ኦርዶቶክስ ሀገር ናት ✞

Description
✍ ✟ ቅዱሳነ ሰማይ ወምድር ማኅበረ ሥላሴ አንትሙ ዝክሩነ በጸሎትክሙ በእንተ ማርያም እሙ
.
.
.
.
.

.
.
.
.
.
.
.
.










https://t.me/ortodoxeth2112 በቴሌግራም እንዲሁም በtik tok tiktok.com/@abe_l2112
Advertising
We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated 1 day, 23 hours ago

Last updated 3 days, 5 hours ago

ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot

🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹

Last updated 2 weeks, 1 day ago

1 month, 2 weeks ago

በዲሜጥሮስ ቀመር መሠረት አጽዋማትን በጠበቀ መልኩ ከትንሣኤ በዓል በፊት ያለው ዓርብ “ስቅለት” ተብሎ እንዲከበር አባቶቻችን ሥርዓት ሠርተዋል፡፡

መጋቢት 27 ቀን በዓቢይ ጾም ላይ ስለሚውል በዓቢይ ጾም ሐዘን እንጂ ደስታ ስለሌለ፤ ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሮ በደስታ እንድናከብረው ቤተክርስቲያን ሥርዓት ሰርታልናለች።

ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ

👉 ሊቃነ መላእክት በመፍራት እና በመንቀጥቀጥ ከፊቱ የሚቆሙለትን በአደባባይ አቆሙት፤
👉 ኃጢአትን ይቅር የሚለውን ኃጥእ አሉት፤
👉 በመኳንንት በሚፈርደው በርሱ ፈረዱበት፡፡
እንዳለ።

መጋቢት 27 ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ

👉 ፀሐይ ጨልማለች
👉 ጨረቃ ደም ሆናለች
ከዋክብት ረግፈዋል

👉 በምድር የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለኹለት ተቀዷል፤
👉 ምድር ተናውጣ ዐለቶች ተሠንጥቀዋል፤
👉 መቃብራት ተከፍተዋል፤ ሙታን ተነሥተዋል፡፡

ስቅለቱን በዲሜጥሮስ ቀመር አውጥተን የጌታን መከራውን አስበን በስግደት ሕማማቱን እናስባለን በዝክረ ጥንተ ስቅለቱ በጥቅምት 27 ደግሞ በመስቀል የተደረገልንን አስበን እናመሰግነዋለን፡፡

የመድኃኔዓለም ይቅርታውና ቸርነቱ ሁላችንንም ይጠብቀን!
አሜን!

እንኳን ለክብረ በዓሉ በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ፡፡

1 month, 3 weeks ago

🕯 ...➋➊....🕯

🌷... እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም

🌹... ድንግል ሆይ...

🕯...እኔ የተጠማሁ ነኝ
አንቺ የወርቅ መቅጃ ነሽ ልጅሽ የሕይወት ውኃ ነው፡፡

🕯...እኔ ነጋዴ ነኝ
አንቺ መርከብ ነሽ ልጅሽ ዕንቈ ነው፡፡

🕯...እኔ ገደል ተሻጋሪ ነኝ
አንቺ ድልድይ ነሽ ልጅሽ የደስታ ሥፍራ ነው፡፡

🕯...እኔ ደሃ ነኝ
አንቺ የክብር ማከማቻ ነሽ ልጅሽ የከበረ ጌጥ ነው፡፡

🕯...እኔ ቁስለኛ ነኝ
አንቺ የመድኃኒት ብልቃጥ ነሽ ልጅሽ መድኃኒት ነው፡፡

🕯...እኔ ዕርቃኔን ነኝ
አንቺ የሸማኔ ዕቃ ነሽ ልጅሽ የማያረጅ ልብስ ነው

2 months ago

*💥 ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን 💥     
🍀 ጽንሐሕ 🍀*
ጽንሐሕ /ማዕጠንት/ የዕጣን ማጠኛ የእጣን ማሳረጊያ ቅዱስ ንዋይ  ነው።

የሚሠራውም ከወርቅ፣ ከብር፣ ከነሐስና ከብረት ሆኖ ቅርጽና ውበት እንዲኖረው ተደርጎ፣ ማንጠልጠያውና እያንዳንዱ ጌጥ ምሥጢሩን ጠብቆ ከቁጥሩ ሳይፋለስ ይዘጋጃል።

እግዚአብሔር ሙሴን ሸምሸር ሸጢን ከሚባል ከማይነቀዝ እንጨት ጽንሐሕ (ማዕጠንተ ወርቅ) እንዲሰራ አዞት እርሱም ሰርቶ ነበር ዘፀ.3ዐ÷6-1ዐ ዘፀ.37÷25-29

በሐዲስ ኪዳንም ጽንሐሕ የዕጣን መሥዋዕት ይቀርብበታል፡፡ ካህኑ እጀታውን ይዞ መንበረ ታቦቱን፣ ቅዱሳት ሥዕላቱን የቤተ መቅደሱን ዙሪያ፣ መሥዋዕቱን ወዘተ ያጥንበታል።

🌷  የጽንሐሕ የተለያዩ ክፍሎችና ምሳሌያዊ ትርጉማቸው  🌷

ጽንሐውን ስንመለከት የምናያቸው እያንዳንዳቸው ክፍሎች ራሱን የቻለ ምሥጢራዊ ትርጉም አላቸው።

፩. ሙዳይ የሚመስለው የጽንሐው ክፍል

ይኸ ዕጣንና እሳቱ የሚዋሐዱበት ሙዳይ የመሰለ ባለመክደኛ ክፍል ነው። እርሱም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ምሳሌ ነው፡፡ እሳቱ በዚህ ክፍል ተቀምጦ ጽንሐውን እንደማያቃጥለው እመቤታችንም እሳተ መለኮትን በማኅፀኗ ተሸክማው አላቃጠላትምና።

፪. የሙዳዩ መክደኛ

ይኸ ክዳን በላዩ ላይ መስቀል አለበት ይህም ከመስቀሉ ጋር በአንድነት የቀራንዮ ምሳሌ ነው፡፡ በቀራንዮ ኮረብታ የተተከለውን መስቀል በኅሊናችን እንድንሥል ያደርገናል፡፡ ገላ 311

፫. በመካከል የሚገኝ አንድ ዘንግ

በሦስቱ ዘንጎች መካከል የሚገኝና ከታች በክዳኑ ላይ ከሚገኘው መስቀል ጋር የሚገናኝ ዘንግ ነው።
ይኸ ዘንግ የቅድስት ሥላሴ የአንድነታቸው ምሳሌ ነው፤ ዘንጉ ከላይ ወደ ታች መውረዱ ወልደ እግዚአብሔር በተለየ አካሉ በተወላዲነት ግብሩ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ የመወለዱ የመሰቀሉ የመሞቱ ምሳሌ ሲሆን ከታች ወደ ላይ መውጣቱ ደግሞ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ የመነሣቱና የማረጉ ምሳሌ ነው።

በመቀጠል ከላይ ወደ ታች መውረዱ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሳው ሥጋ ዳግመኛ ለፍርድ ሊመጣ እንዳለው ያመለክተናል። በአጠቃላይ ይኸ ዘንግ የቅድስት ሥላሴን አንድነት፣ የእግዚአብሔር ወልድን ከልዕልና ወደ ትሕትና መውረድና ዞሮ ማስተማር፣ መሰቀሉን፣ ከሙታን ተለይቶ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱንና ማረጉን የሚያዘክር ነው።

፬. ሻኩራዎችን የያዙ ሦስት ዘንጎች

በመካከል ያለውን ዘንግ ከብበው ያሉና በላያቸው ሻኩራዎችን የያዙ ሦስት ዘንጎች ናቸው። እነዚህ ሦስት ዘንጎች እግዚአብሔር በመለኮት፣ በሕልውና አንድ ቢሆንም በስም፣ በግብር፣ በአካል ሦስት መሆኑን የሚያመለክቱ ናቸው። መካከለኛውን ዘንግ አይተን አንድነቱን ስናስብ በዚያው ያሉትን ሦስቱን አይተን ደግሞ ሦስትነቱን እናስባለን፡፡

፭. በሦስቱ ዘንጎች ላይ የሚገኙ ሻኩራዎች

እነዚህ ሻኩራዎች በቁጥር  ሃያ አራት ይሆናሉ፡፡ የሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ምሳሌ ናቸው፡፡

ጽንሐው ሲወዛወዝ ሻኩራዎቹ ድምፅ ይሰጣሉ።
ሻኩራዎቹ ሃያ አራት ሲሆኑ ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ በሰማይ የሚያሰሙት የምስጋና ድምፅ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” እያሉ የሚያመሰግኑት ምስጋና ምሳሌ ነው። ራእ 4፥7**

4 months, 2 weeks ago

ጾመ ፍልሰታ/ጾመ ማርያም/ 

?ፍልሰታ ማለት ፈለሰ፤ ተሰደደ፤ ተጓዘ፤ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄደ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ «ፈለሰት ማርያም እምዘይበሊ ኀበኢይበሊ፤ ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም፣ ከምድር ሕይወት ወደ ሰማያዊ ሕይወት፣ ተሻገረች» በማለት ፍልሰታ የሚለውን ቃል ትርጓሜ አመሥጥሮ ገልጾታል፡፡

?ጾመ ፍልሰታ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም የዕረፍት ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እመቤታችን በዚህ ዓለም ፷፬ ዓመታትን በሕይወተ ሥጋ ከቆየች በኋላ ጌታችን የእናቱን ተድላ ነፍሷን እንጂ ተድላ ሥጋዋን አይወድምና ጥር ፳፩ ቀን ፵፱ ዓመተ ምሕርት አረፈች፡፡ ዕረፍቷም እንደሌላው ሰው በሕማምና በድካም አይደለም፡፡ በገነት ዕፀዋት መዓዛ ተመስጣ ቅድስት ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይታለች፡፡

?ታሪኩ በነገረ ማርያም እንደተጻፈው ሐዋርያት እመቤታችንን በአጎበር አድርገው አክብረው ወደጌቴሴማኒ መካነ መቃብር ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉም ነበርና ቀድሞ ልጇን ተነሣ ዐረገ እያሉ ሲያውኩ ኖረዋል፤  እርሷን ደግሞ ተነሣች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን ነውና «ኑ የማርያምን ሥጋ በእሳት እናቃጥለው» ብለው በምቀኝነት ተነሱ፡፡ ከመካከላቸው አንድ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ከሐዋርያት እጅ ለመንጠቅ ዘሎ ሄዶ የአልጋውን ሸንኮር ሲይዝ የታዘዘ መልአክ በረቂቅ ሰይፉ እጆቹን ቆረጠው፡፡ እጆቹም በአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ የምሕረት እናት የሆነችው ድንግል ማርያም ቅዱስ ጴጥሮስ ጸልዮ እጆቹን እንዲመልስለት ነግራው እንደነበረ አድርጎለታል፡፡

?የእመቤታችን ሥጋዋን መላእክት ከዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር ወስደው አስቀምጠውታል፡፡ ሥጋዋ ያለበትን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ እነርሱ ባለማየታቸው እመቤታችን ባረፈች በ፮ኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን እስከ ፲፬ ቀን ድረስ ከጾሙ በኋላ በ፲፬ኛው ቀን ሥጋዋን እንደገና ከጌታ ተቀብለው በጌቴሴማኒ ባለው መቃብር ቀብረውታል፡፡

?ከዚህ በኋላ እንደ ልጇ በ፫ኛው ቀን ተነሥታ መላእክት እየዘመሩላት ወደሰማያት ስታርግ፤ ሐዋርያው ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሰ ዕርገቷን በማየቱ መላእክት «እመቤትህ እርሷ ናት፤ስገድላት» አሉት፤ እርሱም «ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ ይላል፤ከደመናው ሊወድቅ ወደደ» ምክንያቱም ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ የእርሷን ትንሣኤ ለማየት ብሎ ነው፡፡ እመቤታችንም «ትንሣኤየን ያየህ አንተ ነህ ሌሎቹ አላዩም» ብላ ሐዋርያት ገንዘው የቀበሩበትን የሐር ግምጃ ሰጥታ አጽናንታ ሰደደችው፡፡

?ቅዱስ ቶማስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የእመቤታችን ነገር እንዴት ሆነ ብሎ ጠየቃቸው፤እነርሱም አግኝተው እንደቀበሯት ነገሩት፤ እርሱም ያየውን ምሥጢር በልቡ ይዞ «ሞት በጥር፤ በነሐሴ መቃብር፤ ለሰሚውም አያምር፤ይህ እንዴት ይሆናል?»፤ ቢላቸው ቅዱስ ጴጥሮስ «ድሮም አንተ ተጠራጣሪ ነህ፤ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ እንዲሉ፤ ገንዘን የቀበረን እኛ እያለን እንዴት ትጠራጠራለህ» ብለው ወደ መቃብሯ ሄደው መቃብሯን ቢከፍቱት ባዶ ሆኖ አገኙት፡፡ በዚህ ተደናግጠው ተያዩ፤ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችን ተነሣች፤ዐረገች፤ ይኸው ምልክቱ» ብሎ ገንዘው የቀበሩበትን ሰበን አሳያቸው፤ እነርሱም አምነው ሰበኗን ለበረከት ተካፈሉት፡፡

?በዓመቱ ነሐሴ ፩ ቀን ሐዋርያት በመንፈሰዊ ቅናት ተነሳስተው «ቶማስ ትንሣኤዋን አይቶ እኛ ሳናይ እንዴት ይቀርብናል» በማለት ነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ጀምረው በ፲፮ኛው ቀን የሐዋርያትን ሱባኤ ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር ጴጥሮስን ተራዳኢ፣ ካህን እስጢፋኖስን ሠራዔ ዲያቆን አድርጉ ቀድሶ አቁርቧቸዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላም ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን  ጾመ ፍልሰታ ተብሎ ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ይጾመዋል፡፡

?የጾሙ እና የትንሣኤዋ በረከት ተካፋይ ያድረገን፤አሜን?
©ምንጭ :- ያሬዳውያን ቴሌግራም ቻናል

4 months, 2 weeks ago

#repost

አንድን ህጻን ልጅ ማሙሽዬ ድንግል ማርያም ላንተ ምንድን ናት
ብዬ ጠየኩት
."ድንግል መርያም ፊደሌ ናት " አለኝ
አንዲት ወጣትንም ድንግል ማርያም ላንቺ ማን ናት ብዬ ጠየኳት
."የደናግል መመኪያ ናት " አለችኝ ።
አንድንም ወጣት ጠየኩት
" ውበት ናት " አለኝ ።
.....
ስደተኛም ሰው አግንቼ ጠየኩ
" እሷ የስደተኞች ስንቅ ናት " አለኝ ።
....
አንዲት እናትንም ጠየኩ
" እሷ የአለም ሁሉ እናት ነች " አሉኝ ።
የቆሎ ተማሪውንም ጠየኩት
" ድንግል ማርያም መመኪያ ናት ስሟን ይዘህ አታፍርም " አለኝ ።
..
ዶክተሩንም ጠየኩት
" የመዳኒት እናት ነች " አለኝ
አናጢውንም ድንግል ማርያም ላንተ ምንድን ነች ብዬ ጠየኩት
.
"የአለም ሁሉ መሰላል ነች " አለኝ
.
አገልጋዩንም ጠየኩት
" የጻድቃን እመቤት ነች" አለኝ
ችግረኛ ድሀውንም ጠየኩት
" የሁሉ ሀብት ነች " አለኝ
.
ባለጸጋውንም ጠየኩት
"ድንግል ማርያም በረከት ነች " አለኝ
ወታደርም አግንቼ ጠየኩ
" ድንግል ማርያም ጋሻ መከታ ናት " አለኝ
.
ያረጁ አዛውንትም አግንቼ ጠየኩ
" ድንግል ማርያም ምርኩዝ ናት " አሉኝ
.........
....
በመጨረሻ ራሴን ጠየኩ
.
አይምሮዬም እንዲህ ብሎ መለሰልኝ
.....
የመስቀል ስር የአደራ ስጦታህ
.
የህይወትህ እንጀራ የተዘጋጀባት መሶብህ
የህይወትህ መጠጥ የተዘጋጀባት ፅዋህ
ከዘላለማዊ ፍዳ ወደ ዘላለማዊ ምህረት የተሻገርክባት መሰላልክ
እንኳን አንተ ቅዱሳን ምሳሌ ያጡላት ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን
እርሷን የሚመስል የሌለ ንግስተ ሰማይ ወምድር ናት።
ድንግል ማርያም የሁሉ መማሪያ ናት" አለኝ
ሁሉ ይማርባታል ፦ ፊደል መጽሀፍ እውቀት ነች ፡
ሁሉ ይማርባታል ፦ ምህረት ታስገኛለች ታማልዳላች ።
እርሷን የሰጠን ይክበር ይመስገን ??

4 months, 3 weeks ago

በብፁዕ አቡነ ናትናኤልና በዲያቆን እንዳለው መለሰ ወደ ኦሮምኛ የተተረጎመው ተአምረ ማርያም መጽሐፍ ተመረቀ፡፡

ሐምሌ ፳፬ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም (አቡቀለምሲስ ሚዲያ ፤ ደብረ ብርሃን)
++++    ++++   ++++   ++++   ++++    ++++   +

በሰሜን አሜሪካ የሚኒሶታና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ  ናትናኤል እና ዲያቆን እንዳለው መለሰ አዘጋጅነት በኦሮምኛ ፣ በግእዝና በአማርኛ ቋንቋዎች የተጻፈው ተአምረ ማርያም መጽሐፍ ዛሬ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ ላይ ተመርቋል።

መጽሐፉ በማኅበረ ቅዱሳን የኤዲቶርያል አገልግሎት ተመርምሮ ለኅትመት የበቃ ሲሆን አሳታሚና አከፋፋይ ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በሰሜን አሜሪካ የሚኒሶታና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቤተ ክርስቲያን በቋንቋ ማገልገልና መገልገልን ከሐዋርያት ተቀበላ እያስቀጠለች መሆኗን ገልጸው እኛም የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ኦርቶዶክሳውያንን መሠረት ያደረገውን መጽሐፍ  እንደ አቅማችን ተርጉመን ለኅትመት አብቅተናል ብለዋል፡፡

ብዙ ከማውራት ትንሽ መሥራት የተሻለ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ይህንን አድርገናል፣ በቀጣይ ደግሞ የትርጉም ሥራዎችን ከዚህ በበለጠ ለመሥራት መጽሐፍትን እየመረጥንና እየተመካከርን ነው ብለዋል፡፡

ቋንቋ ተግባብተን የምንለወጥበትና የምንስማማበት እንጅ መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት አይደለም ሲሉም አጽዕኖት ሰጥተዋል።

ብፁዕነታቸው ጨምረው እንደገለጹት መጽሐፉ የኦሮምኛ  ቋንቋ ተናጋሪ ምእመናንን መሠረት ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እኛ ይህንን የትርጉም ሥራ ለመሥራት ያነሳሳን ምክንያት የቤተ ክርስትያንን ተደራሽነት በመረዳት ምእመናን በቋንቋቸው እንዲገለገሉ በማሰብ ነው ያሉት ዲያቆን እንዳለው ቋንቋን ምክንያት በማድረግ በአጉል ትርክት የተጠቁ ሁሉ ሊማሩበት የሚገባ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ መምህር ዋሲሁን በላይ  በበኩላቸው ማኅበረ ቅዱሳን መንፈሳዊ አገልግሎትን ለማስፋፋት መጽሐፍትን በተለያዩ ቋንቋዎች በመተርጎም ረገድ ዘርፈ ብዙ ሥረዎችን መሥራቱንና ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

ፀሐይሽ አትጠልቅም መንፈሳዊ ማኅበረ ለብፁአን አባቶችና መጽሐፉ ለሚያስፈልጋቸው አብያተ ክርስቲያናት እንዲደርስ 100 መጽሐፍትን ወስደዋል።

በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ በሰሜን አሜሪካ የሚኒሶታና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ሌሎች ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ መምህር ዋሲሁን በላይና የማኅበራት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

ዘገባው፦የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል ነው።

7 months, 1 week ago

[ግንቦት 11 የቅዱስ ያሬድ ዓመታዊ በዓል]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አባቱ አብዩድ (ይሥሐቅ) እናቱ ክርስቲና (ታውክልያ) ሲባሉ የተወለደውም በ፭፻፭ ዓ.ም. በአክሱም ነው፡፡ ሰባት ዓመት ሲመላው አባቱ ስላረፈ፤ እናቱ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲያስተምረው ለአባ ጌዴዎን ሰጠችው፡፡

ነገር ግን ማጥናት ስላልቻለ አባ ጌዴዎን ይቈጣው ነበርና ሸሽቶ ከዱር ውስጥ ገባ፤ ከዐዘኑም ብዛት የተነሣ በዛፍ ሥር ተጠልሎ ሳለ አንዲት ታናሽ ትል ከዛፍ እኩሌታ ደርሶ ሲወድቅ ሲነሣ በመጨረሻም በጭንቅ ከዛፉ ላይ ሲወጣ በማየቱ እግዚአብሔር በዚኽች ታናሽ ፍጥረት እንዳስተማረው በመረዳት ይቅርታ ጠይቆ ወደ መምህሩ ተመልሷል፡፡

“ወእምዝ ሶበ ሰአለ ኀበ እግዚአብሔር በብካይ ብዙኅ ተርኅወ ልቡናሁ ወተምህረ በሐጺር ዕለት መጻሕፍተ ብሉይ ወሐዲስ” ይላል ከዚኽ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ እግዚአብሔር በለመነ ጊዜ ልቡናው ብሩህ ኾኖለት በዐጭር ጊዜ ውስጥ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተምሮ በመጨረስ ዲቁናን ተሾመ፤ እስከ ርሱ ዘመን በማነብነብ እንጂ በከፍተኛ ድምፅ የመዝሙር ማሕሌት አልነበረም፤ እግዚአብሔርም ለዚኽ አባት የመላእክትን ዝማሬ ሊያሳየው ስለወደደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ሦስተኛው ሰማይ እንደተነጠቀ ኹሉ ሊቁም ተነጥቆ የኻያ አራቱ ካህናተ ሰማይን የምስጋና ዝማሬ ሰምቶ ተመለሰ፡፡

ቅዱስ ያሬድ ከአርያም ወርዶ ወደ ምድር እንደ ደረሰ ወደ አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ገብቶ፡- “ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ” (ለአብ ምስጋና ይገባል፣ ለወልድም ምስጋና ይገባል፣ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል፡፡ ከጽዮን አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ ዳግመኛም ለሙሴ የድንኳኑን ሥራ እንዴት እንደሚሠራ አሳየው) ሲል ዘምሮ ይቺኑ መዝሙር ከሰማይ መላእክት አገኘኹት፣ በማለት "አርያም" በሚል ሥያሜ ጠርቷታል፡፡

ይኽነኑ ድርሳነ ዜማ የጻድቁ ካሌብ ልጅ ንጉሥ ገብረ መስቀል በሰማ ጊዜ ጫማውን ሳይጫማ ንግሥቲቱም ደንገጡሮቿን አጃቢዎቿን ሳታስከትል መኳንንቱ፣ ካህናቱና መምህራኑ እነሱን ተከትለው እየተጣደፉ ወደ ዐደባባዩ በመኼድ በተመስጦ ሲሰሙት ውለዋል፡፡

ቅዱስ ያሬድ ዐምስት የዜማ መጻሕፍትን የደረሰ ሲኾን እነርሱም፦
፩ኛ) ድጓ  
፪ኛ) ጾመ ድጓ
፫ኛ) ምዕራፍ
፬ኛ) ዝማሬ
፭ኛ)መዋሥዕት ናቸው፡፡

እነዚኽንም ታላላቅ ድርሰቶቹን በሦስት የዜማ ስልቶች ማለት በግእዝ፣ በዕዝል፣ በአራራይ አዘጋጅቷቸዋል፡፡ “ወአሐተ ዕለተ እንዘ ይዜምር ያሬድ ቀዊሞ ታሕተ እገሪሁ ለንጉሥ ገብረ መስቀል ወእንዘ ያጸምዕ ንጉሥ ቃሎ ለያሬድ ተከለ በትረ ኀጺን ውስተ መከየደ እግሩ ለያሬድ” ይላል፤ ከዕለታት ባንዳቸው ቅዱስ ያሬድ በተመስጦ ልዑል እግዚብሔርን በዝማሬ ሲያመሰግን ንጉሥ ገብረ መስቀል ሳያውቁት ልባቸው በጣዕመ ዜማው በመመሰጡ የብረት ዘንጉን በቅዱስ ያሬድ እግር ላይ ተክለውታል፤ ከእግሩም ብዙ ደም ቢፈስስም ቅዱስ ያሬድ ግን ማሕሌቱን እስከሚፈጽም ድረስ ምንም አልሰማውም ነበር፡፡

ንጉሡም የደሙን መፍሰስ አይቶ ደንግጦ ቅዱስ ያሬድን “የደምኽ ዋጋ የፈለግኸውን ንገረኝ” አለው፤ ቅዱስ ያሬድም ተምኔቱ ወደ ገዳም መኼድ እንደኾነ ነገረው፤ ያን ጊዜ ንጉሡ እያዘነ አሰናብቶታል፡፡

“ወእምዝ ቦአ ያሬድ ውስተ ቤተ ክርስቲያን ወቆመ ቅድመ ታቦተ ጽዮን” ይላል ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በታቦተ ጽዮን ፊት በመቆም የአንቀጸ ብርሃንን ምስጋና ከመዠመሪያው እስከ መጨረሻው በተናገረ ጊዜ በእግዚአብሔር ኀይል ክንድ ያኽል ከምድር ከፍ ከፍ አለ።

ከዚኽ በኋላ ወደ ሰሜን ተራራዎች ወደ ገዳም ሲኼድ የአኲስም ጽዮን ካህናት እስከ ተከዜ ወንዝ ድረስ ሸኙት ርሱም እጅግ ባማረ ጣዕመ ዜማ ድምፁን ከፍ አድርጎ “ሰላም እግዚአብሔር ኲሉ ባቲ ተሃሉ ወትረ ምስለ ኲልክሙ” (በኹሉ ላይ ጸንታ የምትኖር የእግዚአብሔር ሰላም ዘወትር ከኹላችኊ ጋር ትኑር) ብሎ የስንብት መዝሙርን ዘመረ፤ ካህናቱም ይኽነን ቃል ሰምተው መሪር እንባን አለቀሱና ተሰነባበቱ፡፡

በትርጓሜ ቅዳሴ ማርያም መቅድም ላይ እንደምናነብበው ቅዱስ ያሬድ ማይ ኪራህ በተባለው ቦታ ተሰውሮ ጸዋትወ ዜማን ሲያስተምር እመቤታችን ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬምን የብህንሳውን አባ ሕርያቆስን በአካለ ነፍስ እንዲመጡ አድርጋ ኤፍሬም ውዳሴዬን፤ ሕርያቆስ ቅዳሴዬን ነግራችኹት ቅዱስ ያሬድ በዜማ ይድረስልኝ ብላ ነግረውት በዜማ ደርሶታል፤ ይኽም ሊታወቅ ሥረይ በቅዳሴ ማርያም ይበዛል፡፡

ርሱም ጸዋትወ ዜማን ለደቀ መዛሙርቱ እያስተማረ መላእክት ዘወትር እየጐበኙት በጾም በጸሎት ተወስኖ በተጋድሎ ለኻያ ኹለት ዓመት ጸንቶ ኖረ፤ በመጨረሻም ጌታችንም ለቅዱስ ያሬድ ተገልጾለት፦

“ኦ ፍቁርየ ቀዳሚኒ በከመ ሰመርኩ ትርአይ ሥርዐተ ስብሐተ መላእክት ዘበሰማያት ወአስተኀለፍከ ዘንተ ማሕሌተ ዲበ ምድር... ” (ወዳጄ ሆይ ቀድሞ በሰማይ ያለ የመላእክትን ሥርዐተ ማሕሌት እንድታይና ወደ ምድርም አስተላልፈኽ ይኽነኑ ዜማ እንድትመሠርት እንደ ወደድኊ ኹሉ እኔ ዳግም ተመልሼ በምመጣበት ጊዜ ከካህናተ ሰማይና ሄሮድስ ደማቸውን ካፈሰሰው ሕፃናት ጋር በደብረ ጽዮን ትዘምር ዘንድ ሰማያዊ የክብር አክሊልና የብርሃን ልብስ ተዘጋጅቶልኻል” ብሎት ቃል ኪዳንን ሰጥቶት ጌታ በክብር ዐረገ፡፡ የቅዱስ ያሬድ መታሰቢያውም ግንቦት ዐሥራ አንድ ነው፡፡

ሊቁ አርከ ሥሉስም የቅዱስ ያሬድን ነገር በአርኬው ላይ፦
“ሰላም ለያሬድ ስብሐተ መላእክት ለሕዋጼ
እንተ አዕረገ በልቡ ኅሊና መንፈስ ረዋጼ
ለትምህርተ መጽሐፍ ገብአ እምኀበ ኮነ ነፋጼ
በብዙኅ ጻማ ዘአልቦ ሑጻጼ
መልዕልተ ጒንደ ዖም ነጺሮ እንዘ የዐርግ ዕጼ”

(የመላእክትን ምስጋና ለመጐብኘት ከመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ፈጣን ዐሳብን ወደ ልቡናው ያሳረገ ለኾነ፤ ጒድለት በሌለበት በብዙ ድካምም ወደ ዛፍ ግንድ ጫፍ ላይ ትል ሲወጣ ተመልክቶ፤ ኰብልሎ ከኼደበት መጻሕፍትን ለመማር የተመለሰ ለኾነ ለያሬድ ሰላምታ ይገባል) በማለት ሊቁ ማሕሌታይን አመስግኖታል፡፡

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፉ ላይ ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ሊቁ ቅዱስ ያሬድን ሲያወድስ፡-
“ሰላም ለያሬድ ቀሲስ ዘጽጉብ እክለ መንፈስ ቅዱስ፤
ዘአስተጋብአ ምድራሳተ እምኲሎሙ መጻሕፍት
ወአሰርገዋ በሐዋዝ ስብሐት ወበጥዑም ማሕሌት
ለብሔረ ኢትዮጵያ በስብሐት ሃሌ ሉያ
ዘከዐወ ቃለ መለኮት ዲቤሃ
ከመ አስራበ ወርቅ ንጹሐ”፡፡

(የመንፈስ ቅዱስን ምግብን የጠገበ፤ ከመጻሕፍት ኹሉ ትርጓሜያተ ድርሰትን ያሰባሰበ፤ ሃሌ ሉያ በሚል ምስጋና የኢትዮጵያ ሀገርን በጥዑም ማሕሌትና በሚያምር ምስጋና ያስጌጠ፤ የመለኮት ቃልን በላይዋ ላይ እንደ ንጹሕ የወርቅ ሻሻቴ ያፈሰሰ ለኾነ ለካህኑ ያሬድ ሰላምታ ይገባል) ይለዋል፡፡

የቅዱስ ያሬድ በረከት ይደርብን፤ እናንተም ይኽነን ሊቅ አወድሱት።
✍️ በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

7 months, 1 week ago

**በ Online ገንዘብ መስራት ትፈልጋላችሁ?

በኢንተርኔት Dollar መሰብሰብ ይቻላል።
ኑ እንስራ!
?**
@Nahwork
@Nahwork

7 months, 1 week ago

#ጌታችን_አርባ_ቀን_ምን_ይሠራ_ነበር?

የጌታችን መዋዕለ ሥጋዌ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል፦

  1. ቅድመ መስቀል፦ ቅድመ መስቀል የምንለው 33 ዓመት ከ 3ወሩን ነው፤ ይህ ጊዜ ኃጢአት ያልሆነ ማንኛውም ነገር በክርስቶስ የተከናወነበት ልዩ ጊዜ ነው፡፡

  2. ድኅረ መስቀል፦ ድኅረ መስቀል የምንለው ደግሞ 40ዎቹን ቀናት ወይም 1 ወር ከ10 ቀናትን ነው፡፡
    (ከዕርገት እስከ ጰራቅሊጦስ ያሉትን 10 ቀናት ለብቻ እናያቸዋለን)

ጌታችን ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኀላ 40 ቀን በዚህ ምድር ቆይቷል ፡፡ በነዚህ ቀናት ውስጥም በዋናነት 2 ዋና ዋና ሥራዎችን እንደሠራ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡

  1. ለሐዋርያት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እና መጽሐፈ ኪዳንን ማስተማር፦
    ለቅዱሳን ሐዋርያት በጉባኤ የተገለጠላቸው 3 ቀናት ቢሆንም ለእያንዳንዳቸው ለየብቻም 2 ወይም 3 ሆነው ግን ሳይገለጥላቸው የዋለበት ያደረበት ጊዜ አልነበረም፡፡
    "ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው" እንዲል ሉቃስ ፤ሐዋ 1 : 3፡፡

በተገለጠላቸውም ጊዜ ቤተ ክርስቲያን እንዴትና በምን በማን መተዳደር እንዳለባት አስተምሯቸዋል፡፡ ለምሳሌ ፦
" እርሱም። መረቡን በታንኳይቱ በስተ ቀኝ ጣሉት ታገኙማላችሁ አላቸው። ስለዚህ ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ ሊጐትቱት አቃታቸው" ፤ ዮሐ 21 :6 ፤ በማለት ቅዱስ ዮሐንስ እንደጻፈው መረቡ በቀኝ እንዲጣል ማዘዙ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሁሉ በቀኝ በክብርና በፍቅር እንደሚፈጸም ያሳያል፡፡ ሐዋርያት እንደ ቃሉ መሠረት ማድረጋቸው ደግሞ ቤተ ክርስቲያን የምትፈጽመው ሥርዓት ሁሉ መሠረቱ የጌታ ቃል እንደሆነ ይህም በማመን የሚፈጸም መሆኑን ያመለክታል፡፡

ዓሣዎቹም በየጊዜው የሚያምኑ የሚጠመቁ ምእመናን ምሳሌዎች ናቸው፤ ቀጥሎ በተዘጋጀው ማእድ በአንድነት መመገባቸውም የሁላችን ማእድ የሚሆነውን ከመላእክት ጋር የምናመሰግነውን የምስጋናችንን አንድነት ያመለክታል፦

" ወደ ምድርም በወጡ ጊዜ ፍምና ዓሣ በላዩ ተቀምጦ እንጀራም አዩ"፤እንዲል ዮሐ 21 : 9፡፡

ይህንም ማእድ መላእክት እንዳዘጋጁት መተርጉማነ ሐዲስ ገልጸዋል፦ ትርጉሙ ኅብረተ መላእክት ወሰብእ ነው፡፡ "ወኅብስተ መላእክቲሁ በልዑ እጓለ እመ ሕያው"( ሰዎች የመላእክትን ምግብ በሉ) የሚለው ትንቢተ ዳዊት የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜው በዚህ ፍጻሜውን አግኝቷል፤ መዝ 77፡25፡፡ በዓለም መጨረሻም የሚሆነው ይኸው ነው፤ ከመላእክት ጋር ለዘለዓለም ማመስገን!!!

ከዚህም ቀጥሎ ደግሞ ለጴጥሮስ በጎቹን የመጠበቅ ኃላፊነቱን (ክህነትን) አጠንክሮ አደራ ይለዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ሁሉ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ ለዚህም መጠበቂያ መመሪያ የሚሆን ጸሎት 7ቱን ኪዳናት አስተምሯቸዋል፡፡

  1. ለነፍሳት አህጉራተ ገነትን ማካፈልና ምሥጢረ መንግሥተ ሰማያትን ማሳየት፦

ገነት በ15 አህጉራት እኩል የተከፈለች መሆኗን አበው አስተምረውናል፤ ዓለማችን በሰው ሰራሽ አከፋፈል መሠረት 7 አህጉራት አሏት፤ ገነት ግን የአንዱ አህጉር መጠን ባይታወቅም ቅሉ በ15 አህጉራት የተከፋፈለች ሰፊ መሆኗን ያሳያል፤ ይህች ዓለም የቅጣት ቦታችን ናት (ምድረ ፋይድ) ገነት ግን ጥንተ ርስታችን ናት፡፡ ጌታ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ካወጣ በኀላ ወደ ገነት አሳልፏቸዋል፤ እርሱ ባወቀም ነፍሳት መኖር በሚገባቸው እያመሰገኑ እንዲኖሩ ቦታ ቦታቸውን አስይዟቸዋል፤ ፍጡር ሆኖ ያለ ቦታ መኖር አይቻልምና፡፡

"በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው" እንዲል ቅ.ጴጥሮስ፤
1ኛ ጴጥ 3 : 19፡፡

ገነት ከገቡ በኀላም ገነት የዘለዓለም መኖሪያቸው እንዳልሆነችና ለዘለዓለም የሚያወርሳቸውን የማታልፈውን የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር አስተምሯቸዋል፡፡

"ወነበረ አርብዓ መዋዕለ እንዘ ይሜሕሮሙ ምሥጢረ መንግሥተ ሰማያት" እንዲል መቅድመ ወንጌል፡፡
የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር በዓይነ ሥጋ ማየት፤ በእዝነ ሥጋ መስማት፤ በአእምሮ ጠባዕይ ማወቅ አይቻልም፤ የሚታወቀው በአእምሮ መንፈሳዊ በዓለመ ነፍስ ነውና ለነፍሳት አስተማራቸው፤ ይህም መዓርግ ወይም ደረጃ ነው፤ ምሥጢራትን የምናውቅበት ደረጃ አለ በዓለመ ነፍስ የምንረዳውን በዓለመ ሥጋ አንረዳውም ፦

"ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ፤ እንዳለ ቅ.ጳውሎስ፡፡
1ኛ ቆሮ13 : 12፡፡

ዳግመኛም፦
"ነገር ግን ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን"፤  ብሏል፡፡
1ኛ ቆሮ 2 : 9፡፡

እኛም በዚህ በዓለ ሃምሳ ስለ ምሥጢረ ትንሣኤና ስለ ዘለዓለማዊው ሕይወት አብዝተን የምንማርበትና የምንመረምርበት ሊሆን ይገባል፡፡

አምላካችን ምሥጢሩንና ጥበቡን ሁሉ ይግለጥልን!!!

አሜን!

መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ ከፍያለው

7 months, 1 week ago

?<<< በስመ አብ : ወወልድ : ወመንፈስ ቅዱስ : አሐዱ አምላክ . . . አሜን:: >>>

<< ?በበዓለ ሃምሳ ንስሃ ለምን ተከለከለ? ?>>

=>በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያለ ምክንያት የሚደረግ : ያለ ምሥጢርም የሚከወን ምንም ነገር የለም:: የሃይማኖትን ትምህርት አብዝተን በተማርን ቁጥር የምናውቀው አለማወቃችን ነውና ምንም ያህል ብንማር : የአዋቂነት መንፈስም ቢሰማን ከመጠየቅ ወደ ጐን አንበል:: መጠየቅ ለበጐ እስከሆነ ድረስ ሁሌም ሸጋ ነው:: ግን ልብን እያጣመሙ ቢያደርጉት ደግሞ ገደል ይከታል::

+ወደ ጉዳዬ ልመለስና ሁሌ የሚገርመኝ የትውልዱ አመለካከት ነው:: ጾም ሲመጣ "ለምን? . . . አልበዛም? . . ." ዓይነት ቅሬታዎች ይበዛሉ:: በዓለ ሃምሳ ሲመጣ ደግሞ "እንዴት ይህን ያህል ቀን ይበላል? . . ." ባዩ ይከተላል::

+ቤተ ክርስቲያን ግን ሁሉን የምትለን ለጉዳይ : ለምክንያትና ለእኛ ጥቅም ነው:: ለምሳሌ:- በዓለ ሃምሳ ድንገት እንደ እንግዳ ደርሶ : እንደ ውሃ ፈሶ የመጣ ሥርዓት አይደለም:: ይልቁኑ ምሳሌ ተመስሎለት በብሉይ ኪዳንም ሲከወን የነበረ እንጂ::

+እንደሚታወቀው እስራኤል ከግብጽ ባርነት በ9 መቅሰፍት : በ10ኛ ሞተ በኩር ወጥተው : በ11ኛ ስጥመት ጠላት ጠፍቶላቸው ወደ ምድረ ርስት ተጉዘዋል:: ቅዱስና የእግዚአብሔር ሰው ሙሴም ከእግዚአብሔር እየተቀበለ ብዙ ሥርዓቶችን ለቤተ እስራኤል አስተምሯል::

+እነዚህ ሥርዓቶች ሁሉ ለሐዲስ ኪዳን ምሥጢረ ድኅነት ጥላና ምሳሌዎችም ነበሩ:: በኦሪት ዘሌዋውያን ላይ ጌታ እንዲህ ይላል:-
". . . ከሰንበት ማግስት ፍጹም ሰባት ጊዜ ሰባት ቀን ቁጠሩ:: እስከ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቁጠሩ:: አዲሱንም የእህል ቁርባን ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ::" (ዘሌ. 23:15)

+ይህም "በዓለ ሰዊት (የእሸት በዓል)" የሚባል ሲሆን ከፋሲካ 7 ሱባኤ (49 ቀን) ተቆጥሮ : በሰንበት (ቅዳሜ) ማግስት (እሑድ ቀን) በዓለ ሃምሳ ይውላል:: በዓሉ በግሪክኛው "ዸንጠቆስቴ (Pentecost)" ይባላል:: "በዓለ ሃምሳ" እንደ ማለት ነው::

+ለዚያም ነው ቅዱስ መጽሐፍ የመንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት በዚህ ቀን መሰጠትን ሊነግረን ሲጀምር "ወአመ ተፈጸመ መዋዕለ ዸንጠኮስቴ . . ." የሚለው:: (ሐዋ. 2:1) በዓለ ሃምሳ (50ው ቀናት) በብሉይ "የእሸት በዓል" ቢባሉም ለሐዲስ ኪዳን ግን "የሰዊት (እሸት) መንፈሳዊ" ዕለታት ናቸው::

+ጌታ መድኃኔ ዓለም ስለ እኛ መከራ ተቀብሎ : ሙቶ ከተነሳ በሁዋላ 50 ያሉት ቀናት የዕረፍት : የተድላ : የመንፈሳዊ ሐሴት ቀናት ናቸው:: በእነዚህ ዕለታት ማዘን : ማልቀስ : ሙሾ ማውረድ : ንስሃ መግባት ወዘተ. አይፈቀድም::

=>ለምን?

1.ለእኛ ካሣ በጌታችን መፈጸሙን የምሰናስብባቸው ቀናት ናቸውና:: በእነዚህ ዕለታት ብናዝን "አልተካሰልንም" ያሰኛልና::

2.በዚህ ጊዜ መስገድ : መጾም "ክርስቶስ በከፈለልን ዋጋ ሳይሆን በራሴ ድካም (ተጋድሎ) ብቻ እድናለሁ" ከማለት ይቆጠራልና::

3."ፍስሐ ወሰላም ለእለ አመነ - ላመን ሁሉ ደስታና ሰላም ተደረገልን" ተብሎ በነግህ በሠርክ በሚዘመርበት ጊዜ ማዘን . . . ሲጀመር ካለማመን : ሲቀጥል ደግሞ "ደስታው አይመለከተኝም" ከማለት ይቆጠራልና::

4.50ውም ቀናት እንደ ዕለተ ሰንበት ይቆጠራሉና:: መጾምና መስገድ በዓል ያስሽራልና::

5.ዋናው ምሥጢር ግን እነዚህ 50 ዕለታት የአዝማነ መንግስተ ሰማያት (የሰማያዊው ዕረፍት) ምሳሌዎች ናቸው::

ስለዚህ በእነዚህ ቀናት መጾም : መስገድ "መንግስተ ሰማያት ውስጥ ከገቡ በሁዋላ ድካም : መውጣት መውረድ አለ" ያሰኛልና ነው::

+በዚያውም ላይ "ኢታጹርዎሙ ጾረ ክቡደ (ከባድ ሸክም አታሸክሙ)" የተባለ ትዕዛዝ አለና ቅዱሳን አበው በጾም የተጐዳ ሰውነት ካልጠገነ ወጥቶ ወርዶ : ሠርቶ መብላት ይቸግረዋልና ሰውነታችን እንዲጠገን : ይህንን በፈሊጥ ሠርተዋል::

+ስለዚህም:-
"ሐጋጌ አጽዋም እምስቴ::
ወሠራዔ መብልዕ በዸንጠኮስቴ::" እያልን አበውን እናከብራለን:: (አርኬ)

+ስለዚህ በበዓለ ሃምሳ ጾም : ስግደት : ንስሃ : ሐዘን : ልቅሶ . . . የለም:: አይፈቀድምም::
<<ግን ይህንን ተከትሎ 50ውን ቀን ሙሉ ሆድ እስኪተረተር ከበላን ጉዳቱ ሥጋዊም : መንፈሳዊም ይሆናል!!>>

+አበው እንደነገሩን "እንደ ልባችሁ ብሉ" ሳይሆን የተባለው "ጦም አትዋሉ" ነው:: ለምሳሌ:-

1.በልቶ ጠጥቶ ከሚመጣ ኃጢአት : ክፋትና ፈተና ለመጠበቅ 50ውን ቀናት ጥሬ የሚበሉ አሉ::
2.ጠዋት ተመግበው ከ24 ሰዓት በሁዋላ ጠዋት የሚመገቡ አሉ::
3.መጥነው ጥቂት በልተው አምላካቸውን የሚያመሰግኑ አሉ::
4.ነዳያንን አጥግበው እነርሱ ከነዳያን ትራፊ የሚቀምሱ አሉ::

+እኛም ከእነዚህ መካከል የሚስማማንን መርጠን ልንከውን : በተለይ ደግሞ በጸሎት ልንተጋ ይገባል:: አልያ ብሉ ተብሏል ብለን ያለ ቅጥ ብንበላ : ብንጠጣ እኛው ራሳችን የሰይጣን ራት መሆናችን ነውና ልብ እንበል:: ማስተዋልንም ገንዘብ እናድርግ::

"እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና:: እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ::
ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና:: ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው::
ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና:: ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና:: መገዛትም ተስኖታል::
በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም::" (ሮሜ. 8:5)

=>አምላከ ቅዱሳን ማስተዋሉን ያድለን::

<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>
በዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ

We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated 1 day, 23 hours ago

Last updated 3 days, 5 hours ago

ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot

🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹

Last updated 2 weeks, 1 day ago