ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።
@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna
#ኢትዮጵያ
Last updated 3 недели назад
Last updated 2 недели, 2 дня назад
ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot
🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹
Last updated 1 месяц назад
በፈረንሳይ በባለቤቷ እገዛ ከ80 በላይ በሚሆኑ ወንዶች ለዓመታት በተደፈረችዉ ግለሰብ ጉዳይ ቢያንስ 20 ወንዶች ጥፋተኛ ተባሉ
የፈረንሳይ ፍርድ ቤት የጊሴሌ ፔሊኮት የቀድሞ ባል በከባድ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እና በሌሎች ክሶች ላይ ጥፋተኛ ብሎ ሀሙስ እለት ወስኗል።
ፈረንሳዊው ዶሚኒክ ፔሊኮት የገዛ ሚስቱን አስገድዶ ለማስደፈር ከመለመላቸዉ ሰዎች መካከል ቢያንስ 20 ያህሉ በአስገድዶ መድፈር ጥፋተኛ ብይን የተሰጠባቸዉ ሲሆን ለአስር አመታት ያህል ባለቤቱን በአደንዛዥ እፅ በማደንዘዝ ድርጊቱ ሲፈጸምባት ቆይቷል፡፡ከ13 ሳምንታት በፊት ፈረንሳይን እና መላዉ ዓለምን ያስደነገጠው የጅምላ አስገድዶ መድፈር ድርጊት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተሸጋግሯል።ሰለባ የሆነችው ጂዜሌ ፔሊኮት ቃሏን ፍርድ ቤት ተገኝታ መስጠቷ ይታወሳል፡፡ጥንዶች ዶሚኒክ እና ጊሴሌ ፔሊኮት አሁን በ70ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ ጡረተኞች ናቸው።ዶሚኒክ ፔሊኮት በወርሃ መስከረም በደቡባዊ አቪኞን ከተማ ከሌሎች 50 ሰዎች ጋር ለፍርድ ቀርቧል፡፡
በፍርድ ቤቱ ተገኝታ ስለ ጤንነቷ የተናገረችዉ ጊሴሌ በጭንቀት የተነሳ ከህይወቴ 10 አመታትን ተነጥቄያለሁኝ በጭራሽ ወዳጣሁት ዓመታት መመለስ አልችልም ስትል ለፍርድ ቤት መናገሯ ይታወሳል።"አሁን 72 አመቴ ነው እና ምን ያህል ጊዜ እንደቀረኝ አላውቅም" ስትል አክላለች:: በእነዚያ አስጨናቂ ዓመታት ረዥም የእግር ጉዞ በማድረግ ፣ ሙዚቃ በማዳመጥ እና ቸኮሌት በማጣጣም ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ ለማድረግ ሞከርኩ” ትላለች።" ወይ እሞታለሁ አልያም የአእምሮ ሆስፒታል የምገባ መስሎኝ ነበር።"ስትል አክላለች፡፡
የቀድሞ ዶሚኒክ ፔሊኮት ሚስቱን በተለያዩ ወንዶች እንድትደፈር ሲያደርግ ለአስር አመታት ያህል አደንዛዥ ዕፅ መጠቀሙን አምኗል፡፡ለአምስት አስርት ዓመታት በትዳር አብራው የኖረችው ባለቤቷ ከ80 በላይ የሚሆኑ ወንዶችን በመጋበዝ እንዳስደፈራት እና ድርጊቱን እንደቀረጸው የተረዳችው ከፖሊስ ነው።በመድፈር ወንጀሉ ላይ የተሳተፉት ወንዶች ቁጥር ብዛት ፈረንሳይን አስደንግጧል።በቪዲዮው ላይ ከታዩት 83 ወንዶች መካከል ፖሊስ መለየት የቻለው 50ዎቹን ብቻ ነው።
ዕድሜያቸው ከ26 እስከ 68 ሲሆን፣ በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ ያሉ ናቸው። የእሳት አደጋ ሠራተኞች፣ ፋርማሲስቶች፣ ነርስ፣ የእስር ቤት ጠባቂ፣ ጋዜጠኞች ተካተውበታል። በርካቶቹ የልጆች አባት እና ባለትዳሮች ናቸው።አንደኛው ኤችአይቪ በደሙ እንዳለበት እያወቀ ስድስት ጊዜ እንደደፈራት ፖሊስ ይፋ አድርጓል።ምንም እንኳን ኤች አይ ቪ ባይተላለፍባትም ሌሎች በወሲብ በሚተላለፉ በሽታዎች ተይዛ እንደነበር የጤና ባለሙያ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የጤና እክሎች እንደተከሱባት ተገልጿል።
በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
የሹራብ ልብስ ባስከተለው ፀብ ጎረቤቱን የገደለው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ
በኢሊባቡር ዞን ዲረሙ ወረዳ በሁለት ጎረቤታሞች መካከል በተፈጠረ አለመግባበት የሰው ህይወት ያጠፋው ግለሰብ በእስራት መቀጣቱን የኢሊባቡር ዞን ፖሊስ መምሪያ ገልጿል ።
የኢሉባቡር ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ለማ ጎይቶ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን እንደገለጹት ተከሳሽ ናስር አደም የተባለው ግለሰብ ሟች ገመቹን ጋር በጉርብትና አብረው ይኖሩ እንደነበር ገልጸዋል ።
የሁለቱ ጎረቤታሞች የግጭት መንስኤ ተከሳሹ ሹራብ ከሌላ ግለሰብ ገዝቶ እንደነበረ የተናገረ ሲሆን ሟች ደግሞ ሹራቡን ሁለት ሰዎች ደብድበው እንዳወለቁበት በመናገሩ አስደብድበኸኝ ሹራቤን ወስደሃል በሚል ቂም ይዞበት አንደነበር ተገልጿል ።
ይሁን እንጂ ተከሳሽ ሹራቡን ከገበያ ነው የገዛሁት ብሎ ቢናገርም በሁለቱ ጎረቤታሞች መካከል ቅራኔ ፈጥሯል። በዚሁም ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት ላይ ሁለቱ ጎረቤታሞች መንገድ ላይ ተገናኝተው በነበረበት ሰዓት የተሰረቀውን ሹራብ ለብሶ የነበረው ተከሳሽ ቀደም ብሎ የተፈጠረውን ቅራኔ ተንተርሶ ጸብ ውስጥ ይገባሉ ። የግል ተበዳይ የሆነው ሟች የፌሮ ብረት በጎረቤቱ ላይ ሲወረውሩ ጎንበስ ብሎ በማሳለፍ እጅ ለእጅ በመያያዝ አቶ ነስር የታጠቁትን ስለታም ጩቤ በማውጣት አንገታቸውን እና የተለያዩ የፊት አካላቸውን በመውጋት ህይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉ በማስረጃ ተረጋግጧል ።
ፖሊስ በአካባቢው ነዋሪዎች በደረሰው መረጃ መሰረት በስፍራው በመገኘት የሟች አስከሬንን በማንሳት የአስከሬን ምርመራ እንዲደረግ ወደ ሆስፒታል በመላክ የድርጊቱን ፈጻሚ በቁጥጥር ስር አውሎ ጉዳዩን አጣርቷል።
ተከሳሽ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ድርጊቱን መፈጸሙን አምኖ የድርጊቱን መነሻ ሹራብ ሰርቀሃል የሚለው የሀሰት ውንጀላ መሆኑን እና በፌሮ ሊመታኝ ነበር ስለሆነም ራሴን ለመከላከል የወሰድኩት እርምጃ ነው በማለት ለፖሊስ ቃሉን ይሰጣል።
ፖሊስም የምርመራ መዝገቡን በሰው እና በሰነድ ማስረጃ በማደራጀት መዝገቡን ለዓቃቢ ህግ ይልካል ። የደረሰውን የክስ መዝገብ የተመለከተው ዓቃቢህግ ክስ በመመስረት ለኢሊባቡር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል።
ክሱን የተመለከተው ፍርድ ቤትም ተከሳሽ ነስሩ አደም በዓቃቢ ህግ በቀረበው ማስረጃ መሰረት በ12 ዓመት እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ የተላለፈ መሆኑን ረዳት ኢንስፔክተር ለማ ቦይዶ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
በኤደን ሽመልስ
#ዳጉ_ጆርናል
የአእዋፋት ከአውሮፕላን ጋር መጋጨት ለአደጋ የቀረቡ ክስተቶች እየጨመረ መምጣቱን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዮሽን ባለስልጣን አስታወቀ
በኤርፖርቶች የስራ እንቅስቃሴ ላይ ደህንነቱ የተረጋገጠ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት አኳያ የአእዋፋት ከአውሮፕላን ጋር መጋጨት የሚያስከትሉት አደጋ እየጨመረ መምጣቱን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዮሽን ባለስልጣን አስታውቋል::በባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እንዳለ አሰፋ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ከአእዋፋት ጋር በተያያዘ ዘንድሮ ከአምናው ከፍ ያሉ ለአደጋ የቀረቡ ክስተቶች ታይተዋል፡፡
አእዋፋት ከአውሮፕላን ጋር በመጋጨት የሚያደርሱት ተፅዕኖ ችግር አስከፊ ነው ያሉት አቶ እንዳለ ዘንድሮ አደጋ ባይከሰትም ለአደጋ የቀረቡ ክስተቶች ግን በብዛት ታይተዋል ሲሉ ጨምረው ለጣቢያችን ገልፀዋል፡፡የአእዋፋት ጥቃት በኢትዮጵያ በዋናነት ወቅትን ያማከሉ ናቸው የተባለ ሲሆን ክረምት አልፎ የመስቀል ወፎች የሚባሉት በብዛት በሚታዩበት ጊዜ ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ተጠቅሷል::
በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1988 ባህርዳር ላይ በአእዋፋት ጥቃት የደረሰው አስከፊ አደጋ፣አዲስ አበባ ላይ በ1996 በዳሽ-6 አውሮፕላን ላይ የተከሰተው እና ድሬዳዋ ላይ በ2016 ከርከሮ የአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ገብቶ Q_400 አውሮፕላን ላይ የደረሱ ጉዳቶች አስከፊ ተብለው በታሪክ የሚታወሱ ናቸው ተብሏል፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍ በአሁኑ ወቅት የኤርፓርት የዱር እንስሳት አደጋ መከላከል ብሄራዊ የስራ አመራር ኮሚቴ መቋቋሙ ተገልጿል::
በቅድስት ደጀኔ
#ዳጉ_ጆርናል
የቀድሞ የሲአይኤ ሰራተኛ በተለያዩ ሀገራት በደርዘን የሚቆጠሩ ሴቶች አደንዣዥ እፅ በመስጠት ፆታዊ ጥቃት በመፈፀም ወንጀል በሰላሳ ዓመት እስራት ተቀጣ
በዓለም ዙሪያ ከሁለት ደርዘን በላይ ሴቶችን አደንዛዥ እጽ በመጠቀም የፆታዊ ጥቃት ያደረሰው አንጋፋው የማዕከላዊ መረጃ ኤጀንሲ (ሲአይኤ) መኮንን የ30 አመት እስራት ተፈርዶበታል።
ቅጣቱ የተላለፈው በ 48 አመቱ ብራያን ጄፍሪ ሬይመንድ ላይ ሲሆን የላ ሜሳ ካሊፎርኒያ ነዋሪ ነው። የጥፋተኝነቱ ወሳኔ የተላለፈው የጥቃቱ ሰለባዎቹ ደግ ፣ የተማረ እና የኤጀንሲው አካል ነው ብለው ባመኑት ሰው መታላቸውን የገለፁበትን ስሜታዊ የችሎት ሂደት ተከትሎ ነው። ዓለምን ከክፉ ይጠብቃል የተባለው ሰው ወንጀል ውስጥ መገኘቱ በፍርድ ቤቱ ተገልጿል።የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ዳኛ ኮሊን ኮላር-ኮተሊ አቃቤ ህግ የጠየቀውን ሙሉ የቅጣት ውሳኔ ከማስተላለፋቸው በፊት የወሲባዊ ጥቃት አዳኝ ሲሉ ተከሳሹን የገለፁት ሲሆን አሁን ወደ ማረሚያ ቤት ተከሳሹ ሲገባ ለማሰብ የተወሰነ ጊዜ ይኖረዋል ሲሉ ተደምጠዋል።
ከእስር ቅጣት በተጨማሪ ሬይመንድ ለተጎጂዎቹ 260 ሺ ዶላር ካሳ እንዲከፍል ተወስኗል። የዩናይትድ ስቴትስ አቃቤ ህግ ማቲው ግሬቭስ በሰጡት መግለጫ የሬይመንድ ቅጣት በህይወት ዘመኑ እንደ ወሲባዊ ወንጀለኛ ተደርጎ እንደሚቆጠር እና ቀሪውን የህይወት ዘመኑን በእስር ቤት እንደሚያሳልፍ ያረጋግጣል ብለዋል። ጥቃቱ የተፈፀመው በ2006 በተመሳሳይ መንገድ በሜክሲኮ፣ፔሩ እና በሌሎች ሀገራት የተፈፀመ መሆኑን አቃቤ ህግ ገልጿል። ሬይመንድ በቲንደር እና በሌሎች የፍቅር ቀጠሮ መተግበሪያዎች ላይ የሚያገኛቸውን ሴቶች በሜክሲኮ ሲቲ ወደሚገኘው በመንግስት በተከራየለት አፓርትመንት እና ወደ ሌሎች ቦታዎች ይወስድ ነበር።
ዋይን እና መክሰስ ሲያቀርብላቸው በውስጡ አደንዣዥ እፅን ይጨምር እንደነበር ተረጋግጧል። ራሳቸውን ሴቶቹ ሲስቱ እርቃናቸውን ፎቶግራፍ በማንሳት አንዳንድ ጊዜ የዐይናቸውን ሽፋሽፍት ከፍቶ ጣቶቹን አፋቸው ውስጥ ይከት እንደነበር አቃቤ ህግ ተናግሯል።ሬይመንድ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ሲያውቅ ሴቶቹን የሚያሳዩ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን ለመሰረዝ ሞክሯል። በፍርድ ቤት ውስጥ በቁጥር ብቻ ተለይተው የታወቁት 12 የሚሆኑ የሬይመንድ ተጎጂዎች እንዴት ሕይወታቸውን እንዳበላቸው ተናግረዋል ። አንዳንዶች ደግሞ ምን እንደደረሰባቸው እንኳን የተረዱት ኤፍ.ቢ.አይ ራሳቸውን ስተው የተደፈሩባቸውን ፎቶግራፎች ካሳያቸው በኋላ ነው።
ሰውነቴ በአልጋው ላይ ልክ እንደ ሬሳ ይመስላል ነበር ስትል አንድ ተጎጂ ስለፎቶዎቹ ተናግራለች። ሬይመንድ ከ500 በላይ የተጎጂዎችን ምስሎች የያዘ ስብስብ ነበረው። ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ ራሳቸውን የሳቱ እርቃናቸው የሆኑ ተጎጂዎችን ሲመለከት ያሳያል። በፍርድ ቤት ከነበሩት ሴቶች አንዷ "በህይወት ዘመኑ ባደረገው ድርጊት ባስከተለው መዘዝ እንደሚያዝን ተስፋ አደርጋለሁ" ስትል ተናግራለች። የቀድሞ ሰላይ ለዳኛው “የቁልቁለት ጉዞውን” እና ጥፋቱን በማሰላሰል ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰአታት እንዳሳለፈ ተናግሯል። "የቆምኩላቸውን ሁሉ ከድቻለው፣ እናም ምንም አይነት ይቅርታ እንደማይገባኝ አውቃለሁ" ብሏል። ምን ያህል እንዳዘንኩ የሚገልጹ ቃላት የሉኝም ሲል ተከሳሹ በፍርድ ቤት ቃሉን ሰጥቷል።
በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
የሀማስ መሪ የት እንዳሉ የሚያውቁት ሁለት ወይም ሶስት ሰዎች ብቻ መሆናቸው ተነገረ
የሐማስ ምንጮችን ጠቅሶ በለንደን የሚገኘው አሻርክ አል-አውሳት ጋዜጣ እንደዘገበው የሀማስ ቡድን መሪ ያህያ ሲንዋር የት እንዳለ የሚያውቁት ሁለት ወይም ሶስት ሰዎች ብቻ ናቸው። ከሁለት ወይም ከሶስት የማይበልጡ ሰዎች ያሉት በጣም አነስተኛ ቡድን ብቻ ያህያ ሲንዋት ያለበትን ያውቃሉ የተለያዩ ፍላጎቶቹን ያስጠብቃሉ እንዲሁም ከውስጥም ሆነ ከውጭ ካሉ የንቅናቄው መሪዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ያረጋግጣሉ ሲል ማንነቱ ያልታወቀ ምንጭ ተናግሯል።
ምንጩ ቀጥሏል እስራኤል "ብዙዎቹ የሐማስ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ መሪዎችን" ለመግደል ስትሞክር "ሲንዋር በእስራኤል የተሳካ የግድያ ዘመቻ ከተጠቁት መካከል የለም" ብሏል። ምንጮቹ ሲንዋር ከመሬት በላይ ወይም በጋዛ ውስጥ ባሉ ዋሻዎች ውስጥ ስሉመደበቁ አልገለፁም። ከፍልስጤም ግዛት ውጪ እንደማይገኝ ግን አክለዋል። በቀጠለው ውጊያ ከጋዛ ከተማ ሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ በሚገኘው የሼክ ራድዋን ሰፈር እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ ሰባት ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የእስራኤል ከአካባቢው ለቃችሁ ውጡ የሚለው ትእዛዝ የደረሳቸው የካን ዮኒስ እና ራፋህ ነዋሪዎች ከጠቅላላው የጋዛ ህዝብ አንድ ሶስተኛውን የሚሸፍን ስፍራ ሲሆን ይህም ከጥቅምት ወር ጀምሮ በዓይነቱ ትልቁ መፈናቀል እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ተናግረዋል ።ከ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጋዛ ውስጥ ውሃ ፣ ኤሌክትሪክ ፣ ምግብ ፣መድሃኒት እና ነዳጅ አቅርቦት ተቋርጦባቸው ክፍት በሆነ የዓለማችን ግዙፍ እስር ቤት ውስጥ ይኖራሉ ሲሉ የቻይና አምባሳደር ፉ ኮንግ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በሀምሌ ወር መጨረሻ እንደሚገናኙ የዋይት ሀውስ ባለስልጣናት የገለፁ ሲሆን የእስራኤል መሪ በዚህ ወር መጨረሻ ዋሽንግተን ዲሲን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በቆይታቸውም ለኮንግረሱ ንግግር ያደርጋሉ።የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት እንዳስታወቀው የእስራኤል ጦር ፍልስጤማውያንን እንደ ጦር ጋሻ እየተጠቀመ ነው የሚሉ ዘገባዎች የሚረብሽ ነው በማለት ገልጿል።
በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ተከትሎ በአማራ ክልል ስር ሲተዳደሩ የቆዩት የራያ አካባቢዎች ያለ አስተዳዳሪ ወደ ሁለተኛ ሳምንታቸው እየተሻገሩ ነው
ከየካቲት ጀምሮ አልፎ አልፎ ሲከሰት የነበረው “በህወሓት ታጣቂዎች” እና “በአካባቢው ሚሊሺያዎች” መካከል ሲደረግ የነበረው የተኩስ ልውውጥ ከሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍ ባለ ሁኔታ ተካሂዶ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወዲህ የነበረውን መዋቅር ቀይሮታል።
ላለፉት ሦስት ዓመት ገደማ አካባቢዎቹን ሲመሩ የነበሩት ከአማራ ክልል በኩል የተሾሙ አስተዳዳሪዎች፤ ከሚመሯቸው የራያ ወረዳ እና ከተሞች ሸሽተው ቆቦ ከተማ እና ሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ውስጥ ተጠልለዋል።
በቆቦ ከተማ የሚገኙት ከራያ አካባቢዎች የሸሹት የመንግሥት ሹመኞች ብቻ አይደሉም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በወጣው ሪፖርት 50 ሺህ ሰዎች ከራያ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደሮች እንደተፈናቀሉ አስታውቋል። ከተፈናቃዎቹ ውስጥ 42 ሺህ ያህሉ የሚገኙት በሰሜን ወሎ ዞን ስር በምትገኘው ቆቦ ከተማ እንደሆነ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። ሌሎች የራያ አካባቢዎች ነዋሪዎች ግን አሁንም ባሉበት ኑሯቸውን ቀጥለዋል።
የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የየራሳቸው አስተዳዳሪዎች የተሾሙላቸው የአላማጣ እና የኮረም ከተሞች ያለምንም አስተዳዳሪ ከቀሩ ሁለት ሳምንታት ተቃርበዋል። ከሁለቱም ክልሎች የተሾሙ አመራሮች የሚገኙት በየክልላቸው ውስጥ በሚገኙ አጎራቦች አካባቢዎች ውስጥ ነው።
በአላማጣ እና ኮረም ከተማዎች ውስጥ የፌደራል እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሚገኙ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሁለቱ ከተማዎች አምስት ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በከተሞቹ ውስጥ የሚገኙት የፌደራል መንግሥት እንዲሁም የአካባቢ አስተዳደሮችን ተቋማት እና ቢሮዎች እየጠበቁ ያሉት በሁለቱ የፀጥታ አካላት መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች በአሁኑ ሰዓት ከተማዋ ውስጥ አንጻራዊ ሰላም እንዳለ ጠቅሰዋል። ባንኮች፣ የኢትዮ ቴሌኮም ቢሮዎች እንዲሁም የተወሰኑ መደብሮች መከፈታቸውን ሦስት ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ መደብሮች ያልተከፈቱት አካባቢዎቹን ላይ አስተዳዳሪ አለመኖሩ በፈጠረባቸው ስጋት ምክንያት መሆኑን የሚናገሩ አንድ የአላማጣ ነዋሪ፤ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙት የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት እየተንቀሳቀሱ ያሉት በዋና የአስፓልት መንገዶች ላይ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከትግራይ ክልል በኩል የተሾሙት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ዝናቡ ደስታም በተመሳሳይ በከተማዋ ሁለቱ የፌደራል መንግሥት ኃይሎች ቢኖሩም የፀጥታ ሁኔታው በበቂ ሁኔታ እየተሸፈነ አለመሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በኩል የተሾሙት የአላማጣ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ በበኩላቸው የመከላከያ ሠራዊት እና ፌደራል ፖሊስ አባላት ከተማዋ ውስጥ መኖራቸውን አንስተው በአሁኑ ሰዓት ስላለው ሁኔታ ግን “ዝርዝር መረጃ” እንደሌላቸው ጠቅሰዋል።
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ የመንግሥት ኃላፊዎች ከአላማጣ መውጣታቸውን ተከትሎ በመንግሥት ተቋማት ደረጃ የሚሰጡ አገልግሎቶች እስካሁን ድረስ እንደቆሙ መሆኑን ሦስት ነዋሪዎች ገልጸዋል። የከተማዋ አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል።
አንድ የከተማዋ ነዋሪ*፤ “[የጤና አገልግሎት] የለም ማለት ይቻላል። አሁን በቅርብ አንዲት ወላድ ነበረች፤ ደም [ያስፈልጋል] ተብላ ወደ ወልዲያ ሄዳለች። ምንም ዓይነት አገልግሎት የለም። በጣም ተቸግራ እዚህ ያሉ ዶክተሮች በግል ተባበሯት፤ …ወደ ቆቦ በትራንስፖርት ሄዳ፣ ከቆቦ ወደ ወልዲያ ወሰዷት” ሲል በከተማዋ ላለው ሁኔታ ማሳያ ጠቅሷል።
በኮረም ከተማም በተመሳሳይ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች ዝግ መሆናቸውን ሦስት የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። የቀድሞ አስተዳዳሪዎች ለቀው በወጡባት ኮረም ከተማም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ተቋማት እየተጠበቁ ያሉት በፌደራል ፖሊስ እና በመከላከያ ሠራዊት አባላት መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁንና ከአላማጣ ከተማ በተለየ መልኩ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች በከተማዋ ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱ ሦስት ነዋሪዎች ገልጸዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ታጣቂዎቹ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ “ዝርፊያ ፈጽመዋል” ሲሉ ከሰዋል።
ታጣቂዎቹ የሰፈሩት በከማው ውስጥ በሚገኙት ስድስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ መሆናቸውን የሚናገሩ አንድ ነዋሪ፤ “የትምህር ቤት መጽሐፍት ‘የአማራ ክልል ናቸው’ በሚል ተቀድደዋል” ሲሉ በትግራይ ታጣቂዎች ተፈጽሟል ያሉትን ድርጊት ጠቅሰዋል።
ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው፤ በከተማዋ ውስጥ በታጣቃዎቹ በሚፈጸሙት ድርጊቶች ሳቢያ ነዋሪዎች አሁንም ወደ ቆቦ ከተማ እየሸሹ መሆኑን ተናግረዋል። በቆቦ ከተማ የሚገኙት በአማራ ክልል የተሾሙት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉም የኮረም ከተማ ነዋሪዎች አሁንም ወደ ቆቦ ከተማ እየገቡ መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በትግራይ ክልል በኩል የራያ አካባቢ ወረዳ እና ከተማዎችን በስሩ የያዘው የደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ፤ በኮረም ከተማ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች ገብተዋል ስለመባሉ እና ታጣቂዎቹ ፈጽመዋቸዋል ስለተባሉ ድርጊቶች ከቢቢሲ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
በአሁኑ ሰዓት በኮረም “በጣም የተረጋጋ ሰላም እና ደኅንነት” መፈጠሩን የሚናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ “ኮረም እና አላማጣም ላይ በአሁኑ ሰዓት የፌደራል ኃይሎች የፀጥታ እና ሰላሙን የመጠበቅ ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ እየፈጸሙ ነው” ብለዋል።
አቶ ሀፍቱ፤ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች በከተማዋ ስለመግባታቸው እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ ስለ መስረፈራቸው ማረጋገጫ ከመስጠትም ሆነ ከማስተባበል ተቆጥበዋል።
እንደ ራያ ባሉ አካባቢዎች ላይ ከዚህ ቀደም በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳደር መካከል የነበረው “ከመከላከያ ሠራዊት ውጪ ሌላ ታጣቂ ኃይል አይኑር” የሚለው “ንግግር” በአሁኑ ሰዓት “መቀየሩን” ዋና አስተዳዳሪ ገልጸዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነትን የተፈራረሙት የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ከስምምነቱ በታች ያሉ ጉዳዮችን በፖለቲካዊ ንግግር እየፈቱ እና “እያሻሻሉ” እየሄዱ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሀፍቱ፤ “ለምሳሌ አሁን ማሻሻያዎች አሉ።
በዚያ አካባቢ ከመከላከያ ሠራዊት እና ከፌደራል ፖሊስ ውጪ ማንኛውም ታጣቂ መኖር የለበትም የሚል የውይይት ሀሳብ እንደነበር ይታወቃል። አሁን እሱ ተቀይሯል። ሌላ እድገት አለው” ብለዋል።
ዋና አስተዳዳሪው “ተቀይሯል” ያሉት የታጣቂዎች ጉዳይ የሚወያዩት አካላት ይፋ እንደሚያደርጉት በመጥቀስ ዝርዝሩን ከመናገር ተቆጥባዋል።
ሁለቱ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ባለፉት ሳምንታት የተፈጠረውን ሁኔታ የአፍሪካ ኅብረት እና በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ አገራት ተወካዮች እንዳሰሰባቸው እና ሁሉም ወገኖች ከግጭት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ላይ የህወሓት ታጣቂዎች ወረራ ፈጽመዋል ብሎ ባለፈው ሳምንት የአማራ ክልል መንግሥት መክሰሱ ይታወሳል።
ለወሰን እና ለማንነት ጉዳዮች መፍትሄ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን የገለጸው የፌደራል መንግሥቱ የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው ሲል ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
Via ቢቢሲ
#ዳጉ_ጆርናል
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።
@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna
#ኢትዮጵያ
Last updated 3 недели назад
Last updated 2 недели, 2 дня назад
ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot
🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹
Last updated 1 месяц назад