እሸት ሐሳቦች - Fresh Ideas (እ.ብ.ይ.)

Description
Facebook- https://www.facebook.com/atnatiwose.birru/
Advertising
We recommend to visit

Welcome To Amharic films

Best Place To find Amharic Movies

አዳዲስ እና የድሮ አማርኛ ፊልሞችን እና አማርኛ ተከታታይ ድራማዎችን ለማግኝት ቻናላችንን Join ይበሉ ።
Share:- @Amharic_Films

ለማስታወቂያ - @Abusheymc & @Alpha6249

Buy ads: https://telega.io/c/Amharic_films

Last updated 1 год, 6 месяцев назад

ስለ መድፈኞቹ የሚወጡ መረጃዎች ለማግኘት የትም መሄድ አያስፈልግም

- የዝዉዉር ዜና
- የአሰልጣኞች አስተያየት
- የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
- ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት

ለማስታወቂያ ስራ  --> @Aymu_xo

Last updated 1 месяц назад

╔╦╦═╦╔╦═╦═╦═╗
║ እንኳን ደህና መጡ | |
╚══╩═╩═╩╩╩╩═╝
➟ እንኳን ወደ ትልቁ የሊቨርፑል ( መርሲሳይድ) ቻናል በደህና መጡ ።
◉ ስለ ሊቨርፑል ◉
🔴 ዝውውሮች

🔴 ውጤቶች

🔴 የጨዋታ ፕሮግራሞች

🔴 እንዲሁም የተጨዋቾች ግለ ታሪክ

🔴 ጨዋታዎችን በቀጥታ ወደናንተ የምናደርስ ይሆናል።

Owner:- @hackersolo0⭐️

Last updated 2 недели, 1 день назад

2 months, 1 week ago

ችግርህን ወይ ተቋቋመው፤ ወይ ተሰቃይበት!
(Mope or Cope)
(እ.ብ.ይ.)

የብዙዎቻችን ቸግር የደረሰብንን ችግር የምናይበት መንገድ ነው፡፡ ችግሩን የምናይበት መንገድ ራሱ ችግር ነው! (The way we see the problem is the problem)፡፡ አንደኛ ከችግሩ ልንወጣበት ያሰብነው መንገድ ራሱ ሌላ ችግር ውስጥ የሚከትት ነው፡፡ መንገዱ ወደገደል ይዞን የሚገባው መውጫ መንገዱን ያየንበት መንገድ የተሳሳተ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛ ችግሩን ልንፈታበት ያሰብነው መላ ትናንት በወደቅንበት መላ ነው፡፡ በወደቅንበት በኩል መነሳት ከባድ ነው፡፡ ጊዜ ባለፈበት ዘዴ አዲስ በር መክፈት አይቻልም (Old ways do not open new doors)፡፡ አዲስ እይታ፣ አዲስ መንገድ ወሳኝ ነው፡፡

ሰውየው ዛፍ እየቆረጠ ነው፡፡ አንድ መንገደኛ ‹‹ምን እየሠራህ ነው?›› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ዛፍ ቆራጩም ‹‹የምሠራው አይታይህም? ዛፍ እየቆረጥኩ ነው እኮ!›› አለው፡፡ መንገደኛውም ‹‹በጣም የደከመህ ትመስላለህ፡፡ ምን ያህል ጊዜ ሆነህ ዛፍ መቁረጡን ከጀመርክ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ዛፍ ቆራጩም ‹‹ከአምስት ሠዓታት በላይ ይሆናል፡፡ ከአቅሜ በላይ ሆኗል፡፡ ከባድ ስራ ነው›› በማለት ስልችት ባለ ድምፀት መለሰለት፡፡ መንገደኛውም ‹‹ታዲያ ለምን ትንሽ ደቂቃ አታርፍምና መጋዙን ሞርደህ አትቀርጥም? ቶሎ የምትጨርስ ይመስለኛል›› አለው፡፡ ዛፍ ቆራጩም ‹‹ለመሞረድ ጊዜ የለኝም›› በማለት መለሰለት ይባላል፡፡

ዛፍ ቆራጩ ጊዜ የሌለው ለሚያደክም ስራ ነው፡፡ ጊዜውን ባግባቡ ለመጠቀም አልሞከረም፡፡ ፈረንጆቹ Busy for nothing እንደሚሉት ዓይነት ነው፡፡ ድካማችንን የሚያረዝመው ለችግሩ ያለን አስተሳሰብ ነው፡፡ ጊዜን ባግባቡ መጠቀም ማለት እንደዚህ አይደለም፡፡ አምስት ደቂቃ አርፈህና መጋዝህን ሞርደህ ድካምህንና ጊዜህን መቀነስ በማሰብ የሚገኝ መላ ነው፡፡ አምስት ደቂቃ አስቦ አምስት ሰዓታትን ማትረፍ ጊዜን በአግባቡ ከመጠቀም አልፎ ከጊዜ ከራሱ ማትረፍ ነው፡፡

በዋናነት እኛን የሚጎዳን ወይም የሚሰብረን የደረሰብን ወይም እየሆነብን ያለው ነገር ሳይሆን እየሆነ ላለውና ለደረሰብን ነገር የምንሰጠው መፍትሄ ወይም ምላሽ ነው፡፡ (It is not what happens to us but our response to what happen to us that hurts us):: እንቅፋቶቻችንን ሙሉ በሙሉ ቀድመን አውቀናቸው ልናስወግዳቸው አንችልም፡፡ የምንችለው ከእንቅፋቱ በኋላ ያለውን ሁኔታ ነው፡፡ ሳንካ፣ ፈተና፣ ጋሬጣ በህይወት መንገድ ላይ ያጋጥማል፡፡ በሳንካው ወይም በጋሬጣው መሰቃየት ግን ምርጫ ነው፡፡ ከሁኔታው በኋላ ያለው ነው በእኛ አዕምሮ ፈቃድ የሚወሰነው፡፡ በደረሰብን የምንተክዝና የምንሰቃይ ከሆነ የሚተርፈን ወዮታ ብቻ ነው፡፡ የደረሰብንን ነገር ገልብጠን ወደመልካም የምንለውጥ ከሆነ ግን የምናገኘው ከችግር ነጻ መውጣትን፣ አዲስ ልምድና ደስታ ነው፡፡

የጋራ ችግሮቸቻችንም የማይፈቱት ስለማንደማመጥ ነው፡፡ ብንሰማማም አንደማመጥም፤ ብንደማመጥም አንግባባም፡፡ በቃላት የማንግባባው፣ በሃሳብ የምንለያየው፣ በጉንጭ አልፋ ክርክር ጊዜ የምናጠፋው እርስበርስ ለመግባባትና አንዱ አንዱን ለመረዳት ስለማንፈቅድ ነው፡፡ ብዙ ክርክሮቻችን ያን ያህል የሃሳብ ልዩነት የሉባቸውም፡፡ ስቴቨን ኮቪይ “Most arguments are not disagreements but are rather little ego battles and misunderstandings” እንዲል እርስበርስ አለመግባባትና ‹‹እኔ እበልጥ- እኔ እበልጥ›› የሚል በልጦ የመገኘት የግል ጦርነት ነው ልዩነታችንን እያሰፋ ያለው፡፡

ወዳጄ ሆይ..... ከችግርህ ጋር ስትሰቃይ ትኖራለህ? ወይስ ችግርህን ገንድሰህ ትጥለዋለህ? (Are you going to cope or mope?) ምርጫው ያንተ ነው፡፡ ከራስ ጋር የሚደረገው ጦርነት ቀላል አይምሰልህ፡፡ አጉል ልማድህን ድል ማድረግ፣ ለከት ከሌለው ፍላጎትህ ነጻ መውጣት፣ ስሜትህን መግራት ከቻልክ የትኛውም ችግር አያስደነግጥህም፡፡ ችግርህን ተራራ የሚያሳክለው የተሳሳተው አስተሳሰብህና ስሱ ስሜትህ ብቻ ነው፡፡ ስሜትህ ስስ ከሆነ በደረሰብህ ሁሉ ታላዝናለህ፡፡ አስተሳሰብህን ካዘመንክ፣ ስሜትህን ካጠነከርክ ግን ከችግር መውጫ መንገዱን ማግኘት አይከብድህም፡፡ መላው በእጅህ ይሆናል፡፡

በችግርህ ላይ በማላገጥ ከችግርህ መላቀቅ አትችልም፡፡ ችግርህን የሚፈታ አዲስ ሃሳብና ተግባር ግድ ይልሃል፡፡

ቸር ብልሃት!

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑሩ!

_______________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሠኞ ጥቅምት ፲፰ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም.

2 months, 2 weeks ago

‹‹እጅና እግርን ከማጣት የአካልጉዳት በላይ ፍርሃት ትልቁ ጉዳት ነው፡፡››
(Fear is the bigger disability than having no arms and legs)››
(እ.ብ.ይ.)

ፍርሃት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የማይፈራ ማንም የለም፡፡ ሃብታም በለው ንጉስ፤ ደሃ ይሁን ተራ ፍርሃት ሁሉንም ያንቀጠቅጣል፡፡ ከሞት ጋር አብሮ የሚውለው፤ ነፍሱን ለሐገሩ አሲይዞ የሚዋጋው ወታደር እንኳን በፍርሃት ይናጣል፡፡ ፍርሃት ከእኛ ጋር ተፈጥሯል፡፡ ፍርሃት የወደፊቱን ያለማወቃችን ምልክት ነው፡፡ ሁሉን አለማወቅ ደግሞ ሃብት ንብረታችን ነው፡፡ ሁሉን አውቀን መጨረስ አንችልም፡፡ ከምናውቀው በላይ የማናውቀው እልፍ ነው፡፡ በርግጥ ብናውቅም ባናውቅም፤ ሊቅም ሆንን ደቂቅ፤ መረጃ ኖረን አልኖረ የሚያስፈራን ብዙ ነገር አለ፡፡ ነገር ግን ከሚያስፈራን አስፈሪው ነገር የበለጠ ራሳችን በአስተሳሰባችን የፈጠርነው ምክንያታዊ ያልሆነ ፍርሃት (Irrational In-house fear) ነው ከዓላማችን የሚያደናቅፈን፡፡ ብዙዎች በሰው ሰራሽ ፍርሃት ምክንያት ፀጋቸውን አልተጠቀሙበትም፤ ህልማቸውን እውን ሳያደርጉ ያለፉና የጋን ውስጥ መብራት የሆኑ ቤት ይቁጠራቸው፡፡ በአካል ጉዳታቸው ምክንያት በጓዳ የቀሩ ብዙ መክሊቶች አሉ፡፡

ፍርሃታቸው ቤት ካላስቀራቸው ለዓለም ሕዝብ ምሳሌ ከሆኑ ሰዎች መካከል የአንዱ ሰው ታሪክ ግን ለየት ያለ ነው፡፡ ወደዚች ዓለም ሲመጣ Tetra-ameliua syndrome ተጠቂ ሆኖ ነው የተወለደው፡፡ ይሄ በሽታ በዩኤስኤ እንኳን ከአንድ ሚሊየን ሰዎች መካከል ባንድ ሰው ብቻ የሚከሰት በተፈጥሮ የሚመጣ የእጅና እግር የማጣት የአካል ጉዳት ነው፡፡ ሰውየው የሚበላበት እጅና የሚንቀሳቀስበት እግር የለውም፤ ነገር ግን ተረከዝና ጣቱን በመጠቀም በደቂቃ እስከ 45 የሚደርሱ ቃላትን ኮምፕዩተር ላይ መተየብ ይችላል፡፡ ዋና መዋኘት፣ መኪና መንዳት፣ ከበሮ መምታት፣ ቴኒስ መጫወት፣ ሀይለኛ የባህር ሞገድ ላይ መንሳፈፍ (Surfing) አልተሳነውም፡፡ ተሰድቧል፣ ተንቋል፣ ብዙ መከራ አይቷል፤ ነገር ግን መከራውን ሁሉ ተሻግሮ ትልቅ ስኬት ላይ ደርሷል፡፡ ተስፋ ቆርጦ ራሱን እስከማጥፋት ቢደርስም ያንን ጨለማ አስተሳሰቡን አሸንፎና ራሱን ቀና አድርጎ እንደእሱ በእሱ መከራ መንገድ የሚመላለሱትን ሚሊዮኖች ምሳሌ በመሆን መንገድ አሳይቷል፤ የዓለምን ሕዝብ አነቃቅቷል፡፡ አካል ጉዳተኛ ነው፤ ነገር ግን አፍቅሮና ተፈቅሮ፣ አግብቶና ወልዶ ለመሳም አካል ጉዳቱ ምንም አላገደውም፡፡ የሁለት ወንድ እና የመንታ ሴቶች ልጆች አባት ሆኗል፡፡ እጅና እግር አልባ ሆኖ መወለዱ በቤት አስተኝቶ አላስቀረውም፤ እንደውም ዓለምን በአነቃቂ ንግግሩ አጥለቅልቋል፡፡ ራሱን አልደበቀም፤ ይልቁንስ እስከነጉዳቱ በአደባባይ ራሱን ገልጧል፡፡ ተሞክሮውን፣ ያሳለፈውን ውጣውረድ፣ በራሱና በአምላኩ ላይ ያለውን መተማመን፣ እምነትን በተግባር የመግለጥ አስፈላጊነትን፣ የፍቅር ግንኙነቱን፣ ራሱን በራሱ የጎዳበትን (Self destructive thoughts) ሃሳቡን፣ መቆጣጠር የማይችላቸው ከአቅሙ በላይ የሆኑ ክስተቶችን እንዴት ለአምላኩ አደራ እንደሰጠ፣ በአካሉ፣ በአዕምሮው፣ በልቡና በመንፈሱ መካከል ያለውን ሚዛን አጠባበቁንና ወዘተ ወደር የሌላቸው ሃሳቦቹን በተከታታይ ባሳተማቸው ሰባት መፅሐፎቹ ተሞክሮዎቹን በሙሉ ለአንባቢዎቹ አጋርቷል፡፡ መፅሐፎቹም ‹‹Life without limitation (2007)››፣ ‹‹Unstoppable: The Incredible Power of Faith in Action (2013)››፣ ‹‹Limitless: Devotions for a ridiculously good life (2013)›› ‹‹The power of Unstoppable faith (2014)››፣ ‹‹Stand strong (2015)››፣ ‹‹Love without Limits (2016)›› እና ‹‹Be the hands and feet (2018)›› ይባላሉ፡፡

ይሄ ሰው አውስትራሊያዊው አነቃቂና ወንጌላዊ የሆነው ኒክ ቩጂሊክ (Nick Vujicic) ነው፡፡ ‹‹ሰው እግዚአብሔር ካለው እጅና እግርን ማን ይፈልጋል (“Who needs limbs when you have God?”)›› ይላል፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ያለው እምነቱ ጠንካራ ነው፡፡ በራሱ ይተማመናል፣ በአምላኩ ያምናል፡፡ እምነቱን በአፉ ብቻ ሳይሆን በተግባርም (Faith in action) ይኖርበታል፡፡ ልጆቹን አቅፎ የሚያጫውትበት፣ ባለቤቱን ዳስሶ የሚያሞቅበት እጅ የለውም፡፡ ነገር ግን ልቦቻቸውን በፍቅር የሚያቀልጥበት የሞቀ ልብ አለው፡፡

ኒክ ‹‹Unstoppable›› በተባለው ሁለተኛው መፅሐፉ በመጀመሪያው ምዕራፍ ‹‹Faith in Action›› ላይ በብዙ ምሳሌዎች እንደሚያብራራው እምነት ያለተግባር ከንቱ መሆኑን ነው፡፡ እምነትህን የሚያረጋግጠው መልካም ስራህ ነው፡፡ ሃይማኖተኝነት ወይም እምነት ትልቅ ነገር ነው፤ ነገር ግን ያንተን ሕይወት የሚለካው ሃይማኖትህ ብቻ ሳይሆን መልካም ስራህም ጭምር ነው ይላል፡፡ እግዚአብሔር እጅና እግር የሌለው አድርጎ የፈጠረኝ ሊቀጣኝ ሳይሆን ሌሎችን ማስተማሪያ እሆን ዘንድ ሊጠቀምብኝ ነው ብሎ ያስባል፡፡ ጉዳቱን ለበረከት ተጠቅሞበታል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹በሕይወት ውስጥ አማራጮች አሉህ፡፡ መራራውን ወይስ ጣፋጩን ነው የምትመርጠው?›› ብሎ ይጠይቅና ‹‹መራራውን ትተህ ጣፋጩን ምረጥ›› በማለት ይመክራል፡፡ አዎ በሌለህ ነገር እያማረርክ ከኖርክ ሕይወትህን መራራ ይሆናል፡፡ ባለህ ፀጋ ተጠቅመህ ግን ራስህን ለመለወጥ ቆርጠህ ከተነሳህ ሕይወትህን ጣፋጭ ታደርጋለህ፡፡ ጨዋታው ያለው ጠቃሚውን መምረጥ ላይ ነው፡፡

ወዳጄ ሆይ..... ኒክ ‹‹እጅና እግርን ከማጣት የአካልጉዳት በላይ ፍርሃት ትልቁ ጉዳት ነው፡፡ (Fear is the bigger disability than having no arms and legs)›› የሚለው ራስህን ከሚጎዳህ ከአጉል ፍርሃት ራስህን ጠብቅ ለማለት ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ተሸናፊ የሆኑት ባላስፈላጊ ፍርሃት ነው፡፡ መፈራት የሚገባውን መፍራት ተገቢ ነው፡፡ የማያስፈራውን መፍራት ግን ስነልቦናዊ ህመም ነው፡፡ ፍርሃትህ ከአስተሳሰብህ፣ ከህልምህ፣ ከግብህ እንዳያቆምህ ተጠንቀቅ፡፡ ፍርሃትህን መዝነው፤ ሃሳብህን ፈትሸው፤ የምትችለውን ከማትችለው ለይ፡፡ እምነት የሚረጋገጠው በተግባር ነው፡፡ ሃይማኖት ኖሮህ መልካም ስራ ከሌለህ የምታምነውን የእውነት አታምነውም ማለት ነው፡፡ እምነትህን በተግባር ግለጥ፤ ሃይማኖትህን በመልካም ስራ አሳይ!

ቸር እምነት! ደግ ፍርሃት!

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑሩ!

_________________________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሠኞ ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም.

2 months, 3 weeks ago

ምህዋረ ሃሳብ፦
“አውቆ አለመተግበር አለማወቅ ነው”
ጸሐፊ፦እሸቱ ብሩ ይትባረክ
አቅራቢ፦ተስፋዬ ማሞ

4 months, 2 weeks ago

ሰዎች የሚናገሩትን ብቻ ሳይሆን የማይናገሩትንም አስተውል!
(Understand to what people don’t say)
(እ.ብ.ይ.)

ብዙ ጊዜ ሰው በንግግሩ ብቻ አይታወቅም፡፡ የሚናገረው ሌላ ማንነቱ ሌላ የሆነ ሰው እልፍ ነው፡፡ ሰው ከሚናገራቸው ይልቅ ድርጊቶቹ ናቸው የሰውየውን ማንነቱን የሚናገሩት፡፡ ቃል አሳሳች ነው፡፡ አፍ ወላዋይ ነው፡፡ ስሜታዊ ንግግር አይጨበጥም፡፡ ስብከት ብቻ ሰውን አይለውጥም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አትስረቅ እያልክ የምትሰብክ ትሰርቃለህን?›› የሚለው ለዚህ ነው፡፡ ተራ ዲስኩር የሰዉን ልኩን አያሳውቅም፡፡ የሰው ልኩ ያለው ድርጊቱ ላይ ነው፡፡ ድርጊቱ ከሃሳቡ የተወለደ ነው፡፡ የሰውን ሃሳብ ማወቅ አዳጋች ቢሆንም አስተዋይ ከሆንክ ግን ከንግግሮቹ መሃል ያልተናገራቸውንና ያልገለጣቸውን ስሜቶቹን በማንበብ ልትረዳው ትችላለህ፡፡

ብዙ ሰው የእሱን እውነት አምነህ እንድትቀበለውና እንድትረዳው የማያደርገው ጥረት የለም፡፡ እሱ ግን አንተን አንድ ሰከንድ አድምጦህ ሊገነዘብህ አይፈቅድም፡፡ የማያዳምጥ ሰው ማሳመንም ማመንም አይችልም፡፡ ፕሌቶ “ሪፐብሊክ” በተባለ ስራው ‹‹የማያዳምጡ ሰዎችን ማሳመን አትችልም (You can not persuade people who won’t listen)›› የሚለው ለዚህ ነው፡፡ የማያዳምጥ ሰው ቢናገርም ንግግሩ ውሃ አይቋጥርም፤ ቢሰማምም ከልቡ አያዳምጥም፡፡ ዲስኩሩ ከማሳመን ይልቅ ደካማ አስተሳሰቡን ያሳብቃል፡፡

ሰዎች ብዙ ጊዜ ከሚናገሩት ይልቅ የማይናገሩትን ናቸው፡፡ ከተነፈሱት ይልቅ ያልተነፈሱት ነው የነሱን ትክክለኛ ማንነት የሚገልፀው፡፡ ከሚናገሩት መሀል ያልተናገሩትን የምታሰብ ከሆነ የሰዎችን ትክክለኛ ማንነት ልትደርስበት ትችላለህ፡፡ ብዙ ሰዎች ከሚናገሩት በታች አልያም ከሚናገሩት በላይ ናቸው፡፡ የተናገሩትን እሱኑ በትክክል የሆኑ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ወይ ይጨምራሉ፤ ወይ ይቀንሳሉ፤ አልያም ያልሆኑትን ለመምሰል ይሞክራሉ፡፡

ታዋቂዋ አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይት እና የቴሊቭዥን አቅራቢ እንዲሁም ኮሜዲያን የሆነችው ኤለን ዴጄነሬስ (Ellen Degeneres) ‹‹ሰዎች የማያዩትን አያለሁ፤ ሰዎች ትኩረት ያላደረጉበትን፣ ያልተረዱትንና ዋጋ ያልሰጡትን ለመረዳት እጥራለሁ፡፡ ለዚህ ይመስለኛል ኮሜዲያን የሆንኩት፡፡ ሰዎች በሚያዩትና በማያዩት መካከል ትንሽ ቦታ አለች፡፡ ያቺን ቦታ ነው እኔ የተጠቀምኩባት›› ትላለች፡፡ እውነት ነው! ሰዎች የማያዩትን ማየት፣ የማያስተውሉትን ማስተዋል፣ ትኩረት ያልሰጡበትን ትኩረት መስጠት የተለየ አዲስ ሃሳብ እንድትፈጥር የደርግሃል፡፡

ወዳጄ ሆይ.... ሮማዊው ፈላስፋ ሴኔካ ‹‹እኔ ሰውን በአዕምሮ እንጂ በዓይን አልለይም፡፡ ትክክለኛ ዳኛው እሱ ነውና (I do not distinguish by the eye, but by the mind, which is the proper judge of the man)››› የሚለው ሰውን ልትረዳው የምትችለው በነፍሱ መሆኑን አፅንኦት ሲሰጥ ነው፡፡ ዓይንና ጆሮህ በሚሰጡህ መረጃ ብቻ ታምነህ የሰውን ልኩን ልታውቅ አትችልም፡፡ ከቃሉ ጀርባ ያለው ስሜቱን፣ ለንግግሩ መግፍኤ የሆነው መንፈሱን፤ ለድርጊቱ መነሻ የሆነውን ሃሳቡን ለመረዳት ካልሞከርክ የሰውን ማንነት በቀላሉ አታገኘውም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ዘዴ ራስን ማወቅ ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ድርጊትህ መነሻ ሃሳብህንና አመለካከትህን ስታውቅ የአንተነትህን ቦታ ታገኘዋለህ፡፡ ራስህን ማወቅ የምትጀምረውም ለሰዎች ከምታሳየው ፌኩ አንተነትህ ጀርባ እውነተኛው አንተነትህን መረዳት ስትችል ነው፡፡ ከዛ በኋላ ነው ሌሎች ሰዎችን ከንግግራቸውና ከፊታቸው ባሻገር ያለውን ትክክለኛ መልካቸውን አጥርተህ ማየት የምትችለው፡፡

ቸር መረዳት!
ኢትዮጵያና ኢትዮያዊነት ለዘላለም ይኑሩ!
------------------
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሠኞ ነሐሴ ፳ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም.

4 months, 3 weeks ago

ምህዋረ ሃሳብ
“የህይወትህ ጉዳይ ያለው ካለፈው ይልቅ የሚቀጥለው ላይ ነው”
Prescribe versus Subscribe
ጸሐፊ፦እሸቱ ብሩ ይትባረክ
አቅራቢ፦ተስፋዬ ማሞ

5 months ago

ብልሆች ትዕግስተኞች ናቸው፤ ሞኞች ጠባቂዎች ናቸው!
(Patience is not the ability to wait)
(እ.ብ.ይ.)

ብልሆች ትዕግስተኞች ናቸው፤ ሞኞች ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ጠባቂነት ትዕግስተኝነት አይደለም፤ ትዕግስትም ጠባቂነት አይደለም፡፡ የምትታገሰው እየሰራህ ነው፤ ግብህን ቆመህ አይደለም የምትጠብቀው፤ እየሄድክ ነው የምትደርስበት፡፡ መጠበቅ በሽታ ነው፡፡ ከመጠበቅ በሽታ መዳን የሚቻለው በስራ ነው፡፡ ከሰው የምትጠብቅ ከሆነ መተማመኛህ ውጫዊ ነገር ነው፡፡ ከጊዜ የምትጠብቅም ከሆነ ጊዜ በራሱ ይዞት የሚመጣው ነገር የለም፡፡ በጊዜ ውስጥ ያለኸው አንተ ነህ አምጪውም አስቀሪውም፡፡ ዕድል የሚሰምርልህ፣ አጋጣሚ የሚሳካልህ እጅና እግርህን ታቅፈህ ቁጭ ብለህ በመጠበቅ ሳይሆን የልብህን በር ለመልካም አጋጣሚ ክፍት ስታደርግና ዕድልህን ፍለጋ አደባባይ ስትወጣ ነው፡፡ ሎተሪ ካልቆረጥክ እንደማይደርስህ ሁሉ ልታገኘውን የምትሻውን ዝም ብለህ ከጠበቅከው አይመጣም፤ ከሞከርከው ግን አንተው ራስህ በጊዜ ሂደት ታመጣዋለህ፡፡

በአንድ ሐገር ውስጥ ታማኝ ውሻ የነበረው አልቃድር የሚባል ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው ኑሮ አልሰምርለት ሲል የመከራ ጎጆውን ዘግቶ ላይመለስ ተሰደደ፡፡ ውሻው ለሣምንታት በቤቱ በራፍ ላይ ኩርምት ብሎ ጌታውን ሲጠብቅ ከሰነበተ በኋላ በተኛበት ሞቶ ተገኘ፡፡ የአልቃድርን ውሻ መጨረሻ የተመለከተና ሕይወት የከፋችበት የመንደሩ ነዋሪ፡-
‹‹እሄዳለሁ እንጂ፤ እሄዳለሁ የትም፣
እንደአልቃድር ውሻ ስጠብቅ አልሞትም፡፡››..... ሲል አንጎራጎረ ይባላል፡፡

አዎ ትዕግስት እጅን አጣጥፎ መጠበቅ አይደለም፡፡ ትዕግስተኞች እየሞከሩ፣ እየተፍጨረጨሩ ነው የሚሹትን የሚጠብቁት፡፡ ትዕግስት የመጠበቅ ችሎታ አይደለም፡፡ ይልቁንስ እቅድን በትናንሽ ጊዜ ከፋፍሎ በትንሹ እያሳኩ ትልቁን ግብ ለማሳካት ጠንክሮ የመስራት ችሎታ ነው፡፡

ብዙዎቻችን የምንወደውንና የምንፈልገውን ነገር ያላገኘነው ነገርየውን ስለምንጠብቀው ብቻ ነው፡፡ አብዛኛዎቻችን ከቤተሰብ እንጠብቃለን፤ ከወዳጆቻችን እንጠብቃለን፤ ከአለቃችን እንጠብቃለን፤ ከመንግስት እንጠብቃለን፤ ከጊዜ እንጠብቃለን፤ ከአምላክ እንጠብቃለን፡፡ ጠባቂነት ተጠናውቶናል፡፡ ፍቅርንም፣ ደግነትንም፣ ቅን አሳቢነትንም፣ ሰላምንም የምንጠብቀው ከሌላ ነው፡፡ ምንም ነገር እንዲሰጠን (ጠብቆ ይነበብ) እንጂ እኛ ለመስጠት ፍቃደኛ አይደለንም፡፡ እኛ የምንፈልገውን ሌላውም እንደሚያስፈልገውም አንረዳም፡፡ ማህተመ ጋንዲ ‹‹ትዕግስት ማጣት በጦርነቱ መሸነፍ ነው (To lose patience is to lose battle)›› የሚሉን ለዚህ ነው፡፡ አላማህን የሚያደነቃቅፍ ሳንካ ሲገጥምህ ትዕግስት የምታጣ ከሆነ የኑሮህን ጦርነት እየተሸነፍክ ነው ማለታቸው ነው፡፡ እየተንገዳገዱ መራመድ፣ እየወደቁ መነሳት የሚቻለው ትዕግስት ሲኖር ነው፡፡ ትዕግስተኞች ከልፋታቸው የሚጠብቁ፤ ዘርተው ለማጨድ ግባቸውን እየተንከባከቡ፣ እቅዳቸውን ውሃ እያጠጡ ፍሬውን በተስፋ የሚጠባበቁ ምርጥ ገበሬዎች ናቸው፤ ጠባቂዎች ግን እንዲሁ በነፃ ከሰማይ መና የሚጠብቁ አደገኛ ቦዘኔዎች ናቸው፡፡

ወዳጄ ሆይ... መጠበቅ በራስ የሕይወት ጊዜ ላይ መተኛት ነው፡፡ የተኛ ከሞተ የሚሻለው መንቃት ስለሚችል ነው፡፡ አሁን ካልነቃህ፣ ዛሬ ራስህን ካልቀሰቀስክ የመኝታ ዘመንህ ይረዝማል፡፡ የመንቂያ ጊዜ አሁን ነው፡፡ ትክክለኛውን የለውጥ ጊዜ የምትጠብቅበት ትክክለኛው ሰዓት ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው፡፡ አሁን የነገ አልፎም ተርፎም የወደፊቱ የሕይወትህ ዕጣ ፋንታ መክፈቻ ቁልፍ ነው፡፡ ስለነገ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ስለወደፊቱ ለማወቅ አይቻልም፡፡ ነገ ጉልበት ሊከዳህ ይችላል፡፡ ከነገ ወዲያ በህይወትህ ላይ ምን እንደሚፈጠር የማወቅ ችሎታ የለህም፡፡ በእጅህ ያለው ውዱ ሀብትህ አሁን ነው፡፡ ነገን አትጠብቅ፡፡ ዛሬህን ተንከባክበህ ያዘውና ተጠቀምበት፡፡ ዛሬን በእጃቸው ያደረጉ ነገም፣ ወደፊትም የነሱ ነው፡፡ እየሰሩ መታገስ እንጂ ባዶ እጅ ሆኖ መጠበቅ የትም አያደርስህም፡፡ አርባአራት ነጥብ!

ቸር ትዕግስት! ደግ ጅማሬ!

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑሩ!

-----------------------------------
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ማግሠኞ ነሐሴ ፯ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም.

7 months ago

‹‹ፊት አቃጣሪ ነው፤ በጓዳ የሸሸግከውን በአደባባይ ያወጣዋል!››
(እ.ብ.ይ.)

ፊት ላይ የተፃፈ፤ በግምባር የተከተበ ብዙ ድብቅ ፅሁፍ አለ፡፡ ፅሁፉ የስሜት ዓይነትን፣ የጀርባ ማንነትን፣ አሁናዊ ሁኔታን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ግምባር መረጃ ሰጪ ነው፡፡ መልክ የትውስታ ማህደራችን ውስጥ ይቀመጣል፡፡ የአንድን ሰው ማንነት ስናስታውስ ቀድሞ የሚመጣልን ፊቱ ነው፡፡ በመቀጠልም አነጋገሩ፣ አካሄዱ፣ አሳሳቁ፣አስተሳሰቡ፣ ሁኔታው ሁሉ ይከተላል፡፡ ፊት ቀዳሚ ነው፡፡ ፊት ሲኮሳተር፣ ፊት ሲጨማደድ፣ ፊት ሲከሳና ሲጠቁር፣ ፊት ሲፈካና ሲበራ፣ ፊት ሲያብረቀርቅ የሰውየውን ውስጣዊ ሁኔታ ያሳብቃል፡፡ ፊት አቃጣሪ ነው በጓዳ የሸሸግከውን በአደባባይ ያወጣዋል፡፡ የዓኖችህ መንቀዥቀዥ የፊትህ መገርጣት አለመረጋጋትህንና ምቾት የነሳህ ነገር እንዳለ ያስረዳል፡፡ ንጉስ ሠለሞን ‹‹ጋለሞታ ሴት በዓይኗ ታስታውቃለች›› እንዲል የዓይንና የፊት ቅንብር የትየለሌ መረጃ ይሰጣል፡፡ ፊታችን የእኛነታችን ማሳያ ስክሪን ነው፡፡ አፎች ብቻ ሳይሆኑ ፊቶችም ይናገራሉ፡፡ መፅሐፍ ብቻ ሳይሆን ግንባርም ይነበባል፡፡

በርግጥ ፊት ሁሉንም በዝርዝር አያሳይም፡፡ የፊቱ ባለቤት የፊቱን ሁኔታ የሚቆጣጠር ከሆነ የተመልካቹን እይታ ሊያዛባው ይችላል፡፡ ፊት የሚያሳየው እንዳለው ሁሉ የሚደብቀውም አለው፡፡ ድፍኑ እንጂ ዝርዝሩ ሁሉ በ’”ፊት አይታይም፡፡ የሳቀ የሚመስል ፊት ሁሌ ሳቂታ ነው ማለት አይደለም፡፡ ያዘነም የሚመስል ፊት ሁሌም ያዘነ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ጥርስ ቢገጥጥም ፊት ላይስቅ ይችላል፡፡ አንዳንድ ፊት ተመልካቹን ሊያሳስት ይችላል፡፡ ጥቂት ፊት በተፈጥሮው ሰውየው ያልሆነውን ያንፀባርቃል፡፡ የተከፋ የሚመስል ነገር ግን ያልተከፋ፤ ክፉና ጨካኝ የሚመስል ነገር ግን ሩህሩህ የሆነ፤ የተደሰተ የሚመስል ነገር ግን ያልተደሰተ ብዙ ፊት አለ፡፡ ፊት አንድም የሆድን ያሳብቃል፤ አንድም የውስጥን ይደብቃል፤ አንድም ተፈጥሮን ይገልጣል፡፡ ፊትን መተንተን መቻል ትልቅ ጥበብ ይጠይቃል፡፡

ፊት ትንሽ ቢመስልም የመላ አካላችን ወኪል ነው፡፡ ሰዎች ቁርጭምጭሚታችንን አያስታውሱትም፤ አውራ ጣታችን ምን እንደሚመሰል ትኩረት አይሰጡም፤ ፊታችንን ግን በደንብ ይለዩታል፡፡ ፈጣሪ በስምንት ቢሊየን ሰዎች ፊት ላይ የተለያየ መልክ ስሎበታል፡፡ የእግዚአብሔር ስራ ግሩም ነው፡፡ የሰው ስራ ቢሆን ግን የስንቱ ፊት በተደጋገመና አንድ ዓይነት በሆነ ነበር፡፡ በመንታዎች እንኳን አምላክ የተለያየ የፊት ስዕል አስቀምጧል፡፡ አይደንቅም!? ፊት አንድም ፈጣሪ የሳለው ተንቀሳቃሽ ስዕል ነው፤ አንድም በስሜት ውጣውረድ እኛ ራሳችን በራሳችን ላይ የምንስለው የራሳችን ምስል ነው፡፡ ዊሊያም ሼክስፔር ‹‹እግዚአብሔር የሰጠህ አንድ ፊት ነው፡፡ አንተ ግን ሌላ ፊት አድርገኸዋል፡፡ (God has given you one face, and you make yourself another)›› የሚለው ለዚህ ነው፡፡ እውነተኛውን የሰውነት መልካችንን በኑሯችን፣ በአስተሳሰባችን የለወጥን እልፍ ነን፡፡

የሰው ፊት እሳት ነው፤ በቸገረህ ጊዜና በተዋረድክ ጊዜ ይገርፍሃል፡፡ የቸገረው ሰው ችግሩ አደባባይ ሲያወጣው የሰው ፊት ማየት ያስፈራዋል፡፡ ሌባ እጅ ከፍንጅ ሲያዝ መጀመሪያ የሚያስጨንቀው እስር ቤት መግባቱ ሳይሆን የሰው ፊት ማየቱ ነው፡፡ ፊት የክብርህና የሰውነትህ መገለጫ ነው፡፡ ፊት ሲነሱህ የምትበሽቀው፤ ፊታቸውን ሲያጨማድዱብህ የምትበግነው፣ ፊት ሲሰጡህ የምትደሰተው የፊት ሚስጥር ከሞራል፣ ከክብርና ከስብዕና ጋር የተገናኘ ስለሆነ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው ቀለብ ይቆርጥልህ ይመስል ምንም ሳታደርገው በፊቱ ይገላምጥሃል፡፡ ግልምጫ፣ ኮስታራነት ሰዎች ጥላቻቸውን የሚገልጹበት የፊት መሳሪያ ነው፡፡ ፊታቸውን በማየት ብቻ ሰዎች ላንተ የሚሰጡትን ቦታ ማወቅ ትችላለህ፡፡

ፊት ብቻውን በራሱ ብዙ መናገር ይችላል፡፡ የአፍና የዓይን እንቅስቃሴ ሲጨመር ደግሞ የፊት መረጃ የተሟላ ይሆናል፡፡ ዓይንና ፊት ሲግባቡ ለተመልካቹ የማያሳስት መረጃ ይሰጣሉ፡፡ አፍ ቢንቀዠቀዥ እንኳን ዓይንና ፊት ከተናበቡ ተመልካቹ በ’አፍ ከቀረበለት መረጃ ይልቅ ከ’ፊት ያገኘውን ያስቀድማል፡፡ አዳም ረታ ‹‹አፍ›› በተባለ መፅሐፉ ገፅ 149 ላይ ‹‹አፍ ምግብ ማስገቢያ ብቻ ሳይሆን የፊትን ቅጥ እንደሚያበጅ የገባኝ ያኔ ነው›› ያለው የፊት ውበት የአፍ፣ የዓይን፣ የፀጉር፣ የአፍንጫና የጆሮ ቅንብር ውጤት መሆኑንም ለማስገንዘብ ነው፡፡

ፕሮፌሰር ጄሮድ ፓሮት (Professor Gerrod Parrott) የተባለ የስነ-አዕምሮ ተመራማሪ የሰው ልጅ 134 ዓይነት ስሜቶች አሉት ይለናል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ዋና ዋና የሚባሉት መውደድ፣ መደሰት፣ ማዘን፣ መፍራት፣ መናደድና መደነቅ ናቸው፡፡ ሌሎቹ እንደጥርጣሬ፣ ቁጭት፣ ፀፀት ወዘተ የመሳሰሉት በነዚህ ስር የሚገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ታዲያ በመልክ የሚገለጡት ፊት ላይ ነው:: ሌላኛው የመስኩ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አልበርት መህራቢያን (Albert Mehrabian) ደግሞ የሰው ለሰው የስሜት ግንኙነት የሚካሄደው ሰባት በመቶ በሚናገራቸው ቃላት፣ 38 በመቶ በድምጽ አወጣጡ፣ 55 በመቶ ደግሞ በአካል እንቅስቃሴውና በፊቱ እንደሆነ በጥናቱ አረጋግጧል፡፡ ፊት ከቋንቋም በላይ ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ጥሩ አስተዋይ አንባቢ ወይም ልባም ተመልካች ከተገኘ እነዚህን ስሜቶች ከሰው ግንባር ላይ በቀላሉ ማንበብ ይችላል፡፡

ወዳጄ ሆይ... እንግሊዛዊው ቲያትረኛ ጀምስ ኤሊስ ‹‹ከአስቀያሚ አዕምሮ መልከ-ጥፉ ፊት ይሻላል (Better an ugly face than an ugly mind)›› እንዲል ህሊናህን ፉንጋ አታድርገው፡፡ ከሰው ጋር ለመኖር ብለህ ባለመንታ ፊት (Two-Faced) አትሁን፡፡ ለአንዱ ሌላ ፊት ለሌላው ሌላ ፊት የሚያሳዩ ሰዎች በራሳቸው የማይተማመኑና አቋም የሌላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ካህሊል ጂብራንም ‹‹ውበት በፊት ላይ ሳይሆን በልብ ውስጥ የሚገኝ ብርሃን ነው (Beauty is not in the face; Beauty is a light in the heart)›› የሚልህ ፊትህን የሚያፈካው ውስጣዊ አንተነትህ እንጂ የምትቀባባው ኮስሞቲክ አይደለም ለማለት ነው፡፡ ቆዳን መንከባከብ ደግ ነገር ነው፤ ነገር ግን ልብን፣ አዕምሮንና ውስጣዊ ሰላምን ከመንከባከብ በላይ አይሆንም፡፡ በቋሚነት የፊትህን ውበት የሚጠብቀው የሃሳብህ ቅባት ነው፡፡ በመልካም አስተሳሰብና በበጎ ስራ የወዛ ልብ ግንባርህንም ያስውባል፡፡

ከልብ ጋር የተስማማ ፊት!

ቸር ፊት! ደግ ፊት!

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑሩ!

----------------------------------
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
እሁድ ሠኔ ፪ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም.

7 months, 2 weeks ago

ምህዋረ ሃሳብ
"የአእምሮህን ብራና በሚጠቅም ነገር ሙላው"
ጸሐፊ:- እሸቱ ብሩ ይትባረክ
አንባቢ:- ተስፋዬ ማሞ

7 months, 2 weeks ago

የሁለት ዓለም ሰዎች ለአንዲት ሐገር!
(Two Men, Two Worlds)
(እ.ብ.ይ.)

የዛሬዋን አሜሪካ የሰሩ ሀለት ታላላቅ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የሰብዓዊ መብትንና እኩልነትን በሀገሪቱ ያስከበሩና ዘመናዊውን ዲሞክረሲያዊ ስርዓትን ያነበሩ ጀግኖች ናቸው፡፡ ሰዎቹ ከተለያየ አመለካከትና አስተሳሰብ የተገኙ የሁለት ዓለም ሰዎች ነበሩ፡፡ ሁለቱን ያገናኛቸው ደግሞ በሐገራቸው አሜሪካ የነበረው የጥቁርና የነጭ አድሏዊ ስርዓት ነው፡፡ ጊዜው በፈረንጆቹ 1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነበር፡፡ ወቅቱ አሜሪካ መስቀለኛ መንገድ ላይ የነበረችበት ወቅት ነበር፡፡ በሀገሪቱ ተቃውሞዎች እዚም እዚያም ፈንድተዋል፤ ፖሊሶች በአነፍናፊ ውሾቻቸው ጥቁር ሰላማዊ ሰልፈኞችን እስከማስነከስ የደረሱበት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በግልጽ የታየበት ጊዜ ነበር፡፡ ጆን ኦፍ ኬኔዲ የአሜሪካ ሰላሳ አምስተኛው ፕሬዝዳንት ነበሩ፡፡ በስልጣን የቆዩባቸው ጊዜ ሶስት ኣመታትን ያልደፈኑ ቢሆንም ስራቸው ግን ዘወትር ይወደሳል፡፡ አስራ ስድስተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን በባርነት የነበሩትን ጥቁር አሜሪካውያንን ከጌቶቻቸው ነፃ አውጥተዋል፡፡ ምንም እንኳን አብርሃም ሊንከን በዘመናቸው የነበረውን የባሪያ ንግድ ቢያስቆሙም የዘረኝነት ስርዓቱን ግን ሊያስወግዱት አልቻሉም፡፡ ከእሳቸው የስልጣን ዘመን መቶ ዓመታት በኋላ የመጡት ጆን ኦፍ ኬኔዲ ግን አሳክተውታል፡፡ ኬኔዲ በአጭር የፕሬዝዳንትነት የስልጣን ዘመናቸው እስከ ዛሬ ድረስ የሚያኮራና ወደፊትም ብዙ ዘመናትን የሚሻገር ገድልን ፈፅመዋል፡፡ በተለይ በአፍሪካና በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ሃያ ሰላሳ፣ አርባና ሃምሳ ዓመታትን ስልጣን ላይ ሙጭጭ ብለው የሚታይ ለውጥ ሳያመጡ፣ ህዝብና ሀገርን የኋሊት ቁልቁል የሚሰድዱ መሪዎች በነበሩበት ዘመን ሶስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የጥቁሮችን የእኩልነት ነፃነት ማወጅና በዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ ላይ ጉልህ ለውጥ ማምጣት መቻል ተዓምር ነው፡፡

በአንፃሩ ማርቲን ሉተር ኪንግ የጥቁሮችን ነፃነት ያመጡና ይሄን ድል ለመቀዳጀት ብዙ ዋጋ የከፈሉ ቀንደኛና ብርቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነበሩ፡፡ በ2017 ዓ.ም. ስቴቨን ሊቭንግስተን (Steven Levingston) በተባለ ጋዜጠኛና ፀሐፊ ‹‹Kennedy and King (The president, The pastor and the battle overe civili rights)›› በሚል ርዕስ ሁለቱ ሰዎችን በተመለከተ ዳጎስ ያለ መፅሐፍ ፅፏል፡፡ በዚህ መፅሐፍ መግቢያ ላይ ለአሁኒቷ አሜሪካ የህግ የበላይነት፣ የዲሞክራሲና የእኩልነት ስርዓት እንዲኖር ያደረገው ሰው ማርቲን ሉተር ኪንግ ነው ይለናል፡፡ የዚህ መፅሐፍ ፀሐፊ ማርቲን ሉተር የጆን ኤፍ ኬኔዲን ልብ ማሸነፉን ሲገልጽ ጆን ሌዊስ የተባለን የአርበኞች መብት ተከራካሪን ንግግር ተውሶ እንዲህ ይለናል፡- ‹‹ድንቁ ሰው ማርቲን ሉተር ኪንግ የጆን ኦፍ ኬኔዲን ህሊና ወጋው (The very being, the very presence, of Martin Luter King Jr. Pricked the conscience of John F. Kennedy)›› ይላል፡፡

መቼስ ሰላማዊ ትግሉ ቀላል እንዳልነበረ ግልጽ ነው፡፡ ማርቲን ሉተር የኬኔዲን ልብና አዕምሮን ለማሸነፍ ያልሄደበት ርቀት የለም፡፡ ጆን ኦፍ ኬኔዲ ስልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ ማርቲን ሉተር ኪንግ ፕሬዝዳንቱን በፊትለፊት ውይይትም ይሁን ባገኘው ሚዲያ ሲሞግታቸው ነበር፡፡ በስልክ፣ በጋዜጣ፣ በቴሌግራም ዘረኝነትን ይዋጉ ዘንድ መልዕክቶችን ይልክ ነበር፡፡ ጆን ኤፍ ኬኔዲ በመጀመሪያዎቹ ሁለት የስልጣን ዓመታቸው በጥቁሮች የሰብአዊ መብት ዙሪያ የነበራቸው አመለካከት ጥሩ ቢሆንም ለማስተካከል የሄዱበት ርቀት ያን ያህል አልነበረም፡፡ በሶስተኛው ዓመት መጀመሪያ ላይ ግን ሌላ ሰው ሆኑ፡፡ ማርቲን ሉተር የፕሬዝዳንቱን ለውጥ በተመለከተ ሲናገር፡- ‹‹ሁለት ኬኔዲዎችን አይቻለሁ፡፡ የመጀመሪያው ኬኔዲ የሰብዓዊ መብትን የሚደግፍ ነገር ግን በተግባር ለመስራት ያልደፈረ ነበር፤ ሁለተኛው ኬኔዲ ግን ከመደገፍ አልፎ በተግባር ለጭቁኖች ነፃነት የቆመ መሆኑን አይቻለው፡፡›› በማለት ደስታ በተቀላቀለው እንባ ስሜቱን አጋርቷል፡፡

ጆን ኤፍ ኬኔዲና ማርቲን ሉተር ኪንግ የሰላማዊ ተቃውሞን ሞዴል የቀረፁ ብርቱ ሰዎች ናቸው፡፡ ኪንግ ከፕሬዝዳንቱ ጋር የነበረውን የሃሳብ ልዩነት ሲናገር ‹‹ፕሬዝዳንቱን ማስተማር አስቸጋሪ ነገር ነው (It is a difficult thing to teach a president)›› እስከማለት ደርሶ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ፕሬዝዳንቱ በሃሳቡ አምነው የዘረኝነት ስርዓቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገንድሰው ጥለውታል፡፡ አጃኢብ አሜሪካ!

ይሄንን ጭብጥ ወደሐገራችን ስናመጣው የምንወስደው ቁምነገር ብዙ ነው፡፡ በመጀመሪያ የእኛ ሐገር የተቃዋሚነት ሚናው አይታወቅም፤ ሁለተኛ መንግስት የተቃዋሚዎችን ሃሳብ ሰምቶ በሃሳብ ከመሞገት ይልቅ ተቃዋሚዎቹን ወደእስር ቤት ማጋዝና የመሳሪያ ምላጭን መሳብ ይቀለዋል፡፡ ተቃውሟችንም ይሁን ድጋፋችን ጭፍንና ችኩል ድምዳሜ የተጠናወተው ነው፡፡ ኬዝ ባይ ኬዝ መንግስትን የሚሞግት ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ኢምንት ነው፡፡ የሚደገፈውን የሚደግፍ፣ የሚተቸውን የሚተች፣ የሚታረመውን እንዲታረም የሚሰራ አንድ ሁለት ብለን ከምንቆጥራቸው ፖለቲከኞች በስተቀር ብዙዎች ሁሉንም አውጋዦች ናቸው፡፡ ከመሪዎቻችንም ሆነ ከተቃዋሚዎችም ልክ ያልሆነ ነገር አለ፡፡ የተቃውሞ ፖለቲካው አልዘመነም፡፡ መንግስትም ለተቃዋሚዎች የሚሰጠው ቦታ የጠላትነት እንጂ ሐገርን በጋራ በማሳደግ ሂደት ላይ ሚና እንዳላቸው አያምንም፡፡ ‹‹እኔ ብቻ›› በሚል ያልተፃፈ መመሪያ ነው የሚመራው፡፡ መንግስትና ተቃዋሚዎች በሃሳብ ሙግት ተሸናንፈው ለሐገር የሚጠቅመውን ስርዓት ቢሰሩ ህዝባችንም ከስቃይና ከእንግልት፤ ከሞትና ከስደት ያርፍ ነበር፡፡ አላላውስ ያለንን የዘረኝነት ፖለቲካ ገንድሰው ቢጥሉ ለነሱም ስምና ዝና፤ ውዳሴና ሽልማት ለእኛም እረፍት ይሆነን ነበር፡፡ መቼ ይሆን የእኛዎቹ ማርቲን ሉተር ኪንግና ጆን ኦፍ ኬኔዲ የሚወለዱት???

ቸር ጊዜ!

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑሩ!

----------------------------------
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሠኞ ግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም.

9 months, 2 weeks ago

‹‹ማንም ሰው በአጋጣሚና በዕድል ብልህ አይሆንም››
(No man is wise by chance)
(እ.ብ.ይ.)

ብልህነት በዘርና በመወለድ አይገኝም፡፡ ብልህነት ልክ እንደመልክ ውበት ከላይ የሚሰጥም አይደለም፡፡ መልክ፣ ቁመና፣ ቁንጅና፣ ደምግባት አንተ የምትፈጥረው ሳይሆን በዕድልና በአጋጣሚ ወይም በስጦታ የምታገኘው ነው፡፡ መልክህን በቅባት ልታጎላው ትችላለህ እንጂ አትሰራውም፡፡ ለቁመናህ የሚስማማ ልብስ ለብሰህ ግርማ ሞገስህን ትጨምር ይሆናል እንጂ ቁመናህን ግን አንተ ልትፈጥረው አትችልም፡፡ አንዳንድ ሰዎች በመልካቸው ሲኮሩ ሳይ ይገርመኛል፡፡ ሰው እሱ ባልፈጠረውና ለፍቶ ባላገኘው ነገር መኩራት የለበትም፡፡ መኩራት ካለበት ራሱ ለፍቶና ጥሮ፤ ተምሮና ተመራምሮ ባገኘው ማንነትና ዕውቀት ነው መኩራት
ያለበት፡፡ ባልፈጠርከውና ለፍተህ ባላገኘኸው ነገር እንዴት ልትኮራ ትችላለህ? ለመልክህ ማማር፤ ለፊት ቁንጅናህ ያዋጣኸው ምንም ነገር የለምና፡፡

ብልህነትን በደም ከቤተሰብህ የምትወርሰው ሳይሆን አስበህ አሰላስለህ፣ ተፈትነህ፣ ወድቀህ፣ ተምረህ፣ ተመራምረህ የምታገኘው ነው፡፡ ብልህነት ብልጥነት አይደለም፡፡ ብልጥነት ውስጥ ስግብግብነት አለ፡፡ ብልጥነት መነሻ ሃሳቡ ራስወዳድነት ነው፡፡ ብልጥነት ምንም ዕውቀት አይፈልግም፡፡ ሁሉንም ነገር ለእኔ ጥቅም ይሁን ብሎ ለማግበስበስ መፈለግ ብቻ ነው፡፡ ደመነፍሳዊ ፍላጎት ዕውቀት ሳይሆን የሚሰጥ ነው፡፡ ስሜታዊ ፍላጎትን የሚጨምር ሃሳብ ቢኖርም እንደብልህነት ያለ ማሰብን የሚጠይቅ ሁኔታ ግን አይደለም፡፡ ብልህነት ውስጡ ቅንነት አለው፡፡ ቅንነት ዝም ብሎ አይመጣም፤ አሉታዊ ሃሳቦችን አሸንፎ በጎ ሃሳቦችን በመሳብ የሚገኝ ነው፡፡ ቅንነት ውስጥ ፍቅር አለ፤ ፍቅር ውስጥ መልካም አመለካከት አለ፡፡ ፍቅር ስንል ፆታዊ ፍቅርን አይደለም፤ ለሰው ልጅ ሁሉ በነፃ የሚሰጠውን እንጂ፡፡ ምክንያቱም ፆታዊ ፍቅር ውስጥ ሰጥቶ መቀበል አለ፡፡ ሰጥቶ መቀበል ደግሞ ቅልጥ ያለ ቢዝነስ ነው፡፡ መልካም አመለካከት ውስጥ ተፈትነው የወደቁና ያለፉ ሃሳቦች አሉ፡፡ ሃሳባቸውን የሚፈትኑ ሰዎች ትክክለኛውን አመለካከት ለመያዝ መንገድ የጀመሩ ናቸው፡፡

የብልጦች ህልውና ያለው በጅሎች መኖር ላይ ነው፡፡ ቂሎች ባይኖሩ ብልጦች አይኖሩም፡፡ ብልሆች ቀናዎች ናቸው ስንል ሞኞች ናቸው እያልን አይደለም፡፡ ቂልነት ከቅንነት ጋር አይሄድም፡፡ የዋህነት ከሞኝነት ጋር አይዛመድም፡፡ የዋህነት ውስጥ ዕውቀት ከሌለ ሞኝነት ይከተላል፡፡ ቅንነት የአስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ ብልህነት አዋቂነት ነው፡፡ ዕውቀቱ የብልጦችን በር እስከመዝጋት የሚያደርሰው ነው፡፡ ብልሆች በብልጦች አይሸወዱም፡፡ ምክንያቱም ብልጦችን በቀላሉ ያውቋቸዋል፡፡ ከነቃህ ለመሞኘት አትገደድም፡፡ ከብልጦች መልካም ነገር መጠበቅ ማለት ከኮባ ዛፍ ሙዝ እንደመጠበቅ ማለት ነው፡፡ የኮባ ዛፍና የሙዝ ዛፍ ይመሳሰላሉ፤ ነገር ግን ፍሬያቸው የተለያየ ነው፡፡

ብልሆች እንጂ ብልጦች ለፍቅር አይሆኑም፡፡ የብልጦች ፍቅር የሆነ ጊዜ ላይ የሚታጠፍ ፍቅር ነው፡፡ ብልጦች ያሉበት የሃሳብ ክርክር አይሰምርም፡፡ የእነሱ ሃሳብ በምንም ጉዳይ ላይ የበላይነታቸውን ማሳየት ነው፡፡ ዝቅ ብለው መማር አይችሉም፡፡ ሁሌም አናት ላይ ሆነው የበላይ መሆን ነው የሚሹት፡፡ ብልጦች መሪ ከሆኑ ሀገርን በእኩልነትና በፍትሐዊነት መምራት አይችሉም፡፡ ህገመንግስታቸው፣ ስትራተጂና ፖለሲዎቻቸው ሁሉ የራሳቸውን ጥቅም ለማስቀደም የሚፃፍ ነው፡፡ ብልጦች የሃይማኖት አባት መሆን አይቻላቸውም፡፡ ዕድል አግኝተው ቤተክርስቲያንን ከመሩ ምዕመኑን ሃይማኖት አልባ ያደርጋሉ፡፡ ይኸው ዛሬ የምናያቸው አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ለሆዳቸው ያደሩ አይደሉምን?

አዳም ረታ በመረቅ መፅሐፉ ገፅ 414 ላይ ‹‹የለቃቀሙትን ወሬ ይገጣጥሙትና - አመለካከት - ይሉታል›› እንዳለው ነው፡፡ ብልጦችም ዕውቀታቸው የሚያገኙት ከመንደር ወሬ ነው፡፡ በሰሚ ሰሚ የሚሰሙትን ወሬ መረጃ ይሉታል፡፡ ምንም ተያያዥነት የሌለውን መረጃ በግድ ያዛምዱና ዕውቀት ያደርጉታል፡፡ በዛ እውቀታቸው ተነስተው ሳያመዛዝኑ ሌሎችን በጅምላ ይፈርጃሉ፡፡

ብልጦች የሌሎችን ስኬት ሲያዩ ዓይናቸው ይቀላል፡፡ እነሱ ብቻ ስኬት በስኬት እንዲሆኑ ነው የሚፈልጉት፡፡ የሌሎች ማግኘት እነሱን ይረብሻል፡፡ ብልጦች ቁሰኞች ናቸው፡፡ በቁስ የበለጣቸው ጠላታቸው ነው፡፡ ብልጥነት ሁሌ ሌሎችን መብለጥ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የተበለጡ ሲመስላቸው ጨጓራቸው ይላጣል፡፡ ብልጦች ቅናትና ምቀኝነት መገለጫቸው ነው፡፡ ብልሆች ግን ሌሎች ስኬታማ እንዲሆኑ ያግዟቸዋል እንጂ አይመቀኙባቸውም፡፡ ምክንያቱም የብልሆች ስሪታቸው ቀና አመለካከት ነው፡፡ ብልሆች ፍፁሞች ናቸው እያልኩ አይደለም፡፡ ጥሩ ያልሆነ አመለካከት በአዕምሯቸው ሲገባ ወዲያውኑ ያስወግዱታል፡፡ ሲሳሰቱም ቶሎ ይፀፀታሉ፡፡ ስህተታቸውን ላለማድገም ከራሳቸው ጋር ይዋዋላሉ፡፡

ለዚህ ነው ሮማዊው ፋላስፋ ሴኔካ ‹‹ማንም ሰው በአጋጣሚና በዕድል ብልህ አይሆንም›› የሚለን፡፡ ብልህነት ሰውነትን ከመጎናፀፍ የሚገኝ ነው፡፡ ትክክለኛው ብልህነት ከትክክለኛ አመለካከት ነው የሚፀነሰው፡፡ ትክክለኛው አመለካከት ደግሞ ወደትክክለኛው ፍቅር ይመራል፡፡ ትክክለኛው ፍቅር ደግሞ ሃይማኖታዊም ይሁን ዓለማዊ ህግ አይገድበውም፡፡ ሁሉንም ሰው ያለዘርና ሃይማኖት፤ ሃብታም ደሃ ሳይል፤ ጤነኛ በሽተኛ ብሎ ሳይለይ፤ በእኩልነትና በርህራሄ መውደድ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው ደግ የሚሆነው በሰማይ ቤት መልካም ነገር እንዲገጥመው ነው፡፡ የነገን መልስ አስበህ የምትሰጠው ፍቅር ደግሞ እውነተኛ ፍቅር አይደለም፤ ትንሽዬ ንግድ ነው፡፡

ቸር ብልህነት!

ኢትዮጵያና ኢትጵያዊነት ለዘላለም ይኑሩ!

----------------------------------
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሠኞ መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም.

We recommend to visit

Welcome To Amharic films

Best Place To find Amharic Movies

አዳዲስ እና የድሮ አማርኛ ፊልሞችን እና አማርኛ ተከታታይ ድራማዎችን ለማግኝት ቻናላችንን Join ይበሉ ።
Share:- @Amharic_Films

ለማስታወቂያ - @Abusheymc & @Alpha6249

Buy ads: https://telega.io/c/Amharic_films

Last updated 1 год, 6 месяцев назад

ስለ መድፈኞቹ የሚወጡ መረጃዎች ለማግኘት የትም መሄድ አያስፈልግም

- የዝዉዉር ዜና
- የአሰልጣኞች አስተያየት
- የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
- ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት

ለማስታወቂያ ስራ  --> @Aymu_xo

Last updated 1 месяц назад

╔╦╦═╦╔╦═╦═╦═╗
║ እንኳን ደህና መጡ | |
╚══╩═╩═╩╩╩╩═╝
➟ እንኳን ወደ ትልቁ የሊቨርፑል ( መርሲሳይድ) ቻናል በደህና መጡ ።
◉ ስለ ሊቨርፑል ◉
🔴 ዝውውሮች

🔴 ውጤቶች

🔴 የጨዋታ ፕሮግራሞች

🔴 እንዲሁም የተጨዋቾች ግለ ታሪክ

🔴 ጨዋታዎችን በቀጥታ ወደናንተ የምናደርስ ይሆናል።

Owner:- @hackersolo0⭐️

Last updated 2 недели, 1 день назад