ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።
@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna
#ኢትዮጵያ
Last updated 2 months, 1 week ago
Last updated 6 days, 22 hours ago
ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ ? @Esat_tv_comment_bot
??ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ??
Last updated 2 months, 3 weeks ago
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ኅዳር 25-የታላቁ ሰማዕት የቅዱስ መርቆሬዎስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ‹‹መርቆሬዎስ›› ማለት የአብ ወዳጅ ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ወላጆቹ አስሊጥ ከምትባል ሀገር ቢሆኑም እርሱ ግን ተወልዶ ያደገው በሮሜ ከተማ ነው፡፡ አያቱና አባቱ ሥራቸው አውሬ ማደን ስለነበር አንድ ቀን እንደልማዳቸው አውሬ ሲያድኑ ከገጸ ከለባት ወገን የሆኑ ሁለት ወንዶች አግኝተዋቸው የመርቆሬዎስን አያት በሉት፡፡
አባቱንም ሊበሉት ሲሉ የታዘዘ መልአክ ከለከላቸው፡፡ ዙሪያቸውንም በእሳት አጥሮ ከበባቸው፡፡ እነርሱም በተቸገሩ ጊዜ ለመርቆሬዎስ አባት ሰገዱለት፡፡ በዚያን ጊዜም እግዚአብሔር ፍጥረታቸውን ወደገራምነት ለወጠውና እንደበጎች የዋሆች ሆነው አብረውት ወደ መንደር ገቡ፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርቆሬዎስ ተወለደና ስሙ ፒሉፓዴር ተባለ፡፡ የውሻ መልክ ያላቸውም በእርሱ ዘንድ ብዙ ዘመናት ኖሩ፡፡ ከዚህም በኋላ ክርስቲያኖች ሆኑ፡፡ የቅዱስ መርቆሬዎስም ወላጆች አስቀድመው አረማውያን ነበሩና የክርስትና ጥምቀትን በጸጋ ተቀበሉ፡፡ አባቱን ኖህ እናቱንም ታቦት ብለው ሰየሟቸው፡፡
ቀድሞ ፒሉፓዴር የነበረውም ስሙ ተለውጦ መርቆሬዎስ ተባለ፡፡ የውሻ መልክ ያላቸው ግን መልአኩ በተገለጠላቸው ጊዜ እንደነገራቸው ለቅዱስ መርቆሬዎስ አባት የሚታዘዙና የሚያገለግሉ ሆኑ፡፡ ንጉሡም የመርቆሬዎስን አባትና የውሻ መልክ ያላቸውን ዜናቸውን ሲሰማ ወታደሮቹን ልኮ በፊቱ አቆማቸው፡፡ እግዚአብሔርም የቀድሞ ፍጥረታቸውን መልሶላቸው አራዊት አደረጋቸውና ንጉሡን እጅግ አስፈሩት፡፡ ንጉሡም የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት የአራዊት ተፈጥሮአቸውን ያርቅለት ዘንድ ለመነው፡፡ የቅዱስ መርቆሬዎስም አባት በለመነ ጊዜ ተፈጥሮአቸውን መልሶላቸው ገራሞች ሆኑ፡፡
ንጉሡም የመርቆሬዎስን አባት ገዥና የሠራዊቱ አለቃ አድርጎ ሾመው፡፡ የውሻ ፊት ያላቸውም አብረው ያገለግሉት ስለነበር ሁሉም ይፈራው ነበር፡፡ ንጉሡም የመርቆሬዎስን አባት ወደ ጦርነት ከላከው በኋላ ሳይመለስ ስለቀረ ሚስቱን ሊያገባት አሰበ፡፡ የመርቆሬዎስ አባትም የመርዶሳውያን አገሮች ሁሉ ገዢ በነበረው ንጉሥ ተይዞ ቢማረክም ገዥው ክርስቲያን መሆኑን አይቶ አከበረው፡፡ ቆይቶም በሀገሩ ላይ ሾመው፡፡ ሚስቱም ጠፍታ ከሀገሯ ወጥታ ሄዳ ስለነበር ከባሏ ተገናኝተው በዚያው መኖር ጀመሩ፡፡ መርቆሬዎስም አባቱና እናቱ ከሞቱ በኋላ ንጉሡ በአባቱ ፈንታ በመርዶሳውያን አገር ላይ ሾመው፡፡
መርቆሬዎስ መኰንንነት በተሾመም ጊዜ ገጸ ከለባቱ አብሮት ነበር፡፡ ለመዋጋትም በወጣ ጊዜ የቀድሞው የአራዊት የሆነ ተፈጥሮውን እግዚአብሔር ይመልስለት ስለነበር ማንም አይቋቋመውም ነበር፡፡ ለቅዱስ መርቆሬዎስ ታላቅ የድል አድራጊነት ኃይል ተሰጠውና ዜናው በሁሉም ሀገሮች ተሰማ፡፡ በሮሜ ሀገር ጣዖትን የሚያመልከው ዳኬዎስ የተባለውም ንጉሥ የበርበር ሰዎች ጋር ጦርነት ሊገጥም በወጣ ጊዜ እጅግ ሲበዙበት ፈራ፡፡ ቅዱስ መርቆሬዎስም በጦሩ መሀል የተሳለ ሰይፍ የያዘ የእግዚአብሔርን መልአክ ስላየ ንጉሡን እግዚአብሔር ያጠፋቸዋልና አትፍራ›› አለው፡፡ መልአኩም ሰይፉን ለቅዱስ መርቆሬዎስ ሰጠውና ‹‹ጦርነቱን ድል ባደረግህ ጊዜ እግዚአብሔርን አስበው›› አለው፡፡ ጦርነቱን ድል አድርጎ ሲጨርስም መልአኩ ድጋሚ ተገልጦለት ‹‹ለምን የፈጣሪህን ስም መጥራት እረሳህ?›› አለው፡፡ ከጦርነቱም በኋላ ንጉሥ ዳኬዎስ ለጣዖታቱ ዕጣን በማሳረግ በዓልን አደረገ፡፡ ቅዱስ መርቆሬዎስም በዚያ ስላልተገኘ ለጣዖታቱ ዕጣን በማሳረጉ እንዳልተባበረ ንጉሡ ሲያውቅ መልእክተኞችን ልኮ አስመጣው፡፡ ንጉሡም ‹‹ከእኔ ጋር ለምን አታጥንም?›› ባለው ጊዜ ቅዱስ መርቆሬዎስ ትጥቁንና ልብሱን አውልቆ ከወረወረለት በኋላ ‹‹ክብር ይግባውና አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጽሞ አልክደውም፣ ለረከሱ ጣዖቶችህም አልሰግድም›› አለው፡፡ ንጉሡም ተናዶ ልዩ ልዩ በሆኑ ሥቃዮችም እጅግ አሠቃየው፡፡
ንጉሡም ስለ መርቆሬዎስ ብለው የአገሩ ሰዎች እንዳይነሱበት ፈርቶ በብረት ችንካር ቸንክሮ የቀጵዶቅያና የእስያ ክፍል ወደሆነች ወደ ቂሳርያ ከደብዳቤ ጋር ላከው፡፡ በዚያም እጅግ ካሠቃዩት በኋላ ንጉሡ ዳኬዎስ እንዳዘዘ ኅዳር 25 ቀን አንገቱን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነት ተጋድሎውን ፈጸመ፡፡ የሕይወትንም አክሊል ተቀዳጀ፡፡ በዓለሙ ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ታነጹለት፡፡
እግዚአብሔርም ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን በቅዱስ መርቆሬዎስ ስም አደረገ፡፡ ከብዙ ተአምራቱም አንዱ የቂሳርያውን ሊቀ ጳጳስ ባስልዮስን እረድቶ ከሃዲውን ዑልያኖስን የገደለበት ነው፡፡ ዑልያኖስ ነግሦ የክብር ባለቤት ጌታችንን ክዶ ጣዖታትን ማምለክና ክርስቲያኖችን ማሠቃየት ጀመረ፡፡ የቂሳርያው ሊቀ ጳጳስ ባስልዮስም አስተምሮ ሊመልሰው ወደ ንጉሡ ቢመጣ ክብር ይግባውና ዑልያኖስ ጌታችንን ሰድቦ ባስልዮስንም አሰረው፡፡
ባስልዮስም በእሥር ቤት ሳለ በቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕል ፊት ጸለየ፡፡ ሥዕሉም ወዲያው ተሰወረው፡፡ ያንጊዜም ወደ ከሃዲው ንጉሥ ዑልያኖስ ዘንድ ሄዶ በጦር ወግቶ ገደለውና ወዲያው ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡ ከጦሩም አንገት ደም ይንጠፋጠፍ ነበር፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም ከሃዲውን ንጉሥ እንደገደለው ዐውቆ ‹‹የክርስቶስ ምስክር ጌታዬ ሆይ የእውነት ፀር የሆነ ዑልያኖስን ገደልከውን?›› አለው፡፡ ሥዕሉም ያን ጊዜ አዎን እንደሚል ራሱን ዘንበል አደረገ፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም ደስ ብሎት እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡
ሌላው የሰማዕት የቅዱስ መርቆሬዎስ ተአምር ከእስልምና እምነት መልሶ ክርስቲያን ያደረገው አንድ ኢስላም ሰው አለ፡፡ ይኸውም የመሐመድን መቃብር ለመሳለም በሔደው ኢስላም ላይ ያሳየው ታላቅ ተአምር ነው፡፡ ሙሉ ታሪኩን ነገ ላይ እናየዋለን፡፡
ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን!
የታላቁን ሰማዕት የቅዱስ መርቆሬዎስ ረድኤት በረከቱ ይድርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
ከገድላት ከንደበት
✞ ✞ ✞
አባቶቻችን በምድራዊው አገልገሎት ሳይወሰኑ ወደ ሰማየ ሰማያትም ወጥተው ከቅዱሳን መላእክት ጋር አገልግሎታቸውን ፈጽመዋል።
ኅዳር 24 ቀን አባታችን ተክለሃይማኖት ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የሥሉስ ቅዱስን መንበር ያጠኑበት ዕለት ነው፡፡ የመላእክት ምግባቸው ሥላሴን ማመስገን ነውና በቅዱስ ዳዊት "የመላእክትን ምግብ ሰዎች ተመገቡት" የተባለው ቃል በአባቶቻችን በእነ ቅዱስ ያሬድ በእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተፈጽሟል። በጸሎታቸው የቅድስት ሀገራችንን ትንሣኤ ያቅርብልን!
እንኳን ለ24ቱ ካህናተ ሰማይ እና ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓል አደረሰን አደረሳችሁ!!!
በዚኽች ዕለት ኅዳር 24 በዓመታዊ በዓላቸው ስታስበው የሚውሉት ቅዱሳን አባታቶቻችን አቡነ ተክለሃይማኖትና አቡነ ዜና ማርቆስ በጋራ ይኽን ታላቅ ተኣምር አደረጉ፦ አቡነ ዜና ማርቆስ ወግዳ በምትባል ሀገር ሄደው በዋሻ ውስጥ ሳሉ አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ እርሳቸው መጥተው አብረው በዋሻው ብዙ ተአምራትን እያደረጉ ቆይተዋል፡፡ ለአባ ዜና ማርቆስና ለሌሎች ለብዙ አባቶች የምንኩስና አባት የሆኑት አቡነ ተክለሃይማኖት ትሕትናቸውን ያሳዩ ዘንድ አቡነ ዜና ማርቆስን ያገለግሏቸው ነበር፡፡ ወደ ሞረት ሀገር እንዲሄዱ መልአክ ነግሯቸው ሁለቱም ሄደው በዚያም አብረው ተቀምጠዋል፡፡ ጣዖት አምላኪውን የሞረቱ ገዥ ሊገድላቸው ፊልጎ ከነሠራዊቱ ወዳሉበት ዋሻ ሄደ፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስም ተራራዋን በሥላሴ ስም ባርከው ቢያዟት የገዥውን ጭፍሮች አፏን ከፍታ ዋጠቻቸው፡፡ ገዥውን ድል አሰግድንም በተአምራቸው አሳምነውት አስተምረው አጠመቁት፡፡
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ለአቡነ ተክለሃይማኖት ተገልጦላቸው ወደ ግራርያ ሀገር እንዲሄዱ ስለነገራቸው አቡነ ተክለሃይማኖት የመላእክትን አስኬማ ለአቡነ ዜና ማርቆስ አልብሰዋቸው ዜና ማርቆስንም በደብረ ብስራት እንዲጸኑ ነግረዋቸው ወደ ግራርያ ሄዱ፡፡ ሲሄዱም የደብረ ብስራት ዛፎቹ እንጨቶቹና ደንጊያዮቹ ሁሉ አቡነ ተክለሃይማኖትን እንደ ንጉሥ ሠራዊት ከፊት ከኋላ ሆነው ሸኝተዋቸዋል፡፡ አባታችንም ‹‹የወንድሜን የዜና ማርቆስን ቦታ ትታችሁ ከዚህች ምድር ትሄዱ ዘንድ አልፈቅድምና ሁላችሁ በየቦታችሁ ቁሙ›› ብለዋቸዋል፡፡ ‹‹ሰውም እንኳ ቢሆን ለምንኩስና ወደ እኔ ዘንድ ወደ ግራርያ ከመምጣቱ በፊት ይህን ምድር ሳይሳለም ወደ እኔ አይምጣ›› በማለት ቃልኪዳናቸውን ከደብረ ብስራት ጋር አድርገዋል፡፡
አባታችን ዜና ማርቆስ በሕይወተ ሥጋ ሣሉ የሚያደርጓቸው እጅግ ድንቅ የሆኑ ተአምራት በሕዝብ ዘንድ ውዳሴን እያመጣ እንዳያስቸግራቸው ብለው ይህን ድንቅ ተአምር ማድረግን እግዚአብሔር እንዲያርቅላቸው ለመኑት፡፡
+ + +
ዳግመኛም ኹለቱ ቅዱሳን አባታቶቻችን አቡነ ተክለሃይማኖትና አቡነ ዜና ማርቆስ በጋራ ይኽን ታላቅ ተኣምር አደረጉ፦ ሠምረ ክርስቶስ አስቀድሞ የሞረት አገረ ገዢ ሎሌ የነበረ ሲኾን ከኹለት ባልንጀሮቹ የሀገረ ገዢው ሎሌዎች ጋራ ለአደን ይወጣሉ። የኼዱትም ጻድቅ አቡነ ዜና ማርቆስ እና ጻድቅ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት የነበሩበት ዋሻ ጋር ነበር። እዚያም እንደደረሱ ከላይ ኹነው ወደታች ጻድቃኑን ቢመለከቷቸው ኹለቱ ታላላቅ ጻድቃን ለጸሎት ተግተው ቁመው ተመለከቷቸው። ኋላም "እናንተ፣ ከሲህ ምን ታደርጋላችሁ ዋሽውን ትታችሁ ከዚህ ኺዱልን" ሲሏቸው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ወደነርሱ በሰው ተመስሎ ከሰማይ ወርዶ እነዚያን የሀገረ ገዢውን ሎሌዎች አነጋገራቸው። "እነዚህ የምትመለከቷቸው ኹለት ሰዎች እናንተ እንደምታስቡት ለአደን የመጡ አይደለም። ወደ አምላካቸው ወደ ሰማይ በጸሎታቸውና በቅድስናቸው ክንፎች የሚበርሩ ናቸው" አላቸው። ስለዚህ ሰማያዊ አምላክና እኒህም ቅዱሳን ስለሚበሩባቸው ክንፎስ መመራመርና መጠየቅ ሲጀምሩ መልአኩ ወርደው ይመለከቱ ዘንድ ጠራቸው። ከእነዚያም ሦስት ሎሌዎች አንደኛው ሠምረ ክርስቶስንም ከላይ ወደ ቅዱሳኑ ቦታ እንዲወርድ ሲጠራው "ወርጄስ አልመጣም፣ እነዚህ ሰዎች ታምነውበት ወደ ሰማይ የሚበሩበትን ክንፍ የሰጣቸው አምላክ ለእኔም ይስጠኝ ብሎ ከተራራው ወደ ዋሻው ወደታች ተወረወረ"። ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኒትም ክንፉን ዝውርግቶ ተቀበለውና በእግሮቹ አቆመው። ጻድቅ አቡነ ዜና ማርቆስ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ክንፎች የተመለከተው በዚህ ጊዜ ነበርና አደነቀ።
በኋላም ከእነርሱ ዘንድ ይህን በክንፎች በረው በርረው ወደርሱ እንዲመጡ የሚያደርጋቸው አምላክ እንዲገለጥለትና እንዲያየው ሲጠይቃቸው ቆየ። በኋላም አቡነ ዜና ማርቆስ አምላካችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አጽንቶ ቢማጸን ስለአቡነ ዜና ማርቆስ ሲል ጌትቅችን ከእመቤታችን እና ከቅዱሳኑ ጋር ወደዚያች ተራራ መጣ። ያን ጊዜም ተራራዋ ሦስት ጊዜ ተንቀጠቀጠች። እፈርስ እፈርስ አለች። ጌታችንም በቅፉስ ቃሉ አጸናት። ጻድቃን አበው አቡነ ዜና ማርቆስን እና አቡነ ተክለ ሃይማኖትንም ሰላም ካላቸው በኋላ አጽንቷቸውና ያቺንም ቦታ ባርኳት ዐረገ። በዚህም ጊዜ በተመለከተው ነገር ሠምረ ክርስቶስ አመነ። ጌታችንም ከማረጉ በፊት ሠምረ ክርስቶስን ለአቡነ ዜና ማርቆስ አደራ ሰጠው። አቡነ ዜና ማርቆስም ሠምረ ክርስቶስን አጥምቆ አመነኰሰው። የቀድሞ ስሙንም ለውጦ ሠምረ ክርስቶስ አለው። እርሱም በጽኑዕ ገድል ጸንቶ ሲጋደል ቆይቶ ጥቅምት 3 ቀን ዐርፏል።
ምንጭ፦ ገድለ አቡነ ተክለሃይማኖት እና ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ)
የቅዱሳን አባታቶቻችን የአቡነ ተክለሃይማኖት፣ የአቡነ ሊባኖስና የአቡነ ዜና ማርቆስ ጸሎታቸውና በረከታቸው ከሁላችን ከክርስቲያን ወገኖች ጋር ይኑር ለዘለዓለም አሜን፡፡
✞ ✞ ✞
ታላቁ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ በተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፉ ላይ በዚኽች ዕለት በዓመታዊ በዓላቸው የሚታሰቡትን የሃያ አራቱን ካህናተ ሰማይ ስማቸውን እንዲህ በማለት ይጠቅሳቸዋል፦ "በአብ መንበር ዙሪያ ላሉ ለሃያ አራቱ ሰማያውያን ካህናት ሰላምታ ይገባል፤ በእጆቻቸው ውስጥ ላለ ማዕጠንትም ሰላምታ ይገባል፤ በራሶቻቸው ላይ ላሉ አክሊላትም ሰላምታ ይገባል፤ አካኤል፣ ፋኑኤል፣ ጋኑኤል፣ ታድኤል፣ እፍድኤል፣ ዘራኤል፣ ኤልኤል፣ ተዳኤል፣ ዮካኤል፣ ገርድኤል፣ ልፍድኤል፣ መርዋኤል፣ ኑራኤል፣ ክስልቱኤል፣ ኡራኤል፣ ባቱኤል፣ ሩአኤል፣ ሰላትኤል፣ ጣውርኤል፣ እምኑኤል፣ ፔላልኤል፣ ታልዲኤል፣ ፐስልዱኤል፣ አሌቲኤል ለተባሉ ስሞቻቸውም ሰላምታ ይገባል" (አባ ጊዮርጊስ፣ ተአምኆ ቅዱሳን)
ዮሐ ራእ 4፡4፣ 4፡10 "በዙፋኑ ዙሪያም ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፣ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሃያ አራት ሊቃናት ተቀምጠው ነበር… ሃያ አራቱ ሊቃናት በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ 'ጌታችንና አምላካችን ሆይ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብርን ውዳሴንና ኀይልንም ልትቀበል ይገባሃል' እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ"
"ብርሃንን የለበሱ ዕጣንንም የተሸከሙ የቅዱሳንን ጸሎት ወደ መሠዊያህ ፊት የሚያቀርቡ ዐሥራ ኹለቱ ከቀኝ ዐሥራ ኹለቱ ከግራ የሚቆሙ ለጌትነትኽም ምስጋና ጽዋዎችን የሚያቀርቡ ሰማያውያን ካህናት ይምጡ፤ ቊጥራቸው ሃያ አራት ነው ወንበሮቻቸውም ሃያ አራት ናቸው፣ አክሊሎቻቸውም ሃያ አራት ናቸው፤ ማዕጠንቶቻቸውም ሃያ አራት ናቸው" (አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ ኆኅተ ብርሃን)
የልዑል እግዚአብሔርን ዙፋን የሚያጥኑ ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ በማዕጠንታቸው ጸሎታችንን ወደ ጸባኦት ዙፋን ያሳርጉልን፣ ከበዓላቸው በረከት ይክፈለን።
(ምንጭ፦ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ተአምኆ ቅዱሳን ንባቡና ትርጓሜው መጽሐፍ፣ መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ)
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ኤላውትሮስ ምግባር ሃይማኖቱ፣ ተጋድሎ ትሩፋቱ ያመረ የሰመረ ነውና ገና በ20 ዓመቱ አላሪቆስ ለሚባል አገር ጵጵስና ተሾመ፡፡ እርሱም ምእመናንን እያስተማረ በበጎ ጎዳና የሚመራቸው ሆነ፡፡
ከዚህም በኋላ የቅዱስ ኤላውትሮስ ምግባር ሃይማኖቱ
ቅድስናውና ትምህርቱ በሁሉ ዘንድ ተሰማ፡፡ በዚያም ወራት
ከሃዲው ንጉሥ እንድርያኖስ ወደ ሮሜ አገር በመጣ ጊዜ
የቅዱስ ኤላውትሮስን ዜና ሰማ፡፡ ወደ እርሱም ያመጣው ዘንድ መኮንኑን ፊልቅስን ላከው፡፡ ፊልቅስም በሄደ ጊዜ ቅዱሱን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምእመናንን ሲያስተምር አገኘውና ትምህርቱን ቢሰማ ልቡ ቀልጦ በዚያው በጌታችን አምኖ ተጠመቀ፡፡
ንጉሡም ሌሎች ጭፍሮቹን ልኮቅዱስ ኤላውትሮስ ወደ እርሱ ካስመጣው በኋላ ‹‹ለአማልክት ሠዋ፣ አንተ ነፃነት ያለህ ስትሆን ለተሰቀለ ሰው ለምን ትገዛለህ›› አለው፡፡ ቅዱስ ኤላውትሮስም ‹‹ነፃነትማ ሰማይንና ምድርን በፈጠረ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ነው›› አለው፡፡ በዚህም ጊዜ ንጉሡ ተናደደና ቅዱሱን ሰውነትን የሚቆራርጥ መንኮራኩር ካለው የእሳት ማንደጃ ውስጥ እንጨምሩት አዘዘ፡፡ ቅዱስ ኤላውትሮስንም በጨመሩት ጊዜ እሳቱ ፈጽሞ ጠፋ፣ መንኮራኩሩም ስብርብሩ ወጣ፡፡ ንጉሡም ይህን አይቶ አደነቀ፣ የሚደርገውንም እስኪያስብ ድረስ ወህኒ ቤት ውስጥ ጣለው፡፡
ቅዱስ ኤላውትሮስ በወህኒ ቤት ሳለ የታዘዘች ርግብ ከገነት
መብልን አምጥታለት እርሱን ተመግቦ ሰውነቱ ታደሰ፡፡ ቆሊሪቆስ የሚባለው መኮንንም ይህን በግልጽ አይቶ በማድነቅ ‹‹በቅዱስ ኤላውትሮስ አምላክ አምኛለሁ›› ብሎ መስክሮ በሰማዕትነት አንገቱን ተሰይፎ የክብር አክሊልን ተቀዳጀ፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሡ ቅዱስ ኤላውትሮስን በፈረሶች ሠረገላ ላይ አስረው ሥጋው ተቆራርጦ እስኪያልቅ ድረስ ፈረሶቹን በቦታው ሁሉ እንዲያስሮጧቸው አዘዘ፡፡
እንደትእዛዙም በቅዱስ ኤላውትሮስ ላይ ይህንን ባደረጉ ጊዜ ሥጋው ተቆራርጦ ወደቀ፡፡ ወደጌታችንም በጸለየ ጊዜ መልአኩን ላከለት፡፡ መልአኩም የቅዱሱን ሥጋ ከፈረሶቹ ሠረገላ ላይ ነጥቆ ወስዶ በአንድ ከፍተኛ ተራራ ላይ አስቀመጠው፡፡ ቅዱስ ኤላውትሮስም እግዚአብሔርን እያመሰገነ ከአራዊት ጋር በዚያ ተቀመጠ፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ቀን የንጉሥ እንድርያኖስ ጭፍሮች
አራዊትን ያድኑ ዘንድ ወደዚያ ተራራ ሲወጡ ቅዱስ ኤላውትሮስን አገኙትና ወስደው ለንጉሣቸው ሰጡት፡፡ ንጉሡም ለተራቡ አንበሶች ሰጠው ነገር ግን አንበሶቹ እግሮቹን ሳሙለት የፊቱንም ልብ ጠረጉለት እንጂ አልነኩትም ይልቁንም ወደ ንጉሡ ሠራዊት ፈጥነው ተመልሰው 150 ሰዎችን ገደሉ፡፡ ንጉሥ እንድርያኖስም ይህንን አይቶ እጅግ በቁጣ ተመላ፡፡ ወታደሮቹንም ጠርቶ ቅዱስ ኤላውትሮስን ከቅድስት እናቱ ጋር በጦር እንዲወጓቸው አዘዘ፡፡ እናቱን ቅድስት እንትያንንም እንልጇ ብዙ ካሠቃዩአት በኋላ
የልጇን አንገት እንዳቀፈች ከእርሱ ጋር አንድ ላይ በጦር
ወጓቸውና ነፍሳቸውን በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ፡፡
ሰማዕትነታቸውንም ከፈጸሙ በኋላ የክብርን አክሊል ተቀዳጁ፡፡ ከሥጋቸውም ብዙ ተአምራ ተፈጽመው ታዩ፡፡
የሐዋርያውን የቅዱስ ፊሊጶስን፣ የቅዱሳት ደናግል
የአጥራስስንና የዮናን፣ የቅድስት እንትያንና የልጇን የቅዱስ
ኤላውትሮስን ረድኤት በረከታቸውን ያሳድርብን፣ በጸሎታቸው
ይማረን፡፡
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ኅዳር 18-ቁጥሩ ከ12ቱ ሐዋርያት የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ዳግመኛም በዚህች ዕለት ቅዱሳት ደናግል አጥራስስ እና ዮና በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡
+ ቅድስት እንትያ እና ልጇ ኤላውትሮስም እንዲሁ በዚሁ ዕለት ነው በሰማዕትነት ያረፉት፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ፡- ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ቁጥሩ
ከ12ቱ ሐዋርያት ውስጥ ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል 10፡3 ላይ እንተጠቀሰው ከ12ቱ ሐዋርያት ውስጥ በ5ኛ ደረጃ ተጠቅሷል፡፡
ከገሊላ የተገኘ የቤተ ሳይዳ ሰው ሲሆን የግሪክ ሰዎችን ወደ
ጌታችን ያቀረባቸው እርሱ ነው፡፡ ዮሐ 12፡20-22፡፡
ቅዱስ ፊሊጶስ ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤልን ‹‹የናዝሬቱን
ኢየሱስን አግኝተነዋል መጥተህ እይ…›› በማለት ወስዶ
ከጌታችን ጋር አገናኝቶታል፡፡ ዮሐ 1፡44-52፡፡ በኋላም ጌታችንን ‹‹አብን አሳየንና ይበቃናል›› ብሎ የጠየቀውም ይኸው ሐዋርያ ፊሊጶስ ነው፡፡ ይህም ጥያቄው ለእኛ ለሁላችን መሠረታዊውን የክርስትና እውቀት እንድናገኝ እረድቶናል፡፡ ጌታችንም ‹‹እኔን ያየ አብን አይቷል፣ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ›› በማለት ነው መልስ የሰጠው፡፡ ዮሐ 14፡8-14፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ወንጌልን ዞሮ በማስተማር ብዙዎች ጣዖት ማምለካቸውን ትተው በክርቶስ እንዲያምኑ አድርጓል፡፡
ከጌታችን ዕርገት በኋላ ሐዋርያው ፍርግያ፣ ሰማርያና ጋዛ
በሚባሉ አገሮች ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን አሳምኖ
አጥምቆአል፡፡ ሐዋርያው በመጨረሻ ወደ ታናሽዋ እስያ ሄዶ
በሄራፖሊስ ከተማ ሲያስተምር ብዙዎችን በማሳመኑ ክፉዎች ይዘው አሠቃዩት፡፡ ከብዙ ሥቃይም በኋላ ጣዖት አምላኪዎች ኅዳር 18 ቁልቁል ሰቅለውት ሰማዕትነቱን ፈጽሞ የድል አክሊልን ተቀዳጅቷል፡፡
ክፉዎችም በግፍ ከገደሉት በኋላ ሥጋውን በእሳት ሊያቃጥሉት በወደዱ ጊዜ የታዘዘ መልአክ የሐዋርያውን ቅዱስ ሥጋ ከእጃቸው ነጥቆ ወሰደባቸውና ሰወረው፡፡ ይህንንም ድንቅ ተአምር በተመለከቱ ጊዜ ሁሉም በአንድ ድምፅ ‹‹ከቅዱስ ፊልጶስ አምላክ በቀር ሌላ አምላክ የለም›› ብለው ጮኹ፡፡
አሠቀይተው ስለገደሉትም ተጸጽተው እጅግ አዘኑ፡፡ ክብር
ይግባውና በጌታችን ካመኑ በኋላ የሐዋርያው የቅዱስ ፊሊጶስን ቅዱስ ሥጋውን ይሰጣቸው ዘንድ በጸሎት ለመኑ፡፡ ሰውን የሚወድ ቸር ይቅር ባይ ጌታችንም የቅዱስ ፊሊጶስን ቅዱስ ሥጋውን መልሶ ሰጣቸውና እጅግ ተደሰቱ፡፡ ከሐዋርያውም ቅዱስ ሥጋ ብዙ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራት ተፈጸሙላቸው፡፡ የሐዋርያውም መካነ መቃብሩ እስካሁንም ድረስ በዚህች ከተማ ይገኛል፡፡ የሐዋርያው የቅዱስ ፊሊጶስን በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + +
ቅዱሳት ደናግል አጥራስስ እና ዮና፡- ይህችውም ቅድስት
አጥራስስ ጣዖትን ለሚያመልክ ንጉሥ እንድርያኖስ ልጁ ናት፡፡
ከሰው ወገን ማንም እንዳያያት አዳራሽ ውስጥ ለብቻዋ
አኖራት፡፡ እርሷ ግን ስለዚህ ዓለም ኃላፊነት የምታስብ ሆነች፡፡ እውነተኛውንና የቀናውን መንገድ ይመራት ዘንድ በቀንና በሌሊት እግዚአብሔርን ትለምን ነበር፡፡ በአንድ ቀን ሌሊት ‹‹ወደ ፍላጽፍሮን ልጅ ወደ ድንግሊቱ ዮና ላኪ፣ እርሷም የእግዚአብሔርን መንገድ ትመራሻለች›› የሚል
ራእይ አየች፡፡ በዚህም በልቧ እጅግ ደስ እያላት ወደ ድንግል
ዮና መልእክት ላከችና መጣች፡፡ አጥራስስም ከእግሯ ሥር
ወድቃ ከሰገደችላት በኋላ የእግዚአብሔርን ሃይማኖት
ታስተምራትና ትገልጥላት ዘንድ ለመነቻት፡፡
ድንግል ዮናም እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት እስከ ጌታችን ለፍርድ ዳግም መምጣት ድረስ ያለውን እውነተኛውን ሃይማኖት አስተማረቻት ይልቁንም የመድኃኔዓለም ክርስቶስን ሰው መሆንና መከራ መስቀሉን በነገረቻት ጊዜ አጥራስስ ልቧ ይቃጠል ነበር፡፡ በመጨረሻም ስለ ጌታችን ስለስሙ ብለው መከራን ለሚቀበሉና ለሚደክሙ ሁሉ ሰማያዊ ሀብት የዘላለም መንግሥትን እንደሚያወርሳቸው መጻሕፍትን እየጠቀሰች አስረዳቻት፡፡ አጥራስስም የዮናን ትምህርት በሰማች ጊዜ ደስ ተሰኝታ በጌታችን አመነች፡፡
ከዚህም በኋላ እነዚህ ሁለት ደናግል ሌትና ቀን በተጋድሎ
ተጠምደው በአንድነት ተቀመጡ፡፡ ጣዖት አምላኪው ንጉሡ
የአጥራስስ አባቷም ይህን አያውቅም ነበር፡፡ ደናግሉም
በአንድነት በተጋድሎ እየኖሩ ሳለ በአንዲት ዕለት ጌታችን
ተገለጠላቸው፡፡ ክብርት እመቤታችንም እንዲሁ
ተገለጠችላቸውና እንደ ቁርባን ለልጇ አቀረበቻቸውና እርሱም ባረካቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ንጉሡ ወደ ጦርነት ሄዶ በተመለሰ ጊዜ ወደ ልጁ አጥራስስ ገብቶ ‹‹ልጄ ሆይ! ወደ መሞሸሪያሽ ከመግባትሽ በፊት ለአምላክ ለአጵሎን ዕጣን ታሳርጊ ዘንድ ነይ›› አላት፡፡ በዚህም ጊዜ አጥራስስ ድንግል ‹‹አባቴ ሆይ! ነፍስህና ሥጋህ በእጁ ውስጥ የሆነ የፈጠረህን በሰማይ ያለ አምላክን ትተህነፍስ የሌላቸው የረከሱ ጣዖታትን ለምን ታመልካለህ›› ብላ ለአባቷ መለሰችለት፡፡ ንጉሡም ይህን ነገር ከዚህ በፊት ሰምቶ አያውቅም ነበርና ተደነቀ፡፡ በልጁም ላይ ምን እንደደረሰ ልቧንም ማን እንደለወጠው ሲጠይቅ የፍላጽፍሮን ልጅ ድንግል ዮና የልጁን ልብ እንደለወጠች ነገሩት፡፡ ንጉሡም ይህን ሲሰማ እጅግ ተቆጥቶ ደናግሉን ለአማልክቶቹ እንዲሰግዱና እንዲሠው ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ፈጽመው አልታዘዙትም ይልቁንም የረከሱ ጣዖቶቹን ረገሙበት፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሡ ልጁን ድንግል
አጥራስስንና ድንግል ዮናን በእሳት አሠቃይተው ይገድሏቸው
ዘንድ አዘዘ፡፡
በትእዛዙም መሠረት ትልቅ ጉድጓድ ቆፍረው በውስጡ እሳት
አነደዱ፡፡ የእሳቱም ነበልባል እጅግ ከፍ ከፍ አለ፡፡ ደናግሉንም
በወርቅና በብር የተጌጠ የግምጃ ልብሶችን እንደተሸለሙ ወደ እሳቱ ጉድጓድ አወጧቸው፡፡ ደናግሉ የነገሥታት ልጆች ናቸውና ከክብር ልብስ አላራቆቷቸውም፡፡ ቅድስት አጥራስስና ቅድስት ዮናም የሚነደውን የእሳት ነበልባል ባዩ ጊዜ ልባቸውን አጠነከሩ፡፡ የአገሪቱ ታላላቅ ወገኖችና ሕዝቡም ሁሉ ደናግሉ ጨክነው ሰውነታቸውን ለእሳት መስጠታቸውን ባዩ ጊዜ እያዘኑና እያለቀሱ ከሞት እንዲድኑና እምነታቸውን እንዲተው አጥብው ለመኗቸው፡፡ ቅድስት አጥራስስና ቅድስት ዮና ግን እጅ ለእጅ ተያይዘው ከጸለዩ በኋላ ወደ እሳቱ ውስጥ ዘለው ገቡ፡፡
ነፍሳቸውንም ለእግዚአብሔር አሳልፈው ሰጡ፡፡ እነርሱም
ሰማዕተነታቸውን ከፈጸሙ በኋላ እሳቱ ወዲያው ጠፋ፡፡ ቅዱሳት ደናግልም እሳቱ ፈጽሞ እንዳላገኛቸው ሆነው ተገኙ፡፡ የራስ ፀጉራቸው እንኳን አልተቃጠለም ነበር፡፡ ይህንንም ያዩ ሁሉ ‹‹እኛም በእነነዚህ ደናግል ሴቶች አምላክ አምነናል›› እያሉ በመመስከር ሰማዕት ሆኑ፡፡ ከዚህም በኋላ ምእመናን የቅድስት አጥራስይንና የቅድስት ዮናን ሥጋቸውን ወስደው የመከራው ዘመን እስኪፈጸም ድረስ በድብቅ አኖሩት፡፡ በኋላም ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠርተውላቸው ቅዱስ ሥጋቸውን በዚያ አኖሩ፡፡
ከሥጋቸውም ብዙ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራት ተፈጽመው
ታዩ፡፡ የቅድስት አጥራስይና የቅድስት ዮና በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን፡፡
+ + +
ቅድስት እንትያ እና ልጇ ኤላውትሮስ፡- እነዚህም ቅዱሳን እናትና ልጅ ከሮሜ አገር የተገኙ ሰማዕታት ናቸው፡፡ ቅድስት እንትያም ልጇን በሃይማኖት በምግባር ኮትኩታ ካሳደገችው በኋላ ዲቁናና ቅስና እንዲማርላት አንቂጦስ ለሚባል ኤጲስቆጶስ ሰጠችው፡፡ ኤጲስቆጶሱም ኤላውትሮስን እያስተማረ አሳደገውና በ17 ዓመቱ ዲቁና ሾመው፣ ቀጥሎም ከዓመት በኋላ ቅስና ሾመው፡፡
የእናታችን የቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ቅዱስ ዐፅሟ የሚገኝበት ሬማ መድኀኔዓለም ገዳም!
ረድኤት በረከቷ ይደርብንና በዚኽች ዕለት ይኽን ታላቅ ተኣምር አደረገች፦ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ካረፈች በኋላ የዕረፍቷ የመታሰቢያ በዓሏ በደረሰ ጊዜ ከደስያትና ከአድባራት ከገዳማት ከየአገሩ ስፍር ቁጥር የሌለው ሕዝብ ተሰበሰበ፡፡
ከእነርሱም መካከል መምህራንና መነኮሳት፣ ቀሳውስት ዲያቆናት ከነማዕጠንታቸው ነበሩ፡፡ ከእነርሱም መካከል የዕለት ጉርስ የሌላቸው ብዙ ነዳያን፣ ዐይነ ሥውራንና አንካሶች ነበሩ፡፡
የቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ገድሏና ተአምራቷ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ተሰምቷልና ለበዓሏ የመጣውን ሕዝብ የገዳሙ መነኮሳት በየማዕረጋቸው አስቀምጠዋቸው ለዝክሯ
የተዘጋጀውን ብዙ መብልና መጠጥን በልተውና ጠጥተው እስኪያስተርፉ ድረስ ሰጧቸው፡፡ ነገር ግን ከዚያ በፊት
ዝክሯን ሲያዘጋጁ በመነኮሳቱ ዘንድ ታላላቅ ተአምራት ተደረገ፡፡ ይኸውም ለመታሰቢያ ከሚጋገር እንጀራ የተረፈ አንድ እንጀራ ብቻ የሚሆን ሊጥ በትልቅ ጋን ውስጥ ነበር፡፡ ያም አንድ እንጀራ ብቻ የሚሆነው ሊጥ በትልቁ ጋን ውስጥ ሳለ ሊጡ በተአምራት ወደላይ እየፈላ እስኪፈስ ድረስ ሞልቶ እየፈሰሰ ተገኘ፡፡ መነኮሳቱም ወደሌላ ዕቃ እየገለበጡ በሚቀዱ ጊዜ ሊጡ አልጎድል ብሎ ነበር፤ በየቀኑም እየጨመረና እየበዛ ሞልቶ ይገኝ ነበር፡፡ ይህንንም ምሥጢር የሚያውቁ መነኮሳይያት እኅቶች ለማንም አልተናገሩም ነበር-ከእናታችን ከቅድስት ወለተ ጴጥሮስ የተአምራቷ ኃይል የተነሣ እጅግ ያደንቃሉ እንጂ፤ ነገር ግን አንዲት ለመናገር የምትቸኩል እኅት ሊጡ በተአምራት እንደሚፈላ ጮኻ ተናገረች፡፡ ያንጊዜም ሊጡ ወዲያውኑ መፍላቱን አቆመ፡፡ እንጀራ ጋጋሪዋም ከሊጡ በምትቀዳ ጊዜ እያደር እየጎደለ ሔደ፡፡
እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታ በገዳሙ ውስጥ ጥቂት ዱቄት ነበረች፣ ያችም ዱቄት በብዙ ዕንቅብ እየወሰዱ ሌላ ቦታ እስኪያስቀምጡ ድረስ በተአምራት እጅ በረከተ፡፡ ነቢዩ ኤልያስ በሰራጵታ ዱቄቱን አበርክቶ መበለቲቱን እንደመገባት (1ኛ ነገ 17፡7-17) እንደዚሁ ሁሉ የቅድስት ወለተ ጴጥሮስ የዕረፍቷ መታሰቢያ ይደረግበት ዘንድ የተዘጋጀው ዱቄት በተአምር በርክቶ ተገኘ፡፡ በዚህም ጊዜ ሌላኛዋ አንዲት እኅት ይህንን ተአምር አይታ ጮኻ በተናገረች ጊዜ ዱቄቱ መብዛቱ ቆመ፡፡ለመናገር የሚቸኩል ሰው የእግዚአብሔርን በረከት ያሳጣል፡፡ ሐዋርያው ‹‹ሰው ሁሉ ለመስማት ፈጠነ ለመናገር የዘገየ ይሁን›› እንዳለ ዳግመኛም አረጋዊ መንፈሳዊ ‹‹ለመናገር የሚቸኩል ሰውን ፈጣሪው ይርቀዋል›› አለ፡፡ እንደገናም በእናታችን የዕረፍቷ መታሰቢያ ወቅት ጥቂት ዕንጨት በርክታ ብዙ ሆና ከማታ እስከ ጠዋት ድረስ ብዙ እንጀራ ጋገረች፡፡ ሌላም በእንጀራው በወጡ በጠላው ላይ የተደረገው ተአምር ተነግሮ አይዘለቅም-የተአምራቷን ብዛት እግዚአብሔር ያውቃል እንጂ በሰው ዘንድ ተቆጥሮ አያልቅም፡፡››
(ገድለ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ገጽ 107-108)
የእናታችን የቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን።
እግዚአብሔር አምላክ አብርሃምን እና ሳራን የተመለከተ አምላክ በኢያቄምና ሐና አማካኝነት ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነችውን እና ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ልቦና ታስባ ትኖር የነበረች የተነገረላት ትንቢት ሊፈጸም የአባት የእናቷ የቅድመ አያቶቿ ራእይ ሊተረጎም ጌታ የፈቀደበት ጊዜ ሲደርስ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም እሁድ እለት ነሐሴ 7 ቀን በ16 ዓ.ዓ ተፀነሰች፡፡
እመቤታችን ከተፀነሰች በኋላ አይሁድ ቀንተው ተነሱባቸው ቅናቱ እንዴት ነው ቢሉ ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ካጎቱ ቤት ሄዶ ሞተ፤ እነርሱም እንቀብራለን ብለው ባልጋ ይዘው ሲሄዱ ከመንገድ አሳረፉት፡፡ ቅድስት ሐናም የአጎቷ ልጅ ነበርና ለማልቀስ ብትደርስ ዘመዶቿ ሁሉ ተሰብስበው ሲላቀሱ ቆዯአት፤ እርሷም አብራ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ብድግ ብሎ ተነሥቶ "ስብሃት ለኪ ማርያም እሙ ለፀሐየ ጽድቅ ለአብ ሙሽራው ለወልድ ወላዲቱ ለመንፈስ ቅዱስ ጽርሃ ቤቱ ተፈስሂ ደስ ይበልሽ" ብሎ ሰገደላት፡፡ አይሁድም ይህ ተአምር ሲደረግ ከዚያው ነበሩና "ምነው ሳሚናስ ምን አየህ? ምን ትላለህ?" ቢሉት "ከዚች ከሐና ማኅፀን የምትወለደው ሕፃን ሰማይ ምድርን አየርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች እያሉ መላእክት ሁሉ ሲያመሰግኗት ሰማሁ" አላቸው፡፡ ዳግመኛም "እኔንም ያነሣችኝ የፈወሰችኝ ያዳነችኝ እርሷ ናት" አላቸው፡፡ አይሁድም "በል ተወው ሰማንህ" ብለው ቅናት ጀመሩ፡፡ ሐና በእርጅናዋ ጊዜ መፀነሷን የተመለከቱ ዘመዶቿና ያገሯ ሰዎች ተገርመው እየመጡ ይጠይቋት ነበር፡፡ እመቤታችን ማርያም በፅንስ እያለች ብዙ ታምራትን አድርጋለች። ከእነዚህም መካከል ዐይነ ስውር የነበረችው የአርሳባን ልጅ ወደ ሐና መጥታ እውነትም ሐና መጸነሷን ለማረጋገጥ ሆዷን ዳሰሰቻት፡፡ እርሷም ሳታስበው ዐይኗን ስትነካ ዐይኗ በራላት፡፡ እመቤታችንም በተፀነሰች በ9 ወር ከአምስት ቀን የግንቦት መባቻ ዕለት ግንቦት 1 ተወለደች፡፡
አምላክን የወለደች የድንግል ማርያም እናት የክብርት ሐና ዐፅሟን አባቶቻችን ከቅዱስ መስቀሉ ጋር ወደ አገራችን ኢትዮጵያ አምጥተውልናል፡፡ የጌታችን ቅዱስና ክቡር መስቀል ካለበት በወርቅ ከተለበጠው ከዕንጨቱ ሣጥን ውስጥ ዐፅማቸው በክብር ከተቀመጡ ብዙ የከበሩ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ይህ የእናታችን የቅድስት ሐና ዐፅም ነው፡፡ ይህንንም መጽሐፈ ጤፉት በደንብ ይገልጸዋል፡፡
የእናታችን የቅድስት ሐና ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን!
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ኅዳር 11-ክብርት እመቤታችን ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክን የወለደቻት ቅድስት ሐና ዕረፍቷ ነው፡፡ ሐና ማለት ‹‹ጸጋ›› ማለት ነው፡፡ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እናት ናት፡፡ እርሷም ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት ልጁ ናት፡፡ የቅድስት ሐና አባት ማጣትና እናቷ ሄርሜላ ከእርሷ በተጨማሪ ሶፍያና ማርያም የሚባሉ ሌሎች ሁለት ሴት ልጆችን ወልደዋል፡፡ ቅድስት ሐና ከይሁዳ ነገድ የሆነውን ጻድቅ ኢያቄምን አግብታ ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደች፣ ድንግል ማርያምም መድኃኔዓለም ክርስቶስን ወለደች፡፡ ሶፍያ ኤልሳቤጥን ወለደች፣ ኤልሳቤጥም መጥምቁ ዮሐንስን ወለደች፡፡ ከሦስቱም ታናሽ የሆነችው ‹‹ማርያም›› የተባለችው የማጣትና የሄርሜላ ልጅ ደግሞ ሰሎሜን ወለደቻት፡፡
ይህችም ታላቅ እናት ቅድስት ሐና አምላክን በድንግልና ሆና በሥጋ ለወለደችው ለቅድስት ድንግል ማርያም ወላጇ ትሆን ዘንድ የተገባት ሆናለችና ከሴቶች ሁሉ እንደምትበልጥና እንደምትከብር እንረዳ፡፡ ለዓለም ሁሉ ድኅነት የተደረገባትን ልዩ ስጦታ የሆነች ድንግል ማርያምን እርሷ አስገኘቻት፡፡ የዚህች ክብርት እናት የትውልዷ ጥንተ ነገሩ እንዲህ ነው፡- ጴጥርቃ እና ቴክታ የሚባሉ የከበሩ ደጋግ ሰዎች በኢየሩሳሌም በአንድነት ተጋብተው በሕገ እግዚአብሔር ይኖሩ ነበር፡፡ እነዚህም በእግዚአብሔር የሚያምኑ የተወደዱ ጻድቃን ደግ ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱም በእግዚአብሄርም በሰውም ዘንድ የተመሰከረለላቸው ባለጸጎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን መካን ስለነነበሩ የሚወርሳቸው ልጅ አልነበራቸውም፡፡
አንድ ቀን ጴጥርቃ ቴክታን እንዲህ አላት፡- ‹‹እህቴ ሆይ! ይህን ሁሉ የሰበሰብነውን ገንዘባችንን ምን እናደርገዋለን? ልጅ የለን የሚወርሰን፣ አንቺም መካን ነሽ እኔም ካንቺ በቀር ሌላ ሴት አላውቅም›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ወንድሜ ሆይ! አምላከ እስራኤል ለእኔ ልጅ ቢነሳኝ አንተም እንደኔው ሆነህ ትቀራለህን? ከሌላ ደርሰህ ውለድ እንጂ›› ብላ ብታሰናብተው እንደዚህ ያለ ነገር እንኳንስ ላደርገው በልቦናዬም እንዳላስበው አምላከ እስራኤል ያውቃል›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን የሚያውቅ የለም፣ ትላንትና ማታ በህልሜ ነጭ ጥጃ ከማኅፀኔ ስትወጣ ያችም ነጭ ጥጃ ሌላ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንዲሁ እስከ 7ት ትውልድ ሲዋለድ ሰባተኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ፣ ጨረቃዋም ፀሐይን ስትወልድ አየሁ›› አለችው፡፡ እርሱም በጠዋት ከህልም ፈቺ ዘንድ ሔዶ የነገረችውን ሁሉ ነገረው፡፡ ያም ህልም ፈቺ ‹‹እግዚአብሔር በምሕረቱ አይቷችኋል፣ በሳህሉ መግቧአችኀል፣ 7 አንስት ጥጆች መውለዳችሁ 7 ሴቶች ልጆች እና የልጅ ልጆች ትወልዳላችሁ፤ ከቤታችሁ ሰባተኛይቱ ጨረቃ መውለዷ ከሰው የበለጠች ከመላእክትም የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ የፀሐይ ነገር ግን አልታወቀኝም›› አለው፡፡
ጴጥርቃም ሕልም ፈቺው የነገረውን ሁሉ ሔዶ ለሚስቱ ነገራት፡፡ እርሷም ‹‹እንጃ አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን ማን ያውቃል!?›› ብላ ዝም አለች፡፡ ከዚያም ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች፡፡ ስሟንም ሄሜን ብለው አወጡላት፤ ሄሜንም አድጋ ለአካለ መጠን ስትደርስ አጋብተዋት ሴት ልጅ ወለደች፣ በስምንተኛ ቀኗም ዴርዲ ብለው ስም አወጡላት፡፡ ዴርዲም አድጋ እንዲሁ ሴት ወለደችና ቶና አለቻት፣ ቶናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሲካር አለቻት፣ ሲካርም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሴትና አለቻት፣ ሴትናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሄርሜላ አለቻት፣ ሄርሜላም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ንጽህት ቅድስት ክብርት የምትሆን እመቤታችንን የምትወልደውን ሐናን ወለደች፡፡
ይህቺም ሐና በሥርዓት አድጋ ለአእምሮ ስትበቃ አካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ መንግስት ወገን ከነቅዱስ ዳዊት ወገን ከሆነው ከቅዱስ ኢያቄም ጋር አጋቧት፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ኢያቄምና ሐና በአንድነት ተጋብተው ሲኖሩ ልጅ አጡ፡፡ እነርሱም እጅግ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ አንድ ልጅ እንኳ ስላልነበራቸው እጅግ ያዝኑ ነበር፡፡ ወደ ቤተመቅደስ እየሄዱ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ አጥብቀው ይለምኑት ነበር፡፡ መብዓ ይዘው ለሊቀ ካህኑ ሲሰጡት ሊቀ ካህኑም እንኳ ሳይቀር ‹‹እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ያለውን ሕግ በእናንተ ላይ እንዳይፈጸም አድርጎ ልጅ የከለከላችሁ ኃጢአተኛ ብትሆኑ ነውና መብዓችሁን አልቀበልም›› ብሎ በእጅጉ አሳዝኗቸዋል፡፡ በሊቀ ካህኑ እያዘኑና እየተከዙ ሲመለሱ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ዛፍ ሥር ተቀመጠው ሳለ እርግቦች ጫጩቶቻቸውን ሲያጫውቱ ተመልክተው ‹‹ለእነዚህ ወፎች እንኳ ልጆችን የሰጠህ አምላክ ለእኛስ መች ይሆን ልጅ የምትሰጠን?›› ብለው እጅግ አምርረው አለቀሱ፡፡
ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ወደቤታቸው ሲመለሱ ርግብ ከልጆቿ ጋር ስትጫወት አይታ ‹‹አቤቱ ጌታዬ ለዚች እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሳኸኝ?›› እያለች ምርር ብላ አለቀሰች፡፡ እንዲህ ብለው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ከዘካርያስ ከሊቀ ካህናቱ ሄደው ‹‹አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተ እግዚአብሔርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን፤ ሴት ልጅም ብንወልድ ውኃ ቀድታ መሶብ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን›› ብለው ስዕለት ገቡ፡፡ ዘካርያስም ‹‹እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ይስማችሁ ስዕለታችሁን ይቀበልላችሁ የልቦናችሁን ሀሳብ ይፈጽምላችሁ›› ብሎ አሳረገላቸው።
ከዚህም በኋላ ቅድስት ሐና እና ቅዱስ ኢያቄም ዕለቱን ራእይ አይተው ነገር አግኝተው አደሩ፡፡ ራእዩስ እንዴት ነው ቢሉ ኢያቄም ‹‹7ቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› አላት፡፡ ‹‹ወፍ›› የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባህሪው ነው፤ ‹‹ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› ማለቱ የኢያቄምን (የሰውን) ባህርይ ባህርይ እንዳደረገው ዕወቅ ሲል ነው፡፡ 7ቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ልዩ ልዩ ባሕርይው ምልአቱ ስፋቱ ርቀቱ ልዕልናው ናቸው፡፡ ሐናም ‹‹እኔም ደግሞ አየሁ እንጂ›› አለችው፡፡ ‹‹ምን አየሽ?›› ቢላት ‹‹ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ›› አለችው፡፡ ‹‹ርግብ›› የተባለች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፤ ነጭነቱ ንጽህናዋ ቅድስናዋ ድንግልናዋ ነው፡፡ ‹‹ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማኅፀኔ ስትተኛ አየሁ›› ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን መፀነሷን ነው፡፡ ይህንኑም ራእይ ያዩት ሐምሌ 30 ዕለት ነው፡፡
እነርሱም እንዲህ ያለ ራእይ ካየን ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም ይልቁንም ፈቃደ እግዚአብሔር ቢሆን ብለው አዳምንና ሔዋንን ‹‹‹ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት›› ብሎ ያበሰረ አምላክ ለእኛስ ይልክልን የለምን?›› ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ 7 ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ፡፡ ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ‹‹‹ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላቹህና ዛሬ በሩካቤ ሥጋ ተገናኙ› ብሎሏችኀል ጌታ›› ብሎ መልአኩ ለቅድስት ሐና ነገራት፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔርር በብሥራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያምን ፀነሰቻት፡፡
ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስም በዲዮቅልጥያኖስ ሰማዕት ሆኖ ካረፈ በኋላ አኪላስ በእርሱ ፈንታ በ303 ዓ.ም ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ተሾመ፡፡ አርዮስም ወደ አኪላስ ቀርቦ ከውግዘቱ እንዲፈታው በከንቱ ውዳሴ አባበለው፡፡ አኪላስም የቅዱስ ጴጥሮስን አደራ በመዘንጋትና ለአርዮስም ከንቱ ውዳሴ ተሸንፎ አርዮስን ከውግዘቱ ፈታው፡፡ ደግሞም ቅስና ሾመው፡፡ ነገር ግን አኪላስም ብዙ ሳይቆይ በ6 ወሩ ተቀሰፈና ሞተ፡፡
ቀጥሎም እለእስክንድሮስ ፓትርያክ ሆኖ ተሾመ፡፡ አርዮስንም ከነጓደኞቹ አውግዞ አሳደደው፡፡ ብዙዎችም ወደ አባ እለእስክንድሮስ መጥተው አርዮስን ከውግዘቱ እንዲፈታው ቢለምኑትም እርሱ ግን ከውግዘቱ ላይ ውግዘት እንዲጨምርበት እንጂ እንዳይፈታው አባቱ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳዘዛቸው ነገራቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አርዮስ ክህደቱን ከማሰራጨት አልታቀበም ነበር፡፡ እንደውም ሕዝቡ ትምህርቱን በቀላሉ እንዲቀበሉ የክህደት ትምህርቱን በግጥምና ንባብ እያዘጋጀ ማሰራጨት ቀጠለ፡፡ ሕዝቡ ግጥም ስለሚወድ ትምህርቱን ወደ መቀበል ደርሶ ነበር፡፡ የዚህ ጊዜ እለእስክንድሮስ እየተዘዋወረ ከአርዮስ ኑፋቄ እንዲጠበቁ በትጋት ያስተምር ነበር፡፡
በ320 ዓ.ም አንድ መቶ የሚሆኑ የሊቢያና የእስክንድርያ ኤጲስቆጶሳትን እለእስክንድሮስ ሰብስቦ የአርዮስን ክህደት ገለጸላቸው፡፡ ጉባኤውም ተመክሮ ተዘክሮ አልመለስ ያለውን አርዮስን በአንድ ልብ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ለየው፡፡ ከዚህም በኋላ አርዮስ ከጓደኞቹ አንዱ ወደ ነበረው ወደ የኒቆሜዲያ ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስ ዘንድ በመሄድ ‹‹እለእስክንድሮስ በከንቱ አወገዘኝ›› ብሎ ነገር ጨምሮ ነገረው፡፡ አውሳቢዮስም አይዞህ ብሎ ተቀብሎ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙትን ኤጲስ ቆጶሳትን ሰብስቦ በአርዮስ ጉዳይ ሲኖዶስ አደረገ፡፡ የአውሳቢዮስም ሲኖዶስ አርዮስ በግፍ መባረሩን አምኖ ከውግዘቱ ፈቱት፡፡
አርዮስም በ322 ዓ.ም ወደ እስክንድያ ተመልሶ ‹‹እለእስክንድሮስ ቢያወግዘኝ ተፈትቼ መጣሁ›› እያለ የበፊት የክህደት ትምህርቱን በስፋት ማስተማር ቀጠለ፡፡ በዚህም ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ታመሰችና ጉዳዩ ጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዘንድ ደረሰ፡፡ በዚህም ጊዜ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የእስፓኙን ጳጳስ ሆስዮስን ወደ እስክንድርያ ላከው፡፡ ሆስዮስንም ደርሶ ሲመለስ ‹‹ጉዳዩ የሃይማኖት ችግር እንጂ አስተዳደራዊ ስላልሆነ በጉባኤ መታየት አለበት›› ብሎ ለንጉሡ አማከረው፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም በነገሠ በሃያ ዓመቱ በ325ዓ.ም ጉባኤ እንዲደረግ አዘዘ፡፡ በዚህም በኒቅያ 318 የከበሩ ሊቃውንት አባቶች ተሰበሰቡ፡፡
እነዚህ 318ቱ ቅዱሳን አበው ሊቃውንት እጅግ የከበሩ ናቸው፡፡ ቅዱስ እለእስክንድሮስ የጉባኤው ሊቀ መንበር ሲሆን ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ ደግሞ ጸሐፊ ሆነ፡፡ እንደነ አቡነ ቶማስ ዘመርዓስ ያሉት ቅዱሳን በከሃድያን ነገሥታት 22 ዓመት በጨለማ ቤት ታሥረው እጅና እግሮቻቸውን በየተራ ተቆራርጠው ከእሥር ቤት ከወጡ በኋላ በቅርጫት ውስጥ ተደርገው በአህያ ላይ ተጭነው ነበር ወደ ጉባኤ ኒቂያ የሄዱት፡፡
የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ መኮንኖች አቡነ ቶማስን ቶሎ ብለው እንዲሞቱ ሳይሆን በሥቃይ ሆነው እንዲቆዩ በማድረግ ለ22 ዓመታት በጨለማ ውስጥ እያሰሩ አሠቃይተዋቸዋል፡፡ ከሃዲያኑም በየዓመቱ ወደ አሥር ቤቱ እየገቡ አንድ አካላቸውን ይቆርጡ ነበርና የአባታችንን እጅና እግሮቻቸውን በየተራ ቆራረጧቸው፡፡ አፍንጫቸውን፣ ከንፈሮቻቸውን፣ ጆሮዎቻቸውን ሁሉ በየተራ እየቆረጡ ለ22 ዓመትታት ጣዖቶቻቸውን ሲያጥኑበት ኖረዋል፡፡ አንዲት ደግ ክርስቲያን ሴት ግን አቡነ ቶማስ የተጣሉበትን ጉድጓድ አይታ ስለነበር በድብቅ ሌሊት እየሄደች ትመግባቸው ነበር፡፡ ደገኛውና ጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በነገሠ ጊዜ ይህች ሴት ሄዳ ስለ አቡነ ቶማስ ነግረችውና አባታችንን ከተጣሉበት ጉድጉድ አወጣቸው፡፡ ቆስጠንጢኖስም በአርዮስ ክህደት ምክንያት እጅግ የከበሩ 318 ቅዱሳን ሊቃውንትን በኒቅያ አገር እንዲሰበሰቡ ሲያደርግ አንዱ አቡነ ቶማስ ነበሩ፡፡ ወደ ጉባዔውም ሲሄዱ ደቀ መዛሙርቶቻቸው በቅርጫት አድርገው በአህያ ጭነው ወደ ጉባኤ ኒቂያ ይዘዋቸው ሄደዋል፡፡ በመንገድም ሳሉ ዐላዊያኑ አግኝተዋቸው አህዮቻቸውን ሌሊት ራስ ራሳቸውን ቆርጠው ጣሉባቸው፡፡ አቡነ ቶማስም ራሳቸው የተቆረጡትን አህዮች አምጡልኝ ብለው የጥቁሩን አህያ ራስ ከነጩ፣ የነጩን አህያ ራስ ከጥቁሩ ገጥመው ቢባርኳቸው ሁሉም አህዮች ከሞት ተነሥተዋል፡፡
አቡነ ቶማስ ከኒቅያ ጉባዔ ሲደርሱ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጽድቃቸውን ዐውቆ ‹‹አባቴ በረከትዎ ትድረሰኝ›› በማለት በዐላዊያኑ የተቆራረጠ አካላቸውን ዳሶ ተባርኳል፡፡ አቡነ ቶማስ ዘመርዓስም ከሌሎቹ ቅዱሳን ሊቃውንት ጋር ሆነው በጋራ አርዮስን መክረውና አስተምረው እምቢ ቢላቸው አውግዘውት ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ ወዲያው በሰላም ዐርፈዋል፡፡
የመርዓሱን አቡነ ቶማስን ብቻ ላሳያ ያህል ብቻ አነሳን እንጂ 318ቱም የኒቅያ ጉባኤ ተሳታፊ የሆኑ አበው ሊቃውንት እጅግ የከበሩ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ‹‹እጅግ የከበሩ ቅዱሳን›› የሚለው ቃል ራሱ የማይገልጻቸው ሁሉም ለየራሳቸው እጅግ ድንቅ የሆነ ገድል ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህም ቅዱሳን አርዮስን ተከራክረው ክህደቱን ግልጽ አደረጉበት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮቱ ትክክል መሆኑን አስረዱት፡፡ በተለይም ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችንም በቃላቸው ትምህርት እያስተማሩት በእጆቻቸው ተአምራት አድርገው እያሳዩት ቢያስተምሩትም ሰይጣን አንዴ አስቶታልና አርዮስ ከክህደቱ አልመለስ ቢላቸው አውግዘው ለዩት፡፡ በአንዲትም ቃል ሆነው ዛሬ ላይ የጸሎታችን መጀመሪያ የሆነውን ‹‹ጸሎተ ሃይማኖትን›› ደነገጉልን፡፡
የአርዮስ ፍጹም የሆኑ ክህደቶቹ እነዚህ ናቸው፡- ለስም አጠራሩ ክብርና ምስጋና ይግባውና ‹‹ክርስቶስ ዓለም ሳይፈጠር አልነበረም›› አለ፡፡ ዳግመኛ አርዮስ ‹‹ባሕርዩ ከአብ ያነሰ ነው›› ፣ ‹‹የተፈጠረ እንጂ ከአብ የተወለደ አይደለም›› እና ‹‹በመጀመሪያ ዓለሙን ይፈጥርበት ዘንድ እግዚአብሔር እርሱን ፈጠረው፣ እርሱም ዓለምን ፈጠረ›› የሚሉ ከሰይጣን የተገኙ ፍጹም ክህደቶች ናቸው፡፡
እነዚህ የአርዮስ አስተሳሰቦች ዛሬም ድረስ መልካቸውንና ይዘታቸውን ለውጠው በእኛው ቤተ ክርስቲያን ላይ በግልጽ ሲነገሩ መቆየታቸው እጅግ አስገራሚ ነው በእውነት!
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።
@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna
#ኢትዮጵያ
Last updated 2 months, 1 week ago
Last updated 6 days, 22 hours ago
ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ ? @Esat_tv_comment_bot
??ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ??
Last updated 2 months, 3 weeks ago