ወግ ብቻ

Description
✔በየቀኑ ምርጥ ምርጥ የጥበብ ስራዎችን ለማግኘት የቻነላችን ተከታይ ስለሆኑ እናመሰግናለን።

✔ @getem @serenity13
✔ @wegoch @Words19
✔ @seiloch
✔ @zefenbicha

Creator @lula_al_greeko
We recommend to visit

"ይህ የቴሌግራም ቻናሌ ግንቦት1/2011ዓም የተከፈተ ነው። የእኔን የስልክ ወጪ ጨምሮ አገልግሎቴን መደገፍ የምትፈቅዱ ጓደኞቼ በ
👉🏿 https://donorbox.org/zemedemedia እና
👉🏿 https://www.paypal.com/paypalme/ZemedkunB በኩል ማገዝ ትችላላችሁ። በተረፈ ለቤተ ክርስቲያኔና ለኢትዮጵያ ሀገሬ የሚጠቅመውን ሁሉ አበረክት ዘንድ አብዝታችሁ ጸልዩልኝ።

Last updated 1 month ago

The first Telecom operator in Ethiopia https://t.me/EthiotelecomChatBot

Last updated 1 month, 2 weeks ago

ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot

🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹

Last updated 1 week, 2 days ago

1 week, 3 days ago

ክፍል ሁለት

ስመለስ ሌላ ነገር እንደሌለ ሁሉ ክረምት እስኪደርስ ስሙን ዘርዓ እንዳስጠናኝ ወንጌለ ዮሐንስ የምደጋግምለት ክብሮም፣አያቶቼ ጋር አስሬ በመደወልና ዘርዓን ፈልጌው ነው እያልኩ ጥያቄዬን ትቼ ስለእርሱ ቀን ውሎ ወንድሜን  የምነዘንዝለት ክብሮም፡፡ የሆነ ጊዜ ከስድስተኛው ጽጌ ማኅሌት አዳር በኋላ የትላልቆቹን አቋቋምና እሱ ከበሮውን ይዞ እንዴት ሲያጅባቸው እንደነበር ከዜማው ጋር ለእኔና ዘርዓ እያሳየ ተመየጢ ተመየጢ ወይትጎንድኢ ብሎ ሳናስበው ተንሸራቶ ሲወድቅ እኔና ዘርዓ ልባችን እስኪፈርስ የሳቅነው ተመልሶ እግሩን እያመላከተ ስለተፈጠረው የቴክኒክ ስህተት ይቅርታ ብሎ በቀደመው ሀይሉ ተመየጢ ብሎ ሲጀምር ዘርዓ ተቀላቅሎት ተመየጢ እያልን ያመሸንበት፡፡ ክብሮም ናተይ፤እሱንስ ተመየጢ(ተመለሺ) እያለ እንዳትዘገይ የሚለማመናት፣ማኅሌቷን ቀጥ ብሎ የሚቆምላት ፣ልጅነቱን ለውዳሴዋ የሰጠላት ርኅርኂት እመቤት እንዳለችው ይረዱ ይሆን  ከወንዞች ማዶ ይሄንን እያሰበች የምትፅፍ፣ወደፊት ስለእርሱና እሷ ስታስብ የነበረ፣ክረምት አልፎ ልታየው የምትናፍቅ አንዲት ሴት እንዳለችው ይገባቸው ይሆን እንጃ
ስለሁሉም አሰብኩ አብርሃና ክራሩ፣ንግስቲና የኪሮስ አለማየሁ (አንዕጓይ ፍስስ) ዘፈኖች፣ እነቅሳነትን፣ረዊናን ፣ አነ ደሊናና ሸዊትን፣ የኖሩባቸው ቤቶች የተመላለሱባቸው የሽሬ ጎዳናዎች የዋህነታቸውና ሀቃቸው ይነግሩላቸው ይሆን? አላውቅም፣አላውቅም፣አላውቅም
Mahmoud darwish እንዳለ “I don’t know who sold our homeland, but I saw who paid  the price” የከፈለውን አውቃለሁ፣ለምን ሰዎች ሰላምን አብዝተው እንደሚፈልጓት አውቃለሁ፣ለምን ስለሁሉም ባሰብኩ ጊዜ እንደ ሚፋጅ እሳት ውሃ በጉንጮቼ ላይ እንደሚወርድ አውቃለሁ፡፡ አያቴም ለምን ያንን ዜማ እንደምትደጋግመው አሁን አውቃለሁ:: ጦርነት እንደ ሙሽራ ለሁሉም በየተራ ይድረሰው ተብሎ የሚዜምለት አይደለም፣ይበቃል፡፡
ጉንጮቼን እጆች ሲዳብሷቸው ከሄድኩበት ብንን አልኩ አያቴ ነበረች ጓለይ ጓለይ እያለች አብራ እያነባች የምጠርግልኝ ቀስ ብላ እጆቼን ይዛ “ማርያም ታውቃለች “ አለችኝ ፣እንባ ባረገዙ አይኖቼ እያየኋት እጆቿን አጥብቄ አንገቴን እየነቀነኩ አዎ ማርያም ታውቃለች አልኳት፡፡ እጆቿን ወደደረቷ መልሳ እየደቃች በድጋሚ ማዜም ጀመረች
አንቲ ማርያም አክሱም ጽላተ ሙሴ
ተዓረቅና እንዶ መሬት ከይመሴ
ሕራይ በልናዶ መሬት ከይመሴ

ዶክተር ማያ አንጄሎ ለግልታሪኳና ለጥቁሮች ጭቆና ለማመልከት “I know why a caged bird sings”
  እንዳለች ሁሉ እኔም የታሰረች፣የተዘጋባት ወፍ ለምን እንደምትዘምር አውቃለሁ፡፡ አያቴን ተቀላቅዬ ማዜም ጀመርኩ፡፡ አንቺ የሙሴ ጽላቱ የምትባይ ማርያም፣መሬት ሳይመሽ ታረቂን፣ እሺ በይን፣ተለመኚን፡፡
            ተጻፈ በፍናማርያም
          ነሐሴ 16 2015 ዓም
by @markrylos

@wegoch
@wegoch
@paappii

1 week, 3 days ago

የመንገደኚት መጣጥፍ(ፍናማርያም)

“I know why a caged bird sings”
ህይወት ውሰጥ ተነግሮን ከምንረዳው ይልቅ ኖረናቸው የሰረፁን ነገሮች ይበረታሉ፡፡ አንዳንዴ ሰዎችን ከመረዳት ርቀን የምንገኘው፣ህመማቸው የማይሰማን በራሳችን የህይወት መስመር ውስጥ ከህመም ጋር ስላልተዋወቅን ነው፡፡ አሊያም እንደዚህ መኖር(ጠብቆ) አለበት ብለን ካስቀመጥነው የራሳችን ልክነትን ካዘነፉ ከመረዳት እንርቃለን፡፡
እግሬ ሽሬን ከረገጠበት ቀን አንስቶ በተለይም አያቴን ይዤ የስነ-አዕምሮ ህክምና ከመጣንበት ቀን ጀምሮ በሀሣቤ የምጥለው የማነሳው፣ስለህይወት ለመረዳት ከራሴ ጋር የምነዛነዘው በዝቷል፡፡ በስንት ስንክሣሮች በተከበበች ዓለም ጋር እየተላተሙ፣ጭነቷን መሸከም ከከበዳቸው ሰዎች፣ጥሰው ወጥተው አዕምሮና ሀሳባቸው ታፍኖ ከሰመጡ፣ ወደ ልክነት ለመውጣትና ለመተንፈስ ከሚነገዳገዱና ከሚፍጨረጨሩ ሰዎች ጋር ለአያቴ ስል መሰንበት ኑባሬዬ ከሆነ በኋላ ህመም ሰርፆኛል፤ህመም ገብቶኛል፡፡ ታዲያ ግቢውን ከረገጥኩበት የመጀመሪያዋ ሰዓት አንስቶ ልጅ እያለን ሰፈራችን ውስጥ ስለሚታወቁት አዕምሮአቸውን የታመሙ ሰዎች ታሪክ ማውጠንጠን ጀምሬ ነበር፡፡

# አሻግሬ እብዱና ውሸት ታንቃ ትሙት
አሻግሬ ድሮ ድሮ እጅግ ያተረፈ ነጋዴ ነበር ይላሉ የኋላ የኋላ ከሚያምናቸው የሽርክ ጓደኞቹ ተከድቶ ከከሰረ አንስቶ በሰፈራችን መንገድ ላይ  “ውሸት ታንቃ ትሙት” ብሎ በመጮህ ሌላ አሻግሬን ይዞ ተከሰተ፡፡ አምኗቸው የከዱትን፣እውነቱን በሀሰት ገልብጠው የጣሉትን በግሉ ሸንጎ ለመፋረድ ሲል፣ በእርግጥም ለዚህ ሰው እምነትን ማጉደል፣ሀሰትን መንገር ህመም ሆኖበታል ውሸት ታንቃ ትሙትለት፡፡

# እማማ ኡኡ
የሰፈራችን ትላልቅ ሰዎች የሊበን እናት ይሏቸው ነበር እኛ ደግሞ እማማ ኡኡ፡፡ የሊበን እናት እማማ ኡኡ የተባሉት ኡኡ ብሎ የሚጮህ ሰው ከሰሙ ድንጋይ ይዘው በማሯሯጣቸው ነው፡፡ እማማ ያቺን ቃል አምርረው የጠሏት የአንድ ልጃቸውን ሊበን መርዶ ከሰሙት ቀን ጀምሮ ነው፣ምናልባት ሲያረዷቸው የሰሟት የመጀመሪያ ቃል ሆና ኡኡ ሲባል የልጃቸውን አለመመለስ እየደጋገመች ስለምትነግራቸው ነው፡፡
አንዳንዴ ሰዎች ሊሉን የፈለጉትን ነገር ሊነግሩን ባሰቡ ሰዓት አንረዳቸውም፤እንተላለፋለን፡፡ ስንኖር፣፣ስናጣ፣ስንወድቅና ስንሰበር ህመሙን እናውቀዋለን፡፡ አያቴ ከመጣሁ ጀምሮ ብዙ ቃላት አላወራችም ብቻ በየመሀሉ ደረቷን እየደቃች ከምሕላ ጸሎቶች አንዱን ትደጋግማለች፡፡

"አንቲ ማርያም አክሱም ጽላተ ሙሴ
ተዓረቅና እንዶ መሬት ከይመሴ
ሕራይ በልናዶ መሬት ከይመሴ"

ከሁለት ዓመታት በኋላ ሽሬ ስመለስ ለወትሮ በሰዎች የሚከበበው የአያቴ መሪጌታ ወልዳይ ቤት ባዶ ነበር፣አክስቴ አብረኸት የለችም፣ዘርዓ ዳዊትና ክብሮም የሉም፣አባ ክብረቅዱሳንና እማሆይ ሣህለማርያም የሉም፣ ምንምና ማንም የለም ምስኪኗ አያቴ ዕንበባ(አደዬ) ብቻ፣ ቤት ማለት ጣራና ግድግዳ ብቻ ነው እንዴ አይመስለኝም አያቱን ከተኛችበት አልጋ ላይ በራስጌዋ በኩል ተቀምጬ ስለቤተሰባችን ማሰብ ጀመርኩ፡፡እውነት ግን እነዚህን ሰዎች ሀቅ አልነበራቸውም ጦርነትን ይፈልጉ ነበር ?? አላውቅም!!!

#መሪጌታ ወልዳይ
አያቴ መሪጌታ ወልዳይ የአቋቋም መምህር ሲሆን እሱ ለቤተሰቡ ባወጣው ቀጭን ትዕዛዝ መሰረት ከልጅ እስከ የልጅልጅ የአብነት ትምህርት የመማር ግዴታ ነበረብን፡፡ ለእኔም የመጀመሪያ የግዕዝ ቃላቶችን በቃሌ ያስጠናኝ አያቴ ነበር፣ አቡነ ሳልል የሰዓታት መግቢያ ላይ ያለችዋን ነበር የህይወት ስንቅ ናት እያለ ያሸመደደኝ፣ በእግዚአብሔር ታምኛለሁ፣ብወድቅም በእርሱ እነሳለሁ የምትለዋን

"ሠለስተ አስማተ ነሢእየ እትመረጎዝ
እመኒ ወደቁ እትነሣእ
ወእመኒ ሖርኩ ውስተ ጽልመት
እግዚአብሔር ያበርህ ሊተ"

ታዲያ ይሄ ሰው ከዜማው ና ከአቋቋሙ፣ ከመቋሚያና ጽናጽሉ ውጪ ጠመንጃ የጨበጡ እጆች እንዳልነበሩት  ተረድተውለት ይሆን ? አላውቅም፡፡

#አክስቴ አብረኸት
ለሁላችን አምባሻና ህብስት እየጋገረች ከሻይ ጋር የምትሰጠን፣በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሄዶ በቀረው ባሏ ሁሌ የምታለቅስ ናት ፡፡ምናልባት ለእርሷስ ባሏን የነጠቃትን ጦርነት አምርራ ትጠላ እንደነበር ያውቁላት ይሆን? እንጃ

#ዘርዓዳዊት
የአክስቴ አብረኸት የመጀመሪያ ልጅ ነው ወንድሜ ዘርዓ፣ ልጅ እያለሁ አያቴ ወንጌለ ዮሐንስን እንዲያስቀጽለኝ ነግረውት፣በምገድፋቸው ቃላት እየተናደደ፣ወይቤላና ወይቤሎ ማለት ከብዶኝ በ አይደለም ቨ በይ እያለ እስከ ምዕራፍ አራት እየተነዛነዝን ገብተን ወአውስአ ኢየሱስ ወይቤላ እንዳልኩ  መሳሳቴ ገብቶኝ የተለመደው ቁጣውን ስጠብቅ እያነበብሽ ያለውን ተረድተሸዋል ግን ብሎኝ ከተቀመጠበት በሀሳብ ሲጓዝ እኔም ምን ይሆን ብዬ መሳቱን ትቼ ወንጌለ ዮሐንስ ምዕራፍ አራትን ከላይ እስከታች ስደጋግም፣ አይ ዘርዓ … እሺ የሱንስ በዛች ምዕራፍ የተፃፈውን ሣምራዊ አይሁዳዊ የማያስብል አንድ የሆነ የዘላላም መጠጥን ሊጠጣ የወደደ፣እንኳን ሰው ማጥፋት ይቅርና ቃላትና ዜማ ስሰብር የሚቆጣ ወንድሜ እንደነበር ገብቷቸው ይሆን? እንጃ አላውቅም፡፡

# አባ ክብረቅዱሳን
በአያቴ ደብር አብረው የሚያገለግሉ መነኩሴናየቅዳሴ መምህር ናቸው፣አባ ክብረ ቅዱሳን(የኔታዬ)፡፡ እንደሌሎቹ የቤተሰባችን ሴቶች የቅኔ ትምህርትን ትቼ ለነፍሴ የቀረበውን ዜማ ለመቀፀል በማሰቤ ነበር አያቴ በደስታ ከእርሳቸው ስር እንድማር ሲወስደኝ በቅርበት ያወኳቸው፡፡ በደብረአባይናዋልድባ ናፍቆታቸው እኛም የማናቀውን ደብር አስናፍቀውናል፣ስለተቀደሰው የምንኩስና ህይወት ሲነግሩን ዜማውና ካስባሉን በኋላ በኋላ በሚነግሩን የነፍስ ትምህርቶች ስንት የጨለማ ቀናቶቼን ወጥቼባቸዋለሁ፡፡እና የኔታዬ ከቅዳሴ ጸሎት ሀበነ ንኅበር(አንድ መሆንን ስጠን) የምትለዋን እንደሚወዷት በቅዳሴያቸው ለአንድነት እንጂ ለጠብ ዜማ እንደሌላቸው ተሰምቶላቸው ይሆን? አላውቅም፡፡

# እማሆይ ሣህለማርያም
የአያቴ ዕንበባ ታናሽ እህት ነበሩ እማሆይ፣ቁጣቸውና የአቡነ አረጋዊ ዝክራቸው አይረሳኝም፣ አይ እማሆይ ሁሉም ነገር መሰተር እና ትክክል መሆን አለበት የሚሏት ነገር፣ ምስለ ሥዕላቱን የሚቀቡት ሽቶ ሲያልቅባቸው የሚያዝኑት ሀዘን አንድ የሆነ ሰው ሲገዛላቸው እየፈነደቁ ቀድመው ሥዕለ ማርያምን የሚቀቧት ነገር፣ ጠንቅቀው የተማሩ ቢሆኑም የሚደጋግሟት አንድ ጸሎታቸው የሆነው ይትቀደስ ስምከ፣የሆነ ቀን የአቡነ አረጋዊ ዝክር ደርሶባቸው እንዳስለመዱት እኔና ረዊና የበሶ ዱቄት ስለአቡነአረጋዊ እያልን ጠይቀን ከበረከት እንድንካፈል ለመጀመሪያ ጊዜ ሲልኩን እንዴት በየሰው ቤት እንሄዳለን ብለን ስንነጫነጭ በቁጣ እንኳን እናንተ ይቺ እናት ብለው ሥዕለማርያማቸውን እያመለከቱ በየሰው ቤት ሀሜት ሳትፈራ እንጀራ ለምናለች ብለው ሲያበሩን ከንቱነታችንን አምነን በሶ ሰብስበን ስንመጣ የመረቁን ምርቃትና ለቁጣቸው የነገሩን የአንድ ሊቅ ቅኔ

"ማርያም ድንግል ዘኢትፈርሀ ሐሜተ
ፍርፈራተ ሕብስተ ሰአለት በፍና እንዘ ትፀውር ሕብስተ"

እማሆይስ ታዲያ ከዝክራቸውና በደስታ ቅዱሳኖቻቸውን ከሚቀቡት ሽቶ በቀር ሌላ ሀቅ እንዳልነበራቸው ታውቆላቸው ይሆን እንጃ አላውቅም፡፡

# ክብሮም
አንዳንዴ ሰዎች ሰርግና ሞት አንድ ነው ሲሉ ፍቅርም አንድ እንደሆነ ማን በነገራቸው እላለሁ፡፡ ክብሮም የመጀመሪያም የመጨረሻም ፍቅሬ ነበር ፡፡ ለእርሱ ደብዳቤ መፃፍ ሰበብ ትግርኛ መጻፍ የተለማመድኩበት፣ከደብዳቤ ፍቅር ተጣብቄ የቀረሁበት ክብሮም፣ አዲስአበባ

ይቀጥላል

በ@markrylos

@wegoch
@wegoch
@paappii

2 weeks ago

የእንጀራ ዋጋ

የለውጡ ሰሞን: የአንድ እንጀራ ዋጋ : ከአምስት ብር ተነስቶ የመሸጫ ዋጋው በፍጥነት ስምንት ብር ሲገባ ለውጥ ነው እና ብዙም ሳይከፋን በዋጋ ሳንማረር እንገዛ ነበር። እንጀራውም - ወፍራም እና የጤፍ መሆኑ ብዙም የማያከራክር ነበር።

ከሁለት አመት በፊት : የእንጀራ ዋጋ አሁንም አሻቀበ እና አስራ አምስት ብር ሲደርስ : እንጀራው ራሱ ዋጋውን ሰምቶ ሳይሆን አይቀርም ክው ያለ መሰለ ። ይህ እንጀራ ደረቅ ያለ እና ቀለሙም ጥውልግ ያለ ቢሆንም : እንጀራ በመሆኑ ፤የጤፍ እንጀራነቱ ቢያጠራጥረንም : ስንቱን ጠርጥረን እንዝለቅ ብለን ገዛን በላን።

የዛሬ ዓመት ከመንፈቅ አካባቢ ደግሞ : አስራ ሰባት ብር ገባ።' ንጣቱ የሩዝ ይመስላል' እያልን በላን።

የዛሬ ዓመት ደግሞ: ሃያ ሁለትብር ሆነ :-' ሃያ ሁለት' የሰፈር ስም እንጂ የእንጀራ ዋጋ ሆኖ አያውቅም' እያልን :- መከፋታችንን በቀልድ አዋዛን እንጂ አልተከራከርንም ። :'የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት ከዓድዓ ጤፍ ጋ ምን ያገናኘዋል ? እንዳንል ማን ይሰማናል? ሲገናኝ ውሎ ሲገናኝ ቢያድር 'እንጀራ''ም. መኖር' ም' በአንድነት መወደድ ነበረባቸው?

አሁን በሁለትሺ አስራ ስድስት መባቻ ላይ : የአንድ እንጀራ ዋጋ : ሃያ አራት ብር የገባ ሲሆን : ይሄ እንጀራ ንፁህ ጤፍ መሆኑ ከማጠራጠሩ በላይ :የሚገርመው ነገር : በእዚህ ውድ በሆነ ዋጋ የተገዛው የእንጀራ ዓይኖች ውስጥ የምናየው :እንጀራውን ሳይሆን ትሪውን ሆኗል።

የእንጀራዎቹ ዓይኖች መሳሳታቸው በዚህ ከቀጠለ :ያ ያሳደገን እንጀራ : ዓይኖቹ ቀዳዳ በቀዳዳ ሆነውበት: ባለቀለበቶች እንጀራ እንዳይሆን እየሰጋሁለት ነው።

ሁሉ ነገር በዚሁ ከተባባሰ: ወደፊት ጤፍ ዋጋው እጅግ ከመወደዱ የተነሳ አንድ ኩንታል ጤፍ የገዛ ሰው ጤፉን እራሱ ቆሞ አስፈጭቶ::ወደ ቤቱ ለመውሰድ በአካባቢ ፖሊሶች ጥበቃ እና እጀባ እንዲደረግለት: ከወሳኝ ኩነት ጤፉን በግል ንብረትነት አስመዝግቦ: ከወረዳው የድጋፍ ደብዳቤ ሊያፅፍ ይችላል ።

ቡሽራ
ከሠንጋ ተራ

@wegoch
@wegoch
@paappii

3 weeks ago

«… አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት …»

አንድ ወቅት ላይ ለተወሰኑ ቀናት … ወደኾነ የሀገራችን ክፍል የመሄድ ዕድል አገኘኹ።

ከመሄዴ በፊት …ስለቦታው አንድ ኹለት ያኽል ደስ የሚሉ ዘፈኖች ሰምቼ ነበርና …ቦታውን ለማየት በጣም ጓጓኹ።

እንዲኽ የተዘፈነለት፣ ግጥምና ዜማ የተሠራለት ቦታ እንዴት ያለ ቢኾን ነው የሚልን ሀሳብ እያሰብኹ፣ ወደ መንገድ ዳር ወጥቼ ባጃጅ ተሳፈርኩ።

«እስቲ እንትን የሚባለው ቦታ አድርሰኝ»

«እሺ ግባ»

የተወሰኑ ደቂቃዎች እንደነዳ የመንገዱን ጥግ ይዞ ቆመ።

«ምነው?»

«ደረስንኮ»

«እንትን የሚባለው ቦታ ይኼ ነው እንዴ?» ማመን አልቻልኹም…

«አዎ»

ወርጄ ሳይ ወዲያና ወዲኽ ተራርቀው አምስት ቤቶች፣ ስድስት ዛፎችና፣ ሰባት ሰዎች ብቻ ይታዪኛል። … የቀረው ቁጥቋጦ የወረረው በረሃና የተራቆተ ተራራ ነው። ክው ነው ያልኹት። በጉጉት የተሞላው ልቤ በኩርፊያ ኩምሽሽ አለ።

«በቃ ይቺው ናት?» አልኹት ባለማመን

«ምን ፈልገኽ ነበር?» አለኝ እየሳቀ …


አንዳንድ ደስታዎች እንዲኽ አይደሉም ወይ? አብዛኛው መሻትና ፍላጎታችን ጉም እንደመጨበጥ አይደለም ወይ? አንዳንድ ነገሮች በጥበብ ስም፣ በዕውቀት ስም፣ በፋሽን ስም፣ በሥልጣኔ ስም፣ በወጣትነት ስም፣ በሀገር ስም የተጋነኑ ናቸው። እዚኽ ካልደረስክ «ፋራ» የሚያስብሉ … ስንደርስ ግን ኹሉም በጋራ መስማማት እውነት የተደረጉ ውሸቶች መኾናቸውን እንረዳለን። ሀቀኞች ሮጠው ወደመጡበት ይመለሳሉ። ፈሪዎች ግን ራሳቸውን እየዋሹ መኖር ይቀጥላሉ።

አንዳንድ ሰዎች ሲታዪ ረዥም ይመስሉና ደርሳችኹ አጠገባቸው ስትቆሙ አያጥሩባችኹም? ስብዕናቸውም እንደዚያው የኾኑ አሉ። ስታውቋቸው ወርደው ተዋርደው ቅልል የሚሉ እንደገለባ … ምነው ባላውቃቸው ኖሮ የሚያስብሉ አሉ።

አንዳንዴ የኾነን ነገር ደርሶ ከማየት በጉጉት መኖር የተሻለ ነው። አስቡት ዕድሜ ልካችኹን አንድን ነገር ስታሳድዱት ከርማችኹ የደረሳችኹበት ቀን ምንም ሲኾን? … አምስት ምንም፣ ስድስት ከንቱ፣ ሰባት ባዶ … ሲኾን

እና ጥቂት የጥርጣሬ ሥፍራ መተው አሪፍ ነው መሰለኝ።

—————

By 𝙷𝙴𝚗𝚘𝚌𝚔 𝙱. 𝙻𝚎𝚖𝚖𝚊

@wegoch
@wegoch
@paappii

3 weeks, 2 days ago

ከምታነብ ሴት ጋር አትከራከር!

ካደኩበት ሀይቅ ዳር አካባቢ ከሁሉ የተለዩ የሚመስሉኝ አንድ አሳ አጥማጅ ባልና እጅግ በጣም አንባቢ የሆነች ሚስቱን አውቅ ነበር፡፡ አንድ ቀን ታዲያ አሳ አጥማጁ ባል ደክሞት ለማረፍ ወደ ቤቱ መጣና ከሶፋው ላይ ወድቆ እያንኮራፋ እንቅልፉን ይለጥጠው ጀመር፡፡ ሚስት ማንበብ አልቻለችም ስለዚህ ለየት ያለ ነገር ማድረግ አሰበችና መጽሃፏን ይዛ ከቤት ወጣች፡፡
የባሏን ጀልባ ወደ አንድ ጸጥተኛ የሀይቁ ክፍል ቀዘፈችና በስሱ በሚዳብሰው ነፋሻማ አየር እየተዝናናች መጽሃፏን ገልጣ ማንበቧን ቀጠለች፡፡
ከጥቂት ቆይታዎች በኋላ በድንገት የባህሩ ላይ ጠባቂዎች ጀልባ ከች አለ፡፡ ኮስታራው ፖሊስም ማይክራፎኑን በእጁ አንከርፍፎ ይለፈልፍ ጀመር
‹‹ምን እያደረጉ ነው እመቤቴ!››
‹‹መጽሃፍ እያነበብኩ!›› (ምን እንደማደርግ አይታየውም እንዴ! በማለት እየተገረመች!)
‹‹ እመቤቴ በተከለከለው የሀይቁን ክፍል ላይ ስለሚገኙ በፍጥነት አካባቢውን ይልቀቁ!››
‹‹ምን አጠፋሁ ጌታው!›› አለች ደርባባዋ እመቤት
‹‹በዚህኛው የሀይቁ ክፍል አሳ ማጥመድ አይፈቀድም እመቤት!››
‹‹እሱን አውቃለሁ ጌታው! ሆኖም እንደሚያዩኝ አሳ እያጠመድሁ ሳይሆን መጽሃፍ እያነበብኩ ነው!››
ፖሊሱ ፈገግ ብሎ ‹‹እንደማየው ጀልባዎ በአሳ ማጥመጃ መሳሪያዎች ተሞልቷል፤ ስለዚህ እኛ በሌለንበት በማንኛዋም ደቂቃ መረብዎን ጥለው እንደሚያጠምዱ እገምታለሁ፡፡ ስለዚህ አሁኑኑ አካባቢውን ጥለው የማይሔዱ ከሆነ ባልተፈቀደ ቦታ አሳ በማጥመድ በሚለው አንቀጽ መሰረት በቁጥጥር ስር የማውሎት መሆኑን ይገንዘቡ!››
ሴትየዋም ፈገግ ብላ አየችውና ‹‹ጌታው እንዲያ የሚያደርጉ ከሆነ እኔም ጾታዊ ትንኮሳና አስገድዶ መድፈር በሚለው አንቀጽ መሰረት የምከስዎ መሆኑን ይወቁ!›› አለች ኮምጨጭ ብላ
‹‹አይቀልዱ እመቤቴ ይህ የስራ ጉዳይ ነው! እንኳን ልተነኩስዎና ልደፍርዎ ቀርቶ አጠገብዎ እንኳን እንዳልደርስኩ ያውቃሉ!››
‹‹ እውነት ነው አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ያንን ለማድረጊያ (መድፈሪያና መተንኮሻ ይሆን!) የሚያገለግል ማንኛውንም አይነት መሳሪያ እንደያዙና ጭር ሲልልዎ በማንኛዋም ደቂቃ ያን ሊያደርጉ እንደሚችሉ እገምታለሁ!›› አለች ደፋሯ እመቤት
ፖሊሱም ጥቂት አሰብ አደረገና ‹‹ መልካም ቀን ይሁንልዎ እመቤቴ! ይጠንቀቁ!›› የጀልባውን ሞተር ኮርኩሮ ጉዞውን ቀጠለ፡፡
ከአንባቢ ሴት ጋር አትከራከር!
ብልህና አስተዋይ ስለምትሆን ትቀጣሃለች!

(አብይ ተስፋዬ ከ7 አመት በፊት እንደተረጎመው)

@wegoch
@wegoch
@paappii

3 weeks, 3 days ago

<<አልነግረውም >>

ናርዶስ ጓደኛዬ ናት ለምን በተደጋጋሚ ስልክሽን ታጠፊያለሽ ፣ትደበቻለሽ ሙድሽ ፍላክቹዬት ያደርጋል ?

እ ?

<<በፍቅር ሂወቴ ደስተኛ አይደለሁም>>

ታድያ ለምን ችግሩን ለመፍታት አትሞክሪም ፣ለምን ቅር ያለሽን ጉዳይ ለፍቅረኛሽ አትነግሪውም ።

<<አ .ል .ነ .ግ. ረ. ው. ም !!>>

ለምን ???

<<አልነግረውም ኣ ! >>

በንግግር እመኚ እንደ ዘመናዊ ሰው በጠረቤዛ ዙርያ ማውራት ልመጂ ። ልብሽ ውስጥ የተሰማሽን ቅሬታ ካልተወያየሽበት ተጎጂዋ አንቺ ነሽ ?

<<አልነግረው...ም ! >>

መውደዱን እንዲነግረኝ ነው የምነግረው?!
በዙርያው ላሉ ሴቶች ፍቅረኛ እንዳለው እንዲናገር ነው የምነግረው ?!
የጓደኛዬ ፍቅረኛ ቆንጆ ቦርሳ ስጦታ ገዛላት ስለው ለኔም እጮኛዬ ስጦታ በገዛልኝ እያልኩ እንደቀናው ልንገረው ?!

ስለ ነገ ስለ ትዳር ሳወራው ወሬ ሲቀይርብኝ አትቀይርብኝ ወሬ ብዬ ነው የምነግረው ?!

ቤተሰቦቼ እንዳገባ ይወተውቱኛል አንተ ደሞ የጋብቻ ሃሳቡም ውልብም አይልብህም ብዬ ነው የምነግረው?!
ወሲብ ሲያምር ብቻ እንደምትወደኝ እንደናፈከኝ አታስመስል ብዬ ነው የምነግረው ።

አንተ ጋ ስመጣ ፀጉሬን ቦርጬን ፣ዳልዬን መቀመጫዬ ለማየት መስታወት ጋ ተገትሬ አማረብኝ አላማረብኝ ብዬ ነው እምመጣው

ዋው! ፓ ! አምሮብሻል አንዳንዴ እኮ በለኝ ነው ብዬ የምነግረው ?!

ፔሬድ ሲያነጫንጨኝ እና ሲያጠወልገኝ ፣ቅናት ሲያስዶክከኝ ተረዳኝ የኔ መሆንክን አስዳስሰኝ ብዬ ነው የምነግረው ??

አልነግረውም !!

ድሮ የምሆንለት ፣የምነግረውን ፣ የማደረግለትን ችላ ማለቴን ሁኔታዬ ገብቶት ብዙ ሳይረፍድ ከጠየቀኝ ካሳሰበው ብቻ ነው የምነግረው

አድራጎቱ እንደማያፈቅረኝ ምስክር ነው ። ልብ ላይ የሌለ ፍቅር በውይይት የሚመጣ አይመስለኝም !!

ሰው አስፈልጎት ስትሰጠው፣ እገዛ ፈልጎ ስታግዘው፣ ጠይቆ ስትመልስለት በተሻለ ሁኔታ አሰጣጥህን እውቅና ይሰጠዋል ፣በተሻለ ሁኔታ ያገዝከው እገዛህን ይረዳል ፣በተለየ መንገድ የነገርከው ይገበዋል ።

ካለዝያ ዝም ብዬ እርባን ለሌለው ነገር አልደሰኩርም !!>>

ታድያ ለምን አትተይውም ? !

<<እየተውኩት ነው እኮ አብሮ ሆኖ መተውን
መለማመድ እና እርም ማውጣት የመሰለ ቆንጆ ነገር የለም ።

ልክ ስተወው ይመጣል ያኔ እንደተላለፍን የጨከነ ፊቴን አሳይቼ ልመናውን እራመዳለሁ ።
ስተወው ባይመጣም አይገርመኝም አንዳንድ ሰነፍ ብዙ ከዘገየ በሆላ ነው አድራጎቱ የሚገለጥለት !!

የሆነው ሆኖ

ያኔ ከሱ የያዘኝ ሱስ ሙሉ ለሙሉ ስለሚራገፍ ደስታ ከኔ ጋ ይሆናል !!>>

በAdhanom Mitiku

@wegoch
@wegoch
@paappii

3 weeks, 4 days ago

ወንዳላጤዎች ላይ ያለ መንፈስ
(ሚካኤል አ)
እንዲህ እንደዛሬው የትዳርን ጣፋጭ ፍሬ ከመጉረሳችን በፊት በወንደላጤነት ዘመናችን ሳለን ለትዳር የነበረን አመለካከት ይህን ይመስል ነበር ...
.
ጀማው አምስት ትዳርአጤዎችን ያቅፋል ።
ከአምስቱ ሲንግል ወንደላጤዎች ደግሞ ሁለቱ እጅግ በጣም ሰነፎች ነበርን ።
እኔና አሚር... አንድ ቤት ተጋርተን ህይወትን ስንገፋ ስንፍናችን በአይን ከመታየት ልቆ በጆሮ ይሰማ ነበር :)
ጥቂት የልግምና ባህሪያቶች ከበታች ተጠቅሰዋል
....
ስራ 1 ፦ የበሉበትን ሳህን ማጠብ
መፍትሄ ፦ ስስ ፌስታል ሳህኑ ላይ አድርጎ ከበላዩ እንጀራ በመጣል መጠቀምና ምሳው ሲያልቅ ፌስታሉን መጣል
ስራ 2 ፦ ካልሲ ማጠብ
(እዚህ ጋር በተለይ የአሚር ካልሲን መኮቸር እንጠቅሳለን ።
'መኮቸርን ' የወንደላጤዎች መዛግብት ፦ ካልሲ ውሀ ከማጣቱ የተነሳ እንደ ኮብልስቶን መድረቅ የሚል ፍቺ አለው ።
እንደውም አንድ ጊዜ ተጣልተን ካልሲውን ወርውሮብኝ ግንባሬን ስንት ቀን እንዳመመኝ ሳልጠቅስ ማለፍ አልፈልግም ።
መፍትሄ ፦ አዲስ ካልሲ መግዛት እና ኮቾሮውን ካልሲ መጣል
ስራ 3 ፦ መጋረጃ ማጠብ
መፍትሄ ፦ ክፍፍል
የመጋረጃውን ከወገብ በላይ አሚር ያጥባል
የመጋረጃውን የታችኛውን ክፍል ካልተጠላን እኔ አጥበዋለሁ ። በሁኔታዎች ከተደባበርን የታችኛውን ጨርቅ አላጥብም ብዬ ሙዱን እከንተዋለሁ
ስራ 4 ፦ ድስት ማጠብ
መፍትሄ ፦ እንግዳ ሲመጣ የድስቱን የላይኛው ገፅ በደንብ አድርጎ ማፅዳት (ውስጡን ለቄስ)
እናቴ ለእረፍት አዲስ አበባ ዘለቀችና ቤታችን ጎራ አለች ። እኔና አሚር መስሪያ ቤት ሄደን ነበር ።
ማሚ የቤታችንን ንፅህና አይታ ተደነቀች።
የወለሉ ፅዳትና የመጋረጃው መፍካት እጅግ ውብ ነበር ።(የመጋረጃው የታችኛው ክፍልን
የአልጋችን ጠርዝ በመሸፈን ያገለግለናል )
እናም ይሄ ጉብዝናችን ያስደመማት እናቴ የምንሰራውን ወጥ አይታ ለመመዘን ድስቱን ከፈተችው ።
ድስቱ ነጭ ፀጉር አውጥቶ አርጅቷል ። ብዙ ጊዜ ሽበት ስለማያጣው እኔና አሚር ለድስቱ ስም አውጥተንለታል
ችሮታው ከልካይ :)
ማሚ ለዛን ቀን በስልክ እንዴት እንዳንባረቀችብኝ ሳስበው ዛሬም ድረስ ስንፍናዬን እረግመዋለሁ ።
...
በመንፈቅ ልዩነት ከአምስቱ አባላት ሁለቱ ላይ ውሳኔ ለማሳላፍ ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ ስብሰባ ጠራ ።
የስብሰባው አላማ ሁለቱ ወጣቶች የትልቅ ሰው ስራ የመስራት ሙከራ በማድረጋቸው እነሱን ከጓደኝነት መሰረዝን ይመለከታል ።
ሙሉቀንና ዮሀናን ያስባረራቸው ተግባሮች ከበታች ተጠቅሰዋል ።
ጥፋት 1 ፦ ሙሉቀን እንደ ትልቅ ሰው መሬት ለመግዛት ከደላላ ጋር ሲወያይ በመሰማቱ
(ሰው እንዴት የክለብ መጨፈሪያ ጠርሮብን መሬት ይገዛል? ፤ የሚል ብሶትም አለበት)
ጥፋት 2 ፦ ዮሀና ለአንዲት ለወደዳት ፍቅረኛው ሽማግሌ ለመላክ ማሰቡ ሲደረስበት
(ዮሀና እንደሚለው ሁኔታው በድንገት የተፈጠረ ፅንስን ለመታደግ ፍቅረኛውን በወግ ማዕረግ ለማግባት የተወሰነ አማራጭ የሌለው ግዴታ ነበር )
ቢሆንም ዮሀና ኮንዶምን በጥንቃቄ ካለመገልገል አልፎ ማስረገዙ ሳያንስ በዛ ላይ የማግባት ሙከራን ማድረጉ በወንደላጤው ኮሚቴ በቸልታ የሚታይ ነገር አልነበረም።
ሁለቱም ታገዱ ።
ከእግዱ ወዲያ ሶስት ወንደላጤዎች አሸሸ ገዳሜያችንን ቀጠልን ።
ይሄ ጉዞዋችን ዓመት ሲቆይ ግን እኔ በተለይ ሁኔታዎችን ማነፃፀር ጀመርኩ።
ሁለቱ የተለዩ ጓዶች በትዳር በረከት ወዛቸው ችርፍፍ ብሎ በሀብትና ልጅ ተባረኩ።
ሶስቱ ወመኔዎች ዛሬም ድረስ ዩንቨርስቲ ያለን ይመስል ነበር። ወዝ አልባ አመዳሞች ነን።
ደግሞ ከባለትዳሮች የተሻለ ገንዘብም አልነበረንም ።
ያን ጊዜ እኔ አንዲት ሸጋ ወድጄ ቀስ ብዬ ከጀማው ተሸበለልኩ ።
ፓርላማው ለአስቸኳይ ውሳኔ ሁለቱ አባላቱን ጠራ :)

By Mikael aschenaki

@wegoch
@wegoch
@paappii

4 weeks, 1 day ago

ጭራሽ አልተሰማውም አይደል? ምንም ሳይመስለው ተቀበለሽ አይደል? የፍቅርን ትርጓሜ በሙሉ ዘረፍሽና ላገባሽው ሰው ኮንዶም አድርገሽ ሰጠሽው ይኸው ከዛ ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጆች ሁሉ ኑሯችን ጥላቻ ሞታችን ጥላቻ
'ቢያንስ ራስህን ጠብቅ' 'ቢያንስ ራስህን ጠብቅ' 'ቢያንስ ራስህን ጠብቅ'  የገደል ማሚቶ ከአንጀትሽ ነጥቃ በአግራሞት ለመላው ተፈጥሮ ስታስተጋባ ድፍን ህልውና ዓይኑን ከከደነበት ገለጠና ከሰማዩ ላይ አፈጠጠብሽ እንደጸሃይ ሆኖ እንደጨረቃ ሆኖ እንደመኖርም እንዳለመኖርም ሆኖ
ግን አንቺ ይሄንን ሁሉ ተዓምር ጀምሮ ሲጨርስ መች አየሽ? ወደውስጥሽ ከፈትሽና የሴትነት ክብርሽ፤ ምሰሶው በገዛ እጅሽ ተገንድሶ ሲወድቅ ተመለከትሽ
ምናልባት በሌላ ዓለም ቋንቋ ይሄ ነገር ደስ የሚል ስም ወጥቶለት ይሆናል ከውልደቱ አስቀድሞ የተነገረለት ሞቱ ተቀድሶለት ህልውናው አስመልኮም ይሆናል።
በዚህኛው ዓለም ግን ዕለቱ ደሞዝ ከገባ አራተኛው ሃሙስ ነበር ጓዳው ባዶ ነበር ጎረቤት መቀላወጥ ሰልችቶሽ ያልበላ ሆድሽ ሲጮኽብሽ እሳት ጠቅልለሽ አጎረስሽውና ጥቅልል ብለሽ ተኛሽ አንዳንድ እሳት አለ ሲለኮስ ገላሽን እንደፈረንጅ በረዶ ቡንንን የሚያደርግ እየነፈሽ በየመጠጥ ቤቱ ስታስሺው በጽድቅሽ ተሰውረሽ ቀረሽ
ግና
ገድልሽን ሊጽፍልሽ ማን መጣ? ማን የፍቅር ሃይማኖተኛ ሊሰብክልሽ ተገኘ?
ሁሉን የሚያይ አምላክ እንኳን በባልሽ ቀንቶ ወይም አጋፔውን ስለሰረቅሽው ተቆጥቶ በነበልባሉ እንድትጋዪ ተወሽ እኔም አይቻለሁ ማዕበል የሚጋልብ የነበልባል ማዕበል በሩ ጋር እያደረሰ የሚያላትምሽ ዳርቻ ሊያወጣሽ ይልና እጀታው ላይ ስትደርሺ ጌታሽ ሰምቶ ማዕበሉን ቀጥ ሊያደርገው ይመጣል እየዘፈነ ጎረቤት እየረበሸ የወላለቀ ጥርሱን ያባበጠ ፊቱን ይዞልሽ አንጀትሽን ሊበላ
ከዛም እሱ ምን አደረገ ዝም ብሎ ተቀበለሽ ደግሞም ሌላ ቀን እንዳይረሳ ክተችልኝ አለሽ ወንድ ልጅ ያን ያህል....ያን ያህል ደደብ እንስሳ ነው አይደል
ወይስ ወይስ እኔ ስለወንድ ልጅ ምንም አላውቅም ተሳስቻለሁ
ተንገዳግዶ ወደቀ እንዴ አውሬ እንዳየ ሰው ሮጦ አመለጠሽ  የሙት መንፈስ እንዳየ ሰው ተርበተበተ ምንነትሽን አላውቅ ብሎ ተንፈራገጠ ፊቱ እንደሙሴ ከእድሜው አርባዓመት የጨመረ ፊቱ ተጨማደደ ጸጉሩ በአንድ ዕለት ሸበተ የእግዚአብሔርን ጀርባ ፊትሽ ላይ አይቶ...
አይ እንደሱ አላደረገም እንደዛም አልተሰማውም ምንም አልተሰማውም
ረስቶት በነበረ ትንሽዬ ሳንቲም ሌላ ኮንዶም ገዛና የሰጠሽውን ኮንዶም አስቀመጠው አለመግዛት ይቀል ነበር ሌላ ገላ አለመንካት ይቀል ነበር ከመጀመሪያው እንዲህ ዓይነት ፍቅር አለመቀበል መተው ይቀል ነበር ግን ቀላል መስሎት አጉል ቀላል ሸክም ተሸከመ የአዳምን ልጅ ሲረግመው በዘመንህ አቀበት እንጂ ቁልቁለት አትውደድ አለው እሱም ቀላል መስሎት ተንደረደረ ተንደረደረ መውረድ ማለቂያ ያለው መስሎት

@wegoch
@wegoch
@paappii

1 month ago

"ብታዪ ጠይም ነው አይኖቹ አይኖቼ ላይ ሲያርፉ ሰውነቴ ይርዳል ከዛ ደግሞ በነዛ አለንጋ ጣቶቹ ተሣስቶ እንኳን እጁ ሰውነቴ ላይ አርፎ ከነካኝ  ከነካኝ ስልሽ ደግሞ መጨበጥንም ያካትታል ልክ ያኔ ሴት መሆኔን ሁላ እረሣለው ኧረ የምን ሴት ሰው መሆኔ ለሆኑ ሰአታት ይጠፋኛል ፣ በጣም ትኩር ብዬ ካየሁት ቡኀላ አይኖቼን ከሱ ላይ ነቅዬ ሌላ ነገር ላይ ባሣርፍም ሚታየኝ እሱ ብቻ ነው አለ አደለ ጣፋጭ ነገር ቀምሠሽ እስከሆነ ጊዜ ጣእሙ ከአፍሽ እንደማይጠፋ ሁሉ የሱ ምስልም ከአይኔ አይጠፋም..............ሚያምሩ አበቦች ፣ ሚያምሩ ቦታዎች ፣ ሚያምር ሰማይ ፣  ሚያምሩ ህፃናት ራሱ ከእሱ ሚሠሩ ነው ሚመስለኝ ምንም ሚያምር ነገር ባይ አይኔ ላይ የሚመጣው የእሱ ምስል ነው ማንም ሰው ስለወንዳወንድነት ቢያወራ የወንድ መለኪያዬ እሱ ነው ። ደረቱን መንተራስ ልክ ገነትን እንደመውረስ ያህል ህልሜ ነው ተሳስቶ እንኳን ወደኔ ዞሮ ካወራ አይኔን ከከንፈሩና ከጥርሶቹ መንቀል አልችልም ።ደሞ ልክ ሲያወራኝ ምንም አላወራም ምንም ፀጥ ፣ ፀጥ ነው ምለው ተሳስቼ ቃል ከአፌ ባወጣ እንኳን 'እሺ ' ብቻ ነው ምለው ምንም ቢለኝ እሺ ብቻ አንደበቴ ራሱ ይተሣሠራል ግን ..ግን እሱ ይሄን አያውቅም................"ብዙ በጣም ብዙ ስለሱ ጉንጮችዋ እየቀሉ እጆችዋ እየተንቀጠቀጡ  እንዴት እንወደደችው ታወራልኛለች ብዙ ስላላጣጣመችው ስላልቀመሰችው ገላ አይንዋን በእንባ ሞልታ ታወራልኛለች ።  እሱ የእስዋን ፍቅር እንደማያውቀው ሁሉ እሷም የእሷን እንጂ የኔን አታውቅም ........ከተፈጠርኩ የተሳምኩት በሱ ከንፈር እንደሆነ አታውቅም....... ጡቶቼ የተዳበሱት ልክ ተሳስተው ሲነኳት በሚነዝሯት ጣቶቹ መሆኑን አታቅም.......... የሴትነት ደሜ የፈሰሰው እግሮቼ መሀል የነበረው መጋረጃ የተገለጠው በሱ እንደሆነም አታውቅም ........ከንፈሮቹ ግንባሬ ላይ ሲያርፋ ዘውድ  እንደተሠጣት ልዕልት እንደምሆን አታውቅም....... የፍቅር ልኬ መሆኑን አታውቅም....... ደረቱ ላይ ተኝቼ ጨረቃ በፀሀይ እንደተተካች አታውቅም  እሷ ይሄንን ሁሉ አታውቅም .....የሷ ተስፋ የኔ ግን ትዝታ መሆኑን አታውቅ .......። እሱ የሌለበትን ወጣትነቴን እንጂ ለሱ የተሰዋውን ልጅነቴን፣ ወጣትነቴን እንጂ ሳፈቅረው ውስጤ እንዳረጀ አታውቅም ........አታውቅም ።

By ቃልኪዳን ሰለሞን

@wegoch
@wegoch
@paappii

1 month ago

በጽኑ ህመም ውስጥ ከነበረች ልጃቸው ጎን ለ38 ዓመታት ያልተለዩ እናት

ኤድዋርዳ ኦባራ የተባለች የስኳር ህመምተኛ አሜሪካዊት ታዳጊ በ16 ዓመቷ በፈረንጆቹ 1969 የሳንባ ምች ሰለባ ስትሆን በሽታው ተደራራቢ እና ጽኑ ስለሆነም ቤተሰብ ወደሆስፒታል ቢወስዷት ሊሻላት አልቻለችም፡፡

በዚህ ጭንቅ ውስጥ ልጅ የእናቷን አይን እያየች ‘’እናቴ ከጎኔ አትለይ’’ ስትል ትጠይቃለች፡፡የእናት አንጀት እንስፍስፍ ነውና በፍጹም ከጎንሽ አልለይም በማለት እናት ለልጃቸው ቃል ገቡ።

ኤድዋርዳ ህመሟ ይጸናባትና በጽኑ ህመም (ኮማ) ውስጥ ሆና ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራት ተቆጠሩ፤ ዓመታትም አልፈው ኤድዋርዳ ከገባችበት ጽኑ ህመም ውስጥ ሳትወጣ ለ42 ዓመታት ቆይታ ህይወቷ አለፈ።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥም እናት ልጃቸውን ከተኛችበት አልጋ ሳይርቁ የሚችሉትን ሁሉ እንክብካቤ አደረጉ። እንቅልፍ ከ90 ደቂቃ በላይ ተኝተው የማያውቁት እናት ለልጃቸው ሙዚቃ በማንጎራጎር፣ መጽሃፍት በማንበብ እና ታሪኮችን በመንገር ያሳልፉ ነበር።

ቤተሰቡን ይደጉም የነበረው አባትም ልጁን መንከባከብ ግድ ሲለው ስራውን ተወ፤ ለችግርም ተጋለጡ፤ በመጨረሻም ብዙም ሳይቆይ በልብ ህመም በሽታ ለህልፈት ተዳረገ፡፡

እናትም በ2008 ማለትም በ81 ዓመታቸው ከልጃቸው በፊት አለፉ፡፡ ከዚያ በኋላ እህቷ እየተንባከበቻት ለአራት ዓመታት ቆየች፡፡

ሆኖም በሽታውና ስቃዩ በርትቶባት መንቃት ባለመቻሏ እናቷ ከሞቱ ከአራት ዓመት በኋላ ከ42 ዓመታት የጽኑ ህመም ቆይታ በኋላ በ59 ዓመቷ ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል፡፡

በዚህም የዓለም ጊነስ ሪከርድስ ኤድዋርዳን ራሷን ስታ (ኮማ) ውስጥ ለረጅም ጊዜ በመቆየት ሲል መዝግቤያታለሁ ብሏል ሰሞኑን፡፡

ዶ/ር ዌይን ዳየር ከማርሴለን ዳየር ጋር በመሆን “A Promise Is A Promise: Unbelievable Story of a Mother’s Unconditional Love and What It can Teach Us’’ በሚለው መጽሃፍ ውስጥ የኤድዋርዳን ታሪክ ከትቧል።

ጸሃፊው እንዳለውም ይህ ሴራ ቀመስ የሆነ ታሪክ አይደለም፤ ወይንም በፍቅር ስለከነፉ ጥንዶች የሚያትት ልብ ወለድ መጽሃፍ አይደለም፡፡ እውነተኛ ጽናትና ፍጹም ፍቅር የታየበት እናትነት ነው፡፡

በየሬድ ዘ

@wegoch
@wegoch
@paappii

We recommend to visit

"ይህ የቴሌግራም ቻናሌ ግንቦት1/2011ዓም የተከፈተ ነው። የእኔን የስልክ ወጪ ጨምሮ አገልግሎቴን መደገፍ የምትፈቅዱ ጓደኞቼ በ
👉🏿 https://donorbox.org/zemedemedia እና
👉🏿 https://www.paypal.com/paypalme/ZemedkunB በኩል ማገዝ ትችላላችሁ። በተረፈ ለቤተ ክርስቲያኔና ለኢትዮጵያ ሀገሬ የሚጠቅመውን ሁሉ አበረክት ዘንድ አብዝታችሁ ጸልዩልኝ።

Last updated 1 month ago

The first Telecom operator in Ethiopia https://t.me/EthiotelecomChatBot

Last updated 1 month, 2 weeks ago

ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot

🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹

Last updated 1 week, 2 days ago