ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።
@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna
#ኢትዮጵያ
Last updated 2 months, 3 weeks ago
Last updated 2 months, 2 weeks ago
ይህ ስለ Manchester United መረጃዎችን የሚያገኙበት የ Telegram ቻናል ነው 🇪🇹
--------------------------------------------------------------
☞︎| ስለ ማንቸስተር ዩናይትድ ትኩስ መረጃዎች
☞| ቀጥታ ስርጭቶች ከየስታድየሞቹ
☞| የዝውውር ዜናዎች
☞| ስለ ማንችስተር ዩናይትድ ታሪኮች
📩 ለማስታወቂያ ስራ DM :- @Marcoabdu
Last updated 1 month, 1 week ago
አንድ በአይሁድ መምህራን የተከተበ ድንቅ መጽሐፍ አለ። ፒርቄይ አቮት (פִּרְקֵי אָבוֹת) ይሰኛል። በተለያዩ ጊዜያት የኖሩ የአይሁድ ሊቃውንት በግብረገባዊ ጉዳዮች ላይ የተናገሯቸውን አጫጭር ብሂሎች ሰብስቦ የያዘ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ ከጫፍ እስከጫፍ ሳይሰለች የሚነበብ አይነት ነው። በውስጡ እጅግ ብዙ ሊጠቀሱ የሚገባቸው ትምህርቶች ቢኖሩም፥ ለዛሬ ጊዜውን ይዋጃል ብዬ ያሰብኩትን አንዱን ለቅምሻ ያህል ላጋራ።
ከዚህ በታች ያለውን የተናገሩት ሊቅ የአይሁድ ምሁር የሆነው የገማልያል ልጅ ናቸው። ስምዖን ወልደ ገማልያል ይባላሉ። ሊቅነቱ እንደ አባታቸው እንደሆነ ይነገራል። ዮሲፎን "የአይሁዶች ጦርነት" በተሰኘው ሥራው ላይም ስማቸውን ያነሳል። እኚህ ሊቅ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ስለመናገራቸው በፒርቄይ አቮት ሰፍሮ ይገኛል፦
שִׁמְעוֹן בְּנוֹ אוֹמֵר, כָּל יָמַי גָּדַלְתִּי בֵין הַחֲכָמִים, וְלֹא מָצָאתִי לַגּוּף טוֹב אֶלָּא שְׁתִיקָה. וְלֹא הַמִּדְרָשׁ הוּא הָעִקָּר, אֶלָּא הַמַּעֲשֶׂה. וְכָל הַמַּרְבֶּה דְבָרִים, מֵבִיא חֵטְא:
"ሕይወቴን ሙሉ በጠቢባን መካከል አድጌያለሁ፥ ለሰው ልጅ ግን ከዝምታ የተሻለ አንዳች ነገር አለመኖሩን፥ ከመማር ይልቅ ማድረግ [በድርጊት መግለጥ] የተሻለ መሆኑን እና ንግግርን የሚያበዛ ኃጢያትንም እንደሚያበዛ ተረድቻለሁ።"
ይህ ብሂል ከመጽሐፉ ውስጥ ከሰፈሩት ምናልባትም እጅግ አብልጬ ከወደድኳቸው እና ዘወትር ከማስታውሳቸው መካከል ቀዳሚው ነው። ምክሩ ዘመናችንን ያማከለ ጥበብን በውስጡ ያዘለ መኾኑ እሙን ነው። ይህም ስለ ዝምታ እና እምነትን ስለመኖር ነው።
በተለምዶ ዝምታ ወርቅ ነው ይባላል። በግሌ ከወርቅም በላይ መሆኑን አምናለሁ። ዝምታ ከብዙ ስህተት የሚጠብቅ ቁልፍ ነው። አንደበትን ሲከፍቱ አእምሮ ይታያል የሚባለውን ያገናዘበ በሚመስል መልኩ፥ ጠቢቡ ሰለሞን ዝምታ የሰነፍን ውርድት ሳይቀር እንደምታርቅ ሲነግረን “ሰነፍ ዝም ቢል ጠቢብ ሆኖ ይቈጠራል፥ ከንፈሩንም የሚቈልፍ፦ ባለ አእምሮ ነው ይባላል።” (ምሳ 17፥28) ይለናል። መልካም ነገርን የሚናገረው ንጉሥ ዳዊት ስንኳ አንደበቱን ስለመጠበቅ ሲናገር “አቤቱ፥ ለአፌ ጠባቂ አኑር፥ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ።” (መዝሙር 141፥3) ሲል እንሰማዋለን። በኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነትም፥ የቅድስናን መንገድ ፈጥኖ ለመውጣት የሚረዳ መንገድ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል።
በአሁኑ ዘመን፥ ሰዎች ስለማያውቁት ነገር ብዙ ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ ሶሻል ሚዲያ ላይ ሁሉም ሰው ስለሁሉም ነገር ሲናገር፥ በሁሉም ነገር ላይ አሳቡን ሲሰጥ፥ በሚያውቀውም በማያውቀውም ጉዳይ ላይ ሲተነትን ይታያል። ይህ እጅግ አደገኛ ነው። በሁሉም ላይ ደርሶ ተንታኝ መሆኑን ለስህተትም መጋለጥ፥ ራስንም ማልፋት፥ ትዝብት ላይም መውደቅ ነው። በዝምታ ውስጥ ጥበብን እናገኝ። መቼ መናገር እንዳለብን እንወቅ። መናገር ስለምችል ብቻ አንናገር፥ መመለስ ስለምንችል ብቻ መመለስ ይቅርብን። በዝምታ እያሰላሰልን ጥበብን መፈለግ እንልመድ።
ሌላኛው ነጥብ እምነትን ስለመኖር የተጠቀሰው ነው። መምህሩ ከእውቀት ይልቅ ያወቁትን መኖር እንደሚበልጥ ይናገራሉ። ይህ እውነት ነው። እምነታችንን ካልኖርነው ትርጉም አልባ ይሆናል። ወንጌሉም ሆነ የቀደምት አባቶቻችን ትምህርት አስረግጦ የሚያስረዳን ይህንን እውነት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።” (ማቴዎስ 5፥16) በማለት ክርስትናን በተግባር የመኖርን አስፈላጊነት ሲነግረን፥ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ደግሞ "ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥ ከእናንተ አንዱም፦ በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።" (ያዕቆብ 2:15-17) በማለት ይነግረናል።
በአሁኑ ጊዜ ብርሃናችን በሰው ፊት ማብራት አልቻለም። እምነታችንን ልንኖረው አልተቻለንም። ይህ ክርስትናችንን ፉርሽ ያደርገዋል። መማሩን እንማር፥ ነገር ግን እንተግብረው። ሮማዊያን ይሉ እንደነበረው "Non scholæ sed vitæ discimus" (የምንማረው ለአስኳላ ሳይሆን ለሕይወት ነው) የሚለው ቃል መርሕ ይሁነን።
🖋 Fresenbet G.Y Adhanom
----------
የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib
ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett
በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ከብጽዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ንግግር የተሻለ መርህ ለማግኘት ከባድ ነው። ይህንን መርህ ሁላችንም ብንከተል እግዚአብሔር የሰጠንን መክሊት ተጠቅመን ያለምንበት መድረስ እንችላለን። የአባት ምክር እነሆ:-
.
.
.
"እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው ሥራ ሰጥቶታል፤ ያንን መሥራት የእሱ ፈንታ ነው፡፡ ቢቻለው እሱን ማገድ የዲያቢሎስ ሥራ ነው፡፡ በእርግጥ ሥራው እግዚአብሔር እንደሰጠህ ያህል ሰይጣን ሊያግድህ ይጥራል፡፡ ሌላ ነገር በበለጠ ደስ የሚያሰኝ ሊያቀርብልህ ይጥራል፡፡ በዓለማዊ ተስፋዎች ያባብልሃል፡፡የሐሜት ጐርፍ ያስወርድብሃል፡፡
ደራስያን እንዲጠይቁህ፥ እጅግ ስመ ጥር ሰዎችም በክፉ እንዲናገሩብህ ይጠቀምባቸዋል፡፡ ጲላጦስ፣ ሄሮድስ፣
ሐናንያ፣ ቀያፋ ሁሉም በአንተ ላይ ያድማሉ፡፡ ይሁዳም በአጠገብህ ቆሞ በሠላሳ ብር ሊሸጥህ ይከጅላል፡፡ ይሄ ሁሉ የደረሰብህ ሰይጣን በዚህ ከሥራህ ሊስብህና እግዚአብሔርን ከመታዘዝ ሊያሰናክልህ መሆኑን ልትገነዘብ አትችልምን?
አንተ ግን ሥራህን ሥራ!
አንበሳው ሲያጓራ ፍንክች አትበል፣ የሰይጣንን ውሻዎች ለመውገር አትቁም፡፡ ጥንቸሎቹንም በማባረር ጊዜህን አታጥፋ፡፡ ሥራህን ሥራ! ዋሾች ይዋሹ፣ ጠበኞች ይጣሉ፣ ማኀበሮችም ይወስኑ፣ ደራሲዎችም ይድረሱ፣ ሰይጣንም የፈለገውን ያድርግ፣ አንተ ግን ምንም ነገር እግዚአብሔር የሰጠህን ሥራ ከመፈጸም እንዳያግድህ ተጠንቀቅ፡፡
ገንዘብ እንድታተርፍ አልተላክም፣ እንድትበለጽግም አልታዘዝክም፣ ለክብርህ ተከላከል ብሎ አልነገረህም፣ ሰይጣንና አገልጋዮቹ የሚነዙትን የሐሰት ወሬ እንድታስተባብል አልተጠየቅክም፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ብታደርግ ሌላ ሥራ ልትሰራ አትችልም። ይህም ብቻ ሳይሆን ለራስህ እንጂ ለእግዚአብሔር አልሠራህም፡፡
ዓላማህ እንደ ኮከብ የጸና ይሁን ፤ ተወው ዓለም እንደፈለገው ይነታረክ፣ ይጨቃጨቅ፣ ጥቃት ይደርስብህ ትበደል፣ ትሰደብ፣ ትታማ፣ ትቆስልና፣ ትናቅ ይሆናል፡፡ ኃይለኛ ያጐሳቁልህ፣ ወዳጆች ይተውህ፣ ሰዎችም ይንቁህ ይሆናል፡፡
አንተ ግን በጸና ውሳኔ የማያወላውል ቅናት በመጨረሻ ላይ ጸንተህ፣ የሰጠኸኝን ሥራ ፈጸምኩ ሃይማኖትንም ጠበቅሁ ለማለት እስክትችል ድረስ የሕይወትህን ዓላማ እና የተፈጠርክበትን ግብ ተከተል!"
ብጽዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ
+• ጊዜው ገና ነው •+
አንድ ምንጩ የማይታወቅ አስተማሪ የሆነ አፈ-ታሪክ አለ። በዚህ አፈ-ታሪክ መሠረት፥ ከእለታት በአንዱ ቀን አጋንንት ስብሰባ አደረጉ ይባላል። ይህንን ስብሰባ የጠራው የአጋንንቱ አለቃም “ዓለምን ሁሉ ከእኔ ጋር ለማሰለፍ እፈልጋለሁ። ምን ይደረግ? ማንንስ ልላክ?” ብሎ ጠየቀ። ከሥሩ ያሉትም አንድ በአንድ እየተነሱ አሳቦችን ማቅረብ ጀመሩ።
አንዱ ተነሳና፥ “እኔን ብትልከኝ፥ ፈጣሪ የለም ብዬ ሰዎችን ማሳመን እችላለሁ!” ብሎ ተናገረ። የአጋንንቱ አለቃ ግን፥ “እርሱ አይሠራም። ብዙዎቹ አያምኑህም። ፈጣሪ እንዳለ ያውቃሉ።” ብሎ መለሰ።
ሌላኛው ተነሳና፥ “እኔን ከላክኸኝ፥ ገነትም ሆነ ሲኦል የሚባል ቦታ እንደሌለ አሳምናቸዋለሁ!” አለ። የአጋንንቱ አለቃ ግን፥ “እርሱም አይሠራም። ብዙዎቹ ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ ያውቃሉ።” ብሎ መለሰ።
ሌላው ደግሞ ተነሳና፥ “እኔን ላከኝ። ፈጣሪም አለ፥ ገነትም አለ፥ ሲኦልም አለ፤ ነገር ግን ስለዚህ ነገር ሁሉ ለማሰብ ጊዜው አሁን አይደለም ብዬ አሳምናቸዋለሁ።” አለ። የአጋንንቱ አለቃም ደስ እያለው “ይህ ጥሩ መንገድ ነው!” በማለት አሳቡን ተቀበለና ላከው ይባላል።
ሰይጣን ማዘግየት ጥሩ ስልት መሆኑን ስለሚያውቅ፥ ለማዘግየት ይፋጠናል። በሐዲስ ኪዳን ላይ ቅዱስ ጳውሎስ "ወደ እናንተ ልንመጣ ወደን ነበርና፥ እኔ ጳውሎስም አንድና ሁለት ጊዜ፥ ሰይጣን ግን አዘገየን።” (1 ተሰ 2:18) ሲል እናገኘዋለን። ሰይጣን ላያስቀረን ይችላል፥ ግን ቢያንስ ሊያዘገየን ብዙ ይሞክራል።
እርሱ ዓለማዊ ጓዞቻችንን ለአፍታ ስንኳ አውርደን ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ግንኙነት እንድናስብ አይፈልግም። ስለ ጸሎት ብታስብ፥ "አሁን ደክሞሃል። ጊዜው አይደለም። ሌላ ጊዜ ትጸልያለህ" ይልሃል። ለመጾም ብትዘጋጅ "አሁን ጉልበት ስለሚያስፈልግህ ብላ። የምትጾምበት ጊዜ አይደለም፤ ሌላ ጊዜ ትጾማለህ።" ይልሃል። ለመስገድ ብትዘጋጅ "ኧረ ተረጋጋ፤ ጊዜው አይደለም፥ ጾም ሲገባ ትሰግዳለህ" ይልሃል። ንስሃ ልትገባ ብትዘጋጅ "ቆይ እንጂ፥ ዘልለህ ጨርሰህ አንዴ ብትታጠበው አይሻልም?" ለማለት የሚቀድመው የለም። ቅዱስ ቁርባን ልቀበል ነው ካልክ "አንተኮ ገና ነህ፥ ለወደፊት ጣጣህን ስትጨርስ ቀስ ብለህ አመቻችተህ ትቆርባለህ" ብሎ ያዘናጋሃል።
በዚህ ሁሉ መዘግየት ውስጥ መልአከ ሞት መቼ እንደሚመጣ ማን ያውቃል? ለመንፈሳዊ ነገር ስንነሳ፥ ሰይጣን "ጊዜው ገና ነው" ማለቱ አይቀርም። እኛ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል“ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው።” (2ኛ ቆሮ 6፥2) እንደሚል እናስታውስ። ለመዳናችን ቀጥሮ አንስጥ።
🖋 Fresenbet G.Y Adhanom
----------
የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib
ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett
+• አሥራት ለምን ታወጣለህ? •+
አባ ታድሮስ ማላቲ “Stories for the Youth” በሚል ርዕስ ለወጣቶች ባዘጋጁት መጽሐፍ ላይ፥ ስለ አሥራት ጥቅም አንድ አጭር ታሪክ ጸፈዋል፤ እንደሚከተለው ተርጉሜ አቅርቤዋለሁ።
--
ከሃያ ዓመት ቆይታ በኋላ፥ በካሊፎርኒያ ከተማ አንድ የመንፈስ ልጄን አገኘሁት እና ወደ ቤቱ ወሰደኝ። ቤቱ እጅግ ግዙፍ እና ውብ ነበር። አብረን ተቀምጠን ሳለም፥ “አባ፥ የዛኔ በካሊፎርኒያ መኖር ስጀምር ትዝ ይልዎታል? ኑሮን ለማሸነፍ ትግል ላይ ነበርኩ፥ አሁን ግን እግዚአብሔር ከጠየቅሁትም በላይ ሰጥቶኛል።” አለኝ።
እኔም “ይህ የእግዚአብሔር ቸርነት ነው። በእውነቱ አምላካችን ያስብልናልና እናመሰግነዋለን።” አልኩት።
እርሱም ቀጠለና፥ “እግዚአብሔር ምን ያህል ቸርነት እንዳደረገልኝ ያውቃሉ? ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ጀምሮ ‘እዚህ በምድር ላይ ስኬታማ ብሆን፥ መንግሥተ ሰማያትን ግን ካጣሁ ምን እጠቀማለሁ?’ እያልኩ መብሰልሰል ጀመርኩ። ከዚያ አንድ ቀን፥ በአምላኬ ፊት ተንበርክኬ፥ ሁኔታዬ ምንም ያህል ቢከፋ፥ ከማገኘው ገቢ ላይ አሥራቴን ላለመንካት ቃል ገባሁለት። አሥራት የእግዚአብሔር ነዋ! ቀጠልኩና ‘ጌታዬ ሆይ፥ ሁሉም ያንተ ስጦታ ነውና፥ ከዘጠኝ እጁ ላይ ደግሞ በእዚህ በአሜሪካም ሆነ በግብጽ ላሉ ነዳያን እመጸውታለሁ።’ አልኩት።
“ከዚያም በልግስና መስጠት ጀመርኩ፤ የገነት በሮችም ተከፈቱልኝ! በእውነቱ እግዚአብሔር ከሚያስፈልገኝ በላይ ሰጠኝ። አንዳንዴ፥ ተንበርክኬ እያለቀስኩ፥ ‘እባክህ በቃህ አምላኬ! ከዚህ በላይ ከሰጠኸኝ የሃብት ብዛት ነፍሴን እንዳያጠፋት እፈራለሁ’ ብዬ እለምነው ነበር። እርሱ ግን እንዲህ እያልኩም የበለጠ ይሰጠኝ ነበር።”
? Fresenbet G.Y Adhanom
----------
የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib
ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett
+• የሐዋርያው የመጨረሻ አደራ •+
በጥንቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ የሚነገር አንድ ትውፊት አለ:: ይህንን ትውፊት ቅዱስ ሄሬኔዎስ በሥራዎች ውስጥ አካትቶት እናገኛለን :: በትውፊቱ መሠረት የተወደደው ሐዋርያ ሊለያቸው መሆኑን የተገነዘቡት ደቀ-መዛሙርቱ ተሰብስበው "ለእኛ ምን መልእክት ተተውልናለህ?" ብለው ጠየቁት:: እርሱም "ልጆቼ ሆይ፥ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ" አላቸው:: ይህንንም እጅግ ብዙ ጊዜ ደጋገመው:: ደቀ-መዛሙርቱም "ከዚህ ሌላስ የምትለን አለ?" ብለው ጠየቁት:: እርሱም "ይህ ይበቃችኋል፤ የጌታ ትእዛዝ ይህ ነውና" ብሎ መለሰላቸው::
የክርስትና መነሻው፥ ማዕከሉም ሆነ መጨረሻው ፍቅር ነው:: ከክርስትና ውጪ "አምላክ ፍቅር ስቦት ኃጢአተኛ የሆነውን ሰውን ለማዳን እርሱ ራሱ ሰው ሆነ" የሚል ሃይማኖት የለም:: ክርስትና በአንድ ቃል ይገለጽ ቢባል "ፍቅር" የሚለው ቃል ይገልጸዋል:: የእውነተኛ ክርስቲያኖች መገለጫ ምንድር ነው ቢባል "ፍቅር" ተብሎ ሊጠቀለል ይችላል:: ጌታችንም ይህንን ሲያስረዳ "እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።" (ዮሐ 13:35) ብሎን ነበር:: ሰዎች ዛሬ ላይ አይተውን የክርስቶስ ደቀ-መዛሙርት ስለመሆናችን ቢጠረጥሩን አትደነቁ - እንደኛ ፍቅር ያጣ የለምና!
አንዳንዴ እድሜ ልካችንን ክርስቲያን መሆናችንን እያወጅን እግዚአብሔርን ግን ላናውቅ እንችላለን:: 'ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?' ልትሉኝ ትችላላችሁ:: ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ የዚህን መልስ ሲሰጠን:- "ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።" (1 ዮሐ 4:8) ይለናል:: ክርስቲያን መሆናችንን ለዓለም ሁሉ ልናውጅ እንችላለን፤ ፍቅር ከሌለን ግን አዋጁ ሁሉ ከንቱ ነው:: ይህ ምን እንደሚያሳጣን ልብ በሉ:: ሐዋርያው "ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።" (2 ዮሐ 1:9) ይለናል:: እንግዲህ የክርስቶስ ትእዛዝ ፍቅር ከሆነ፤ እኛ ደግሞ ፍቅር ካጣን፤ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል ብለን እየፎከርን ክርስቶስን አጣነው ማለት አይደለም? ክርስቶስን ካጣን ደግሞ አብም ሆነ መንፈስ ቅዱስ አጣን ማለት አይደለም?
ለክርስቲያን ከዚህ በላይ ኪሳራ ምን ይኖር ይሆን?
እንኳን ለወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
? Fresenbet G.Y Adhanom
----------
የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib
ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett
የእንግሊዙ መሪ የነበሩት ዊንስተን ቸርችል እጅግ አንደበተ ርቱዕ፥ ሲናገሩ የሚያፈዙ፥ ጨዋታም ጭምር አዋቂ ናቸው ይባልላቸዋል። እርሳቸው ንግግር ሊያደርጉ ነው የተባለ እንደሆነ፥ ሰው ሁሉ ካለበት መጥቶ ተሰብስቦ ያዳምጣቸው ነበር። በአንድ ወቅት አንድ ጋዜጠኛ ሲጠይቃቸው፥ “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር፥ እርስዎ ንግግር ሲያደርጉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ የሚያዳምጥዎት መሪ ነዎት። ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስቦ ሲያዳምጥዎት ምን ይሰማዎት ይኾን?” ብሎ ጠየቃቸው። እርሳቸው ግን የሰውን ስነልቡና በደንብ ጠንቅቀው የተረዱ ብልህ ስለነበሩ፤ “ተፈርዶበታል ይሰቀል ቢባል ከዚህ በላይ ሕዝብ አይሰበሰብም ብለህ ነው?” ብለው መለሱለት ይባላል።
ታላቁ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ወልደሕይወት ሲመክር እንደ ንብ ሁኑ ይላል። ንብ መልካም መልክ እና መዓዛ ካላቸው አበቦች ስትደክም ውላ ማር ትሠራለች። እርሷ የሠራችው ማር፥ ከራሷ አልፎ ሌላውን ይመግባል። የራሷን እድሜ ተሻግሮ ከአንድ ሺህ ዓመት በላይም ሳይበላሽ ይቆያል። በዚህ ‘ዘመናዊ’ በተባለው ዘመን ግን የሰው ልጅ ከንብ ይልቅ የዝንብን ጠባይ እየተዋረሰ መሄዱን ማሰብ ያሳዝናል። ይህንን ለማወቅ ወደ ዩቲዩብ ጎራ ብሎ በብዙ መቶ ሺህ እይታዎች ያላቸውን ቪዲዮዎች ርእስ ማንበብ በቂ ነው። ከሚጠቅመን ምክር ይልቅ የሚጎዳንን አሉባልታ፥ ከሚያንጸን ትምህርት ይልክ የሚያውከንን ዜና ለመስማት እንከጅላለን። የተወደዱት ሲጠሉ፥ የተከበሩት ሲዋረዱ፥ የተመረቁት ሲረገሙ ለማየት ያለን ጉጉት ያስፈራል። የሰው ልጅ በታሪኩ ውስጥ የተከበሩትን ለማዋረድ የሮጠበት ጊዜ ብዙ ነው። ሰው አንዳንዴ ለጌታም አይመለስም። “ሆሳዕና” ያለ ሕዝብ መልሶ “ይሰቀል” ለማለት ብዙ ጊዜ እንዳልፈጀበት ማስታወስ መልካም ነው።
አንድ መምህር ወረቀት ላይ ነጥብ አስቀምጦ “ምን ይታያችኋል?” ብሎ ተማሪዎቹን ሲጠይቅ፤ እነርሱም “ጥቁር ነጥብ” ብለው መለሱለት። ሰፊ ቦታ የያዘው ነጩ ወረቀት ሆኖ ሳለ፥ ተማሪዎቹ ግን ያዩት ጥቁሩን ነጥብ ነው። ከብዙው መልካም ትንሿን ሕጸጽ አጉልቶ ማየት የሚያስገርም ነው። እኛም ብዙ ሰዎች ከመልካም ጎናቸው ሰዋዊ ድካማቸው ጎልቶ ይታየናል። የብዙ ዓመት ድካማቸውን በአንድ ቀን የተዛነፈ ሚዛን አሽቀንጥረን እንጥላለን። በመረቅናቸው አፍም መልሰን ስንረግማቸውም ለነገ አንልም። ዛሬ የመረቀ አንደበት፥ ነገ ተሳዳቢ ሆኖ ሲገኝ ያሳፍራል። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “ከአንድ አፍ በረከት እና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም።” (ያዕ 3፡10) ብሎ ይመክረናል። እኛም እንዲህ ብለን እንለምናለን - ጌታ ሆይ፥ ዛሬ መርቀውን ነገ ከሚሰድቡን፥ ዛሬ አልብሰውን ነገ ከሚገፍፉን፥ ዛሬ አቅፈውን ነገ ከሚነክሱን ጠብቀን!
? Fresenbet G.Y Adhanom
----------
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/fre.asalib
ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett
ሊንክድኢን፡ https://www.linkedin.com/in/fresenbet-g-y-adhanom/
ኢንስታግራም፡ https://www.instagram.com/fresenbet_et/
በአንድ ዘመን ላይ የተሻሉ የሚባሉት ሰዎች ካማረሩ ችግር በርትቷል ማለት ነው። አዋቂው ስለ እውቀት መጥፋት ከተናገረ፥ አማኙ ስለ እምነት መድከም ካዘነ፥ ሀብታሙ ስለ ኑሮ ውድነት ካነሳ የዘመኑን መክፋት ልክ ያሳያል። ከጌታ ልደት የቀደመውን ዘመን ስንመረምረው፥ እጅግ የከፋ የጨለማ ዘመን እንደነበር የምንገነዘበው “የነቢያት አክሊል” የሚባለው ነቢዩ ኢሳይያስ ስንኳ “ሁላችን እንደ ረከሰ ሰው ሆነናል፤ የጽድቅ ሥራችን እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችን እንደ ቅጠል ረግፈናል፤ ኀጢአታችንም እንደ ነፋስ ጠራርጎናል።” (ኢሳ 64፡6) እያለ ሲያዝን ስናገኘው ነው። ከፈጣሪው ጋር ቃል በቃል የሚነጋገር ነቢይ እንዲህ ካለ፥ ‘ለምዕመኑማ ምን ያህል በርትቶበት ይኾን?’ ያሰኛል።
የሀገራችን ሰው ሲተርት ‘ሲያልቅ አያምር’ ይላል። እውነትም ዘመኑ እያለቀ ነው መሠል፤ ነገሮች ሁሉ እየተበላሹ ነው። ዓለማችን እንደ ሃያኛው እና ሃያ አንደኛው ክፍለዘመን ስለ ሰላም የጮኸችበት ጊዜ የለም። በዚያው ልክ እንደ እነዚህ ዘመናትም ሰላምን ያጣችበትም ጊዜ የለም። የብዙ ሰው ሕይወት መከራ ተዘርቶ መከራ የሚታጨድበት አውድማ ሆኗል። ጦርነት ባይኖር ስንኳ፤ በልቶ መጥገብ፥ ጠጥቶ መርካት፥ ተኝቶ ማረፍ ያልተቻለበት ሕይወት የቁም ስቃይ መሆኑ አይቀርም። አንዱ የዚህ ማሳያ በተለያየ ምክንያት ራሱን የሚያጠፋው ሰው መበራከት ነው። ‘እገሌኮ ራሱን አጠፋ’ ሲባል፥ አንዳንድ ሰው ‘በራሱ ላይ እንዴት እንዲህ ጨከነ?’ ብሎ ይገረማል። ሰው ሁሉ ነገር ሐዲድ ሲስተበት ራሱን ባያጠፋ ስንኳ ሞቱን ይመኛል። ዘመን ሲከፋ፥ ጊዜ ሲጠም፥ አቅም ሲከዳ፥ የእግዚአብሔር ነቢይ ስንኳ “አቤቱ፥ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና፥ ነፍሴን ውሰድ” (1 ነገ 19፡4) ብሎ ሞትን በፈቃዱ ይጠራል።
እንዲህ ያለን ዘመን ያለ ተስፋ መሻገር አይቻለም። ተስፋ ከመጀመሪያው ዘመን ጀምሮ የሰው ልጅ ስንቅ ሆኖ እስከዛሬ አለ። አዳምና ሔዋን እግዚአብሔርን ከመሠለ አባታቸው እና ገነትን ከመሠለ ቤታቸው ሲለዩ፥ እግዚአብሔር “ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔዴን ገነት አስቀመጠ” (ዘፍ 3፡24) ተብሎ ተጽፏል። ሊቃውንት ይኽንን ሲተረጉሙት እግዚአብሔር በመላእክት ያስጠበቀበት አንዱ ምክንያት አዳም "እግዚአብሔር ፈጽሞ ቢጣላኝ ኖሮ ገነትን ለሌላ ይሰጥብኝ ነበር እንጂ በመላእክት አያስጠብቀውም ነበር ብሎ ተስፋ እንዳይቆርጥ ነው" ይላሉ። ተስፋ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ታላላቅ ስጦታዎች መካከል አንዱ ነው። ዙሪያ ገባችን ሲጨልም ብርሃን እንዳለ የሚያስታውሰን ተስፋ ነው። ሐዘን ሲበረታበን እንደሚያልፍ ሹክ የሚለን ተስፋ ነው። ሰው በብዙ ነገር ‘ክፉ ነው’ ሊባል ይችላል፤ ተስፋን ከሌላው እንደሚነጥቅ ያለ ክፉ ግን በየትም የለም።
ቅዱስ ጳውሎስ “እምነት፥ ተስፋ፥ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ” (1 ቆሮ 13፡13) በማለት ሦስት ጸንተው ከሚኖሩ ነገሮች መካከል ተስፋን ያካትተዋል። ተስፋን ለየት የሚያደርገው ግን ከእምነትም፥ ከፍቅርም ጋር ተገምዶ የሚገኝ በመሆኑ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እምነትን በራሱ “ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ” (ዕብ 11፡1) መሆኑን በመናገር ተስፋን ከእምነት ይገምደዋል። በሌላ መልእክቱ ደግሞ “በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ፥ ተስፋ አያሳፍርም።” (ሮሜ 5፡5) ብሎ ፍቅርን ከተስፋ ይገምደዋል። ጠቢቡ “በሦስት የተገመደ ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም” (መክ 4፡12) እንዳለ፤ እምነትን ከተስፋ፥ ተስፋን ደግሞ ከፍቅር ጎንጉኖ የሚኖር አማኝም ክፉ ዘመንን የሚሻገርበትን ብልሃት ይዟል ማለት ነው። ሦስቱም ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ ሲሆን ይጸናል። እምነትህን በእግዚአብሔር ላይ ከሆነ፤ ክፉውን ጊዜ ታልፈዋለህ። ተስፋህን በእግዚአብሔር ላይ ካደረግህ፥ በወደቁት መካከል ትቆማለህ። ፍቅርህ ለእግዚአብሔር ከሆነልህ፤ የጽድቅን ብርሃን ትለብሳለህ።
ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ፥ በዚህ ዘመን፤ የሰው ልጅ በስልጣኑ፥ በሀብቱ፥ በትምህርቱ ይቅርና በቆመበት መሬት ላይ ስንኳ ተስፋ ማድረግ እንደማይችል እያየ ነው። በድንግዝግዙ ውስጥ የምናይበት የማይጠፋ ብርሃናችን፥ በመናወጹ ውስጥ የምንቆምበት የማይናወጽ ዐለታችን አንተ ብቻ ነህ። ለአዳም በሐዘን፥ ለኖኅ በቃልኪዳን፥ ለአብርሃም በስደት፥ ለሙሴ በበረሃ፥ ለዮሴፍ በእስር ቤት፥ ለሩት በሰው ሀገር የሰጠኸውን ተስፋ ለእኛም በያለንበት አትንሳን።
? Fresenbet G.Y Adhanom
----------
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/fre.asalib
ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett
ሊንክድኢን፡ https://www.linkedin.com/in/fresenbet-g-y-adhanom/
ኢንስታግራም፡ https://www.instagram.com/fresenbet_et/
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።
@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna
#ኢትዮጵያ
Last updated 2 months, 3 weeks ago
Last updated 2 months, 2 weeks ago
ይህ ስለ Manchester United መረጃዎችን የሚያገኙበት የ Telegram ቻናል ነው 🇪🇹
--------------------------------------------------------------
☞︎| ስለ ማንቸስተር ዩናይትድ ትኩስ መረጃዎች
☞| ቀጥታ ስርጭቶች ከየስታድየሞቹ
☞| የዝውውር ዜናዎች
☞| ስለ ማንችስተር ዩናይትድ ታሪኮች
📩 ለማስታወቂያ ስራ DM :- @Marcoabdu
Last updated 1 month, 1 week ago