ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።
@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna
#ኢትዮጵያ
Last updated 2 months, 1 week ago
Last updated 6 days, 22 hours ago
ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ ? @Esat_tv_comment_bot
??ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ??
Last updated 2 months, 3 weeks ago
[የራማው ልዑል
ራማው ልዑል ገብርኤል /2/
ተመላለስ መሀላችን
ስምህን ጠርተን ነዓ ስንልህ/2/
ብርሃን ለባሽ እሳታዊው መልአክ
አንተ አማልደን ከመሐሪው አምላክ /2/
የምሥራች ነጋሪ ድንቅን ልደት አብሣሪ
የጽድቅ ፋና የድህነት ጎዳና /2/
ላመኑብህ ለተማጸኑብህ
ተጥኖ ደራሽ አለኝታቸው ነህ/2/
የአናንያ የአዛርያ የሚሳኤል ከለላቸው
ከእሳት ነበልባል ያዳንካቸው/2/
ምሰሶ ዐምዳችን መጠጊያችን
ቅዱስ ገብርኤል ከለላችን/2/
ዕለት ዕለት የምንማልድህ
ልጆችህን ይምራን መንፈስህ /2/](https://t.me/Yemezmur_Gitimoche)
┈┈┈┈••●◉❖◉●••┈┈┈
@yemezmurgetemoche
┈┈┈┈••●◉❖◉●••┈┈┈
በአንደኛውም ቀን አቡነ ሀብተ ማርያም ከሌሎች ቅዱሳን ጋር ሆነው ሲሄዱ ብዙ አጋንንት እየተደነባበሩ ወደ ታች ሲወርዱ ተመለከቱና አባታችን ሥራቸውን ለማየት ተከተሏቸው፡፡ አንዱንም ኃጥእ ይዘው ነፍሱን ከሥጋው ለዩዋትና ወደ ሲኦል አወረዷት፡፡ አባታችንም ከሌሎቹ ቅዱሳን ጋር ሆነው ያችን ነፍስ ይምርላቸው ዘንድ ጌታችንን በጸሎት ማለዱት፡፡ ነገር ግን ‹‹ለጣዖት ስትሰግድ ስለኖረች ይህችን ነፍስ አልምራትምና አትድከሙ›› የሚል ቃል ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ መጣላቸው፡፡ ቅዱሳኑም ‹‹ልመናችንን የማትቀበል ከሆነ በከንቱ ሰብስበኸናል›› ብለው ቢያዝኑ እግዚአብሔርም ‹‹ሕገ እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎችን ቅጣት እንድታዩ ነው›› አላቸው፡፡ እነርሱም ሕገ እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎችን ሲቀጣቸው ለደጋጎቹ ሰዎች ደግሞ መልካሙን ዋጋቸውን ሲሰጣቸው አይተው አንድ ሆነው አመስግነውታል፡፡
ከዚህም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ራጉኤል አንዱን ሰው በመብረቅ ቀሰፈውና ቅዱስ ሚካኤል ሄዶ ቅዱስ ራጉኤልን ሲከራከረው አባታችን ተመለከቱ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹የእኔ አገልጋይ ነውና ለምን ገደልከው?›› ሲለው ቅዱስ ራጉኤልም ‹‹ሰንበት ሳይለይ ዝሙትን መሥራት የለመደ ሥራውም ዝሙት ስለሆነ በፈጣሪዬ ታዝዤ ነው የገደልኩት፡፡ ኃጥአንን ሊያጠፋ እንጂ ጻድቃንን ለመቅጣት መብረቅ እንዳይታዘዝ አንተስ ታውቅ የለም እንዴ?›› አለው፡፡ ይህንንም ተባብለው ከሥላሴ ፊት ሰግደው ቅዱስ ሚካኤል የተገባለትን ቃልኪዳን በማሳሰብ ምልጃውን አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም በጎና ክፉ ሥራዋን ባስመዘነ ጊዜ በጎ ሥራዋ ስለበለጠ ቅዱስ ሚካኤል ያችን ነፍስ ታቅፎ ወስዶ ለቅዱስ ገብርኤል ሰጠው፡፡ ሰባቱም ሊቃነ መላእክት እየተቀባበሉ ወስደው ከመስቀል ዘንድ አደረሷት፡፡ ለቅዱስ መስቀልም ካሰገዷት በኋላ አሳልመዋት በቅዱስ ሚኤካል አማላጅነት ወደ ገነት አስገቧት፡፡ አቡነ ሀብተ ማርያምም ይህን በተመለከቱ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤልን ‹‹መስቀል ታሳልሟት ዘንድ ያችን ነፍስ ወደ መስቀል ለምን ወሰዳችኋት?›› ብለው ጠየቁት፡፡ መልአኩም ‹‹በትልቅም በትንሽም ነገር ክርስቲያናዊትን ነፍስ የሚቃወም ቢመጣባት ድል የምትነሳበትን በመስቀል ፍርድ ይታይላታልና ስለዚህ ነው፡፡ የሚከራከራት ቢኖር ግን እንዳየኸው ወደ መስቀል ባደረሷት ጊዜ የሚቃወማት ሰይጣን ፈጥኖ ይርቅላታል ዳግመኛም ሊከራከራት አይችልም›› አላቸው፡፡
ከአቡነ ሀብተማርያም በረከት ለመቀበል ብዙ ቅዱሳን ከሮም፣ ከግብፅ፣ ከአስቄጥስና ከሲሐት ገዳም ወደ አባታችን ዘንድ ይመጡ ነበር፤ ከየሀገራቸውም በአንበሳ ተቀምጠው የሚመጡ አሉ፤ ክንፍ ተሰጥቷቸው እንደ ንስር የሚበሩም አሉ፤ ብፁዕ አቡነ ሀብተ ማርያምም የቅዱሳኑን ብቃት አይተው ‹‹ሥራችሁ እንዲህ እንዲህ ሲሆን ለምን ወደኔ መጣችሁ?›› ብለው ሲጠይቋቸው ቅዱሳኑም ‹‹በማንኛውም ሥራ እግዚአብሔርን በለመነው ጊዜ በኢትዮጵያ የሚኖር እንደ ሙሴ ያለ ሀብተ ማርያም የሚባል ወዳጄ አለና ሁሉን ስለሚነግራችሁ ዘወትር እርሱን ጠይቁ ብሎ ስላዘዘን ወደ አንተ መጣን›› አሏቸው፡፡ አባታችንም ቅዱሳኑን ከባረኳቸውና ከእነርሱም ከተባረኩ በኋላ አባታችን ለቅዱሳኑ የሚመጣውን እንዳለፈ የሚደረገውንም እንደተደረገ አድርገው ይነግሯቸዋል፡፡ ቅዱሳኑም ከልጅነታቸው ጀምረው እስከዚያች ቀን ድረስ የሠሩትን ሥራ ሁሉ ይነግሯቸዋል፡፡ እነርሱም እጃቸውን እየሳሙ በረከታቸውን ይቀበሉ ነበር፡፡ እንደዚሁም አቡነ ሀብተ ማርያም ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል እየተራዱዋቸው ቀድሰው በሚያቆርቡ ጊዜ ተሰውረው የሚኖሩ 500 ስውራን ቅዱሳን መጥተው ሥጋ ወደሙን ከአባታችን እጅ ተቀበሉ፡፡ ቀድሰውም ወደበዓታቸው እንደገቡ እመቤታችን ተገልጣላቸው ‹‹በነገውም ዕለት ቅዳሴዬን ቀድስ፣ ይህም ቅዳሴ መዓዛ ቅዳሴ ነውና፡፡ የዓለም መሠረት ማርያም ወደኔ ነይ ብለህ በጠራኸኝ ጊዜ ነቢያትን ሐዋርያትን አስከትዬ መጥቼ እባርክሃለሁ›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም ‹‹በነገው ዕለት ሌላ ተረኛ ቄስ ይቀድሳልና ይህ እንዴት ይሆንልኛል?›› አሏት፡፡ እመቤታችንም ‹‹ፈቃዴ ስለሆነ አንተ እንድትቀድስ አደርጋለሁ›› አለቻቸው፡፡ በነጋታው ተረኛው ቄስ ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ ቸኩሎ እየተፋጠነ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገሰግስ ወድቆ ጥርሱ ደማና ስለ ሥጋ ወደሙ ቅዳሴ እጅግ ደንግጦ ወደ አባታችን መጥቶ ‹‹ቅዳሴው በእኔ ስም ከሚታጎል አንተ ቀድስልኝ›› አላቸው፡፡ አባታችንም አስቀድማ እመቤታችን የነገረቻቸውን ነገር አስበው እያደነቁ ሄደው ቀደሱ፡፡ እመቤታችንም ነቢያትን ሐዋርያትን አስከትላ መጥታ ባረከቻቸው፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።
አባታችንም ከጌታችን ይህን ቃል ኪዳን ከተቀበሉ በኋላ ነፍሳቸውን ‹‹ነፍሴ ሆይ ከፈጣሪሽ ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት አፍ ለአፍ ትነጋገሪ ዘንድ ደፍረሻልና በጎም ሥራ ሳይኖርሽ ከፈጣሪሽ ቃልኪዳን ተቀብለሻልና ከዛሬ ጀምሮ እንደ መላእክት ዘወትር አትተኝ›› እያሉ ተጋድሏቸውን አብዝተው ቀጠሉ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም አባታችንን እንደ ጓደኛ ሆኖ ዘወትር ይጎበኛቸው ነበር፡፡ ቅዱሳን አባታቸንን ሊጎበኟቸው መጥተው ከደጅ ቆመው እንደሆነ ቅዱስ ሚካኤል አባታችንን ‹‹እከሌ ጉዳዩ እንዲህ ነው እንዲህ ብለህ ተናገረው…›› እያለ ያማክራቸው ነበር፡፡ እሳቸውም ቅዱስ ሚካኤል ካዘዛቸው በቀር ምንም አይሠሩም ነበር፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትንም ባነበቡ ጊዜ ኃይለ ቃሉን እየተረጎመ ምሥጢራትን ይነግራቸዋል፤ የተሰወረውንም ይገልጥላቸዋል፡፡ ከእንስሳት ጩኸት ጀምሮ ከዱር አራዊት ድምፅና እስከ አእዋፍ ቋንቋ ያለውን ያስረዳቸው ነበር፡፡
ይኸውም መልአክ አንድ ቀን አቡነ ሀብተ ማርያምን ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገብቷቸው ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ተዘጋጅተው ሳለ ወንጌል የሚነበብበት ሰዓት ሲደርስ ያልተማረ ቄስ የክርስቶስ ጌትነቱን የምትናገር ወንጌልን ሲያነብ ‹‹ወዮሴፍ ብእሲሃ ለማርያም ጻድቅ ውእቱ›› የሚል ከቄሱ አፍ ይህን ንባብ አባታችን ሲሰሙ እጅግ ደንግጠው ወንጌል ወደሚነበብበት ስፍራ ሄደው የሚያነበውን ቄስ ገሠጹት፡፡ ‹‹ወዮሴፍሰ ፈሃሪሃ ለማርያም ጻድቅ ውእቱ በል እንጂ ብእሲሃ አትበል›› ብለው መከሩት፡፡ ቄሱም አቡነ ሀብተ ማርያም እንዳዘዙት ከስህተቱ ወደ ቀና ንባቡ ተመለሰ፡፡ ይህን ጊዜ ጌታችን ለአባታችን ድጋሚ ተገልጦላቸው ‹‹ሀብተ ማርያም ሆይ ይህን ትምህርትህን ወድጄ አመሰገንኩህ፣ የእናቴን የድንግል ማርያምን የድንግልናዋን ንጽሕና ስለ አከበርክ እኔም በመንግስተ ሰማያት ፈጽሜ አከብርሃለሁ›› አላቸው፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ‹‹አሁንም ዮሴፍ ብእሲሃ ለማርያም የሚሉትን ሁሉ ለያቸው እንጂ አትተዋቸው፤ እንዲህ የሚል ጽሑፍም ብታገኝ እንዳይኖር እርሱን ፍቀህ ፈሃሪሃ ለማርያም የሚለውን ጻፍ›› ብሎ አባታችንን ካዘዛቸው በኋላ ሰላምታ ሰጥቷቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ አባታችንም በዚህ ጊዜ ፊታቸው ላይ ብርሃን ስለተሳለባቸውና እንደ ፀሐይ ስላበራ ሰዎችም አይተው ባደነቁ ጊዜ ወደ በዓታቸው ገቡና ጌታችንን ‹‹አቤቱ ጌታዬ ሆይ በሰው ፊት ክብሬን አትግለጥብኝ ሰውርልኝ፣ በቸርነትህም አድነኝ›› ብለው ጸለዩ፡፡ እንዲህም ብለው በጸለዩ ጊዜ ፊታቸው መልኩ ተለውጦ እንደ ቀድሞው ሆነ፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አባታችን ታመው ተኝተው ሳለ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ መጥተው ሥጋ ወደሙን አቀብለዋቸዋል፡፡፡ አባታችን በጸሎት ላይ ሳሉ ቅዱስ ሚካኤል ነጥቆ ወደ ሰማይ ወስዶ ቅዱሳን የሚኖሩባቸውን ዓለማት፣ መንግስተ ሰማያትን እንዲሁም ኃጥአን የሚኖሩበትን ሲኦልን አሳያቸው፡፡ በገነት ያሉትንም ከአዳም ጀምሮ እሳቸው እስካሉበት ጊዜ እስከ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ድረስ ያሉትን ቅዱሳን አሳያቸው፡፡ ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው ሳለ ሰይጣንም መጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ቆመና ‹‹አቤቱ ጌታዬ ሆይ በሀብተ ማርያም ላይ እንደ ኢዮብ ብዙ መከራ አጸናበት ዘንድ ፍቀድልኝ›› ብሎ እየጮኾ ሲናገር አባታችን እጅግ ፈርተው አለቀሱ፡፡ እግዚአብሔር ግን በሰይጣን ላይ ተቆጥቶ ‹‹በነፍሱም በሥጋውም መከራ ታጸናበት ዘንድ አልፈቅድም›› አለው፡፡ ‹‹እኔ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መርጨዋለሁና በንጽሕናና በቅድስና ኃጢአት እንዳይሠራ ዘወትር እጠብቀዋለሁ፤ በእርሱ ላይ ማሰልጠንስ ይቅርና በሀብተ ማርያም ጸሎት በተማጸነኝ ሁሉ ላይ እንኳን አላሠለጥንህም›› አለው፡፡ ሰይጣንም ይህን ቃል ሰምቶ አፍሮ እያዘነ ሄደ፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ከእርሳቸው በኋላ በመንበራቸው ከተሾሙት ከስምንቱ መምህራን ጋር ለሀብተማርያም ተገለጡላቸው፡፡ እነርሱም ኤልሳዕ፣ ፊሊጶስ፣ ሕዝቅያስ፣ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ዮሐንስ ከማ፣ እንድርያስና መርሐ ክርስቶስ ናቸው፡፡ እነዚህም መልካቸው እንደ ፀሐይ ያበራ ልብሳቸው እንደ መብረቅ ያንጸባርቅ ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ልብሳቸው የእሳት ላንቃ የከበበው መልኩም ነጭ የሆነ የሚያስደንቅ ሆኖ ‹‹በቅድምና ለነበረ ለአብ በቅድምና ለነበረ ለወልድ በቅድምና ለነበረ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል›› እያለ ልብሳቸው በሰው አንደበት ያመሰግን ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም አቡነ ሀብተ ማርያምን ‹‹ልጄ ሀብተ ማርያም ሆይ! ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ስለወደደህ ብዙ ምርኮ እንዳገኘህ በአንተ ፈጽሞ ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን የምለምንህ ነገር አለና እሺ በለኝ›› አሏቸው፡፡
አቡነ ሀብተ ማርያምም ‹‹ጌታዬ ነገሩ ምንድን ነው?›› ሲሏቸው አቡነ ተክለሃይማኖት ‹‹ከተቀበርኩበት ቦታ እንድትቀበር ቃል ኪዳን ግባልኝ›› አሏቸው፡፡ አቡነ ሀብተማርያምም ‹‹አባቴ ሆይ ይህንን አደርግ ዘንድ ስለምን ትወዳለህ?›› አሏቸው፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖትም በሀገሬ ላይ የታዘዙ አምስት መቅሰፍቶች አሉና ስለዚህ ነው እነዚህም አንዱ መብረቅ ነው፤ ሁለተኛውም ቸነፈር ነው፤ ሦስተኛውም ረሃብ ነው፤ አራተኛውም ወረርሽኝ ነው፤ አምስተኛውም የእሳት ቃጠሎ ነው፡፡ የአንተ አጽም በውስጡ የተቀበረ እንደሆነ አጥንቴ የተቀበረባት ሀገሬ ከነዚህ መቅሰፍታት ትድናለች›› አሏቸው፡፡
አቡነ ሀብተ ማርያምም ‹‹ንዑድ ክቡድ የምትሆን አባቴ ሆይ ልዩ ክቡር በሚሆን በአንተ አጽም መቀበር ያልዳነች በእኔ አጽም መቀበር ድኅነት ታገኛለችን? ይህንስ ተወው›› ብለው በተከራከሯቸው ጊዜ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም መልሰው ‹‹ልጄ ሀብተ ማርያም ሆይ አንተ የማታውቀው ከፈጣሪያችን ከእግዚአብሔር የተሰጠህ እኔ የማውቀው ክብር አለህና ስለዚህ ነው፡፡ ይልቁንስ እንዳልኩህ በተቀበርኩበት ቦታ እንድትቀበርልኝ ቃልኪዳን ግባልኝ›› ብለው ማለዷቸው፡፡ ይህንንም ሲባባሉ እንዲህ የሚል ቃል መጣላቸው፡- ‹‹ከወዳጄ ከሀብተ ማርያም አንደበት ይህ ቃልኪዳን አይወጣም፣ ዳግመኛም ወዳጄ ተክለ ሃይማኖት ሆይ! እርሱ በወደደው የሚቀበር አይደለምና እኔ ከተቀበርኩበት እንድትቀበር ብለህ የምታስገድደው ለምንድን ነው? እኔ በወደድሁት ቦታ ይቀበራል እንጂ›› የሚል ቃል ተነገረ፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖትም እየለመኑናና እየሰገዱ ከሥላሴ ዙፋን ፊት ተንበረከኩ፡፡ ሦስተኛውም ‹‹ይሁን እንዳልከው ይቀበርልህ›› የሚል ቃል ተሰማ፡፡ ዳግመኛም ‹‹በአንተም አጽም በሀብተ ማርያምም አጽም ቦታህ ከመቅሰፍታት ትዳንልህ፤ ልጆችህ ግን በቸነፈር ደዌ ቢሞቱ ከሰማዕትነት ተቆጥሮላቸው ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዲገቡ በራሴ ምዬ ቃልኪዳን ገብቼልሃለሁ›› አላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አቡነ ተክለሃይማኖት እጅግ ደስ ተሰኝተው ሦስት ጊዜ ሰገዱ፡፡
ከዚህም በኋላ መልአኩ ለአቡነ ሀብተ ማርያም ክብሯ እንደ ጽርሐ አርያም የሆነች አገርን አሳያቸው፡፡ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውም ቅዱሳን መላእክት በውስጧ ተድላ ደስታ ያደርጉባት ነበር፡፡ አባታችንም መልአኩን ‹‹ይህች ክብሯ ፍጹም የሆነችን አገር ማን ትባላለች በውስጧ ለመኖር በእጅጉ ወድጃለሁና›› ብለው ሲጠይቁት መልአኩም ‹‹ይህችማ አገር የአባትህ የተክለ ሃይማኖት አጽም ያረፈባት ደብረ ሊባኖስ ናት፤ ከእርሱም ጋር በክብር እስክትነሣ ድረስ በውስጧ ትቀበርባት ዘንድ ለአንተም ተሰጥታሃለችና ደስ ይበልህ፡፡ አባትህም እንደ ኢየሩሳሌም እንደትሆንለት ቃልኪዳን ተቀብሎባታል›› አላቸው፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ዕለት አባታቸን በጎችን ሲጠብቁ ሌሎች እረኞች በአመጻ ከሰው ሰርቀው ቆርጠው ያመጡትን እሸት ‹‹ና እንብላ›› አሏቸው፡፡ አባታችን ግን ‹‹ከየት እንዳመጣቸሁት ምንም ስለማላውቅ አልበላም›› አሏቸው፡፡ እረኞቹም ሀብተ ማርምን በቁጣ ዐይን እያዩአቸው ተቀምጠው ሲበሉ አባታችን ‹‹የማንችለው ዝናብ መጥቷልና ተነሡ በፍጥነት ወደቤታችን እንሂድ›› አሏቸው፡፡ እረኞቹም ‹‹ሰማዩ ብራ ነው ምንም ደመና የለውም፤ ነፋስም አይነፍስም፡፡ እኛ የማናየው አንተ ብቻ የምታየው ምን ነገር አለ?›› እያሉ በአባታችን ላይ ተዘባበቱባቸው፡፡ አባታችን ግን በጎቻቸውን እያስሮጡ በፍጥነት ወደ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ወዲያውም በጣም ኃይለኛ ዝናብ ዘነበ፡፡ የጥፋት ውኃው በላያቸው እስኪፈጸምባቸው ድረስ እነዚያን እረኞች ከቦታቸው አልተነቃነቁም ነበርና በጥፋቱ ውኃ አለቁ፡፡ በዚያችም ሌሊት አቡነ ሀብተ ማርያን ከሰማይ ሦስት ጊዜ ‹‹ሀብተ ማርያም ሀብተ ማርያም›› የሚል ድምፅ ጠራቸው፡፡ አባታችንም እንደ ሳሙኤል ‹‹ጌታዬ ባሪያህ ይሰማሃል ተናገር›› ሲሉ ጌታችን አናገራቸው፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ ለሚሰሙህ ለመረጥኳቸው ቃሌን ትነግራቸው ዘንድ ከእኔም ጋር በምሥጢር በባለሟልነት ትነጋገር ዘንድ መርጨሃለሁ›› አላቸው፡፡
ከጥቂት ቀንም በኋላ አባታችን በጎችን እየጠበቁ ሳሉ አንድ አመጸኛ መጣና በትራቸውን በኃይል ነጥቆ ወሰደባቸው፡፡ አቡነ ሐብተ ማርያምም ‹‹በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ እቋቋምህ ዘንድ ኃይል የለኝምና በትሬን መልስልኝ›› ቢሉት የትዕቢትን ቃል ተናገራቸው፡፡ አባታችንም ‹‹እምቢ ካልክስ እሺ የእግዚአብሔርን ኃይል ታያለህ›› አሉት፡፡ ወዲያም ያ አመጸኛ ላዩ ታች፣ ታቹ ላይ፣ ግራው ቀኝ፣ ቀኙ ግራ ሆኖ በአየር ላይ ተሰቅሎ ዋለና እየጮኸ አባታችንን ለመናቸው፡፡ አባታችንም ‹‹የቀጣህ እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ›› ባሉት ጊዜ ከተሰቀለበት ወርዶ በእግሩ ቆመ፡፡ በዚያ የነበሩና ይህንን ተአምር ያዩ እረኞችም እጅግ ፈርተው ሄደው ለወላጆቻቸው ያዩትን ተናገሩ፡፡ የሀገሩ ሰዎችም ‹‹ቀድሞ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ እያለ ሲጸልይ ሲሰግድ አይተነዋል አሁንም ጠላቱን በነፋስ የሚቀጣ ይህ ልጅ ወደፊት ምን ይሆን!›› እያሉ አደቁ፡፡ ወላጆቻቸውም ይህን በሰሙ ጊዜ በግ ጠባቂነቱን አስተዋቸውና ወስደው ለመምህር ሰጧቸው፡፡ አቡነ ሀብተ ማርያምም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ በሚገባ ተማሩ፡፡
ከዚህም በኋላ አባታቸው ከሀገሪቱ ታላላቅ ሰዎች አንዷን እጮኛ አጨላቸው፡፡ ነገር ግን አቡነ ሀብተ ማርያም ‹‹አባቴ ሆይ እኔ ራሴን ለክርስቶስ በድንግልና ለመኖር አጭቻለሁ፣ ተራክቦዬም ቃለ ወንጌልን መስማት እንጂ ሌላ አይደለምና ለምን እንዲህ ትለኛለህ?›› አሉት፡፡ አባታቸውም ይህን ሲሰማ ተቆጥቶ ያለ አቡነ ሀብተ ማርያም ፈቃድ ሙሽራይቱን ለማምጣት ሄደ፡፡ አባታችን ግን ሀገር ጥለው ለመሰደድ ከቤት ተደብቀው ወጡ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በመብረቅ አምሳል አባታቸውን ገስጻቸውና በዚህ ድንጋጤ ምክንያት ከዚህ ኃላፊ ዓለም ዐረፈ፡፡
አባታችንም የአባታቸውን ዕረፍት ሳያዩ አፋር ወደምትባል ሀገር ሄደው አባ ሳሙኤል ከሚባል ደግ መነኩሴ ቦታ ገብተው መነኩሴውን እያገለገሉት ኖሩ፡፡ አንድ ቀን አባታችን እንስራ ተሸክመው ውኃ ይቀዱ ዘንድ ወደ ወንዝ ወረዱና ውኃውን ቀድተው ሲመለሱ ድንጋይ አደናቀፋቸውና እንስራው ከላያቸው ላይ ወደቀ፡፡ ነገር ግን መሬት ከመድረሱ በፊት አባታችን ፈጥነው የጌታችን ስም በጠሩ ጊዜ እንስራው ወድቆ ሳይሰበር ተመልሶ በትከሻቸው ላይ ተቀመጠ፡፡ አባ ሳሙኤልም ይከተሏቸው ነበርና ይህን ጽኑ ተዓምር አይተው እጅግ አደነቁ፡፡
እንዲሁ ከዕለታት በአንድ ቀን በሌሊት መብራት ለአባ ሳሙኤል እያበሩ ሳለ መብራቱ ከእጃቸው ላይ ወድቆ ጠፋ፡፡ መምህሩም አባ ሳሙኤል ቁጡ ነበረና ስለ መምህራቸው ቁጣ በጣም ደንግጠው ወድቆ የጠፋውነ መብራት ፈጥነው ባነሱት ጊዜ መብራቱ በእግዚአብሔር ተዓምር ራሱ በርቶ ታየ፡፡ አባ ሳሙኤልም ይህን ተዓምራት አይቶ እጹብ እጹብ በማለት ‹‹የዚህ ቅዱስ ልጅ መጨረሻ ምን ይሆን?›› ብሎ ካደነቀ በኋላ ‹‹የዓለም ሁሉ የጥበብ መብራት ይሆናል›› ሲል ትንቢት ተናገረላቸው፡፡ እመቤታችን ለአባ ሳሙኤል ተገልጣላቸው የአቡነ ሀብተ ማርያምን ክብር ነግራዋለች፡፡ አባታችንም አባ ሳሙኤልን 12 ዓመት ከትሕትና ጋር እየታዘዙ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ ኖረው ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወጥተው ሄደው እለ አድባር በተባለ ገዳም መኖር ጀመሩ፡፡ ከቦታውም ደርሰው ጥቂት ከቆዩ በኋላ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከአባ መልኬጼዴቅ እጅ የምንኩስናን ስርዓት ተቀበሉ፡፡ ይኸውም የሚዳው አቡነ መልኬጼዴቅ በደጃቸው የተቀበረውን ሰው አፈር የማያስበሉት ጻዲቅ ናቸው፡፡ ይህንንም የጻድቃኑን አባትና ልጅነታቸውን መሠረት በማድረግ የይሰበይ አቡነ ሀብተ ማርያም ገዳም ካህናት፣ መሪጌቶችና ዲያቆናት ግንቦት 4 ቀን ወደ ሚዳ መራቤቴ በመሄድ የአቡነ መልኬጼዴቅን በዓል እጅግ በደማቅ ሁኔታ ያከብራሉ፡፡
አቡነ ሀብተ ማርያምም ምንኩስናን ከተቀበሉ በኋላ ገድላቸውንና ትሩፋታቸውን በማብዛት በሳምንት አንድ ጊዜ ቅጠልን ብቻ የሚመገቡ ሆኑ፡፡ አርባ አርባ ቀን ሰማንያ ሰማንያ ቀንም የሚጾሙበት ጊዜ ነበር፡፡ በሌሊትም ወደ ጥልቅ ባሕር እየገቡ መዝሙረ ዳዊት፣ አራቱን ወንጌላትና ሌሎች የጸሎት መጽሐፍትን ይደግሙ ነበር፡፡ ፊታቸውም እንደ ንጋት ምሥራቅ ኮከብ ያበራ ጀመር፡፡
ከዚህም በኋላ ወደ ምሥራቅ ሄደው ጎሐርብ ወደምትባል ሀገር ደረሱ፡፡ በዚያም በዓት አጽንተው ሲጸልዩ ጌታችን ቅዱስ ገብርኤልንና ቅዱስ ሚካኤልን በቀኝና በግራ አስከትሎ ተገለጠላቸውና ‹‹ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን›› አላቸው፡፡ ያን ጊዜ አባታችን ከፈጣሪአቸው ግርማ የተነሳ ደንግጠው ከመሬት ወድቀው እንደ በድን ሆኑ፡፡ ጌታችንም አንስቶ ክቡራን በሆኑ እጆቹ አጸናቸውና ‹‹የመጣሁት ለጸናህ ነው ሰውነትህንም እንደ ንስር ላድሳት ነው እንጂ ላጠፋህ አይደለም፡፡ ድካምህና ገድልህ ሁሉ ለዘለዓለም መታሰቢያ ሊሆን በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ተጽፎልሃል ብዬ በእውነት እነግርሃለሁ፡፡ ለአንተ ለወደድኩህና ለመረጥኩህና ወዳጄ የማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ተጭነህ ወደምትሄድበት ቦታ የሚያደርስህ የብርሃን ሰረገላ ሰጥቼሃለሁ፡፡ እንደ አንተም ካሉ በዋሻ በመሬት ፍርኩታ ከሚኖሩ ከመረጥኳቸው ቅዱሳን ጋር ትገናኝ ዘንድ ወደ አራቱም አቅጣጫ ትበር ዘንድ የብርሃን ሠረገላ ሰጥቼሃልሁ፡፡ ዳግመኛም የሉቃስንና የዮሐንስን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ትሄድ ዘንድ የእሳት ሠረገላ ሰጥቼሃለሁ›› አላቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹በጸሎትህ አምኖ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሉ፣ ስምህን የጠራውን ዝክርህን ያዘከረውን ሁሉ የሀብተ ማርያም አምላክ ሆይ ከጠላት እጅ አድነኝ ያለኝን በኅሊና ያሰበውን በልቡናው የወሰነውን እፈጽምለታለሁ፡፡ አንተን ገድልህንና ቃል ኪዳንህን የናቀውን ያቃለለውን ሁሉ ፍጹም መበቀልን እበቀለዋለሁ፡፡ እንደ ወዳጄ እንደ ፊቅጦርም በእናቴ በማርያም ድንግል አተምኩህ›› ካላቸው በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ከእርሳቸው እንዳይለይ የዘወትር ጠባቂ አድርጎ ሰጣቸውና በታላቅ ግርማ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
❗ቅዱስ ገብርኤል ማን ነው❗
,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,
?? ገብርኤል ማለት " እግዚእ ወገብር”፦ የእግአብሔር አገልጋይ ማለት ነው። ፍጥረታት መፈጠር በጀመሩበት በዕለተ እሑድ እግዚአብሔር መላእክትን ከፈጠራቸው በኋላ ተሰወራቸው መላእክትም “መኑ ፈጠረነ፦ማን ፈጠረን” ሲሉ ዲያብሎስ እኔ ፈጠርኳችሁ ብሎ መላእክት በተረበሹ ጊዜ “የፈጠረንን ❗አምላካችን እስክናውቅ በያለንበት ጸንተን እንቁም❗ ብሎ ያረጋጋቸው መልአክ ነው።
?? በዚህም ምክንያት ጌታ “በእንተዝ ይደልዎ ከመ ይጹር ዜናሃ ለማርያም” እንዲል ሥጋዌውን ለድንግል እንዲያበስር አድሎታል።
?? ቅዱስ ገብርኤል ለብስራት የሚላክ ከሰዎች ጋር ታላቅ ግንኙነት ያለዉ ተወዳጅና ፈጣን መልአክ ነዉ ።
?? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደምትወልድ እመቤታችንን ያበሰራት እና ለመጀመርያ ጊዜ ከሰዎች በፊት ያመሠገናት ቅዱስ ገብርኤል ነዉ ።
?➡ስለስቱ ደቂቅን ናቡከደነጾር በእሳት ላይ በጣላቸዉ ጊዜ ፈጥኖ በመድረስ ከእሳት ያዳናቸዉ ቅዱስ ገብርኤል ነዉ ::
?▶እንዲሁም ኢየሉጣና ቂርቆስ በፈላ ዉኃ ዉስጥ በተጣሉ ጊዜ ዉኃዉን በማቀዝቀዝ ያዳናቸዉ ቅዱስ ገብርኤል ነዉ ::
?? ሳጥናኤል ሥላሴን በካደ ጊዜ መላእክትን በቃሉ ያጽናናቸው ቅዱስ ገብርኤል ነዉ ::
?? ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱና በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም ቅዱስ ገብርኤል ነዉ ::
?? በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ብርሃን የገለጸና የሰበከ ቅዱስ ገብርኤል ነዉ ::
?? ዳንኤልን ከአናብስት ያዳነው ቅዱስ ገብርኤል ነዉ ::
?? ወደ ዘካርያስ የተላከ የዮሐንስን ልደት ያበሰረ ቅዱስ ገብርኤል ነዉ ::
?? ሰብአ ሰገልን በኮከብ ምልክት የመራቸው ቅዱስ ገብርኤል ነዉ ::
?? ድንግል ማርያምና ሕፃኑን ክርስቶስን በምድረ በዳ በስደታቸው የመራ ቅዱስ ገብርኤል ነዉ ::
?? የብርሃን ራስ ወርቅ የተቀዳጀ መላኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው !
❗የመልአኩ ጥበቃ እና ረድኤት አይለየን❗
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ ዘጠኝ በዚች ቀን የታላቁ #አባ_መቃርስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ፣ የደግነት የምጽዋት የፍቅር አባት የሆነው #ደጉ_አብርሃም ጣዖት የሰበረበት፣ የአልዓዛር ልጅ #የቅዱስ_ፊንሐስ መታሰቢያው ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ነሐሴ ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ቀን ሳስዊር ከሚባል አገር ወደ አስቄጥስ ገዳም የታላቁ አባ መቃርስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ።
ከዕረፍቱ በኋላ ከሀገሩ ከሳስዊር ሰዎች መጥተው ሥጋውን ሰርቀው ወደ ሀገራቸው ወሰዱት ቤተ ክርስቲያንም ሠርተውለት ሥጋውን በዚያ አኖሩት እስላሞች እስከ ነገሡበት ዘመንም በዚያ ኖረ።
ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ ቦታ አፍልሰውት በዚያም ቤተ ክርስቲያን ሠሩለት። ለአባ መቃርስ ገዳም አበ ምኔት ሁኖ አባ ዮሐንስ እስከ ተሾመበት ዘመን ኖረ።
ሊቀ ጳጳሳቱም የከበረች ጾመ አርብዓን ሊጾም ወደ አባ መቃርስ ገዳም በወጣ ጊዜ ፈጽሞ አለቀሰ እንዲህም ብሎ ጸለየ። #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ የከበረ የአባ መቃርስ ሥጋ በዚህ ገዳም በመካከላችን ይሆን ዘንድ እንድትረዳኝ እመኛለሁ።
ከጥቂት ቀኖችም በኋላ አባ ሚካኤል ሔደ ከእርሱ ጋራም ስለ ገዳሙ አገልግሎት አረጋውያን መነኰሳት አሉ ልቦናቸውም በመንፈሳዊ ሁከት ተነሣሥቶ ያመጡት ዘንድ የአባ መቃርስ ሥጋ ወደ አለበት ቦታ ደረሱ።
የአገር ሰዎችም በአዩአቸው ጊዜ በትሮቻቸውንና ሰይፎቻቸውን በመያዝ ከመኰንናቸው ጋራ ተሰብስበው ከለከሏቸው። በዚያቺም ሌሊት በልባቸው ፈጽሞ እያዘኑ አደሩ። አባ መቃርስም በዚያች ሌሊት ለመኰንኑ በራእይ ተገለጠለትና ከልጆቼ ጋራ መሔድን ለምን ትከለክለኛለህ እንግዲህስ ተወኝ ከእሳቸው ጋራ ወደ ቦታዬ ልሒድ አለው።
ያ መኰንንም በጥዋት ተነሣ እየፈራና እየተንቀጠቀጠ የከበሩ አረጋውያን መነኰሳትን ጠርቶ የከበረ የአባ መቃርስን ሥጋ ሰጣቸው። እነርሱም ደስ ብሏቸው ተቀበሉት በመርከብም ተሳፍረው ተርኑጥ ወደሚባል አገር ደረሱ ከእርሳቸውም ጋራ የሚሸኙአቸው ከየአገሩ የመጡ ብዙ ሕዝቦች ነበሩ። በዚያችም ሌሊት በዚያ አደሩ ጸሎትንም አደረጉ ቀድሰውም ለሕዝቡ ሥጋውንና ደሙን አቀበሉ።
ከዚህም በኋላ ተሸክመው ወደ ገዳም ተጓዙ ሲጓዙም ከበረሀው እኵሌታ ደርሰው ከድካማቸው ጥቂት ሊአርፉ ወደዱ። አባ ሚካኤልም የከበረ የአባታችን የአባ መቃርስን ሥጋ የምናሳርፍበትን #እግዚአብሔር እስከ ገለጠልን ድረስ እንደማናርፍ ሕያው #እግዚአብሔርን ብሎ ማለ።
ከዚህም በኋላ የከበረ የአባ መቃርስን ሥጋ የተሸከመ ገመል ወደ አንድ ቦታ ደርሶ በዚያ በረክ አለ። የከበረ የአባ መቃርስ ሥጋ ያለበትንም ሣጥን ይጥል ዘንድ በራሱ ወዲያና ወዲህ ይዞር ጀመረ። አረጋውያን መነኰሳትም #እግዚአብሔር የፈቀደው ያ ቦታ እንደሆነ አወቁ እጅግም አደነቁ #እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ያም ቦታ እስከ ዛሬ የታወቀ ነው።
ወደ ገዳሙም በቀረቡ ጊዜ መነኰሳቱ ሁሉም ወጡ ወንጌልና መስቀሎችን ይዘው መብራቶችን እያበሩ እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን እስከ አስገቡት ድረስ በታላቅ ክብር በራሳቸው ተሸክመው ወሰዱት።
#እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት ተአምራትን አደረገ።
#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ አባቶቻችን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የሃይማኖት የደግነት የምጽዋት የፍቅር አባት የሆነው ደጉ አብርሃም ጣዖት የሰበረበት እለት ይታሠባል።
በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የአብርሃም አባቱ ታራ ጣዖትን ይጠርብና ይሸጥ ነበር። ሽጦ ገንዘብ የሚያመጣለት ደግሞ ልጁ አብርሃም ነበር። በዚያ ወራት አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ፍለጋ ገብቶ ነበር። አንድ ቀን ጣዖቱን ሊሸጥ ወደ ገበያ እየሔደ የተሸከመውን እንጨት ይመራመረው ገባ። "አሁን ይሔ ምኑ ነው አምላክ!" እያለም ያደንቅ ገባ። መንገድ ላይም ደክሞት ካረፈበት "ለምን አልጠይቀውም" በሚል አናገረው።
"እርቦኛል አብላኝ" አለው:: መልስ የለም:: "እሺ አጠጣኝ" አለው:: አሁንም ያው ነው:: "ባይሆን እሺ አጫውተኝ" አለው:: ጣዖቱ ተራ እንጨት ነውና መልሱ ዝምታ ነበር:: ከዚያ ተነስቶ ወደ ገበያው ሲደርስ "ዐይን እያለው የማያይ: ጀሮ እያለው የማይሰማ አምላክ የሚገዛ" እያለ ይጮህ ጀመር::
ይህን ሲሰሙ አንዳንዶቹ "የታራ ልጅ አብዶ" ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ "እሱ ያቀለለውን ማን ይገዛዋል" ብለውት ሔደዋል:: ከገበያ ሲመለስም ጣዖቱን ተመልክቶ አብርሃም እንዲህ አለ:: "አንተ ቀድሞውን በዕለተ ሠሉስ የተፈጠርክ ዕፅ ነህ" ብሎ ሰባበረው።
ወደ ቤቱ ሲመለስም ሁሉንም ጣዖታት ሠባበራቸው:: ይህ የተደረገው ከ2,000 ዓመታት በፊት በዚህች ቀን ነው። የመንግስተ ሰማያት አበጋዝ የ #እግዚአብሔር ወዳጅ አባታችን አብርሃም በመጨረሻው በውሃ፣ በነፋስ፣ በእሳትና በፀሐይ ተመራምሮ ፈጣሪውን አግኝቷል።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አብርሃም ጸሎት ይማረን በረከቱም ይድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የአልዓዛር ልጅ የፊንሐስ መታሰቢያው ነው። ካህኑ ፊንሐስ የብሉይ ኪዳን ዘመን አገልጋይ: ከነገደ ሌዊ: የሊቀ ካህናቱ የአሮን የልጅ ልጅ ነው:: አባቱም ሊቀ ካህናቱ አልዓዛር ነው:: ፊንሐስ እሥራኤል ከግብጽ ሲወጡ ሕጻን የነበረ ሲሆን አድጐ በመጀመሪያ ካህን፤ አባቱ አልዓዛርና አያቱ አሮን ሲያርፉ ደግሞ ሊቀ ካህንነትን ተሹሟል::
አንድ ቀን በጠንቅዋዩ በበለዓም ክፉ ምክር እሥራኤላውያን ከሞዐብ ሴቶች ጋር በኃጢአት በመሳተፋቸው #እግዚአብሔር ተቆጥቶ ነበር:: ያጠፋቸው ዘንድም መቅሰፍት ተጀምሮ ሳለ ፊንሐስ ወንድና ሴት: በደብተራ ኦሪቱ አንጻር የማይገባውን ሲሠሩ አያቸው::
ለፈጣሪው ቀንቶ በአንድ ጦር ሁለቱንም በአንድ ላይ ጥሏቸዋል:: ያን ጊዜ ጌታ "አስተንፈስካ ለነፍስየ" ብሎታል:: መቅሰፍቱም ተከልክሏል:: በዚህም ምክንያት ካህኑ ፊንሐስ የ300 ዓመት ዕድሜ ተጨምሮለት: #እግዚአብሔርን ሲያገለግል ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል:: (ዘኁ. 25፥7, መዝ. 105፥30)
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ አባቶቻችን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
እየሄድን የተመለስን
በአንድ ወቅት እስራኤላውያን በግብፅ ባርነት እየተሰቃዩ በነበረበት ወቅት አምላካችን እግዚአብሔር ሊቀ ነብያት ሙሴን መርጦ ህዝቡን እየመራ ወደ ተስፋዪቱ ምድር ያስገባቸው ዘንድ እንደመረጠውና ከዛም ባርነት አምላካችንን ይዘው በሙሴ መሪነት ከባርነት እንደወጡ እናስታውሳለን።
ታድያ በዚህ ታሪክ ውስጥ እስራኤላውያን እየሄዱ ያልሄዱበት፣ ወደፊት እየተራመዱ ወደኋላ የተመለሱበት በአምላካቸው እቅፍ ውስጥ ሆነው ከእቅፉ ለመውጣት የታገሉበት ታሪክ ነበር ፤ ያም ታሪክ ሁላችን እንደምናስታውሰው ሊቀ ነብያት ሙሴ ወደ ሲና ተራራ ከአምላካችን ጋር ለመነጋገር በወጣ ጊዜ 40 ቀንና 40 ሌሊት እየተነጋገረ እንደቆየ ህዝቡ ባዩ ጊዜ ዘደ አሮን መጥተው "ይህ ከግብፅ ምድእ ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደሆነ አናውቅምና ተነስተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክትን ስራልን " አሉት ።
ከልጆቻቸው ፣ከሚስቶቻቸው ላይ ያለውን የወርቅ ጌጥ ሁሉ ሰብስበው የጥጃ ምስል ሰሩ፤ ለዛ ለጥጃ ምስል ሰገዱለት ፣ መስዋዕትም ሰዉለት።
ይህንን ሲያደርጉ ታድያ ከአምላካቸው ጋር የነበረውን ቃልኪዳን ረስተው እስራኤላውያን እየሄዱ እየመሰላቸው ተመለሱ ።
የተከበራችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ የዛሬው ክርስትናችንም ከዚህ ብዙ የተለየ አይደለም ፣ አምላካችንን ላንከዳው ወደፊት ከእርሱ ጋር ለመጓዝ ቃል ገብተን ስንት ጊዜ ወደ ኋላ ተመለስን?
ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ባላስብሽ ምላሴ ከትናጋዬ ትጣበቅ ብለን ቃል የገባንላትን ቤተክርስቲያን ረስተን ስንቶቻችን በዓለም ባህር ውስጥ ተዘፈቅን ይሆን ?
በምርኮ በባቢሎን በባቢሎን ወንዞች አጠገብ የተቀመጡ እስራኤላውያን
" በባቢሎን ወንዞች አጠገብ ተቀምጠን ፅዮንን ባሰብናት ጊዜ አለቀስን በአኻያ ዛፎቿ ላይ መሰንቆዎቻችንን ሰቀልን "
ብለው ስቅስቅ ብለው እንዳለቀሱ
ዛሬስ ስንቶቻችንን እንሆን በሀጢያት አረንቋ ውስጥ ቁጭ ብለን ቤተክርስቲያናችንን፣ እመቤታችንን ባሰብናት ጊዜ እያለቀስን ያለን?
መሰንቆ የተባሉ የጸሎት መፅሐፎቻችንን፣የምናስቀድስባቸውን ነጠላዎች አጣጥፈን ያስቀመጥን ስንቶቻችን እንሆን? አምላክ በቸርነቱ ይጎብኘን ፤ እንጂማ የእኛ ህይወት ለመወራት አይደለም ለማሰብም የሚከብድ ሆኗል፣ ዳሩ ግን አሁንም ተስፋ አለን።
የተከበረች ፣የተወደደች፣ንፅህት ፣ክብርት እመቤታችንን አለሽልን እንበላት፤ ከአባታችን ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ጋር ሆነን እንዲህ እንበላት :-
*ድንግል ሆይ
እኔ የተጠማሁ ነኝ፣አንቺ የወርቅ መቅጃ ነሽ ፣ ልጅሽ የህይወት ውሃ ነው።
ድንግል ሆይ
የእኔን አመንዝራነት፣ያንቺን ንፅህና፣ የልጅሽን ቸርነት እናገራለሁ።
ድንግል ሆይ
የእኔን ስህተት፣ያንቺን ማማለድ የልጅሽንም መታገስ እናገራለሁ ።
ድንግል ሆይ
የእኔን ስንፍና ፣ የአንቺን ምክር የልጅሽንም ይቅርታ እናገራለሁ ።
የተወደደ ልጇንም ቀረብ ብለን እነሰዲህ እንበለው
ጌታ ሆይ
የመርገም ያይደለ የበረከት ተክል አድርገኝ።
ጌታ ሆይ
የኃሳር የጉስቁልና ያይደለ የክብር ተክል አድርገኝ።
ጌታ ሆይ
የጥፋት ያይደለ የህይወት ተክል አድርገኝ።
ጌታ ሆይ
የሰይጣን ያይደለ የቅዱሳን ቅድስት ተክል ፣ በነቢያት ትንቢት ካፊያ የምለመልም አድርጊኝ።*
አቤቱ ጌታ ሆይ ክርስቲያን አድርገኝና እየሄዱ ከመመለስ ፣ እየደረሱ ወደ ቤትህ ካለመግባት ሰውረኝ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
ተክለሀና ነሃሴ 18/2016
በበህሊና
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።
@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna
#ኢትዮጵያ
Last updated 2 months, 1 week ago
Last updated 6 days, 22 hours ago
ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ ? @Esat_tv_comment_bot
??ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ??
Last updated 2 months, 3 weeks ago