ፍኖተ አበው ዘኦርቶዶክስ (መ/ር ንዋይ ካሳሁን)

Description
በዚኽ ቻናል ጽሑፍ የሃይማኖታዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ ነው
We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated 2 months, 3 weeks ago

Last updated 2 months, 2 weeks ago

ይህ ስለ Manchester United መረጃዎችን የሚያገኙበት የ Telegram ቻናል ነው 🇪🇹
--------------------------------------------------------------
☞︎| ስለ ማንቸስተር ዩናይትድ ትኩስ መረጃዎች
☞| ቀጥታ ስርጭቶች ከየስታድየሞቹ
☞| የዝውውር ዜናዎች
☞| ስለ ማንችስተር ዩናይትድ ታሪኮች

📩 ለማስታወቂያ ስራ DM :- @Marcoabdu

Last updated 1 month, 1 week ago

1 month, 1 week ago

የጥምቀት ጥያቄ

"መጽአ ቃል እምደመና ዘይብል፣ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር"
"የምወደው ልጄ ይኽ ነው የሚል ቃል ከደመና ውስጥ መጣ" የሚል ነው። መዝሙሩ የአብ ምስክርነት ነው።
መሠረታዊ ኾኖ ለእኛ ያለው ትርጉም "ለእኔ በጥምቀቱ የማስበው ሰማያዊ ቃል ምንድነው? ጥምቀትን ሳከብር ምን አሰብኩ ነው። የመጣልኽ ቃል ምን የሚል ነው?
ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር እያልክ ስትዘምር አብሮኽ ካለው ወንድምህ ግን ተጣልተህ ተኳርፈኽ ይኾን የምትዘምረው? ወይስ " ወንድሜን እኽቴን እወዳለሁ በሚል ምስክርነት ነው።
በዓሉ ወደ ውስጥ እንዴት እንደሚገባ አስተውል።

1 month, 1 week ago

የጌታችን በዮሐንስ እጅ መጠመቅ

ጌታችን በዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ ሲመጣ የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ነበር።” ሉቃ.3:23 ይኽ ለመርቅያውያን ግራ መጋባትን የሚፈጥርባቸው ነጥብ ነው። እርሱ ሥጋን ከድንግል ማርያም ያልነሣ ከሆነ እንዴት ሊጠመቅ ወደ ዮሐንስ ሊመጣ ቻለ? መለኮት በባሕርይው መጠመቅ አያስፈልገውምና፡፡ ይልቁኑ “ሠላሳ ዓመት” የሚለው ቃል በእውን ሰው ስለመሆኑ የሚያስረዳን አይደለምን?

ጌታችን ዮሐንስን፡- “እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን?'' ብሎት ነበር። ማቴ.3:14 ዮሐንስ እንዲህ ማለቱ ጌታን በመቃወም አይደለም ነገር ግን የጌታን ቅድስና ይገልጥ ዘንድ ነው። እርሱ ዮሐንስ የጌታውን ጫማ መሸከም የማይበቃ ከሆን እንዴት እርሱን ለማጥመቅ ሊበቃ ይችላል? እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ “ትንሹም በታላቁ እንዲባረክ ክርክር የሌለበት ነገር ነው።” ዕብ.7:7  

ስለዚህ የዮሐንስ ፈቃደኛ አለመሆን ተገቢ ነበር፤ እንዲሁ የእርሱ መታዘዝ የተገባነበር። ከእርሱ በላይ የሆነውን ማጥመቅ የተገባ እንዳልሆነ እንዲሁ የጌታን ትእዛዝ ላለመቀበል ማመንታት ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ ጌታ የጎደለው ስላለ አንዳች ነገር ሊሞላለት በዮሐንስ የተጠመቀ አይይለም፡፡ ነገር ግን የተዋረደውን የአዳምን ሥጋ ስለ መልበሱ ለማጠየቅ በዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ መጣ።

ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀትን በማወጅ ኃጥአንን እያጠመቀ የመጣ ቢሆንም ስለ ጌታችን "እርሱ ኃጢአት አላደረገም።"  ተብሎ ተጽፏልና ጌታችን ንስሐ ከሚገቡት ጋር ወደ ጥምቀት መቅረቡ ኃጢአተኛ ሆኖ እንዳልሆነ በዚህ እንረዳለን። 1 ጴጥ.2:22

ዮሐንስ በፍርሃትና በትሕትና ሆኖ ለጌታችን "እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል፤ አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ሲለው ኢየሱስም መልሶ "አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” ባለው ቃሉ ጌታችን ንስሐ እንደሚያስፈልጋቸው ሰዎች በዮሐንስ ሊጠመቅ እንዳልመጣ እናረጋግጣለን። ማቴ.3:14

ስለዚሀም በጥቂት ነገር ሕግን ተላልፈው የሚገኙ ሁሉ ከርግማን በታች ስለሚሆኑ እንዲሁም ማንም በሕግ የተጻፈውን ጽድቅን ሁሉ ሊፈጽምና ከእርግማን ማምለጥ ስለማይቻለው ጽድቅን ሁሉ ሊፈጽምና ርግማንን ሊያስቀር ኃጢአትንም ሊያጠፋ ጌታችን መምጣቱን በዚህ ቃሉ አስረዳን። “ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና።” ገላ.3:10

ጌታችን ለዮሐንስ፡- “አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” አለው:: መሳፍንትና ነገሥታት የሚሆኑ በካህናት ተቀብተው ሥልጣንን ሲቀበሉ አብረው አስተባብረው ሕግንም ይቀበሉ ነበር። 

ጌታችንም ሥጋን ለብሶ መገለጡ አስፈላጊ እንደሆነ እንዲሁ ሕግን ሁሉ ይፈጽም ዘንድ ግድ ነው። ስለዚህም የእርሱን ሰው መሆን ለማስረዳት ወደ ጥምቀቱ ቀረበ። በተለይ በእርሱ ጥምቀት የዮሐንስ ጥምቀት ማብቃቱንና በዮሐንስ የተጠመቁ በእርሱ ድጋሚ መጠመቅ እንደሚያስልጋቸው ለማስረዳት ወደ ዮሐንስ መምጣት ተገባው፡፡ በእርሱ ጥምቀት የዮሐንስ ጥምቀት ሊያገለግል የሚችለው እርሱ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ብቻ እንደነበረ አሳወቀን። በሕጉ ምክንያት ከሆነው ርግማን ሊዋጀን አማናዊው ጥምቀት በጌታችን ተሰጠን።

ጌታችን “አሁንስ ፍቀድልን'' አለ፡፡ ወደ መንጋው ሲመጣ እንደ ወንበዴ ተሰውሮ እንዳልሆነ ልብ እንዲባል "ጌታችን “አሁንስ ፍቀደልን' አለ፡፡ እንዲሁም የዮሐንስን ጥምቀት የሚያጣጥሉ የፈሪሳውያን አመለካከት የተሳሳተ መሆኑን ለማስረዳትም ጌታችን “አሁንስ ፍቀደልን" አለ። አንድም የመልእክተኛውንም ትሕትና ሊገልጥ እንዲህ አለ፡፡ እንደተጻፈው “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላልና።” ማቴ.23:12

ዮሐንስ “እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ ነኝ" በማለት በእውነተኛ ትሕትና ራሱን በጌታው ፊት አዋርዶአል፡፡ እናም ጌታችን የብሉይ ኪዳን ሕግ ፍጻሜ የሆነውን ያዮሐንስን ቀኝ እጅ በመያዝና ራሱ ላይ በማኖር “አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው::” ማቴ.3:15

እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ “ሕግና ነቢያት እስከ ዮሐንስ ነበሩ::" ሉቃ.16:16 መሢሕ ክርስቶስ ግን ለሐዲስ ኪዳን በኵር ሆነ።

ጌታችን በቅባት የሚሰጠውን ሥልጣን ፍጹም ለማድረግና ለደቀ መዛሙርቱ ሙሉ ለሙሉ ለዘለዓለም ለመስጠት በጥምቀት የብሉይ ኪዳኑን ጽድቅ ፈጸመ፡፡ በዚህም የዮሐንስን ጥምቀትንና ሕጉን በአንድ ጊዜ አሳለፋቸው፡፡ “እርሱ ጽድቅን ይፈጽም ዘንድ ተጠመቀ" ምክንያቱም ኃጢአት የለበትምና፡፡ ነገር ግን ሌሎችን አጠመቃቸው ምክንያቱም ኃጢአተኞች ነበሩና። በእርሱ ጽድቅ ሕግን አሳለፋት። በእርሱም ጥምቀት የዮሐንስ ጥምቀት ቀረች፡፡

አንድም “ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባል" ሲል የበጎች በር ከተባለው ዮሐንስ ዘንድ የእስራኤል በጎች በአንድነት ተሰብስበው ስለ ነበር ነው። ጌታችንም ወደ መንጋው በኃይሉ ሳይሆን በጽድቁ ገባ። ሲጠመቅ በርግብ አምሳል በእርሱ ላይ ያረፈው መንፈስ ቅዱስ እርሱ የበጎች እረኛ መሆኑን መሰከረ፣ ነቢይነትና ክህነትን ከዮሐንስ ወደራሱ መለሰ፡፡ ንግሥናን ግን ከዳዊት ቤት በመወለድ ወደ ራሱ መለሰ። ክህነትንም ከሌዊ ወገን ከሆነው ከአሮን ልጅ ከዮሐንስ እጅ ወደ ራሱ መለሰ፡፡

በዚያም ጊዜ ወደ ጥምቀቱ የመጡ ብዙዎች ቢሆኑም ክርስቶስ በአካል ከእነርሱ ጋር አንድ ሆኖአልና እርሱን ከሌሎች ለመለየት መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ በማረፍ እርሱ ከሌሎች የተለየ መሆኑን በምልክት ገለጠላቸው:: በእርሱ ጥምቀት መንፈስ ቅዱስ እንደወረደ እንዲሁ እርሱ በመሠረተልን ጥምቀት መንፈስ ቅዱስ በእኛም ላይ ያርፋል።

@ኅብረ ወንጌል 

ንዋይ ካሳሁን

1 month, 2 weeks ago

ፍጡነ ረድኤት ጊዮርጊስ

ለደካማውም ለብርቱውም ፣ለእርዳታ ፈጥነህ የምትደርስለት ጊዮርጊስ ሆይ፤ ደግነትህ በጎነትህ ከመጠን በላይ ነውና። በአማላጅነትህ ለሚተማመኑትም ሁሉ ነፍስ፤ ዋስ ጠበቃ ነኽ። ከቂም በቀል ንጽሕ በመሆን እንደ ክብርት እመቤትህ እንደ ማርያም ርኅሩኅ ልብ ነህ።

ፍጡነ ረድኤት ጊዮርጊስ ሆይ፣ ከላይ ባለ በሰማይ ከታች ባለ በምድር በብዙ ወገን ለርዳታ ፈጥነህ አደራረስህ የኤፍራታ ርግብ የተባለችው እንደ እመቤትህ ማርያም ነው እኮን። በመሆኑም በእናትህ በቴዎብስታ ስም እንደስምህ መንታነት የባለ ሟልነት ስምህን ትሰጠኝ ዘንድ ቃል ኪዳን እንድትገባልኝ እማልድሃለሁ።

ፍጡነ ረድኤት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ፤ አንተን በመታመን ለጠራህ ሁሉ ፈጥነህ ስትደርስለት ከአውሎ ነፋስ ይልቅ በተፋጠነ ሩጫ ነው እኮን።

ጊዮርጊስ ሆይ፤ የዘወትር ጸሎቴንና የቃሌንም የልመና ጩኽት ትቀበል ዘንድ ለይቅርታና ለምሕረት ፈጥነህ ወደ እኔ ቅረብ።

ፍጡነ ረድኤት ፈጥኖ ደራሹ ጊዮርጊስ ሆይ፤ ለጠላቴ መሳለቂያ አታድርገኝ ለሚተነኳኮሉኝም መሰደቢያ አታድርገኝ፤ ለክፉ ጐረቤቴም መዘባበቻ አታድርገኝ።

አባቴ ጊዮርጊስ ሆይ፤ የልቤን ኅዘን ስነግርህ ፈጥነህ ጸሎቴን ስማኝ ነገሬንም አድምጠኝ። ያዘኑትን የምታረጋጋ ሆይ፤ ወደኔ ቅረብ፤ በአጠገቤም ተገኝተህ አለሁልህ በለኝ።
ፍጡነ ረድኤት ፈጥኖ ደራሹ ጊዮርጊስ ሆይ፤ አሁንም ለጠላቴ መሣለቂያ አታድርገኝ። አባቴ ጊዮርጊስ ሆይ፤ የምነግርህን ባለመናቅ ተቀብለህ ልጄ ወዳጄ አገልጋዬ ታዛዤ ደረስኩልህ በለኝ።

ፍጡነ ረድኤት ፈጥኖ ደራሹ ጊዮርጊስ ሆይ፤ እንደ ወይን ጠጅ ልብን ደስ የምታሰኝ ነህ እኮን። ሐዘንን ታስረሳለህና።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ፤ ልመናችንን ፈጥነህ ስማ። በባሕር ላይ የምንንሳፈፈውን በየብስ የምንነጉደውን ሁሉ ፈጥነህ እርዳን እምነታችን በአንተ ላይ አድርገናል።

የእግዚአብሔር እውነተኛ ምስክሩ ፈጥኖ ደራሹ ሰማዕት ኃይሉ ጊዮርጊስ ሆይ፤ በየዕለቱ እርዳታህ አይለየኝ። የዚህ ዓለም ነጋዴ ያለትርፍ መውጣት መውረድ ከንቱ ድካም ነውና።

ንዋይ ካሳሁን

1 month, 2 weeks ago

አሳሳቢ ከሆነ እናስብበት

በሁካታ፣ በዘማሪ፣ በግርግር፣ በጫጫታ ብዛት ሁኔታን መርሳት እየተለመደ ነው። የሕሊና ዐይኔ ነው? ወይስ ተሳስቼ ነው? በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየሆኑ ያሉትን ለመርሳት የሚደረገው የሁካታ፣ የዝማሬ፣ የግርግር፣ የጫጫታ ብዛት አይታያችሁምን?

ወይስ እኔ ተሳስቸ ነው? ሁኔታውን ለመርሳት የሚደረገው ለጥብዓት ተብሎ ይሆንን?
የግርግር፣ የዘማሪ፣ የሁካታ፣ የለበጣ ደስታ..ብዛት ሌሎቻችሁን አኹናዊ የቤተ ክርስቲያንን ሁኔታ እንዳታስቡ አልጋረዳችሁም? ማዕበሉ ጎርፉ አላንገላታችሁም?

ሚድያው ኹሉ ምንም እንዳልተፈጠረ፣ በነጻ ኹኔታ እንዳለ በደንብ ደልቁ የሚለው፣ የአልበም ምረቃን በብዛት የሚያስተዋውቀው በቃ ቤተ ክርስቲያን ጥሩ ላይ ናት ማለት ነው? ወይስ መፍትሄ መንገዱ ይሄ ኹኖ ይሆን?

ቤተ ክርስቲያኗን በማዘጥዘጥ  በመደለቅ ድግሙ ሠልሱ በማለት  እያስበላናት የመከራ ማደንዘዣ እየጨመርንላት ይሆን?

ልክ እንደ አጥማቅያን፣ እንደ ትንቢታውያን፣ እንደ ተሀድሶአውያን..ይሄም አንድ ሁኔታን ማስረሻ ሕሊናን ማፋዘዣ ስልት ይሆን?

መከራችንን እንዳናይ እና እንዳናስታውስ ወደ መፍትሄያችንም እንዳንሄድ አንድ ማደንዘዣ ሁኖ ከተሠራበት በጣም አደገኛ ነው።

የማኅሌቱ ቸብቸቦም መጠን የለሽ ጭብጨባ ሲጠናወተው ሳይ በጣም አስፈራኝ። ለአፍታም እንኳን መዘንጋት የሌለብን ነገር ቢኖር የምእመናንን መከራ ነው።

@ምሥራቀ ጸሐይ ጉባኤ ቤት

1 month, 2 weeks ago

ስለ ኢትዮጵያ እንድናስብ ትንሽ ለመጻፍ ፈልጌ ብዙ ጣድቃን "ጽድቃቸው" እየጠፋባቸው ስለተቸገሩ ነው የተውኩት። ግን እመለስበታለኹ።

1 month, 2 weeks ago

አገልግሎት ወይስ ፓተርን ነው ያለን?

ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደየ አይነታ ስብስባችን ለሕይወታችን ያበጀነው sense of self አለ። የራስ ማንነት ስሜት ነው። ለምሳሌ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ ሰበካ ጉባኤ፣ ሰንበት ተማሪ፣ ምእመናን አሉ። በእርግጥ ምእመናን የኹሉም መጠሪያ ነው። 

ሳናውቀው ውስጣችን የሚሠራ ስሜት sense of self አለ። ቀጥታ ከትክክለኛው ከቅዱሳት መጽሐፍት የተቀዳ ከክርስቶስ ግንድነት ከቅዱሳን ሕይወት የተሳሰረ ማንነት አይደለም። በልምምድ የመጣ ነው። 

እኛ “መንፈሳዊ ሕይወት” የምንለው ነገር  ግን መንፈሳዊ ሕይወት ያልኾነ በውስጣችን pattern ፓተርን አበጅቷል። ፓተርን ማለት አንድ ድርጊት የምንከውንበት ተደጋጋሚ የሚደረግ እንቅስቅሴ፣ ንግግር፣ የሰውነት እንቅስቃሴ፣ ድምጽ…. ነው። (a repeated decorative design.)

እኛ መንፈሳዊ ሕይወት አልያ አገልግሎት እያልን ራሳችንን እናታልልለን እንጂ ሕይወት ሳይኾን ፓተርን ሠርቶብናል። እሱን ስንጠብቅ አገልግሎት ይመስለናል እሱን ትንሽ ስንለቅ ሰውነታችን ኹሉ አይታዘዘንም። ይኽንን ሰውነታቸው በቅጽበት automatic ነው የሚፈጽመው፣ ደመ ነፍሳዊ ነው። 

ለአንድ ሰንበት ተማሪ የራሱ ፓተርን አለው። ከውጭ ሲመጣ፣ ነጠላ ሲያጣጥል፣ የአቋቋሙ፣ በአገልግሎት ወቅት ዓይን አስተያየቱ፣ ሌሎችን የሚያስተናግድበት፣ ሲናገር ድምጽ አወጣጡ ፓተርን የተከተለ ነው። ደመ ነፍሳዊ ነው።
ሲዘምሩ መዝሙሩ ተጠንቶ ነው። የሚጠናው የመዝሙሩ ግጥሙ ይሸመደዳል ዜማው (melody) ይዜማል። ከዛው ሽብሸባው፣ ከበሮ ይጨመርበታል። እንቅስቃሴ ይከተላል። ይኽ የመዝሙር ፓተርን ነው። 

ዋና ነጥቡ ግን የመዝሙሩን ምስጢር ከነሕይወቱ ያስተውሉታል ወይ? መዝሙሩ ዜማ ኾኖ ነው የሚቀረው ወይስ ወደ ሚፈለገው መንፈሳዊ ክፍታ ይወስዳቸዋል ወይ? የሚለው ነው። 

ነፍሳቸውን ካሉበት ወደ ሚዘመረው ጉዳይ ይነጥቀዋል ወይ? አልያ ያንን የሚዘምሩትን ወደ ምስጢሩ ጥልቀት ስቦ በዚያው ቅጽበት ላይ ያደርሳቸዋል ወይ? ለምሳሌ “ዮም ሰማያዊ በጎል ሰከበ ለዘተወልደ እም ቅድስት ድንግል” እያሉ ሲዘምሩ። በመዝሙሩ ወደ ቤተልሔም ወስዶ ሕጻኑን ከበው ሲዘምሩ ያሳያቸዋል። ያ ሕጻን በጨርቅ ተጠቅልሎ በእናቱ እቅፍ ኾኖ በአኹናዊ ቅጽበት በልባቸው ሲወለድ ያዩታል? ወይስ ዜማው ወይም ሜሎዲው ነው አፋቸው ላይ የሚጮኽው? “ዮም” ዛሬ ሲሉ ራሳቸውን በዚያ ክርስቶስ በተወለደበት ቅጽበት ውስጥ ይከቱታል ወይ? ወይስ ዝም ብሎ ሽምደደ pattern ነው። 

የፓተርንን ጉዳይ እንይ። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስንገባ የምንቆምበትን ቦታ እናስበው። ሌላ ሰው እዚያ ቦታ ቆሞ ቢጠብቀን ሌላ ቦታ ቀይሮ መቆም ደስ ይለናል ወይ? 

መዘምራን ሦስት መዝሙር አንጥተው ሰዓት የለም ዛሬ አትዘምሩም ወይም ኹለት ብቻ ዘምሩ ቢባል ምን ይፈጠራል?። ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ይነሳል ወይስ ከእኛ መዝሙር ይልቅ መታዘዝ ይበልጣል ብለው ያቆማሉ። ከተለማመዱ “ማቅረቡ” ነው እንጂ መታዘዙ ዋና ጉዳይ መኾኑ አይታወስም። ምክንያቱም መዝሙር ጥናት ሕይወት ሳይኾን የሥራ ድርሻ ኾኖ ፓተርን ሠርቷል። እሱ ሲነካ ኹከት (Cheos) ኾኖ ብቅ ይላል። ፓተርን ማንም ጣልቃ እንዲገበባት አይፈቅስም። 

በቅርቡ ለንግሥ መዝሙር እየተዘመረ ሲዞር መደማመጥ ሳይችሉ ተዘበራረቀ። ድምጼን ከፍ አድርጌ አንድ የሚያደርጋቸውን መዝሙር አስጀመርኩ። ኹሉም ተቀበሉ ተከተሉ። ከወዲያ ወዲኽ እየተዘዋወረች የምታዘምረዋ ወጣት ግን ብስጭት አለች። ምክንያቱም ፓተርኑ ውስጥ የሌለ ነገር ሳመጣ ለዚያ ፓተርን cheos ኹከት ፈጠርኩ ማለት ነው። ፓተርኑ ሲነካ ማንም ቢኾን አይከበርም። እሷ ፓተርኑን ነው የምታስጠብቀዋ። 

ጓደኛሞች መካከል የማናውቀው ሰው መጥቶ ቆሞ ቢያስቀድስ በስልት ገፍተን ነው የምናስወጣው። አስበን ላይኾን ይችላል። ቆመን ስናስቀድስ ቅዳሴው ላይ ሳይኾን ዋና ትኩረታችን ፓተርኑ ላይ ስለኾነ ነው። ስለዚኽ ፓተርን ነው እየኖርን ያለነው እንጂ ሕይወቱን አይደለም። 

ጥምቀት ምንድነው፣ እኔ ለምን አከብረዋለኹ፣ ዋናው ምስጢር ቁም ነገር ምንድነው፣ የምዘምረው ነገር ምን ማለት ነው፣ በእኔ ሕይወት ያለው ትርጉም፣ እኔስ በዚኽ በዓል ውስጥ ሕይወቴ ምንድነው የሚል ጥያቄ አይመጣም። ይኽ ነው ዋናው ሕይወት። ይኼ በፓተርን አይመጣም። ቁጭ ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ቁም ነገር ያለው ትምህርት መስማትን ይጠይቃል ከራስ ጋር ትግል ይፈልጋል። 

ፓተርን በመደጋገም ለምደን የምናደርገው እንጂ ይቅርታ፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ ቅድስና፣ መቁረብ፣ መቀደስ፣ ጸጥታ፣ ትኅትና ለሚሉ ጉዳዮች ደንቆሮ ነው። እነዚኽን አይፈልግም። እነዚኽ ፓተርን ውስጥ ከገቡ ሰውየውን ከፓተርን ወደ መንፈሳዊ ሰው ይለውጡታል። ሰዎች ከለመዱት ፓተርን ለመውጣት በጣም ይቸገራሉ። አይፈልጉምም። ሊለውጡ ሲሞክሩ እንደ ተገለሉ፣ ብቻቸውን እንደ ቀሩ ይቆጥሩታል። 

እርስዎ በልምድ የያዙት ፓተርን ነው ወይስ ሕይወት ነው? ፓተርናችሁ  በማስመሰል ሳይገላችሁ አጥፉትና ወደ እውነተኛ ማንነት ተመለሱ ለማለት ነው። ብዙም ግልጽ ካልኾነ አለፉት። 

ንዋይ ካሳሁን

4 months ago

አይደለም ወይ?

ያለ ተግባር ብቻውን ደም በማልቀስ ድንጋይ በመንከስ  የቤተ ክርስቲያን ችግር አይወገድም። አውጥቶ አውርዶ ራስን ሰጥቶ ነገን ተንብዮ በመሥራት ነው እንጂ።

የዘመናት ወረቱን እንደተቀማ ነጋዴ አንገት ደፍቶ ልቡናን አሙቶ ተስፋን አጥቶ በመቆዘም ችግሩ አይፈታም። ትናንትን መሠረት አድርጎ ለነገ የሚደርስ የዓላማ የተግባር ዘርን በመዝራት ነው እንጂ።

እንዲያው ላይሆን ከንቱ እስኪሞት ድረስ እንጀራ ከመፈለግ እስኪሞቱ ድረስ የቤተ ክርስቲያንን ዕረፍት መፈለግ  የተሻለው ዓላማ ነው።

ምክንያቱም መኖራችን እንኳን የሚታወቀው ለፍትህ ለእውነት  እሺ ፦ ለጥፋት እና ለውድመት ግን እንቢ ማለት ስንችል ነው።
ሁሉም ዘመዶች ሁሉም ወገኖቻችን የምቾት ጊዜ ጌጦች ናቸው እንጂ የፍትሕ የእውነት ጊዜ ማደንዘዣዎች  ማስቀየሻዎች አይደሉም።

@ ምሥራቀ ጸሐይ ጉባኤ ቤት

4 months ago

ሰው መኾን :- ቅውም ማንነት state of bing "እነት" ነው
ብሔር:- ማኅበረሰባዊ ስሪት social construction

4 months, 1 week ago

አጋግና  አጋጋውያን

አማሌቃውያን በሰማርያ በረሃ የሚኖሩ ወራሪ ሕዝቦች ናቸው። ከኢየሩሳሌም በደበብ በኩል ሲኖሩ ከሙሴ ጀምሮ እስከ ሕዝቅያስ ድረስ ኢየሩሳሌምን የሚቃወሙ ነበሩ። ዘጸ.17

አማሌቅ ኤሊፋዝ (የኤሳው ልጅ) የተወለደ ነው። የኤሳው ትውልድ ውስጥ ጎሳ ነው። አማሌቃውንያ ከእስራኤላውያን በዝምድና ሩቅ ናቸው። እስራኤልን ለማጥፋት በመጀመርያ የተነሡ ሕዝቦች ናቸው። 
አማሌቅ በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔር ስም የሚነሳባቸውን ሁሉንም ነገር ለማጥፋት ቆርጠው የተነሡ ነበር። 

በንጉሡ ሳኦል ዘመን እግዚአብሔር አማሌቃውያን ውጋ አለው። በተደጋጋሚ የመለኮት ትዕዛዝ በሳሙኤል አማካኝነት ደርሶታል። "አሁንም ሄደህ አማሌቅን ምታ፥ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፥ አትማራቸውም፤ ወንዱንና ሴቱን ብላቴናውንና ሕፃኑን በሬውንና በጉን ግመሉንና አህያውን ግደል" 1.ሳሙ.15:8

አማሌቃውያን እግዚአብሔርን ባለመፍራት ብዙ ክፉ ዘር ዘርተዋል። ምንም እንኳ እግዚአብሔር ብዙ ቢታገሳቸውም ጥጋበኛ መቀጣቱ አይቀርምና ፍርድ መጣባቸው። 

አጋግ የአማሌቃውያን ንጉሥ ነው። እጅግ ጨካኝ ከመኾኑ የተነሣ ሕጻናትን በመግደል ይደሰት ነበር። እርጉዝ እናቶችን በሕይወት ሳሉ በሰይፍ ሆዳቸውን እየሰነጠቀ የጽንሱ አቀማመጥ እንዴት ነበር እያለ ያያል በስቃያቸው ይቀልድ ነበር። 
ሳኦል አስር ሺኽ ሠራዊት አዘጋጅቶ ዘመተ "ሳኦልም አማሌቃውያንን ከኤውላጥ ጀምሮ በግብጽ ፊት እስካለችው እስከ ሱር ድረስ መታቸው"

ሳኦል የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን ከነ ሕይወቱ ማረከው። እግዚአብሔር በሳኦል አልተደሰተም። ማንንም እንዳትምር ሰውንም እንስሳውንም አጥፋ ብሎት ነበር። ሳኦል ግን ከሰው ክፉውን አጋግን ከእንስሳቱ የደለቡትን የአማሌቅ ንብረት ይዞ መጣ እግዚአብሔር አዘነበት። 

እግዚአብሔር ለሳሙኤል ማዘኑን ነገረው ሳኦልን ናቀው። ለምን እንስሳቱን እንደተዋቸው ሲጠየቅ "ለእግዚአብሔር መስዋዕት ይሆናሉ ብዬ ነው አለ"

እግዚአብሔር አጋግን በሳሙኤል እጅ ሊቀጣው አዘዝው። ደም አፍሳሽ የሚሞተው ደሙ ፈሶ ነው። ደም ማፍሰስ ደም መፍሰስን ይወልዳል። ዘፍ.9:6

ሳሙኤል አጋግን አምጡልኝ አለው። አጋግ ፍርሃት ፍርሃት አለው መቆም አቃተው። ሞት ሸተተው። "ሳሙኤልም፦ የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ አለ። አጋግም እየተንቀጠቀጠ ወደ እርሱ መጣ። አጋግም፦ በውኑ ሞት እንደዚህ መራራ ነውን? አለ" 1.ሳሙ.15:32

በሠራዊት በወታደር በመሳሪያ የተከበበ ኹሉ ጀግና አይደለም ሴትና ሕጻናት የገደለ ኹሉ ጀግና አይደለም። ጀግና ማለት ብቻውን ኾኖ በልበ ሙሉነት የሚቆም ማለት ነው። አጋግ ብቻውን ሲኾን ጉልበት ከዳው። በደሉ ታየው። 
የሞት አስከፊነት በትክክል ገባው። "በውኑ ሞት እንደዚኽ መራር ነውን" አለ። ጀግና  ሰው በሰው ሞት ይማራል ፈሪ ሰው በራሱ ሞት ይማራል። 

ብዙ መሪዎች በጦር ሠራዊት ሲከበቡ በመሳሪያ ታጥረው ሲናገሩ ጀግና ይመስላሉ እንጂ ለብቻ ሲያዙ የመጨረሻ ፈሪ ናቸው። 

"ሳሙኤልም፦ ሰይፍህ ሴቶችን ልጆች አልባ እንዳደረገቻቸው እንዲሁ እናትህ በሴቶች መካከል ልጅ አልባ ትሆናለች አለ፤ ሳሙኤልም አጋግን በእግዚአብሔር ፊት በጌልገላ ቈራረጠው" ይላል

ሳሙኤል አጋግን በሰይፍ እንደ መስዋዕቱ ቆራረጠው። የአጋግ ታሪክ ተደመደመ።

ዛሬ አጋጋውያን በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ቆመው ይፎክራሉ የቤተ ክርስቲያን ጉልላት መስቀል ታቦት ማዕተብ አያሳየን እያሉ ነው። 
የእግዚአብሔርን በዓል ማየት አይፈልጉም። 
አጋጋውያን በሳሙኤል እጅ ገብተዋል። በሕጻናትና እርጉዞች ላይ የሰነዘሩት ስለት በራስቸው አንገት ተሰንዝሯል። 

አጋግ የሰይጣን ቋሚ ግብረ አበር ነበር። ሳሙኤል እንደ መስዋዕት በግ አወራረደው። 
የእኛ አባቶች በአማሌቅ ገንዘብ ይራኮታሉ። ጵጵስና ሹመት የአማሌቅን ገንዘብ እንደ ማትረፍ ተቆጥሯል። ገንዘብ አማሌቅ ኾኖብናል። እግዚአብሔር የአማሌቅን ንብረት ወደ መቅደሱ ወደ ከተማው እንድዲገባ አይፈልግም። 

አጋጋውያን ዋጋቸውን ማግኘታቸው ጥርጥር የለውም። ሴቶችን ልጅ አልባ ሲያደርጋቸው ወላጅን ገድሎ ልጆችን የሙት ልጅ። ልጆችን ገድሎ ወላጅን ያለ ቀባሪ አስቀርቶ ነበር። ሌላው ሲያልቅ እሱና መኳንንቱ ይስቁ ነበር። እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ ነውና መጣበት ታሪኩን በክፉ ሞት ደመደመው። 

ንዋይ ካሳሁን

4 months, 1 week ago

የቤተሰብ ጠላቶች

፩ ሰይጣን
፪ ግለሰባዊ ጠባይ፣ እውቀት፣ ብስለት ማጣት
፫ ሥልጣኔ

We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated 2 months, 3 weeks ago

Last updated 2 months, 2 weeks ago

ይህ ስለ Manchester United መረጃዎችን የሚያገኙበት የ Telegram ቻናል ነው 🇪🇹
--------------------------------------------------------------
☞︎| ስለ ማንቸስተር ዩናይትድ ትኩስ መረጃዎች
☞| ቀጥታ ስርጭቶች ከየስታድየሞቹ
☞| የዝውውር ዜናዎች
☞| ስለ ማንችስተር ዩናይትድ ታሪኮች

📩 ለማስታወቂያ ስራ DM :- @Marcoabdu

Last updated 1 month, 1 week ago