Dive into the Ultimate Free Library: Your One-Stop Hub for Entertainment!

ቶኔቶር ሀገረ እግዚአብሔር

Description
ኢትዮጵያ በጥንት ግብጻውያን ቋንቋ ቶኔቶር፣ጵንጥ፣የኩሽ ሀገረ እየተባለች ትጠራለች።ቶኔቶር ሀገረ እግዚአብሔር ማለት ነው።በሌሎች ሀገሮች ስነ ጽሑፍ ኢትዮጵያና አቢሲኒያ በማለት ተገልጻለች።በቻናሉ መንፈሳዊ ትምህርቶች ወደ እናንተ ይደርሳሉ። እግዚአብሔር አምላካችን ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያን ከነጣቂው ተኩላ ይጠብቅልን።ድንግል ሆይ የአስራት ሀገርሽን ኢትዮጵያን ጠብቂያት።
ለመረጃ ያግኙን 👉 @tonetore
Advertising
We recommend to visit

"ይህ የቴሌግራም ቻናሌ ግንቦት1/2011ዓም የተከፈተ ነው። የእኔን የስልክ ወጪ ጨምሮ አገልግሎቴን መደገፍ የምትፈቅዱ ጓደኞቼ በ
👉🏿 https://donorbox.org/zemedemedia እና
👉🏿 https://www.paypal.com/paypalme/ZemedkunB በኩል ማገዝ ትችላላችሁ። በተረፈ ለቤተ ክርስቲያኔና ለኢትዮጵያ ሀገሬ የሚጠቅመውን ሁሉ አበረክት ዘንድ አብዝታችሁ ጸልዩልኝ።

Last updated 1 month, 3 weeks ago

The first Telecom operator in Africa https://t.me/EthiotelecomChatBot

Last updated 1 day, 15 hours ago

እንኳን ወደ ውዱ 4-3-3 Film ቻናላችን በሰላም መጣቹ

አዳዲስ እና የድሮ እንግሊዘኛ/አማርኛ/ህንድ/ቱርክ ፊልሞችን እና ከ1000 በላይ ተከታታይ ፊልሞችን የምታገኙበት ቻናል ነው

ለማስታወቂያ ስራ - @Abusheymc

ሃሳብ አስታየት ካሎት - @Abushecbot

Buy ads: https://telega.io/c/Films_433

Last updated 1 month, 2 weeks ago

2 months ago
ቶኔቶር ሀገረ እግዚአብሔር
2 months ago

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

የተወደዳችሁ እና የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች!

በእግዚአብሔር ፍጹም ሰላም እንደምን ሰነበታችሁ?

እኔ በቅዱሳኑ ጸሎት እና ቅድስና የባሕርይ ገንዘቡ በሆነው በእግዚአብሔር ቸርነት ይኸው ዛሬን ደርሻለሁ።

ዛሬ መድረስ ከሱቅ የሚገዛ የሸቀጥ ዕቃ አይደለም።

ዛሬ መድረስ ከመንግሥት መሥሪያ ቤት በስጦታ መጠቅለያ ላስቲክ ታሽጎ የሚሰጥ የስጦታ ዕቃም አይደለም።

ዛሬ መድረስ ከቤተሰብ በውርስ የሚገኝ የውርስ ገንዘብም አይደለም።

ዛሬ መድረስ ከእግዚአብሔር ብቻ የምናገኘው ልዩ ስጦታ ነው።

ስለዚህ አይታለፉም በተባሉ በሞት በተከበቡ ዘመናት ውስጥ አልፈን በሕይወት ዛሬ የመድረሳችን ምሥጢር የእግዚአብሔር የቸርነቱ ምልክት ማሳያ ነው።

በአባታዊ ፍቅሩ እየወደደን፤
በቸርነቱ ብዛት እየጠብቀን ዛሬን ያደረሰን እግዚአብሔር ምስጋና ለስሙ ይሁን!

አሜን!!!

እንግዲህ ይህንን ያህል በእግዚአብሔር በቸርነቱ ብዛት ተጠብቀን ዛሬ ከደረስን ዛሬ ያደረሰንን እግዚአብሔርን እያመሰገንን ለነገው ሕይወታችን ስንቅ የሚሆነውን የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቃል ደግሞ አሁን ለጥቂት ደቂቃ በጋራ እንማማራለን።

የትምህርታችን ርዕስ፦
“ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናል።”
የሚል ነው።
1ተሰ.4፥7

እንደሚታወቀው የዐቢይ ጾም ፪ተኛው ሳምንት "ቅድስት" ይባላል።

የስሙ ስያሜ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ከሆነው ከቅዱስ ያሬድ የተገኘ ነው።

በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን
በሥርዓተ አምልኮዋ፤
በሥርዓተ ቅዳሴዋ፤
በመዝሙሯና
በስብከቷ ሁሉ ስለ ቅድስና በሰፊው ታስተምራለች።

በቅዳሴ ላይ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፦
፩ኛ=በገባሬ ሠናይ ዲያቆን 1ተሰ.4፥1-13
፪ኛ=በንፍቅ ዲያቆን 1ጴጥ.1፥13-ፍ.ም.
፫ኛ=በንፍቅ ካህን
ሐዋ.10፥7-30

ምስባክ፦
"እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ
አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ
ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ።"
የሚል ሲሆን ትርጉሙም፦
"እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።
ምስጋናና ውበት በፊቱ፥
ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው።"
ማለት ነው።
መዝ..95(96)፥5

በምሥጢራዊ ትርጉም ሲፈታ ደግሞ፦
"እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ"
እግዚአብሔር ምን ሠራ ትለኝ እንደ ሆነ እግዚአብሔርስ እርሱ እግዚአብሔር ስለሆነ ሰባቱን ሰማያት ሠራ።

"አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ"
እምነትና መልካም ምግባር ያለውን ሰው ይወድዳል።

"ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ"
ቅዱስ ቅዱስ ተብሎ መመስገንም የባሕሪይ ገንዘቡ ነው።
የሚል ትርጉም አለው።

በዚህ እለት የሚነበበው የወንጌል ክፍልም
ማቴ.6፥16-25 ሲሆን፦

በዛሬው እለት የሚቀደሰው ቅዳሴ ደግሞ ካሉት 14 ቅዳሴያት መካከል "ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ" ነው።

አሁን መጀመሪያ ወደ አነሣነው ርዕሰ ጉዳይ ስንመለስ፤

የትምህርታችን ርዕስ፦
“ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናል።”
የሚል ነው።
1ተሰ.4፥7

እዚህ ላይ ስለ ቅድስና ስናነሣ፤
"ቅድስና" የእግዚአብሔር የባሕሪይ ገንዘቡ ነው።
"አንተ ብቻ ቅዱስ ነህ" ተብሎ የሚዘመርለት እንደ እርሱ ያለ ቅዱስ የትም የለምና።
ራእ.15፥3-4

“አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው?
በምስጋና የተፈራህ፥
ድንቅንም የምታደርግ፥
በቅድስና የከበረ እንዳንተ ያለ ማን ነው?” ተብሎ እንደ ተጻፈ።
ዘጸ.15፥11

የቅዱሳኑ "ቅድስና" ከእግዚአብሔር በስጦታ ይሰጣቸዋል።

እግዚአብሔር ግን በባሕሪዩ ለዘላለም ቅዱስ ነው።

በመሆኑም ሰማያውያን መላእክት፦
“ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤
ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች"
እያሉ ያለማቋረጥ ቀን እና ሌሊት ያመሰግኑታል።
ኢሳ.6፥3

ስለዚህ፦
“እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ።”
ኢሳ.40፥25

እንግዲያውስ ኑ!
እኛም ከቅድስት ሐና ጋር፦
እንደ እግዚአብሔር ያለ ቅዱስ የለም፥
እንደ አምላካችንም ያለ ጻድቅ የለም፤
እያልን እንዘምርለት!
1ሳሙ.2፥2

ስለ እግዚአብሔር የባሕሪይ ቅድስና ከመጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን መመልከት እንችላለን።
ኢሳ.57፥15
ሕዝ.36፥20-21
ሉቃ.1፥50
ኢሳ.6፥3
ራእ.4፥8

እንግዲህ ይህ በባሕሪዩ ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር፦

"እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና፤ ሰውነታችሁን ቀድሱ፥
ቅዱሳንም ሁኑ፥
እኔ ቅዱስ ነኝና፤
በምድርም ላይ በሚሳብ ተንቀሳቃሽ ሁሉ ሰውነታችሁን አታርክሱ።
እኔ አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንግዲህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ!" ይለናል።
ዘሌ.11፥44-45

እርሱ አባታችን ነው፤
እኛም ልጆቹ ነን፤
ስለዚህ ልጆች በአባታቸው ሊወጡ ስለሚገባ አባታችን እግዚአብሔር እርሱ በባሕሪዩ ቅዱስ እንደ ሆነ እኛም ደግሞ በኑሮአችን ቅዱሳን ልንሆን ይገባል።

ምክንያቱም መጠራታችንም በቅድስና ለቅድስና ነው እና።
1ተሰ.4፥7

ስለዚህ በቅድስና መኖር ያልቻለ ሰው ከተጠራለት ዓላማ ውጪ ሆኖአል ማለት ነው።

በቅድስና መኖር ሲባል ግን ምን ማለት ነው???

እንደ ዘካርያስና እንደ ኤልሣቤጥ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝና ሕግጋት
እየፈጸሙ በእግዚአብሔር ፊት ጽድቅን ጠብቆ መኖር።
ሉቃ.1፥6

በተረገመ ትውልድ ውስጥ እንኳ እንደ ኖኅ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆኖ መገኘት።
ዘፍ.7፥1

ከአፍ ወደ ውጭ የሚወጣው ክፉ ንግግር ሰውን ያረክሳልና ክፉ ከመናገር መቆጠብ።
ማቴ.15፥18
ኤፌ.4፥29
1ሳሙ.2፥3

ከሕሊና ውስጥ ክፉ አሳብን ማስወገድ።

በልብ ውስጥም ቂምን አለመቋጠር።

በጠቅላላው በቅድስና መኖር ማለት የራስን ምኞት ትቶ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብና ፈቃድ መኖር ማለት ነው።

ርኩሰት ግን የሥጋ ሥራ ነው።
እርሱም፦
👉ዝሙት፥
👉ርኵሰት፥
👉መዳራት፥
👉ጣዖትን ማምለክ፥
👉ምዋርት፥
👉ጥል፥
👉ክርክር፥
👉ቅንዓት፥
👉ቁጣ፥
👉አድመኛነት፥
👉መለያየት፥
👉መናፍቅነት፥
👉ምቀኝነት፥
👉መግደል፥
👉ስካር፥
👉ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። እንደዚህ ያሉትን የርኩሰት ሥራ የሚሠሩ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም ተበሎ በግልጥ ተጽፎልናል።
ገላትያ 5፥19-21

ኑ!
ቅዱስ እግዚአብሔር በቅድስና እንድንኖር ጠርቶናልና ሀጢአትን ሁሉ ትተን በቅድስና ጎዳና ላይ እንመላለስ!

ለቅድስና ተጠርታችሁ አትርከሱ!

ለዝማሬ ተጠርታችሁ ዘፋኞች አትሁኑ!

ለፍቅር ተጠርታችሁ በጥላቻ አትመላለሱ!

ለዕርቅ ተጠርታችሁ ቂመኞች አትሁኑ!

ለሕይወት ተጠርታችሁ ለሞት እጅ አትስጡ!

በብርሃ ተጠርታችሁ ወደ ጨለማ አትሂዱ!

ለክብር ተጠርታችሁ ለውርደት አትሁኑ!

ደግሞም ይህንን ምክር የሚጥል ሰውን የጣለ አይደለም፥
መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር የሰጠውን እግዚአብሔርን ነው እንጂ።
1ኛ ተሰ.4፥8

ስለዚህ "እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።”
1ጴጥ.1፥15-16
╭✥✥✥✥✥✥✥✥✥╮
✥┈┈••●◉✞◉●••┈••✥
. አባ ኒቆዲሞስ (ጳጳስ)
. 07/07/2016 ዓ.ም
. ከሕይወት ተራራ ላይ
✥┈┈••●◉✞◉●••┈┈✥
╰✥✥✥✥✥✥✥✥✥╯

2 months, 3 weeks ago
ቶኔቶር ሀገረ እግዚአብሔር
2 months, 3 weeks ago

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የጾመ ነነዌ መልዕክት
++++++++++++++++++++++++++++++++++
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
'ተንሥእ ወሑር ኅበ ነነዌ ሀገር ዐባይ - ተነሥተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ"
ዮና ፩;፪
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት፤
መንፈሳዊ ተልእኮ ተቀብላችሁ በየተሰጣችሁ ጸጋ በተለያየ ስፍራ ሆናችሁ የምታገለግለ‐ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤
በመንፈስ ቅዱስ ልደት የከበራችሁ ምእመናን ወምእመናት ልጆቻችን በሙሉ፤ ዘመንን በዘመን እየተካ፣ መዓቱን በምሕረት እየመለሰ የሚያኖረን እግዚአብሔር እንኳን ለ2016 ዓ.ም ጾመ ነነዌ አደረሰን አደረሳችሁ ለማለት እንወዳለን፡፡

በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩት የሰው ልጆች በኃጢአት በወደቁ ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ የሁሉ አባት በመሆኑ ተወልዶ ብልጫ የለም" እንዲሉ ከእስራኤል ውጭ ወዳለችው ነነዌ ነቢዩ ዮናስንና ነቢዩ ናሆምን ልኳል። በበደል ውስጥ ሆነው ቢጾሙም ሆነ ቢጸልዩ ጸሎቱ ድል የሚነሣ መሥዋዕቱም የሚያስምር አይሆንምና፡ ንስሐም ለድሀና አቅም ለሌለው የሚሰበክ ሳይሆን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያደፈ ሁሉ የሚጠራበት የሕይወት መስታወት ነውና የሕይወት ትንሣኤ በሆነው ንስሐ ነነዌን ለማንሣት ዮናስ ወደ ንጉሡና ወደ ሠራዊቱ የንስሐ ሰባኪ ሁኖ ተልኳል።

ነነዌ ከተማዋ አድጎ፡ ልማቷ ቢሰለጥንም እግዚአብሔር ግን የተመለከታት ፈርሳና ተበላሽታ ነበር፡፡ በፈረሰ ልብ የሚገነቡ ከተሞች የቀን ጉዳይ እንጂ ፍርስራሽ መሆናቸው አይቀሬ ስለሆነ ዛሬ ነነዌ ከታሪክ መዝገብ ላይ ብትሰፍርም በዓይን ግን የምትታይ አይደለችም። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የነነዌን ጾም ያወጀችው ዓመት ሙሉ የተጣላ በነዚህ ሦስት ቀናት እንዲታረቅ፣ ሲካሰስ የሚኖር ሕዝብም ወደፈጣሪው በንስሐ እንዲመለስ ነው።

እግዚአብሔር አምላክ ነቢዩን ወደ ነነዌ ሲልከው፡- “ተነሥተህ ሂድ" ማለቱ በበደል የሳተን በሩቅ ሆኖ መተቸት መንፈሳዊ ተልእኮ ባለመሆኑ ተነሥተን ብንሄድ፣ መንገድ አጋምሰን ወገኖቻችንን ብንፈልግ ሁሉንም ለንስሐ ማብቃት እንደምንችል ሲያስተምረን ነው፡፡ ለመነሣት ስንፍናንና ፍርሃትን ድል መንሣት ያስፈልጋል። ለይቅርታ ስንነሣ ትዕቢትን እናሸንፋለን። ፉክክርን እናርቃለን። ለጋራ ሀገራችን የጋራ መፍትሔ፡ ለጋራ ቤተ ክርስቲያናችን የጋራ መድኃኒትን እናገኛለን።

በሌላ በኩል አምላካችን እግዚአብሔር በደለኛይቱን ከተማ ታላቂቱ ከተማ በማለት ሲጠራት ሕዝቡንም ግራና ቀኙን የማያውቅ በማለት ራርቷል። እግዚአብሔር አምላክ አክባሪ፤ አዛኝ፡ በደለኛውንም በክብር እንጂ በውርደት የማይጠራ አምላክ ነው። እኛም ይህንን የነነዌን ጾም ስንጾም በአንድ በኩል እንጀራን የተራቡ፣ በሌላ በኩል ሰላም የተራቡ ወገኖች ስለአሉን ወደ እነዚህ ወገኖች የንስሐን ስብከት፣ የማጽናናትን መልእክት ይዘን መሄድ አለብን። በተጨማሪም ከቀዬአቸው የተፈናቀሉትን፡ በረሃብ፣ በመታረዝ፣ በጦርነት ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንን የመከራ ማቅ በሕሊናችን ተሸክመን ስለጸሙ የተውነው የዕለት ቊርሳችንን ለእነርሱ ሞትን ማባረሪያ እንዲሆን ልንፈቅድ ያስፈልጋል።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!

ይህንን የነነዌ ጾም ልንቀበል ዋዜማ ላይ ባለንበት በዚህ ጊዜ በቤተክርስቲያናችን ጥንታዊ ከሆኑት ገዳማት አንዱ በሆነው በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የሚገኙ፣ ዓለሙን ትተው በፈቃዳቸው ረሀብተኛ እና ጥማተኛ ሆነው ሀገርን በጸሎት የሚጠብቁ መነኮሳት ጫካው መኖሪያችሁ፣ ዳዋው ልብሳችሁ፤ ቅጠሉ ምግባችሁ መሆን አይችልም ተብለው የሰማዕትነትን ጽዋ ተጎንጭተዋል፡፡ እነርሱ በሥጋ እየሞቱ እኛም በየቀኑ ሟቾችን እየቆጠርን በኀዘን ለመኖር የተፈረደብን ሆነናል፡፡
ይህ ለእነርሱ ክብር ቢሆንም ለቤተክርስቲያን ግን ታላቅ ደወል ያሰማ ክስተት ነውና ውሉደ ክህነት ቤተክርስቲያናችሁን የምትጠብቁበት፣ የመከራውን ማዕበል ለማለፍ በመንፈሳዊ ፍቅር አንድነትን ማጽናት የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን እናሳስባለን፡፡

በመጨረሻም ታላቅ ሀገር ይዘን፣ ምድሩ ሳይጠበን አመል እያጋፋን ነውና ጸማችን፣ ጸሎታችን ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ለሀገር ደኅንነት፡ ለሕዝብ ድኅነት እንዲያመጣልን፡

እግዚአብሔር ይቅር ብሎን ዘመኑን በምሕረት ያሻግረን ዘንድ በታላቅ ንስሐ፣ በጸሎትና በአስተብቍዖት ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ አባታዊ መልእክታችንን በመሐሪው አምላክ ስም እናስተላልፋለን።

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ || ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! አሜን።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ
የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

2 months, 3 weeks ago

ሕንዳዊው ብፁዕ ዶ/ር ር ግ ሪርየስ የጻፉትን መሠረት አድርገው ብፁዕ ዖር ዘካርያስ ሰር ኤፍሬም እንዳት፤ መንበርን ከምድር እስከሰማይ ስቶርያት የሰጣቸው ጌታችን ነው - ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፡፡ እውነት እላችኃለሁ እናንተስ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ልትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ። ማቴ ፲፱፥፳፰ የሚገርማችሁ መንበርን ለሐዋርያት ሲሰጥ ለይሁዳም ሰጥቶት ነበር፤ ነገር ግን ይሁዳ ሥልጣኑን ስለናቃት፤ መጠራቱን ለምድራዊ ሥራና ቁሳዊ ፍላጎት ስለሸጠ፣ ጌታውን ክዶ ለሰዎች ፍላጎት ስለተንበረከከ መንበሩ ለሌላ ተሰጠች ብሏል፡፡ በርግጥም የይሁዳ ከሐዋርያዊ ጥሪው እና ከተሰጠው መንበር ተዋረደ ለሰማያዊ ሥልጣን ተጠርቶ ምድራዊ፤ ለመንፈሳዊ ክብር ተጠርቶ ቁሳዊ ስለሆነ በምትኩ ማትያስ ተመረጠ፡፡ እሱ ጎደለ እንጅ መንበረ ሐዋርያት አልጎደለም፡፡

ሐዋርያት ያስተማሩት ከጌታችን የተማሩትን ነው፤ የሐዋርያት ተከታዮች የሆኑ ጳጳሳት የሐዋርያትን ትምህርት ለመጠበቅ ሲሉ ሐዋርያት ባስተማሩባቸውና ሐዋርያት በመሠረቷቸው ቦታዎች መናብርትን መሠረቱ፤ መናብርቱ ግጭትና ጭቅጭቅ ለማስነሣት፣ በአንድ ቦታ ተወስኖ ለመቆየት የእኔ እኔ ለመባባል ወይም ልዩነት ለመፍጠር የተቋቋሙ ሳይሆን ትምህርተ ሐዋርያትን ለማስፋፋት እና ለመጠበቅ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ መናብርቱ የተመሠረቱበት ዋና ምክንያት ለክፍፍል እና ለልዩነት፣ ወይም ለምድራዊ ዓላማ ሳይሆን ማንም እየተነሣ የራሱ መሠረት እንዳይፈጥር፣ አስተዳደራዊ ማእከላትን ለመፍጠር፤ የሥልጣነ ክህነትን ደረጃ ለመወሰን፣ አገልግሎትን ለማሳለጥ፣ ለወንጌልና ለትምህርተ ሐዋርያት መስፋፋት ሲሆን መናብርቱን ለማቋቋም እንደመሥፈርት የተወሰደው የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መቅድመ ትምህርት፤ መሥዋዕትነት፣ ተልእኮና ሥምሪት እንጂ ዘርን፣ ጎሣን፣ ፖለቲካዊ አቋምን መሠረት ያደረገ አይደለም፡፡ መናብርት ለአብያት ክርስቲያናት አንድነት፡' የተበታተነውን አንድ ለማድረግ ሥልታዊ መዋቅር ለመዘርጋት፣ ለወንጌል መስፋፋት እና ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለትውፊት መጠበቅ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ
ነው፡፡

እዚህ ላይ በትልቅ አጽንዖት ማየት የሚያስፈልገው የመናብርቱ ምሥረታ ከፖለቲካ ወይም ከመንግሥት መዋቅር ጋር ግንኙነት አልነበረውም፤ ክርስትና እንኳንስ በሮም መንግሥታት መዋቅር ልታቋቍም ይቅርና እንዲያውም በሮማውያን የምትሳደድ ነረች፡፡ የቤተ ክርስቲያን መዋቅር የራስዋን ሐዋርያዊ ተልእኮ መሠረት ያደረገ፣ ሁሉንም የዓለም ሕዝብ በቋንቋው፣ በባህሉ ሳትከፍል በአንድነት ለማዳረስ የተፈጸመ ነው፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ መዋቅርን በተከተለችበት ጊዜ ሁሉ የገጠማት ችግር እና ስደት ነው።

፪) መንበር ያለ "ፓትርያርክ" እና ያለ "ሲኖዶስ"

#ይቀጥላል --->

2 months, 3 weeks ago

ቅዱስ አቡነ ሰላማ የማያውቁት "የሰላማ መንበር"

[በመ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል]

#ክፍል_1

፩) መግቢያ እና ትርጉም

የቤተ ክርስቲያን መንበር ሐዋርያዊ ነው። ሐዋርያዊ መንበር ጌታችን አስተምሮ ከሾማቸው ከዐሥራ ሥያሜ የወጣ አይደለም፣ ሥልጣነ ክህነት የሚተላለፍበት፣ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ትምህርተ ሃይማኖት እና ቀኖና ምንጩ ወይም ሥሩ የሚነገርበት የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን አማናዊና ሐዋርያዊ ታሪክ፣ ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ትውፊት የሚጀመርበት መነሻ ነው፡፡ መንበር ሥርወ ክህነት፣ ሥርወ ሃይማኖት፣ ሥርወ ቀኖና/ትውፊት ነው፡፡ በየትኛውም ዓለም ያሉ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት መንበራቸው ከሐዋርያት የሚወረስ ነው፡፡ የመንበራቸውም ሥያሜ በራሳቸው ያገኙት ወይም ራሳቸው እንደ ፈለጉት የለጠፉት ሳይሆን ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትን፣ ታሪክን እና ቀኖናን መሠረት ያደረገ የሌሎች ቤተሰብ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትን መስማማት የሚጠይቅ፣ ዓለማዊ የሆኑ የፖለቲካ፣ የጎሣ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል ሙያዎችን መሠረት ያላደረገ ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን ነቢዩ ሙሴ የሕገ ኦሪት መንበር ተሠይሞለታል! ስለዚህ ጌታችን (በማቴ.፳፫፥፪) “ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ መንበር ተቀምጠዋል” በማለት የኦሪት ሕግ መንበር የሙሴ መሆኑን ገልጧል፡፡ ምክንያቱም ነቢዩ ሙሴ የተጻፈ ሕግን የተቀበለ የመጀመሪያው ሰው ስለሆነ ነው፡፡ መምህራንም ሲናገሩ እስራኤል ኣብርሃምን በእምነት መሠረት፣ ሙሴን በሕግ መሠረት፣ አሮንን በሥርወ ክህነተ ኦሪት፣ ዳዊትን በሥርወ መንግሥት ይተረጕማል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ከነገሥታትም ከካህናትም ትወለዳለች ሲባል የእርስዋ እናትና አባት በዘመናቸው ንጉሥና ካህን ናቸው ለማለት ሳይሆን ከሥርወ መንግሥት ከዳዊትና ከሥርወ ክህነት ዘኦሪት ከአሮን ሐረገ ትውልድ ስለምትገኝ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመቅድመ ተአምረ ማርያም ላይ “ሥርወ ልደታ ለእግዝእትነ እምቤተ ዳዊት ንጉሥ መንገለ አቡሃ ወእም ቤተ አሮን ካህን መንገለ እማ” እንዲል፡፡

ክርስትና በራስዋ መሠረት ላይ የቆመች፣ የራስዋ ትውፊት ያላት በዓለማዊ ተለዋዋጭ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ አስተሳሰብ ክስተቶች የማትወሰን፤ በዓለማዊ ወጀብ የማትናወጥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ አንተ አለት ነህ በአንተ ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ” ባለው መሠረት በሐዋርያዊ አለት (ኰኩሕ) ላይ የቆመች በመሆኗ ሥርዋም፣ ግንዷም ቅርንጫፎቿም፣ ፍሬዎቿም የራስዋ ናቸው፡፡ (ማቴ.፲፮፥፲፱) በመሆኑም የሐዋርያት መሠረተ እምነትና የትምህርት ሥምሪት የዓለምን መንገድ የተከተለ ሳይሆን የራስዋን ትውፊት፣ ዘዴና ሥልት የተከተለ ነው፡፡

ሥርወ ትውፊት ዘሐዋርያት የሆነው “ሐዋርያዊ መንበር" በአንድ ሀገር/ሀገራት ውስጥ ያለ ቤተ ክርስቲያን የሥልጣነ ክህነቱ ምንጭ፤ የእምነቱን መሠረት የትውፊቱን ዋልታ የሚያስረዳበት ቀኖናዊ፣ ታሪካዊ መነሻ ነው፡፡ ስለዚህም ቀደምት ኢትዮጵያውያን ማርቆስ አባታችን ሲሉ ኖረዋል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ፡ የግብጽ፡ የሊቢያ፤ ... አብያተ ክርስቲያናት ሐዋርያዊ መንበራቸው ቅዱስ ማርቆስ ነው። ይህ በታሪክ፣ በቀኖና፣ በእምነትና በመላው ዓለም ባሉ ክርስቲያናዊ ትውፊቶች የተረጋገጠ ነው፡፡

ከሐዋርያት ያልተገኘ ሥርወ ክህነት የለም፤ ስለዚህ ሁሉም የሚጠሩት በሐዋርያት ስም ነው፡፡ የሮም መንበር የቅዱስ ጴጥሮስ፤ የኤፌሶን የቅዱስ ዮሐንስ፤ የአንጾኪያ የቅዱስ ጴጥሮስ ቀዳሚ መንበር፣ የእስክንድርያ የቅዱስ ማርቆስ ነው፡፡ (ፍትሕ መንፈሳዊ ፵፩)፤ የኢየሩሳሌም የቅዱስ ያዕቆብ፣ የአርመን የያዕቆብ፤ የታዴዎስና በርተሎሜዎስ፤ የሕንድ የቶማስ፤ እያለ ይቀጥላል፡፡ ይህ ትክክለኛ ታሪክ ሲሆን በቀኖናም የታወቀ ነው፡ ፡ ቅዱስ ጳውሎስ የሮምን፣ የገላትያን፤ የተሰሎንቄን... አብያተ ክርሰቲያናት መሥርቷል፤ ወይም አጽናንቷል፣ ግን በስሙ አልተጠሩም ምክንያቱም ቅዱስ ጳውሎስ ከጌታችን ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ቁጥር አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ቅዱስ ጳውሎስ በስብከቱ በደብዳቤዎቹና በኋላም የአሕዛብና የአይሁድ ሊቃናትን ወደ ክርስትና በመመለሱ በእሱ ምክንያት የተመሠረቱት አብያተ ክርስቲያናት መሥራቻችን ቅዱስ ጳውሎስ ነው! የሐዋርያዊ ትውፊትና የመንበር ሥያሜ ግን በ፲፪ቱ ሐዋርያት ነው ይላሉ፤ ለዚህም እንደ ምሳሌ የግሪክ እና የቁስጥንጥንያ አብያተ ክርስቲያናትን ማየት ይቻላል።

አቴናን የሰበከው ቅዱስ ጳውሎስ ነው (የሐዋ ፲፯)፣ በቀዳሚ ስብከቱ የምኩራብ አለቃና የሽንጎውን ዋና ዳኛ ዲዮናስዎስን አሳምኗል፣ እጅግ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ፈላስፋ፣ ዳኛ፣ እና የአርዮስ ፋጎስ መሪ የነበረው ዲዮናስዮስ እና ሀብታም የነበረችው ዲማሪስም ተጠመቁ፣ ዲዮናስዮስ የመጀመሪያው የአቴና ጳጳስ ሆነ፣ የአቴና መንበር ግን በዲዮናስዮስም ሆነ በሰባኪው ቅዱስ ጳውሎስ አልተጠራም፡፡ የአቴና መንበር ሐዋርያዊ መጠሪያ ቅዱስ እንድርያስ ነው።

ሁለተኛም የቊስጥንጥንያ ግዛት በነበሩት ተሰሎንቄ፤ ገላትያ መቄዶንያ፤ ኤፌሶን፤ ቆሮንቶስ በሙሉ ያስተማረው ስሙን በአሕዛብ ዘንድ የሚሸከም ንዋይ ኅሩይ የተባለ ቅዱስ ጳውሎስ ነው። መንበሩ የሚጠራው ግን በቅዱስ እንድርያስ ነው፡፡ ምክንያቱም ከቅዱስ ጳውሎስ በፊት ሐዋርያው ስላስተማረና ሐዋርያት ቀዳሚ ስለነበሩ ነው፡፡ ሐዋርያት ቀደምት ሌሎቹ ደኃርት ናቸው፤ ከቅዱስ ጳውሎስ በፊት ሐዋርያት ስላሉ የሐዋርያዊ መንበር ምንጭ ወይም ሥር ሊሆን አልቻለም! መንበር ምንጭ ነው፡፡ መንበር ሥር ነው! የትውፊትና የኦርቶዶክሳዊ ሐረገ ትውልድ መነሻና ጥንተ መሠረት ነው፡፡

መንበር በሰው ፍላጎት የሚሠየም ቢሆን ኖሮ አርመኖች ልክ እንደ አቡነ ሰላማ በ፫፻፩ ዓ/ም የአርመን ኦርቶዶክስን የመንግሥት ሃይማኖት ያደረጋት እና የመጀመሪያው የአርመን ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ከሣቴ ብርሃን ስም በሰየሙት ነበር፡፡ ኮፕቲኮች ዘመን አቆጣጠርን በቀየሩበት (ሐሳበ ሰማዕታትን) በተፍጻሚተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ወይም በታላላቆቹ ዓለም አቀፍ ቅዱሳን በቅ/አትናቴዎስ፣ ወይም በቅ/ቄርሎስ፣.. በሰየሙት ነበር፡፡ በሂደትም ሐዋርያዊ መንበር (Apostolic Throne) የሚለው ሥያሜ በፓትርያርክ ደረጃ የሚመራ መንበሩ ከጥንታውያን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንዱ በሆነ ሐዋርያ ወይም ወንጌላዊ የተሠየመ ማለት ሆነ፡፡

በታሪክ የታወቁት መንበረ ፓትርያርክ ሁሉም ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ወይም ከወንጌላውያን በአንዱ ብቻ ተጠርተዋል፡፡ ስለ መንበረ ሐዋርያት ጥንታዊ ትርጉምና ትውፊት ከታሪክ ጸሐፊዎች ውስጥ ተርቱለስ (ተርቱሊያን) በ፪ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲናገር “መንበረ ሐዋርያት ከሐዋርያት ጀምሮ የተከበሩ ናቸው፣ እነሱም ሐዋርያት (የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት) የመሠረቷቸው ሲሆኑ ሥልጣነ ክህነትን፣ እምነትን እና የዶግማ ትምህርትን አንዳቸው ከአንዳቸው በመውረስ የቆዩ ናቸው፡፡” (የተርቱለስ፡ መናፍቃንን ስለመቃወም የጻፈው መጽሐፍ፡ ሦስተኛ ምዕራፍ)

የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዝሙር ቅዱስ ሄሬንዮስ በዚሁ በ፪ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተናገረው “የሐዋርያት መንበር የሐዋርያት ትውፊት ምንጭ ነው፤ ሥር ነው፣ የሃይማኖት ቅብብል ማሳያ ነው፤ ንጹሕ የሆነ የክርስትናን ትምህርት በሚገባ ለማወቅ የሚፈልግ በእነዚህ መናብርት የተጠበቀውን ትውፊት ማወቅ ይበቃል በማለት መናብርቱ የሐዋርያትን ትምህርት እና ትውፊት ለመጠበቅ የተመሠረቱ መሆናቸውን ገልጧል፡ (የሄሬንዮስ መናፍቃንን ስለመቃወም የጻፈው መጽሐፍ፡ ምዕራፍ ሦስትና አራት)

5 months ago

“ሰላም ለበርባራ ወዮልያና በፍኖተ ስምዕ እለ ቆማ፤
በድሮን እለ ፈጸማ
እለ ተጋደላ ከመ ሐራ
አርዑተ መስቀሉ ለክርስቶስ እለ ጾራ
መርዓዊሆን እስከ ረከባ
ድንግልናሆን እለ ዓቀባ”፡፡
(ሙሽራቸው ክርስቶስን እስኪያገኙ ድረስ ድንግልናቸውን የጠበቁ፤ የክርስቶስ መከራ መስቀሉን የተሸከሙ፤ እንደ ጭፍሮች የተጋደሉ፤ ሩጫቸውንም የፈጸሙ፤ በምስክርነት ጐዳና የቆሙ ለኾኑ ለበርባራና ለዮልያና ሰላምታ ይገባል) በማለት አወድሷቸዋል፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ አርከ ሥሉስም ይኽነን በዐርኬው ላይ፡-
“ሰላም ለበርባራ እንተ አግሀደት ሃይማኖታ
እንዘ ታርኢ ሥላሴ በመስኮተ ቤታ
ኢያፍርሃ መጥባሕት ወሞሠርተ ሐጺን ኢያሕመመታ
ወሰላም ካዕበ ለዮልያና ካልዕታ
እንተ ሰቀልዋ በክልኤ አጥባታ”

(በቤቷ መስኮት የሥላሴን ምሳሌ እያሳየች ሃይማኖቷን የገለጠች ለኾነች ለበርባራ ሰላምታ ይገባል፤ ሰይፍም አላስፈራትም የብረት መጋዝም አላሳመመቻትም፤ ዳግመኛም በኹለት ጡቶቿ የሰቀሏት የርሷ ኹለተኛ ለምትኾን ለዮልያናም ሰላምታ ይገባል) በማለት የተቀበሉትን ጽኑ መከራ ጽፏል፡፡

ቅድስት በርበራ እመቤታችንን ለምና የገድሏን መጽሐፍ በሰረቁት ላይ ያደረገችውን የመስከረም 25 ተአምሯን ደግሞ፦
"ሰላም ለበርባራ ወለዮልያና አምሳላ
በዛቲ ዕለት ዘአስተርአየት ኀይላ
በክልኤ ዕደው ዘሰረቁ መጽሐፈ ገድላ
ፈደየቶ ለአሐዱ እንባዜ እምኀበ ማርያም ስኢላ
ወለዐይነ ቢጹ ካልዕ አጽለመት ጸዳላ"

(የገድሏን መጽሐፍ በሰረቁ በሁለት ወንዶች ላይ በዚህ ዕለት ኃይሏን ያሳየች ለሆነች ለበርባራና ርሷን በተጋድሎ ለምትመስል ለዮልያና ሰላምታ ይገባል። ከእመቤታችን ማርያም ለምና ለአንዱ መቅበዝበዝ የሁለተኛው ጓደኛውን ዐይን ብርሃኑን አጨለመች) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የበርያሱስን ዐይን እንዳጨለመ ተመሳሳይ ተአምርን እንደሠራች ይጽፋል ኢትዮጵያዊው ሊቅ አርከ ሥሉስ በመስከረም 25 ስንክሳር አርኬ።

💥 ❖የቅድስት በርባራ ዐለም ዐቀፍ ክብሯ❖💥

በእጅጉ የሚገርመው ከጥንት ጀምሮ በየክፍላተ ዘመናቱ እስከ ዛሬ ድረስ በበርካታ የዓለም ክፍሎች በቅድስት በርባራ ከሚፈነዱ የጦር መሣሪያዎች፤ ከመብረቅ አደጋና ከድንገተኛ ሞት በቃል ኪዳኗ እንደምትጠብቅ ሲታመን፤ በጣሊያን የባሕር ኀይላችን ጠባቂ (the patron of the Italian Navy.) ይሏታል።

በቃል ኪዷና በእጅጉ ከመታመን የተነሣ በጊዜያችን ያሉ በርካቶች ኀያላን ሀገራት ብሪታኒያ (Royal Artillery, RAF Armoures, Royal Engineers) በካናዳ (Explosiv Ordance Technicaians) በአውስራሊያ (RNZAF Armourers) በኒውዝላንድ፤ በስፔን፣ በአሜሪካ፣ በግሪክ የቅድስት በርባራን በዓል በዐየር ኀይላቸው፣ በጦር ካምፓቸው፣ በባሕር ኀይላቸው ዲሴምበር 4 ላይ እንደሚያስቡ ጥናቶች በግልጽ ያሳያሉ::

በስፓኒሽና በጣሊያን ይታተም የነበረው መጽሔት መርከበኞች ከድንገተኛ አደጋ መርከባቸው ይጠበቅ ዘንድ ሥዕሏን ይይዙ እንደነበር ይጽፋል።

በሰሜን አሜሪካ የጦር ኃይልም ቅድስት በርባራ የምትታሰብ ሲሆን በጦር ኃይሉ ላይ ከፍተኛ ጀብዱ ለሠሩ ምርጥ ወታደሮች በቅድስት በርባራ ስም የተሠየመ የቅድስት በርባራ ሥዕል ያለበት ሜዳልያ (ANCIENT ORDER OF SAINT BARBARA) ይበረከትላቸዋል። (https://www.fieldartillery.org/awards)
💥 (United States Field Artillery Association, fieldartillery.org. retrieved 23 January 2010,) (Cyprus Army notes on Saint Barbara, Army)

በሰሜን አሜሪካ ከሎስ አንጀለስ ሰሜን ምዕራብ 100 ማይልስ በሚገመት አግጣጫ ያለችው በቅድስተ በርባራ ስም ሳንታ ባርባራ Santa Barbara በመካከለኛው ካሊፎርንያ ከተማ ተሠይሞላታል፤ በተመሳሳይ መልኩ በስፔንና ፖርቱጋል ቦታ ላይ በብራዚል፣ በቺሊ፣ በኮሎምቢያ፣ በሆንዱራስ፣ በሜክሲኮ፣ በቬንዝዌላ፣ በፊሊፒንስ በቅድስት በርባራ ስም የተሠየመ አለ። በሊባኖስ ክርስቲያኖችም በጣም ትታሰባለች (Hammond Atlas of the World.1997.)፡፡

ታላቁ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ ሊቁ አርከ ሥሉስ ያወደሷት፤ ክብሯ በስንክሳር ላይ የተጻፈላት በርካቶች ቃል ኪዳናትን የተቀበለች ቃል ኪዳኗም ከድንገተኛ ሞት የሚጠብቀው የቅድስት በርባራ ጥንታዊ ሥዕላት በብራና ላይ እንዳሉ ባውቅም በስሟ የተሰየመ ታቦት እንዳለ ግን ጥናቱ የለኝም።

💥 እኔ ከክብሯ በዐጭሩ በረከቷን ለመሳተፍ ያኽል እንደጻፍኩ እናንተም ታኅሣሥ 8 በስሟ ለነዳያን በመመጽወት በቃል ኪዳኗ በመማጸን በረከቷን ተሳተፉ። በአስተያየት መስጫው ላይም ውዳሴን አቅርቡላት።

ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
👉 @tonetore ይቀላቀሉ

5 months ago

[ታኅሣሥ 8 በዓሏ የሚከበረው ቃል ኪዳኗ ከድንገተኛ ሞት የሚጠብቀው የቅድስት በርባራ ድንቅ ታሪኳ፤ በቀደምት የኢትዮጵያውያ ሊቃውንት የቀረበላት ውዳሴና ዓለም ዐቀፍ ክብሯ]
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
የተቀበለችው ቃል ኪዳን ከድንገተኛ ሞት የሚጠብቀው በመላው ዓለም ከጥንት ጀምሮ የምትታወቀው ከ273-306 ዓ.ም የነበረችው ሰማዕቷ ቅድስት በርባራ Αγία Βαρβάρα, (Great Martyr Barbara) ከ305-311 ዓ.ም. በነገሠው በመክስምያኖስ (emperor Maximian) ዘመነ መንግሥት መስፍን የነበረው የዲዮስቆሮስ ልጅ ናት። እጅግ ውብ ስለነበረች ሰው እንዳያያት ጣዖት አምላኪ የነበረ አባቷ ለርሷም ለብቻዋ ሰገነት ያለው ማረፊያ ታላቅ ሕንፃ አሠርቶላት አንድ አረማዊ መምህር ብቻ ወደርሷ እንዲገባ አደረገ።

ያሠራላት ሰገነት ከፍ ያለ ስለነበር አበባዎችን ይልቁኑ በምሽት የሚያበሩትን ከዋክብት የምሽቱ አስደናቂ ግርማ እየተመለከተች መደነቅ ጀመረች። በዚህ ጊዜ እነዚህ የአባቷ አማልክት አስደናቂ ዓለማትን እንደማይፈጥሩ ተረዳች። በሕይወቷ የዓለማት ፈጣሪን ለማወቅና በድንግልና ሕይወት ለመኖር ወሰነች። ብዙ የጋብቻ ጥያቄን ውድቅ አደረገች። በዚህ ምክንያት አባቷ ውጪውን እንድትለምደው ከግቢ እንድትወጣ ፈቀደላት።

በዚህ ጊዜ ከክርስቲያን ሴቶች ጋር በመገናኘቷ ስለ ምስጢረ ሥላሴ፣ የአምላክ ሰው የመሆን ምስጢርን አስረዷት። እውነተኛውን የድኅነት መንገድ በመረዳቷ ከእስክንድር ወደ ሄሊዎፓሊስ መጥቶ በነበረ ካህን በድብቅ ተጠመቀች።

በዚያ ወቅት አባቷ በመታጠቢያ ክፍሏ ላይ ደግሞ ኹለት መስኮቶችና ቅንጡ የሆነ መታጠቢያ እንዲሠሩላት ዐናጺዎችን አዘዘ፤ ርሷ ግን የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት በማመኗና በመጠመቋ ምስጢረ ሥላሴን አስባ ሦስተኛ መስኮትን እንዲጨምሩ ዳግመኛም አዳኝ የኾውን የመስቀሉን ምልክት በውሃ መታጠቢያው ላይ እንዲሠሩ ሐናጺዎችን አዘዘቻቸው፡፡

አባቷም ወደዚኽ ሕንጻ በገባ ጊዜ ልጁ ያሠራችውን አይቶ ዐናጺዎችን ሲጠይቃቸው፤ ይኽነን እንዲሠሩ ያዘዘቻቸው ልጁ መኾኗን ነገሩትን ርሱም “ለምን እንደዚኽ አደረግሽ” ብሎ ጠየቃት፡፡ “ወትቤሎ አእምር ወለቡ ኦ አቡየ እስመ በሥሉስ ቅዱስ ይትፌጸም ኲሉ ግብር በእንተዝ አግበርኩ ሣልሲተ መስኮተ፤ ወዘንተኒ መስቀለ በአምሳለ ስቅለቱ ለመድኀኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ” ይላል ርሷም “አባቴ ሆይ አስተውል፤ ልዩ ሦስት በኾነ በሥላሴ ስም ሥራ ኹሉ ይፈጸማልና ስለዚኽ ሦስተኛ መስኮት አሠራኊ፤ ይኽም መስቀል ዓለሙ ኹሉ በርሱ በዳነበት በመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል አምሳል ነው አንተም አባቴ ሆይ ከስሕተትኽ ተመልሰኽ የፈጠረኽን አምላክ አምልከው” በማለት ተናገረችው፡፡

አባቷም ከርሷ ይኽነን በሰማ ጊዜ በንዴት ሰይፉን መዝዞ በኋላዋ ሮጠ፤ ያን ጊዜ ሸሽታ በዐለት ውስጥ ገብታ ለጊዜው ብትሸሸግም በኋላ ግን ወደ አባቷ ተመለሰች፤ ርሱም እንድትሠቃይ ለሌላ መኰንን አሳልፎ ሰጣት፤ ርሱም እየገረፈ በጊዜው አሉ በተባሉ በታላላቅ ሥቃይን ቢያሠቃያትም የባሕርይ አምላክ ክርስቶስን ግን አልካደችም፤ ከዚያም ብቻዋን ወደ ወህኒ ተጣለች፤ በዚያም ኾና “ጌታዬ አምላኬ ሆይ አትተወኝ” ብላ ጸለየች፤ በእኩለ ሌሊትም የእስር ቤቱን ደማቅ ብርሃን መላው፤ “ከአንቺ ጋር ነኝና አትፍሪ” የሚለውን የአምላክን ድምፅ ሰማች፤ ከዚያም ጌታችን ቊስሎቿን ኹሉ ፈወሰላት፡፡

በነጋታው ቅድስት በርባራን በማርቲያኑስ ፊት አቆሟት፤ ኹሉም ሰዎች ሙሉ በሙሉ እንደዳነችና ፊቷም እንደ ፀሓይ ጨረር ሲያንጸባርቅ ተመለከቱ፤ መኰንኑም “አማልክቶቻችን ስለፈወሱሽ የምስጋና መሥዋዕትን ሠዊ” አላት፤ ቅድስት በርባራም ለአገረ ገዢው “በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው የዳንኩት” አለችው፡፡ ማርቲያኑስም በቊጣ ኾኖ በአስከፊ ኹኔታ ቅድስት በርባራ እንድትሠቃይ አዘዘ፤ በዙሩያዋ ቆመው ይመለከቱ የነበሩ ሕዝቦች ርሷን ለመከላከል ምንም ቃል አልወጣቸውም፡፡

በዚያም የሂሊኦፓሊስ ነዋሪ ዮልያና የምትባል ሴት ነበረችና ቅድስት በርባራን ሲያሰቃይዋት አይታ ከርሷ ጋር በክርስቶስ ስም መከራን ለመቀበል በመወሰን አብራት መከራ መቀበል ጀመረች። ሁለቱም ሰማዕታትን በምስማር ሰውነታቸውን እየወጉ ያሰቃይዋቸው ነበር። ለመዘባበት ዕርቃናቸውን በአደባባይ ሊወስዷቸው ቢሞክሩም በቅድስት በርባራ ጸሎት ጌታ መልአኩን ልኮ በአስደናቂ መጎናጸፊያ ሰውነታቸውን ጋርዶታል።

በመጨረሻም ጨካኙ መኰንን ብዙ ዐይነት ሥቃይ ቢደርስባቸው እነዚኽ ቅዱሳት አንስት በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት እንደማይለውጡ ባየ ጊዜ አንገታቸው እንዲቈረጥ አዘዘ።

ከወታደሮቹ መኻከል አንዱ አንገታቸው ለመቊረጥ ሰይፉን መዘዘ፤ በአባቷ ወደተዘጋጀው ወደመግደያው ስፍራ ይዟቸው ኼደ፤ ያን ጊዜ ቅድስት በርባራ እንዲኽ ብላ ጸለየች “ዘላለማዊ እግዚአብሔር ሆይ ከእኔ ሞት በኋላ እኔንና መከራዬን ለሚያስቡ ኹሉ ሥጦታኽን ስጣቸው፤ ድንገተኛ ሕመምና ብርቱ (አስጨናቂ) ሞትን በእነርሱ ላይ ፈጽሞ አታምጣባቸው” አለች፡፡

ከዚያም የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ መሻቷን ኹሉ እንደሚፈጽምላት ቃል ኪዳን ሲገባላት በሰጣት ቃል ኪዳን የሚታመኑ ኹሉ ድንገተኛ ሞት እንደማያገኛቸው ቃል ኪዳን ገባላት።

በመጨረሻም አባቷ የርሷንና የባልንጀራዋ የዮልያና አንገታቸው እንዲቈረጥ አዘዘና ታኅሣሥ 8, በ306 ዓ.ም. አንገታቸው ተቈርጦ የሰማዕትነት አክሊል ሲቀዳጁ፤ ቅድስት ዮልያናንም በኹለት ጡቶቿ በኩላብ ሰቅለው ሰይፈዋታል፡፡ በዚያን ጊዜ ከሰማይ መብረቅ ወርዶ አባቷንና ጓደኛው የኾነ መኰንን መርትያኖስን አቃጠላቸው፤ ከዚኽ የተነሣ በዓለም ባለው ሥዕሏ ላይ የመብረቅ ብልጭታ ይሣላል፡፡ ቅድስት በርባራም በዚህ ምክንያት በአማላጅነቷ ከጥንት ጀምሮ ባሉት ክርስቲያኖች ከመብረቅ አደጋና ከእሳት የምትጠብቅ እንደሆነች ይነገራል።

ያም በመታጠቢያ ቤት ውስጥ በመስቀል ምልክት ያሠራቸው መታጠቢያ ለታመመ ኹሉ ከርሱ በታጠበ ጊዜ የሚያድን ኾነ፤ ከዚኽም በኋላ የሰማዕታቱን ሥጋቸውን ወስደው ከከተማ ውጪ ባለች ቤተ ክርስቲያን ስሟ ገላልያ በሚባል ቦታ አኖሯቸው፤ ይኽ ሥጋቸውም በቅዱሳን ሰማዕታት በአቡቂርና በዮሐንስ በምስር አገር ባለ ቤተ ክርስቲያን ተቀመጠ፡፡

ይኽነን ተጋድሎዋን ለማዘከር በመላው ዓለም በሚሣለው ሥዕሏ ላይ ሦስት መስኮት ያለው ሰገነት፣ ዘንባባ፣ ጽዋ፣ መብረቅ፣ የሰማዕትነት አክሊል ይዛ ይታያል፡፡ በዐዲስ አበባ በምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ባሉት የግድግዳ ላይ ሥዕላት ላይ ቅድስት በርባራና ቅድስት ዮልያና ተሥለዋል። በዓለም ላይ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በስሟ የታነጹላት ሲኾን በሩሲያ ብዙዎች ቤተ ክርስቲያናት በስሟ ሲሠየሙላት አንደኛው በሞስኮ ከቅዱስ ባስልዮስ ካቴድራል አጠገብ ይገኛል::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ 8 በሚነበበው መዝገበ ቅዱሳን በሆነው ስንክሳር ላይ ቅድስት በርባራና ዮልያናን ታስባለች።

ቀደምት የኢትዮጵያ ሊቃውንት ቅድስት በርባራን አመስግነው በቃኝ አይሉም ነበር፤ ለምሳሌ ያኽል ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እና ቅዱስ አርከ ሥሉስ እንዴት እንዳመሰገኗት ብናይ፤ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በተአምሆ ቅዱሳን መጽሐፉ ላይ፡-

5 months, 4 weeks ago

ቅዱስ ሲኖዶስ ሀገራዊ ሰላምን፣ መረጋጋትንና አንድነትን ለማስፈን የታወጀውን የጾምና የጸሎተ ምሕላ አፈጻጸምን አስመልክቶ መግለጫ ሰጠ !

ኅዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም (ተ.ሚ.ማ /አዲስ አበባ)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሀገራዊ ሰላምን፣ መረጋጋትንና አንድነትን ለማስፈን የታወጀውን የጾምና የጸሎተ ምሕላ አፈጻጸምን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

ሀገራዊ ሰላምን፣ መረጋጋትንና አንድነትን ለማስፈን የታወጀውን የጾምና የጸሎተ ምኅላው አፈጻጸም በቅደሱ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት ከዚህ በመቀጠል አቀርባለሁ፡፡

ቀደም ሲል ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በመላው ዓለም ለሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያን የታወጀውን አዋጅ አስተላልፈዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ያለፈውን በይቅርታና በምህረት ዘግተን በእውነተኛ ንሥሓ ልቅሶና በምህላ፣ በጾምና በጸሎት ወደ ፈጣሪ እንድንቀርብ፣ በመካከላችንም ፍቅርና አንድነት እንዲመጣ ይኽንን ጾመ ነቢያት ወይም የገና ጾም በልዩ ሁኔታ እንድንጾም መንፈሳዊ አዋጅ ተላልፏል፡፡ 

ይኽ ጥንታዊ የአዋጅ ጾም ሁለት አበይት ታሪኮችን የያዘ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል ቅዱስ አብርሃም ሶርያዊ የተባለ ጻድቅ አባት በጸሎት፣ በጾምና በምኅላ ተራራን ከመሬት ከፍ በማድረጉ ኃይለ ጸሎቱና ክብረ አምለኩ የሚዘከርበት ነው፡፡ በሁለተኛው ክፍል ነቢያት የጌታችንን ሰው መሆን እያፈለጉ፣ ድህነትንና ሰላምን በመሻት መጾማቸው ይዘከራል፡፡ (፩ኛ ጴጥ ፩፡፲) እኛም ይኽንን አብነት አድርገን ታላቋ ቤተ ክርስቲያን፣ ኃላፊነቷን እንድትወጣ ስለችግራችን፣ ስለሀገር ሰላምና ስለ ሕዝቡ ደኅንነት በአንድነት ሆነን ወደፈጣሪያች እንድንጮኽ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጥቅምት ወር ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም ወስኖ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ሀገራችን እንድትፈወስ፣ የወገን በወገን ደም መፋሰስ እንዲቀር፣ ያለፈውን በይቅርታና በንሥሓ ዘግቶ ለወደፊቱ ብሩህ ዘመንን እንዲመጣ በንሥሓና በፍጹም ለቅሶ፣ በቁመትና በሰጊድ፣ በሰፊሕና በአንቅአድዎ፣ ወደፈጣሪ እንድንቀርብ የምልኣተ ጉባኤውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ ቋሚ ሲኖዶስ በኅዳር ወር ፳፻፲ወ፮ዓ/ም የሚከተለውን ዝርዝር አፈጻጸም አውጥቷል፡፡ 

፩ኛ. የጾሙ የመጀመሪያ ሳምንት ከቅዳሜ ኅዳር ፲፭ እስከ ኅዳር ፳፩ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም በሁሉም የሀገራችን ክፍልና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባለችበት በመላው ዓለም የንሥሓ፣ የጾም፣ የጸሎትና የምኅላ ሳምንት እንዲሆን፤

፪ኛ. በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ በአጥቢያ አለቆችና በገዳም አበምኔቶች መሪነት ሁሉም ዲያቆናት፣ ቀሳውስት፣ መነኰሳት፣ ሰባክያንና ሊቃውንት በሙሉ በየመዐርጋቸው ልብሰ ተክህኖና ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት ዩኒፎርማቸው ለብሰው፣ ሁሉም ምእመናን ጋር በአንድነት በዐውደ ምህረት ጸሎተ ምኅላውን እንዲያደርሱ፤ 

፫ኛ. በላው ሕዝበ ክርስቲያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ እናቶች አባቶች አረጋውያን ሁሉ የቻለ በቤተ ክርስቲያን፣ ያልቻለ በያለበት ሆኖ የተጣላ ታርቆ፣ በፍቅርና በአንድነት፣ በእውነተኛ ንሥሓና ጸጸት በምኅላው እንዲሳተፍ፤ በማእከል የሚደረገው ጸሎተ ምኅላ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ገዳም ሆኖ በመገናኛ ብዙኀን የቀጥታ ሥርጭት ለመላው ዓለም እንዲተላለፍ፤

፬ኛ. በመጀመሪያው የሱባኤ ቀን ኅዳር ፲፭ ቀንና፣ በሰባተኛው ቀን ኅዳር ፳፩ ቀን በጸሎተ ምኅላው በሚደረግበት ጊዜ ታቦቱ ከመንበሩ ተነሥቶ በዐውደ ምኅረት በቀሳውስት እንዲከብር ሆኖ፤ በሁሉም የምኅላው ቀናት ሥዕለ ማርያም፣ ወንጌልና መስቀል ወጥቶ በአራቱ መዐዝን ሥርዓተ ጸሎተ ምኅላው ከጸሎተ ወንጌል ጋር በየቀኑ በነግህና በሠርክ የሥራ ሰዓትን በማይነካ ሁኔታ እንዲፈጸም፤

፭ኛ. በየዕለቱ የሚነበቡት የወንጌል ክፍሎችን ስለ ሰላም፣ ስለንሥሓና ጸጸት፣ ስለ ፍቅርና አንድነት፣ ስለ በጎነትና መደማመጥ፣ ስለመሰማማትና ጥላቻን ስለማራቅ እንዲሆን፤

፮ኛ. በሰፊህና በአንቀዓድዎ፣ በሰጊድና በአስተብርኮ፣ ምኅላው ከደረሰና፣ ጸሎተ ወንጌል ደርሶ ዕለቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላ በአንድነት የንሥሓ መዝሙር በመዘመር፣ ሕዝበ ክርስቲያን ስለሀገራቸውና ስለሰው ልጆ ደኅንነት እያሰቡ ወደቤታቸው እንዲሄዱ፤

፯ኛ. ከመጀመሪው ሳምንት በኋላ እስከ በዓለ ልደት ድረስ የሰርክ ምህላ ሳይቋረጥ መደበኛው ሥርዓተ ጾምና ጸሎት እንዲቀጥል፣ የቤተ ክርስቲያንን ታላቅነት፣ የአበውን ተቀባይነት በሚገለጽ፣ በቀጣይም ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን በመንፈሳዊ ጽናት የሰላም ልዑካን ሆነው እንዲቀጥሉ በሚያደርግ ሁኔታ እንዲፈጸም፤ 

፰ኛ. አስቀድሞ የደረሰውንና፣ እየደረሰብን ያለው ችግር የጦርነትና የግጭት ብቻ ሳይሆን የረሀብ፣ የድርቅ፣ የኑሮ ውድነት፣ የመፈናቀልና የስደት ጭምር ስለሆነ ከጸሎትና ምኅላችን ጎን ለጎን መረዳዳትና መተዛዘን፣ ርኅራሄና መደጋገፍ አብሮ እንዲፈጸም፤   

፱ኛ. ይኽንኑ መልእክት መላው ዓለም እንዲውቀው፣ በተለይም የኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በጸሎት እንዲያስቡን፣ የጸሎታችንና የምኅላችን መነሻ ምክንያቱ የሀገራችን ወቅታዊ ችግር ቢሆንም የምንጸልየው ለመላው ዓለም መሆኑ ተገልጾ በደብዳቤ እንዲላክ እንዲደረግ፣ በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ መመሪያ አስተላልፏል፡፡ 

እግዚአብሔር አምላካችን በእንባና በንሥሓ የምናቀርበውን ጸሎተ ምኅላችንን በምህረቱ ተቀብሎ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን፣ ሕዝባችንን ይጠብቅልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 
ቅዱስ ሲኖዶስ
@tonetore

6 months, 3 weeks ago
ቶኔቶር ሀገረ እግዚአብሔር
We recommend to visit

"ይህ የቴሌግራም ቻናሌ ግንቦት1/2011ዓም የተከፈተ ነው። የእኔን የስልክ ወጪ ጨምሮ አገልግሎቴን መደገፍ የምትፈቅዱ ጓደኞቼ በ
👉🏿 https://donorbox.org/zemedemedia እና
👉🏿 https://www.paypal.com/paypalme/ZemedkunB በኩል ማገዝ ትችላላችሁ። በተረፈ ለቤተ ክርስቲያኔና ለኢትዮጵያ ሀገሬ የሚጠቅመውን ሁሉ አበረክት ዘንድ አብዝታችሁ ጸልዩልኝ።

Last updated 1 month, 3 weeks ago

The first Telecom operator in Africa https://t.me/EthiotelecomChatBot

Last updated 1 day, 15 hours ago

እንኳን ወደ ውዱ 4-3-3 Film ቻናላችን በሰላም መጣቹ

አዳዲስ እና የድሮ እንግሊዘኛ/አማርኛ/ህንድ/ቱርክ ፊልሞችን እና ከ1000 በላይ ተከታታይ ፊልሞችን የምታገኙበት ቻናል ነው

ለማስታወቂያ ስራ - @Abusheymc

ሃሳብ አስታየት ካሎት - @Abushecbot

Buy ads: https://telega.io/c/Films_433

Last updated 1 month, 2 weeks ago