updated hace 1 mes, 1 semana