መንፈሳዊ ጉባኤ

Description
ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ነውርም የለብሽም።
መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 4 : 7

@Menfesawi_Gubae

ጥያቄ ካላችሁ ከታች ባለው አድራሻ መጠየቅ ትችላላችሁ።

@HenokAsrat3
Advertising
We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated 3 weeks, 2 days ago

Last updated 2 weeks, 4 days ago

ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot

🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹

Last updated 1 month ago

2 months ago

የወገኖቼም ኃጢአት እንዲሁ በታየኝ ጊዜ አለቅሳለሁ" አሉት፡፡ በሌላም ጊዜ ጌታችን በመሠዊያው ላይ ሆኖ ተገልጦላቸው የእያንዳንዱን ሰው ኃጢአት መላእክት ሲያቀርቡለት አሳያቸው፡፡ ቀጥሎም "ሕዝቡን አስተምረህ ከክፋታቸው መልሳቸው" አላቸው፡፡ እሳቸውም "አይሰሙኝም" ቢሉት ጌታችንም "አስተምረሃቸው ከክፋታቸው ባይመለሱ ደማቸው በራሳቸው ላይ ይሆናል" አላቸው፡፡

መናፍቁ ንጉሥ መርቅያኖስና ተከታዮቹ ክብር ይግባውና ጌታችንን "ሁለት ባሕርይ" በማለታቸው ጉባዔ ሠርተው አባቶች ሲሰበሰቡ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ አባ መቃርስን አስከትሎ በጉባዔው ተገኘ፡፡ አባ ዲዮስቆሮስና አባ መቃርስም ሁለት ባሕርይ ባዮችን አስተምረዋቸው እምቢ ቢሏቸው አውግዘውና እረግመው ከቤተ ክርስቲያን ለዩአቸው፡፡ ለመከራም የተዘጋጁ ሆነው ራሳቸውን አሳልፈው ሰጧቸው፡፡ ከሃዲው ንጉሥም ወደ ጋግራ ደሴት አጋዛቸው፡፡ አባ ዲዮስቆሮስም ለአባ መቃርስ "አንተ በእስክንድርያ ሀገር ሰማዕትነት ትቀበላለህ" በማለት ትንቢት ነግረዋቸው ከአንድ ነጋዴ ጋር ወደ እስክንድርያ ላኳቸው፡፡ እዚያም ሲደርሱ መናፍቁ ንጉሥ መርቅያኖስ አባ መቃርስን ይዞ ብዙ ካሠቃያቸው በኋላ ኩላሊታቸውን ብሎ ገደላቸውና የሰማዕትነታቸው ፍጻሜ ጥቅምት 27 ቀን ሆነ፡፡ ክርስቲያኖችም ሥጋቸውን ወስደው ከነቢዩ ኤልሳዕና ከመጥምቁ ዮሐንስ ሥጋ ጋር በአንድነት አኖሩት፡፡ ከሥጋቸውም ብዙ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛን በአባ መቃርስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥቅምት27 ስንክሳርና መዝገበ ቅዱሳን።

      • የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ "እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም። ወገብረ መድኃኒት በማእከለ ምድር። አንተ አጽናዕካ ለባሕር በኃይልከ"። መዝ73፥12-13። የሚነበበው ወንጌል ማቴ27፥20-57።
      • የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ "ተሣለኒ እግዝኦ እስመ ኬደኒ ሰብእ። ወኵሎ አሚረ አሥርሐኒ ቀትል። ወኬዱኒ ፀርየ ኵሎ ዓሚረ በኑኀ ዕለት"። መዝ55፥1-2። የሚነበቡት መልዕክታት 1 ኛቆሮ 12፥20-28፣ 1ኛ 2፥20-ፍ.ም፣ የሐዋ ሥራ 5፥12-17። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ3፥11-25። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዳሴ ነው። መልካም የመድኃኔዓለም የስቅለቱ መታሰቢያ በዓል፣ የአባ ጽጌ ድንግልና የአቡነ መብዓ ጽዮን የዕረፍታቸው በዓልና የጽጌ ጾም ለሁላችንም ይሁንልን።
        መልካም። ቀን
2 months ago

ጌታችን ለአቡነ መብዓ ጽዮን የወርቅ በትር ሰጥቷቸው በእርሷ ነፍሳትን ከሲኦል ያወጡባት ነበር፡፡ መቋሚያዋም እሳቸው ካረፉ በኋላ የሚሞተውን ሰው እየለየች ትናገር ነበር፡፡ አባታችን እንደ አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በመልአክ ተጥቀው ተወስደው የሥላሴን መንበር ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር አጥነዋል፡፡ ጌታችን ከተረገመችና ከተወገዘች ዕፅ ጋር በተገናኘ ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክና ለአቡነ መብዓ ጽዮን ልዩ ምሥጢር እንደነገራቸው በሁለቱም ቅዱሳን ገድላት ላይ በሰፊው ተጽፏል፡፡

አቡነ መብዓ ጽዮን በይበልጥ የሚታወቁት ሁልጊዜ ወር በገባ በሃያ ሰባት መድኃኔዓለምን አብልጠው በመዘከራቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት "እንደ አንተም በየወሩ በሃያ ሰባት የሞቴ መታሰቢያ ለሚያደርግ ነፍሳትን ከሲኦል አወጣለታለሁ" የሚል ድንቅ ቃልኪዳን ከጌታችን ተቀብለውበታል፡፡ ይኸውም የመድኃኔዓለምን የሞቱን መታሰቢያ የሚያድርግ ቢኖር ነፍሳትን ከሲኦል እንደሚያወጣ ሲነግራቸው ነው፡፡ ቅዱስ አባታችን "ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ! በዓልህን አደርግ ዘንድ አንተ የምትወደውን ግለጥልኝ" ብለው ጌታችንን ሲጠይቁት እርሱም "የሞቴን መታሰቢያ ያደረገ እንደ እኔ ነፍሳትን ከደይን ያወጣል፣ "በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ይሠራል፣ ከዚያም የበለጠ ይሠራል" ብዬ በወንጌሌ እንደተናገርሁ" አላቸው"፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን ለልጆቻቸው እንዲህ ብለው መከሯቸው፡- "ክርስቲያኖች ሁሉ የፈጣሪያችንን የመድኃኔዓለም ክርስቶስን የመታሰቢያ በዓሉን እናድርግ፡፡ የአባቶቻችን የሐዋርያት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የመላእክት መታሰቢያቸው ባረፉበት በተሾሙበት ቀን ይከበራል፡፡ እነርሱን የፈጠራቸው እርሱ መድኃኔዓለም ነው፣ ያከበራቸው፣ ከፍ ከፍ ያደረጋቸው፣ ስማቸውን ለጠራ መታሰቢያቸውን ያደረገ እንደሚድን ቃልኪዳን የሰጣቸው እርሱ ነው፡፡ የመድኃኔዓለምን የሞቱን መታሰቢያ ያደረገ ግን የተኮነኑ ነፍሳትን ከደይን ያወጣል፣ በሞቱም ጊዜ ሥቃይን አያያትም"፡፡

የአቡነ መብዓ ጽዮን በዓለ ዕረፍታቸውም እጅግ አብዝተው በሚዘክሩበትና ዓመታዊ ክብረ በዓሉ ታስቦ በሚውለው በመድኃኔዓለም ቀን ጥቅምት ሃያ ሰባት ነው፡፡ ከአባታችን አቡነ መብዓ ጽዮን እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን፣ በጸሎታቸው ይማረን!።

      • አቡነ ጽጌ ድንግል፡- ደራሲና ማኅሌታዊ ሲሆኑ የላመ የጣፈጠ ከመብላት ተቆጥበው ጥሬ ቆርጥመው 9 ዓመት ከቆዩ በኋላ የእመቤታችንን ስደት በጣም በጥልቀት የሚተርከውን "ማኅሌተ ጽጌን" የደረሱ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ውኃም በሦስት ቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነበር የሚጠጡት፡፡

አቡነ ጽጌ ድንግል ከደብረ ሐንታው ከአቡነ ገብረ ማርያም ጋር እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው እመቤታችንንና ፈጣሪ ልጇን በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየመሰለ የሚያመሰግነውን ድርሰቱን በመዝሙረ ዳዊት መጠን 150 አድገው ደርሰዋል፡፡ አቡነ ገብረ ማርያምና አቡነ ጽጌ ድንግል ማኅሌተ ጽጌን በጥምረት ሊደርሱት የቻሉት አቡነ ገብረ ማርያም በወሎ ክፍለ ሀገር በወረኢሉ አውራጃ ልዩ ስሙ ደብረ ሐንታ በሚባለው ገዳም የሕግ መምሕር ሆነው በተሾሙበት ወቅት ነው፡፡ እነዚህም ሁለት ቅዱሳን የዘመነ ጽጌ የማኅሌት አገልግሎትን ሳይለያዩ በሰላምና በፍቅር በአንድነት አግልግለዋል፡፡ ይኸውም የሆነው እንዲህ ነው፡-
አንድ ዓመት አቡነ ገብረ ማርያም የክረምት መውጫና የዘመነ ጽጌ ዋዜማ በሆነው መስከረም 25 ቀን ከደብረ ሐንታ መጥተው ደብረ ብሥራት አቡነ ጽጌ ድንግል ገዳም ገብተው ከመስከረም 25 ቀን እስከ ኅዳር 5 ቀን ያለውን የዘመነ ጽጌ የ40 ቀን አገልግሎት ከአቡነ ጽጌ ድንግል ጋር ፈጽመው ኅዳር 8 ቀን ወደ ደብራቸው ደብረ ሐንታ ይመለሳሉ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ አቡነ ጽጌ ድንግል ከገዳማቸው ከደብረ ብሥራት ተነሥተው ወደ ደብረ ሐንታ ሄደው እንዲሁ እንደ አቡነ ገብረ ማርያም 40ውን ቀን አግልግለው ይመለሳሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ቅዱሳን እንደዚህ እያደረጉ በየተራ አንደኛው ወደ ሌላኛው ገዳም እየሄዱ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ በፍጹም ፍቅርና በትሕትና አብረው እመቤታችንን ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡ ይኸውም በራሳቸው በአቡነ ገብረ ማርያም ገድል ላይ እና በአቡነ ዜና ማርቆስ ገድል ገጽ 72-73 ላይ በሰፊው ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ የሁለቱ ድርሰታቸው የሆነው "ማኅሌተ ጽጌ" ድርሰት የእመቤታችንንና የልጇን የጌታችንን ሥጋዊ ስደት የሚገልጽ ሲሆን በጨማሪም ስደት የማይገባው አምላካችን ወደ አህጉራችን አፍሪካ ተሰዶ የሠራቸውን ድንቅ ድንቅ ተአምራትና የእመቤታችንን ንጽሕናዋን ቅድስናዋን አማላጅነቷን የሚያስረዳ ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡

አባ ጽጌ ድንግል ከማኅሌተ ጽጌ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ አስደናቂ ድርሰቶችን ደርሰዋል፡፡ የጻድቁ ቅዱስ ዐፅማቸው፣ ታቦታቸውና የደረሷቸው በርካታ ድርሰቶች በገዳማቸው ደብረ ጽጌ ውስጥ በክብር ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ አምሃራ ሳይንት ቦረና ከአቡነ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም የ5 ሰዓት የእግር መንገድ ከተሄደ በኋላ የሚገኘው ገዳማቸው "ደብረ ጽጌ" ከአንድ ወጥ ዓለት ተፈልፍሎ የተሠራው ሲሆን አሠራሩም እጅግ ድንቅ ነው፡፡

የአቡነ ጽጌ ድንግል ገዳም ከአቡነ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ጋር የሚያገናኘው "የእግዜር ድልድይ" የተባለ አስገራሚ ታሪክ ያለው ድልድይ አለው፡፡ ሁለቱ ቅዱሳን በመንፈስ ተጠራርተው ለመገናኘት ቢያስቡም የወለቃ ወንዝ ሞልቶ በአካል ሳይገናኙ ቀሩ፡፡ በዚህም በጣም አዝነው ከወንዙ ወዲያና ወዲህ ሆነው ተላቅሰው አፈር ተራጭተው ወደየገዳማቸው ቢመለሱም ያ ተላቅሰው የተራጩት አፈር በተአምር ትልቅ ድልድይ ሆነ፡፡ ድልድዩን ሁለቱም በበዓታቸው ሆነው በመንፈስ አዩት፡፡ የበጎ ነገር ጠላት ሰይጣንም ይህንን ሲመለከት ድልድዩን
በትልቅ ሹል ድንጋይ በስቶ ሊያፈርሰው ሲል አቡነ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመንፈስ አዩትና ከጋስጫ ተነሥተው በደመና ተጭነው በመሄድ ሰይጣኑን በግዘፈ ሥጋ ገዝተው ያንን ድልድዩን አፈርስበታለሁ ያለውን ትልቅ ሹል ድንጋይ አሸክመውት በዓታቸው ጋስጫ ድረስ ወስደውታል፡፡ ያ ድንጋይ ዛሬ በጋስጫ አቡነ ጊዮርጊስ ገዳም ለመነኮሳቱ ደወል ሆኖ እያገለገለ ይኛል፡፡ ድልድዩም እስከ አሁን ድረስ ለአካባቢው ኢስላም ማኅበረሰብ ብቸኛው የወለቃ ወንዝ መሻገሪያቸው ሆኖ እያገለገላቸው ነው፡፡
ከአባታች አቡነ ጽጌ ድንግል እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከትን ይሳትፈን፣ በጸሎታቸው ይማረን! ምንጭ፦ገድለ አቡነ መባዓ ጽዮን፣ መዝገበ ቅዱሳን።

      • አባ መቃርስ ዘሀገረ ቃው፡- ለዚህም ቅዱስ የዝንጉዎችን ምክር ተከትሎ ያልሔደ በኃጢአተኞችም ጎዳና ያልተጓዘ በዘባቾችም መቀመጫ ያልተቀመጠ የእግዚአብሔርን ሕግ መጠበቅ ፈቃዱ የሆነ እንጂ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያነብ የሚያስተምር ብፁዕ ነው የሚለው የነቢይ ዳዊት ቃል ተፈጽሞለታል።

ይህም አባ መቃርስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመጠበቅ በመክሊት ነግዶ ዕጥፍ አድርጎ አትርፎአልና እግዚአብሔርም በእጆቹ ያደረጋቸውን ታላላቆች ድንቆች ተአምራት ስንቱን እናገራለን። ስለርሱም እንዲህ ተባለ እርሱ በአገረ ቃው ተሾሞ በወንበር ተቀምጦ ሕዝቡን በሚያስተምራቸው ጊዜ ዘወትር ያለቅሳል ከደቀ መዛሙርቶቻቸውም አንዱ በእግዚአብሔር ስም ካማላቸው በኋላ ለምን ሁልጊዜ እንደሚያለቅሱ በመሐላው አምሎ ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም ስለመሐላቸው ፈርተው ነገሩት "ዘይት በብርሌ ውስጥ ጎልቶ እንደሚታይ

2 months ago

"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

ጥቅምት ፳፯ (27) ቀን።

እንኳን ለመድኃኔዓለም ለስቅለቱ ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል፣ ለኢትዮጵያውያኑ ጻድቃን ማኅሌተ ጽጌን ከአባ ገብረ ማርያም ጋር በመሆን ለደረሱት ለታላቁ አባት ለአቡነ ጽጌ ድንግል፣ ጌታችን በዕለተ አርብ የጠጣው መራራ ሐሞት እያሰብ ሁል ጊዜ አርብ አርብ ኮሶ ይጠጡና የመድኃኔዓለም ዝክር ይዘክሩ ለነበሩት ለታላቁ አባት ለአቡነ መብዓ ጽዮንና በዋሻ ውስጥ አርባ ዓመት ለኖሩ መና ሲመገቡ ለነበሩት ለታላቁ አባት ለአቡነ ጊዮርጊስ ዘጣና ለዕረፍታቸው በዓል መታሰቢያ ለሀገረ ቃው ኤጲስ ቆጶስ ለአባ መቃርስ ለዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን።
በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ በዋሻ ከሚኖር ከጳውሎስና ከዮልያኖስ ከእነርሱም ጋር ላሉ ሰማዕታት ከመታሰቢያቸው ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

      • የዕለቱ አንገርጋሪ ግእዝ ዜማ፦ "እስመ ውእቱ ክብሮሙ ለቅዱሳን፤ መድኃኒቶሙ ለጻድቃን አሠርገዋ ለምድር በጽጌ ሮማን፤ ስብሐት ዋህድ ዘምስለ ምሕረት፤ በመስቀሉ ወበቃሉ አዕበዮሙ ለአበዊነ። ትርጉም፦ እርሱ የቅዱሳን ክብራቸው፤ የጻድቃን መድኃኒታቸው ነው፤ ምድርን በሮማን አበባ አስጌጣት፤ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ከምሕረት ጋር ያለ የወልድ ምስጋና በመስቀሉና በቃሉ አባቶቻችንን ከፍ ከፍ አደረጋቸው።
      • "ሰላም ለሕማሙ ወሰላም ለሞቱ። ሰላም ለገቦሁ ቅድስት ዘውኅዘ እምኔሃ ደመ ወማይ፡ፅሙር። አንቅዕተ ብዕል ወክብር። ሰላም ለግንዘቱ በዘጠብለልዎ ሰላም ለመቃብሩ ኀበ ቀበርዎ"። ትርጉም፦ ለሕማሙ ሰላምታ ይገባል፤ ለሞቱም ሰላምታ ይገባል። የሀብት (የብልጥግና) የክብር ምንጮች የኾነ ደምና ውሃ አንድነት (ተባብሮ) ከርሷ የፈሰሰ ለኾነች ለቅድስትጐኑ ሰላምታ ይገባል። በሚጠቀልሉት ገንዘብ ለኾነ ለግንዘቱ ሰላምታ ይገባል፤ በቀበሩት ዘንድ ላለ መቃብሩ ሰላምታ ይገባል። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።
      • አቡነ ጊዮርጊስ ዘጣና፦ አገራቸው ጣና ዘጌ ነው። በዋሻ ውስጥ አርባ ዘመን ሙሉ ዘግተው ሲኖሩ መና ከሰማይ እየወረደላቸው ውሃም በዋሻ ውስጥ ፈልቆላቸው ይኖሩ ነበር። አንድ ቀን መልአክ መጥቶ ምን ቢጋደሉ የጌታችንን ስጋውን በልተው ደሙን ካልጠጡ እንደ ማይድኑ ነገራቸው። በመልአኩም ትዕዛዝ መሰረት ከዋሻው ወጥተው ሊቆርቡ ቤተ ክርስቲያን ገቡ በቅዳሴም ላይ ሳሉ አንድ ድንቅ ምስጢር ተመለከቱ ይህም በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ካህኑ "ሀበነ" ሲል ጌታችን በዕለተ አርብ እንተ ተሰቀለ ሆኖ ደሙ ሲፈስ የካህኑ እጅ በደም ተነክሮ በመንበሩ ቆሞ ቢያዩት በድንጋጤ ሳይቀሳቀሱ አርባ ዓመት ተኝተዋል ይህም በሰው አቆጣጠር በጌታችን ዘንድ ግን ምን ያይህል ጊዜ እንደ ሆነ እራሱ ባለቤቱ ያውቀዋል። በመጨረሻም ጻድቁ በዐረፉ ጊዜ መቃብራቸውን አራዊት ቆፍረውላቸው መነኰሳቱ ገንዘው ቀብረዋቸዋል። ታቦታቸው በጣና ይገኝል። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳንና ቅዱሳን በዓላት።
      • አቡነ መብዓ ጽዮን፡- አባታቸው ንቡረ ዕድ እናታቸው ደግሞ ሀብተ ጽዮን ይባላሉ፡፡ በሌላኛው ስማቸው ተክለ ማርያም ይባላሉ፡፡ ይህንንም ስም ያወጣችላቸው እመቤታችን ናት፡፡ እመቤታችንን ከሕፃንነታቸው ጀምረው እጅግ ይወዷት ነበር፡፡ ትንሽ ልጅ ሳሉ አንድ ካህን ወደ ሀገራቸው በእግድነት መጣና አባታቸው ሀብተ ጽዮን አሳደሩት፡፡

እንግዳውም ካህን የእመቤታችንን ሥዕል ምስለ ፍቁር ወልዳን ይዞ ነበር፡፡ ሲተኛም በራስጌው ያኖራት ስለነበር በሀብተ ጽዮንም ቤት አድሮ ጠዋት ተነሥቶ ሲሄድ የእመቤታችንን ሥዕል በራስጌው እንዳኖራት እረስቶ ሄደ፡፡ ያንጊዜ ሕፃን የነበሩት አባ መብዓ ጽዮንም ሥዕሏን ወስደው ሳሟት፣ በእርሷም ደስ ተሰኙባት፡፡ ለሌላም ሰው አልሰጥም ብለው በአንገታቸው አሰሯት፡፡ ሀብተ ጽዮንም "ይህችን የእግዳው ካህን ንብረት የሆነች የእመቤታችንን ሥዕል ከቤት እንዳላስቀምጣት ኃጢአት ይሆንብኛል እንዳልሰጠውም ከየት አገኘዋለሁ" እያለ ሲቀጨነቅ ከዕለታት በአንደኛው ቀን ያንን እንግዳ አገኘው፡፡ ባገኘውም ጊዜ ከቤት የተዋትን የእመቤታችንን ሥዕል እንዲወስድ ነገረው፡፡ መጀመሪያ ሕፃን መብዓ ጽዮን እንዳገኛትና በጣም እንደወደዳት ለሌላ ሰውም አልሰጥም ብሎ በግድ ቀምቶ እንዳስቀመጣት ነገረው፡፡ እንግዳውም ይህን ሲሰማ "የሥዕሊቱ ባለቤት እርሷ የሕፃኑ እንድትሆን ፈቅዳለታለች፤ ከእኔ ዘንድ መሆኗን ፈቅዳ ቢሆንማ ኖሮ ባልተረሳችኝ ነበር ለዚያ ላገኛት ልጅህ የተገባች ናት" ካለው በኋላ እርስ በእርሳቸው ሰላምታ ተሰጣጥተው ተለያዩ፡፡

አቡነ መብዓ ጽዮን ዕድሜያቸው ከፍ ሲል ወላጆቻቸው ሚስት ሊድሩላቸው ሲሉ እርሳቸው ግን አላገባም ብለው የዚህን ዓለም ጣዕም ንቀው ነው የመነኑት፡፡ የምንኩስና ልብስ ከለበሱበት ጊዜ ጀምረው በበቅሎና በፈረስ ላይ ተቀምጠው አያውቁም፤ በአልጋም ሆነ በምንጣፍ ላይ አልተኙም ይልቁንም የአንድ ሰው ሸክም የሚያህል ትልቅ ድንጋይ በደረታቸው ተሸክመው ከአመድ ላይ ይተኙ ነበር እንጂ፡፡ ከሰንበት ቀናት ውጭ ሲቀመጡም ድንጋዩን በራሳቸው ላይ ይሸከሙታል፣ ሲሰግዱም በጀርባቸው ያዝሉት ነበር፡፡

አባታችን ለቅዱስ ሥጋ ወደሙ እጅግ ትልቅ ክብር ስለነበራቸው የቆረበ ሰው ከቤተክርስቲያን ወጥቶ ሲሄድ እንቅፋት እንኳን ሲመታው ስለሥጋ ወደሙ ክብር ብለው እግሩ የደማበትን ሰው ደሙን ይጠጡት ነበር፣ ደሙ የፈሰሰበትንም አፈር ይልሱታል፡፡ ይህም የመድኃኔዓለምን ሥጋና ደም ከማክበራቸው የተነሣ ነው፡፡ ጻድቁ ጌታችን በዕለተ ዓርብ መራራ ሐሞት መጠጣቱን አስታውሰው ሁልጊዜ ዐርብ ዐርብ ኮሶ ይጠጡ ነበር፡፡ መድኃኔዓለምም በየጊዜው በሕፃን አምሳል ይገለጥላቸዋል፡፡ በዕለተ ዓርብም እንደተሰቀለ ሆኖ ይገለጥላቸው ነበር፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ለአቡነ መባዓ ጽዮን በመሠዊያው ላይ በነጭ በግ አምሳል ይገለጥላቸው ነበር፡፡

መከራ ሞቱን እያስታወሱ ሰውነታቸውን ይጎዱ እንደነበር በቅዱስ ገድላቸው ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡- "በተቀደሰች በዓርባ ጾምም የመድኃኔዓለምን ግርፋት እያሰበ ሰውነቱን በእጅጉ ገረፈ፡፡ ደሙ ከመሬት እስኪወርድ ድረስ ልቡንም አጥቶ ከምድር ላይ ወደቀ፡፡ የመድኃኔዓለምን መከራውን አስቦ እንደሞተም ሆነ፡፡ መድኃኔዓለምም ወደ እርሱ መጣና "ተነሥ እኔ ቁስልህን እፈውስሃለሁ" ብሎ የጀርባውን ቁስል ዳሰሰው፡፡ ምንም ሕማም እንዳላገኘውም ሆነ፡፡ መድኃኔዓለምም አባታችንን "በአንተው እጅ ትገደልን? እኔ እንኳ የተገደልኩት በአመፀኞች በአይሁድ እጅ ነው" አለው፡፡ በዚያችም ሰዓት ጌታ የመባዓ ጽዮንን ከንፈሮቹን ይዞ ሦስት ጊዜ እፍ አለበትና "የከበረ ትንፋሼም ከትንፋስህ ጋራ ይጨመር፣ ሥጋህም ከነፍስህ ጋራ የከበረ ይሁን› አለው፡፡ "አንተ በላዩ እፍ ያልህበትም የተቀደሰና የከበረ ይሁን" አለው"፡፡

5 months ago

#ነሐሴ_7_ጽንሰታ_ለማርያም

?? ነሐሴ 7 የአምላክ እናት የፅንሰቷ በዓል በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል። በነገረ ማርያም ላይ እንደተጻፈ በእናቷ በሐና በኩል ያሉ የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ጴጥሪቃ ቴክታ ይባላሉ።

?? ጴጥርቃ እና ቴክታ የሚባሉ ሰዎች በኢየሩሳሌም በአንድነት ተጋብተው ይኖሩ ነበር። እነዚህም በእግዚአብሔር የሚያምኑ የተወደዱ ጻድቃን ደግ ሰዎች ነበሩ። እነዚህም ሰዎች በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ የተመሰከረላቸው ባለጸጎች ነበሩ። ነገር ግን የሚወርሳቸው ልጅ አልነበራቸውምና መካን ነበሩ። ከዕለታትም ባንድ ቀን ቴክታ ለባሏ ጴጥርቃ አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን የሚያውቅ የለም ትላንትና ማታ በሕልሜ “ርኢኩ በሕልምየ ጸዓዳ ጣዕዋ ወጽአት እምከርስየ - ነጭ ጥጃ ከማኅጸኔ ስትወጣ ያችም ነጭ ጥጃ ሌላ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንዲሁ እስከ ፯ት ትውልድ ሲዋለድ ሰባተኛይቱም ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃዋም ፀሐይን ስትወልድ አየሁ አለችው።

?? እርሱም በጧት ከሕልም ፈቺ ዘንድ ሂዶ የነገረችውን ሁሉ ነገረው፤ ያም ህልም ፈቺ “እግዚአብሔር በምህረቱ አይቷችኋል በሣህሉ መግቧችሁኋል ፯ አንስት ጥጆች መውለዳችሁ ፯ ሴቶች ልጆች እና የልጅ ልጆች ትወልዳላችሁ፤ ከቤታችሁ ሰባተኛይቱ ጨረቃ መውለዷ ከሰው የበለጠች ከመላእክትም የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ። የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጠልኝም” አለው። እርሱም የነገረውን ሁሉ ሄዶ ነገራት።

?? እርሷም እንጃ አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን ማን ያውቃል? ብላ ዝም አለች። ከዚያም ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስሟንም ‘ሄሜን’ ብለው አወጡላት፤ ሄሜንም አድጋ ለአካለ መጠን ስትደርስ አጋብተዋት ሴት ልጅ ወለደች። በስምንተኛ ቀኗም ‘ደርዲ’ ብለው ስም አወጡላት። ደርዲም አድጋ እንዲሁ ሴት ልጅ ወለደች እና ‘ቶና’ አለቻት። ቶናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ‘ሲካር’ አለቻት። ሲካርም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ‘ሴትና’ አለቻት። ሴትናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ‘ሔርሜላ’ አለቻት።ከቤተ ሔርሜላም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ንጽህት ቅድስት ክብርት የምትሆን እመቤታችንን የምትወልደውን ሐናን ወለደች። ሐና በሥርዓት አደገች፡፡ ለአእምሮ ስትበቃ፣ አካለ መጠን ስትደርስ መንግሥት ወገን ከነቅዱስ ዳዊት ወገን ከሆነው ከቅዱስ ኢያቄም ጋር አጋቧት።

?? እነዚህ ቅዱሳን ኢያቄም እና ሐና በአንድነት ተጋብተው ሲኖሩ ልጅ አጡ፤ ከእለታት አንድ ቀን ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሂደው ሲጸልዩ ሲያዝኑ ዋሉ። ሀዘናቸው እንዴትስ ነው ቢሉ፡- ኢያቄም፡- "አቤቱ ጌታዬ ያባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ አትጣለኝ አትናቀኝ ጸሎቴን ስማኝ ፈቃዴን ፈጽምልኝ፤ ለዐይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የሚሆን የተባረከ/ች ወንድ ወይም ሴት ልጅ ስጠኝ" ብሎ ሲለምን ዋለ። ሐናም በበኩሏ "አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ፤ ስማኝ ለዐይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የምትሆነኝ የተባረከች ሴት ልጅ የማኅጸኔን ፍሬ ስጠኝ" ብላ ስትለምን ዋለች።

?? እንዲህ ብለው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ርግብ ከልጆቿ ጋር ስትጫወት ዐይታ አቤቱ ጌታዬ ለዚች ግእዛን ለሌላትመጋረጃ እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሳኸኝ ብላ ምርር ብላ አለቀሰች። ከሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ሄደው አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ፣ ቤተ እግዚአብሄርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን፤ ሴት ልጅም ብንወልድ ማይ (ውሃ) ቀድታ፣ መሶብ ወርቅ ሰፍታ፣ ፈትላ፣ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን ብለው ስዕለት ገቡ። ዘካርያስም እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ይስማችሁ ስእለታችሁን ይቀበልላችሁ ጻህቀ ልቦናችሁን ይፈጽምላችሁ ብሎ አሳረገላቸው።
የተባለው
?? ከዚያም በኋላ ቅድስት ሐና እና ቅዱስ ኢያቄም ዕለቱኑ ራዕይ ዐይተው ነገር አግኝተው አደሩ። ራዕዩም ኢያቄም “ርኢኩ በህልምየ እንዘ ይትረኀው ሰባቱ ሰማያት - ፯ቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ” አላት ፤ ወፍ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ነጭነቱ ንጽሐ ባሕሪው ነው፤ ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ ዐየሁ ማለቱ፤ አምላክ የኢያቄምን ( የሰውን) ባሕርይ ባሕርይኀቤየ እንዳደረገው ሲያጠይቅ ነው፤ ፯ቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ልዩ ልዩ ባሕርይው፣ ምልአቱ፣ ስፍሃቱ፣ ርቀቱ፣ ልእልናው፣ ዕበዩ መንግሥቱ ናቸው።

?? ሐናም እኔም አየሁ አለችው፤ ምን አየሽ ቢላት፤ “ዖፍ ጸዓዳ መጽአት ወነበረት ዲበ ርዕስየ ወቦአት ውስተ ዕዝንየ ወኀደረት ውስተ ከርስየ - ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማኅጸኔ ስትተኛ አየሁ” አለችው። ርግብ የተባለች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት። ነጭ መሆንዋ ንጽህናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ድንግልናዋ ነው። ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማሕጸኔ ስትተኛ አየሁ ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን መጽነሷን ነው። ይህንኑም ራዕይ ያዩት ሐምሌ ፴ (ሠላሳ) ዕለት ነው።

?? እነሱም እንዲህ ያለ ራዕይ ካየን ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም፤ ፈቃደ እግዚአብሔር ቢሆን ብለው አዳምንና ሔዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሏት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለኛስ ይልክልን የለምን? ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ ፯ ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ። በነሐሴ በሰባተኛው ቀን ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁና ዛሬ በሩካቤ ሥጋ ተገናኙ ብሏችኋል ጌታ ብሎ መልአኩ ለሐና ነገራት። በፈቃደ እግዚአብሔር በብሥራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም በዕለተ እሑድ ነሐሴ ፯ ቀን ተፀነሰች።

?? እመቤታችን ከተፀነሰች በኋላ አይሁድ ቀንተው ተነሱባቸው። ከቅናትም የተነሳ ሊገድሏቸው ይፈልጉ ነበርና በመልአኩ ትዕዛዝ ሸሽተው በሊባኖስ ተራራ ላይ እመቤታችን እግዝትእነ ማርያም በተፀነሰች በ፱ ወር ከአምስት ቀን የግንቦት መባቻ ዕለት ግንቦት ፩ ተወለደች።

።።።።#ወስበሐት_ለእግዚአብሔር ።።።።
።።።።። #ወለወላዲቱ_ድንግል ።።።።።
።።።።። #ወለመስቀሉ_ክቡር ።።።።።

የአምላክ እናት የተፀነሰችበት ዕለት!
ነሐሴ 6 / 2016 ዓም

5 months ago

#የሰኞ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችን ከባረከችው በኋላ ምስጋናውን የጀመረው #“ፈቀደ እግዚእ…” ብሎ ነው፡፡
፩. በመቅድመ ወንጌል “ወአልቦቱ ካልእ ሕሊና ዘንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢያቱ - በኃጢአቱ ከማዘን፣ ከማልቀስ በቀር ሌላ ግዳጅ አልነበረውም” እንዲል ጌታ ፭ ሺህ ከ፭፻ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ ያዝን ይተክዝ የነበረ አዳምን ነጻ ያደርገው (ያድነው) ዘንድ ወደደ፡፡ ምድራዊ ንጉሥ የተጣላውን አሽከር “ሰናፊልህን (ልብስህን) አትታጠቅ፤ እንዲህ ካለ ቦታም አትውጣ” ብሎ ወስኖ ያግዘዋል፡፡ በታረቀው ጊዜ ግን ርስቱን፣ ጉልበቱን፣ ቤቱን፣ ንብረቱን እንደሚመልስለት ኹሉ ንጉሠ ሰማይ ወምድር እግዚአብሔርም “ጥንቱንም መሬት ነህና ወደ መሬት ተመለስ” /ዘፍ.፫፡፲፱/ ብሎ ፈርዶበት የነበረ አዳምን ይቅር ብሎ ወደ ቀደመ ቦታው ወደ ገነት፣ ወደ ቀደመ ክብሩ ወደ ልጅነት ይመልሰው ዘንድ ወደደ /ሉቃ.፳፫፡፵፫/፡፡
#ሊቁ (ቅዱስ ኤፍሬም) በኦሪ. ዘፍ ፫፥፱ ያለውን ኃይለ ቃል ሲተረጕምም እንዲህ ይላል፡- “ቸር ወዳጅ የኾነው እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን ወዲያው እንደተሳሳቱ ፍርዱን አላስተላለፈባቸውም፤ ታገሣቸው እንጂ፡፡ ይኸውም ምኅረት ቸርነቱን ይለምኑት ዘንድ ነው፡፡ እነርሱ ግን አልለመኑትም፡፡ እግዚአብሔርም ምንም ሳይናገራቸው በገነት ውስጥ በእግር እንደሚመላለስ ሰው ኾኖ በድምፅ ብቻ መጥራቱን ቀጠለ፡፡ አዳምና ሔዋን ግን አሁንም አልመለስ አሉ፡፡ በመጨረሻም አምላክ ድምፁን ማሰማት ጀመር፡፡ ‘አዳምን ወዴት ነህ?’ ይላቸው ጀመር፡፡ አስቀድሞ በእግር እንደሚመላለስ ሰው ኾኖ በድምፅ ብቻ መጥራቱ መንገድ ጠራጊው ዮሐንስን እንደሚልክላቸው፣ ቀጥሎ ድምፅ አሰምቶ ወዴት ነህ ብሎ መፈለጉም ወልደ እግዚአብሔር ራሱ በተዋሕዶ ፍጹም ሰው ኾኖ ሊያድናቸው እንደ ፈቀደ ያጠይቃል” ይላል /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Genesis/፡፡
#ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ኦሪት ዘልደትን በተረጐመበት በ፲፯ኛው ድርሳኑ ላይ፡- “በዚህ ንግግሩ የእግዚአብሔር ከአእምሮ የሚያልፈውን ፍቅሩን እንመለከታለን፡፡ አንድ አባት ልጁ የማይረባውን ነገር በማድረግ ከክብሩ ቢዋረድም አባቱ እጅግ እንዲወደውና ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ እንዲደክም፤ እግዚአብሔርም ከሰው ልጆች ጋር ይህን የመሰለ ፍቅር ሲያሳይ እናስተውላለን፡፡ አንድ ሐኪም ወደ ታማሚው አልጋ ጠጋ ብሎ በሽተኛውን እንዲጠይቀውና አስፈላጊውን ኹሉ እንደሚያደርግለት፣ ሰው ወዳጁ እግዚአብሔርም ወደ አዳም ጠጋ ብሎ ሲያነጋግረው እንመለከታለን” ይላል፡፡
ዳግመኛም #በሌላ አንቀጽ “አዳም ሆይ ወዴት ነህ” ማለቱ፣ ለአቅርቦት መኾኑን ሲገልጥ፡- “አዳም ሆይ! ምን ኾንክብኝ? በመልካም ቦታ አስቀምጬህ ነበር፤ አሁን ግን ቦታህ ተለወጠብኝ፡፡ ብርሃን ተጐናጽፈህ ነበር፤ አሁን ግን ጨለማ ውስጥ አይሃለሁ፡፡ ልጄ! ወዴት ነህ? ይህ ኹሉ እንደምን ደረሰብህ? በአንተ ውስጥ ያኖርኩት መልኬ ማን አበላሸብኝ? በዚህ ያህል ፍጥነት የጸጋ ልብስህን ገፎ የጽልመት ልብስ ያከናነበህ ማን ነው? ውዴ! ባለጸጋ አድርጌ ፈጥሬህ አልነበረምን? ታድያ አሁን ድኽነት ውስጥ የከተተህ ማን ነው? ያን የግርማ ልብስህን ሰርቆ ዕራቆትህ ትኾን ዘንድ ያደረገህ ማን ነው? እኮ የጸጋ ልብስህን እንድታጣ ያደረገህ ማን ነው? ይህን የመሰለ ቅጽበታዊ መለወጥ ከወዴት መጣብህ? የከበረ ዕንቁህን እንድትጥል ያደረገህ ምን ቢገጥምህ ነው? አክብሮ በተወደደ ቦታ ካስቀመጠህና ኹል ጊዜ በስስት ዐይን ሲያነጋግርህ ከነበረው አምላክህ ተደብቀህ እንድትሸሸግ ያደረገህ ምንድነው? ማንም የወቀሰህ ሳይኖር፣ እንዲህ እንዲህ አድርገህ በድለሃል ብሎ የመሰከረብህ ሳይኖር ይህን ያህል በፍርሐት መናጥ ከወዴት አገኘህ?” ይላል /Daily Readings of St. John Chrysostom/፡፡
#ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ሆይ! ፭ ሺሕ ከ፭፻ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ የነበረ አዳምን ነፃ ካደረገው ልጅሽ ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡ #“ቅድስት” ማለቱ ንጽሕት፣ ጽንዕት፣ ክብርት ልዩ ሲል ነው፡፡ ይኸውም፡-
· ሌሎች ሴቶች ከነቢብ ከገቢር ቢነጹ ከሐልዮ አይነጹም፡፡ እሷ ግን የዕንቆራው #ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ቴዎዶጦስ “ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ ድንግል በሕሊናሃ ወድንግል በሥጋሃ- ከፈጠራት ጀምሮ በምንም በምን (በሕሊናዋም በሥጋዋም) ከድንግልናዋ አልተለወጠችም” /ሃይ.አበ.፶፫፡፳፪/ እንዲል ከነቢብ፣ ከገቢር፣ ከሐልዮ ኃጢአት ንጽሕት ናትና፡፡
· #ጽንዕትም አለ፡፡ ሌሎች ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው፤ ኋላ ተፈትሖ አለባቸው፡፡ እሷ ግን ቅድመ ፀኒስ ጊዜ ፀኒስ፤ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ጽንዕት (ወትረ ድንግል) ናትና፡፡
· #ክብርትም አለ፡፡ ሌሎችን ሴቶች ብናከብቸው ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንትን ወለዱ ብለን ነው፡፡ እሷን ግን ወላዲተ አምላክ ወልዳልናለች ብለን ነውና፡፡
· #ልዩም አለ፡፡ እናትነትን ከድንግልና፣ አገልጋይነትን ከእናትነት፣ ወተትን ከድንግልና ጋር አስተባብራ የተገኘች፤ በድንግልናም እያለች ከጡቶቿ ወተት ተገኝተው በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግብ መጋቤ ፍጥረታት አምላክን የወለደች፤ እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል ሱራፌልም በፍርሐት በረዐድ ኹነው ዙፋኑን የሚሸከሙት እሳተ መለኮት ጌታን ፱ ወር ከ፭ ቀን በማሕፀኗ የተሸከመች፣ በክንዷ የታቀፈች፣ በዠርባዋ ያዘለች ከእመቤታችን በቀር ሌላ ሴት የለችምና፡፡
#“ለምኚልን” ሲልም ልክ በዚህ ምድር እንደነበረው ዓይነት ልመና ከዚያ በኋላ ኖሮባት አይደለም፡፡ ስንኳን በሷና በሌሎችም የለባቸውም፡፡ በቀደመ ልመናዋ የምታስምር ስለ ኾነ እንዲህ አለ እንጂ፡፡ ይኸውም በቃል ኪዳኗ ማለት ነው፡፡ አንድም በቁሙ ይተረጐማል፡፡ ማዘከር (ማሳሰብ) አለና፡፡
#“ሰአሊ ለነ ቅድስት” የሚለው ቅዱስ ኤፍሬም የተናገረው አይደለም፡፡ “ታድያ ይህን የጨመረው ማን ነው?” በሚለው ላይም ኹለት ዓይነት አመለካከለት አለ፡፡ “ቅዱስ ያሬድ ለዜማ መከፈያ ተናግሮታል” የሚሉ አሉ፤ “የኋላ ሊቃውንት ተናግረውታል” የሚሉም አሉ፡፡

5 months, 1 week ago

ፆመ ፍልሰታ የእመቤታችን እረፍት ትንሳኤና እርገት ሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡ እመቤታችን በተለያዩ ጊዜያት ሞትና ትንሣኤዋን ለሐዋርያት የገለጸችበትን ምስጢር ከነሐሴ 1-16 ድረስ ምእመናን በጾም በጸሎት ተወስነው የልጇን ቸርነት የእርሷን አማላጅነት በሱባኤ ይማጸናሉ፡፡ የሱባኤው ወቅት ሲፈጸም “እመቤታችን በእውነት ተነሥታለች” ብለው በደስታ የጾሙን ወቅት ይፈጽማሉ፡፡ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን ቅዱስ ያሬድ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የሐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው፡፡ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል” በማለት ገልጾታል፡፡
በኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ 64 ዓመታት ያህል ቆይታ አርፋ ተነሥታ በክብር አርጋለች፡፡ ይህንን የትንሣኤና ዕርገት ዐቢይ ምሥጢር ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ተንሥአ እግዚኦ” ውስተ ዕረፍትከ፡፡ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፡፡ አንተና የመቅደስህ ታቦት” /መዝ.131፡8/፤ እንዲሁም “ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” /መዝ.44፡9/ ሲል የተናገረው ቃለ ትንቢት በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና የጸናች የቅድስት ድንግል እመቤታችንን ዕረፍት፣ ትንሣኤ፣ ፍለሰት /ዕርገት/ ያስገነዝባል፡፡ /ራእ.11፡19/
እመቤታችን ታቦተ እግዚአብሔር መሆኗን አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ሲገልጽ “ከመ ታቦት ሥርጉት በወርቀ ዓረብ ወተርሴስ በድንግልና ማርያም ሥርጉተ ሥጋ ወነፍስ” ሲል አመስግኗታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በትርጓሜያቸው ይህንን ቃለ ትንቢት ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ከገለጣት “ንግሥተ ሰማይ፤ የሰማይ ንግሥት” /ራእ.12፡1/ ጋር በማገናዘብ የእመቤታችንን ሁለንተናዊ ክብርና ልዕልና አምልተውና አስፍተው ገልጸውታል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ “… በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው፡፡….. ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ሥራቸውም ይከተላቸዋል” /ራእ.14፡13/ ብሎ እንደመሰከረው እመቤታችን ከዕረፍቷና ዕርገቷ በኋላ የመጨረሻ ወደ ሆነው ክብር መሸጋገሯ ያስረዳል፡፡
ይህንን ክብርዋን በመረዳት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር “ወበእንተዝ ናዐብየኪ ኩልነ ኦ እግዝእትነ ወላዲተ አምላክ ንጽሕት ኩሎ ጊዜ፡፡ ንስአል ወናንቀዐዱ ኀቤኪ ከመ ንርከብ ሣህለ በኀበ መፍቀሬ ሰብእ፤ ሁልጊዜ ንጽሕት የምትሆኚ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ ስለዚህ ነገር እናከብርሻለን፣ እናገንሻለን፡፡ ሰውን ከሚወድ ልጅሽ ዘንድ የቅርታንና ምሕረትን እናገኝ ዘንድ ሁል ጊዜ ዓይነ ልቡናችንን ወደ አንቺ እናነሣለን፡፡ በማለት ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ሁል ጊዜ ዓይነ ልቡናችንን ወደ አንቺ እናነሣለን፡፡ በማለት ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣትን ልዩ የቃል ኪዳን ጸጋና አምላካዊ ክብር እያመሰጠሩ ያመሰግኗታል፡፡ ሊቁ “ቀስተ ደመና ማርያም ትእምርተ ኪዳኑ ለኖኅ፣ ዘእግዚአብሔር ሤመኪ ለተዝካረ ምሕረት ወፍትሕ፣ ህየንተ ቀስፋ ለምድር ወአማሰና በአይኅ፡፡ ብሎ እንዳመሰገናት፡፡
እመቤታችን በአጸደ ሥጋ ሳለች ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ በመዋዕለ ሥጋዌ ላደረገው የድኅነት ዓለም ጉዞ ምክንያት ነበረች፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ባርነትና ስደት ለማጥፋት ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ የሰው ልጆችን ያሳደደ ሠይጣን በሄሮድስ አድሮ ሲያሳድደው ልጇን ይዛ በመሰደድ ለድኅነታችን ምክንያት ነበረች፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ባርነትና ስደት ለማጥፋት ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ የሰው ልጆችን ያሳደደ ሠይጣን በሄሮድስ አድሮ ሲያሳድደው ልጇን ይዛ በመሰደድ ለድኅነታችን ምክንያት ነበረች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በራእዩ እንዳየው፤ “ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች፡፡ እርስዋም ፀንሳ ነበር፡፡ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጨንቃ ጮኸች፡፡ ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ፡፡ አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔር ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ፡፡ ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስልሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች ”/ራእ.12፡1-6/

5 months, 1 week ago

#ፍልሰታ_መጣች ?
"ሕፃኑም ወጣቱም ወንዱም ሴቱም ዕድሜው የገፋውም ሁሉም በፍቅር የሚፆሟት፣ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድዔትና በረከት የሚታፈስባት፣ ፍቅረ እግዚአብሔር በሰው ልቡና የሚሰለጥንባት ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር የሚያይልባት #የንሰሐና_የምህረት_ጾም_ጾመ_ፍልሰታ_መጣች ?

በዓለም ያሉ ወደ ቤተክርስቲያን በቤተክርስቲያን ያሉ ወደ ገዳማት የሚገሰግሱባት ጾመ ፍልሰታ መጣች?

የተዋህዶ ልጆች እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ ?

??❤️ ለሀገራችን ምህረትን ፣ ሰላም እና ፍቅርን የድንግል  ማርያም ልጅ ያድልልን የበረከት የምህረት የይቅርታ ፆም ይሁንልን ??❤️

5 months, 1 week ago

Henok Asrat:
? #ሱባዔ_ለምን? ?

1⃣እግዚአብሔርን ለመማፀን

ምንም የምንጠይቀው /የምንማጸነው/ ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኘው መልስ አይኖርም። አንድ ሰው ለገባው ሱባዔ መልስ ወዲያውኑ ሊያገኝ ይችላል ወይም ደግሞ መልሱ ሊዘገይ ይችላል። በዚህ ጊዜ  ከተሐራሚው ትዕግስት /መታገሥ/ ይጠበቅበታል፤ “ለምን ላቀረብኩት ጥያቄ ቶሎ መልስ  አልተሰጠኝም” በማለት ማማረርና እግዚአብሔርን መፈታተን ተገቢ አይደለም። እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበትና ለሚማጸነውም መልስ የሚሰጥበት የራሱ ጊዜ አለው።

2⃣ #የቅዱሳንን_በረከት_ለመሳተፍ

ቅዱሳን በሚጋደሉበት ቦታ “ከወንዶችና ከሴቶች ይልቅ የሚበልጥ ስም እሰጣቸዋለሁ” ኢሳ 56፥6 በማለት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለገባለቸው ሱባዔ በመግባት በረከታቸውን መሳተፍ ይቻላል። #በጾመ_ነቢያት_የነቢያትን_በረከት_ለመሳተፍ_በጾመ_ፍልሰታ_የእመቤታችንን_በረከት_ለመሳተፍ_ሱባዔ_መግባት_የነበረና_ወደ_ፊትም_የሚኖር_የቤተ_ክርስቲያን_ሥርዓት_ነው። ነቢዩ ኤልሳዕ መምህሩን ኤልያስን በማገልገል የኤልያስ በረከት በእጥፉ በኤልሳዕ ላይ አድሮበታል። ይህን አብነት በማድረግ በየገዳማቱ በትሕርምት የሚኖሩ መናንያንን ያገለገሉበትን ገዳም አባት በረከት በእጥፍ እየተቀበሉ ለሌሎችም የሚያቀብሉ አባቶች በየገዳማቱ አሉ። 1ነገ 2፥9

3⃣ #የተሰወረ_ምስጢር_እንዲገልጥልን
ቅዱሳን በየራሳቸው ያዩት ራእይ ምስጢር ሲከደንባቸው የራእዩ ምስጢርና ትርጉም እንዲገለጥላቸው ሱባዔ ይገባሉ። እግዚአብሔርም በንጽሕና ሆነው የገቡትን ሱባዔ ተመልክቶ ምስጢር ይገልጥላቸዋል። ለምሳሌ ነቢዩ ዕዝራ የመጽሐፍትን ምስጢር እንዲገልጥለት ሱባዔ ቢገባ የጠፉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዳግም መልሶ ለመጻፍ ችሏል። መዝ 8፥1 በዘመነ ብሉይ የነበሩ ነቢያትም በዘመናቸው የነበሩ ነገሥታት ራእይ አይተው ነገር ግን ምስጢሩ የተሰወረባቸውን ለመተርጎምና ምስጢሩን ለመረዳት ሱባዔ ይገቡ ነበር። ዘፍ 41፥14-36 ፣ ዳን 4፥9 ፣ ዳን 5፥4 ፣ ዳን 5፥25 በዘመነ ሐዲስ በስፋት የሚወሳው ቅዱሳን ሐዋርያት ከነሐሴ 1 – 14 ተሰውሮ የነበረውን የእመቤታችንን ትንሣኤ ለማየት የገቡት ሱባዔ ነው።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

??????????????

5 months, 2 weeks ago

"ወእምዝ ፈትሐ አፉሁ ከመ ይጽርፍ ላዕለ እግዚአብሔር ወላዕለ ስሙ ወላዕለ ጽርሐ መቅደሱ"

"እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ" ራዕ 13፥6

በፈረንሳይ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ኦሎምፒክ ውድድር የተፈጸመውን አስነዋሪ ድርጊት ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ሊቃወመው እንደሚገባ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ አሳሰቡ።

ሐምሌ ፳፫ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም (አቡቀለምሲስ ሚዲያ ፤ ደብረ ብርሃን)
++++ ++++ ++++ ++++ ++++ ++++ +

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጥስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በፈረንሳይ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ኦሎምፒክ ውድድር የተፈጸመውን አስነዋሪ ድርጊት ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ሊቃወመው እንደሚገባ አሳስበዋል።

በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ በኦሎምቢክ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ በመላው ክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን ምሥጢረ ቊርባንን ያቀለለ እኩይ ተግባር በወገንተኛነት የደገፈ ትርኢት በዓለም ዜና ማሰራጫ ተመልክተናል።

ይህንን በኦሎምፒክ ጨዋታ መክፈቻ ሥርዓት ላይ የተደረገውን አስነዋሪ ተግባር እንቃወማለን፡፡

ዓለም አቀፋዊ መከባበርን እና የሥነ ምግባር መርሆችን ለማመልከትና ለመግለጽ በተዘጋጀ ዝግጅት ላይ እንደዚህ ዓይነቱን የሰብአዊ ክብርንና የነፃነት ድንቁርናን መመልከት የሰው ልጅ ምን ያህል ከፍተኛ ውርደትና ዝቅጠት ላይ መሆኑን ዓይነተኛ ማሳያ ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ በምዕራፍ 13፡6 ጀምሮ ‹‹እግዚአብሔርንም ስሙን ማደሪያውንና በሰማይ የሚኖሩትን ለመሳደብ አፉን ከፈተ›› ይላል በኦሎምፒክ ጨዋታዎች መክፈቻ ሥርዓትና በጨዋታ ጊዜ ይታይ የነበረው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ይህን አስጸያፊና አስነዋሪ ተግባር ያመላክታል፡፡

በክርስትና እምነት የከበረውን ፣ በቅድስት ቤተክርስቲያን የቅዱስ ቁርባን ሥርዓትን ለማቃለል የተደረገው አሳፋሪ ተግባር ከመሆኑም በላይ ኢ-ሰብዓዊ እና ኢ-ሞራላዊ ጭምር ተግባር ነው፡፡

በመሆኑም ይህን አሳፋሪ ሥራ ማንኛውም ክርስቲያን ሊቃወመው ይገባል፡፡

በማለት ይህን ክፉ ድርጊት አጽንዖት ሰጥተን የምንቃወመው መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ይህ ተግባር የሃይማኖትን ነጻነት የሚጋፋ፣ ጾታ የሚለውጡ አካላትን ሰይጣናዊ ድርጊት የሚያበረታታና በክርስትና ሃይማኖትና በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመ ታሪካዊ ጥቃት ስለሆነ መላው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እንዲቃወሙት ጥሪያችንን እናቀርባለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!!

አባ ቀሌምንጦስ
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጥስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ሐምሌ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ፤ ደብረ ብርሃን
ኢትዮጵያ

7 months, 4 weeks ago

#ከሐልዮ_ኃጢአት_መጠበቅ

ሰይጣን ነቅዓ ሐልዮን መጠበቅ ላልቻለ ወጣት በቀጣይ እርሱን የሚወጋበት ኹለተኛው ጦር ሐልዮ ኃጢአት ነው። “የሐልዮ ኃጢኣት ምን ትጎዳለች?” እያለ እንዲያስብ ያደርገዋል። በሐልዮ ኃጢአት ያዝለዋል። ይኸውም ደቂቀ ሴት ደቂቀ ቃኤልን ከመስማት አልፈው እንዲመለከቷቸው በማድረግ በዝሙት ፍላጻ እንደነደፋቸው ነው። ስለዚህ የተለያዩ ነገሮችን እንዲመለከት ያደርገዋል። ለምሳሌ ራስን በራስ ስለ ማጎሳቆል፣ ወይም ስለ ምስለ ሩካቤ፣ ወይም ስለሚያውቃት ሴት በዝሙት ሕሊና እንዲያስብ ያደርገዋል። ጓደኞቹ የተናገሩትን ነገር ወይም በመጽሔት ያነበበውን ወይም በተለያየ መንገድ ሲወራ የሰማውን “ይህ ምን ያረክሳል?” እያለ በሕሊናው እንዲያመላልሰው ያደርገዋል።

እንደዚህ በሚኾንበት ጊዜ በየትኛውም ቀን ቢሰግድ ፆሩ ይመለስለታል። አንድ ወንድሜ እንደ ነገረኝ፡ እንደዚህ ያለ ፆር ሲመጣበት በሩካቤ አካሉ አከባቢ ካለው ፀጕር የተወሰነውን ይነጫል። በጣም ያማል። በዚያ ሰዓትም ከፆሩ ይልቅ ሕመሙ ስለሚበልጥ ፆሩን ከማሰብ ይመለሳል። ሕሊናው አድርገኝ አድርገኝ ብሎ እንዳይገፋፋው፣ ነጉዶ የመጣውን ፆሩን በተግባር ለመፈጸም ሰይጣንን እንዳይታዘዘው ያደርገዋል። እንደ ነደ እሳት የሚያቃጥለውን የፍትወትን ፆር እንዳያስነሣበት ይከልለዋል።

የሐልዮ ኃጢኣት በተነሣ ጊዜ "ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ” እንደ ተባለው፥ ለዚህ ከሚዳርጉን ነገሮች (ቦታ፣ ኹኔታ) መራቅ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። “ይህ አሳብ የእኔ አይደለም” ብሎ ለመሸሽም የሐልዮ ኃጢአት የምታመጣውን መከራ የሚነግረን መምህር ወይም አበ ነፍስ ማግኘት እጅግ አስፈላጊ ነው (2ኛ ጢሞ.2፥22)። መካሪ መምህር ሳናገኝ ቀርተን ካዋልናትና ካሳደርናት ለሰይጣነ ፍትወት እጅ እንደ መስጠትና ወድቀን ወደ ቀጣዩ ደረጃ ወደ ገቢር ልናልፍ እንችላለንና። ከክፉ አሳብ መራቁ ብቻውን በቂ አይደለም። ክቡር ዳዊት “ከክፉ ሽሽ” ካለ በኋላ በዚያ ሳያቆም ጨምሮ “መልካምንም አድርግ" ይላልና (መዝ.33፥14)። እርስ በእርሳቸው የተያያዙ ናቸው። ስለዚህ አንዲት ሴት ጥሩ ልብሷን ተሸላልማ ተጊያጊጣ እየተኩነሰነሰች ስትሔድ አይቶ ፈላስፋው ዲዮጋንስ ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች "ከዚች ክፉ ወጥመድ ሽሹ" እንዳላቸው ሸሽቶ ወደ በጎ ሥራ ፊትን ማዞር ይገባል። ከወደቁ በኋላ ከመጠበብ ሳይወድቁ መጠንቀቅ ይሻላልና።

በሌላ መልኩ ደግሞ ተፈጥሮ ስለኾነ እነዚያ ስሜቶች ለምን መጡ ማለት አይቻልም። ስሜቶቹን ግን መቀደስ ስለሚቻል ከክፉ ሸሽቶ መልካም በማድረግ መቀደስ ይቻላል። አንድ ፈረስን የሚጋልብ ሰው፥ ፈረሱ ወደ ገደል ቢያመራ ጋላቢው የሚያደርገው ልጓሙን ማጥበቅ ብቻ አይደለም፤ ፈረሱ በትክክለኛው መንገድ እንዲሔድም ይመራዋል እንጂ። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ስሜቶች ሲመጡብን ከመራቅ ባሻገር ወዲያው መንፈሳዊ ተግባር ማከናወንም አስፈላጊ ነው። ጸሎት ሊኾን ይችላል፤ ስግደት ሊኾን ይችላል፤ መጽሐፍ ማንበብ ሊኾን ይችላል፣ መንፈሳዊ አባት ጋር መደወል ሊኾን ይችላል።

ከበረኻ አባቶች ከተሰጡት ምክሮች አንዱ እንዲህ የሚል ነው፦“ሌላ እኁም ከሰይጣነ ዝሙት ጋር ይጋደል ነበር። በሌሊት ተነሥቶም ከአረጋውያኑ ወደ አንዱ መጥቶ ስለ ሕሊናው ነገረው። አረጋዊውም ይታገሥ ዘንድ መከረው። በዚህ መንገድ እገዛ አግኝቶም ወደ በዓቱ ተመለሰ። ለኹለተኛ ጊዜም ወደ አረጋዊው መጥቶም እርዳታ አግኝቶ ወደ በዓቱ ተመለሰ። ውጊያው ለሦስተኛ ጊዜ ሲመጣበትም እንደገና  በሌሊት ወደዚያ አረጋዊ ሔደ። አረጋዊውም ወጣቱን አላሳዘነውም፤ እንደሚጠቅመው መክሮ ዘክሮ ነገረው እንጂ፤ እንዲህ ሲል፡- ምንም ዕድል እንዳትሰጠው። ሰይጣነ ዝሙት በፈተነህ በማናቸውም ሰዓት ወደ እኔ ና። ከዚያም ታጋልጠዋለህ። ስታጋልጠው ሸሽቶ ይሔዳል። ሰይጣነ ዝሙት እነዚህን አሳቦች የሚደብቃቸውንና የማይገልጣቸውን ሰው ያህል የሚፈትነው የለምና።" ያ እኁም በዚያች ሌሊት እርዳታ ፈልጎ ዓሥራ አንድ ጊዜ ወደ አረጋዊው እየተመላለሰ አሳቦቹን ተቃወማቸው። አረጋዊውም ሰይጣነ ዝሙቱ ከእርሱ እንደ ራቀ ነገረው። ነገር ግን ወደ በዓቱ በተመለሰ ጊዜ ውጊያው እንደ ገና መጣበት። ከብዙ ጊዜ ምልልስ በኋላም ያ እኁ አረጋዊውን:- አባ! ቸርነትህ ይደረግልኝ፡ እንዴት አድርጌ መኖር እንዳለብኝ ምከረኝ አለው። አረጋዊውም፡- ልጄ ፥ በርታ! እግዚአብሔር ፈቃዱ ከኾነ የእኔ ሕሊና ወደ አንተ ይመጣል። ከዚያም በኋላ ንጹሕ ሕሊና ይዘህ ትሔዳለህ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ አትፈተንም' አለው። ይህን ብሎ ሲጨርስም እግዚአብሔር ሰይጣነ ዝሙቱን እስከ ወዲያኛው ከዚያ እኁ አራቀለት።”

ስለዚህ ሰይጣነ ዝሙት መጥቶ ሲያሳስበን ወይም በሌላ መንገድ ያየነውንና የሰማነውን በሕሊናችን እንድናመላልሰው በሚፈልግበት ጊዜ ምንም ሳንሰለችና ዕድል ሳንሰጥ ወደ አበ ነፍሳችን መሮጥ እንዳለብን ያስረዳል። አበ ነፍሶችም በትዕግሥት ልጆቻቸውን የመርዳት መንፈሳዊ ግዴታ አለባቸው። ወላጆቻችንም ሊያግዙን ይችላሉ።

የሐልዮ ኃጢአት በእኛ ላይ እንዲነግሥ ከሚያደርጉ ነገሮች ኣንዱ ለብቻና ሥራ ፈት መኾን ነው። ሥራ ፈትተን ለብቻችን ስንኾን ሰይጣን መጥቶ ያንን ኃጢአት በደንብ እንድናስብበት፣ ተግብረው ተግበረው ይለናል። ልክ ለሔዋን በለስን የምታስጎመጅ አድርጎ እንዳሳያት፥ በእኛም የማስተዋል ሕሊናችንን አጣምሞ ከዚያ ኃጢአት ስለምናገኘው ደስታ ያሳስበናል። “ሥራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀድዶ ይሰፋል” የተባለው መነኰሴ ሥራ ላለመፍታትና ከሓልዮ ኃጢኣት ለመራቅ ሲል ይህን ስለሚያደርግ ነው። ስለዚህ ዝም ብለን መቀመጥ አይገባንም። ይልቅስ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በመሳተፍ፣ ሌሎች በጎ ሥራዎችንም በመሥራት እንጠመድ።

በዚህ ከተጎዱት ሰዎች መካከል አንዱ ነቢዩ ዳዊት ነው። ነቢዩ ዳዊት ወጣት ኾኖ በጎችን በሚጠብቅበት፣ ለሳኦል ጋሻ ጃግሬው ኾኖ በገና እየደረደረ በሚያገለግልበት፣ ሳኦል በምቀኝነት ተነሥቶበት በሚያሳድደው፣ ወደ ንግሥናው መጥቶ መንግሥቱ እስከ ተደላደለ ጊዜ ድረስ በዝሙት አልወደቀም ነበር። መንግሥቱ ተደላድሎ ከተመሠረተ፣ ክብሩ ከጨመረ በኋላ ግን ሥራ ፈትቶ በሰገነት ላይ ሲመላለስ የኦሪዮን ሚስት ቤርሳቤህን ስትታጠብ ተመለከታት። ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ፡- “ሰውነት ሥራ ሲፈታ፥ ሕሊናም ሥራ ይፈታል” እንዳለው፥ ንጉሥ ዳዊት ሥራ ፈትቶ ስለ ነበረም በቀላሉ በነቅዓ ሐልዮ ሳያበቃ ስለ እርሷ በማሰብ ወደ ሐልዮ ኃጢኣት ገባ። ስለዚህም “መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፣ ወደ እርሱም ገባች፥ ከርኩሰትዋም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ" (2ኛ ሳሙ.11፥4)።

በመኾኑም ራሳችንን ሰይጣን ወደ ሕሊናችን የሚያስገባውን የሐልዮ ኃጢአትን ከላይ በጠቀስናቸው መንገዶች በማራቅ፥ ንጽሕናችንን ጠብቀን ከሴት ከወንድ ርቀን እስከ ጋብቻ ድረስ መጽናት ይኖርብናል።

አንዳንድ ጊዜ በሕልማችን ሩካቤ ስንፈጽም ልናይ እንችላለን። በዚህ ጊዜ እኛ ራሳችን ቀን ላይ ያሰብነው አሳብ አለመኾኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በቀን ያሰብነው ሌሊት ቀጥሎ ከኾነ ከአበ ነፍስ ጋር ተነጋግሮ አሳቡን ማራቅ፣ ከዚያ ውጭ ግን ወጣቶች በመኾናችንና “ፒቱታሪ” የተባለው ዕጢ የዘር ፈሳሽ ማመንጨቱና አንዳንድ ጊዜ በራሱ ተስፈንጥሮ ስለሚወጣ በዚህ መነሻነት ወደ ሌላ ኣሳብ እንዳንሔድ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

(ገብረ እግዚአብሔር ኪደ  ከተጻፈው #ትንሿ_ቤተክርስቲያን መጽሐፍ - ገጽ 161-163)

We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ

Last updated 3 weeks, 2 days ago

Last updated 2 weeks, 4 days ago

ለማንኛውም አስተያየት እና ጥቆማ 👉 @Esat_tv_comment_bot

🇪🇹ኢሳት የኢትዮጵያ አይን እና ጆሮ🇪🇹

Last updated 1 month ago