꧁༒꧂ አዕማድ ꧁༒꧂

Description
የእግዚአብሔር አብ ጸጋ፣ የወልድ ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ያለ ጥርጥር በፍጹም ልባችን ከምናምን ምእመናን ጋር ይኹን! [፪ኛቆሮ.፲፫፥፲፬]
Advertising
We recommend to visit

Welcome To Amharic films

Best Place To find Amharic Movies

አዳዲስ እና የድሮ አማርኛ ፊልሞችን እና አማርኛ ተከታታይ ድራማዎችን ለማግኝት ቻናላችንን Join ይበሉ ።
Share:- @Amharic_Films

ለማስታወቂያ - @Abusheymc & @Alpha6249

Buy ads: https://telega.io/c/Amharic_films

Last updated 1 year, 5 months ago

ስለ መድፈኞቹ የሚወጡ መረጃዎች ለማግኘት የትም መሄድ አያስፈልግም

- የዝዉዉር ዜና
- የአሰልጣኞች አስተያየት
- የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
- ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት

ለማስታወቂያ ስራ  --> @Aymu_xo

Last updated 16 hours ago

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

#ኢትዮጵያ

ያግኙን +251913134524

Last updated 2 weeks, 1 day ago

6 days, 12 hours ago

✥••┈• ዑራኤል የተባለ መልአክ ሊረዳኝ መጣ፡፡” [መ/ዕዝ. ሱቱ. 2፡1] •┈••✥
በመላእክት ከተማ በራማ ካሉት ሦስት ነገዶች ውስጥ አንዱ ነገድ ሥልጣናት ይባላል፡፡ በሥልጣናት ላይ ከተሾሙ ሊቃነ መላእክት ውስጥ አንዱ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሱርያል ይባላል፡፡ ሱርያል የሚለው ስም በአንዳንድ ድርሳናት ካልሆነ በስተቀር እምብዛም አይታወቅም፡፡ ትርጉሙም ‹‹ዐለቴ እግዚአብሔር ነው›› ማለት ነው፡፡ ሱርያል የቅዱስ ዑራኤል ሌላ ስሙ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያንም በስፋት የሚተወቀው ስም ዑራኤል የሚለው ስም ነው፡፡ [ድርሳነ ዑራኤል 1991 ገጽ 14]

ዑራኤል ማለት “ብርሃነ እግዚአብሔር” ማለት ነው። “ዑራኤል ሥዩም ላዕለ ኵሎሙ ብርሃናት፤ ዑራኤል በብርሃናት ላይ ሁሉ የተሾመ ነው” እንዲሁም “ዑራኤል አሐዱ እመላእክት ቅዱሳን እስመ ዘረዓም ወዘረዓድ፤ ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ዑራኤል በመብረቅና በነጎድጓድ የተሾመ ነው” እንዲል፡፡ [ሄኖክ 6፥2] ከሊቃነ መላእክት አንዱ መሆኑንና ፍርሃት ረዓድ ላለባቸው ረዳታቸው እንደሆነ የመላእክትን ነገር የተናገረ ሄኖክ ነግሮናል፡፡ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሠፍራል” በማለት ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረ እግዚአብሔርን በሚፈሩና በሚያከብሩት ሰዎች ጭንቀት ጊዜ በመካከላቸው እየተገኘ ያጽናናቸዋል። [መዝ.33፥7]ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፤ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ይጠብቃቸዋል።

አንድም ዑራኤል የሚለው ስም “ዑር” እና “ኤል” ከሚሉ ኹለት ቃላት የተመሠረተ ነው። ዑራኤል ማለት ትርጉሙ “የብርሃን ጌታ”፣ ”የአምላክ ብርሃን” ማለት (እግዚአብሔር ብርሃን ነው) ማለት ነው። "በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ 7 መላእክትን ዐየሁ" [ራዕ. 8፡2] እንዳለ ሊቃነ መላእክት በቊጥር 7 ናቸው። ቅዱስ ዑራኤልም ከ7ቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ በመብረቅና በነጎድጓድ ላይ የተሾመ መልአክ ነው። በመሆኑም መባርቅት ለጥጋብና ለበረከት እንዲበርቁ ነጎድጓድም ለሰላም እንዲሆን ያሰማራል። [መ.ሄኖክ. 6፥2] ምስጢረ ሰማይና እውቀትንም ኁሉ ለሄኖክ የገለጸለት የፀሐይን የጨረቃን የከዋክብትንና የሰማይ ሰራዊትን ብርሃንን የሚመራ እርሱ መሆኑን ለሄኖክ ነግሮታል። [መ.ሄኖክ 28፥13] “ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ ከልጇ ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወደ ግብጽ ስትሰደድ መንገድ የመራ፤ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ በተሰቀለ ጊዜ፣ ክቡር ደሙን በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ፣ በብርሃነ መነሳንስ በዓለም ላይ የረጨ፤ እውቀት ለተሰዎረባቸው ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል ጽዋ ጥበብን ያጠጣ፤ ኢትዮጵያዊውን ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መርካታ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንዲደርሱ ያገዘ፣ የረዳና የዕውቀት ጽዋን ያጠጣ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡

የመልአኩ ዓመታዊ ክብረ በዓላት
• ጥር 22 በዓለ ሲመቱ፣
• መጋቢት 27 የጌታችንን ክቡር የሆነ ወርቀ ደሙን ለዓለም የረጨበት ነው፡፡
• ሐምሌ 21 እና 22 ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የእውቀት ጽዋ ያጠጣበት ቀን ነው።

አፈቅሮ ፈድፋደ፡- ዑራኤል ሆይ፣ ከመልኮች ሁሉ ይልቅ ያንተን መልክአ ጸሎት እወዳለሁ፡፡ የመልክህ ስነ ጸዳል በደመ ወልድ እግዚአብሔር የታተመ ነውና፡፡
ዑራኤል ሆይ፣ እግዚአብሔር ኃይሉን የሚገልጽብን መልአከ ብርሃናት አንተ ነህ፡፡ በዕለተ ሥቅለት በደመ ወልድ ዓለምን ለመቀደስ ከሁሉ ይልቅ አንተ ተሰይመሃልና፡፡ ስለክብርህ የሰማይ መላእክት አደነቁ፡፡

ለተፈጥሮትከ፡-
ዑራኤል ሆይ
፡- ያለ መናገር በጥንት አርምሞ ከነፋስና ከእሳት ለተፈጠረ ተፈጥሮህ ሰላም እላለሁ፡፡ ዑራኤል ሆይ የተፈጥሮና የይቅርታና የቸርነት ክቡር መልአክ ነህና ስለኛ ስለሰው ልጆች ወደ ልዑል እግዚአብሔር ማልድ አማላጅነትህ ዘወትር ከጥፋት ያድናልና፡፡

ለዝክረ ስምከ፡-
ዑራኤል ሆይ፡- ከማርና ከወተት ይልቅ ለሚጥመው ስም አጠራርህ ሰላም እላለሁ፡፡

ዑራኤል ሆይ፡- ክፍልህ /ክንፍህ/ በደመ ወልድ እግዚአብሔር የተከበረ /የታለለ/ ነውና፡፡ ለዓለሙ ሁሉ መድሃኒት ትሆን ዘንድ ግሩም የሚሆን የእግዚአብሔር ሥልጣን በክብር ከፍ ከፍ አደረገ፡፡ [መልክአ ዑራኤል]

በአምላኩ አማላጅነቱን ኑና ተማጸኑት። በጸሎቱ ለተማጸነ ከአምላኩ በረከትን ምህረትን የሚያሰጥ አዛኝ እርሩህ መልአክ ነው። የቅዱስ ዑራኤል በረከት በኁላችንም ላይ ይደር!! አሜን።

✥••┈••●◉ ✞ ◉●••┈••✥

6 days, 12 hours ago
꧁༒꧂ አዕማድ ꧁༒꧂
1 week ago

እመቤታችን ሆይ፣ የቅዱሳንና የምእመናንን ኹሉ ጸሎት በማዕጠንታቸው ከምድር ወደ ሰማይ በሚያሳርጉ በሰማያውያን የካህናት አለቆች አጆች ውስጥ ባለ የወርቅ ማዕጠንት እንመስልሻለን። እንዲኹም ስምሽን በመጥራት የሰው ልጆችን ልመና ወደ ልዩ ሦስትነት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ያሳርጋሉ። የወገኖችሽንም ኅጢአት ታስተሠርዪ ዘንድ ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ተፈቅዶልሻልና። ለሰዎች ልጆች የዘለዓለም ሕይወት ድልድይ ትሆኝ ዘንድ የዓለም ኹሉ መድኃኒት ሆይ፣ ለምእመናን ወገኖችሽ መድኃኒታቸው ልትባይ ይገባል። ቅድስት ሆይ ልጅሽ ይቅርታውን ያድለን ዘንድ ለምኝልን።

አንቀጸ ብርሃን

1 week, 2 days ago

በሠራዊት ሁሉ ላይ የተሾመ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው። [ሄኖ.10:14]
ሰላም ለሰኰናከ
ገብርኤል ሆይ፥ በዚያ ድብቅልቅና ሽብር በሆነበት ዕለት ከጌታ እግረ መስቀል ሥር ለቆሙት ተረከዞችህና ጫማዎችህ ሰላም እላለሁ፤ ገብርኤል ሆይ የጌታን ትዕግሥት የአይሁድን ግፍ ተመልክተህ በታላቅ ዐደባባይ ላይ ሰይፈ ቁጣህን አምዘገዘግኸው ቅዱሳት አንስት ግን ክርስቶስ ተነሥቷል ስላልካቸው የትንሣኤውን ምሥራች ይነግሩ ዘንድ ወደ ሐዋርያት ሄዱ።

1 week, 4 days ago

በአንድ ወቅት በብዛትና በአንድነት ሲጠፉ ለምን ጠፍ ምክንያቱ ምንድን ነው ሳንል ራሳችንን አገልግሎታችንን ሳንፈትሽ ጸጥ ብለን በሆነ ወቅት ደሞ እነዛው የጠፉት መመለስ ሲጀምሮ የምን ማንጎራጎር ማብዛት ነው። አገልግሎት ምንድን ነው
አገልግሎት ማለት በፍቃደኝነት በተሰጠን ጸጋ(ስጦታ ) ልዑል እግዚአብሔርን ማገልገል ማለት አይደለምን? ለዚህ ደግሞ ሁሉም ተጠርቷል፡፡

አገልግሎት በእግዚአብሔር ጥሪ የሚጀመር መንፈሳዊ ተልዕኮ ነው፤ 
እግዚአብሔር ሰዎችን ያገለግሉት ዘንድና የፍቅሩ ተሳታፊዎች ይሆኑ ዘንድ ይጠራል፡፡
አግልግሎት በእግዚአብሔር እና በሰው ልጆች መካከል ያለ የፍቅር መግለጫ ነው፡፡
አግልግሎት ከእግዚአብሔር የተደረገልንን ውለታ ማሰብ ነው፡፡
አንድ አባት ”ቤተ ክርስቲያን አምጥታናለች፤ አስተምራናለች ለጌታችንም አንድንገዛ አድርጋናለች“ ብለዋል፡፡

አገልግሎት ማለት ያዩትን እና የሰሙትን የእግዚአብሔርን ቸርነት መመስከር ያወቁትን መንፈሳዊ ዕውቀት ላላወቀ ማሳወቅ ማለት ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን አገለግሎት ዋና ዓላማው የጠፋውን የሰው ልጅ ለድኀነት ማብቃት ነው፡፡ ሰው ለድኀነት የሚበቃው አዕማደ ምስጢራትን አምኖ ሲፈጽም በአመነበት እምነት ጸንቶ ከኃጢአት በመጠበቅ እግዚአብሔርን ሲያገልግል ነው፡፡ [2ኛ ጢሞ 2፤15 ”የእውነት ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ኾነኽ፥ የተፈተነውን ራስኽን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ።"
ለመጣችሁም በመምጣት ሂደት ላይ ያላችሁም የምትመጡም እንኩዋን ወደ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችሁ ተመለሳችሁ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን ደግሞም ያጽናችሁ።

1 week, 6 days ago

ለምን ያህል ሰዓት ምግብ ከመብላት እንቆጠብ?
አንድ ሰው በጾም ወቅት ምግብ ከመብላት የሚቆጠብበት ጊዜ እንደ እድሜ፣ አቅም፣ የጤና ኹኔታ እና የሥራጫና የሚወሰን ነው፡፡ እነዚህን መሠረታዊ መስፈርቶች እንመልከታቸው፡፡
1. መንፈሳዊ አቅም/ብስለት [Spiritual Maturity] - አንድ ሰው ከፍተኛ የሆነ መንፈሳዊ አቅም/ብስለት ካለው፤ ለረጅም ሰዓት ምግብ ሳይበላ መቆየት ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል፡- አንዳንድ ገዳማውያን እና ባህታዊያን በሦስት እና በአራት ቀን አንድ ጊዜ ብቻ በጥቂቱ እየተመገቡ መቆየት ይችላሉ፡፡ ዝቅተኛ የሆነ መንፈሳዊ አቅም ያለን ግን በአቅማችን መጾም መቻል አለብን፡፡ ሌሎችን ዐይተን ‘ለምን ይበልጡናል’ በሚል ስሜት ብንንጠራራ ግን ራሳችንን እንጎዳለንእንጂ፤ መንፈሳዊ በረከትን አናገኝበትም፡፡

2. እድሜ [Age] - በጾም ወቅት የምናየው ኹለተኛ መስፈርት እድሜ ነው፡፡ አንድ ጾምን በመለማመድላይ ያለ የስምነት ዓመት ልጅ፣ ወደ ወጣትነት እየተሸጋገረ ያለ የዐሥራ ስድስት ዓመት ልጅ፣ የሃያ አራት ዓመት ወጣት፣ የአርባ ዓመት ጎልማሳ እና የሰባ ዓመት አዛውንት እኩል የሆነ የመጾም አቅም አይኖራቸውም፡፡ በመሆኑም የጾም ሰዓት ከእድሜ ጋር መገናዘብ አለበት፡፡ አንድን የስምንት ዓመት ልጅ እስከ ዐሥራ አንድ ካልጾምክ ብሎ ማስገደዱ ጾምን በልኩ እንዳይለማመድ ከማድረጉም በተጨማሪ፣ እየተሰላቸ እና እየተማረረ እንዲጾመው በማድረግ መንፈሳዊ በረከቱን እንዳያገኝ ሊያደርገው ይችላል፡፡

3. የጤና ኹኔታ [Status of Health] - ሌላው አጽንኦት የሚሰጠው ጉዳይ ደግሞ የጤና ኹኔታ ነው፡፡ በሕመም ከደከሙ ሰዎች ይልቅ ሲነጻጸር ፍጹም ጤናማ የሆነ ሰው በተሻለ ኹኔታ የመጾም ችሎታ ይኖረዋል፡፡ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አስቸጋሪ የሆነ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ከንስሐ አባቶቻቸው ጋር በመመካከር ለአጭር ሰዓት ብቻ ከጸሎት ጋር መጾም ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ‘አንድ ጊዜ እንዲህ አሞኝ ነበር፤ አሁንም ብጾም ሊያመኝ ይችላል’ በሚል ፍራቻብቻ ደግሞ ከጾም መሸሽ እንደማይገባ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

4.የሥራ ክብደት [Heaviness of Work] - አንድ ሰው የሚሠራው የሥራ ዓይነትም ግምት ውስጥ ይገባል፡፡አንዳንድ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ አካላዊ አቅም የሚጠይቅ ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ብዙ አካላዊ እንቅስቃሴ የማያስፈልገውእና ቢሮ ውስጥ ቁጭ ተብሎ የሚሠራ ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ፡፡በዚህ ዓይነት ያሉ ኹለት ሰዎች እኩል ላይጾሙ ይችላሉ፡፡ የመጾም አቅማቸውም ከሥራቸው አኳያ ሊለያይ ይችላል፡፡

3 months, 1 week ago

አካላቱን ዳሠሠው ፊቱንና ዓይኖቹን አሻሸው ጽድቁንም ዐውቆ << አባቴ በረከትህ ትድረሰኝ >> በማለት ተባርኳል፡፡

ትምህርተ ሃይማኖትን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ካጸና በኋላ ወደ ሀገረ መንበረ ሢመቱ ተመልሶ ካህናቱንና መንጋዎቹን ሁሉ ሰብስቦ ጸሎተ ሃይማኖትን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አነበበላቸው ይኅን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም አጽንተው እንዲጠብቁት አዘዛቸው፡፡ ጥቂት ዘመናትም ከኖረ በኋላ ቅዱስ ቶማስ ጵጵስና በተሾመ በ40 ዓመቱ ነሐሴ 24 አርፏል፡፡ የጻድቃንን የሰማዕታትን የሐዋርያትንና የሊቃውንትን አክሊልም ተቀብሏል።

ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት ሐምሌ 1-15/2014 ዓ.ም

3 months, 1 week ago

በቶማስ ስም የሚጠሩ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የሚታወቁ በርካታ ቅዱሳን ቢኖሩም የዚህ ዓምድ ዋና ትኩረቱ የክርስቶስ ምስክሩና ሐዋርያው የሆነ የመርዓስ ኤጲስ ቆጶስ ተጋዳይ ቶማስ ላይ አድርጎ ዘመናችንን ይፈትሻል፡፡ የቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ ትሩፋትና ገድሉን ሰው ተናግሮ ሊፈጽመው አይቻልም እርሱ አስቀድሞ ከልጅነቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን የተማረ ገና በወጣትነቱ መንኖ ገዳም የኖረ በጾም በጸሎት በሰጊድ ቀን እና ሌሊትም በመትጋት ለድኆችና ለምስኪኖችም በመራራት ተጠምዶ የኖረ ነበር፡፡ ቅዱስ ቶማስ "መርዓስ" በምትባል አገር የወጣ የንጋት ኮከብ ጻድቅ ገዳማዊ ጳጳስ ሐዋርያ ሰማዕትና ሊቅ ነው፡፡ የእርሱ ሕይወት ኦርቶዶክሳዊ የክርስትና ሕይወትና የጵጵስና የሹመት ሕይወት ምን እንደ ሆነ በትክክል የሚያሳይ ነው፡፡ መርዓስ በምትባል ሀገር ጳጳስ ሆኖ ተሹሞ በእረኝነት ያገለገል ዘንድ የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መረጠው መንጋውንም እንደ ሐዋርያት ጠበቀ፡፡ በሹመት ዘመኑ በሰላሙም በመከራውም ዘመን << መኑ ያኀድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?›› [ሮሜ 8፥35-37] እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ለክርስቶስ ያለውን ፍቅር መከራ ጭንቀት ስደት ራብ ራቁትነት ፍርሃት ሰይፍ ሳይለየው ለአርባ ዓመታት ስለ ክርስቶስ ቀኑን ሁሉ እንደሚታረድ በግ ሆኖ እግዚአብሔርን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አገለገለ፡፡

ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ብዙ አሕዛብን ወደ ክርስትና የመለሰ እና በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው፡፡ ጨካኞቹ ቅዱሱን ለ፳፪ ዓመታት አካሉን እየቆራረጡ ለጣዖታቸው ያጥኑ ስለ ነበር 2 እግሮቹ 2 እጆቹ 2 ጀሮዎቹ 2 አፍንጫዎቹ እና 2 ዐይኖቹ አልነበሩም:: ነገር ግን እንዲህም ሆኖ አልሞተም እግዚአብሔርንም ማገልግለ አልተወም ነበር፡፡ በመጨረሻም በዘመነ መናፍቃን አርዮስን ካወገዙት 318ቱ ሊቃውንት አንዱ ለመሆን የበቃ ነበር።
የሰንክሳር አርኬ ደራሲው አርከ ሥሉስም ስለ ቶማስ ዘመርዓስ ለሌሎቹ ቅዱሳን እንደጻፈላቸው ሁሉ <<ሰላም ለቶማስ ዘአባላቲሁ ግሙድ እስከ አስተርእየ ኅብሩ አምሳለ ውዑይ ጕንድ ለዝ መዋዒ በነጽሮ ገድሉ ፍድፉድ ወሰላም ለእለ ምስሌሁ ሙቁሐነ እድ አእላፈ ክርስቶስ ተስዓቱ እልፍ በፍቅድ ሰወነቱ እንደደረቀ ግንድ እስኪመስል ደድረስ አካላቱ ለተቆረጡ ለቶማስ ሰላምታ ይገባል። የዚህን የአሸናፊ ቶማስን የበዛ ገድሉን በማየት በፈቃድ ከእርሱ ጋር ለታሰሩትና የክርስቶስ ወገኖች ለሆኑ ለዘጠኝ እልፍም ሰላምታ ይገባል።›› በማለት አርኬ ደርሶለታል።

ምንም እንኳን በአቡነ ተክለ ሃይማኖትና በቶማስ ዘመርዓስ የዕረፍት ቀን በመካከላቸው የ ፩ሺህ ዓመት ልዩነት ቢኖርም የአቡነ ተክለይማኖት መልክእ ደራሲው ዮሐንስ ከማ ሁለቱ ቅዱሳንን በማነጻጸር <<ሰላም ለጸአተ ነፍስከ በስብሐተ አእላፍ እንግልጋ ለዓለመ ዛቲ እም ግብርናቲሃ ወጹጋ ተክለሃይማኖት ቶማስ ለመርአስ ዐቃቤ ሕጋ ለእመ ገብሩ ተዝካረከ እለ ሀለዉ በሥጋ ሀቦሙ• እግዚእየ ሞገሰ ወጸጋ የመርዓስ የሕጓ ጠባቂ ቶማስ ተክለ ሃይማኖት ሆይ ከዚች ዓለም ሥራና ድካም በአእላፍ መላእክት ምስጋ ለነፍስህ መውጣት ሰላምታ ይገባል፡፡ በሥጋ ሳሉ ተዝካርህን ያደረጉትን ጌታየ ሆይ ሞገስንና ጸጋን ስጣቸው።›› በማለት ጽፏል። ከሃዲው ዲዮቅልጥያኖስ በነገሠ ጊዜ ክርስቲያኖቹን ሲያሰቃዩ በነበረበት ወቅት ከንጉሱ መኳንንት አንዱ ወደ መርዓስ ሄዶ ቶማስ ዘመርዓስን በጭፍሮቹ አስያዙት፡፡ እንደያዙት ደብድበው በምድር ላይ እየጎተቱት ደሙ እየፈሰሰ ወሰዱት፡፡

መኰንኑ ቅዱስ ቶማስን ‹‹ለአማልክት ስገድ›› አለው፡፡ ቶማስ ዘመርዓስም ‹‹እኔ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለረከሱ ጣዖታት አልሰግድም ለረከሱ ጣዖታት የሚሰግድ ሁሉ የተረገመ ነውና ከእግዚአብሔር በቀር የሚሰግዱለት አምላክ የለም >> አለው፡፡ መኰንኑም እጅግ የብዙ ጽኑ ስቃዮችን አሰቃየው፡፡ የነዳጅ ድፍድፍ አፍልተው በሰውነቱ ላይ እንዲሁም በአፍና በአፍንጫው ውስጥ ጨመሩበት እስከ ብዙ ዘመናት ኖረ፡፡ እነዚህ ከሀድያን ልባቸው እንደ ደንጊያ የጸና ስለነበረ ቶሎ ብለው እንዲሞቱ ሳይሆን በሥቃይ ሆነው እንዲቆዩ በማድረግና ሌሎች ብዙዎች ሰዎችን ያስፈሩአቸው ዘንድ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ይክዱ ዘንድ የሥቃዩን ዘመን አስረዘሙት፡፡

ቶማስ ዘመርዓስ ግን በጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል የጸና ነውና ማሰቃየቱን ከሃዲያን በደከማቸው ጊዜ ስለስሕተታቸው ይዘልፋቸው ስለ ነበር ወደ ጨለማ ቦታ ጣሉት በዚያም ለ22 ዓመታት በጨለማ ውስጥ አስረው አሠቃዩት፡፡ ከሀድያኑም በየዓመቱ ወደ እስር ቤቱ እየገቡ አንድ አካሉን ይቆርጣሉ፡፡ <<መተሩ አንፎ ወከናፍሪሁ ወእዘኒሁ ወእደዊሁ ወእገሪሁ ወመሰሎሙ ለመርዓቱ ዘአዕረፈ ወነበሩ እንዘ ይገብሩ ተዝካሮ ለለዓመት አፍንጫውን ከንፈሮቹን ጆሮዎቹን እጆቹንና እግሮቹን ቆረጡ መንጋዎቹም ያረፈ መስሏቸው በየዓመቱ መታሰቢያውን ሲያድርጉ ኖሩ፡፡››
ከሃዲያኑ እጅና እግሩን በየተራ የቆራረጡትን የሰውነት አካላቱን አፍንጫውን ከንፈሮቹን ጆሮዎቹን ሁሉ በየተራ እየቆረጡ ለ 21 ዓመታት ጣዖታቸውን ሲያጥኑበት ኖረዋል፡፡ አንዲት ደግ ክርስቲያናዊት ሴት ቶማስ ዘመርዓስ የተጣለበትን ጉድጓድ አይታ ስለነበረ በድብቅ በሌሊት ተሰውራ እየሄደች ትመግበው ነበር፡፡ ደገኛውና ጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እስከ ነገሠና የቀናች የክርስቶስን ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖትን ክብር እስከ ገለጠበት ድረስ ቶማስ ዘመርዓስ ሲሰቃይ ቆየ፡፡

ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመታመኑ የታሠሩ እሥረኞችን ሁሉ በሀገሮች ሁሉ በወህኒ ቤት ያሉትን ይፈቷቸው ዘንድ አዋጅ አውጥቶ ሲያዝ ክርስቲያናዊቷ ሴት ሄዳ ስለ ቅዱስ ቶማስ ስለ እርሱ የሆነበትን ሃያ ሁለት ዓመት ተጥሎ እንደኖረ ለካህናቱ ነገረቻቸው በውስጡ ወደ ሚኖርበትም ቦታ መራቻቸው፡፡ ካህናቱም አንሥተው ተሸከሙት እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አደረሱት በቤተ መቅደሱም ፊት ለፊት በወንበሩ ላይ አስቀመጡት ምእመናንም ሁሉ ወደእርሱ እየመጡ ከእርሱ ይባረኩና የተቆረጡ አካላቱን ይሳለሙ ነበር፡፡

ቶማስ ዘመርዓስ ወደ ሠለስቱ ምዕት ጉባኤ ሲሄድ ዞሮ እንዳያስተምር እግሩን ጽፎ መልእክታት እንዳይልክ እጁን በሰማእትነት በሃያ ሁለት ዓመታቱ ሰማእትነት አሰጥቶአቸው ስለነበር ደቀ መዛሙርቱ በቅርጫት ውስጥ አድርገው በአህያ ጭነው ወደ ጉባኤ ኒቂያ ይዘውት ሄደዋል፡፡ በመንገድም ሳሉ ዐላውያን አግኝተዋቸው ጥቁርና ነጭ አህዮቻቸውን ሌሊት ራስ ራሳቸውን ቆርጠው ጣሉባቸው፡፡ በማግስቱም ቶማስ ዘመርዓስም ራሳቸውን የተቆረጡትን አህዮች አምጡልኝ ብሎ የጥቁሩን አህያ ራስ ከነጩ የነጩን አህያ ራስ ለጥቁሩ ገጥሞ ቢባርካቸው ሁሉም አህዮች ከሞት ተነስተዋል፡፡ የአህዮቻቸውም መልክ እጅግ ያማሩ ሆኑ፡፡ ንገሥ ቈስጠንጢኖስ የከበሩ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳቱን በኒቂያ ሀገር እንዲሰበሰቡ ሲያደርግ ይህ የከበረ ቶማስ ዘመርዓስ ከሊቃውንቱ አንዱ ነበር። ከጉባኤው ሲደርሱ ንጉሡ ቈስጠንጢኖስ ወደ ጉባኤው ገብቶ ለቅዱሳን ሊቃውንቱ ሰላምታ ሰጣቸውና ከሊቃውንቱ ቡራኬ ተቀበለ ። የዚህን ቅዱስ የቶማስ ዘመርዓስን ተጋድሎውን በነገሩት ጊዜ ወደ እርሱ ቀርቦ ሰገደለት አካላቱም ከተቈራረጡበት ላይ ተሳለመው። ከዚያም አዝኖና አጅግም ተደንቆ አድንቆ

3 months, 1 week ago

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ወይም ዞረሬ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ክልል ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው፤ በ፲፩፻፺፯ ዓ.ም ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ ማለት ነው፡፡

«አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ . . . ደካማ ለሆንኩ ለእኔ ያለ አንተ የሚያፀናኝ የለም። ለምፍገመገም ለእኔ ያለ አንተ ደጋፊ የለኝም። ለወደቅሁ ለእኔ ያለአንተ የሚያነሳኝ የለም። ለአዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም። ለድሀው ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም፡፡» [ገድለ ተክለ ሃይማኖት ምዕ ፳፰ ቁ ፪ - ፫]

ይህን ብለው ትሕትና በተሞላበትና በተሰበረ ልብ ወደ ፈጣሪያቸው ከለመኑ በኋላ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ሃይማኖት መልሰዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ ተብለዋል፡፡
[http://www.good-amharic-books.com/library?id=466 አስደናቂ ገድላቸውን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ]

ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን ክታቡ ስለ ቅዱሳን መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲገልፅ:-
*«እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሱ» [ዕብ. ምዕ ፲፩ ቁ ፴፫] እንዳለ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖትም በመንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲሁም በትህትና በተአምራት አላዊ የነበረውን ንጉሥ ሞቶሎሚን ወደ ክርስትና መልሰዋል፡፡

*«ጽድቅን አደረጉ» እንዳለው አባታችን ወንጌልን በተጋድሎ ሕይወታቸው ተርጉመዋል፡፡

*«የአንበሶችን አፍ ዘጉ» [ምዕ ፲፩ ቁ ፴፫፤ ምዕ ፲፩ ቁ ፴፬] እንዳለው አባታችንም የአውሬውን፥ የዘንዶውን ራስ ቀጥቅጠዋል።

*«ከሰይፍ ስለት አመለጡ» እንዳለው አባታችንም ሞቶሎሚ ከወረወረው ጦር በተአምራት ድነዋል፡፡

*«ከድካማቸው በረቱ» እንዳለው አባታችንም ያለ ዕረፍት በብዙ ተጋድሎ በጾምና በስግደት በብዙ መከራ በርትተዋል፡፡

ይህን ሁሉ ገድልና ትሩፋት እየፈጸሙ ዕረፍታቸውም በደረሰ ጊዜ ደቀመዝሙሮቻቸውን «ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኮስ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም፤ ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ፤ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ፤ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ እያሉ ይመክሯቸው ነበር. . .» በኋላም «ለዓለም ጨው ለራሴ አልጫ ሆንኩ፤ ለዓለም ብርሃን ለራሴ ጨለማ ሆንኩ፣ ከእውነተኛው ዳኛ ከጌታዬ ፊት ስቆም ምን እመልሳለሁ?» እያሉ በፍጹም ትህትና እና በልዩ መንፈሳዊ ተመስጦ ይጸልዩ ነበር፡፡

በመጨረሻም አባታችን በነሐሴ ፳፬ ቀን ዕረፍታቸው ሆነ። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ለእኚህ ዕረፍታቸው በእግዚአብሔር ፊት ለከበረና ብዙ ክብር ለተሰጣቸው ለጻድቁ ተክለ ሃይማኖት በየዓመቱ በነሐሴ ፳፬ ቀን በዓለ ዕረፍታቸውን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡ እኛንም ከጻድቁ ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡

በበለጠ ለማወቅ ስለ '''አባታችን''' ሰፊውን ገድላቸውን ማንበብ እጅግ አርጎ ይጠቅማል።

ምንጭ
http://eotc-mkidusan.org/site/index.php?option=com_content&task=view&id=346&Itemid=26
St-Takla.org
• ^ ታሪካቸው በኢትዮጵያ ሥንክሳር በነሐሴ ፳፬ የሰማዕታትና ቅዱሳን ታሪክ ውስጥ ይነበባል

3 months, 2 weeks ago

ሸምሸርሸጢን ከሚባለው ከግራር እንጨት የተቀረጸው ታቦት አይነቅዝም አይበላሽም
እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ያደረባት የጌታ ዙፋን የሆነች የወላዲተ አምላክ የታቦተ መቅደስ የድንግል ማርያም ሥጋዋ በምድር አይኖርም ተነሥታለች ዐርጋለች!

ታቦት በወርቅ ልቡጥ እምኵለሄ ዘግቡር እምዕፅ ዘኢይነቅዝ እንዲል ቅዱስ ኤፍሬም

ታቦቱ ?
1. እግር አለው ?የንጹሐን አበው ምሳሌ ነው
2. መያዣ አለው ? የንጹሐን ምእመናን ምሳሌ ነው
3. በውስጥና በውጪ በወርቅ የተለበጠ ነው ? አመቤታችን በነፍሷም በሥጋዋም ንጹሕ የመሆኗ ምሳሌ ነው
4. ፈለግ አለው ? የልቡናዋ ምሳሌ ነው
5. ብጽብጽ ወርቅ አለው ?ሁከት መንፈሳዊ ነው እመቤታችን በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ምሥጢራት በልቡናዋ ይወጣሉ ይወርዳሉና
6. አራት ቀለበት አለው ? አመቤታችን በአራት ወገን (ከርእይ ከሰሚእ ከአጼንዎ ከገሢሥ) ንጽሕት ናትና
7. ሁለት መሎጊያ አለው ? የአዳምና የሔዋን አንድም የዮሴፍና የሰሎሜ ምሳሌ ነው
8. ታቦቱ ርዝመቱ 2 ከንድ ተኩል ፣ ቁመቱ 1 ክንድ ተኩል ፣ ወርዱ 1 ክንድ ተኩል ነው ። ይህ ሲደመር 5 ክንድ ተኩል ነው ይኸውም 5500 ዘመንን የሚያሳይ ነው
የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ ከአማናዊት ታቦት እመቤታችን ጽላት ጌታ ተገኘ።

እመቤታችን ?
• ሕሊናዋ ልቡናዋና አእምሮዋ በመንፈስ ቅዱሰ የተሞላ ነው
• ሕይወቷ ለጽድቅ የተሰጠ ነው
• አካሏ ለቅድስና የተሠዋ ነው
• እጆቿ አካለ መለኮትን የዳሠሡ ናቸው
• እግሮቿ ለእኛ መዳን እንዲሆንልን እንዲደረግልን የተንከራተቱ ናቸው
• አንደበቷ ምስጋናን ብቻ ያውቃል
• ፍቅር እና ትሕትና ቋንቋዋ ነው
• በአጠቃላይ ቀድማ ትነሣኤ ልቡናን የተነሣች በመሆኗ የጌታ እናት የዓለም ሁሉ እናት ሆናለች
• ስለዚህም ከጌታ ቀጥላ ከእኛ አስቀድማ ተነሥታለች ዐርጋለች!!!
አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት" ብሎ ዳዊት እንደተናገረ [መዝ 131፥8]
እርሱ የመቅደሱ ታቦት ተነሥተዋል!!!

“ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው.....”
— [1ኛ ቆሮንቶስ 15፥23]

ከመጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ ከፍያለው
በረከቷ አማላጅነቷ
ልጅዋ የሚቀበለው ጸሎቷ በሁላችንም ላይ ይደርብ።

We recommend to visit

Welcome To Amharic films

Best Place To find Amharic Movies

አዳዲስ እና የድሮ አማርኛ ፊልሞችን እና አማርኛ ተከታታይ ድራማዎችን ለማግኝት ቻናላችንን Join ይበሉ ።
Share:- @Amharic_Films

ለማስታወቂያ - @Abusheymc & @Alpha6249

Buy ads: https://telega.io/c/Amharic_films

Last updated 1 year, 5 months ago

ስለ መድፈኞቹ የሚወጡ መረጃዎች ለማግኘት የትም መሄድ አያስፈልግም

- የዝዉዉር ዜና
- የአሰልጣኞች አስተያየት
- የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
- ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት

ለማስታወቂያ ስራ  --> @Aymu_xo

Last updated 16 hours ago

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

#ኢትዮጵያ

ያግኙን +251913134524

Last updated 2 weeks, 1 day ago