Welcome To Amharic films
Best Place To find Amharic Movies
አዳዲስ እና የድሮ አማርኛ ፊልሞችን እና አማርኛ ተከታታይ ድራማዎችን ለማግኝት ቻናላችንን Join ይበሉ ።
Share:- @Amharic_Films
ለማስታወቂያ - @Abusheymc & @Alpha6249
Buy ads: https://telega.io/c/Amharic_films
Last updated 1 year, 5 months ago
ስለ መድፈኞቹ የሚወጡ መረጃዎች ለማግኘት የትም መሄድ አያስፈልግም
- የዝዉዉር ዜና
- የአሰልጣኞች አስተያየት
- የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
- ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት
ለማስታወቂያ ስራ --> @MKHI7
Last updated 4 days, 15 hours ago
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።
#ኢትዮጵያ
ያግኙን +251913134524
Last updated 1 week, 5 days ago
ደግሞም እንደ መውሊድ ካሉ ወደ አላህ መቃረቢያ ተደርገው ከሚታሰቡ በሺርክ ከተቀላቀሉ አምልኮታዊ ቢድዐዎች ይልቅ እንዲሁ ባህል ተደርጎ የተያዘው “ብሄራዊ ቀን” የሚባለው የጥፋት ክብደቱ በንፅፅር ቀለል ያለ ነው። አምልኮታዊ ስላልሆነም ነው አንዳንድ ዓሊሞች ሲፈቅዱት የሚታዩት። የሚፈቅዱትን ብናይ በግልፅ ዒባዳ እንዳልሆነ ይገልፃሉ። መውሊድስ? ከመሆኑም ጋር ብሄራዊ ቀኑም ተቀባይነት የሌለው ድግስ ነው። በውስጡም ሙንከራት አሉበትና በርካታ ዑለማኦች አውግዘውታል። አንዱ አፍቃሪ-ሺዐ ግን “አንድም የሳኡዲ ኡለማም ሆነ ሙፍቲ ሀራም ነው ቢዲአ ነው ብሎ ትንፍሽ ብሎም አያውቅም” እያለ ደምድሞ ይናገራል። ወላሂ ይሄ የለየለት ቅጥፈት ነው። የሚገርመው ይሄ ሰው የኢራን ደጋፊ መሆኑ ነው። ኢራን በያመቱ ብሄራዊ ቀን እንደምታከብር ግን አያውቅም። ወይም እንደሚያደንቃቸው ሺዐዎች ውሸትን መንገዱ ያደረገ ነው። ይሄው ታላላቅ ዑለማዎች ይህንን ብሄራዊ ቀን እየተባለ የሚከበረውን በዓል አውግዘዋል። ምሳሌ ልጥቀስ፡-
1. የቀድሞው የሰዑዲያ ጠቅላይ ሙፍቲ ሸይኽ ሙሐመድ ብኑ ኢብራሂም። [ፈታወ ሸይኽ ሙሐመድ ብኒ ኢብራሂም፡ 3/122]
2. ከሳቸው በኋላ የተተኩት የሰዑዲያ ጠቅላይ ሙፍቲ ሸይኽ ኢብኑ ባዝ”ቢድዐ ነው” “በአላህ ጠላቶች መመሳሰል ነው” ብለዋል። [መጅሙዑ ፈታዋ ሸይኽ ኢብኒ ባዝ፡ 5/189] [ዱሩሱ ሸይኽ ዐብዲል ዐዚዝ ብኒ ባዝ፡ 10/11፣ 17/31]
3. ሸይኽ ዐብዱረዛቅ ዐፊፊ። በሳዑዲ ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ በኩል ከኢብኑ ባዝ ጋር የሰጡትን ፈትዋ መመልከት ይቻላል። [ፈታዋ ለጅነቲ ዳኢማህ፡ ፈትዋ ቁ. 9403]
4. ሸይኽ ኢብኑ ሷሊሕ አልዑሠይሚን። [አሸርሑል ሙምቲዕ፡ 5/113፣ 5/146] [መጅሙዑ ፈታዋ ወረሳኢሊ ኢብኒ ዑሠይሚን፡ 16/119]
5. ሸይኽ ፈውዛን አልፈውዛን እንዲሁ በኹጥባቸው ላይ ባደባባይ ነው ያወገዙት።
6. ሸይኽ ዐብደላህ አልበሳም። [ተውዲሑል አሕካም፡ 2/411]
7. ሸይኽ ሷሊሕ አሉሐይዳን እንዲሁ ይህንን ቀን በዓል አድርጎ መያዝ ባጢል ነው ይላሉ። ዩቲዩብ ላይ ታገኙታላችሁ። ከነዚህም ውጭ የነ በራክ፣ ጉነይማን፣ ረዪስ፣ ወዘተ. ብዙ ፈተዋዎችን መዘርዘር ይቻላል። ይህ ሁሉ ከመሆኑም ጋር ግን “አንድም የሳኡዲ ኡለማም ሆነ ሙፍቲ ሀራም ነው ቢዲአ ነው ብሎ ትንፍሽ ብሎም አያውቅም” የሚል ቅጥፈት እያየን ነው። ሱብሓነላህ!
በነገራችን ላይ በቀርዷዊ የተመሰረተው ራሱን “አለም አቀፍ ዑለማኦች ማህበር” እያለ የሚጠራው ማህበር የአሁኑ ሊቀመንበር ዐሊይ ሙሕዩዲን አልቁረህዳጊ ይህንን በዓል እየፈቀደ የሰጠው ፈትዋ በማህበሩ ዌብሳይት ላይ ይገኛል። በዚሁ ማህበር የቀርዷዊ ምክትል የነበረው ዐብዱላህ ብኑ በየህ እንዲሁ ብሄራዊ ቀን ማክበር ይፈቅዳል። እስኪ በነዚህ ሙፍቲዎች ላይ ያሰማችሁትን ተቃውሞ አሳዩን። አስመሳይ ስብስብ! ከፊሎቹ "ፈትዋ አላልንም። የተቃወሙበትን አሳዩን" እያሉ ነው። ካፈርኩ አይመልሰኝ ማለት ይሄ ነው። እስኪ በኢራን፣ በኳታር፣ በሌሎችም ሙስሊም ሃገራት ውስጥ ብሄራዊ ቀን ሲከበር የተቃወማችሁበትን አሳዩን። ቱርክ ውስጥ የኦቶማን ተርክ “ኺላፋ” ወድቆ በምትኩ የከማል አታቱርኳ ቱርክ የተመሰረተችበት ቀን በተለያዩ ድግሶች በያመቱ ይከበራል። በዚህ ሁሉ ላይ ግን ትንፍሽ የሚል የለም። ዲንን ሽፋን የሚያደርግ የእባብ ስብስብ!! ይሄ ንፅፅሬ የሚያበሽቃችሁ እንዳላችሁ አውቃለሁ። “ስለ ሳዑዲ ሲነሳ ስለ ቱርክ ለምን ታነሳለህ?” ይላሉ። አላማችሁ ዲንን ሽፋን ማድረግ እንጂ ለዲን መቆርቆር እንዳልሆነ፣ ሰዑዲ ላይ ብቻ በተለየ እንድትጮሁ የሚያደርጋችሁ ዑለማኦቿ ላይ ያረገዛችሁት ጥላቻ እንደሆነ፣ በተመሳሳይ ሚዛን የተለያየ ስፍር የምትሰፍሩ አስመሳዮች እንደሆናችሁ ለማጋለጥ ነው ይህን የማደርገው። ሐቀኛ ሰው በተመሳሳይ ጉዳይ አንዱን እያለፈ ሌላውን አያወግዝም። ደግሞስ እንዴት መፃፍ እንዳለብኝ እናንተ ናችሁ የምትነግሩኝ?!
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor
Telegram
Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)
كناشة ابن منور
የሳዑዲ ብሄራዊ ቀን
~
ሃገራት በያመቱ ብሄራዊ ቀን እያሉ ማክበራቸው ከሌሎች ህዝቦች የተወረሰ የጃሂሊያ ሱና ነው። እንደ ዒድ ከተያዘ ደግሞ ቢድዐ ነው። አከባበሩ ላይ ጭፈራና አጉል ቅልቅል ሲኖር ደግሞ ይበልጥ የከፋ ሙንከር ይሆናል። ይህንን አጉል ልማድ ከሚከተሉ ሃገራት አንዷ ሳዑዲ ናት። ሰሞኑንም "የውመል ወጠኒ" ብላ እያከበረች ነው። ይሄ ጉዳይ በሳዑዲ ሲፈፀም የተለየ ብይን አይዝም።
ይህ እንዳለ ሆኖ በያመቱ በዚህ ሰሞን በአህለ ሱና ደዕዋ ላይ ቂም ያረገዙ የስሜት ተከታዮች ሲንጫጩ ማየት የተለመደ ነው። አስተውሏቸው! ሁሌም ቢሆን ጩኸታቸው ይህንን መጤ በዓል ማውገዝ ላይ የተገደበ አይደለም። ይልቁንም አጋጣሚዎችን በመጠቀም የተካኑት እነዚህ አካላት ክስተቱን የሱና ዑለማዎችንና ዱዓቶችን በነገር ለመውጋት ሲጠቀሙት ነው የሚታዩት። መቼስ ስለ ዑለማእ ክብር ሲያወሩ ከራሳቸው ሰዎች ለመከላከል እንጂ የእውነት እንደማይሰሩበት ባህሪያቸውን ጠንቅቆ የተረዳ ሰው በቀላል ይረዳዋል። ውንጀላቸው ውስጥ ድንቁ -ርናም፣ ስሜታዊነትም፣ ፍርደ-ገምድልነትም ህብረት ሰርተው ይታያሉ። ለምሳሌ ያክል፡ {እንደ መድከሊዎች አስተሳሰብ ከሆነ የሳውዲ ህግ እሚፈቅደው ነገር ሁሉ ሃላል ሲሆን የሳውዲ ህግ እሚከለክለው ሁሉ ሀራም ነው። መድከሊዎች ቁረንና ሀዲስን እሚረዱት በሰለፎች አስተሳሰብ ሳይሆን ንጉሶች ባስቀመጡት ህግ መሰረት ነው።} ብሎ የፃፈ አይቻለሁ። የሌሎቹም ስሜትና ክስ ተመሳሳይ ነውና አንድ ላይ ምላሽ እሰጣለሁ።
በመጀመሪያ ሸይኽ ረቢዕን በጭፍን የምንከተል አይደለንም። ቢሆንም እነዚህን ልክፍተኞች ለማሳመን አንጨነቅም። የቢድዐ አንጃዎችን መዋጋት "መዳ .ኺላ" እስካስባለ ድረስ ሰውም ጂኑም ይወቅ መዳ.ኺላዎች ነን። እንጥፍጣፊ ሚዛናዊነት ያለው አካል እንዲያስተውል ያክል ግን በምንም መልኩ ለሸይኽ ረቢዕ ከሌሎች ዑለማዎች የተለየ እይታ እንደሌለን እንገልፃለን። ለሳቸው ድንበር ያለፈ እይታ ያለው፣ ንግግራቸውን ከሌሎች ዑለማዎች ንግግር በላይ መመዘኛ የሚያደርግ አልፎም እሳቸውን መሰረት ያደረገ ጥላቻና ወዳጅነት የሚመሰርት ካለ ወደደም ጠላም የስሜት ተከታይ ሆኗል። ይህ ነው እምነታችን።
ሳዑዲን በተመለከተ ከየትኛውም ሃገር በተሻለ ኢስላማዊ ነፀብራቅ እንዳለ ወዳጅ ቀርቶ ጠ^ላትም አይዘነጋውም። ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲዎቿ ከመላው ዓለም ተማሪዎችን ተቀብለው ተውሒድን ያስተምራሉ። በመንግስት ደረጃ የተቋቋሙ ኢስላማዊ ተቋማት ሰፋፊ ዲናዊ ስራዎችን ይሰራሉ። የፈለገ ክፍተቶች ቢዘረዘሩ ከየትኛውም ስርኣት እንደሚሻሉ ስሜቱ ሸብቦ ላልያዘው ሁሉ ግልፅ ነው። ይህንን ደግሞ እነዚህ ሳዑዲን በማብጠልጠል ላይ የተጠመዱ አካላትም የሚመሰክሩት ሐቅ ነው። “ሳዑዲን ከምትተቹበት የበለጠ ብዙ ጥፋት ቱርክ ውስጥ አለ። ከሳዑዲ ጋር ምንድን ነው በተለየ የሚያፋጥጣችሁ?” ሲባሉ “ቱርክ ሴኩላር ስርአት ነው ያላት፣ ከሳዑዲ ጋር ማወዳደሩ ምን አስፈለገ?” ይላሉ። እና የማይወዳደሩ ከሆነ የባሰውን ጥላችሁ በአንፃራዊነት የሚሻለው ላይ ይህን ያክል በጥላቻ የታወራችሁት ለምንድን ነው? ማሰብ የተሳናቸው ጉዶች! ብዙዎቹ አንድ ሰው ቱርክን ወይም ኤርዶጋንን ቢያደንቅ ምንም አይሉም። ሰዑዲን የሚያደንቅ ሲመለከቱ ግን ነብር ሆነው ይነሳሉ። ለምን እንዲህ ሙዳቸው እንደሚቀያየር ራሳቸውን እንኳ አይጠይቁም። የሚደንቀው የተለያዩ መስመሮችን የሚከተሉ ሆነው እንኳ ጥላቻ እያግባባቸው በጋራ የሚጓዙ መሆናቸው ነው። አንዱ ሱፊ ሆኖ፣ ሌላው ኤርዶጋንን የሚያንቆለጳጵስ ኢኽዋኒ ሆኖ፣ ሌላኛው ኤርዶጋንን የሚያወግዝ የአይ.ሲስ ደጋፊ ኻሪጂ ሆኖ፣ ሌላው የሌሎችን ጩኸት የሚያስተጋባ በቀቀን ሆኖ፣ ... ሳይነቃ እንደነቃ የሚያስበው ሁላ እዚሁ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ አንዱ ሌላውን እያዳነቀ ሲቀባበሉ ይታያሉ። ምክንያታቸው የጋራ ጠላት መያዛቸው ብቻ ነው። የሳዑዲ መንግስት እና ከዚህ መንግስት የሚከላከሉ ዑለማኦችን መጥላት። በቃ!
ሳዑዲ ውስጥ ከሸሪዐ ጋር የሚፃረሩ ነገሮች መኖራቸው ማንም የሚክደው አይደለም። ብሄራዊ ቀን ከመያዝ ባለፈ ሌሎችም ችግሮች በተጨባጭ አሉ። ስርኣቱን ፍፁም የሚያደርግ አንድም የለም፣ እደግመዋለሁ አንድም!! ግና የስሜት ተከታዮችን ተቅዋም፣ ህሊናም፣ ሞራልም ስለማይገድባቸው ሰዎች ላይ በማያምኑት ያሻቸውን ከመለጠፍ አይመለሱም። “የሳዑዲ መንግስት የሚሰራው ሁሉ ለነሱ ሱና ነው” እያሉ ይወነጅላሉ። ሳዑዲ ላይ ዘፈንና ጭፈራ ካለ ጥፋቱን መቃወም አይደለም የሚያሳስባቸው። የሚያስጨንቃቸው በዚያ አቆራርጠው የሱና ዑለማኦችን ለመንካት አጋጣሚውን መጠቀም ነው። እንጂ በዲን ስም ዘፈን በመፍቀድ የሚታውቁት እንደ ቀርዷዊ ያሉ የኢኽዋን ቁንጮዎች ላይኮ ትንፍሽ አይሉም። ስለ መውሊድ ፀጥ ብለው ያሳልፉና የሳዑዲ ብሄራዊ በዓል ሲከበር አንገታቸውን አስግገው ይወጣሉ። በዓሉን መቃወም አይደለም አላማቸው። በሆኑ አካላት ላይ ያረገዙትን ቂም ማራገፍ ነው ትኩረታቸው። ዲናዊ ርእሰ ጉዳዮችን ለቡድናዊ ትርፍ የሚጠቀሙ የዲን ነጋዴዎች ናቸው። እንጂ ብሄራዊ በዓል ማክበርኮ ሳዑዲ ብቻ አይደለም ያለው። በብዙ ሙስሊም ሃገራት አለ። ከብዙ ሃገራት መሃል ግን ተቃውሞ የሚያሰሙት በአንድ ሳዑዲ ላይ መሆኑ ስለነሱ የሚሰጠው መልእክት አለ።
ከላይ የጠቀስኩት ፀሐፊ “እንደ መድከሊዎች አስተሳሰብ ከሆነ የሳውዲ ህግ እሚፈቅደው ነገር ሁሉ ሃላል ሲሆን የሳውዲ ህግ እሚከለክለው ሁሉ ሀራም ነው” ማለቱ የብዙ የስሜት ተከታዮች የጋራ ውንጀላ ነው። ከዐርሹ በላይ ባለው ጌታዬ ስም እምላለሁ! ከየትኛውም አንጃ ቢሆኑ በዚህ ውንጀላ ላይ የሚረባረቡ ሁላቸውም ስሜት የሚያሾራቸው ቀጣ.ፊዎች ናቸው። “የሳውዲ ህግ የሚፈቅደው ሁሉ ሃላል፣ የሳውዲ ህግ የሚከለክለው ሁሉ ሀራም” የሚል አንድ ዓሊም፣ አንድ ጧሊበል ዒልም የለም። አንድ!! እንዲያውም በዚህ መልኩ የሚያምን አካል ሙስሊም አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሰዑዲ መንግስት ድክመት እንዳለበት እየጠቀሱ ነገር ግን ከሁሉም የተሻለ እንደሆነ የሚገልፁ ብዙ የዓሊሞችን ንግግር ማግኘት ይቻላል። በግልፅ ድክመቶች እንዳሉ እየተናገሩ እንዴት ነው መንግስቱን ፍፁም ነው የሚሉት?!
የሳዑዲ አመታዊ በዓል በመጣ ቁጥር የሚያራግቡ ሰዎች ስንት ሺርክ የሚፈፀምበት የመውሊድ ቢድዐ ላይ ግን ይህን ያክል ወኔ አያሳዩም። ጭራሽ “መውሊድ ላይ ስትጮሁ የነበራችሁ ምነው እዚህ ላይ ዝም አላችሁ?” ይላሉ። ሲጠይቁ እንደሚጥጠየቁ አይገባቸውም። ምነው እናንተ መውሊድ ላይ ፀጥ አላችሁ? መጅሊሱ መውሊድ ሲያስተባብር የት ነበራችሁ? እንዲያውም ከፊሎቻችሁ የመውሊድ ደጋፊዎች ናችሁ። ታዋቂ የሃገራችን “ኡስታዞች” ለዘመን መለወጫ የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ ሲያወጡ የት ነበራችሁ? ከሳዑዲ ውጭ ሌሎች የሙስሊም ሃገራት ብሄራዊ በዓል ሲያከብሩ የት ነበራችሁ? ከኢኽዋን ታዋቂ ሰዎች ውስጥ ብሄራዊ በዓል ማክበር ይቻላል እያሉ ፈትዋ ሲሰጡ ምን አላችሁ? የኢ^ኽ^ዋን አልሙስሚንሊሚን ቡድን የተመሰረተበትን ጊዜ በያመቱ የሚዘክሩ የኢ^ኽ^ዋን ሰዎች አሉኮ። ይሄ ሁሉ አካሄድ ላይ እነዚህ የዲን ነጋዴዎች ትንፍሽ አይሉም። በቃ ሲደግፉም ሲቃወሙም መሰረት የሚያደርጉት ስሜታቸውን ብቻ ነው።
ጥቂት ምክሮች ለሙስሊም ተማሪዎች
~
ትምህርት እየተጀመረ ነው። ፈተና ሲደርስ መደናበር ወይም የአመቱ መጨረሻ ላይ ውጤትን ጭንቅ ውስጥ ሆኖ መጠበቅ ምንም ፋይዳ የለውም። ይልቁንም በየትኛውም ደረጃ ላይ ያሉ ተማሪዎች ከቀን አንድ ጀምረው በቁም ነገር መዘጋጀት ነው የሚያዋጣው። ከልቡ የተዘጋጀ ሰው በአላህ ፈቃድ የልፋቱን አያጣም። ጥሮ ግሮ ውጤት ባይመጣ እንኳ ሰበብ ያደረሰ ሰው የሚጠበቅበትን ተወጥቷል።
ይህን እንደ መግቢያ ካልኩኝ ለተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም የተሻለ ስብእና እንዲኖራቸው ያግዛሉ ያልኳቸውን የተወሰኑ ነጥቦት እንደሚከተለው አስፍሬያለሁና በማሰራጨት ብታግዙኝ ደስ ይለኛል።
① መምህርህን አክብር። አስተማሪህ ለደሞዝ ቢሰራም ላንተ ውለታ እየዋለ ነው። ኋላ ከሚፀፅትህ ዛሬ ለአስተማሪህ ትሁት ሁን። እድሜውንም አክብር። የሚያስተምርህን መናቅ የሚያጎርስህን መንከስ ነው። እንዲያዝንብህ፣ "ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ" እንዲል አታድርገው። ውለታ ይግባህ። የወጣትነት ስሜት ድፍን ቅል አያድርግህ።
"አስተማሪን መናቅ እውቀትን መናቅ ነው።"
"ለእውቀት ያለህ ክብር መጠኑ ለአስተማሪህ ባለህ ክብር ልክ ነው።"
② ተባባሪ ሁን። እንዳቅምህ የምታግዛቸው በርካታ ደካማ ተማሪዎች በዙሪያህ አሉ። የእለት ጉርስ የሚጎድላቸው፤ የደንብ ልብስ አቀበት የሆነባቸው፤ የሳሙና፣ የኮፒ፣ የታክሲ፣ የቤት ኪራይ፣ የህክምና፣ የደብተር፣ … የሚቸግራቸው፤ ብዙ ናቸው። ቢቻል አስተባብራችሁ የተቀናጀ ስራ ስሩ። ካልሆነ የራስህን ሐላፊነት ተወጣ። ደካማ ተማሪዎችን አስጠና፣ አግዝ። በዱንያ እርካታን ታገኝበታለህ። ልምድን ትቀስምበታለህ። ህይወትን ትማርበታለህ። በኣኺራ እጥፍ ድርብ ትሸለምበታለህ።
③ ከመንደሬነት ራቅ። የሰፈር፣ የቀበሌ፣ የወረዳ፣ የአካባቢ ብሽሽቅ ውስጥ አትግባ። ዘረኝነትን በየትኛውም መልኩ ተፀየፍ። ዘረኞችንም ከቻልክ ምከር። ካልሆነ አፍንጫህን ይዘህ ሽሻቸው። በዘርህ ከማንም በላይም፣ ከማንም በታችም አይደለህም። ለዘር ተኮር ቀልዶች ጥርስህን አታሳይ። ሌሎችን በዘር አትውጋ። በዘር ለሚተነኩስህም ንቀህ እለፍ እንጂ እሳት ጎርሰህ አትነሳ። የማንም ሙገሳ ከፍ እንደማያደርግህ ሁሉ የማንም ትችትም ዝቅ አያደግህም። ትእግስት ፍርሃት እንዳልሆነ ለራስህ ሹክ በለው።
"ዘረኝነት ጥንብ ሲሆን ዘረኛ ደግሞ ጥንብ አንሳ ነው።"
④ ለዲንህ ጊዜ ስጥ። አንተ ያለ ዲንህ ባዶ ነህ። ያለ ዲን ስኬትም ስኬት፣ ህይወትም ህይወት አይደለም። ስለ ዲንህ ስትማር ክፍል ውስጥ ዲንህን አታስነካም። የተሳሳተ ቲዎሪ አያነቃንቅህም። ውሎህ በፕሮግራም ይሆናል። ሕይወትህ ጣእም ይኖረዋል። ስለዚህ ቁርኣን ቅራ። አስቀራ። ኪታብ ተማር። አስተምር። ደዕዋ ሞክር። ሶላት ስገድ። ስታልፍ ስታገድም ዚክርህን አድርግ። ዲንህን በራስህ ላይ አንፀባርቅ። ዲንህ የሚወራ ሳይሆን የሚንኖር ነው።
"ዲንህ ህይወትህ ነው። ዲንህ ከሌለ አንተ እራስህ የለህም።"
⑤ በትምህርትህ ላይ ሃላፊነት ይሰማህ። ቤተሰብ የላከህ ለዋዛ አይደለም። ገንዘቡም፣ ጊዜውም፣ ድካሙም ዋጋ አይጣ። ስለዚህ በወጉ ተማር። ክፍል ውስጥ በሚገባ ተከታተል። ንቁ ተሳትፎ ይኑርህ። በሚገባ አጥና ። ስንፍናን አትቀበል። "አልችልምን" አርቅ ። ኩረጃን፣ ጥገኝነትን ተፀየፍ። በጥረትህ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ወኔ ይኑርህ። አትጠራጠር! ስትጥር ዛሬ ካለህበት የተሻለ ትሆናለህ። ባለ መጣሩ እንደ ሰነፍ የሚታይ፣ ራሱን የማያውቅ ስንት ባለ ብሩህ አእምሮ አለ?! መማርህ ካንተ አልፎ ለወገን የሚተርፍ ዋጋ ሊኖረው እንደሚችል ተረዳ።
"Education is a better safeguard of liberty than a standing army."
⑥ ራስህን ሁን። የመጣውን ፋሺን ሁሉ ካልሞከርኩ አትበል። ለራስህ ክብር ስጥ። አንተ የማስታወቂያ አሻንጉሊት አይደለህም። አርአያህን ለይ። መልካም ስብእና ያላቸውን እንጂ፣ ያለ ቁም ነገር ስማቸው የገነነ ሰዎችን ለመምሰል አትፍሰስ። አንተ ህሊና የተሰጠህ ክቡር ፍጡር እንጂ በቀደዱለት የሚፈስ የቦይ ውሃ አይደለህም።
"ራሱን ያላገኘ ሌሎችን ሲከተል ይኖራል።"
⑦ ጊዜህን በአግባቡ ተጠቀም። አንተ ዘንድ አላህ ከሰጠህ ሃብት ሁሉ ርካሹ ጊዜህ የሆነ'ለት ያለ ጥርጥር ከስረሀል። ወደ ጨለማ ጥግ ከሚያደርስ የድንግዝግዝ ባቡር ላይ ተሳፍረሀል።
እባክህን ሕይወትህ ላይ አንዳች እሴት በማይጨምሩ ነገሮች ዳግም የማታገኘው ውድ ጊዜህን አታባክን። የምልህ እየገባህ ከሆነ በሙዚቃ ከመመሰጥ፣ ፊልም ጋር ከመርመጥመጥ፣ የፈረንጅ እርግጫ ከማሳደድና መሰል አልባሌ ነገሮችን ራቅ እያልኩህ ነው። እነዚህ ነገሮች ከእለት መዝናኛነት ባለፈ ተሻጋሪ ሱስ የሚሆኑ ወጥመዶች ናቸው።
"ጊዜ ሰይፍ ነው። ካልቆረጥከው ይቆርጥሀል።"
"አንተ የጊዜያት ድምር እንጂ ሌላ አይደለህም። እያንዳንዷ የጊዜ ክፍልፋይ ስታልፍ አንተ ራስህ እያለፍክ ነው።"
⑧ ጓደኞችህን ለይ። ጓደኛህ ወይ የምትጠቅመው ወይ የሚጠቅምህ መሆን አለበት። ከዚህ ውጭ የሆነ ጓደኛ የፋንዲያ ያክል ዋጋ የለውም። እንዲያውም ያጠፋሀል። በዱንያ ቁም ነገር ላይ ከመድረስ ያሰናክልሀል። አልፎም ኣኺራህን ያጨልመዋል። ኧረ ለመሆኑ አንተ ራስህ ምን አይነት ጓደኛ ነህ? አልሚ ወይስ አጥፍቶ ጠፊ? በል ከዛሬ ጀምሮ ከጓደኛህ ጋር ቁጭ ብላችሁ የአብሮነታችሁን ሂሳብ አወራርዱ። ጓደኝነታችሁ የምትጠቀሙበት እንጂ የምትጎዱበት እንዳይሆን በስርኣት ተመካከሩ።
"ሰው በወዳጁ እምነት ላይ ነው። ስለሆነም አንዳችሁ ማንን እንደሚወዳጅ ይመልከት።"
⑨ መልካም ስነ ምግባርን ተላበስ። አትሸማቀቅ፤ ግን አትኮፈስ። ትሁት ሁን፤ ግን አትልፈስፈስ። ሰከን በል፤ ግን አትፍዘዝ። ረጋ በል፤ አትንጣጣ። ከአንደበትህ ክፉ አይውጣ።
ፊትህ ሁሌ በፈገግታ ይታጀብ። ተግባቢና ለሰዎች ቀላል ሁን። የደረስክበትን ሁሉ በሰላምታ አውደው። በትህትና አጊጥ። በቅንነት አሸብርቅ። "መጣብን" ሳይሆን "መጣልን" የምትባል ሁን። አታጣላ። አታባላ። ሃሜትና ውሸትን ክላ።
"ህዝብ ማለት ስነ ምግባር ነው። ስነ ምግባር የሌለው ህዝብ ካለ አይቆጠርም።"
(10) በትምህርት ሕይወትህ ላይ ሳለህ መዝናኛህን ቁም ነገር መጨበጫ አድርገው። ቁም ነገር አዘል መፃህፍትን አንብብ። ከቻልክ እንደ የመጀመሪያ እርዳታ /first aid/ አሰጣጥ፣ ቴኳንዶ፣ የእጅ ሙያዎች፣ የችግኝ ወይም የጓሮ አትክልት አተካከል፣ እና መሰል ጠቃሚ ስልጠናዎችን ሰልጥን፣ አሰልጥን። አካባቢህን አስተባብረህ አፅዳ።
"ራስን ብቁ ዜጋ ማድረግ ለሀገርም ለወገንም እሴት መጨመር ነው።"
(11) ከህገ ወጥ ፆታዊ ግንኙነት አጥብቀህ ራቅ። ህጋዊ በሆነ መልኩ ተረጋግተህ ለምትደርስበት ነገር በህገ ወጥ መልኩ ለማግኘት እየቸኮልክ ስብእናህን አታቆሽሽ። የሌላን ህይወትም አታበላሽ። ከአላማህም አትሰናከል። ክፉ ምሳሌም አትሁን።
"ስድ ግንኙነት ለህሊና ጠባሳ፣ ለቤተሰብ ጦስ፣ ለህዝብ መቅሰፍት ያስከትላል።"
"ከጓደኞቿ የወጣች ማሽላ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ ትሆናለች።"
**በሹብሃ የወደቁ ወንድሞች የጠየቁት ጥያቄ እና መልሶች
በ ኡስታዝ ኸድር አሕመድ አል ከሚሴ(አቡ ሓቲም)**https://t.me/UstazKedirAhmed/8218https://t.me/UstazKedirAhmed/8218
በ ጀምዕያ እና በ ዑዝር ቢል ጀህል በተሰኘው አርእስት ላይ ሹብሃ ላይ የወደቁ ተማሪዎች ኡስታዝ ኸድር ዘንድ መተው የጠየቁትን ጥያቄ እና መልስ የምንልክ ይሆናል
ታላቁ የሐዲሥ ፈርጥ ከአውሮፓዊቷ አልባኒያ ምድር
~
የዘመናቸው ምሁራን አላህ በየክፍለ ዘመኑ ዲኑን እንዲያድሱ ከሚልካቸው የለውጥ ሰዎች አንዱ እንደሆኑ ያምናሉ። በሐዲሡም በፊቅሁም መስክ የነጠረ እውቀት ያካበቱ ለመሆናቸው ሁለት ሚዛናዊ ሰዎች አይወዛገቡባቸውም፣ ሸይኽ ሙሐመድ ናሲሩዲን አል አልባኒይ ረሒመሁላህ።
ሸይኹል አልባኒይ በ1332 ዓመተ ሂጅሪያ (1914 እ.ኢ.አ) በጊዜው የአልባኒያ ዋና ከተማ በነበረችው አሽቆድራ ተወለዱ። ቤተሰባቸው ድሃ ግን ኢስላማዊ ድባብ ያከበረው ነበር። አባታቸው ሐጂ ኑሕ ከኢስታንቡል የሸሪዐ ተቋም የተመረቁ ሲሆኑ በአካባቢያቸው እውቅ የሐነፊያ መዝሀብ አስተማሪ ነበሩ።
በአልባኒይ የልጅነት ዘመን ሀገራቸው አልባኒያ አሳዛኝ በሆነ ታሪካዊ ቀውስ ውስጥ ወደቀች። በጊዜው የሀገሪቱ መሪ የነበረው አህመድ ዛጉ ሀገሪቱን መርዛማ ዝገት አለበሳት። ሀገሪቱ ፅንፈኛና ለኢስላም ጥላቻን የደቀነ ምእራብ-ወለዱን የክህ .ደት ስርዓት/ሴኩላሪዝም የሀገሪቱ ስርዓት አድርጎ አወጀ። የዚህን ጊዜ ነበር የአልባኒይ አባት ሐጂ ኑሕ ከነቤተሰባቸው ኩፍርን ሸሽተው ሂጅራ ያደረጉት፣ እትብታቸው ከተቀበረበት አልባኒያ ወደ ደማስቆ ሶሪያ። ለአላህ ሲባል የተከፈለ ታላቅ መስዋእትነት! አልባኒይ ይሄንን የአባታቸውን ውለታ እንዲህ ሲሉ ደጋግመው ያነሱት ነበር። “ጌታዬ በኔ ላይ የዋለውን ፀጋ ቆጥሬ አልዘለቀውም። ምናልባትም ከዋለልኝ ፀጋዎች ሁሉ ትልልቆቹ የአባቴ ወደ ሻም መሰደድና የሰዓት ጥገና ሙያውንም ለኔ ማስተማሩ ነው።”
ሸይኹል አልባኒይ በደማስቆ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት ቢያጠናቅቁም መደበኛው ትምህርት የአባታቸው ፍላጎት አልነበረምና ሳይገፉበት ቀርተዋል። ይሁን እንጂ በቁርኣን፣ በተጅዊድ፣ በነሕውና ሶርፍ እንዲሁም ፊቅህ በሐነፍያ መዝሀብ አጠናክረው ቀጠሉ። ቁርኣንን ካባታቸው ላይ የሐፈዙት ሸይኹልአልባኒይ የሰዓት ጥገና ሙያንም በሚገባ ቀስመዋል። በሙያውም ታዋቂ ከመሆናቸውም በላይ እየጨመረ ለመጣው ዲናዊ ትጋታቸው ጊዜ እንዲኖራቸው አስችሏቸዋል።
የሐነፊያን መዝሀብ አጥብቀው የሚከተሉትና ከሱ ውጭ ግራ ቀኝ ማየት የማይፈልጉት የአልባኒይ አባት ልጃቸውም በዚሁ ፈለግ እንዲጓዝ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በሐዲሥ ጥናት ላይ እንዳይሰማሩ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር። ይሁን እንጂ የአንድን መዘሀብ ጭፍን ተከታይነት በፅኑ ለሚያወግዙት አልባኒይ ይሄ ነገር ፈፅሞ የሚዋጥላቸው አልሆነም። ገና በሀያ ዐመታቸው አካባቢ ነበር የሐዲሥ ጥናታቸውን አፋፍመው የጀመሩት። ለጥናታቸው አጋዥ የሆኑ ኪታቦችን አቅማቸው በፈቀደ እየገዙ ከዚህ ባለፈም ደማስቆ ከሚገኘው “አዟሂሪያ” ቤተ መጻህፍት እየተዋሱ ይጠቀሙ ነበር። በጥናታቸው በገፉ ቁጥር ሱቃቸውን እየዘጉ ሰፊ ጊዜያቸውን በቤተ መጻህፍቱ ማሳለፉን ተያያዙት። ትጋታቸውን ያስተዋሉት የቤተ መጻህፍቱ ሀላፊዎችም ባሰኛቸው ጊዜ መጠቀም ይችሉ ዘንድ አንድ ልዩ ክፍልና የቤተ መጻህፍቱን ቁልፍ በማስረከብ ለሸይኹ ብቻ ሳይሆን ለሙስሊሙ ዐለም ባጠቃላይ ትልቅ ውለታን ጥለው አልፈዋል። ከዚህ በኋላ አልባኒይ ከሶላት ውጭ ከማለዳ እስከ ዒሻ በኋላ ቤተ መጻህፍቱን ቤታቸው አደረጉት።
ጥናታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ሸይኹልአልባኒይ የኋላ ኋላ በሐዲሥ ጥናት መስክ ብቻ ከመቶ በላይ ኪታቦችን ለኡማው አበርክተዋል። በዘርፉ ከተሰማሩ ሌሎች ዐሊሞች ጋር ሲታዩ ሸይኹል አልባኒይ ጫፍ የደረሱ ነበሩ ማለት ይቻላል። እንዲያውም ዐሊሞች “የነኢብኑ ሐጀር አልዐስቀላኒን፣ ኢብኑ ከሢርንና የሌሎችንም ሙሐዲሦች ዘመን እንደ አዲስ አመጣው” ሲሉ አወድሰዋቸዋል።
የተውሒድና የሱናን ባንዲራ ሶሪያ ምድር ላይ ቀላል ለማይባል ጊዜ ያውለበለቡት ሸይኹል አልባኒይ ከተቀናቃኞቻቸው ጋር በዐቂዳ፣ በኢቲባዕ (ረሱልን ﷺ በመከተል)፣ በመዝሀብ ጭፍን ተከታይነትና በቢድዐ ዙሪያ በርካታ ውይይቶችን አድርገዋል። በሂደቱም በመዝሀብ ጭፍን ተከታዮችና በሱፊያ ሸይኾች ቀስቃሽነት ብዙ ፈተና ደርሶባቸዋል። በተመሳሳይ ጊዜ ደማስቆ ውስጥ ከሚገኙ ስመ ጥር ዓሊሞች በአቋማቸው እንዲገፉ ያላሰለሰ ማበረታቻ ከጎናቸው ነበር።
ትግላቸውን አጠናክረው የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች ጭምር የሚካፈሉበት ደርስ እንዲሁም ወደተለያዩ የሶሪያና የዮርዳኖስ ከተሞች እየተዘዋወሩ ወርሃዊ ደዕዋ ማድረግ ቀጠሉ። ኳታር፣ ግብጽ፣ ኩዌት፣ ዐረብ ኢማራት፣ አውስትራሊያ፣ እንግሊዝና ስፔን በተለያዩ ጊዜያት ለደዕዋ ከተጓዙባቸው ሃገራት ውስጥ ናቸው።
ስራዎቻቸው ለህትመት ከበቁ ስማቸው በሰፊው ከታወቀ በኋላ በዝነኛው የመዲና ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሆነው ተመርጠው ለሶስት ዓመታት አገልግለዋል። ከዚህ በኋላ ሱቃቸውን ለአንድ ወንድማቸው በመተው ሙሉ ለሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ጥንታዊው የ“አዟሂሪያ” መክተባ ተመለሱ።
ኢማሙል አልባኒይ ምንም እንኳ ከፖለቲካ የራቁ ቢሆኑም በተለያዩ ጊዜያት መንግስት በዐይነ ቁራኛ ይከታተላቸው ነበር። ሁለት ጊዜም ለእስራት ተዳርገዋል። በሁለተኛ እስራታቸው ከታላላቅ ዐሊሞች ጋር የተገናኙ ሲሆን በእስራት ላይ እያሉም የሙንዚሪን “ሙኽተሶሩ ሶሒሕ ሙስሊም ‘ተሕቂቅ' አድርገዋል።
ለሐቅ ባላቸው ፅኑ አቋምና ለለውጥ ባላቸው የማይታጠፍ ተጋድሎ የሚታወቁት ሸይኹል አልባኒይ ውጫዊ የአመለካከት ወረራዎችን ብቻ ሳይሆን የኢስላምን ውበት ያደበዘዙ ውስጣዊ ወረራዎችንም በመዋጋት ፋና ወጊ ነበሩ። አልባኒይ ለተስፊያና ተርቢያ ማለትም ኢስላምን ከቢድዐ፣ ከሺርኪያት፣ ከደካማ ማስረጃዎችና ሰርጎ-ገብ አመለካከቶች ማፅዳት እንዲሁም ትውልድን ቁርኣንና ሶሒሕ ሱና ላይ በተመሰረተው ንፁሁ ኢስላም ላይ ኮትኩቶ የማውጣት አካሄድ ልዩ ትኩረት ይሰጡ ነበር። ከግማሽ ክፍለ-ዘመን በላይ የተጓዙበትን ይህን አካሄዳቸውን በርካቶች እንዲያጤኑበትና እንዲሄዱበት ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል። ለኡማው አንድነት እጅግ የሚጨነቁት አልባኒይ ለአንድነት የሚደርገው ጥረት ፍሬ ያፈራ ዘንድ ግን ከባዶ የ”አንድ እንሁን” ጩኸት ባለፈ የግድ ወደ ቁርኣንና ሱና መመለስ እንደሚያስፈልግ በፅኑ ያሳስባሉ። እዚህ ላይ በአንድ ወቅት ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡትን መልስ ብናነሳ አይከፋም።
ጥያቄ፡- “ትክክለኛ ነገር ካልያዝን ብለን ከምንበታተን በስህተት ላይ ሆነን ብንሰባሰብ ይሻላል። መክንያቱም ሐቅ ሁሉ ትክክል አይደለምና። እንዲሁም ባጢል (ውድቅ ነገር) ሁሉም ስህተት አይደለምና!”
አልባኒይ፡- “ይሄ ምናባዊና ቅዠታዊ ንግግር ነው። በስህተት ላይ ከሆንን መሰባሰባችን ምንድን ነው ፋይዳው? ከፊላችን በስህተት ላይ ከፊላችን ደግሞ በሐቅ ላይ ከሆንን ብንለያይ ምንድን ነው ጉዳቱ? አሸናፊና የላቀው ጌታችን እንዲህ ይላል:- {ከሐቅ በኋላ ጥመት እንጂ ምን አለ?}
ሸይኹል አልባኒይ በጠንካራ የሰለፊያ አቋማቸው የተነሳ ብዙ ሰቃይና እንግልት ደርሶባቸዋል። ለኢስላም ሲባል ከአልባኒያ የተጀመረው ስደት ደማስቆን መጨረሻው አላደረገም። በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት ከሶሪያ ወደ ዮርዳኖስ፣ ከዮርዳኖስ ዳግም ወደ ሶሪያ፣ ከዚያም ወደ ሊባኖስ፣ ከዚያም ወደ ዐረብ ኢማራት፣ በመጨረሻም ወደ ዮርዳኖስ ዐማን ተንከራተዋል።
እየተስተዋለ
~
ለማንኛውም ኒቃብን ሽፋን በማድረግ የተፈፀሙ ስርቆትና መሰል ወንጀሎች ሲገጥሙን እዚያው ጉዳዩ በተከሰተበት ቦታ ባግባቡ ማስተናገድ በቂ ነው። እንደኛ ሃገር ባለ ህግን ሽፋን የሚያደርጉ ጨቋኞች በበዙበት ምድር እንዲህ አይነት ክስተቶችን ግራ ቀኝ ሳያዩ ወደ ማህበራዊ መገናኛዎች አምጥቶ መነጋገሪያ ማድረግ ለኒቃብ ጠሎች ትልቅ ስጦታ ማቅረብ ነው። እንኳን እንዲህ አይነት ሰበብ አግኝተው የሌለ ነገር እየፈጠሩ ኒቃብን የሚዋጉ ብዙ ናቸው። ዛሬ በዚህ መልኩ ካሳየናቸው ነገ ራሳቸው 'ስክሪፕት' አዘጋጅተው አጥንተው፤ ራሳቸው እየተወኑ ለጥላቻቸው ማመሀኛ ያደርጉታል። "ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል።" ያኔ ከውጭ ቀርቶ ከውስጥ ጭምር የሞኞችን የድጋፍ ድምፅ ያገኙበታልና በጊዜ ብንጠነቀቅ መልካም ነው።
በተረፈ ሰሞኑን ኒቃብ የለበሰች ሴት ስትደበደብ አይተን ያዘንንበትን ቪዲዮ "ሰውየው'ኮ ወንድ ሆኖ ተገኘ" እያሉ ሌላ ቪዲዮ እያቀረቡ ያሉ ሰዎች ትልቅ ጥፋት ነው እየፈፀሙ ያሉት።
በመጀመሪያ ሁለቱ ቪዲዮዎች የተለያዩ ናቸው። ይህንን በሁለቱ ቪዲዮዎች ላይ ያሉትን ኒቃቦች በጥንቃቄ ያስተዋለ ሰው በቀላሉ የሚደርስበት ነው። ሳናጣራ በቀላሉ አንመን።
ሁለተኛ "በተደጋጋሚ በስርቆት ላይ የተሰማራች የሌላ እምነት ተከታይ ናት" እያሉ በፅሁፍም በምስልም ካሰራጩ በኋላ እንደገና "ወንድ ሆኖ ተገኘ" የሚል ሌላ አጀንዳ ሲፈጥሩ በጥርጣሬ ሊታይ የሚገባው ነገር ነው። "በስርቆት ላይ የተሰማራች የሌላ እምነት ተከታይ ናት" ሲሉም ማመን፤ "ወንድ ሆኖ ተገኘ" ሲሉም ማመን? በዚህ መጠንማ የዋህ መሆን የለብንም። በስንተኛው ዙር ነው የምንነቃው?
ደግሞም በደንብ ካጤንነው የሰሞኑ ስራችን ዞሮ እኛን ነው የሚጎዳን። ነገ ተጨባጭ የሆነ በደል አንዷ እህታችን ላይ ቢፈፀም ብዙ ሰው ጉዳዩን በጥርጣሬ በማየት ድምፅ እንዳይሆናት በር ከፍተናል። "ኒቃብን ሽፋን ያደረገች ሌባ ልትሆን ትችላለች"፣ "ወንድ ሊሆን ይችላል" በሚል ብዙ ሰው ችላ ሊለው ይችላል። እና ባላሰብነው አቅጣጫ ለኢስላም እና ሙስሊም ጠል ኃይሎች ወይም እንደጠቃላይ ለበደለኞች እገዛ የሚሆን ነገር እንዳናሰራጭ ብናጣራና ብንጠነቀቅ መልካም ነው።
=
የቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/IbnuMunewor
https://t.me/IbnuMunewor
Telegram
Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)
كناشة ابن منور
አስገዳጅ ሁኔታ ሲገጥም ፊትን ለወንድ መግለጥ
~
አንዳንዴ ፊታቸውን ከባዳ ወንዶች የሚሸፍኑ እህቶቻችን እንዲገልጡ የሚገፋ ጫና ይገጥማቸዋል። ለምሳሌ ጥጋበኛ እጅ ላይ ወድቀው ካልገለጡ ለከባድ ጥቃት ሊጋለጡ ይችላሉ። በመሰል ሁኔታዎች ላይ መግለጥ ይችላሉ? ወይስ ችግሩ የፈለገ ቢከፋ እምቢ ማለት አለባቸው?
አስገዳጅ ሁኔታ ሲገጥም የማይፈቀድ ነገር ይፈቀዳል። الضرورات تبيح المحظورات የሚለው የፊቅህ መርህ ጠንካራ መነሻ ያለውና የታወቀ ነው። አላህ እንዲህ ይላል፦
{ لَا یُكَلِّفُ ٱللَّهُ نَفۡسًا إِلَّا وُسۡعَهَاۚ }
አላህ ነፍስን ከችሎታዋ በላይ አያስገድዳትም።" [አልበቀረህ: 286]
በአስገዳጅ ሁኔታ ህይወትን ለማትረፍ በክት መብላት ይቻላል። ተጨባጭ የሆነ አስገዳጅ ሁኔታ ከገጠመ የክህደት ንግግር በመናገርም ራስን ማትረፍ ይቻላል።
{ مَن كَ.فَرَ بِٱللَّهِ مِنۢ بَعۡدِ إِیمَـٰنِهِۦۤ إِلَّا مَنۡ أُكۡرِهَ وَقَلۡبُهُۥ مُطۡمَىِٕنُّۢ بِٱلۡإِیمَـٰنِ }
"ከእምነቱ በኋላ በአላህ የካደ ሰው (ብርቱ ቅጣት አልለው)፡፡ ልቡ በእምነት የረጋ ሁኖ (በክህደት ቃል በመናገር) የተገደደ ሰው ብቻ ሲቀር።" [አነሕል: 106]
ሌሎችም ጉዳዮች እንዲሁ ይታያሉ። የሙስሊሟ ለባዳ ወንዶች ፊቷን መግለጥም በዚሁ አግባብ የሚታይ ይሆናል። ይህንን መርህ በመንተራስ አስገዳጅ ጉዳይ ሲገጥም ጊዜ ሴት ልጅ ፊቷን መግለጥ እንደምትችል ዓሊሞች ይገልፃሉ። በዚህ ላይ በምሳሌነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉትን ማንሳት ይቻላል:-
1ኛ፦ በማጨት ጊዜ :- ይሄ ሐዲሦች የመጡበት እንዲሁም ኢጅማዕ ያለበት በመሆኑ ለብዙ ሰውም የሚሰወር ስላልመሰለኝ ለማሳጠር ያክል በዚሁ ልለፈው።
2ኛ፦ ለህክምና፦ ጉዳቱ ያለበት ክፍል ፊትም ሆነ ሌላ ክፍል መግለጥ ይቻላል። ከተቻለ ባል ወይም ሌላ መሕረም (ቅርብ ቤተሰብ) አብሮ መኖር አለበት። ባይሆን ሴት ሃኪም ካለ ወደ ወንድ፣ ሙስሊም ካለ ወደ ሌላ መሄድ አይገባም ይላሉ ዓሊሞች። ለህክምና በሚያስፈልገው መጠን ሃኪሙ አካሏን መመልከት ይችላል ይላሉ ኢብኑ ቁዳማ። [አልሙግኒ፡ 7/459]
በነገራችን ላይ ጦር ሜዳ ላይ ሴቶች ሶሐቢያት ወንዶችን ያክሙ ነበር። ኡሙ ዐጢያህ - ረዲየሏሁ ዐንሃ - እንዲህ ትላለች፦
غَزَوْتُ مَعَ رَسُولِ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ سَبْعَ غَزَوَاتٍ أَخْلُفُهُمْ فِي رِحَالِهِمْ، فَأَصْنَعُ لَهُمُ الطَّعَامَ، وَأُدَاوِي الْجَرْحَى وَأَقُومُ عَلَى الْمَرْضَى
"ከአላህ መልእክተኛ ﷺ ጋር ሰባት ዘመቻዎችን ዘምቻለሁ። እቃዎቻቸውን እጠብቅ፣ ምግባቸውን አዘጋጅ፣ ቁስለኞችን አክም እንዲሁም ህመምተኞችን እንከባከብ ነበር።" [ሙስሊም፡ 1812] የቡኻሪን باب هل يداوي الرجل المرأة، والمرأة الرجل እንዲሁም ዘርዘር ያለ ነገር የፈለገ ፈትሑል ባሪን መመልከትም ይቻላል።
3ኛ፦ ችሎት ላይ፦ በፍርድ ችሎት ላይ ፍርድ ለመስጠት ዳኛው አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ፊቷን ይመለከታል። ካልሆነ ሐቅን ማስከበር አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል። ምስክር ሆና ስትቀርብ ወይም በሷ ላይ ምስክርነት ለመስጠትም እንዲሁ መገለጥ ግዴታ ሊሆን ይቻላል። ኢብኑ ቁዳማ እንዲህ ይላሉ፦
وللشاهد النظر إلى وجه المشهود عليها لتكون الشهادة واقعة على عينها، قال أحمد: لا يشهد على امرأة إلا أن يكون قد عرفها بعينها
"መስካሪ ሰው ምስክርነቱ ቦታው ላይ ያረፈ ይሆን ዘንድ የሚመሰከርባትን ሴት ሊመለከት ይችላል። (ኢማሙ) አሕመድ 'በትክክል ለይቶ እስካላወቃት ድረስ አንዲት ሴት ላይ አይመሰክርም' ብለዋል።" [አልሙግኒ፡ 7/459]
ይሄ የሳቸው ሃሳብ ብቻ አይደለም። ሌሎችም "ኒቃብ በለበሰች ሴት ላይ ፊቷን ሳትገለጥ መመስከር አይቻልም" ይላሉ። [አሸርሑል ከቢር፣ ደርዲር፡ 4194]
4ኛ፦ በግብይት ላይም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ሻጭ ወንድ ገዢዋን ሴት ሊመለከት እንደሚችል ዑለማኦች ይገልፃሉ። [አልሙግኒ፡ 7/459] ያለበለዚያ በግብይቱ ላይ ለተፈጠረ ክፍተት ማስተካከያ ለማድረግ ሊቸገር ይችላል። ለምሳሌ እቃ ሽጦላት ፊቷን ካላየ ኋላ ላይ እቃው ችግር ኖሮበት መመለስ ቢያስፈልግ በትክክል እሷ መሆኗን መለየት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።
5ኛ፦ አስገዳጅ ህግ ባለበት ሁኔታ፦ በአንዳንድ ሃገራት ህግ ወይም ኤርፖርት አካባቢ ወይም ሌላ አስገዳጅ ሁኔታ ከገጠመም ፊቷን መግለጥ ትችላለች። ለምሳሌ በመጥፎ ሰዎች እጅ ላይ ወድቃ ራሷን አደጋ ላይ ከምትጥል ፊቷን በመግለጥ ራሷን ማትረፍ ትችላለች። "አስገዳጅ ሁኔታዎች የተከለከለን ነገር ያስፈቅዳሉ።" ስለዚህ ማንነቷን ለመለየት የሚጠይቅ አስገዳጅ ሁኔታ ቢገጥም ወይም ሌላ ተጨባጭ ምክንያት ከኖረ ፊቷን መግለጥ ትችላለች ማለት ነው።
ይሄ እንግዲህ ከዑለማኦች አቋም ውስጥ ለደረሰች ሴት ልጅ ፊትን መሸፈን ግዴታ ነው የሚለውን ስንወስድ ነው። የሆነ ሆኖ ጫን ያለ ሁኔታ ካልገጠማት በስተቀር ለትንሽ ለትልቁ እጅ ልትሰጥ አይገባም። ፍተሻና መሰል ቦታዎች ላይ ሴቶችን መጠቀም የሚቻልበት ሁኔታ ካለ ወይም ደግሞ ጉዳዩ አንገብጋቢ ካልሆነ ባዳ ለሆኑ ወንዶች ፊትን መግለጥ አይገባም። አስገዳጅ ችግር ሲገጥም ደግሞ ጉዳዩን በችግሩ መጠን ብቻ ማስተናገድ ይገባል። "አስገዳጅ ሁኔታዎች በልካቸው ነው የሚስተናገዱት።" እንጂ ችግሩን ማመሀኛ አድርጎ አጉል መዘናጋት ውስጥ መግባት አይገባም። ወላሁ አዕለም! በነጥቡ ላይ ሃሳብ ያለው ሰው ማካፈል ይችላል።
=
(ኢብኑ ሙነወር፣ መስከረም 01/2017)
የቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/IbnuMunewor
https://t.me/IbnuMunewor
Telegram
Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)
كناشة ابن منور
ዓሹራእን ለመውሊድ?
~
የዓሹራእን ፆም ለመውሊድ መረጃ አድርጎ ማቅረብ ከሱፍዮች ዘንድ የተለመደ ነው። ታሪኩ እንዲህ ነው፦ ነብዩ ﷺ ወደ መዲና ሲገቡ አይሁዶች ዓሹራን ሲፆሙ አግኝተዋቸው ነበር። የሚፆሙበትን ምክንያት ሲጠይቋቸው “አላህ ፊርዐውንን አስጥሞ ሙሳን ያተረፈበት ቀን ስለሆነ ነው” ይላሉ። በዚህን ጊዜ ነብዩ ﷺ “ለሙሳ እኛ ከናንተ ይበልጥ የተገባን ነን” አሉ። እናም ይህንን መነሻ በማድረግ ትልቅ ድል ወይም ትልቅ ፀጋ የተገኘባቸውን እለቶች አስቦ መዋል እንደሚቻል ሐዲሡ ያመላክታል። የነብዩ ﷺ መወለድ ደግሞ ከነዚህ ፀጋዎች ውስጥ ቀዳሚው ነው ይላሉ።
ለዚህ የሚሰጠው ምላሽ፡-
ነገሩ እንዲያ ከሆነ ለምን ገንናንም ከክርስቲያኖች ጋር አታከብሩም? ዒሳ የኛ ነብይ አይደሉም የሚል አንድ ሱፊ ሰምቻለሁ። እንግዲያው ሙሳም የናንተ ነብይ አይደሉምና ታሪካቸውን አታጣቅሱ። የዓሹራእ ታሪክ'ኮ የሙሳ ታሪክ ነው። ስለዚህ ዓሹራእንም አትፁሙ። ሂሳባችሁ ይህንን ነው የሚሰጠው።
የዓሹራእ ፆም ማስረጃ የሚሆናችሁ ከሆነ ለምን ዓሹራእንም በጭፈራ አታከብሩትም? ወይ ደግሞ ለምን ለመውሊዱም እንደ ዓሹራው ፆም አይበቃችሁም?
ስለዚህ ዓሹራእና መውሊድ አፈፃፀማቸውም ለየቅል ነው። ሱናው ፆም ሲሆን ቢድዐው ግን መብላት፣ መጨፈር ነው። እናም ማስረጃው ያስኬዳል ቢባል እንኳ እለቱን መፆም ላይ የሚገደብ ነበር። ይህንን ነጥብ ለመዝለል የመውሊድ አክባሪዎች የሚሰሩት ውሽልሽል ሰበብ ራሳቸውን ከመሸወድ ያለፈ ዋጋ የለውም።
ዓሹራእን ነብዩ ﷺ እንዲፅፆም ማዘዛቸው አስተማማኝ መረጃ የመጣበት ሲሆን አመታዊ ልደታቸውን ግን እንኳን በጭፈራ በፆምም አላሳለፉትም። አላዘዙበትምም። ቅንጣት ታክል መረጃም የለውም። ሶሐቦቹም፣ ታቢዒዮቹም፣ አትባዑ ታቢዒንም፣ አራቱ ኣኢማዎችም አላከበሩትም። ይህም የዓሹራእ ጉዳይ ፈፅሞ ለመውሊድ ማስረጃ እንደማይሆን ያሳያል። ስለሆነም ዓሹራእ ራሱን የቻለ ዒባዳ እንጂ የሌሎች ቢድዐዎች መነሻ አይደለም። ያለበለዚያ ለ600 አመታት የሙስሊም ምሁራን ሐዲሡን አልተረዱትም ማለት ነው። ይሄ ከባድ ውንጀላ ነው።
በነብዩም ﷺ ይሁን በሶሐቦቹ ዘመን ታላላቅ የአላህ ፀጋዎች የተፈፀሙባቸው ቀናት ብዙ ሆነው ሳለ በየአመቱ ያስቧቸው እንደነበር የሚጠቁም መረጃ አንድም የለም። ለምሳሌ በዚያ ድንቅ ዘመን ከተፈፀሙ እጅግ ትልልቅ የአላህ ፀጋዎች ውስጥ በሒራእ ዋሻ ሳሉ መልአኩ ጂብሪል የሳቸውን ነብይነት ይዞ የመጣበትና የመጀመሪያው ቁርኣን (ኢቅራእ) የወረደበት ቀን፣ በአንድ ሌሊት ከመካ በይተል መቅዲስ ድረስ ተጉዘው፣ ሰማየ ሰማያት ወጥተው ከጌታቸው ጋር ተገናኝተው አምስት ወቅት ሶላቶችን የተቀበሉበት (የኢስራእና ሚዕራጅ) ቀን፣ ነብዩ ﷺ ከመካ ወደ መዲና የተሰደዱበት ቀን፣ ሙሽሪኮችን በድል ያንበረከኩበት የበድር ዘመቻ ቀን፣ የአሕዛብ ድል፣ አስራ ሶስት አመት ተሰቃይተው በከሃዲዎች ግፍ ምክንያት ጥለዋት የሄዷትን መካን ተመልሰው በድል የተቆጣጠሩባት ቀን፣ ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው። እስኪ ከነዚህ ውስጥ ነብዩ ﷺ የትኛውን ነው በያመቱ ሲያከብሩ የነበረው? በአቡበክር ጊዜም የአፈንጋጮች አከርካሪ የተሰበረበት ጦርነት ተካሂዷል። በዑመር ጊዜም ሙስሊሞች በርካታ ተከታታይ ድሎችን በመጎናፀፍ የዘመኑን ልእለ-ሃያላን አፈራርሰዋል። ለምሳሌ የቃዲሲያ ድል፣ የኒሃውንድ ድል፣ የፈለስጢን፣ የዒራቅ፣ የግብፅ … መከፈት። በዑሥማን ጊዜም በድል ላይ ድል እየደራረቡ ግዛታቸውን አስፍተው እስከ አውሮፓ ዘልቀዋል። በዐሊይ ጊዜም ዐሊይን በደስታ ሱጁድ ያስወረደ ልዩ ድል በኸዋ .ሪጅ ላይ ተመዝግቧል። በ 41ኛው ሂጅራም ነብዩ ﷺ “ይሄ ልጄ ታላቅ ነው። ምናልባትም አላህ በሱ ሳቢያ ሁለት ትልልቅ የሙስሊም ጎራዎች ያስታርቃል” ያሉት ትንቢት ሐሰን ብኑ ዐሊይ ረዲየላሁ ዐንሁ ስልጣናቸውን ለሙዓዊያ በማስረከባቸው ምክንያት ለሁለት ጎራ ተከፍለው የነበሩት ሙስሊሞች ህብረትን አጣጥመዋል። [አልቡኻሪይ፡ 2704] አመቱንም “የአንድነት አመት” በማለት ሙስሊሞች ደስታቸውን ለታሪክ አስተላልፈዋል። እነዚህ ሁሉ አንፀባራቂ ገድሎች ቢመዘገቡም ባለ ገድሎቹ ሶሐቦች ግን በያመቱ እነዚህን ገድሎች እየተሰባሰቡ የሚዘክሩ አልነበሩም። ሐዲሡ ስላልገባቸው ነው? ታቢዒዮቹስ? አትባዑት ታቢዒንስ? አራቱ አኢማዎችስ? እነ ቡኻሪ እነ ሙስሊምስ?
ሶሐቦችን እንዲህ አይነቱ የመረጃ አጠቃቀም እንዴት ተሰወራቸው? ዘግይቶ የመጣው ትውልድ ከነሱ የበለጠ አላህን አመስጋኝ ነውን? የነብዩ ﷺ ምስጢረኛ የነበረው ሶሐባው ሑዘይፋህ ብኑል የማን ረዲየላሁ ዐንሁ “የአላህ መልእክተኛ ﷺ ሶሐቦችና ቤተሰቦቻቸው አላህን ያላመለኩበትን እያንዳንዱን አምልኮት አላህን አታምልኩበት። የመጀመሪያዎቹ ለኋለኞቹ የተውት ቦታ የለምና” ይላሉ። [አዙህድ፡ 47]
ደግሞም ሐዲሡ ውስጥ ትልልቅ ፀጋዎች የተገኙባቸውን ቀናት ለማሰብ መረጃ ማድረግ እንደሚቻል ብንግባባ እንኳን ለመውሊድ መረጃ መሆን አይችልም። ምክንያቱም ነብዩ ﷺ የተወለዱበት የአመቱ ቀን ከውዝግብ በፀዳ በትክክል አይታወቅምና። በየትኛውም የአመቱ ጊዜ መውሊድን ማክበር ይቻላል የሚሉ ሰዎች ይህንን ሐዲስ ማስረጃ ማድረግ አይችሉም። ምክንያቱም በሐዲሡ ውስጥ ዓሹራእ የሚፆመው ፊርዐውን በሰመጠበት፣ ሙሳን አላህ ባተረፈበት ቀን እንጂ አመቱን ሙሉ ወይም ባሰኛቸው ቀን አይደለምና።
(ኢብኑ ሙነወር፣ መስከረም 28/2014)
የቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/IbnuMunewor
https://t.me/IbnuMunewor
Telegram
Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)
كناشة ابن منور
ሒልየቱ ጧሊቢል ዒልም
ክፍል - 16
የሱና ብርሃን ትምህርት ቤት ግሩፕ ላይ በኢብኑ ሙነወር በየ ሳምንቱ የሚሰጥ ትምህርት።
የቴሌግራም ቻናል፡‐
https://t.me/fejir_tube
Welcome To Amharic films
Best Place To find Amharic Movies
አዳዲስ እና የድሮ አማርኛ ፊልሞችን እና አማርኛ ተከታታይ ድራማዎችን ለማግኝት ቻናላችንን Join ይበሉ ።
Share:- @Amharic_Films
ለማስታወቂያ - @Abusheymc & @Alpha6249
Buy ads: https://telega.io/c/Amharic_films
Last updated 1 year, 5 months ago
ስለ መድፈኞቹ የሚወጡ መረጃዎች ለማግኘት የትም መሄድ አያስፈልግም
- የዝዉዉር ዜና
- የአሰልጣኞች አስተያየት
- የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
- ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት
ለማስታወቂያ ስራ --> @MKHI7
Last updated 4 days, 15 hours ago
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።
#ኢትዮጵያ
ያግኙን +251913134524
Last updated 1 week, 5 days ago