Why Pay for Entertainment? Access Thousands of Free Downloads Now!

የዮቶር ልጅ - አምባዬ ጌታነህ

Description
እኛ ከዮቶር፦
☞ የጥበብ ምሳሌን
☞ የአስተሳሰብ ውጤትን
☞ የፍልስፍና ዳራን
☞የአመራር ብቃትን
☞የአኗኗር ዘይቤን
ተምረናል!!!
ስለዚህ ሁላችንም የዮቶር ልጆች ነን ማለት ነው።

ለአስተያየት ና ሀሳብ via creater
@Adwa1888 [አምባዬ ጌታነህ]
Advertising
We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ ነው። ሰውነትን አስቀድመው ግለሰብን፣ ህዝብና ሀገርን የሚያከብሩ፣ ሚዛናዊ አመለካከትን ያዳበሩ፣ ከጥላቻ አመለካከት የነፁ ኢትዮጵያውያን ቤት ነው።

ያግኙን +251913134524

Last updated 1 month ago

ስለ መድፈኞቹ የሚወጡ መረጃዎች ለማግኘት የትም መሄድ አያስፈልግም

- የዝዉዉር ዜና
- የአሰልጣኞች አስተያየት
- የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
- ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት

ለማስታወቂያ ስራ  --> @MKHI7

Last updated 1 month ago

BoA Social media links
@ https://www.facebook.com/BoAeth
@ https://www.instagram.com/abyssinia_bank
@ https://www.linkedin.com/company/bankofabyssinia/
@ https://twitter.com/abyssiniabank
@BOA_ATM_bot

Last updated 2 weeks ago

1 year, 11 months ago

"ናፊባ"
ክፍል ~ ዘጠና አራት~
በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888
"መኖር የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ድርሻው ብቻም ሳይሆን
ኃሴት እንዲያገኝ የሚያደርገው እጣ ፈንታው ነው።
ረሀብና በሽታ ብቻ ሰውን አይገለውም።
ቤት የሌላቸው በርካታ ሰዎች ቢኖሩም አንተ ግን....."
" አንተ እስክትመጣ ድረስ በተደጋጋሚ እያነበብኩት ነበር። ፍፁም አልገባህ አለኝ። የሆነ ትርጉም ግን እንዳለው ልቤ ይነግረኛል።ብዙ የቅኔ አመስጣሪዎች ሀሳባቸውን በስነግጥም እና በስድ ንባብ ያስቀምጣሉ። እንዲሁም የሀገራችን ላቃውንትም ምስጢርን በብራና ሀሳብ ጥቅል ከይነው ለትውልድ ያስቀምጣሉ። ያን ቁልፍ የሚያገኝበት በርካታ ጥቅሎችም ይቀመጡለታል። ይህም ልክ እንደ ዴርቶጋዳ ላይ እንደተቀመጠው የሎሬት ግጥም ላይ እንዳለ የምስጢር ሀሳብ ነው። እና የውጮቹ ሰላዮችና ጠቢባን በርካታ ከያኒያን እና የደህንነት ሰዎች ሳይቀሩ እንቆቅልሾችን ይጠቀማሉ። ለምሳሌ row and column puzzle በሚባል እንቆቅልሽ ያስቀምጣሉ።በዛ መሠረት ከሁሉም አራፍተነገሮች የመጀመሪያ የመጀመሪያ ቃሎቹን ወስጄ ደረደርኩ
መኖር
ኃሴት
ረሃብና
ቤት
ብሎ ቁልቁል በመፃፍ ለኢንስፔክተር ሸዋንግዛው አሳየው "እኔ እንደሚመስለኝ እነዚህ ሰዎች የሚኖሩት እና ከመኖርም በላይ ኃሴት የሚያገኙት ረሀብ በተጠናወታቸው ሰዎች ነው። ለዚህም ስለቤት አያስቡም።ምክንያቱቤ ቤት የሌላቸው በርካታ ሰዎች ቢኖሩም አንተ ግን... ይላል።ይህም ማለት ቤታቸውን ጥለቅ በረሃብ ምክንያት ይሰደዳሉ። በዚህ ሀሳብ ላይ የተሰናሰለ ይመስለኛል"አለ ተሕሚድ።ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ግን አንዱንም ያለውን አልሰማውም ነበር። አእምሮውና ልቡ የተደረደሩት ቃላት ላይ ነበር። ተሕሚድ የሸዋንግዛውን ምንም አለማለት እና ከእርሱ ጋር አለመሆኑን የተረዳው በኋላ ነበር። "ፍቅሬ አጎቴ ሌላ ሀሳብ ውስጥ ገብቷል እኮ ዝም ብለህ ነው ስትደክም የነበረው"ብላ ሳቀች።
"አገኘኋት!!! መ..ኃ..ረ..ቤ!" አለ ሸዋንግዛው። ተሕሚድ በቀጥታ ያወጣቸውን ቃሎች ተመልክቶ የመጀመሪያ የመጀመሪያ ቃላቸውን ወስዶ ሲደረድር ኢንስፔክተር የተናገረውን ስም አገኘ። መኃረቤ!!! "የሰው ስም ነው?" አለ። "በሚገባ እንጅ ለዛውም የመጀመሪያው ሟች ኄኖክ የቤት ሰራተኛ ከዛ በኋላም እዛ አትሆንም ብለን ትላንት የሞተው የዋና ሳጅን አክሊሉ የቤት ሰራተኛ ሆና ነበር። ነገር ግን ከወራት በፊት ተሰወረችብን"አለና በምናብ ወደ ኋላ ሄዶ ሒዎትን በኄኖክ እና ዮዳሔ ግድያ ተጠርጥራ ለምርመራ በነበረችበት የኄኖክ ሰራተኛ በመሆኗ እንደምታውቃት እና መረጃ እንድትሰጥ መኃረቤ ስትጠየቅ በጣም ደንግጣ ነበር። በምላሿም ጥርጣሬ እንደገባውና ግን ምን አልባት የዛኑ እለት አስፈራርታት ቢሆንስ ብሎ ያሰበው ትዝ ብሎት"ራሱን በመነቅነቅ ቀጥታ ወጥቶ ወደ ፕሮፌሰር እስጢፋኖስ በመሄድ ስለ መኃረቤ ሁሉንም ሲነግረው። ከተሽከርካሪው ወንበር ቀስ ብሎ ተነሳና ፈገግ ብሎ "የሼክስፔር ተዋናይት ናታ?" አለ "ማለት አልገባኝም!" አለ ሸዋንግዛው እንዲያብራራለት " የእንግሊዞች የጥበብ ጣኦት ሼክስፔር ነው። እጅግ በሚባል ደረጃ በጣም ይወዱታል። የሱን ስራዎች ከሰራው በላይ በዓለም እንዲዳረስና እንዲስተጋባ አድርገዋል። እና አርት በጣም ያስደስታየዋል ድርሰትና ትወጣ ስራቸውን ከሚያቀሉላቸው ነገሮች ቀዳሚዎቹ ናቸው። ለዚህም ሰላዮቻቸውን በከፍተኛ ጠሰንቃቄና ብቃት የትወና ጥበብን ያስተምሯቸዋል።በየሀገሩ የሚልኳቸውና ተልዕኳቸውን የሚያስፈፅሙሏቸው ሰዎች የትወና በቃታቸው በጣም ትልቅ ነው። አንተን ያሳምኑሀል። በቃ ከምነግርህ በላይ በጥበባቸው የአንተን ደካማ ጎንና የማመን ሀይልህን ይቆጣጠሩብሀል። ደግሞ እኛ ኢትዮጵያዊያን ለማዘንና ለሰዎች በጎ ነገር ማሰብ ቀዳሚው ተግባራችን እንደሆነ ስለሚታወቅ ይህን እንደ ትልቅ ግበአት ይጠቀሙበታል። ስለዚህ የእንግሊዞች መሣሪያ አሉ ማለት ነው። በርግጥ እንግሊዝ ከአሜሪካ የበለጠች አደገኛና መሠሪ የሆነች አገር ስለመሆኗ የክሪሚላን ፖለቲከኞች ሳይቀሩ ይናገራሉ።በራሺያውያን ራሱ በቀዳሚ በሚባል ደረጃ የሚጠሉት እንግሊዞች ናቸው።

መንግስት ከጠበቀው በላይና ሊቆጣጠረው ከሚችለው በላይ ሲሆንበትና የማህበራዊ ሚዲያው ተቃውሞ ሲበዛበት የዳታ አገልግሎቱን በማቋረጥ ለማርገብ ሞከረ። በዚህ ድርጊት የተቆጡ አዲሳበባዊያን በተለያዩ አጋጣሚዎች በመቀሳቀስ ተቃውሟቸውን ለመግለፅ በአደባባይ ወጥተዋል። ህዝቡ በተመሳሳይ ስሜት ውስጥ ሆኖ በየቦታው በተመሳሳይ ስአት በመገንፈል የአዲስ አበባ ጎዳናዎችን በሰላማዊ ሰልፈኛ ተቃዋሚዎች ተጥለቀለቀች። ከፈረንሳይ የመጣው ሰላማዊ ሰልፈኞ ከሽሮሜዳ በከሉ በመነን አድርጎ በስድስትኪሎ ዩኒቨርሲቲ አድርጎ ስድስት ኪሎ ሰማዕታት ሀውልት ላይ ተገናኝተው ቁልቁል በአምስትኪሎ አድርገው ሲወርዱ መንግስት ከቅድስተማርያም በታች እንዳያልፉ ከፍተኛ የሆነ ሀይል አሰማርቶ መንገዱን ዘጋ። ነገር ግን ሰልፈኛው በቅድስተማርያም በኩል አድርጎ በሰባ ደረጃ በመታጠፍ ወደ ፒያሳ ነጎደ። ከቀጨኔ ከ አዲሱ ገበያ፣ እና ከገዳም ሰፈር በኩል የመጡት ሰልፈኞች ደግሞ ምኒሊክ ሀውልት ላይ ተገናኙ። ከጳውሎስ መድኃኒዓለም እና ዩሐንስ በኩል የመጡትም በአቡነጴጥሮስ ሀውልት አድርገው ምኒሊክ ሀውልት ላይ ተገናኙ ከአቧሪ ካዛንቺስ መገናኛ በኩል የመጣው ሰልፈኛ ደግሞ ወደ መስቀል አደባባይ እየተመመ ነው። ከልደታ በኩል ከሳሪስ ከጎተራ ከጠመንጃ ያዥ በቅሎ ቤት ከጨርቆስ አውቶብስ ተራ ከሜክሲኮ ልደታ ከተክለሀይማኖት አብነት የጎረፈው ህዝብም በለገሀር አድርጎ በስታዲዮም ብቅ ብሎ ከወደፒያሳ የተሰባሰበው ህዝባዊ ሀይልም በቴዎድሮስ አደባባይ በኩል በቸርችል ጎዳና ወርዶ በአምባሳደር አድርጎ በጊዮን ሆቴል ብቅ ብሏል።ከቦሌ መስቀል ፋለወር በኩል የመጣውም ሰው በቀይ ሽብር በኩል አሰፍስፎ ወደ መስቀል አደባባይ እንዳይገቡ በሚከለክሉ መንግስታዊ ሀይሎች ጋር ተፋጧል። በመጨረሻ ተቃውሞው እየበዛና የህዝቡ ቁጣ እያየለ ሲሄድ ብረት ለበሶቹ የፌደራል ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ ለመጠቀም ተገደዱ። ዳሩ ግን የነሱ አስለቃሽ ጭስ የህዝቡን ንዴት ጨመረው እንጅ ፈርተው እንዲያፈገፍጉ አላደረጋቸውም። መንግስት ለዚህ ሰልፍ ሀላፊነት የወሰደ ሰው ባለመኖሩና ምንም አይነት ህጋዊ ማረጋገጫ ሰነድ ስለሌለው ማንንም መጠየቅ እንዳለበት እና ማንን ማሰር እንዳለበት ግራ ገብቶት አብዝሀኛዎቹን በጅምላ ዝም ብሎ ወደ መኪና እንዲጫኑ ሊያደርግ ሲል ሰልፈኛው ሆ ብሎ እንደ ንብ ይወጣባቸዋል። ከዛ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ከላይ በወረደ ትዕዛዝ ብረት ለበሶቹ ፌደራል ፖሊሶች ስፍራውን ለቀው ወጡ። "ይህ መንግስት ለሆዱ እንጅ ለህዝብ አያስብም!" "በንፁሀን ደም መቀለድ እስከየትም አያደርስም!" "ኢንስፔክተር ሸዋንግዛውን ልቀቁት! እርሱን በማሰር የህዝቡን ፍላጎት ልታስቆሙ አትችሉም።! የሞቱት እህት ወንድሞቻችንን ገዳይ እንፈልጋለን!" በማለት የተቃውሞ መፈክራቸውን በማሰማት ቀጥሉ። በዚህ ህዝባዊ ማዕበል አንድም ሰው ወጥቶ የተናገረም ሆነ ማይክ በመጠቀም የሁላቸውንም ድምፅ ለማስተጋባት የሞከረ አልነበረም። ምክንያቱም ምንም የተዘጋጀ ሳውንድ ሲስተም ስላልነበረ። ይህ እንዳይሆን መንግስት ቀድሞ በየቀበሌው ተናጋሪዎች ናቸው የተባሉ ወጣቶችን አስሯቸዋል።

@amba88
@amba88

1 year, 11 months ago

"ናፊባ"
ክፍል ~ ዘጠና ሦሥት~
በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888
"መረጃውን አትሰማም የሚል እምነት በግሌ የለኝም።ምክንያቱም በስአታት ልዩነት ነው የዋሽንግተን ፖስት ያንተንና የልጆችህን ምስል ከፊት አድርጎ ለዜና ያበቃው" ብሎ ስካይፑን እየነካካ ሳለ የመልስ ደወል ጠራ። በፍጥነት ነክቶ የስካይፑን ምስል አደብዝዞ የቤቱን ከለር ወደ አረንጓዴነት የሚቀይረውን ማብሪያ ማጥፊያ በመጫን አንስቶ ድምፁን ጨመረው። ሜላት ነበረች። ፍፁም የሆነ ሰላም እየተሰማው እፎይ አለና ሸዋንግዛውን እንዲያወራ ብቻውን ትቶት ወጣ። የተለመደ ስጋቷን ያለምንም እረፍት እያዥጎደጎደችለት ትንፋሽ አሳጣችው። ሸዋንግዛውም ሁኔታዋ ስለገባው በፈገግታና በስስት ይመለከታት ጀመር። "አሁን ምንም አትጨነቂ ያለሁበት ቦታ አስተማማኝ ነው። ስለዚህ ተረጋግተሽ ስራሽን መስራት ትችያለሽ!"
ፕሮፌሰር እስጢፋኖስ የኋላሸት ውጪ ላይ እየተንጎራደደ እጆቹን ወደ ኋላ አድርጎ እርምጃውን የሚቆጥር በሚመስል ማቀርቀር ውስጥ ሆኖ አንድ ሀሳብ መጣለትና በሩን ከፍቶ በመግባት ወደ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ጆሮ ጠጋ ብሎ "ማንኛውም ሰው ደውሎ እንዳገኘችህ እንዳትናገርእና የሚጠይቃት ካለ ምንም እስካሁን እንዳልደወልክላት እንድትናገር አድርጋት " ብሎት ወጣ። ሸዋንግዛውም አፍታም ሳይጠብቅ "የኔ ፍቅር እንዳወራሁሽ ለማንም አትናገሪ እሺ ያው መንግስት ሊያስረኝ ሲል ነው እነዚህ ሰዎች ቀድመው ደርሰው የጠበቁኝ እና ማንም ሰው እኔን እንዳገኘሽኝ ከጠየቀሽ ጭንቀት ላይ እንደሆንሽ በማሳየትና በጭራሽ እንዳልደወልኩልሽ በሁኔታሽ አስረጃቸው። በኤምባሲው በኩል ክትትል ሊደረግብሽ ስለሚችልና ንግግርሽ ሊቀዳ ስለሚችልም ላልተወሰነ ጊዜ አንደዋወልም። በጭራሽ ስጋት እንዳይገባሽ። ልጆቹም ፍፁም ደህና ናቸው። ይህን የተደዋወልንበትንም አጥፊው" አለና ተሰናበታት። ሜላት ሁኔታውን በትንሹም ቢሆን ስለተረዳችው ልትጫነው አልፈለገችም። ግን ደግሞ እስከመቼ ነው እንዲህ የሚቀጥለው? የሚል ጥያቄ ራሷን እየጠየቀች ነበር።
ኢንስፔክተር ሸዋንግዘው በትንሹም ቢሆን የፈራው ፍርሃት ለቀቀው።አሁን አንድ ሀሳብ ብቻ ቀርቶታል።እሱም የማያ ወላጆች ናቸው። ደህንነቱን ካላወቁ በጭንቀት የሚሞቱ መሠለው። " i think you are fine now!" አለ ፕሮፌሰር እስጢፋኖስ የኋላሸት ሜላትን ስላገኛት ጭንቀቱ ሙሉ ለሙሉ የጠፋ መስሎት "አዎ በትንሹ ግን ፕሮፌሰር የልጆቼ አያቶች የእኔንም ሆነ የልጆቹን ደህንነት ካላረጋገጡ በጣም ይጨነቃሉ።ስለዚህ የምትችል ከሆነ እንደው ብትተባበረኝ!!" አለ " ok የማያ ወላጆች! ኦሺ የሆነ መፍትሔ እናበጅለታለን የአካባቢውን ሁኔታ አጥንተን አንድ ልጅ ልኬ እንዲያገናኝህ አደርጋለሁ!!" አለና ቀለል አድስጎ መለሰለት። "በጣም አመሰግናለሁ!!" በማለት ከአንገቱ ጎንበስ በማለት ምስጋናውን ችሮ ተቀመጠ። በብዙ ሀገራዊ ጉዳዮችና የጋራ ፍላጎቶች ላይ ከተግባቡ በኋላ "ከዚህ በኋላ ማን ማን ስጋት እንደሆነብን ማን በዚህ ምስጢራዊ ተልዕኮ ተዋናይ እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል። ስለዚህ እሱን አንተ ተመራመርበት እንዲሁም የማን እጅ ከጀርባው እንዳለም ማወቅ ያስፈልጋል። ስለዚህ የናፊባን ጉዳይ በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ አዲስ ነገር እንደምታገኝ ተስፋ እያደረኩ ለሚኖርህ ማንኛውም ጥያቄና አስተያየት ካለ በማንኛውም ጊዜ መጥተህ ልታናግረኝ ትችላለህ "ጨለና ፍፁም በሆነ ፈገግታ እጁን ዘርግቷ ሰላም ካለው በኋላ በክብር ወደ ክፍሉ እየሸኘው እያለ "ፕሮፌሰር እነዚህ ምስሎች በጣም ነው ልብ የሚነኩት። እጅግ ማራኪዎች ከመሆናቸውም በላይ ነብስን በሀሴት ያረሰርሳሉ"አለ ኢንስፔክተር ሸዋንግዘው። "አየህ እዚች አገር ላይ በርካታ ሀብቶች አሉ።ሁሉም በሚባል ደረጃ ሙሉ ነው። ኢትዮጵያዊያን ሀብታቸው ላይ ተኝተው ነው የሚለምኑት። ምዕራባዊያን ደግሞ ያለህን ሀብት እንድትጠቀም ሳይሆን የእነሱን ስንዴና ገንዘብ እንድትለምን በሀገርህ ሰርተህ እንደምታድግ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ይልቅ ወደ ሀገራቸው ሄደህ እንድታገለግላቸው ነው የሚያደርጉት። ለዚህ ነው እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እነዚህን ሀገሮች የምጠላቸው። ለምሳሌ ምዕራባዊያን እርዳታ ሲያደርጉ ብር ብቻ ነው የሚሰጡህ። ቻይናና ራሺያ ግን ብር አይደለም የሚደግፉት ህንፃ ወይም መንገድ ወይም ድልድይ ማሰሪያ ከሆነ የሚያስፈልገው ያን ህንፃ ድልድይና መንገድ ሰርተው ነው በብድር የሚያፅፉት።አሜሪካና የምዕራቡ ዓለም ግን እንደዛ አይደሉም። እና እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እነዚህ የምትመለከታቸውን ምስሎች በቅርብ እርቀትና በየቦታው የሰቀልኳቸው ሰርክ ባየኋቸው ቁጥር የባከነው ፍቅራችን የባከነው ሀብታችን ያለቦታው የተዘራው ወጋችን በደንብ ሳናጌጥበት የጠፋውን ስልጣኔያችንን እንዲያስታውሰኝና እነዚህን ውብ ሀብቶቻችንን በመመለስ ታላቋን ኢትዮጵያ መስራት ስለሆነ ነው" ሸዋንግዛው የተለመደውን የአድናቆት ምልከታ እየተመለከተ ክፍሉ እስኪደርስ ድረስ እያዳመጠው ነበር።
ራዕይ የሰውን ልጅ በዓላማ እኖዲኖር የሚያደርግ ቀጥተኛ መንገድ ነው።የሰው ልጅ ወደዚህ ምድር የመጣበትን ዓላማ በፀሎት መጠየቅ ይኖርበታል ሁሉም እንደየእምነቱ ባለው ጥንካሬ ሊማፀን ይገባል። ምክንያቱም ፈጣሪ መቼም ያለምንም ነገር ተፈጥረን ይቺን አለም እንድንቀላቀላት አያደርግምና። ያን ዓላማ ሰዎችንና ፈጣሪያችንን በምን እንድናገልግል እንደፈጠረን አንድ ጊዜ ጠይቀን ከዛ በኋላ በምስጋና እንዲገልፅልን ማድረግ ይኖርብናል። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ራዕያቸውን በግልፅ ሳያስቀምጡ ፈጣሪ የሆነ ታዕምር እንዲፈጥርላቸው ይሻሉ። ይህ ስህተት ነው መሆን የለበትም። ላስቀመጣችሁት ራዕይ የሚሆን ገንዘብም ሆነ ሀብት በግልፅ ካስቀመጣችሁ በኋላ በየቀኑ ያን ራዕይ የምትመለከቱበት ቦታ ሰቅሎ ለአእምሯችን ፕሮግራም ማስደረግ ነው። አአምሯችን በተደጋጋሚ የሚመለከተውንና የሚያየውን ነገር የመቀበልና ይሆናል የማለት ከዛም የማድረግ አቅም አለው። ፕሮፌሰር እስጢፋኖስ የኋላሸትም ያደረገው ይሄን ነው። የሚፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመስራት ካሰበ በኋላ የሚፈልጋትን ኢትዮጵያ የሚገልፁለትን ምስሎች በየግድግዳው በመስቀል በየቀኑ ለአእምሮው እየነገረ የሚሰራው። ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ለነበራቸው ቆይታ አመሰግኖ ወደ ክፍሉ ሊገባ ሲል "ለልጆቹም የሚሆን ቦታ ስላለ አታስብ እዚህ የምርምር እውቀታቸውን ሀ ብለው የሚጀምሩበት ቦታ ይሆናል።የፍላጎታቸውን አዝማሚያ ተመልክተን እንዳይጨናነቁ አእምሯቸውን ዘና ሊያደርጉ የሚችሉ የሶፍትዌር ፈጠራዎች በአፕሊኬሽን መሠረት ስላሉ ልጄ በሚገባ ያሳያቸዋል። ስለዚህ ስለ እነሱም ሳታስብ ሙሉ ጊዜህን ስራው ላይ ብቻ ትኩረት አድርግ። ስለተሕሚድ መጀመሪያ ስሰማ ተገርሜ ነበር።እዚህ እኛ ጋር የሚሰራ አንድ ልጅ አለ በእሱ በኩል ነበር ስለ እሱ ያወቅነው። እና ጥሩ እያገዘህ እንደነበር በሚገባ እናውቃለን። እርሱም ለጥበብ ቅርብ ስለሆነ ብዙ ነገሮች ላይ ሀሳብ ያዋጣልሀል ብዬ አስባለሁ።ለማንኛው አንተ በፈለከውና በሚመችህ መንገድ ስራ። ብቻ ዋናው በፍጥነት ሰርተን የኢትዮጵያን አረሞች ዳግም እንዳይበቅሉ አድርገን መንቀል ነው።" ብሎ እጁን ትከሻው ላይ ደገፍ አድርጎ አንገቱን ከነቀነቀ በኋላ ወደ ቢሮው ተመለሰ።

@amba88
@amba88

1 year, 11 months ago

"ናፊባ"
ክፍል ~ ዘጠና ኁለት~
በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888
" ጤና ይስጥልኝ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው" በማለት በቀኝ እጁ ሰላምታን ከሰጠው በኋላ በግራ እጁ እንዲቀመጥ አመላከተው። የሰውዬውን አክብሮትና ፈገግታ ከልቡ እየተቀበለ ከአንገቱ ዝቅ በማለት ለአክብሮቱ ምስጋና በማቅረብ ተቀመጠ። " እንግዲህ በዚህ መንገድ ስለ ተዋወቅን በጣም ይቅርታ እጠይቃለሁ" በማለት ሁለት እጁቹን አገናኝቶ ወደ ግንባሩ በማቅረብ እንደ ህንዶቹ ምስጋናና ይቅርታ ቡራኬ አቀረበ።ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ያለምንም ቃል አንገቱን ሰበር በማድረግ ብቻ እሺታውን ገለፀለት። "ጥሩ እንግዲህ ጊዜ ለሁሉም ነገር አመላካች መስታውት ነውና አንተን የመሰለ ኢትዮጵያዊ በማወቄ በማግኘቴም ደስተኛ ነኝ። " ኢንስፔክተር በፅሞናና በዝምታ ብቻ እያዳመጠው ነው። "እኔ ሀሳብህንና ፍላጎትህን መጋራት ብቻ ሳይሆን ማራመድ የምፈልግ ግለሰብ ነኝ። ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው በአንተ እድሜ እያለሁ ትንታግና ቁጡ እልኸኛ ነበርኩ።እና አንተን ስመለከት በእያንዳንዱ ሁኔታህና ድርጊትህ ራሴን የምመለከት ነበር የሚመስለኝ።ሀቀኝነትህን ታማኝነትህን ከምንም በላይ እወድልሀለሁ አከብርልሀለሁ። ለብዙ ጊዜ ከተከታተልኩህ በኋላ ነበር ልረዳህ እንደሚገባ ያመንኩት። አሁን አጉል ታሪክ አንስቼ በማውራት ጊዜያችንን አልገድልም። ምክንያቱም እዚህ በምናባክናት ደቂቃ ውስጥ እንኳ ብዙ ሰቆቃ ላይ ያሉ ዜጎቻችን ስላሉ። ስለዚህ ስለ እኔ ሙሉ ነገር ባይሆንም ግርታህን ለማንሳት ያህል የተወሰነ ልንገርህ ፕሮፌሰር እስጢፋኖስ የኋላሸት እባላለሁ። ለበርካታ አመታት በራሺያ ዜኒትስ በርግ በምርምር ስራዎች ስሳተፍ እና ስሰራ የነበርኩ ሰው ነኝ። አንተን አለቃዬ እየፈለገህ ነው ብሎ ወደ እኔ ያመጣህ ልጄ ነው። የመጀመሪያ ድግሪውን በሞስኮ ቶሎስቶይ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ የተመረቀ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ እዛው በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ሰርቷል። ለብዙ አመታት ኑሯችንን እዛው ብናደርግም ዳሩ አይናችንም ልባችንም እዚች ታሪካዊት ሀገር ነበር። እዛው ሀገር እያለሁ ነበር ይሄን አካባቢ በህጋዊ መንገድ አስፈላጊውን ካሳ ለባሎቦታዎቹ ሰዎች ከፍዬ የገዛሁት። ከዛም ቀጥታ ወደዚህ የህንፃ ግንባታ ገባሁ።መንግሥት ይሄን ልዩ የሆነ ምስጢራዊ የሆነ ድብቅ ቦታ እንዳያየው በከፍተኛ ጥንቃቄና በራሺያ መንግስት ድጋፍ ልሰራ ቻልኩ። ያው መቼም ስለ ራሺያ ብዙ ነገር ታውቃለህ።ኢንስፔክተር እንደመሆንህ የቀድሞዋን ሶብዬት ሕብረት ታሪካዊና ፖለቲካዊ ዳራ ሳትጎረጉር አትቀርም። እናም የአሜሪካን ፍላጎት ብቻ የሚያንፀባርቀውን አሻንጉሊት የኢትዮጵያን መንግስት ለማስወገድ ያለን አማራጭ በረጅም አመት እቅድ በዚህ መልኩ መደራጀትና ቀስ በቀስ ማስወገድ ነበር። የምዕራቡ ዓለም እና የአሜሪካ አካሄድ ህገወጥ ወረራና ዘመናዊ የባርነት ቀንበር ያነገበ ፍልስምና በተመለከትኩና ባየሁ ጊዜ ይቺን መልዕክተ ዮሐንስ ብዬ የእወቀት አድማሴን ያሰፋሁባትን የፊደልን ቅጠል የዘነጠፍኩባትን፣ የአእዋፋትን ዝማሬ እየሰማሁ የንጋትን ደዎል ባወጀኩባት ሀገር ሌሎች ላይ የሆነው እንዲሆን ባለመፍቀድ አንድ ታላቅ ራዕይ በማንገብ ሀገሬን ከነዚህ ሰይጣኖች መታደግ ሆነ። ለዚህ ዓላማዬም ይረዱኝ ዘንድ በርካታ ተማሪዎችን ከየትምህርት ቤቱ በመልቀም ላለፉት አስር አመት በራሺያ በማሰልጠን የዚህ ምስጢራዊ ተልዕኮ ቡድን አባል አድርጌ በተንኳቸው። በየህዝቡ ላይ ተሰግስገው አስፈላጊውን መረጃ እንዲሰበስቡ በማድረግ ስራዬን በጥንቃቄ እየቀጠልኩ ለልጆቹ እንደ ወጣት ጎልማሳ ጎደኛም እንደ የእውቀት አባትም በመሆን ስራችንን እየሰራን ባለንበት አንድ ምስጢራዊ ቡድን ደግሞ በሌላ ፅንፍ እየተንቀሳቀሰ እንደሆን ተረዳሁ። በዚህም በቂ ክትትል በማድረግ መረጃዎችን በመሰብሰብ አንድ አብሯቸው ይሰራ የነበረን ልጅ በተለያዩ አባላቶቻችን በሰው በሰው በማድረግ አስፈላጊውን ምርመራ ስናደርግበት ልጁም ስራቸውን ለማገለጥ እንደሚፈልግና ነገር ግን ይሄን ምስጢር ቢያወጣ እጣፈንታው ሞት እንደሆነ በፍርሃቴ ውስጥ ሆኖ አጫወተን። ከዛ ምስጢራዊው ቡድንም እኛ እንድናርፍባት የምንፈልግባትን ኢትዮጵያ ትርጉም ያዘለ "ናፊባ"የተሰኘች የምስጢራዊ ተልዕኳቸውን ማስፈፀሚያና መከተያ ህግ ያዘለች።አጠቃላይ ስለቡድኑ ምንነትም በሚገባ የምትገልፅ መፅሐፍ እንደሆነች ከልጁ በወሰድነው መረጃ መሠረት አንዳንድ መረጃዎችን ስናሰባስብና በዚህ ቡድን ላይ መንግስት የራሱን ፍላጎት ለማሟላት እና ህዝቡን ለማስፈራራት የሚጠቀምበት የአሸባሪ ቡድን እንደሰራ በመገመት ማጣሪያዎችን ስናደርግ።ይህን ቡድን መንግስትም እንደማያውቀው ተረዳን። ከዛም ባለስልጣናቶች ይኖሩበት ይሆናል በሚል ፍርሃት መረጃውን ለማንም እግዳይደርስ ካደረግን በኋላ ስለ አንተ በጎ ስራና ጥሩ ስነምግባር ስናውቅ በህዝቡም መልካም የሆነ ቅቡልነት በመማረካችን እኛስ ከህዝቡ ወገን አይደለን በማለት አንተን መርዳት ዋናኛ ተግባራችን አደረግን። ይህን ስራችንንም የአንተን የምርመራ ጥበብ ለመጨመር ብዙም በማይከብዱ እንቆቅልሾች እያደረግን እስከዚህ አደረስንህ። ነገር ግን በተደጋጋሚ በአንተ ስሜታዊነት የተነሳ ከመንግስት ሀላፊዎች ጋር ቅሬታ እየገባህ ስትሄድ ሁኔታህ አሳስቦን ቀድመን ልንሰውርህ እያሰብን ባለበት መንግስት ቀደመን።ከዛ በኋላ የሆነው ይሄው ነው። ከምንም በላይ የአንተና የልጆችህ የሁላችሁም ሕይወት በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑ ነው።" አለና ንግግሩን ገታ አድርጎ ነጭና ጥቁር የተቀላቀሉበትን ፂሙን ይነካካ ጀመር። ቀልጣፋና ንቁ የሆነ ሰው መሆኑን እየተመለከ ለረጅም ደቂቃ ሲያዳምጠው ከቆየ በኋላ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው " በጣም የሚገርም ነው ፕሮፌሰር።በቅድሚያ ከእኔ በላይ የተከበረ ሙያዎን ትተው ለትውልድ ሀገረዎ በማሰብ ያደረጉትን ነገር በሙሉ አደንቃለሁ። አከብራለሁ። ለዚህ ውለታችሁም ታሪክ የሚዘክራችሁ ይሆናል። በዚህ ደረጃ በመደራጀታችሁም በጣም ነው የተገረምኩት። ይህ የሚያሳየው ድንበር አልባ ሀገር እንዳለችን ነው። የእናንተስ ለመልካም ነገር የተቋቋመ ምስጢራዊ ቡድን ነው። ለሌላ ችግር የተቋቋመ ምስጢራዊ ቡድን በዚህ መልኩ ስለመደራጀቱም ጥርጥር የለኝም።ምክንያቱም የሀገሪቱ ደህንነት ምን ያህል የዘቀጠ እንደሆነ ያሳያል"በማለት በቁጭትና በንዴት አንገቱን አወዛወዘ። "አሁን እሱን ማሰቡ በእሱ መነመደዱ እርባቢስ ነው። የሚጠቅመው ቀጣይዋ ኢትዮጵያን በደህንነቱም በጥበቃውም ረቂቅ ንስር ካሜራዎቿን በመግጠም መቆጣጠር የምንችልበትን ስራ መስራት ነው። ስለዚህ አንተ አሁን የምትሰራው ስራ የናፊባ ምስጢራዊ ቡድን ማንነት እንድታጣራ እንድትመረምር ነው። በመቀጠል የደህንነት ስጋት ያለባቸው ዘመዶች በቅርበት ካሉህ እንድናመጣቸው ነው።"አለ ፕሮፌሰር ቆፍጠን በማለት። "ማንም የለም። ባለቤቴ ግን ስለ እኔ የሆነ ዜና ከሰማች በቀጥታ ልምጣ ማለቷ አይቀርም" አለ ሸዋንግዛው። ፕሮፌሰሩ በድንጋጤ በርገግ ብሎ "የት ነው የምትኖረው?" " አሜሪካ" ሸዋንግዛው በፍጥነት መልሶ የፕሮፌሰሩን የፊት ገፅ ተመለከተ። " ምንም ችግር የለም። ዜናው ሁሉም ጋር ስለተዳረሰ ባለቤትህ እዛ መሆኑን በፍፁም ረስቼዋለሁ። እሺ አሁኑኑ እንደውልላታለን "አለና ስልኳን ተቀብሎ ፊት ለፊቱ ባለው ስክሪን ተች ላይ ፅፎ ደወለላት። በተደጋጋሚ ቢሞክሩም አልነሳ አላቸው። "በቃ እንደታፈንኩ ከሰማች መንገድ ትጀምራለች ። ከዚህ በላይም ብቻ ባለቤቴ በጣም ነው የምትጨነቀው " አለ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው፣ ፕሮፌሰሩ መደወሉን አላቆመም......

@amba88
@amba88

1 year, 11 months ago

"ናፊባ"
ክፍል ~ ዘጠና አንድ
በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888
የራሺያው Russian Times ጋዜጣና የአሜሪካው Washington Post የኢንስፔክተር ሸዋንግዛውን መታፈን የዜና አርዕስታቸው በማድረግ የእርሱንና የልጆቹን ምስል የፊት ገፅ በማድረግ ከሰፊ ሀተታ ጋር ለንባብ አበቁ። የኢትዮጵያ መንግስት በፍጥነት እየተሰራጨ ላለው የኢንስፔክተሩ አፈና ይህን ያህል አጥጋቢ መልስ ባይሆንም አፈናውን እንደሚቃወምና መንግስት አስፈላጊውን ሀይል በመጠቀም ወንጀለኞችን ለፍርድ እንደሚያቀርብና ኢንስፔክተሩን ነፃ እንደሚያወጣ ዝቷል። ነገር ግን ዜጎቹ ደግሞ በተደጋጋሚ የመንግስትን ለዘብተኝነትን እየተቸ ከአንድ ጊዜም ሁለት ጊዜ የመንግስትን የተሳሳተ አካሄድ ስለሚቃወም ኢንስፔክተሩን ያፈነው ራሱ መንግስት ነው ባይ ናቸው። ይህንን የህዝቡን ፍላጎት የሚያራምዱ በርካታ ተከታይ ያላቸው የማህበረሰብ አንቂዎችም በስፋት እያስተጋቡት ይገኛሉ። በሌላ በኩል ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው በኃላፊነት የሚሠራበት ዋና የግድያ ወንጀል ክፍል ያሉ ባልደረቦች በኢንስፔክተሩ መታፈን ዙሪያ የመንግስት እጅ ይኖርበታል በማለት ጥርጣሪያቸውን ያልደበቁ አባላቶች እንዳሉ አንዳንድ የማህበረሰብ አንቂዎች የተለያዩ ማስረጃዎችን ዋቢ በማድረግ በማህበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ሰንደዋል። የኢንስፔክተሩ መታፈን ታላቅ ፖለቲካዊ ኪሳራ ነውና በኢንስፔክተሩ ጉዳይ መንግስት የወሰደው አቋም ካለ ባስቸኳይ ማብራሪያ መስጠት አለበት ሲል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ይገልፃል"በማለት የፕሬዚዳንቱን ሙሉ ሀሳብ ያሰፈረውን ዜና በስፋት ያትታል። በአንፃሩ የሩሲያ ታየምሱ ዜና ደግሞ "መንግስት የህዝቡን ስሜትና ፍላጎት በሚገባ ሊረዳና ሊያከብር ይገባል። በማንኛውም ዓለም የመንግስት ጠመንጃ ያዥ ሀይሎች እውነትንና ፍትሕን በሚሹ አቢዮተኞች ድል ተደርገዋልና መንግስት ከወዲሁ የህዝቡን ተቃውሞ በጠመንጃ እፈታለሁ ብሎ የሚያስበውን ከመጀመሪያው እንዳይጀምር ከጥልቅ ምሳሌና ማብራሪያ ጋር የሩሲያን የውጪ ጉዳይ ምኒስቴር ቃለ አቀባይ ዋቢ በማድረግ አስፍሯል። በአንድ ጀንበር የአለምን የዜና ሽፋን የተቆጣጠረው የኢንስፔክተሩ መሰወር የኢትዮጵያ መንግስትን ክፉኛ ከማስቆጣትም በላይ አስፈርቶታል። ህዝቡ ደግሞ ከቀፎው ወጥቶ የመንግስት ሁነኛ ቦታዎች ላይ ተቃውሞ ለማስነሳት በመንጋ ለመውጣት የልባቸውን ደወል ብቻ እየተጣበበቁ ይገኛሉ። ውጤት አልባው የፓርላማና የምኒስቴሮች ስብሰባ አሁንም በጭንቀትና በግራ መጋባት ያለ ስአታቸው ቀድመው ወንበራቸውን ይዘው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።የጦር አዛዦችና የመከላከያ አባላትም በዚህ ልዩ የሆነ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ በጊዜ ተገኝተዋል። በዚህ አስቸኳይ ስብሰባም የጦር ውሳኔዎች ሳይቀሩ ይተላለፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ መንግሥት አይንና ጆሮ ነው የሚባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና አስተዳዳሪም በስብሰባው ላይ ተገኝቷል።

"አለቃ ይሄ ነገር በጣም እየተስፋፋ ነው። ምንም የምናደርገው ነገር የለም?" "የምናደርገው ነገርማ አለ አሁን ነው ወደ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው መሄድ ያለብኝ።"በማለት በፈገግታ ታጅቦ ቀጥታ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ወዳረፈበት ክፍል ሊገባ ሲል ከእንደገና ሀሳቡን በመቀዬር "አይ ጥሩ አይደለም ወደ እኔ ክፍል እሱ ቢመጣ የተሻለ ነው። ልጆቹ ፊት ማናገሩ ጥሩ አይደለም። ምን አልባት ፍርሃት ሊያድርባቸው ይችላል። ስለዚህ እናንተ አምጡልኝ" በማለት ወደ ዋና ቢሮው የሚወስደውን ኮሪደር ይዞ መሄድ ጀመረ። ምድራዊው ሰፊ ነፀብራቅ።በርካታ ኮምፒወተሮችና ካሜራዎች የሚበዙበት ይህ ከምድር በታች የተሰራ ህንፃ ፍፁም እጅግ በሚማርኩ ጌጣጌጦችና የቀለም ቅቦች ዲዛይኖች የተዋበ ሲሆን በየግድግዳዎቹም ላይ የኢትዮጵያን መልክና ገፅ የሚያንፀባርቁ ስዕሎች ተሰቅለውበታል። ለአብነት ያህል የአልነጃሺ መስጊድ፣የንግስተ ሳባ ደንገጡሮችና ሎሌዎች እንዲሁም ንጉሱ ሰለሞንን ለመጎብኝት ወደ እየሩሳሌም በመሄድ ላይ እያለች የሚያሳይ ምስል፣ የቅኔ ተማሪዎችና ቁምጣ ለብሰው በረባሶ ጫማቸውን ተጫምተው ራሳቸው ላይ በእዳይት የተጠለፈ ጉኒና በማድረግ ከመርጌቶች ትምህርታቸውን በዋሸራ ሲከታተሉና ሲያጠኑ የሚያሳይ ምስል ይታያል እንዲሁም ወሎ ወረባቦና ሀራ ላይ ታላቅ ሊቅ ዑለማዎች ደረሳቸውን ቁራዕን ሲያስቀሩ የሚያሳይ ምስል፣ በሌላኛው ኮሪደር ደግሞ በሬዎቹን እያረሰ ከኋላው የምታጎለጉለውን ሚስቱን ዞሮ ሲመለከት የሚያሳይ ምስል፣ በሌላኛው ግድግዳ ደግሞ የገደሉ አፋፍ ላይ ተቀምጦ ከፊት ለፊቱ ማዶ ላይ የሚወርደውን የፏፏቴ ድምፅ እየሰማና ጭሱን እየተመለከተ በዋሽንቱ ተፈጥሮን በትንፋሹ የሚዘክር ድንቅ እረኛ ይታያል። ይህ ምስል ድምፅ ሲያወጣ ነፍስን በዋሽንቱ ዜማ ሲያመንን ከምስል አልፎ በድምፀም የሚያጋባ ነው። በሌላኛው ገፅ ደግሞ አንዲት አቅመ ደካማ የምትመስል ሴት አንገቷን ወደ ግራ ጠንዘል አድርጋ ወፍጮ ስትፈጭ ያሳይና ከእሷ አናት ላይ ደግሞ ዶሮዎች የቤቱ ምሰሶ ላይ ቆመው ያሳያል። ይች የተንጋደደች የገጠር ጎጆ ውስጥ የሚታይ ምስልም ሌላኛው ትልቅ ሀሳብ የተንፀባረቀበት ምስል ነው። እነዚህነና ሌሎችም በርካታ አይነት ምስሎች ያሉበትን ቦታ አልፎ ወደ ቢሮው ሊገባ ሲል በሩ ላይ በትልቅ ሸራ የሚታየው ምስል ይበልጥ ኢትዮጵያን የሚገልፅ ይመስላል ሁለት መርጌቶችና ሼሆች በሀሴት ፈገግ ብለው የሚታዩበት ምስል ሲሆን ከጎኑም በርካታ ሰዎች የሚገበያዩበት የገበያ ቦታ ይታያል። ምስሉ የድሮ መልክ እንዲኖረው black &white ቀለምን ተጎናፅፏል።በሩን ከፍቶ በቀጥታ ኮቱን አውልቆ የኮት ማስቀመጫው ላይ አስቀምጦ ወንበሩ ላይ ተቀመጠ። ወንበሩን ወደ ኋላና ወደፊት እያደረገ አንድ ክብ የሚሆን ከተሽከረረከ በኋላ ከመሳቢያው አንድ ሪሞት አውጥቶ የቀይ መብራቷን ሲነካ ፊት ለፊቱ የተቀመጠው ባለ 45 inch የቴሌቪዥን እስክሪን ተከፍቶ በጥሩ ጥራት እያንዳንዱ ኮሪደር ላይ ያሉ እና ውጪ ላይ የተገጠሙ ካሜራዎቸን ይመለከት ጀመር።
ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው የልጆቹን ፀጉር እያሻሸ ባለበት ወደ ጆሮው ጠጋ ብሎ" አለቃዬ አሁን ሊያገኝህ ይፈልጋል። ለአንተና ለልጆችህ ባለው ፍቅርና አክብሮት የተነሳ ወደ ክፍልህ መጥቶ ሊያገኝህ ነበር ሀሳቡ ነገር ግን ልጆችህ እንዳይፈሩ በማሰብ ወደ ቢሮው እንድትመጣ ይፈልጋል" አለ ቀልጠፍ ያለና ፊቱ ላይ የፈገግታ ፅንፍ የማይለየው ወጣት። ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው በፅሞና ካዳመጠው በኋላ በወጣቱ ሀሳብ በመስማማት አንገቱን ነቀነቀና ልጆቹን በቀስታ አስተኝቶ ተነስቶ ይከተለው ጀመር። ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው የግድግዳ ምስሎቹን ሲመለከት ፍፁም የሆነ አግራሞትን ፈጥሮበታል። በዛን ስአት በርካታ ጥያቄዎችን ራሱን እየጠየቀ ስለሰውዬው ሀገራዊ ፍቅር ለመገመት አፍታ አልፈጀበትም።ስዕሎቹ እንኳን የሀገር ፍቅር የሚሰማውን አንድ ኢትዮጵያዊ ይቅርና የሌላ ሀገር ዜግነት ያለውን ሰው ሳዬቀር የሚያማልሉና ሆድ የሚያባቡ ናቸው።ፍፁም ሰላማዊ ና እረፍት እንዲሰማ የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያዊያንን የሚገልፁ በመሆናቸው ኩራትም ሀሴትም ተሰምቶታል። ምስሎቹን ለመመልከትና በደንብ ለማጤን ዘግየት ሲል ከፊት ለፊት ሆኖ የሚመራው ወጣት ቆም ብሎ ሲጠብቀው ከእንደገና እየጠበቀው መሆኑን ሲመለከት ሲከተለውና ሲተያዩ በፈገግታ እየተሸነጋገሉ ዋና ቢሮው ደረሱ።

@amba88
@amba88

1 year, 11 months ago

ሰላም እንደምን አመሻችሁ ዮቶራዊያን እስኪ ዛሬ በአንድ ወሳኝ ሀሳብ ላይ እንመካከር።

ስለ ራዕይ እናውራ። ራዕይ ምን ማለት ነው? ለምንስ ያስፈልጋል?

1 year, 11 months ago

"ናፊባ"
ክፍል ~ ዘጠና ~
በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888
"ይሄን ሁሉ ድራማ የፃፉት ግን እነማን ናቸው?"ስትል ራሷን ብትጠይቅም ዳሩ ግን ለእሷ ትልቅ እፎይታን ፈጥሮላታል።ከሁሉም ነገር ገሸሽ ያደረጋት በመሆኑ ትልቅ ደስታን አጎናፅፏታል። ያለውን ነገር ለማጣራት ለወንድሟ በተደጋጋሚ ብትደውልለትም ስልክ ሊያነሳላት ባለመቻሉ በፈገግታ ውስጥ ሆና "ምነው አንተ እንደዚህ ጠፋህ የመጨረሻሽ ነው ተደርሶብሻል ምናምን እያልክ ስታቅራራ አልነበረም እንዴ ምነው ዝም አልክ?"የሚል ስላቅ የበዛበት መልዕክት ብትልክለትም አንድም ምላሽ ባለማግኘቷ የሆነ ሀሳብ ነገር ገብቷታል። ምን አልባት ተንኮል እየሸረበ ይሆን? ወይንም እዚህ ሁሉ ግብግብ እጁ ይኖርበት ይሆን? አዎ ሊኖርበት ይችላል።ያው የኢንስፔክተሩ ደጋፊ አይደል። እኔ ላስገድለው እንደሆነ ገብቶታል ማለት ነው!።ነገር ግን ያልገባኝ የመንግስት ሀይሎች ለምን ባልተጠበቀ መንገድ እንደዛ ሊጠብቁት በድንገት ፈለጉ? ትንሽ ጥያቄ የሚያጭረው እሱ ነው!" አለችና ስልኳን አንስታ ለአንድ ታማኝ የመረጃ ምንጯ ደውላ ስትጠይቅ ሁሉንም ነገር አጫወታት።ራሷን በፈገግታ እየነቀነቀች "በቃ አንድ አረም ነቀልኩ።ከዚህ በኋላ መንግስት ለራሱ ሲል ይከታተለዋል።እናም ወደተቀዛቀዘው ስራዬ ሙሉ ለሙሉ በመዞር አቅሜን ና ሀብቴን በመጠቀም ያለምንም ሰቀቀን መስራት እችላለሁ" በማለት ተንጠራራችና ስልኳን ከፍታ ስትመለከት ሶሻል ሚዲያው በሸዋንግዛው ፎቶ ተጥለቅልቋል። የተፃፈውን የመንግስትን አፈናም ስትመለከት ድንግጥ አለች።በፍፁም መንግስት ራሱ ያስረዋል የሚል ግምት አልነበረባትም። ሁሉም ሰው በስአት በሚባል ደረጃ አጥለቅልቆታል።

"በጣም የሚገርም ነው። ሶሻል ሚዲያ ለካ መሳሪያ ያልታጠቀ ወታደር የሚኖርበት ቦታ ነው። በዚህ ስአት ብቻ ከሁለትመቶ ሺህ ሰው በላይ ተደራሽ ሆኗል። ኢንስፔክተሩን ፕሮፋይል በማድረግ ከወዲሁ "እኔ ከሸዋንግዛው ጎን ነኝ!" የሚል ሀሽታግ እየተጠቀሙ ከጠበቅነው በላይ ነገሩን አግለውታል። በራሪ ወረቀቱም በሚገባ ነው ስራውን የሰራው።አሁን ህዝቡ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰ ይመስላል። ወትሮም ይሄን መንግስት የታገሱት በኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ከመጠን ያለፈ እምነት ስላላቸው ነው እንጅ መንግስቱ ቋቅ ብሏቸዋል።" "በጣም አሪፍ ታዲያ እኛስ የምንፈልገው ይሄን ስርአት መቀየር አይደል?!"አለና በፈገግታ። " አየህ ወዳጄ ሀገር ዝም ብላ አትመራም በህዝብ ይሁንታና እሺታ እንጅ። ህዝብ የወደደው መሪ ምንም አይሆንም ከማንም እና ከምንም ነፃ ይሆናል። ሸዋንግዛውን ተመልከት ሀብቱ ስልጣኑና ገንዘቡ ሳይሆን ህዝቡ ነው። በህዝቡ ውስጥ ደግሞ ዝም ብሎ አይደለም የገባው። በቀላል ስራ ብቻ።ስራውን አክብሮ በሀቀኝነት ስለሰራ ነው። ለምሳሌ የቱርኩን ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ብንመለከት መፈንቅለ መንግስት ሊካሄድበት ሲል እናቶች ናቸው ታንክ ስር ሆነው ነፍሳቸውን ሳይሰስቱ በመስጠት ነፍሱን ያዳኑት።ከአሜሪካ ባርነትም ህዝቡ ራሱ የሚፈልገውን መሪ በመጠበቅ አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ደርሳለች። እኔም የምፈልገው ሀገሬን እንዲህ አይነት የህዝብ ልጅ የሆነ መሪ እንዲመራት ነው። የህዝቡን ደህንነት የሚጠብቅ ችግሩን በሚገባ ተረድቶ ለችግራቸው እውቅና ብቻ ሳይሆን መፍትሔ የሚለግስ መሪ እንዲኖር። የትግሌ ራዕይ ይሄ ነው። እናንተ ገና ልጆች ናችሁ ከእናንተ በታች ያሉት ደግሞ ይበልጥ ልጆች ናቸው። ሀሳባቸው የሰላም እና የምግብ እጦት መሆን የለበትም። ከማንም ጣልቃ ገብነት የተገለለች የማንም ቡችላ ነጭ እንደፈለገ ሀሳብ የማይሰጥባትን ሀገር መገንባት ነው።ለዚህም ነው ትልቅ ዋጋ የምከፍለው።"አለና ትከሻውን መታ መታ አድርጎት የምድሩን አሳንሱር ነክቶ ወደላይ ወደ አፓርትመንቱ የሚያስወጣውን ቁልፍ ተጫነ "ግን እስካሁን እኮ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛውን አልጎበኘኸውም" አለ "ገና ነው የምጎበኘው አሁን አይደለም ልጅ። ጊዜው ራሱ ሲደርስ እኔ እሄዳለሁ።አሁን ከራሱና ከልጆቹ ጋር ጊዜ እንዲያሳልፍ እንተወው።አሁን ከምንም በላይ የሚያስፈልገው እኔን ማወቅ ሳይሆን ልጆቹ ጋር ጊዜ ማሳለፉ ነው" በማለት ስቆ ወደ ላይ ይወጣ ጀመር።

መንግስት በሶሻል ሚዲያው በከፈተው አብዮት በጣም ደንግጧል።ሁሉም ነገር ሊቆጣጠረው ከሚችለው በላይ ሆኖበታል።ባሰበው መንገድ ሳይሆን ባልጠበቀበትና ጭራሽ ፈፅሞ ባልገመተው አካሄድ በመሄዱ ጭንቀት የወለደው መግለጫ በመንግሥት ኮምኒኬሽን ክፍል በኩል ተከታዩን መግለጫ ሰጠ።" የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዞቦች ከምንም እና ከማንም በላይ እናንተ ዜጎቻችን አምናችሁን በመረጣችሁን መሠረት ሀገራችንን እያገለገልነበት ባለበት በዚህ ጊዜ ለወራት የቀጠለው የግድያ ተግባር በመቀጠሉ ከምንም በላይ በሀዘን የተቀጣን ብንሆንም ነገር ግን አንዳንድ ግለሰቦች ደግሞ የእነዚህን አሸባሪ ሰዎች እኩይ ተግባር ለማስፈፀም የሚታትሩ እንዳሉ እናውቃለን።ወንጀለኞችንም ለፍትህ ለማቅረብ ተግተን እየሰራንበት ባለበት በዚህ አጣብቂኝ ወቅት አንዳንድ ሰዎች የመንግስትን አደረጃጀት ጥላሸት በመቀባትና ያለስም ስም በመስጠት ላይ ሲሆኑ ለዚህም ማሳያቸው በሬ ወለድ ትርክታቸው በመሆኑ ከሰሞኑም በእናንተው ልጅ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ጉዳይ የተለመደ ውሸታቸውን እና የፈጠራ ታሪካቸውን በዚህ በሶሻልሚዲያ እያስተጋቡ ይገኛሉ። የእኛ የጥበቃ ሀይሎች ከሰሞኑ የዋና ሳጅን አክሊሉ የሺህዋስ ሞት በኋላ በተፈጠረ ስጋት የኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ጉዳይም ስጋት ስለጣለን ከመንግስት ጋር በመነጋገር ልዩ ኮማንዶዎችን ለደህንነቱ በቤቱ አቅራቢያ ለጥበቃ ብናሰማራም ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ተኩስ ተከፍቶ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛውንና መላ ቤተሰቡን ይዘው የተሰወሩ ሲሆን ለዚህ እኩይ ተግባራቸውም ራሳቸውን ከሳሽ አድርገው መንግስትን እየወቀሱ ይገኛሉ።ምንም እንኳ ህዝባችን ይህንን መረዳት አይችልም ብለን ባናስብም ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናልና ከዚህ የድግግሞሽ የበሬወለድ ዜና ራሳችሁን በማራቅ የተለመደውን አብሮነታችሁንና ትብብራችሁን እንፈልጋለን። መንግስትም በአሁኑ ስአት ሙሉ ሀይሉን በማሰማራት ከየአካባቢው የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን ታጋቾቹን ኢንስፔክተር ሸዋንግዛውን ሁለት ልጆቹን እንዲሁም የወንድሙ ልጅ የሆነችውን ሲሐምንና ባለቤቷን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ሲሆን ለዚህም የእናንተን የህዝባችንን እርዳታ እንጠይቃለን!" በማለት ለሁሉም የሀገሪቱ ሚዲያዎች መግለጫ ሰጡ። መግለጫውም በሬዲዮዎችና በቴሌቭዥኖች ተስተጋባ።

@amba88
@amba88

1 year, 11 months ago

"ናፊባ"
ክፍል ~ ሠማንያ አምስት
በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888
"ሙሉ አዳር አልወጣም። ሲመስለኝ መርዶው አልተነገረውም። የዋና ሳጅኑን መሞት ቢሰማ ኖሮ አስችሎት አይቆይም!" አለ የራሱን ፀጉር በጣቶቹ እየመነሸረ። ከእንቅልፍ መባነኑ እንዳይታወቅበት በተቻለው መጠን ሳይተኛ እንዳደረ ለማሳወቅ እየጣረ።" ተኝተህ በነበረበት ስአት ሄዶ ከሆነ ግን እኔ የለሁበትም!!" ንዴት የተቀላቀለበት ዱብዳ አነጋገር "ኧረ በጭራሽ ለሰከንድ ያህል እንኳን ልተኛ አላንቀላፋሁም።አይኔንም ከበራቸው አልነቀልኩም"አለ "እሺ ብቻ ለቅሶው ጋር ቀድሞህ ከተገኘ የሚያሳውቀኝ ሌላ አባል አለ" ብላ አስፈራራችውና ስልኩን ዘግታ አዲስ ነገር እንዳለ ለማወቅ ስልኳን ወደሌላኛው አሻንጉሊቷ ደወለች። የስልክ ተቀባይዋም ስልኩን አንስቶ ምንም ነገር እንደሌለና እስካሁን እንዳልመጣ ሲነግራት ከጥርጣሬዋ በመላቀቅ እፎይ አለች። ጥርጥሬ እንደምግብ የምታመሰኳው ነገር ነው። ለእሷ እያንዳንዱ ድርጊት ትልቅ ትርጉምና ዋጋ አለው። ይህን ምስጢራዊ ቡድን በሀላፊነት ስትመራ እያንዳንዱ ሰራተኛዋን በጥርጣሬ ነው የምትመለከተው። አንዳቸውንም የውሸት እንጅ የእውነቷን አታምናቸውም። ሁሉም የግቧ መውጫ መሰላላቸው እንጅ ሌላ አንዳች ጥቅም የላቸውም። ለዚህም በእነሱ ፊት ኮስታራ ፊቷን ነው ሰርክ የምታሳያቸው። አሁን ላይ ግን በርካታ ሰራተኞቿን በሞትና በክህደት ካጣች በኋላ ውስጧን ፍርሃት ቢገባውም ፍርሀቷን ግን በእነሱ ፊት አታሳይም።ቀን በቀን በወንድሟ እየተሳደደችም ፅንፍ ህልሟን ለማሳካት ማንኛውንም ነገር ማድረግ እንዳለባት አውቃለች። በጥንቃቄና በብልሀት የተወጠሩት የሚሽን ክሯቿ ለመበጠስ እየመነመኑ ቢመስሉም ነገር ግን እሷ በፍፁም ተስፋ አልቆረጠችም። ነገር ግን ግማሽ ነፍሷ የተሸነፈች እንደሆነ ይነግራታል። ቢሆንም እስከመጨረሻው ድረስ እታገላለሁ በሚል ፅኑ ፍላጎት መንገዷን ቀጥላለች።

ንጋት ከጨለማ ወስዶ መልዕይተ ቀኑን ለፀሐይ ካስረከበ በኋላ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው በማለዳ ቢነቃም ሀዘን እንዳጠላበት ነው። እስካሁን ፊቱ በጭራሽ የነቃ አይመስልም። የክብር ልብሱን አንድ በአንድ ከለበሰ በኋላ "በል ተሕሚድ ውሎዬ ለቅሶ ላይ ነው የሚሆነው።አንተ እንግዲህ የተለዬ ነገር ለማንኘት ሞክር የቻልከውን ያህል ጣር። ይሄ ሊሆን ይችላል ብለህ የጠረጠርከውን በሙሉ በማስታወሻህ ይዘህ ጠብቀኝ።የሕይወቴ ፈታኙና እጅግ ልዩ ትርጉም ያለው ምርመራዬን ነው የተጋራኸኝ። ከአንተ የሚጠበቀው ጥርጣሬዎችህነ ባገኘኽበትና ባሰብክበት ልክ ማስፈር ነው የሚጠበቅብህ ሌላ ከአንተ ምንም አይጠበቅም።ብሎ ትከሻውን መታመታ አድርጎት ትቶት ወጣ ።
ሸዋንግዛው በሀሳብ ውስጥ ትክዝ እንዳለ ነው። በአንዳች ነገር ክንፉ ተሰብሮ ዋጋ ቢስ የማይረባ ንስር ስነልቦናን ሀያ አራት ስአት ባልሞላ ጊዜ ተላብሷል። አቅሙ እስከዬት እንደሆነ የነገሩት መሰለው። የነዚህ ምስጢራዊ ሰዎች ማንነትና ምንነት የውሃ ሽታ ሆነበት። ሁኔታው ከአቅሙ በላይ እንደሆነ እንዲያውቅ አውቆም እንዲያምን ያደረጉት መሠለው።በዚህ ሁሉ የራስ ጥያቄና መልስ ተወጥሮ ባለበት ዝም ብሎ የመሀሉን ስፖኪዮ ሲመለከት ከኋላው ባለ አንድ ቅያስ ላይ መኪና ቆሞ ተመለከተ። ሽጉጡን ከመሳቢው አቀባብሎ በማውጣት ቀስ አድርጎ ማርሹ ጋር ያለበት ክፍት ቦታ ቀስ አድርጎ አስቀመጠው። ሰረቅ አድርጎ ወደ ኋላ እየተመለከተ "እነዚህ ውሾች እኔንም እየተከታተላችሁኝ ነበር? የማትረቡ ብሎ ሊዞር ሲል አይኑ ላይ አንድ ነገር ተመለከተ። የሚከታተለው መኪና ላይ "ዓደይ ሞል" የምትል በራሪ ወረቀት ነገር የመኪናው መስታውት ላይ ተመለከተ። የምፀት ፈገግታ ፈገግ አለና "መች አጣኋችሁ የዚህን ሰው ማንነትና ምንነት ያወኩ ጊዜ ያኔ እኔ ኢንስፔክተር ሸዋንግዘው አይደለሁም ልጆቼን ይንሳኝ!" አለ ከንፈሩን ንክስ እያደረገ።

ሲሐም ኤሌዝንና ብሩክታዊትን ትምህርት ቤት አድርሳ ከመጠች በኋላ ተሕሚድን ትተሻሸዋለች።"ኧረ ተይ የኔ ፍቅር ኢንስፔክተር በጣም ትልቅ ሀላፊነት ነው ሰጥቶኝ የሄደው"አለ የሚሰራውን ስራ አቁሞ አይኖቿን በስስት እየተመለከተ። " ትንሽ ጊዜ ብቻ ነው እኮ።ከዛ ስራዬን ስጨርስ ምንም ችግር የለውም።የፈለግነውን ጊዜ አብረን እናሳልፋለን"ብሎ ወደስራው ሊዞር ሲል ሲሐም መላፋቷን ስትቀጥል ትሕሚድ ቦግ አለበትና "እየነገርኩሽ አይደል ሲሓ! ምንድን ነው እንደ ህፃን ልጅ የምታዳግሚኝ"ብሎ ኮስተር አለባት። "እና ልትቆጣኝ ነው?" አለች እሷም ከመቅፅበት ኩስትር አለች። "የምገላው ባህሪሽ ይሄን ነው።በተደጋጋሚ ነግሬሻለሁ።ከዚህ በኋላ ግን ደግሜ አልነግርሽም እንዳታስቢው እሺ"አለና ዝም ብሎ ወደ ላፕቶፑ አይኖቹን ላከ። ሲሐም ጥፋቷ ታውቋት ይሁን በተሕሚድ ተናዳ በውል ባታስታውቅም እየተመናቀረች ክፍሉን ለቃለት ወጣች። የእሷን መውጣት ተከትሎ ትንሽ ጊዜ ከቆዬ በኋላ በሩን ከውስጥ ቆለፈው። መዘጋቱን የተመለከተችው ሲሐም ይበልጥ በመናደድ "ቆይ አሁን በሩን መዝጋት ምን ይሉታል?" ብላ አጉተመተመች።

በርካታ የፖሊስ መኮንኖች፣ የፖሊስ አባላት፣ የፌደራል ፖሊሶች፣የደህንነት ተወካዮች ሰቪሎች እና ሲቪሎች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ከሆስፒታል የአስከሬን የማውጣት ስነስርአትና በክብር እየተደረገለት ይገኛል። ሁሉም ፊት ላይ አንዳች ሀዘን ይነበባል። በተለመደው ዝግጅት በስነስርአት አስከሬኑ ወደ መኖሪያ ቤቱ ተሸኝቶ ዘመድ አዝማድ የስራ ባልደረባዎችና ጓደኞች በተገኙበት የማስተላለፍ ስራ ከተሰራ በኋላ የሁሉም የፖሊስ የደህንነትና የወንጀል ምርመራ ክፍል እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ ለስብሰባ እንዲገቡ የፍትሕ ምኒስቴሩና የደሕንነት ኃላፊው ለሁሉም መረጃውን አደረሰ።
ጥሪ የተደረገላቸው የስራ ሀላፊዎች ሁሉም ተገኝተው ስብሰባው መካሄድ ሲጀምር ሁሉም በየተራ ሀሳብና አስተያየት መስጠት ጀመረ። ሰብሳቢዎቹም ፍፁም በሆነ መረጋጋት የተፈጠረው ነገር ምንም ሳይመስላቸው ፊታቸውን አለስልሰው ልባቸውን አደንድነው ስበሳባቸውን ማካሄድ ቀጠሉ። ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ለአንድ ሀያ ደቂቃ ስብሰባው አብ የሚል ነገር ያለው እስኪመስለው ድረስ ቢቆይም ነገር ግን። ዝም ብሎ ሁኔታውንና ድርጊቱን ውሃ ለመቸለስ ለማቀዝቀዝ እንደሆነ ሲረዳ የደህንነት ምኒስቴሩ ለአስተያየት ሰጪዎች እድል በሚሰጥበት ጊዜ እጁን አውጥቶ እድል ከተቀበለ በኋላ የደህንነት ምኒስቴሩን ይሁንታ ሳያገኝ መናገር ጀመረ። ሁሉም በድንጋጤ ዞረው ተመለከቱት "እስካሁኑ ደቂቃ ዴረስ በትዕግሥት ስጠባበቅ ነበር። ምን አልባት ሄደን ከምንሰራው ስራ በላይ የበለጠ ቁምነገር ካለ ብዬ ነበር የተቀመጥኩት። እንጅ የፖለቲካ ሽኩቻውንና አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር ስብሰባ የምትሉት ነገር በጣም ይሰለቻል። ትላንት ንፁሀኖች ሲሞቱ ነበር።ዛሬ ደግሞ ይሄው ቢሯችን ላይ ገብቷል።ዋና ሳጅን አክሊሉ የሺህዋስ ከወራት በፊት ልክ እንደኛ የንፁሀን ደም ደመክልብ ሆኖ እንዳይቀር ለዘመዶቻቸው ደግሞ ፍትህን ለማስገኘት ሌት ተቀን ሲሰራ የነበር ጓዳችን ነበር። ነገር ግን በዚህ ስአት እሱም የነዛ ምስኪን ዜጎች እጣ ፈንታ ደርሶት እሱም አርፏል። እኛ ደግሞ አሁንም በቸልተኝነት ስብሰባ ላይ ተቀምጠን የማይሆነውንም የሚሆነውንም እያወራን ነው። ይቅርታ እኔ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ ስብሰቤውን መቀጠል አልችልም!" ብሎ .......

@amba88

1 year, 11 months ago

"ናፊባ"
ክፍል ~ ሠማንያ አራት
በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888
"እስካሁን አልተኛሽም የኔ ፍቅር?" አለ። "እንዴት ብሎ እንቅልፍ ይውሰደኝ አንዱን ከአንዱ እየደራረብኩ ሳስብ"አለች። "ምንድን ነው እንደዚህ በጣም ተጨንቆ ማሰብ እ የኔ ፍቅር ሀሳብሽንም ጭንቀትሽንም ልወስድልሽ ወይም ልጋራሽ አይደል ባልሽ የሆንኩት። በይ ሁሉንም አንድም ሳታስቀሪ ንገሪኝ አለና ብብቶቿን እየነካ ሊያስቃት ሞከረ። ሙከራው ባክኖ አልቀረም። በሚገባ ነው የሳቀችለት። ተሕሚድም በዛው እቅፍ አድርጎ ወደ እቅፉ አስጠግቶ ይስማት ጀመር።ጥልቅ በሆነ የስሜት ውቅያንስ ውስጥ ሆነው እየተሳሳሙ ከቆዩ በኋላ ተሕሚድ በጆሮዋ የሆነ ነገር ሹክ አላት። ሲሐም በሳቋ ልጆቹንም ላለመቀስቀስ እንዲሁም ሸዋንግዛውን ላለመረበሽ አፏን አፍና ለረጅም ጊዜ ሳቀችና "አርፈህ ተኛ የራስህ ቤት እንደለመድከው ይሻልሀል። ይሄ የሰው ቤት ነው። የሆነ ድምፅ ብናሰማ አጎቴ ይረበሻል። አጎቴ ደግሞ እንዲረበሽ አልፈልግም"አለች እየሳቀች።እና በዚህ ስአት ከባልሽ በላይ የምታስቢው ለአጎትሽ ነው ማለት ነው?"አለ ተሕሚድ ለቀልድ ያህል ኮስተር እያለ። "አዎ በመጀመሪያ በቤቱ ልናከብረው ይገባል።ሁለተኛ ደግሞ ያው አጎቴ ነው ሶስተኛው ደግሞ ያው አጎቴ ነው"ብላ ስቃ ከንፈሩን ጉርስ አደረገችውና ሰውነቱ ላይ ልጥፍ አለች።

"አንተ ለሊቱን በሙሉ ሳስብ እኮ ነው ያደርኩት የሆነ ነገር ገርሞኝ" "ደግሞ ምንድን ነው የገረመህ?" "አንድ ያልጠበኩት ልጅ ያልጠበኩት ቦታ ላይ አግኝቼው!"አለ "ደግሞ ማን ነው ያልጠበከው ቦታ ያገኘኸው? ሲጀመር ሸዎች ስንባል እኮ ያልተጠበቅንበት ቦታ መገኘት ደስ ይለናል! ስለዚህ ብዙ መደነቅህን አቁም። እኔ ብዙ ሰዎችን ያልጠበኳቸው ቦታ አግኝቻቸዋለሁ። ሲጀመር የነሱን መዳረሻ የሚያውቁት እነሱ እንጅ አንተ ወይም እኔ አይደለሁም። አሁን ለምሳሌ ባለው የሰዎች ተግባቦትና ለእኛ እሱ በታዬን ልክ ይሄ ልጅ እንዲህ ቢሆን እዚህ ቦታ ላይ እናገኘዋለን። ይሄ ቦታ ይሆነዋል ብለን እናስባለን!። ነገር ግን ሰውዬው ውስጡ ላይ ያለውን መነሸጥ አናውቀውም።ስለዚህ ማንንም በየትኛውም አጋጣሚ ብታገኘው መገረም የለብህም ጃል!" "አንተ ደግሞ እስኪ ዝም ብለህ አትቀደድ ለመሆኑ ስለማን እንደማወራ አውቀህ ነው እይደዚህ የምትለኝ?" "እኔ ደግሞ ማወቅ አይጠበቅብኝም አልኩህ።አጠቃላይ የሰዎችን ስነ ባህሪ ና ድብቅ መሻት ያጠናውን ሳይንስ ቀይጬ ነው የነገርኩህ። ሰዎች አሁን ያልጠበካቸው ቦታ ካገኘኻቸው።ያ ለማንም ያልተገለጠው የእነሱ የውስጥ መሻት ብቻ የነበረ ሁነት እንጅ አንተ እንዳየኸው ባጋጣሚ ላይ የተመረኮዘ አይደለም።ስለዚህ አእምሮህን ሰፋ አድርገውና በሰዎች ከመደነቅ ወጣ በል"አለ "ዛሬ ምንድንነው በጠዋቱ እየጋትከኝ ያለኸው? ለመሆኑ አንተ በምን ስራ እየሰራህ ነው እንደዚህ በጠዋቱ ልቤን የምትጠባው?" "አንተ የማትጠብቀው ቦታ ነው እየሰራሁ ያለሁት"አለና ሳቀ። "በቃ እሺ ወዳጄ ምንም ስራ ችግር የለውም።እኔ አሁን የደወልኩበት የተሕሚድን ጓደኛ ስልክ እንድታፈላልግልኝ ነው።" "ቆይ እስኪ እኔ ጋር ልፈልግልህ።አይጠፋም በቅርብ ነው ከእኔ ጋር ራሱ የተገናኘነው!" "የምር በጣም ደስ ይላል ምን ላይ ተገናኝታችሁ ነው? ስራችሁ ተመሳሳይ ነው እንዴ?" በማለት አጋጣሚውን በመጠቀም ጥያቄዎችን ሲያዥጎደጉድበት "ምነው ሰውዬ የአጋጣሚውን ቀዳዳ ተጠቅመህ በጥያቄ ዘጋኸቸውኮ ቀዳዳዎቹን። የምርመራ ቡድን ውስጥ ነው እንዴ የምትሰራው"ብሎ ኩም ካደረገው በኋላ "ለማንኛውም በአንድ ካምፓኒ በተዘጋጀ ሴሚናር ላይ ነው የተገናኘነው። እሱ ደግሞ የክብር እንግዳ ነበር የሕይወት ልምዱንም (Life Experience Share) ሲያጋራን ነበር። ሲበዛ ትሑትና አስተዋይ ልጅ ነው። የቃላት ቅንብሮቹም እጅግ የሚገርሙ ናቸው በጣም ደስ የሚል ልጅ ነው!" "ኧረ በጣም ይገርማል።ስለዚህ የዛን እለት ያለ ጉዳዩ ነዋ የመጣው። እኔ ደግሞ ስራው መስሎኝ ነበር!" "ቆይ የፈለከውን ለምን በቀጥታ አትነግረኝም!" "ምን እንደሚሰራ ማወቅ ፈልጌ ነው!" "ለምንህ?" "ያው ማወቁ መች ይጎዳል ይጠቅማል እንጅ። ለአንድ ወንድሜ ስራ እያፈላለኩ ስለሆነ ድንገት ትዝ ብሎኝ ነው። ሌሎቹንም እያስታወስኩ ስለነበር" ብሎ መከላከያ ሀሳብ አቀረበ። አሁንም ግራ በመጋባትና በሰጠው ምክንያት ባለመርካት በእርጣሬ "እንደዛ ከሆነ ቀጥታ ተሕሚድን ከመጠየቅ እኔን አትጠይቀኝም ነበር። ለእኔ ደውለህ እኔን መጠየቅ እንዳለብህ ረስተኸዋል ወይስ ትዝ አላልኩህም?" በማለት የመጨረሻ የሚመስል ጥያቄ ጠየቀው። ስህተቱ ወዲያው ገባውና "ፅ ፅ ልክ ነህ በናትህ እግዚአብሔርን አንተን መጠየቅ እንዳለብኝ ርስተሰ አድርጌዋለሁ። በዛ ላይ ሁልጊዜ የማገኝህ ያህል ሆኖ ነው የተሰማኝ ለማንኛውም አሁን ይቅር ካደረክልኝ አንተም ፈልግለት"አለ መንተፍረቱን "አይይ የአንተ ነገር ለማንኛውም ከቀልብህ ሁን። እንደ እውነቱ ለመማገር ከተሕሚድ ጋር ችግር ያለብህ ነው የምትመስለው አጠያየቅህ አወራርህ"ብሎ ትንሽ ፈገግ ካለ በኋላ "እንደ እውነቱ ለመናገር ምን እንደሚሰራ እንኳ አላውቅም ግን ሲመስለኝ አንድ ትልቅ ድርጅት ላይ ነው የሚሰራው እይደዛ ባይሆን በክብር እንግድነት ተጋብዞ የሕይወት ልምዱን እንዲያካፍል አይጋበዝም ነበር። ዝግጅቱ ደግሞ ደመቅ ያለ ነው። ከዛ አንፃር የገመትኩት ይሄን ነው ግን የጓደኛውን ስልክ እልክልህና እሱን በይበልጥ ትጠይቀዋለህ" አለና ዝም አለ። "አመሰግናለሁ በቃ በቴክስት ላክልኝ ወይም አጠገቤ ማስታወሻ ስለያዝኩ በቃልህ ልትነግረኝ ትችላለህ"አለና ምላሹን ይጠብቅ ጀመር። ጥሩ እሽ ያዝ አለና ንግግራቸውን ያሳየው ቋርጡ እዛው ስልኩ ላይ በመፈለግ የጓደኛውን ስልክ ነገረው።"በጣም አመሰግናለሁ ጓደኛዬ" በማለት ላደረገለት ነገር ሁሉ በትሕትና አመስግኖ ዘግቶ ምንም ደቂቃ ሳያባክን በቀጥታ ወደተቀበለው የተሕሚድ ጓደኛ ቁጥር ደወለ። በአሁኑ ስአት ጓደኛ እንዳልሆኑና በእሱ ስራ ምክንያት ለጊዜው እንደተዘጋጉ አስቀድሞ እያንዳንዱን ነገር አንድ በአንድ ሁሉንም አጫወተው።
"እና አለቃ ጓደኛው እንደነገረኝ ተሕሚድ እጅደጠረጠርነው ስውር ፖሊስ ሳይሆን የኢንስፔክተር ሸዋንግዛውን የወንድም ልጅ አግብቶ ነው። ከእሱ ጋር የተዛመደው። እና ልጁ እንዳለኝ ከሆነ ኢንስፔክተር በፈለገው ጊዜና ወቅት ሁሉ አብሮት ይታያል ነው የሚለው።እንጅ ትክክለኛ የስራ ፖዚሽኑ በአንድ የውጪ ግብረሰናይ ድርጅት ነው የሚሰራው NGO ውስጥ መሰለኝ የሚሰራው"በማለት የሰማውን መረጃ በሙሉ ነገረው። "በጣም ጥሩ ነው የሰራው።እኔ የምወደው እንዲህ አይነት የተፋጠነና ጥራት ያለው ስራ ነው። ጎበዝ በርታ አሁን በአጭር ጊዜ ይሄን ያህል መስራት ከቻልክ ምንም የሚያቅትህ ነገር አይኖርም።በርግጥ እስካሁን ያቃተህ ስራ የለም።አሁን ዋናው ነገር ስለ ተሕሚድ ይሄን ያህል ካወክ ሌላው ትርፍ ስራ ነው። ስለዚህ በቅርቡ የኢንስፔክተር እህት ታግታለች ተብላ የተወራላት የተሕሚድ ባለቤት ነበረች ማለት ነው"አለና "በል ይሄኛውን ግዴታህን በሚገባና ያለጊዜው ስለጨረስክ መጥተህ ቡድንህን መቀላቀል ትችላለህ!" ብሎት ተሰናበተው። የደስታ ወጋገን ፊቱ ላይ እንደ ብርሃን ፀዳል ተጎናፅፎ በሀሴት ፈገግ አለ። ማንም ሰው የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት ሲወጣ በጣም ደስ ይሰኛል።የእሱም የነፍሱ ጥጋብ የተጣለበትን ኃላፊነት እንደተወጣ ኃላፊነቱን በሰጠው ሰው ማረጋገጫ ሲቀበል ነበር።

@amba88
@amba88

1 year, 11 months ago

"ናፊባ"
ክፍል ~ ሠማንያ ሦሥት
በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888
"ተመልከት ኢንስፔክተር አሁን ለምሳሌ ይችን ፓርት........"አለና ቪዲዮውን አቁሞ ዙም እያደረገ "ይችን አምፖል ቀለሟ እጅግ ድምቅ ያለ ሆኖ ነገር ግን ውስጧ ላይ ምንም አይነት ነገር የላትም። ይችኛዋን ደግሞ ተመልከታት።አንድ ጊዜ ነካ አድርጎ ከእንደገና ቪዲዮውውን እያቆመ።የቅድሟ አበባ በሌላ ከለር ውስጥ ሆና ወደ ግራ በኩል ዘመም ብላ ሌላኛዋ ቅርንጫፏ ደግሞ በቀኝ በኩል ጠንዘል ብሎ ክብ ሰርቷል።ቀለሙ ደግሞ ክቦቹን ፓርት በሚገባ ቀብቶ የቀለበት ቅርፅ አስይዟቸዋል።ሁለቱም ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው የቀለበት ቅርፅ መያዛቸውና ትኩረት እንዳይደረግባቸው ደግጋጎ ከለራቸውን የተለያየ አድርገውታል። የዚችኛው ቅርንጫፍ ደማቅ ሰማያዊ ነው የተጠቀሙት።የዚችኛዋን ደግጋጎ ደብዛዛውን ሰማያዊ ነው የተጠቀሙት ይሄ በአጋጣሚ አይመስለኝም። ጥልቅ የሆነ ምስጢር እንደተቀመጠበት ያስታውቃል።ቪዲዮውን ለቀቀ ሳደርገው የፊደል ቅርፅ እየያዘች ትጠፋለች። ይቺ ፊደል ደግሞ ተመልከታትና ከመጀመሪያው መነሻ ቪዲዮ ጋር ስናመሳስላት አንዳች ዝምድና ነገር እናገኝባታለን። "ሌላው ይሄኛው ቪዲዮ ነው የገረመኝ ዓደይ ሞል። እዚህም ላይ "ዓ" ላይና "ሞ"ላይ የተጠቀሱት ፊደል ላይ የተቀረፁት የቀለምና የቅርፅ መጠን ተመሳሳይ መሆናቸው ነው።ስለዚህ በዚህኛው ፊደል መሠረት አጥሩ ላይ ቦግ ብላ ስትጠፋ የነበረው ፊደል "መ" ነች ማለት ነው። አበባዋን በሌላኛዋ ሳይድ ሆነን ስንመለከትና የስር ግንዷን ደግሞ ወደ ታች ሳብ ስናደርገው የ"ሞ"ቅርፅ ይዛ እንመለከታታለን።ሁለቱን ፊደሎች ስንገጥማቸው "መሞ"የሚሉ ይሆናቸዋል።በእርግጥ ምንም አይነት ትርጉም አይሰጡም።ግን ሁለቱን ቃላቶች አንድ ላይ ገጥመን ካነበብናቸውና የመጨረሻውን ፊደል በራሳችን ብንገጥመው የሚሰጠን ትርጉም ረብ የለሽ ነው። ማለት መቼም "ይሄን ሁሉ ምስጢራዊ ፅሁፍ ሲያስቀምጡ "መሞት"የሚል ሀሳብ ያለው ፍቺ ቀርፀው አይሆንም።ምክንያቱም ይህ የእነሱን ድብቅነት ስለማያመለክት እናም አንዷን ፊደል ወስደን መፅሐፍህ ላይ ብንመረምር የተሻለ ነው የሚሆነው።በመቀጠልም ሌላም ፍንጭ ልናገኝ እንችላለን"አለ ተሕሚድ። ሸዋንግዛው በአድናቆት እየተመለከተው "እንዴት ግን እንደዚህ በጥልቀት ልትመረምር ቻልህ? የሚገርም ከፖሊስም በላይ ነው የመረዳትና የመመርመር ብቃትህ?"አለ ሸዋንግዛው በአግራሞት ተሕሚድን እየተመለከተው። "ያው ተፅእኖ በለው የልጅነት ጊዜዬን ብዙ ጊዜ በሌባና ፖሊስ ጨዋታ ነው የምናሳልፈው።ከዛ በኋላ ደግሞ አደግ ስል የወንጀል መፅሐፎችን አለም ላይ አሉ የተባሉ ዝነኛ የወንጀል መርማሪዎችን መፅሐፍ አብዝቼ አነብ ነበር። እና እንዲሁም ፊልሞቻቸውን አያለሁ።ለምሳሌ በፊልሙ የአሌክስንና የስኮፊልድን ጨዋታ ሳታየው የቀረህ አይመስለኝም።እኖዲሁም #The fact of abody #The devil on the white city #Empire of pain #People who Eat Darkness የሚሉት መፅሐፎች በደንብ አድርገው ተፅዕኖ ፈጥረውብኛል። የሚገርመው ወንጀለኞቹም አሳዳጆቹም መርማሪዎችም የሚፅፉት እንዴት ተቀናቃኞቻቸው መፅሐፎቻቸው የተረዳሁት የጭንቅላት ውስብስብ ምስጢር ጉዟቸውን ነው።ከዚህ አንፃር ነው። ብቻ ረጅም ታሪክ አለው።ስለ እኔ ታሪክ መናገር የምቀጥል ከሆነ ምርመራችንን እናቆማለን።" በማለት ፈገግ ብሎ በአጭሩ ቋጭቶት ወደ ቪዲዮው መለሰው። ሸዋንግዛው በጥሦና ከሰሜው በኋላ በአድናቆትና በጥርጣሬ ይመለከተው ጀመር። ጥርጣሬ ትልቅ መድኃኒትም ትልቅ በሽታም ነው። በፖሊስነት ሞያ ሁሉንም መጠርጠር ሁሉንም ከማመን በእጥፍ የበለጠ ነው። የሚል የስራ ፍልስምና አላቸው። ፖሊሶች ጋር ተራ ቃላት የሚባል ነገር የለም። ሁሉም ትርጉም አላቸው።ዝም ብሎ ነው ያወራው ሳላስበው ነው የተናገረው ምናምን የሚባል ነገር አይሰራም። ከምን የተነሳ ነው እንደዚህ ያለው ምን አስቦስ ነው?"በሚል ምንዘራ ነው የሚፈረጀው።በዚህ የተነሳ የተገባ በሚል ጥርጣሬ ያልተገባ ጥርጣሬያቸው ከብዙ ወዳጆቻቸውና የቅርብ ሰዎቻቸው ጋር ያራርቃቸዋል። ሸዋንግዛውም አጉል ጥርጣሬ ወደ ውስጡ ሲመጣበት "ለምን ታዲያ በዚህ ልክ ግልፅ ሆኖ ምርመራውን ያለምንም ፍራቻ ያካፍለኛል?" በማለት ከእንደገና ሀሳቡን ሙሉ ለእሱ ሰጥቶ ምርመራቸውን ቀጠሉ። ተሕሚድ በጥሞና ነው ቪዲዮውን እየመለሰ እየከለሰ የሚያየው። ሸዋንግዛው በውስጡ "ይሄን ነበር አነፍናፊ መርማሪ ማድረግ"እያለ መመልከቱን ቀጠለ።
ለብዙ ደቂቃ እያቆሙ እየቀጠሉ እየመለሱ እያሳለፉ ቢመለከቱም መጀመሪያ ካገኙበት መረጃ የተለዬ ሊያገኙ ባለመቻላቸው በጣም ግራ ተጋቡ። "አሁን i think መተኛት ሳይኖርብን አይቀርም ይሄን ምርመራ ጠዋት ብንቀጥለው ይሻላል!"አለ ሸዋንግዛው "ሳይሻል አይቀርም በአዲስ አእምሮ ግን የተወሰነ ፈሰንጭ እንኳ እንዴት አናገኝም። ትንሽ እንቆይ እንዴ?"አለ ተሕሚድ ""ግዴለህም ተወው አአምሯችን መስራት ከሚገባው ስአት በላይ ነው የተጠቀምነው ስለዚህ እናሳርፈውና ጠዋት ከቻልን ቀደም ብለን ተነስተን ይሻላል"ብሎ ሸዋንግዛው ላፕቶፑን ዘጋው። "ወደ ባልደረባህ ስንት ስአት ላይ ነው የምትሄደው?" አለ ተሕሚድ " ጠዋት ወደ አስራሁለት ስአት ወይም አንድ ስአት አካባቢ"አለ ሸዋንግዛው ላፕቶፑን ወደ ትንሿ ባግ እያስገባ።"ነገ ወደ ስራ ትገባለህ እንዴ?"አለ ሸዋንግዛው "አዎ የሆነች ስራ አለችብኝ ገባ ብዬ እወጣለሁ!"አለ ተሕሚድ "እ እ በቃ እሺ"አለ ሸዋንግዛው የሆነ ነገር ሊል ፈልጎ ነገር ግን ከእንደገና ሀሳቡን ወደ ራሱ እያቆዬ "የምታዘኝ ነገር ካለ ወይም እንዳደርግልህ የምትፈልገው ነገር ካለ ንገረኝ!" "ያው እሱማ ነበር ነገ ልጆቹን ማን ወደ ትምህርት ቤት ወስዶ ያመጣቸዋል።በዛ ላይ ልዩ የሆነ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል።ልቤ የሆነ ነገር ይለኛል። ለመጀመሪያ ጊዜ ነው እንደዚህ ፍርሃት ፍርሃት ያለኝ"አለ ሸዋንግዛው። "እሺ ኢንስፔክተር ችግር የለውም በቃ እኔም ሆንኩ ሲሐም ነገ ወደየትም አንሄድም ልጆቹን አስገብተን እነሱን እንጠብቃለን።አንተ ስራህን ያለምንም ስጋት መስራት ትችላለህ!"በማለት ተሕሚድ ምንም ማሰብ እንደሌለበት ለኢንስፔክተር ሸዋንግዛው አስረግጦ ነገረው። ሸዋንግዛው በተሕሚድ ትሕትናና ታዛዥነት ቅንነት በመደሰት የጠዋቱን መርሀግብር አንድ በአንድ ማውጣት ጀመረ። ወደ ዋና ሳጅን አክሊሉ የሺህዋስ አስከሬን ወደሚገኝበት ሆስፒታል ከሄደ በኋላ አንዳንድ መረጃዎችን መሰብሰብ እንዳለበትና ምርመራውንም እስከዛሬ ከሚጠቀመው ሀይል በላይ ተጠቅሞ መመርመር እንዳለበት አንድ በአንድ በሀሳቡ ጨርሶ ተሕሚድን "በል ደህና እደር"በማለት ወደ መኝታ ክፍሉ ሄደ። ተሕሚድም ለሸዋንግዛው ተመሳሳዩን የደህና እደር መልስ መልሶ ሚስቱ ወደ ተኛችበት ክፍል አመራ።ሲሐም አይኖቿን ቁልጭ ቁልጭ እያደረገች ጠበቀችው። ተሕሚድ የሲሐምን አለመተኛት ሲያይ ድንግጥ ብሎ.....

@amba88

2 years ago

"እነሆ ዛሬዬን እንዴት እንዳገኘኋት! የልደት ቀኔን"
አምባዬ ጌታነህ
ልጅነቴንና የትምህርት ጊዜዬን ባሰብኩ ቁጥር ሁሌም በብዙ ክስተቶች ወደ አእምሮዬ የሚመጣ አንድ መምህር አለ። ደረሰ ጫኔ ይባላል። ረቡኒ ደረሰ ጫኔ ከብዙ ልጅነት ወለድ በሽታ በጊዜ ያዳነኝ ባለውለታዬ ነው። አንድ ጊዜ ሁላችንንም ምን መሆን እንደምንፈልግ ጠየቀን። ሁላችንም እየተነሳን ያሻችንን ተናገርን።በዛን ወቅት ቀጥታ የሆነ የህልም አለም የለም። የመጀመሪያው የአንድ የገጠር ተማሪ ህልም ከተማ መኖር ነው። ያው ዘይት ያለው ወጥ በሽቶ ያጌጠ ቤት ውስጥ መኖር ለነዚህ ፍቱን መድኅኒቱ አስተማሪ መሆን ነውና የአብዛኞቻችን ህልም አስተማሪነት ነው። በተለይ አስተማሪ ሆኖ የተወለድንበት አካባቢ ካለ ትምህርት ቤት ማስተማር በጣም ሀሴት ይሰጣል።" ፐ የእንትና ልይኮ አስተማሪ ሆኗል ዋ እንዲህ ነውይ አራት መቶ ብር ነው አሉ ደሞዙ"እየተባለ በአካባቢው ዘንድ በአድናቆት ይወራለታል። በተለይ የአካባቢው መፅሔት የሚባለው የእድር ና የሰንበቴ ማህበር ላይ የቶክሾው ርዕስ ይሆናል።" ከዚህ ሁኔታና ፍላጎት አንፃር የሁላችንም ህልም በወቅቱ አስተማሪነት ሆነ። አስተማሪያችን ደረሰ ጫኔም ዘወትር የማትጠፋውን ፈገግታ እየለገሰን "እሺ እድሚያችሁ ስንት ነው?" በማለት ሁለተኛ ጥያቄ አስከተለ። ሁላችንም እድሜያችንን ተናገርን ቀጣዩ ጥያቄ ነበር እኔን ያፈዘዘኝ "የተወለዳችሁበት ቀንንስ ታውቃላችሁ?" የደረሰ ጫኔ የመጨረሻ ሳልሳዊ ጥያቄ ይሄኔ እኔ መቁለጭለጭ ጀመርኩ ሁሉም በሚባል ደረጃ የተወለዱበትን ወር ከነ ቀኑ ከቤተሰብ እንደተነገራቸው ተናገሩ። እኔ ግን ቄሱም ዝም መፅሐፉም ዝም ሆነ። የተወለድኩበትን ቀን አለማወቄ አበሳጨኝ።
እሳት ለብሼ እሳት ጎርሼ ቤት እንደገባሁ እናቴን በጥያቄ አፋጠጥኳት እኔ በንዴት የተቃጠልኩበትን ጥያቄ እናቴ ፈገግታዋን ቸለሰችበትና "አይይ አምባዬ ነው ይሄ ነው ያናደደህ የኔ ልጅ?" ብላ ቀጭን ሳቅ ሳቀችና "የተወለድከውማ የአያሌው ጌጤ ልጅ ደመቁ አያሌው በተዳረች ሰሞን ነው"ብላ ነገሩን ላትከፍት ዘጋታው ቁጭ አለች።ግራ በተጋባ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ "በቃ ይሄው ነው እታተይ?" አልኋት! "አዎ ልጄ"ብላ ወደ ጓዳዋ ትታኝ ገባች። "እንዴ ደመቁ አያሌው መቼ እንዳገባች ቀኑና ወሩን መቼ እንደሆነ አታውቂም?" አልኩ ከስር ከስሯ እየተከተልኩ! "አይ እንግዲህ ቀሪውን አስልተህ ድረስበት ተማሪም አይደለህ ከፈለግክ ደግሞ ሙሽሪት ፍቅርን የአበይ መንበሩንና የሲሳይ ወርቁን እናት ጠይቅ በተለይ ሙሽሪት ፍቅር ታስታውስ ይሆናል።"ብላኝ ነገሩን እስከወዲያኛው ተስፋ አሳጣችው።
" የልደት ቀንን የማግኘት ዘመቻ" በሚል ርዕስ የሰጠሁትን የራሴን ተልዕኮ በልዩ ጥበብ ለማጠናቀቅ ዋናዋና የተባሉ ሁነቶችን ለመፈፀም አጀንዳው ላይ በየተራ ፃፍኩ።
ተልዕኮ1፦ሙሽሪት ፍቅርን ማናገር ተልዕኮ2:፦እንዲሁም የሌሎቹንም የእድሜ እኩያዎቼን ልጆች እናቶች መጠየቅ ተልዕኮ3፦ ደመቁ አያሌው የተወለደችበትን ቀን ማግኘት ለዚህም የሚጠቅሙ given dataዎችን ከአካባቢያችን ትልልቅ ሰዎች መሰብሰብ። እነዚህን ተልዕኮኾች በሁለት ቀን ለማጠናቀቅ ቀነ ገደብ አስቀምጨ ተነሳሁ።
የባልንጀሮቼን እናት ስጠይቃቸው "ውይ እኛማ ምኑን እናውቀዋለን እናትህ ናት እንጅ ብልህ እኛማ ደንቆሮ አይደለን"በማለት የኔን እናትየደመቁ አያሌውን ሰርግ ትውስታ እንደ ትልቅ ጀግንነት በመውሰድ ለእኔ ሌላ ፍንጭ ከመስጠት ይልቅ ለእናቴ አድናቆት መስጠትን ምርጫቸው አደረጉ። ወደ መጀመሪያዋ ተልዕኮ ሙሽሪት ፍቅር ጋር በመሄድ ጉዳዩን በሰከነ መንገድ ጠየኳት። ሙሽሪት ፍቅር ረጋ ብላ ትንሽ አሰብ አደረገችና "እኔ ቀኑን ይሄ ነው ብዬ አላስታውስም ግን ወቅቱ በልግ ነበር። እናንተ የተወለዳችሁ ሰሞን ዝናብ ጥሎ ገበሬ በሬውን ጠምዶ መሬቱን የገመሰበት ወቅት ነበር"ብላ ሌላ ምንም ነገር እንደማታውቅና እንደማታስታውስ ነግራኝ ተስፋዬን አጨለመችው ግን ቢያንስ አንድ ነገር አግኝቻለሁ ይህም የተወለድኩበት ወር የበልግ ወር ላይ እንደሆነ ይህም ፍጥጫዬ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ያሉት ወራቶች እንደሆኑ አውቄ ሌሎቹን ወራቶች አጥፍቼ ትኩረቴን መጋቢት ሚያዚያ ግንቦት ላይ አደረኩና ለነገረችኝ መረጃ ምስጋናዬን አበርክቼ ወጣሁ። በርግጥ የልደት ቀኔ ብቻም ሳይሆን አመቴም ግራ የሚያጋባ ነው ብዙ የጠራ ነገር የለውም። ወደ ተልዕኮ ሶስት በመቀጠል የመንደራችንን አንቱ የተባሉ ዋርካችን አቶ አያሌው ጌጤ ጋር በመሄድ ጉዳዬን ነገርኋቸው። ነጭ የፈረስ ጭራቸውን ወዲያና ወዲህ እያደረጉ ከበርካታ ልጆቹ አንዷ የሆነችውን ደመቁ አያሌው የተዳረችበትን ወቅት እና አመት የኋሊት ለማስታወስ ለአንድ ደቂቃ ያህል አሰብ አደረጉና "እንግዲህ ሚያዚያ ወር ላይ ነው ያ ማለት ታጋይ በገባች በአራት አመቷ መሬት ከተካሄደ ደግሞ ሶስት አመት በኋላ ነው!" አሉ። ትንፍስ አልኩ ከምፈልጋቸው መልሶች አብዝሀኛውን አቶ አያሌው ጌጤ መልሰውልኛል። ታጋይ ማለት ህወሃት ናት። እሷ ደግሞ በ1982 ነው የገባችው በ1983 ደግሞ መሬት ተካሄደ(ተከፋፈለ)። በዚህም መሠረት የተወለድኩት በ1986 ዓም መሆኑ ተረጋግጧል። አሁን የሚቀረው ሚያዝያ ስንት ቀን የሚለው ነው? ይሄን ጥያቄ ብቻ ይዤ በሀሴት የአጎት አያሌው ጌጤን ጉልበት ስሜ ወደ ቤት ተመለስኩ። "አምባዬነው ከሄድክ በኋላ ትዝ ብሎኝ ነው።ከጠቀመህ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው"አለች እናቴ " ንገሪኝ እታተይዬ"አልኩና አንጀቷን አላወስኩት። "እንዴት እንደረሳሁት የተወለድከው የሚያዚያ የመድኀኒዓለም እለት እንደውም ቀኑ ሐሙስ ነው። የነ ሲሳይ ወዳጁ ማህበር እየተደገሰ እያለ አንተ ተወለድክ!" ዘልዬ አቅፌ እያገላበጥኩ ሳምኳት። አንቺኮ ከልብ እናት ነሽ!" አልሁና አሞካሸኋት። "አይ ይሄን ድለላህን ተወው ብቻ ሀተቀመህ በቂ ነው ብላኝ ወደ ደጅ ወጣች። እነሆ ያቺ ወር ያቺ ቀን ያቺ ዕለት ዛሬ ከ28 አመት በኋላ ተደገመች። 1986/08/27 ሐሙስ ይችን ምድር የተቀላቀልኩባት ቀን።

@Adwa1888

We recommend to visit

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ ነው። ሰውነትን አስቀድመው ግለሰብን፣ ህዝብና ሀገርን የሚያከብሩ፣ ሚዛናዊ አመለካከትን ያዳበሩ፣ ከጥላቻ አመለካከት የነፁ ኢትዮጵያውያን ቤት ነው።

ያግኙን +251913134524

Last updated 1 month ago

ስለ መድፈኞቹ የሚወጡ መረጃዎች ለማግኘት የትም መሄድ አያስፈልግም

- የዝዉዉር ዜና
- የአሰልጣኞች አስተያየት
- የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
- ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት

ለማስታወቂያ ስራ  --> @MKHI7

Last updated 1 month ago

BoA Social media links
@ https://www.facebook.com/BoAeth
@ https://www.instagram.com/abyssinia_bank
@ https://www.linkedin.com/company/bankofabyssinia/
@ https://twitter.com/abyssiniabank
@BOA_ATM_bot

Last updated 2 weeks ago