Venue

Description
መድረሻ ባይኖር ፣ መጓዝ ብርቅ ነበር!
:
መራመድ ባልከፋ ፣ መድረሻም ባልጠፋ
ነገ ላይ ለመድረስ ፣ ሰው ባያጣ ተስፋ ።
Advertising
We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ ነው። ሰውነትን አስቀድመው ግለሰብን፣ ህዝብና ሀገርን የሚያከብሩ፣ ሚዛናዊ አመለካከትን ያዳበሩ፣ ከጥላቻ አመለካከት የነፁ ኢትዮጵያውያን ቤት ነው።

ያግኙን +251913134524

Last updated 1 month, 2 weeks ago

ስለ መድፈኞቹ የሚወጡ መረጃዎች ለማግኘት የትም መሄድ አያስፈልግም

- የዝዉዉር ዜና
- የአሰልጣኞች አስተያየት
- የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
- ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት

ለማስታወቂያ ስራ  --> @MKHI7

Last updated 1 month, 2 weeks ago

BoA Social media links
@ https://www.facebook.com/BoAeth
@ https://www.instagram.com/abyssinia_bank
@ https://www.linkedin.com/company/bankofabyssinia/
@ https://twitter.com/abyssiniabank
@BOA_ATM_bot

Last updated 3 weeks, 5 days ago

1 month, 2 weeks ago

#ዝክረ_ክብር ②③
:
« ከፍጥረታት ውስጥ እንደ ረሱሉላህ የወደደን፣ የተጨነቀልን የለም። እንደ ረሱሉላህ ሌት ተቀን ዱዓ ያደረገልን የለም። እንያ የተላቁ ታላቅ ነብይ፣ ያለፈውም የሚመጣውም ወንጀሎቻቸው ተምሮላቸው አመስጋኝ ባርያ ለመሆን ሌት ተቀን የሚተጉት ባለ ታላቅ ጠባይ ዱዓቸው፣ ጭንቀታቸው ሁሉም ለህዝቦቻቸው ነበር።
አንድ ጊዜ ረዉሉላህን አንቱ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ ዱዓ አድርጉልኝ አሏቸው የምዕመናን እናት የሆኑት እናታችን አዒሻ ቢንት አቡበከር ረድየላሁ አንሃ። ረሱሉላህም ወድያው እጆቻቸውን ለፍ አድርገው
‹ አላህ ሆይ የአዒሻን ሁሉንም ወንጀሎቿን ይቅር በላት፣ ያለፈውን፣ የሚመጣውንም ድብቁንም ሁሉንም ወንጀሎቿን ይቅር በላት፣ ማራት። › ብለው ዱዓ አደረጉላቸው።
እናታችን አዒሻ ይህን ሲሰሙ እጅጉን ሀሴት ተሰማቸው። በደስታ ፈገግ እያሉ ጭንቅላታቸውን ረሱሉላህ ላይ ደገፍ አደረጉት። እንያ ፍቅር አዋቂ ሸጋው ነብይ
ዱዐዬ አስደሰተሽን? አሏቸው። አዒሻም እንዴት የእርሶ ዱዓ ላያስደስተኝ ይችላል? ብለው መለሱላቸው። ረሱሉላህም
በአላህ እምላለሁ ይህን ዱዓ በእያንዳንዱ ሰላቴ ውስጥ ለኡመቶቼ የማደርገው ዱዓ ነው። አሉ። መገን የአላህ ነብይ!
አዒሻ ሲናገሩ አንድ ቀን በምሽት እየሰገዱ እያለ አንዲትን የቁርዓን አንቀፅ በጣም በተደጋጋሚ ሲቀሩት አዳመጥኳቸው። አንዴ ወይም ሁለቴ አይደለም በጣም በተደጋጋሚ ለሊቱን ሙሉ እየደጋገሙ ሲቀሩት ነበር። ደጋግመው ሲቀሩት የነበረው የቁርዓን አንቀፅ ይህ ነበር።
إِن تُعَذِّبْهُمْ فَإِنَّهُمْ عِبَادُكَ ۖ وَإِن تَغْفِرْ لَهُمْ فَإِنَّكَ أَنتَ الْعَزِيزُ الْحَكِيمُ

[ ሱረቱ አል-ማኢዳህ - 118 ]
«ብትቀጣቸው እነርሱ ባሮችህ ናቸው፡፡ ለነርሱ ብትምርም አንተ አሸናፊው ጥበበኛው ነህ» (ይላል)፡፡
ያ አላህ! ይህ እኮ ለእኔ፣ ላንተ፣ ላንቺ እና ለሁላችንም የተደረገ ዱዓቸው ነው። ረሱሉላህ አንዲትም ቀን ለእኛ ዱዓ ሳያደርጉ አያሳልፉም ነበር። በአንዲትም ዱዓቸው ውስጥ ለእኛ ለህዝቦቻቸው ዱዓ ሳያደርጉ አያነጉም። ረሱሉላህ ለኡመታቸው ያላቸው ፍቅር እና ርህራሄ ስትመለከቱ አትገረሙም ዎይ?
ወላሂ እኛ እኮ ለአንደበት ቀላል የሆነውን ሰለዋት ማውረድ ከባድ ነገር ስናደርገው ልናፍር ይገባናል። ረሱሉላህ ከእንቅልፋቸው ተነስተው፣ እረፍታቸውን ሰውተው፣ ያውም እያነቡና እየተንሰቀሰቁ ኡመቴ ኡመቴ ይላሉ ስለኛ! እኛስ? ምነዋ ፍቅራችን ፉከራ ብቻ ወረሰው! ምነዋ የምር ወዳጃቸው መሆን አቃተን!
ስለእኛ በጣም ሲጨነቁ አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ በህዝቦችህ እናስደስትሀለን፣ አናስከፋህም! አላቸው። ያ አላህ! አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ለነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ባለው ፍቅር አትገረሙም ዎይ?
ረሱሉላህ ዱዓ እንዳደረጉላችሁ ስታውቁ ሀሴት አታደርጉም ዎይ?
እናንተ ያመናችሁ ሆይ ሌት ተቀን በዱዓቸው የማይዘነጓችሁ ነብይ ላይ ሰለዋት ለማውረድ እንደምን ሰነፋችሁ? እናንተ አማኞች ሆይ ሰለዋት አብዙ፣ በሰለዋትም ልቦቻችሁን አፅዱ! ሰለዋት እያደረጋችሁም ፁሙ። »
[አብዱልሀኪም ሰፋ]
:
@Venuee13
@Venuee13

1 month, 2 weeks ago

#ዝክረ_ክብር ②②
:
« ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ኡሁድ ላይ ከደረሰባቸው ጉዳትና በመካ በቁረይሾች ከደረሳባቸው እንግልትና ስቃይ በላይ አንድ ቦታ ላይ ልባቸው እጅጉን አዝኗል። የምዕመናን እናት የሆኑት እናታችን አዒሻ ቢንት አቡበከር ለነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለው ጠየቋቸው። ከኡሁድ ቀን ይበልጥ የከፋ ቀን አጋጥሞዎት ያውቃልን? ረሱሉላህም እንዲህ ብለው መለሱ። ከወገኖችሽ ብዙ ስቃይ ደርሶብኛል። ይበልጥ አስከፊው ግን የዐቀባህ ዕለት የገጠመኝ ነው። ዐቀባህ ተብላ የተጠቀሰችው ጧኢፍ እንደሆነች ልብ ይሏል።
አዎ በእርግጥም የጧኢፍ ውሎ እጅጉን መራር፣ ልብን የሚያደማ፣ ተስፋ አስቆራጭ ውሎ ነበር። ለምን የአላህ መልዕክተኛ ወደ ጧኢፍ መሄድን መረጡ ከሚለው እንነሳ።
ጧኢፍ ለቁረይሾች ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት ቦታ ነች። ከዚህ ቀደም ቁረይሾች ጧኢፍን ለመውረር ዘምተው ነበር። ዋጂ የተሰኘው ሸለቆ ሲደርሱ የጧኢፍ ህዝቦች ፍርሀት ስላደረባቸው ከቁረይሾች ጋር በአጋርነት ተስማሙ። ከዚህ ስምምነት በኋላ ነበር የመካ ባለጸጎች በጧኢፍ ንብረት ማፍራት የቻሉት። የመካ ሙቀት እጅጉን ሲያይል ወደ ጧኢፍ በመሄድ ያሳልፉ ነበር። ጧኢፍን የተቆጣጠሯት በኑ ማሊክ እና አል አሕላፍ ይባላሉ። ከጥንት ጀምሮ እዚያ የሰፈሩ ስለነበር መንበር ስልጣኑ በእጃቸው ሆነ። እነዚህ ጎሳዎች የኢኮኖሚ አቅማቸውን ተጠቅመው ጧኢፍን መቆጣጠር ቢችሉም ከውጪ ወራሪዎች ጧኢፍን ለመከላከል የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም። ለዚህም ሲባል ጧኢፍ ህልውናዋ የቆመው ያጠቁኛል ብላ ከምታስባቸው ጠላቶቿ ጋር በመስማማት ነበር። የደህንነት ስጋት ስለነበረባቸው ሁለቱ የጧኢፍ ጎሳዎች በኑ ማሊክ ከሃዋዚን ጎሳ ጋር፣ አል አሕለፍ ደግሞ ከቁረይሾች ጋር የየአጋርነት ስምምነት መሰረቱ።
ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ይህ ስምምነታቸው በፍርሀት ላይ እንጂ በመተማመን ላይ ያልተመሰረተ ስለሆነ በቀላሉ ውሉ ሊፈርስ እንደሚችል ጠንቅቀው ያውቃሉ። የጧኢፍ ህዝቦች እስልምናን ቢቀበሉ ቁረይሾች ስትራቴጂካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸው በቀጥታ ስለሚያጡ እነሱን በኃይል ለመገዳደርና ሙስሊሞችም በዚህች ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ባላት ምድር እስላማዊ መንግስት በመመስረት መልዕክቱን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማዳረስ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጠርላቸው ረሱሉላህ ስለተረዱ ነው ወደ ጧኢፍ ያቀኑት። ታድያ ጉዟቸው በይፋ ሳይሆን በምስጢር ነበር። ይህም የሆነበት ምክንያት ቁረይሾች ካወቁ ግፍና በደላቸው እንዲሁም የበቀል ዱላቸውን እንዳያሳርፉባቸው ስለሰጉ ነው።
መካ ለቀው ሲሄዱ አብሯቸው የነበረው ዘይድ ኢብኑ ሓሪሳ ብቻ ነበር። በቅድመ ኢስላም የጉዲፈቻ ልጃቸው ስለነበር ማንም ከእሳቸው ጋር ቢመለከተው ለጉዞ እየሄዱ ነው የሚል ጥርጣሬን አይፈጠርበትም። ዘይድ የረሱሉላህ የቅርብ ቤተሰባቸውና ታማኝ ስለነበር አብሯቸው ተጓዘ። አድካሚውን ጉዞ ተጉዘውም ጧኢፍ ደረሱ። ኢብን ሂሻም ስለ ክስተቱ ይህን ከትበዋል
‹ ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ጧኢፍ እንደ ደረሱ የሠቂፍ ጎሳ ዋና ሹሞች ወደ ነበሩት ሰዎች ነበር የሄዱት። እነርሱም ሶስቱ ወንድማማቾች ዐብድ ኢብን ዓምር ኢብን ዑመይር፣ መስኡድ ኢብን ኡመይር እና ሐቢብ ኢብን አምር ኢብን ዑመይር ናቸው። ከሶስቱ በአንደኛቸው ቤት ከቁረይሽ የጁምሕ ጎሳ የምትወለድ ሴት ነበረች። የዓምር ልጆች(ወንድማማቾቹና ዘመዶቻቸው) የቁረይሽ ዐረቦችን ተጽዕኖ በመስጋት ስጋት አድሮባቸው ነበር። ስለሆነም ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ላቀረቡላቸው ጥሪ መልስ አል ጡም። ከዚያ ይልቅ ከእነሱ የማይጠበቅና የቂላቂልነት ባሕሪ የሚንጸባርቅበት ጠባይ ነበር ያሳዩዏቸው። ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ከነርሱ ምንም ተስፋ እንደሌለ ሲገነዘቡ ኢስላምን መቀበል ባትችሉ እንኳን ቢያንስ በእኔና በእናንተ መካከል የተደረገውን ይህን ንግግር ምስጢር አድርጋችሁ ያዙልኝ በማለት ተሰናብተዋቸው ሄዱ። ›
የዓምር ቤተሰቦች ግንኙነታቸውን በምስጢር ከመያዝ ይልቅ ዕብዶቻቸውን፣ ባሮቻቸውንና ልጆችን በማሰማራት ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለምን እየተሳደቡ ድንጋይ እንዲያዘንቡባቸው አደረጉ። የሲራ ሊቃውንቶች የጧኢፍ ክስተትን ሲገልፁ ሁሉም ከዳርና ከዳር ረጅም ሰልፍ ሰርተው በመሀል ረሱሉላህና ዘይድ እንዲያልፉ አድርገው ሁሉም ተራ በተራ ያለማቋረጥ፣ ይሰድቧቸው፣ ድንጋይ ይወረውሩባቸው ነበር ይላሉ። በዚህም ሳቢያ የነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ተረከዝ በደም ተጨማልቆ በጣኢፍ ምድር ላይ ፈሰሰ። ዘይድ በሁለመናው ለረሱሉላህ ሊከላከልላቸው ታገለ፣ እርሱም ቆሰለ ደማ። እያሳደዱም የዑትባ እና ሸይባህ ኢብን ረበሀዓህ የወይን ማሳ እስኪገቡ ድረስ አሰቃዩዋቸው። የአላህ ነብይ እንያ ባለ ታላቅ ጠባይ በአንድ ዛፍ ጥላ ስር ከዘይድ ረድየላሁ አንሁ ጋር አረፍ አሉ። በዚያ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታና በስቃይ ላይ ሆነውም የሚከተለውን ዱዓ አደረጉ።
‹ አላህ ሆይ! የአቅሜን ደካማነት፣ የብልሀቴን ጥቂትነት፣ ከሰዎች ዘንድም የተናቅሁ መሆኔን ላንተ ስሞታ አቀርባለሁ። የአዛኞች ሁሉ አዛኝ የሆንከው የደካሞች አምላክ ሆይ! ለማን ትተወኛለህ? ለሚጠሉኝ ባእዶች? ወይስ ጉዳዬን ሁሉ በቁጥጥሩ ስር ላደረገ ጠላቴ? አንተ ካልተቆጣህብኝ ግድ የለኝም። ማርታህና ይቅርታህ ይበልጥብኛል። ቁጣህ እንዳይሰፍርብኝ ጨለማን በገሰስክበት ብሩህ ማንነትህ ይህችንም ሆነ መጪውን ዓለም ባቆምክበት ኃይልህና ችሎታህ እጠይቅሀለሁ። ውዴታህንም እስካገኝ እደክማለሁ። መላም ሆነ ኃይል ባንተ ቢሆን እንጂ የለም። ›
በአላህ እምላለሁ በዚህ ዱዓቸው ውስጥ ምን ያህል እንግልቱና ስቃዩ ልባቸውን እንዳደማው ይስተጋባል። በአላህ እምላለሁ ልበ ደንዳና ካፅሆነ በቀር ይህን ዱዓቸውን በጥልቀት ላስተነተነ ልቡ ይራራል። የጧኢፍን መራራ ውሎ፣ እንግልታቸውን በዚህ ዱዓቸው ውስጥ ለሚያስተውሉት ቁልጭ ብሎ ይታያል። ያ አላህ እንዲያ በስቃይ፣ ክብራቸውን ያጎደፉትን አላህ አጥፋልኝ አለማለታቸው፣ አለመራገማቸው አይገርማችሁም? እንዴት ያለ ልበ መልካም የሆኑ ነብይ ናቸው ግን? ያ አላህ እንዴት ያሉ ልበ ሩህሩህ ቢሆኑ ነው ግን? በእርግጥም ከአላህ በቀር ረሱሉላህን በተገቢው መልኩ በሚመጥናቸው ልክ ሊገልፃቸው የሚችል የለም። በእርግጥም አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ የማለቱ ምስጢር እጅግ እጅግ ጥልቅ ከመሆኑ ጋር የማያልቅ መሆኑ ያስገርማል።
እናንተ አማኞች ሆይ የልበ ሩህሩህ ደጉ ባለ ታላቅ ጠባይ የሆኑት ነብይ ተከታይ ሆናችሁ ሳለ እንደምን መተዛዘን ከበዳችሁ?
እናንተ አማኞች ሆይ ልባችሁ በእዝነት ይሞላ ዘንድ ሰለዋት አብዙ። ሰለዋት በማድረግም ፁሙ። »
[አብዱልሀኪም ሰፋ]
:
@Venuee13
@Venuee13

1 month, 2 weeks ago

#ዝክረ_ክብር ②①
:
« ጠቢብ ወግ አዋቂ፣ አንደበተ ርቱዕ የሆኑት ነብይ በምን ወቅት፣ በምን ሁኔታ እንዴት ብለው ምን መናገር እንዳለባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። ምንም ቢናገሩ የሚደመጡ ሆነው ሳለ እሳቸው ግን ለአድማጮቻቸው፣ ለተከታዮቻቸው ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር። ኢብኑ መስኡድ ሲናገሩ ነብዩ ሰለላሂ አለይሂ ወሰለም ሊመክሩን ከፈለጉ ትክክለኛውን ጊዜ በጥንቃቄ ይመርጡ ነበር። ይህን የሚያደርጉት እንዳንሰላች ስለሚፈሩ ነው። ይላሉ።
እንግዲህ አንደበታቸው ሁሉ ማር ወለላ የሆነው፣ ምንም የማይጠገቡት ነብይ ምን ያህል ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ልብ አድርጉ። ወላሂ ሲተናነሱ እኮ የፍጥረታት ሁሉ በላጭ አይመስሉም እኮ! መገን የአላህ ነብይ!
ጃቢር ኢብኑ አብደላህ እንዲህ ይላል። ‹አንድ ዕለት የአላህ መልዕክተኛ ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም በገበያ በኩል ሲያልፉ አንዲት ጆሮዎቿ ትናንሾች(የተቆረጡ) የሞተች የፍየል ግልገል ተመለከቱ። ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም በጆሮዋ አንጠልጥለው ካነሷት በኋላ እንዲህ አሉ። ይህችን ፍየል በአንድ ዲርሀም የሚገዛኝ ማነው?
ይህችን በምንም ዓይነት ዋጋ አንገዛም ምን ታደርግልናለች? ተባሉ። አትፈልጓትም? አሉ ረሱሉላህ። በአላህ ይሁንብን በሕይወት ያለች ብትሆን እንኳን ጆሮዎቿ ትናንሾች በመሆናቸው ጎደሎ ናት ከሞተች በኋላማ ምን ዋጋ አላት? አልናቸው። ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለምም እንዲህ አሉ። በአላህ ይሁንብኝ ይህች ዓለም በአላህ ዘንድ ያላት ስፋራ ከዚህች ፍየል ያነሰ ነው። ›
ረሱሉላህ ሁሉ ነገራቸው የሚደመጥ፣ የሚማርክ፣ የሚስብ ሆኖ እንኳ ሲናገሩ ሁኔታዎችን ይመርጡ ነበር። ለዚህ ነው አንዲትም ንግግራቸውም ሆነ ተግባራቸው ባልደረባዎቻቸው የማያዛንፉት፣ ፍፁም በልበ ሙሉነት በደስታ የሚቀበሉት። ሃቢቡላህ ሁሉ ነገራቸው ጀነት ሆኖ ሳለ ሰዎች እንዳይሰላቹባቸው ብለው ከተጨነቁ እኛስ?
እናንተ አማኞች ሆይ የእንያ መወሳታቸው የተላቀው፣ የፍጥረታት ዕንቁ፣ አይጠገብ ጠቢብ ወግ አዋቂ ነብይ ተከታዮች ሆናችሁ ሳለ እንደምን እዝነት ያልታከለበት ንግግርን ለወንድሞቻችሁ መናገር ቻላችሁ? እናንተ አማኞች ሆይ አንደበታችሁን በሰለዋት አለስልሱ። በባለ ታላቅ ጠባይ ላይም ሰለዋት እያወረዳችሁም ፁሙ።»
[አብዱልሀኪም ሰፋ]
:
@Venuee13
@Venuee13

1 month, 3 weeks ago

#ዝክረ_ክብር ①⑦
:
« ሐሰት እጅጉን አይሎ፣ መሳርያ ታጥቆ፣ በትዕቢት ተወጥሮ ወደ በድር ተመመ። ሐቅ ለጦርነት በወጉ ሳይሰናዳ ከታጠቀው ሐሰት ጋር ሊዋጋ ተገደደ።
ሐሰትን ትምክህተኛው፣ ወራዳው ግዙፉ አቡጀህል መራው፣ ሀቅ ደግሞ በሀቅ የተላኩት ታማኙ ነብይ መሩት። ከፍልምያው ሜዳ ሀቅ እና ባጢል ተፋጠዋል። ባጢል በኩራት ሙባረዛህ ወይም የአንድ ለአንድ ፍልምያ ጠየቀ። በባለሀቆቹ ወድያው ቅስሙ ተሰብሮ ወደ ጀሀነሙ ገሰገሰ። ኢማን ከክህደት ጋር ተፋጠጡ። ክህደት ፈርጠም እንዳላላ በኢማን ፊት ሟሸሸ።
« አሀዱን አሀድ… አሀድ… አሀድ! » የባለ ሀቆች ድምፅ ነው። የተከበሩት ነብይ፣ የጀግኖቹ ሁሉ ጀግና ከላያቸው የለበሱት ኩታ እስከሚወድቅ ድረስ እጆቻቸውን ከፍ አድርገው አሸናፊ ወደ ሆነው አላህ ተማፀኑ። አፍቃሪው ሲዲቅ ግራ ግብት ቢለው፣ ሁኔታቸውን እየተመለከተ አንቱ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ ይበቃዎታል! እያለ ይከተላቸዋል። ጅብሪል ብስራት ይዞ ከተፍ አለ። ከጦሩ አውድማ ገባ። ባለ ታላቅ ጠባይ ልባቸው ተደሰተ። ሀቅ ባጢል ላይ ክንዱን አሳረፈ። የክህደት ወኔ ራደ። የሐሰት ግርማ ሞገስ ኮሰሰ። የባጢል ድንፋታ ጋብ አለ። የኡማው ፊርዓውንም ተገደለ። ሀቅ አሸነፈ። የጊዜ ሚዛን ተለወጠ። በስነ ፍጥረት ውስጥ እጅግ ውብ የሆነው ድምፅ ተሰማ። ሁሉም «አላሁ አክበር! አላሁ አክበር! አላሁ አክበር! » ዓለም ይህን ውብ ድምፅ ከባለ ሀቆቹ አንደበት አደመጠ።
ረሱሉላህ ባልደረዎቻቸውን በምን አይነት የስብዕና ከፍታና፣ የሞራል ልዕልና እንዳነፇቸው ምስክር የሚሆኑ አንድ ሁለት ምሳሌ እናንሳ።

አል ሐፊዝ ኢብን ሀጀር አላህ ይዘንላቸውና አል ኢስባህ በተሰኘው መፅሀፋቸው አንድ ነገር ከትበዋል። ሙስሊሞች ወደ በድር ሊዘምቱ ሲነሱ ሰዕድ ኢብን ኸይሰማህ እና አባቱ ረድየላሁ አንሁም ተወዛገቡ። ከሁለቱ አንዱ ብቻ ነበር መዝመት የሚችለው። ምክንያቱም ቤተሰባቸውን የሚንከባከብላቸው ስለሌለ ነበር። በዚህም ምክንያት ዕጣ ተጣጣሉ። ዕጣው ለሰዕድ ስለወጣለት ከነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ጋር ለመሄድ ተዘጋጀ። ይሁን እንጂ ሸሂድ(ሰማዕት) መሆን የናፈቀው አባቱ ልጄ ሆይ የዚህችን ዕለት ዘመቻ ለእኔ ተውልኝ አለው። ሰዕድ በዚህ ጊዜ አባቴ ሆይ ይህ የጠየቅኸኝ ነገር ከጀነት ውጪ ቢሆን ኖሮ አደርገው ነበር አለው። ሰዕድ ይህን ከተናገረ በኋላ ከረሱሉላህ ጋር ወደ በድር ዘምቶ ሸሂድ ሆነ። አላህ ለአባቱ በኡሁድ ጦርነት ሰማዕትነትን ወፈቀው። ረሱሉላህ ስብዕናውን ያነፁት ሰው ሞት እንዴት ሊያስፈራው ይችላል? ፍርሀትስ እንዴት ሊጠጋው ይችላል? ጉዳዩ የመጪው ዓለም ነው። አባትና ልጅ በመጪው ዓለም ስኬታማ ስለመሆን ነው ያወጉት። ምድርን ሙታን ተብሎ ከመሰናበት ህያው ተብሎ አልፎ በፊርደውስ መደላደልን ስለመከጀል ነው ያወጉት። አላህም ሁለቱንም ህያው አደረጋቸው። እነዝያ በሴቶች ለመደነቅ፣ በባለቅኔዎች ለመሞካሸት፣ በባለስልጣኖች ለመወደድ ብለው ሲዋጉ፣ ሲጋደሉ የነበሩ ሰዎች ሁሉን እርገፍ አድርገው ትተው ሸሂድ ሆነው አላህን ለማግኘት በመፎካከራቸው ውስጥ ረሱሉላህ በውስጣቸው የገነቡት ስብዕና ስታስቡ አትደነቁም ዎይ? መገን የአላህ ነብይ!
ረሱሉላህ ወደ በድር ሲያመሩ የዘማቾቹን ሰራዊት ሁኔታና የእያንዳንዱን ተዋጊ ብቃት ለመገምገም ቆም ብለው መቃኘት ጀመሩ። የዑመይር ረድየላሁ አንሁ ወንድም የሆነው ሰዕድ ኢብን አቢ ወቃስ ስለ ወንድሙ እንዲህ ብሏል። ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም የተዋጊዎቹን ሁኔታ ሲገመግሙ ዑመይር ራሱን ከእይታቸው ለመደበቅ ሲሞክር ተመለከትኩት። ከዚያም ወንድሜ ሆይ! ምን ሆነሀል? በማለት ጠየቅኩት። እርሱም የአላህ መልዕክተኛ ካዩኝ ገና ልጅ ነው ብለው እንዳይመልሱኝ ፈርቼ ነው። እኔ መዋጋት እፈልጋለሁ። ምናልባት አላህ ሸሂድነትን ያጎናፅፈኝ ይሆናል። አለኝ። መቼም ከረሱሉላህ እይታ ሊደበቅ አልተቻለውም። ረሱሉላህ ተመለከቱትና ወደ መዲና እንዲመለስ አዘዙት። ዑመይር በዚህ ጊዜ ሸሂድነትን ናፍቆ በአላህ መንገድ ላይ ለመዋጋት ባለመቻሉ አለቀሰ። ልበ ሩህሩሁ እንስፍስፉ ነብይ ሁኔታውን ካዩ በኋላ እንዲዋጋ ፈቀዱለት። በጀግንነትም ተዋጋ። አላህም የፍላጎቱን ሞልቶለት ሸሂድ ሆነ።
ይህን ስብዕና እንዴት ሊያገኝ ቻለ ካላችሁ ምክንያቱም የስብዕናው ቀራፂ ባለ ታላቅ ጠባይ ስለሆኑ ነው። የበድር ጦርነት ወቅት የነብዩ ባልደረቦች እንዴት ብለው በጀግንነት ሲዋጉ እንደነበር ስታጤኑ እንደው ረሱሉላህ ምን አይነት ስብዕና ቢኖራቸውና በምን መልኩ ቢገስፇቸው፣ ቢያስተምሯቸው ነው ለዚህ የበቁት ትላላችሁ። በእያንዳንዱ የነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ባልደረባዎች ውስጥ የታየው ጀግንነት የረሱሉላህ ጀግንነት ነፀብራቅ ነው። ጀግና ብትጠሩ ከረሱሉላህ አይቀድምም፣ አዛኝ ብትፈልጉ ከረሱሉላህ የሚበልጥ አታመጡም። ጀግናም አዛኝም ብታፈላልጉ ከረሱሉላህ የበለጠ አታገኙም። ምሉዕ የሆነ ከሁሉም የላቀ ፍጥረት ለመዘርዘር ብትሞክሩ ነብዩ ሙሀመድ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ብቻ ብላችሁ ታቆማላችሁ። እናንተ አማኞች ሆይ የረሱሉላህ ኡመት በመሆናችሁ አትደሰቱም ዎይ? የረሱሉላህ ተከታይ ሆናችሁ ሳለ አንገታችሁን ቀና አታደርጉም ዎይ? እናንተ አማኞች ሆይ ነፍስያችሁን ታገሉ፣ ለዚኛውም ለዚያኛውም ዓለም የሚጠቅማችሁን ሰለዋት አብዙ። በሁለገቡ ምሉዕ ነብይ ላይ ሰለዋት እያወረዳችሁ ፁሙ። »
[አብዱልሀኪም ሰፋ]
:
@Venuee13
@Venuee13

1 month, 3 weeks ago

#ዝክረ_ክብር ①⑥
:
« መዲና ይህን ያህል ለምን ተወደደች ከተባለ ረሱሉላህ ስለወደዷት ነው። የረሱሉላህ ዱዓ ስላላት ነው መፈቀሯ፣ የባለ ታላቅ ጠባይ የስብዕና ማዕከል መሆኗ ነው መናፈቋ፣ የረሱሉላህን ትዝታ መያዟ ነው መወደዷ፣ ረሱሉላህን ሽሽግ አድርጋ በጉያዋ ማቀፏ ነው ልቅናዋ። መዲና እኮ ረሱሉላህ ሳይገኙባት በፊት የማትመች ከተማ ነበረች። በወባ በሽታዋ የምትታወቅ ስክነት የራቃት ከተማ ነበረች። የሥሪብ የሚለው ስሟ ገናና ነበር ከሌሎች ስሞቿ የበለጠ። ባለ ታላቅ ጠባይ ከደረሱ ወዲህ የየሥሪብ ዕጣ ፈንታ ተቀየረ። ሰዎች መዲነቱ ረሱሉላህ(የረሱል ከተማ)፣ አል መዲና አልሙነወራህ፣ ጠይባ አሏት።
በእርግጥም መዲና… የአማኝ ህልመኞች ምስጢር፣ የቀልብ አደብ የሥክነት እንባ የሚገኝበት ጸዓዳ የሩህ ቀዬ! ዓሊምም ጃሂልም የሚናፍቀው ረቂቅ የእዝነት እቅፍ!
የአላህ መልዕክተኛ ከባልደረባዎቻቸው ጋር ከመካ ተሰደው መዲና ሲደርሱ በመዲና የነበረው ወረርሺኝ ብዙዎቹን ለህመም ዳረጋቸው፣ ሲዲቁ፣ ቢላል ሳይቀር በወባ በሽታ ተጠቁ። ሁሉም ባልደረባዎቻቸው በመዲና መኖር ከብዷቸው መካ ይበልጥ ይናፍቃቸው ጀመር። ይሄኔ ነው እንግዲህ የመዲናን መፃኢ እድል የቀየረ ዱዓ ሀቢቡላህ ያደረጉት። እንዲህም አሉ
አላህ ሆይ መዲናን መካን እንደምንወዳት ወይም በበለጠ ሁኔታ እኛ ዘንድ ተፈቃሪ አድርጋት። አላህ ሆይ! በቁናዋና በእፍኛዋ ውስጥ በረከትን አድርግ። በውስጧ ያለችውንም ትኩሳት(ወረርሺኝ) ወደ ጁሕፋህ አዛውር።
ከዚህ ወዲህ ነገር ዓለሙ ተቀየረ መዲና በፍቅር ተሞሸረች፣ በናፍቆት ተገመደች፣ በስክነት ታጀበች። መወደድ፣ መፈቀር፣ መናፈቅ የማይለቋት መዓዛዋ ሆኑ።
ረሱል የወደዱትን አላህ ሲያልቀው በእውን ለማየት ካሻችሁ መዲና ምልክት ትሁናችሁ። ቀጣፊው ደጃል እርሙን መዲናን አይረግጥም። የአላህ ነገር መቼም ድንቅ ነው።
መዲና ውስጥ የትኛውም ፈተና ቢገጥም በውስጧ ታግሶ መኖር በራሱ ትሩፋት አለው። ሰዕድ ኢብን አቢ ወቃስ ረድየላሁ አንሁ ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም እንዲህ ማለታቸውን ያወሳል። ሰዎች የሚያውቁ ቢሆኑ ኖሮ መዲና ለመኖሪያነት በላጭ ናት። አንድ ሰው እርሷን ለቆ የሚወጣ የለም አላህ ከርሱ በተሻለ ሰው ቢተካው እንጂ። እንዲሁም በመከራና በፈተና ጊዜ እርሷ ውስጥ ፀንቶ የሚቆይ የለም በፍርዱ ቀን የእኔን አማላጅነት ወይም ምስክርነት የሚያገኝ ቢሆን እንጂ! ብለዋል ረሱሉላህ። መዲና… የመናፈቋ ምስጢር ሀቢቡላህ ናቸው።
ረሱሉላህ ስለሚወዷት፣ ስለወደዷት መዲና በውስጧ የሚሞት ሁላ ትሩፋት ያገኛል። የነብዩ ባልደረቦች ሳይቀር በመዲና መሞትን ለአላህ ተማፅነዋል። ኡመር ኢብኑል ኸጣብ አላህን እንዲህ በማለት ይለምኑ ነበር። አላህ ሆይ! ሰማዕት አድርገህ ግደለኝ። ሞቴንም በመልዕክተኛህ አገር ላይ አድርግልኝ። አላህ ልመናቸውን ተቀበላቸው። በረሱሉላህ ሀገር ሰማዕት ሆነው አለፉ።
ረሱሉላህ የወደዱትን አላህ ይበልጥ ዝንት እንዲወደድ አደረገ። የመዲና ነገር መቼም ተወርቶም አያልቅ። ልብ ሰከን፣ አቅል ሰብሰብ፣ ሩህ እርግት ይልባታል። ለምን ቢሉ ለዓለማት እዝነት እንዲህ ብለዋልና። በእርግጥም እርሷ(አል መዲናህ) ጦይባህ(ቆንጆ) ስትሆን ልክ እሳት ከብር ላይ ቆሻሻውን (አንጥሮ) እንደሚያስወግድ ሁሉ ኃጢአትን ታስወግዳለች።
አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ረሱሉላህ መዲናን ሲወዷት በመዲና እና በነዋሪዎቿ ላይ ተንኮል ከሚሸርቡ ሰዎች እንዲጠበቁ አደረገ። ለዓለማት እዝነት የተላኩት፣ መዲናን የሚወዱት ነብይ እንዲህ አሉ። ማንም በአል መዲናህ ሕዝቦች ላይ ተንኮል አይሸርብም ልክ ጨው ውሀ ውስጥ ገብቶ እንደሚሟሟው ሁሉ ማሙቶ የሚቀር ቢሆን እንጂ!
አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ለረሱሉላህ ባለው ፍቅር አትገረሙም ዎይ?
መዲና የናፍቆት ማዕድ፣ የክቡር እንባ ገበታ፣ ሰማይና ምድርሽ በተውሒድ ሰንደቅ አውለብላቢው መዓዛ ታውደዋል። ነብዩን ከመናፈቅ ጋር ተናፍቀሻል። የረሱሉላህ ዱዓ ስላለሽም ተወደሻል።
መዲናን አለመናፈቅ፣ አለመውደድ ለአንድ አማኝ አይቻለውም። ከተቻለው በእርግጥም ልቡ ታሟል! ረሱሉላህ የወደዱትን አልወደደምና አላህ ይዘንለት። ከያዘውም በሽታ አላህ ይፈውሰው።

ጌታዬ በዚያች በመውደድ ከተማ፣ በተቀደሰችዋ ምድር ላይ አስገኘን። የአልፋሩቅን ዱዓ ለኛም ይግጠመን። ጌታዬ ረሱሉላህ በወደዷት ከተማ ሳንዘልቅ ዱንያን አንሰናበት። በናፍቆት ቀዬ ክቡር እንባን አድለን። እናንተ አማኞች ሆይ በስነ ምግባር ጠበብቱ፣ በመዲናው ሚስክ፣ ለዓለማት እዝነት ተደርገው በተላኩት ባለ ታላቅ ጠባይ፣ የመዲና የመናፈቅና የመወደድ ምስጢር በሆኑት በረሱሉላህ ላይ ሰለዋት እያወረዳችሁ ፁሙ። »
[አብዱልሀኪም ሰፋ]
:
@Venuee13
@Venuee13

1 month, 3 weeks ago

« March 26 2018 በዛሬው ቀን Venue በሚል ሀሳቦችን የማካፍልበት ማስታወሻ ወደ ማህበራዊ ሚድያው(ቴሌግራም) ብቅ አለ። እንደ አላህ ፍቃድ የተለያዩ ሀሳቦችን እያነሳን አወጋን። በዚሁ በቬኑ ቻናል ሰበብ የምወዳቸውና የማከብራቸውን ሰዎች አገኘሁ። በነገራችን ላይ ከነጅዋ ጋር የተዋወቅነው በቬኑ ቻናል ሰበብ እንደሆነ ታውቁ ይሆን? የቀድሞው የተዘጋው የቬኑ ቻናል እና አሁን ያለው ቻናል በተወሰነ መልኩ…

2 months ago

#ዝክረ_ክብር
:
« ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ከመምህራን ሁሉ ምርጡ፣ ትልቅ ወኔ አስታጣቂ፣ አበረታች፣ ለትልቅ ዓላማ አዘጋጅ ናቸው። ባልደረባዎቻቸው በላጭ ትውልድ ለመሆናቸው ዋነኛ ምክንያት የስብዕናቸው ሞራጅ እና አስተካካይ ረሱሉላህ ስለሆኑ ነው። ረሱሉላህን ለመኻደም የሚሽቀዳደሙት ዓላማቸው ሩቅ እና ዘውታሪ ስለነበር ነው። ረሱሉላህን ይበልጥ ከተወዳጁ በስተመጨረሻ ምን እንደሚያገኙ በደንብ ስለገባቸው ነው።
ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም በመዲና መስጂዳቸው ሲሰራ ከአጠገቡ መሳኪኖች፣ ምንም መሔጃ የሌላቸው፣ አቅመ ደካማዎች፣ የለት ቀለባቸውን እንኳ መስፈር የማይችሉ የጀነት ባለፀጋዎች ግና በዱንያ ህይወት ከንብረት ምንም የሌላቸው ባልደረባዎቻቸው የሚሰባሰቡበት፣ እንደቤታቸው በነፃነት የሚኖሩበት ማረፍያ አሰርተዋል። በዚህ መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አህሉ ሱፋ በሚል ይታወቃሉ። አቡ ኹረይራ ረድየላሁ አንሁ ከአህሉ ሱፋ ውስጥ እንደነበር ልብ ይሏል። ታድያ እንያ ልበ ሩህሩህ ደግ ነብይ ምንም ነገር ሲሰጣቸው ከአህሉ ሱፋዎች ጋር ሳይካፈሉ አይቀምሱም። ከእነዚህ አህሉ ሱፋ ከተሰኙት የነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ሰሀባዎች ውስጥ ረቢዓ ኢብኑ ካዕብ አል አስለሚ ረድየላሁ አንሁ አንዱ ነው። ምንም የሌለው ያጣ የነጣ ባልደረባቸው ነው። ረቢዓ ረሱሉላህን ለመጀመርያ ጊዜ የተመለከታቸው ቅፅበት ሲናገር
ገና እንደተመለከትኳቸው ሁሉ ነገሬ በእርሳቸው ፍቅር ተሞላ ይላል። መቼስ የምር አፍቃሪ ያፈቀረውን ለማየት፣ የሚያስደስተውን ነገር ለማድረግ ይተጋ የለ ረቢዓም እንዲህ ነበር። ረቢዓህ ረሱሉላህን ለማገልገል ሁሉ ነገሩን ሰጠ። ወደ ህዝቦቹ ቢመለስ የሀገሩ ህዝቦች ይንከባከቡትና የተሻለ የኑሮ ሁኔታ እንደሚኖረው አልጠፋውም። ግና ከሁሉም በላጩን አስቀደመ።
ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም በተፈጥሯቸው ሰዎችን የሚኻድሙ እንጂ ሰዎች እንዲኸቀድሟቸው የሚያስቸግሩ ወይም የሚፈልጉ አይደሉም። ረቢዓህ ይህ ገብቶታል። አይናቸው የሆነች ቦታ ካረፈ ወድያው ሊያቀርብላቸው ይጣደፋል። አንድ ቀን ረሱሉላህ ሊሰግዱ ሲነሱ ረቢዓህ ቀልጠፍ ብሎ ውዱዕ የሚያደርጉበትን ውሀ አቀረበላቸው። ረሱሉላህ ረቢዓን እየተመለከቱት አንተ ረቢዓህ የፈለግከውን ጠይቀኝ ላድርግልህ አሉት። ያ ያጣ የነጣው፣ ችግርተኛ መሆኑ በሁሉም የሚታወቀው ረቢዓህ ሩቅ አለመ። ስብዕናውን የገሩትን ነብይ ዝንት አፈቀረ። እንዲህም አላቸው። አንቱ ያ ረሱለላህ ካንቱ ጋር በጀነት መጎራበት ነው የምፈልገው አላቸው። ሃቢቡላህ መልሱን አዳመጡና ከኔ አቅም በላይ የሆነን ነገር ጠየቅከኝ፣ እንግዲያውስ በሱጁድ አግዘኝ አሉት። ሩቅ ዝንት የሚዘልቅን ነገር በእርግጠኝነት በልቦናቸው እንዲሰርፅ ያደረጉት ነብይ እንዴት ያለ ስብዕና ቢኖራቸው ነው?
ረሱሉላህ በጅህልና ቀንበር እየተቀበሩ፣ ከሰውነት የማይቆጠሩ የነበሩትን ክቡር የአላህ ፍጥረት የሆኑትን ሴቶች ስብዕናቸውን ያነፁበት መንገድ ያስገርማል። በጅህልና ዘመን ከጅህልና ሳይላቀቁ ሴቶችን የሚንቁት የነበሩት እስልምና ሴቶችን የበላይ ሲያደርጋቸው በእርግጥም ብዙዎች ተገረሙ። ብዙ አስደናቂ ስብዕና ያላቸው ሴት ሰሀባዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዷን ደግ እናንሳ። አሸሂዳ(ሰማዕቷ)
የበድር ጦርነት ወቅት አንዲት ከኸዝረጅ ጎሳ የሆነች የመዲና ሴት ረሱሉላህ ዘንድ መጥታ እንዲህ አለች። አንቱ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ ካንቱ ጋር ወደ በድር ጦርነት እንድሄድ ፍቀዱልኝ፣ አላህ ሸሀዳን እንዲወፍቀኝ እፈልጋለሁ፣ ሰማዕት መሆን እፈልጋለሁ አለች።
ረሱሉላህም ቀሪ ፊ በይቲክ ፈኢነላሀ ተዓላ የርዙቁኪ ሸሀዳ
ከቤትሽ ሁኚ አላህ ሸሀዳን ይወፍቅሻል(ይሰጥሻል) አሏት። ረሱሉላህ ይህን ካሏት በኋላ ይህች ሴት አሸሂዳ በሚል ታወቀች። ሱብሀነላህ በህይወት እያለች ሸሂድ እንደምትሆን እያወቀች ስትኖር።
ይህች ባለ ታላቅ ስብዕና ስሟ ኡም ወረቃ ቢንት አብዱላህ ኢብኑሀሪስ ይባላል። ቁርዓንን በቃሏ የሀፈዘች ነች። ቤቷ የእውቀት እና የጥበብ ማዕከል ነበር። በመዲና ውስጥ መፃፍና ማንበብ ከሚችሉ ሴቶች ውስጥ አንዷ ነበረች። ብዙዎችንም አስተምራለች። ረሱሉላህ ወደሷ ሊሄዱ ሲሉ አሸሂዳን እንጎብኛት ይሉ ነበር። ሁሉም ሰሀባዎች ሰማዕት እንደምትሆን ያውቃሉ፣ ግና እንዴት የሚለው አላህ ብቻ ያውቃል። ሁሉም ግን ሰማዕቷን እንጎብኝ፣ ሰሟዕቷ ጋር እንማር ይሉ ነበር። ከነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ህልፈት በኋላ በኡመር ኢብኑል ኸጣብ የአስተዳደር ዘመን ላይ ሁሌም እንደሚያደርጉት ኡመር ኢብኑል ኸጣብ በምሽት ሲዟዟሩ በቤቷ በኩል ሲያልፉ ድምፇን አልሰሙም። በነጋታው ኡመር እንዲህ አሉ በአላህ ይሁንብኝ ትላንት ምሽት የኡም ወረቃን ቂርዓት አልሰማሁም አሉ። ቤቷ ሔደው ሲመለከቷት ሌቦች ንብረቷን ዘርፈው ተገድላ አገኟት። ኡመርም የአላህ ነብይ እውነት ተናገሩ አሉ። እራሳቸውም ሰላተል ጀናዛውን መርተው ከተሰገደባት በኋላ ተቀበረች። ያቺ በጃሂልያ ዘመን ምንም ክብር ያለነበራት የነበረች እንስት የቁርዓን ሀፊዝ ሆና ትንሽ ትልቁን አስተምራ ሰማዕት ሆና ሙታን ሳትባል ህያው ሆና ወደ አኼራ አቀናች።
ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ባልደረባዎቻቸው የስብዕና ከፍታ ላይ እንዲሆኑ እንዴት አድርገው እንዳነፇቸው አትገረሙም ዎይ? ከነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ጋር በጀነት ለመወዳጀት ፈልጎ ምድራዊ እጦቶችን ሁሉ መርሳትና ናቅ አድርጎ ለመተው በባለ ታላቅ ጠባይ ስብዕና መታነፅ አለበት። የባለ ታላቅ ጠባይ ስብዕና ከስብዕና ጋር መዋሐድ አለበት። አላዋቂ፣ ባስ ሲልም የአላህ የተከበረ ፍጡር ሆኖ ሳለ ተንቆ፣ ተቀብሮ፣ ተዘልፎ ኖሮ ሊቅ እና ሰማዕት ለመሆን በባለ ታላቅ ጠባይ ስብዕና መሞረድ አለበት። በእርግጥም አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ « በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ » ሲላቸው ገና ብዙ ለጥቀን ጠልቀን ስለ ረሱሉላህ አስተንትነን ልንረዳ የሚገባ ነገር እንዳለ አመላካች ነው። ገለፃው ጥልቅ እና ረቂቅ ነውና።

አንቱ የምርጥ ስብዕና ትርጉም፣ አንቱ የመልካም ስነ ምግባር ፍቺ፣ አንቱ የመምህራን ሁሉ ምርጡ፣ አንቱ ባለ ታላቅ ጠባይ አላህ አንቱን ወደውና ፈለጎን ተከትለው በጀነት ከሚጎራበቶ ወዳጆ ያድርገን። ረመዳን ውብ ነው፣ በሰለዋት ሲታጀብ ሰኪናው ሀሴት ይሰጣል። በባለ ታላቅ ጣበይ ላይ ሰለዋት እያወረዳችሁ ፁሙ። »
[አብዱልሀኪም ሰፋ]
:
@Venuee13
@Venuee13

2 months ago

#ዝክረ_ክብር
:
« ረሱሉላህን ለዓለማት እዝነት አድርጎ የላከው፣ አንዲትም ቀን ረሱሉላህ ሳይወሱበት እንዳያልፍ ላደረገው ለዓለማቱ ጌታ፣ የፍቅር ምንጭ ለሆነው ለአል ወዱድ ጥራት ይገባው።
አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ለሚወዳቸው ነብይ ባሮቹ ፍቅራቸውን እስከ ዕለተ ቂያማ እንዲገልፁ አድርጓቸዋል። ወትሮስ ከአላህ የበለጠ ረሱሉላህን ማን አብልጦ ይወዳቸውና! ሁሌም በሰላታችን ላይ በቀን ቢያንስ ለ17 ጊዜ የሱረቱል ፋቲሀን የቁርዓን አንቀፆች እንቀራለን። ከሱረቱል ፋቲሀ አንቀፆች ውስጥ
صِرَاطَ الَّذِينَ أَنْعَمْتَ عَلَيْهِمْ
የሚለውን የቁርዓን አንቀፅ የቁርዓን ተፍሲር ልሒቃን ሲተረጉሙት
የእነዚያን በነርሱ ላይ በጎ የዋልክላቸውን ማለት ነብያቶች፣ አሹኸዳዕ(በአላህ መንገድ ላይ መስወዓት የሆኑ)፣ ሲዲቆች(እውነተኞች)፣ አሷቢሪን(ታጋሾች)፣ አል ሙተወኪሊን(በአላህ ላይ ፍፁም የሚመኩት)፣ የነብዩ ባልደረባዎች፣ ለመግለፅ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ከሁሉም ይህ አንቀፅ አብልጦ የሚገልፀው፣ አላህ በጎ ከዋለላቸው የመጀመርያው ረድፍ፣ የበላይ ቁንጮ ላይ የሚገኙ ረሱሉል አሚን ሰለዋቱ ላሂ አለይሂ ወሰለም ናቸው። አንድ አማኝ በእያንዳንዱ ሰላቱ ውስጥ በረሱሉላህ መንገድ ላይ እንዲያፀናው ሳይጠይቅ ሰላቱን ሊያጠናቅቅ አይችልም። ቢያጠናቅቅም ሰላቱ ተቀባይነት የለውም። አንድ አማኝ ሱረቱል ፋቲሀን ሲቀራ እንደ ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ምግባር ምግባሩን እንዲያሳምርለት አላህን እየጠየቀ ነው። አንድ አማኝ በግዴታ አምልኮው ውስጥም ሆነ በፍቃዱ በሚያደርጋቸው አምልኳዊ ተግባራት ላይ ለረሱሉላህ ፍቅሩን ሳይገልፅ፣ ሳያልቃቸው ምንም ተግባር አይፈፅምም። አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ለነብዩ ባለው ፍቅር አትገረሙም ዎይ?
አላህን ያላመፀ ለረሱሉላህ ፍቅሩን ሳይገልፅ፣ ሳያልቃቸው ሊያመሽም፣ ሊያነጋም አይችልም። ተጨማሪ የተወደዱ አምልኳዊ ተግባራት ባይፈፅም እንኳ በግዴታ አምልኳዊ ተግባራት ውስጥ አንድ አማኝ፣፣ ተረጋግቶ፣ ንፁህ ሆኖ(ውዱዕ አድርጎ)፣ ቀልቡን አፅድቶ ለረሱሉላህ ፍቅሩን ሳይገልፅ፣ ሳያልቃቸው አምልኳዊ ተግባራቱን አያጠናቅቅም። ምክንያቱም أَنْعَمْتَ عَلَيْهِمْ
የተባሉት ሁሉ ቁንጮና የበላይ ለዓለማት እዝነት ተደርገው የተላኩት ነብዩ ሙሀመድ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ናቸውና።

አንቱ መወሳቶ የተላቀ ባለ ታላቅ ጠባይ፣ አንቱ የተወዳጆች ሁሉ የበላይ፣ አንቱ ክቡር የተከበሩ፣ የሚከበሩ ድንቅ ሰው አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ አንቱን ወደውና ፈለጎን ተከትለው በጀነት ከሚዋዳጆት ያድርገን። ረመዳን ውብ ነው፣ ሰለዋት ደግሞ ውበቱን ያጎላል። በተወዳጁ ባለ ታላቅ ጠባይ ላይ ሰለዋት እያወረዳችሁ ፁሙ። »
[አብዱልሀኪም ሰፋ]
:
@Venuee13
@Venuee13

2 months ago

#ዝክረ_ክብር
:
« ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ሁለንተናዊ ናቸው፣ ሁሉን አቀፍ፣ ሁሉንም ያሟሉ ናቸው። በመስጂዳቸው ውስጥ ባልደረባዎቻቸው አንድ ላይ ተሰባስበው ከተቀመጡ ይቀላቀሏቸዋል። የሚቀመጡት የተለየ ቦታ ላይ ሳይሆን ያገኙት ቦታ ላይ ነው። የተለየ አቀባበልም፣ ሆነ ትኩረት እንዲሰጣቸው አይፈልጉም። አነስ ኢብኑ ማሊክ ሲናገር ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ሲመጡ መነሳታችን ስለማይወዱት ከመቀመጫችን አንነሳም ነበር። ይላል።
አዲ ኢብኑ ኻቲም አ ጧዒ እንዲህ ይላል። ስለ እስልምና ልጠይቃቸው ወደ ረሱሉላህ ዘንድ ሔድኩ። ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለምም እንድቀመጥ ጋበዙኝ። ከዚያም መከዳ(ትራስ) አስመጡ። በመሀከላችንም አስቀመጡት። አንድ እጃቸውን ደገፍ ብለው በሌላኛወ በኩል በክርኔ እንድደገፍ ተደገፍ፣ ተመቻች አሉኝ። በዚያው ቅፅበት ንጉስ እንዳልሆኑ አወቅኩ። ምክያቱም ከየትኛውም ንጉስም ሆነ ትልቅ ስልጣን ካለው ሰው ሁሉ የተለዩ ነበሩና። ይላል።
ገና እኮ አልሰለመም ግና በምግባራቸው ቃላትን ሳያወጡ ልቦናውን አናገሩ።
ከሰዎች ጋር ተቀምጠውም ይሁን በማንኛውም ሁኔታ አንድ ሰው አንድ ነገር ከጠየቃቸው ባዶ እጁን አይመልሱትም።
ጃቢር ኢብኑ ሳሙራህ ከነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ጋር ተቀምጠህ ታውቃለህ ተብሎ ተጠየቀ እንዲህም ሲል መለሰ። አዎ። ሁሌም ፈጅር ከሰገዱ በኋላ ባሉበት ቁጭ ብለው አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላን አስታውሰው እስቲግፋር ካደረጉ በኋላ ሰብሰብ ብለው የተቀመጡ ባልደረባዎቻቸው ጋር አመሩ። ተሰብስበው የነበሩት ባልደረባዎቻቸው የጃሂሊያ ዘመን የነበረውን እያስታወሱ፣ ግጥም እየገጠሙ፣ እርስ በርስ እየተጨዋወቱ ሲስቁ ነበር። ረሱሉላህ ከተቀላቀሏቸው በኋላ ፈገግ ብቻ ብለው፣ በዝምታቸው አላህን ያወሳሉ። ሲል መለሰ።

ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም የትኛውም ስብስብ ውስጥ አላህን ማስታወስ እንዳይዘነጉ አበክሮ በመግለፅ፣ የተከለከሉና ጠያፍ ወሬዎችንም ይከለክሉ ነበር እንጂ ባልደረባዎቻቸው ምንም ነገር ትንፍሽ እንዳይሉ አያሳቅቋቸውም። ሰሀባዎችም እያወሩ ከነበረ ረሱሉላህ ሲመጡ ተሸማቀው ወሬያቸውን አይቀይሩም። ይልቁኑ ከማንም በላይ ይበልጥ ነፃነት ተሰምቷቸው የሚያወሩትም ለሀቢቡለላህ ነበር። ስብስባቸው ላይ ረሱሉላህ ከተገኙም መድረኩን ሁሉ አይቆጣጠሩም። እራሳቸው ብቻ በማውራትም አያሳልፉም እንደማንኛውም ሰው፣ ልክ አንድ እንግዳ የሆነ ሀገር ሔዶ በማያቀው ስብስብ ውስጥ ተረጋግቶ እና ተናንሶ እንደሚቀመጠው ይቀመጣሉ። ግርማቸው እንዳለ ሆኖ እሳቸው ግን ትኩረትን ለመሳብ ምንም አያደርጉም። ረሱሉላህ ሁለገብ ናቸው። ስለምንም ቢያወሯቸው የሚያወሩትን ያውቃሉ። ከየትኛውም ጉዳይ የጎደላቸውም ሆነ የማያውቁት የለም።
ዘይድ ኢብኑ ሳቢት(ሁቡ ረሱሉላህ) ስለ ጠቢብ ወግ አዋቂው ነብያችን እንዲህ ይላል።
ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ተሰባስበን ባለበት ስለ ዓለማዊ ጉዳዮች እያወራን ከሆነ አብረውን ያወራሉ፣ ስለ መጪው ዓለም የምንወያይም ከሆነ አብረውን ውይይታችን ይካፈላሉ። ስለ ምግብ እያወራን ከሆነ እንኳ ስለምግብ ያወሩናል።

ሀቢቡላህ ንግግራቸው እንዲሁ ዝም ብሎ ለዛ ቢስ አይደለም። በእያንዳንዷ ቅፅበት ጠቃሚ የሆነ ነገርን እያመላከቱ ነው የሚያወጉት። ኢብኑ መስኡድ እንዲህ ይላል።
መስጂድ ውስጥ ወጣቶች ተሰባስበን ስለ ጋብቻ እያወራን ነበር። ከዚያም ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉን። እናንተ ወጣቶች ሆይ ከእናንተ መሀል ማግባት የቻለ ያግባ፣ ያልቻለ ደግሞ ይፁም። ይህም በመጥፎ ነገር ላይ እንዳይወድቅ መጠበቅያው ይሆናል።
ረሱሉላህ ባልደረባዎቻቸውን ሲያገኟቸው ጥሩ ህልም ተመልክተው ከነበረ እንዲያካፍሏቸው ይጠይቋቸዋል። መጥፎ ህልም ከነበረ ግን ለማንም ሳይናገሩ በአላህ እንዲጠበቁ ይመክሯቸው ነበር። ከረሱሉላህ ጋር ሰሀባዎች ለማውጋት ከመጓጓታቸው የተነሳ አላህ ሁሌም ህልም እንዲያሳያቸው ይመኙ ነበር።
አብዱላህ ኢብኑ ዑመር ከረሱሉላህ ጋር ለማውጋት ብቻ
አላህ ሆይ በኔ ላይ አንተ የምታውቀው ጥሩ ነገር ካለ ለነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም የምነግራቸው ጥሩ ህልም አሳየኝ እያለ ዱዓ ያደርግ ነበር።
ወንድ ሰሀባዎች ከረሱሉላህ ጋር ተቀምጠው የሚያሳልፉት ጊዜ ስላለ ሴት ሰሀባዎች ቅሬታ ገባቸው። ከዚያም ሴቶች መጥተው
አንቱ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ ከወንድ ባልደረባዎቾ ጋር ይቀማመጣሉ። እኛ ግን ይህን ዕድል ስላላገኘን ከእርሶ መጠቀም አልቻልንም አሉ። እንያ ታላቁ ሰውም አንድ ላይ ሴቶቹ ተሰባስበው እነሱ ብቻ መጥተው እንደሚያስተምሯቸው በትህትና አበሰሯቸው። ሴቶቹም ሁሌም ረሱሉላህን የሚያገኙበትን ቀን ቆርጠው ተሰባስበው ይጠብቋቸው ነበር። ሃቢቡላህም ለሴት ባልደረባዎቻቸው ተግሳፅና እውቀትን ያስተምሯቸው ነበር። በመጀመርያ ሲያገኟቸው እንዲህ ነበር ያሏቸው
ከእናንተ መሀል ሶስት ልጆች ሞተውበት የታገሰ የወመል ቂያማ ልጆቹ ጋሻ ይሆኑለታል ሲሏቸው ያ ረሱለላህ ሁለት ልጅ የሞተብንስ አሉ። ረሱሉላህም ሁለት እንኳ ቢሆን ብለው መለሱ።
ሲተናነሱ ምንም ክብር የሌላቸው እስኪመስል ነው፣ ሲተናነሱ ምንም ልቅና የሌላቸው እስኪመስል ነው። የፍጥረታት ዕንቁ ሆነው ሳለ እንደማንኛውም ሰው ዝቅ ብለው፣ ትኩረት ሳይስቡ፣ በእርጋታ ያዳምጣሉ። እንደ ጓደኛ፣ እንደ ቅርብ ወዳጅ፣ ሁሉንም ያዳምጣሉ። ከሁሉም ያወጋሉ። መገን አኽላቅ!

አንቱ የልብ ወዳጅ፣ አይጠገብ ንፁህ ፍቅር፣ አንቱ የአኽላቅ ትርጉም፣ የሰውነት ፍቺ፣ አንቱ ጠቢብ ወግ አዋቂ፣ አንቱ አንደበተ ርቱዕ ማር ዘነብ አንቱን ወደውና ፈለጎን ተከትለው በጀነት ከእርሶ ጋር ተቀማምጠው ከሚያወጉት ሰዎች ውስጥ አላህ ያድርገን። ረመዳን ውብ ነው፣ ሰለዋት ደግሞ የውበቱ ዘውድ ነው። በነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ላይ ሰለዋት እያወረዳችሁ ፁሙ። »
[አብዱልሀኪም ሰፋ]
:
@Venuee13
@Venuee13

4 months ago

#የአላህ_ወር
#ረጀብ

« የወሮች ቁጥር አላህ ዘንድ በአላህ መጽሐፍ ውስጥ ሰማያትንና ምድርን በፈጠረበት ቀን ዐሥራ ሁለት ወር ነው፡፡ ከእነሱ አራቱ የተከበሩ ናቸው፡፡ ይህ ቀጥተኛው ሃይማኖት ነው፡፡ በእነርሱ ውስጥም ነፍሶቻችሁን አትበድሉ፡፡ » አትተውባህ፥36

የተከበሩ ከተባሉት አራቱ ወራት መካከል አንዱ ዛሬ የጀመርነው ታላቁ የረጀብ ወር ነው። በእነዚህ ውድ ወራት ውስጥ አላህ "ነፍሶቻችሁን አትበድሉ" ይላል።

አባ የዚድ (ራህመቱላህ) እዚህ አንቀጽ ላይ የመጣውን "በደል" ትርጓሜ ሲሰጡት እንዲህ ይላሉ፦ “በአምልኮ አላህን መታዘዝ መተው እና  አላህን የሚያስቆጣውን ሥራ መሥራት ነው።”

ዐሪፎች በቀጣይ ስለሚመጡት ተከታታይ ወራት ከተጅሩባቸው (መንፈሳዊ ልምዳቸው) ሲያካፍሉ እንዲህ ይላሉ :

« ረጀብ የተውበት (የንሰሃ) ወር ነው፣ ሻዕባን የመሐባ (የፍቅር) ወር ነው፣ ረመዳን ደግሞ የመቃረብ ወር ነው። »

እንዲህም ብለዋል « ረጀብ የጥብቅነት ወር ነው፣ ሻዕባን የአገልግሎት (ኺድማ) ወር ነው፣ ረመዳን የጸጋ ወር ነው።»

እንዲህ ያሉም አሉ፦ « ረጀብ የአምልኮ (ዒባዳ) ወር ነው፣ ሻዕባን ፍላጎት የሚገታበት ወር፣ ረመዳን የጭማሬ ወር ነው።»

« ረጀብ በርከታ ምንዳዎች የሚሸመቱበት ጊዜያት ሲኾን ቀጥሎ ያለው የሻዕባን ወር ደግሞ ወንጀሎች የሚሰረዝበት ወር ነው። ረመዳን ተዓምራት (ከራማ) የምንመለከትበት ወር ነው።» ያሉም ዐሪፎች አልሉ።

እንኳን ለታላቁ ወር በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ። የሚቀጥሉት ሦስት ወራት የተያያዙ ናቸው። በዚህ ወር ከገፍላችን መባነን ከቻልን ታላቁ የሰይዲ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ወር የኾነውን ሻዕባን በአግባቡ መጠቀም እንችላለን።

ረጀብ ወር የአላህ ወር ነው፣ ሻዕባን የሰይዲ (ዐለይሂ ሰላም) ወር ነው፣ ረመዳን ደግሞ የኡመቱ (የሕዝቡ) ነውና በወራቱ መካከል መንፈስን ለማደስና ከጀርባቸው ያዘሉትን ምስጢራት ለመረዳት መጣር ተገቢ ነው።

በረጀብ አንድ መጅሊሳችን ላይ ከሱልጣኑል አውሊያ ከሸይኽ ዐብዱልቃዲር ጄይላኒ (ቀደሰላሁ ሲረሁ) "ከጉንያቸው" ላይ በጥቂቱ ያወጣሁት ሐሳብ ነው።

አላህ የረጀብንና የሻዕባንን ወር ይባርክልን።

አስተግፊሩላሀ ዘል ጀላሊ ወልኢክራም ሚን ጀሚዕ ዙኒቢ ወልአሳም!

We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ ነው። ሰውነትን አስቀድመው ግለሰብን፣ ህዝብና ሀገርን የሚያከብሩ፣ ሚዛናዊ አመለካከትን ያዳበሩ፣ ከጥላቻ አመለካከት የነፁ ኢትዮጵያውያን ቤት ነው።

ያግኙን +251913134524

Last updated 1 month, 2 weeks ago

ስለ መድፈኞቹ የሚወጡ መረጃዎች ለማግኘት የትም መሄድ አያስፈልግም

- የዝዉዉር ዜና
- የአሰልጣኞች አስተያየት
- የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
- ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት

ለማስታወቂያ ስራ  --> @MKHI7

Last updated 1 month, 2 weeks ago

BoA Social media links
@ https://www.facebook.com/BoAeth
@ https://www.instagram.com/abyssinia_bank
@ https://www.linkedin.com/company/bankofabyssinia/
@ https://twitter.com/abyssiniabank
@BOA_ATM_bot

Last updated 3 weeks, 5 days ago