ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

Description
ፍልስፍና  እውነትን በመፈለግ- ሀሳዊ እምነቶችን በማጋለጥ እና ጭፍን አመለካከቶችን በጥበብ በመመርመር ወደ ላቀ አሰተሳሰብ ያሻግራል።

በዚህ ቻናል አለም ላይ ያሉ ፍልስፍናዎች ፤ ርዕዮት አለሞች ፤  ሀይማኖቶች እና አስተሳሰቦች በነፃነት ይዳሰሳሉ።
Advertising
We recommend to visit

Welcome To Amharic films

Best Place To find Amharic Movies

አዳዲስ እና የድሮ አማርኛ ፊልሞችን እና አማርኛ ተከታታይ ድራማዎችን ለማግኝት ቻናላችንን Join ይበሉ ።
Share:- @Amharic_Films

ለማስታወቂያ - @Abusheymc & @Alpha6249

Buy ads: https://telega.io/c/Amharic_films

Last updated 1 year, 5 months ago

ስለ መድፈኞቹ የሚወጡ መረጃዎች ለማግኘት የትም መሄድ አያስፈልግም

- የዝዉዉር ዜና
- የአሰልጣኞች አስተያየት
- የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
- ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት

ለማስታወቂያ ስራ  --> @MKHI7

Last updated 4 days, 15 hours ago

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

#ኢትዮጵያ

ያግኙን +251913134524

Last updated 1 week, 5 days ago

2 months, 1 week ago
***❤️***ስለ ፍቅር

❤️ስለ ፍቅር

"ፍቅር ያልገባበት ልብ ፦ ሙት የኖረበት ፣ በድን የከረመበት ጥቁር የሬሳ ሳጥን ነው።ያለ ፍቅር ያለፈ እድሜም የጥላቻ ብል የሚበላው የከንቱ ነው።ሕይወታችሁ በዘላለማዊ ጥልቀት ውስጥ ሕያው ሆና ትቅጥል ዘንድ ፍቅርን ሁኑ!"
ኦሾ

"ፍቅር እንደ ውቅያኖስ ማዕበል ብስለትን ተንተርሶ • በሰውነት የሚሰርፅ በልብ የሚቀረፅ በህሊና የሚታነፅ እንጂ እንደ መብረቅ ብልጭታ ታይቶ በቅፅበት ድርግም የሚል ሊሆን አይገባም"

ሲግመንድ ፍሮውድ

"ፍቅር የሁሉ ነገር መነሻና መድረሻ ነው ። አንድን ቤት ስንሰራ ሁሉም ነገር ካልተዋደደና በአንድ ካልተዋሃደ እኮ ቤቱ ይወድቃል እንጂ አይቆምም ። ይቺ መሬታችንንም ብንወሥድ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ብናኞች በፍቅር የመሰረቷት ህብር ናት ። እያንዳንዱ ግዙፍ ነገር ሁሉ ፍቅር የገለፀው የረቂቅ ብናኞች ህብር ነው።"
ያልታወቀ

"ፍቅር ከሚነደው የነፍስ ጉድጓድ በመመንጨት ምድሪቱን በብርሃን የሚሞላ አስማታዊ ጨረር ነው፡፡ፍቅር ሰው የአምላኩን ሀይል እንዲያይ የሚያስችለው ሰማያዊ ዕውቀት ነው፡፡"

ካህሊል ጂብራን

@Zephilosophy
@Zephilosophy

2 months, 1 week ago

የብቸኝነትና የባዶነትን ስሜት መጋፈጥ

በውስጣቸው ከራሳቸው ጋር ብቻቸውን የሆኑ፣ አዕምሮና ልባቸው ከብቸኝነት ስቃይ የፀዱ ሰዎች እውነተኞች ናቸው

አዝናኝና አስከፊ ነገር በሞላበት ዓለም ሁሉም ሰው ተሳታፊ ከመሆን ይልቅ ተመልካች መሆኑ አያስገርምምን? አብዛኞቻችን ትንሽ ነፃ ጊዜ ስናገኝ አንድ የሚያስደስተን ነገር እንፈልጋለን፡፡ ከተማ ውስጥ ከሆንን  ቴሌቪዥን ወይም ሞባይል እንከፍታለን ወይም ወሬ እንጀምራለን፤ አለዚያም መፅሀፍ ወይ መፅሄት እናነሳለን፡፡ የመደነቅ የመዝናናት፣ ራሳችንን የመርሳት የማያቋርጥ ፍላጐት አለን፣ ብቸኝነትን፣ ጓደኛ ማጣትን፣ ሳይረበሹ መቆየትን እንፈራለን፡፡ ሳናወራ ወይም ሳንዘፍን በፀጥታ በመስክ ወይም በጫካ ውስጥ እየተራመድን ስለ ራሳችንና በውስጣችን ስላለው ነገር የምናስተውል ጥቂቶቻችን ነን፡፡ አብዛኞቻችን እንዲህ ማድረግ የሚሳነን ስልቹዎች ስለሆንን ነው፤ በመማር ወይም በማስተማር፣ በቤት ጣጣ ወይም በስራ ተጠምደናል፡፡ ስለዚህም ነፃ ጊዜ ስናገኝ በቀላሉ ወይም በከባዱ መደነቅን እንፈልጋለን፡፡ እናወራለን ወይም ወደፊልም ቤት እንሄዳለን - ወይ ወደ አንዱ ሃይማኖት እንዞራለን። ሃይማኖትም አንደኛው ዓይነት ከስልቹነት የማምለጫ መንገድ ሆኗል፡፡

ይህን ሁሉ ተገንዝባችሁ እንደሆነ አላውቅም:: አብዛኞቹ ሰዎች በአንድ ነገር ተጠምደዋል - የተወሰኑ ቃላትን በመደጋገም፣ በዚህ ወይም በዚያ ጉዳይ በመስጋት - ምክንያቱም ከራሳቸው ጋር ብቻቸው መሆንን ስለፈሩ። የሚረብሻችሁ ነገር ሳይኖር ብቻችሁን ለመሆን ብትሞክሩ ምን ያህል ከራሳችሁ መውጣት እንደምትፈልጉና ማንነታችሁን ለመርሳት እንደምትሹ ትገነዘባላችሁ። ለዛም ነው ይህ ግዙፍ የደስታ መዋቅር፣ ፈጣን ረብሻ ስልጣኔ የምንለው ነገር አካል የሆነው:: አስተዋዮች ከሆናችሁ የዓለም ህዝቦች ይበልጥ እየተረበሹ እንደመጡ፣ ውስብስብና ዓለማዊ እየሆኑ እንደሄዱ ትመለከታላችሁ። የደስታው መብዛት፣ አዲስ የሚወጡ ፊልሞች መብዛት፣ የጋዜጦች በስፖርታዊ ጉዳዮች መሙላት - እነዚህ ሁሉ ያለማቋረጥ መደሰትን እንደምንፈልግ ያመለክታሉ፡፡ ውስጣዊ ባዶነት ስላለብን ግንኙነቶቻችንና ማህበራዊ ለውጦቻችን ከገዛ ራሳችን ለማምለጥ እንደ መሳሪያ እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ብቸኝነት የወረራቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ አስተውላችኋልን? ከብቸኝነታቸን ለማምለጥ ተሽቀርቅረን ፣ ግብዣ ወዳለበት እንሔዳለን፣ ቴሌቪዥን እናያለን፣ ሞባይል እንነካካለን፤ እናወራለን ወዘተ፡፡

ብቸኝነት ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? አንዳንዶቻችሁ ቃሉን ባታውቁም ስሜቱን በደንብ ታውቁት ይሆናል። ብቻችሁን ሽርሽር ስትወጡ ወይም ከሞባይል ስትላቀቁ ወይ ከሰው ጋር መነጋገር ስታቆሙ ይህ ሁሉ ነገር እንዴት አሰልችቷችሁ እንደነበር ትገነዘባላችሁ፡፡ ይህን ስሜት በደንብ ታውቁታላችሁ፣ ነገር ግን ለምን እንደሰለቻችሁ አታውቁም፤ ምን ብላችሁ ጠይቃችሁም አታውቁም:: ያን ስልቹነት በጥቂቱ ብትመረምሩት መንስኤው ብቸኝነት እንደሆነ ትገነዘባላችሁ፡፡ አብረን መሆን የምንፈልገው፣ መዝናናት የምንፈልገው፣ የሚረብሹንን መምህራን ወይም ምርጥ ፊልሞች የምንሻው ከብቸኝነታችን ለማምለጥ በማሰብ ነው፡፡ ውስጣዊ ብቸኝነት ሲሰማን የህይወት ተመልካች እንሆናለን ፤ ይህን ብቸኝነታችንን ተገንዝበን አልፈነው ስንሄድ ብቻ ተሳታፊዎች መሆን እንችላለን፡፡

ብዙ ሰዎች እንዴት በብቸኝነት መኖር እንደሚችሉ ስለማያውቁ ትዳር ይይዙና ሌላ አይነት ማህበራዊ ግንኙነት ይመሰርታሉ፡፡ ይህ ሲባል ግን አንድ ሰው ብቻውን መኖር አለበት አይደለም። መወደድ ስለፈለጋችሁ ብቻ የምታገቡ ከሆነ ወይም ሰልችቷችሁ ስራችሁን ራሳችሁን እንደ መርሻ ከተጠቀማችሁበት መላ ህይወታችሁ ረብሻን ፈላጊ እንደሆነ ትገነዘባላችሁ፡፡ ከዚህ ልዩ የብቸኝነት ፍርሃት በላይ የሚሆኑ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ፍርሃት በላይ ሲኮን እውነተኛው ሀብት ይገኛልና ሁሉም ሰው ፍርሃቱን መብለጥ አለበት፡፡

በብቸኝነትና ብቻን በመሆን መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡ አንዳንድ ወጣት ተማሪዎች ብቸኝነት ምን እንደሆነ አያውቁ ይሆናል፤ በዕድሜ የገፉት ግን ይህን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ብቸንነት ጨርሶ  የመቆረጥ፣ ያለምንም ምክንያት በድንገት የመፍራት ስሜት ነው። አእምሮ የሚጠጋው ነገር ሲያጣ፤ የባዶነቱን ስሜት የሚያስወግድለት ነገር ሲያጣ ይህ ፍርሃት ይሰማዋል። ይህ ብቸኝነት ነው፡፡

ብቻን መሆን - ግን ፍፁም የተለየ ነገር ነው፤ በብቸኝነት ውስጥ አልፋችሁ ስትገነዘቡት የሚመጣ የነፃነት ሁኔታ ነው። በዚያ የብቻ መሆን ሁኔታ ውስጥ ስትሆኑ በስነ - ልቡና ረገድ የማንም ጥገኛ አትሆኑም፡፡ ምክንያቱም ደስታን፣ ምቾትን መፈለጋችሁ ያቆማል፡፡ ይህን ጊዜ ብቻ አዕምሮ ሙሉ በሙሉ ብቻውን ይሆናል፤ ፈጣሪ ይሆናል፡፡

የብቸኝነትን፣ የባዶነትን ልዩ ስሜት የመጋፈጡን፣ ያለ መፍራቱን፣ ስሜቱ ሲመጣ ሞባይል ያለመጠቀሙን፤ በስራ ያለመጠመዱን ወይ ወደሲኒማ ቤት ያለመሮጡን፤ ከዚህ ይልቅ ስሜቱን የመመልከቱን፣ የመገንዘቡን ነገር መፍጠር ያለበት ትምህርት ነው:: ስጋትን የማያውቅ ወይም ያላወቀ ሰው የለም፡፡ ይህንን ስሜት በወሲብ፣ በሀይማኖት፣ በስራ፣ በመጠጥ፣ ግጥሞች በመፃፍ ወይም በልባችን የተማርናቸውን ጥቂት ቃላት በመደጋገም ወዘተ ለማምለጥ ስለምንሞክር ፈፅሞ አንገነዘበውም።

ስለዚህም የብቸኝነት ህመም ሲመጣባችሁ ትታችሁት ከመሮጥ ይልቅ ተጋፈጡት፡፡ ትታችሁት ከሮጣችሁ ፈፅሞ አትገነዘቡትም፤ ሁልጊዜ በየጥጋጥጉ ቆሞ ይጠብቃችኋል። ስሜቱን ተገንዝባችሁ አልፋችሁት ብትሄዱ ግን ማምለጡ፣ መዝናናቱ አስፈላጊ እንዳልሆነ - ትረዳላችሁ፤ አዕምሯችሁ የማይበላሽ፣ የማይነጥፍ ብልፅግናን ይጎናፀፋል፡፡ 

ይህ ሁሉ የትምህርት አካል ነው፡፡ በትምህርት ቤት ፈተና ለማለፍ ብቻ የተወሰኑ ትምህርቶችን የምትማሩ ከሆነ ትምህርት ራሱ ፣ ከብቸኝነት የማምለጫ መንገድ ይሆናል፡፡ ትንሽ ብታስቡበት ይገባችኋል።

በውስጣቸው ከራሳቸው ጋር ብቻቸውን የሆኑ፣ አዕምሮና ልባቸው ከብቸኝነት ስቃይ የፀዳ ሰዎች እውነተኞች ናቸው- ምክንያቱም እውነታውን ከራሳቸው ይረዳሉ፣ ጊዜ የማይወስነውን መቀበል ይችላሉ፡፡

ክሪሽና ሙርቲ

@Zephilosophy
@Zephilosophy

2 months, 2 weeks ago

"ምን ሆኛለሁ?"

የግድ ሊያነቡት የሚገባ የስነልቦና መፅሀፍ!

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስነልቦና ሳይንስ ተመርቃ የእርቅ ማዕድ ኘሮግራም መሰራች እንዲሁም እንመካከር የEBS ኘሮግራም ከዛም ባለፈ የአእምሮ ቁስለት (trauma) ላይ ለ17 አመታት የስነ ልቦና ሕክምና ስትሰጥ በቆየችው በ ትዕግስት ዋልተንጉስ እና ከዛዉ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትያትር ጥበባት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቶ በተለያዩ የመንግስትና የግል ኘሬሶች ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት እንዲሁም ሦስተኛው አይን፣ ሰዓት እላፊ፣ ሩብ ጉዳይ እና ከትዳር በላይ ትያትሮችን "ፍልስምና" በሚል ርዕስ 6 መፅሀፍትን በማሳተም ለተደራሲያን እንዲደርስ ባደረገው በቴዎድሮስ ተክለአረጋይ የተዘጋጀ እንደ ሀገር ፈር ቀዳጅ የሆነ መፅሀፍ ነው።

በታመመ ቤተሰብ ውስጥ ማደግ ፈተና ነው፡፡ ፍቅር፣ ትኩረት፣ መደመጥ የምግብ ያህል ይርበናል፡፡ ቤተሰብ ለእኛ ጊዜ የለውም፤ ምናልባት በአደንዛዠ እፅ ተይዟል፤ ቤት ውስጥ ቀን ተቀን የሚደበድብ ወንድም ወይም እህት፣ አክስት ወይም አጎት ይኖራሉ፡፡አንደኛው ወይም ሁለተኛው ወላጅ የአዕምሮ እክል ሊኖርበት ይችላል፡፡ እንደ ችግሩ አይነት ስሜትም ይቀያየራል፡፡ አሳዳጊ ራሱ የተሸከመው የልጅነት የአዕምሮ ቁስል ይኖረዋል፡፡ ወላጆች ከመጠን ባለፈ በሀይማኖት ውስጥ ጠልቆ በመቅረት የልጆችን ፍላጎት ከፈጣሪ አይበልጥም በማለት ረስቷል፡፡ እዚህ ቤተሰብ ውስጥ የልጅ አካላዊ እና ስሜታዊ ፍላጎቶች አይሟሉም ፡፡ በታመመ ቤተሰብ ውስጥ ቤተሰብ ለልጁ እንዴት ማሰብ፣ ፍላጎቶቹን ማስተናገድ፣ ከሰዎች ጋር መቀላቀል እንዳለበት ሚና ተሰጥቶታል፡፡ ልክ እንደ መድረክ ወይም ቴሌቪዥን ድራማ በዚሀ ቤተሰብ ውስጥ ሚና አለን፡፡ አንድ ድራማ ውስጥ የሚጫወት ተዋናይ የተሰጠውን ሚና በደንብ ካልተጫወተ ቦታውን ሊነጠቅ እንደሚችል ሁሉ በታመመ ቤተሰብ ውስጥም ልጆች ሚናቸውን ካልተወጡ ከባድ ችግር ይፈጠራል፡፡

ይህ መጽሐፍ ለየትኛውም አይነት የባህሪ አለመረጋጋት በራሱ መድሀኒት አይደለም። ችግሩን ማወቅ እና መረዳት ለችግሩ መድሀኒት እንዳለውና መድሀኒቱ የት እንደሚገኝ ነው የሚጠቁመው፡፡ ዛሬ ላይ የምናየው ችግር ከአሁን ይልቅ የትናንት የዞረ ድምር ውጤት እንደሆነ ማወቅ በራሱ ለመፍትሔው አንድ መንገድ ነው፡፡ ይህን መንገድ ነው መጽሐፉ የሚያሳየው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ማሳየት የፈለግነው ሰዎች ለገጠማቸው ችግር መፍትሔውን የማይገኝበት ቦታ ላይ እንዳይፈልጉ ለማስቻል ነው፡፡ የሰዎች ትናንትና ከዛሬያቸው ጋር እንዲታረቅ (ትናንትናቸው ከዛሬያቸው ጋር እንዲጨባበጥ) ለማስቻል ነው ።

ትዕግስት ዋልተንጉስ

ሁላችሁም ገዝታችሁ አንብቡት ታተርፋበታላቹ።

@Zephilosophy
@Zephilosophy

2 months, 2 weeks ago
2 months, 2 weeks ago

መላውን ዓለም ከመጨበጥ ይልቅ ራስን መጨበጥ የተሻለ ነው
ኦሾ

ሰው ሲወለድ እንደ ዘር ሆኖ ነው - እንደ አንድ እምቅ አቅም፡፡ ሲወለድ ልከኛ ሆኖ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በጣም ልዩ ነው - ምክንያቱም በመላው ህልውና ውስጥ ሰው ብቻ ነው አንድ አቅም ሆኖ የሚወለደው፤ ሌሎች እንስሳት ልከኛ ሆነው ነው የሚወለዱት፡፡

አንድ ውሻ ሲወለድ ውሻ ሆኖ ነውና መላ ህይወቱንም እንዲያ ሆኖ ይኖራል። አንድ አንበሳ ሲወለድ አንበሳ ሆኖ ነው፡፡ ሰው ሲወለድ ግን ሰው ሆኖ አይደለም፡፡ ሰው ሲወለድ እንደ ዘር ሆኖ ነው። ሰው ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ሰው የወደፊት ተስፋ አለው! ሌሎች እንስሳት ግን ተስፋ የላቸውም፡፡ ሁሉም እንስሳት ሲወለዱ በደመነፍስ ፍፁም ሆነው ነው፡፡ ሰው ብቸኛው ፍፁም ያልሆነ እንስሳ ነው። ስለዚህም በሰው ላይ እድገት፣ ዝግመተ - ለውጥ ይቻላል።

ትምህርት በእቅምና በልከኝነት መካከል ያለ ድልድይ ነው። ትምህርት በዘር መልክ ራሳችሁን እንድትሆኑ ያግዛችኋል፡፡ በተራ ትምህርት ቤቶች፣ በኮሌጆችና በዩኒቨርስቲዎች እየተሰጠ የሚገኘው ትምህርት አይደለም። በእነዚህ ተቋማት የምታገኙት ትምህርት ጥሩ ስራ፣ ጥሩ ገንዘብ እንድታገኙ የሚያደርጋችሁ ብቻ ነው:: እውነተኛ ትምህርት አይደለም፤ ህይወትን አይሰጣችሁም። በቃ የኑሮዋችሁን ደረጃ ከፍ ቢያደርገው ነው፤ ነገር ግን የተሻለ ኑሮ የተሻለ ህይወት አይደለም፤ ሁለቱ አንድ አይደሉም።

በዓለም የሚሰጠው ትምህርት ተብዬ ነገር ዳቦ እንድታገኙ ብቻ የሚያዘጋጃችሁ ነው። ኢየሱስ እንዳለው «ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም::>> ዩኒቨርሲቲዎቻችሁ ደግሞ ይህን ነው እያደረጉ ያሉት - በተሻለ፣ በቀለለ፣ በተመቸ፣ ጥረት፣ ድካም በሌለበት መንገድ ዳቦ እንድታገኙ ያግዛችኋል። ስራቸው በሙሉ እናንተን ዳቦና ቅቤ እንድታገኙ ማዘጋጀት ነው፡፡ ይህ አይነቱ ትምህርት በጣም፣ በጣም ኋላቀር ነው:: ለህይወት አያዘጋጃችሁም፡፡

ስለዚህም ብዙ ሮቦቶች ሲረማመዱ ታያላችሁ:: እንደ ተላላኪዎች፣ የጣቢያ ተቆጣጣሪዎች፣ ዋና ሰብሳቢዎች ብቃት አላቸው:: ፍፁማን ናቸው፣ ጥበበኞች ናቸው:: በጥልቀት ብትመለከቷቸው ግን ለማኞች እንጂ ሌላ ምንም እንዳልሆኑ ትረዳላችሁ፡፡ የህይወትን እንዲት ቅንጣት እንኳን አልቀመሱም፡፡ ህይወት ምን እንደሆነ፣ ፍቅር ምን እንደሆነ፣ ብርሃን ምን እንደሆነ አያውቁም፡፡ ስለ እግዚአብሄር ምንም አያውቁም፣ ህልውናን አልቀመሱም፣ እንዴት መዝፈን፣ መደነስ፣ መደሰት እንዳለባቸው አያውቁም:: የህይወትን ሰዋሰው የማያውቁ መሀይማን ናቸው። አዎ፣ ከሌሎች የበለጠ ያገኛሉ፤ ከሌሎች የበለጠ ብልጣ ብልጦች ናቸው፤ በስኬት መሰላል ከፍ ብለው ይወጣሉ - በውስጣቸው ግን ባዶ፣ ምስኪኖች ናቸው፡፡

ትምህርት ውስጣዊ ብልፅግናን ያጐናፅፋል፡፡ የበለጠ መረዳ መስጠት በጣም ኋላቀር የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ነው። ኋላ ቀር ነው ያልኩት በፍርሃት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው፤ ካልተማርኩ በህይወት መቆየት አልችልም፣ በሚለው አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው። ሗላቀር ነው ያልኩት በውስጡ ነውጥን ስላዘለ ነው፤ ውድድርን ያስተምራችሗል፣ ምኞታም ያደርጋችኋል። ሌላ ምንም ሳይሆን ሰዎች እርስ በርስ የሚጠላሉበት የውድድር ዓለም ለመፍጠር የሚደረግ ዝግጅት ነው።

ስለዚህም ዓለም የእብዶች መኖሪያ ሆናለች። በዚህ ሁኔታ ፍቅር ሊወጣ አልቻለም። አንዱ  የሌላኛውን ጉሮሮ በሚበጥስበት በዚህ ነውጠኛ፣ ምኞታም የውድድር ዓለም ውስጥ እንዴት ፍቅር ሊታይ ይችላል? ሗላ ቀር ነው ያልኩት «በደንብ ካልተማርኩ፣ በቂ ከለላ ካላገኘው፣ ደህና መረጃ ካልያዝኩ በህይወት ፈተና ውስጥ አሸናፊ አልሆን ይሆናል>> በሚል ፍራቻ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው። ህይወትን እንደ ትግል ብቻ ነው የሚመለከታት፡፡

እኔ ትምህርትን የማየው ህይወትን እንደ ትግል ሳይሆን እንደ ደስታ ሲቀርፅ ነው፡፡ ህይወት ውድድር ብቻ መሆን የለባትም፣ ደስታ ጭምር እንጂ፡፡ ትምህርት በዓለም ላይ ከሚገኙ ዘፈን፣ ዳንስ፣ ቅኔ፣ ሙዚቃ፣ ስዕል፤ ዛፎች፣ አዕዋፋት፣ ሰማይ፤ ፀሃይ፣ ጨረቃ እና ሌሎች ነገሮች በሙሉ ሊያዋህዳችሁ ይገባል፡፡

ትምህርት ራሳችሁን እንድትሆኑ ሊያዘጋጃችሁ ይገባል። አሁን ግን አስመሳዮች እንድትሆኑ እያዘጋጃችሁ ነው፤ ሌሎችን እንዴት መምሰል እንዳለባችሁ እያስተማራችሁ ነው፡፡ ይህ ትምህርት ማሳት ነው፡፡ ትክክለኛ ትምህርት ራሳችሁን በእውነተኛ መንገድ እንዴት እንደምትሆኑ ያስተምራችኋል። እናንተ የተለያችሁ ናችሁ። እናተን የሚመስል ማንም የለም ፡ ወደፊትም አይኖርም። ይህ እግዚአብሄር ያጐናፀፋችሁ ታላቅ በረከት ነው። ይህ የእናንተ ክብር ነው! ልዩ መሆን ነው፡፡ አስመሳይ አትሁኑ፤ የካርቦን ቅጂዎች አትሁኑ።

እናንተ ትምህርት የምትሉት ነገር ግን ይህን እያደረገ ነው፡፡ የካርቦን ቅጂዎችን ይፈጥራል፤ እውነተኛ መልካችሁን ያጠፋል። <<ትምህርት>> የሚለው ቃል ሁለት ትርጉሞች አሉት፤ ሁለቱም ደግሞ ውብ ናቸው። አንደኛው ትርጉሙ ተግባር ላይ ባይውልም በደንብ ይታወቃል- አንድ ነገር ከውስጣችሁ ማውጣት። <<ትምህርት» ማለት በውስጥ ያለን ማውጣት፣ ውሀን ከጉድጓድ እንደ ማውጣት አቅምን በተግባር ማውጣት ነው።

ይህ ግን አልተተገበረም፡፡ ከዚህ ይልቅ ነገሮች ወደ ውስጥ እንዲገቡ እንጂ እንዲወጡ አልተደረገም። ህብረተሰብ እና ታሪክ፣ ሳይንስ እና ሂሳብ ወደ ውስጣችሁ ያንቆረቁርላችኋል። እናም ፓሮቶች ትሆናላችሁ። ልክ እንደ ኮምፒዩተር ይጉሰጉሱባችኋል:: የእናንተ የትምህርት ተቋማት ነገሮች በጭንቅላቶቻችሁ ውስጥ የሚታጨቁባቸው ስፍራዎች ናቸው፡፡

እውነተኛ ትምህርት በውስጣችሁ የተደበቀውን (እግዚአብሔር በውስጣችሁ እንደ ሃብት ያስቀመጠውን) አውጥቶ፣ ገልጦ አንፀባራቂ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፡፡

ትምህርት ሌላም ትርጉም አለው:: ትምህርት (Education) የሚለው ቃል የመጣው Educare ከሚለው ቃል ነው:: ትርጉሙም ከጨለማ ወደ ብርሃን ማምጣት እንደማለት ነው፡፡ ከጨለማ ወደ ብርሃን ማምጣት በጣም አስፈላጊ ትርጉም አለው፡፡ ዮፓኒሻዶች እንዲህ ይላሉ «ጌታችን ሆይ፣ ከሃሰት ወደ እውነት ምራን፡፡ ጌታችን ሆይ፣ ከሞት ወደ ህይወት ምራን፡፡ ጌታችን ሆይ ከጨለማ ወደ ብርሃን ምራን፡፡» ይህ ነው «የትምህርት» ትክክለኛ ትርጉም፡- ከጨለማ ወደ ብርሃን።

ሰው ግን በጨለማ፣ ባለመንቃት ውስጥ እየኖረ ነው:: ሆኖም በብርሃን ምሉዕ መሆን ይቻላል፡፡ ነበልባሉ እዚያ አለ፡፡ ይሁንና መንበልበል፣ ወደ ውጭ መውጣት አለበት፡፡ ንቃት እዚያ አለ፤ ይሁን እንጂ መቀስቀስ አለበት:: ሁሉም ነገር ተሰጥቷችኋል! ስትወለዱ ይዛችሁት መጥታችኋል፡፡ ሰብአዊ አካል ስላለን ብቻ ሰው ነን ማለቱ ስህተት ነው፡፡ ለዘመናት ለብዙ መሳሳቶች መንስኤ የሆነው ይህ አስተሳሰብ ነው፡፡

ሰው ሲወለድ እንደ አንድ እድል፣ ሁኔታ ሆኖ ነው። ይህን የተጠቀሙበት ደግሞ እጅግ ጥቂቶች ብቻ ናቸው - ኢየሱስ፣ ቡድሀ፣ መሐመድ፣ ባሃውዲን። እውን ሰው የሆኑት እጅግ ጥቂቶች ናቸው- በብርሀን ሲመሉ የቀረ ጨለማ አይኖርም፣ በነፍስ ውስጥ የሚተርፍ አለመንቃት አይኖርም- ሁሉም ነገር ብርሃን ሲሆን፣ እናንተ ንቃትን ስትሆኑ...

ንቃት፣ ንቃት ብቻ፣ ንፁህ ንቃት... ይህ ያለው ብቻ ምሉዕ ይሆናል። ይሄን ጊዜ ህይወት ቡራኬ ትሆናለች።

ትምህርት ከጨለማ ወደ ብርሃን ይወስዳችኋል።

@Zephilosophy
@Zephilosophy

2 months, 3 weeks ago

.... ካለፈው የቀጠለ

ከስጋዊ አካል ወጥቶ ወደ ንቃተ አካል የሚደረግ ሽግግርም ከሁለንተናዊ ህልውና ጋር የመዋሀድ ሂደት ነው፡፡ ሂደቱ ወደ ውህደቱ መጨረሻ ሲደርስ ልክ እንደ አሊስ ተሞክሮ እኔነት ይጠፋና በሁሉም ፍጥረቶች ምንነት ውስጥ ዘልቀን እንገባና እንዋሀዳለን፤ ሁለንተና እንሆናለን፡፡ የ20 ዓመቷ ኮረዳ ጃኒት ከወንድ ጓደኛዋ ጋር ሆና የኮሲዮስኮን ተራራ ስትወጣ ድንገት ያጋጠማት ስጋ አልባ ጉዞ ይሄንኑ ሁለንተናዊነት የሚያረጋግጥ ነው፣

“ድንገት ከስጋዊ አካሌ ወጣሁና የአካባቢው አካል ሆንኩ፣ አካባቢውን ማየት ሳይሆን እኔ ራሴ ሙሉ በሙሉ የአካባቢው አካል ሆንኩ፤ ከመቅፅበት የዛፎች ቅርፊት፣ የቅጠሎች ህዋስ፣ የአየሩ ሞለክዩል ሆንኩ፤ በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር ሆንኩ፡፡ በፍቅር፣በሰላምና በደስታ ስሜቶችም ተሞልቼ ነበር፡፡”  (Jeanette's experience 12/05/05)

እግዚአብሔርም የዚህ ውህድ የመጨረሻ መልክ ነው፤ እንደዚህ ዓይነትን ውህድ ምስራቃውያን ሁለንተና (Nirvana, the ultimate) ይሉታል፡፡ እግዚአብሔር የሁሉ ነገሮች ምንነት (Essence)ውህድ ነው ሁለንተና፡፡ እኛ እንደምናስበው እግዚአብሔር ሰዋዊ (ንቁ) ብቻ ሳይሆን፣ እንስሳዊ፣ ቁሳዊ፣ እፅዋታዊ፣ ሰማያዊ (cosmic) ውህድ ያለበት ሁለንተና ነው፡፡ እግዚአብሔር ሁሉም ንቃቶች፣ ሁሉም ዓይኖች፣ ሁሉም ጆሮዎች፣ ሁሉም ስሜቶች፣ ሁሉም ውበቶች... ሁሉም ህጎች፣ ሁሉም ሥርዓቶች፤ ሁሉም ጥበቦች፣ሁሉም ሳይንሶች... ... ነው፡፡ ባሩክ ስፒኖዛም እንዳለው፣ ‹‹እግዚአብሔርና ተፈጥሮ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ሳይሆኑ፣ ፍፁም አንድ ነው፤ ተፈጥሮ የእግዚአብሔር ሌላኛው አካሉ ነው፡፡››

ኦሾ ይሄንን ሁለንተና (nirvana) ወይም 7ኛ አካል.. እንዲህ በማለት ይገልፀዋል፤

‹‹ፍፁም ነፃነትና ዕውነት የሚገለፅበት ከአምላክ ጋርም ውህደት የምንፈፅምበት አካል ነው፡፡ እዚህ ሁለንተና ላይ በሕልውናና በሕልውና አልባነት መካከል ልዩነት የለም ሁለንተና ምንምነትና የትምነት ነው፤ ልዩነት የላቸውም፡፡ ሁለንተና ምንምነትና የትምነት ስለሆነ የተከሰተ ነገር አይደለም፤ በቦታና በጊዜም የሚወሰንና የሚገለፅም አይደለም፤ በተወሰነ ህልውናነት ብቻ የሚገለጥም አይደለም፤ ሁለንተና ሁሉም ነገር የትምና መቼም ነው፡፡ ሁለንተና የትምነት መቼምነትና ምንምነት ስለሆነ የመንስዔ ውጤት ዓለምን ተሻግሮ ፍጥረት ከመጀመሩ በፊት ነገሮች በውህደት የነበሩበት የመጀመሪያው ክስተት ነው፡፡››

ከስጋዊ አካል የመውጣትን ክስተት (Astral projection) ከህልም ወይም ከሃሳብ መሰረቅ የተለየ ክስተት መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡

ህልም ስሜት አልባና የተዛባ ሊሆን ይችላል፣ የንቃተ አካል ጉዞ ግን ትክክለኛና በስሜት የተሞላ ነው፡፡

ህልም ስጋዊ አካል ውስጥ የሚፈጠር ሲሆን ንቃተ አካል ግን ከስጋዊ አካል ወጥቶ የሚሄድና ስጋዊ አካልን ማየትም ሆነ መንካት የሚችል ነው፡፡

ንቃተ አካል የነፃነት፣ የደህንነት፣ የላቀ ንቃት የሚሰማው ሲሆን መብረርና በጠጣር ነገሮች ውስጥ ሳይቀር ማለፍ የሚችል ሲሆን፤ ህልም ግን እነዚህ ስሜቶች አይሰሙትም፡፡

ንቃተ አካል ከስጋዊ አካል ሲወጣና ወደ ስጋዊ አካል ሲመለስ ያለውን ሁኔታ ይገነዘባል፤ ህልም ላይ ግን እነደዚህ ዓይነት ግንዛቤ የለም፡፡

የንቃተ አካል ጉዞ (astral projection) ማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል ሲሆን ክስተቱ ድንገተኛ (spontaneous) ወይም ሆን ተብሎ የሚፈፀም ሊሆን ይችላል፡፡ ማንኛውም ሰው የሕይወት ኃይሉን (bio-energy) በመቆጣጠር፣ ከአካላዊ ስሜቶች ነፃ በመሆን (አካልን በመርሳት)፣ አእምሮ ውስጥ የሚመላለሱ ሃሳቦችን ቀስ በቀስ በመግደል፣ የስጋ አልባ ጉዞን ለማጣጣም በራስ ላይ ጠንካራ ፍላጎት በመፍጠር፣ ቁርጠኛ በመሆንና ትኩረትን በከፍተኛ ደረጃ በማሰባሰብ ከስጋዊ አካል ወጥቶ የንቃተ ኣካል ጉዞ ማድረግ ይቻላል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በተሟሉበት ደረጃ ማንኛውም ግለሰብ ባላሰበው ቅጽበት ስጋ አልባ ጉዞ ሊያደርግ ይችላል፡፡

ስጋ አልባ የንቃተ አካል ጉዞ የተለያዩ ደረጃች ያሉት ሲሆን፣ ደረጃዎቹም የሚወሰኑት የሕይወት ኃይላችን ላይ በሚኖረን የበላይነት፣ የሕይወት ኃይላችን ባለው የጥራት መጠንና በአስተሳሰብ ደረጃዎች ሲሆን፣ እነዚህም ሁኔታዎች ከልምድ ጋር አብረው የሚያድጉ ናቸው፡፡

የንቃተ አካል ጉዞ አካላዊ የውስጥ ለውስጥ ምልከታንም (internal autoscopy) ሊያካትት ይችላል፡፡ ይሄ ምልከታ የራስን የውስጥ አካል አሠራር፣ አደረጃጀትና የርስበርስ መስተጋብር (ለምሳሌ የደም ዝውውርን) መመልከት የሚያስችል ነው፡፡ ስጋ አልባው ጉዞ የትንቢትና የኋላ ምልከታም አለው፤ ወደፊት ምን እንደሚከሰት፣ ወደኋላ ደግሞ ስጋዊ አካል ውስጥ ከመግባትህ በፊት እንዴትና ምን እንደነበርክ መመልከት ያስችልሃል፡፡

በስጋ አልባ ጉዞው ያገኘውን ልምድ ፅፎ በኢንተርኔት ያሠራጨው ሎሪ አን አልቫሬዝ፣

“ሽብርተኞች፣ በአሜሪካ መንትያ ህንፃዎች ላይ መስከረም 11፣ 2001 ላይ የፈፀሙትን አደጋ፣ በአሜሪካዋ ኮሎምቢያ መንኮራኩር ላይ የደረሰውን አደጋ፣ እናቴ ያጋጠማትን የቆዳ ካንሰር፣ የእህቴን የደም መዛባትና ሌሎች ጥቃቅን ድርጊቶችን ሁሉ አስቀድሜ አይቻለሁ፡፡” ይላል፡፡

ስጋ አልባው ጉዞ የርስበርስ ምልከታንም (extra pysical) መከወን ያስችላል፤ በዚህ የርስበርስ ግንኙነት ውስጥ እያንዳንዱ ንቃተ አካል ከሌሎች ስጋዊ ሰዎች ጋርም ሆነ ከሌሎች ስጋ አልባ አካሎች (ንቃተ አካሎች) ጋር ግንኙነት መፈጸም ይችላል፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ነቢያት ትንቢት መናገር፣ ማየትና ከመለኮት ጋር መገናኘት የቻሉት በስጋ አልባው የንቃተ አካል ጉዞ ነው፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ‹‹በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርኩ፣ በኋላዬም የመለኮትን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ፤›› ብሎ የፃፈውም ሆነ፣ ቅዱስ ጳውሎስ

“ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ፡፡ ሰውን በክርስቶስ አውቀዋለሁ፤ በስጋ እንደሆነ አላውቅም፤ እግዚአብሔር ያውቃል፡፡ እንዲህ ያለው ሰው ከ14 ዓመት በፊት እስከ 3ኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ፤ ወደ ገነት ተነጠቀ፤ ሰውም ቢናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ፡፡...›› 2ቆሮ.12 ÷ 2 – 4

ብሎ የፃፈው ሁሉ በስጋ አልባው የንቃተ አካል ጉዞ ወቅት የተፈፀመ ነው፡፡

@zephilosophy
@zephilosophy

2 months, 3 weeks ago

ከስጋ እስር ቤት መውጣት፤ መቼምነትና የትምነት

ምንጭ ፦ ፍልስፍና ፩
ደራሲ፦ ብሩህ አለምነህ

በትርፍ አንጀት በሽታ ክፉኛ የምትሰቃየው Laura H. ኦፕራሲዮን ለመሆን ማደንዘዣ ተሰጥቷት ራሷን ስታ ተኝታለች፡፡

“እንደ ድንገት ግን ኦፕራሲዮን በምደረግበት ክፍል ውስጥ ከስጋዊ አካሌ ወጥቼ ኮርኒሱ ስር ሆኜ ዶክተሮቹ የኔን አካል ኦፕራሲዮን ሲያደርጉት እመለከት ጀመር፡፡ ዶክተሮቹ የሚያወሩትን ነገር ሁሉ እሰማ ነበር፡፡ ዶክተሮቹ የሚያወሩት ስለአንዲት ስለሚያውቋት ሴት ነበር፡፡ እኔ ሊገባኝ ባይችልም ስለውስጥ አካሌም እያወሩ ነበር፡፡ ከማደንዘዣው ስነቃ ታዲያ ዶክተሮቹ ሲያወሩት የነበረውን ነገር ብነግራቸውም፣ እነሱ ግን ‹‹ሰዎች ማደንዘዣ ሲወስዱ አስቂኝ ህልሞችን ያያሉ፤›› ብለው ቢያስተባብሉም ንግግሬ እንደረበሻቸው ግን ፊታቸው ላይ ያስታውቃል፡፡ ከዚያ በኋላ ሊያናግሩኝ እንኳን አልፈለጉም፡፡››

ሁላችንም በስሜት ህዋሶቻችን መታሠራችንን፣ በስጋም መወሰናችንን ይታወቃል፡፡ አዲስ አበባ እየኖርን በተመሳሳይ ሰዓት አውሮፓ ላይ ምን እየተደረገ እንደሆነ አለማወቃችን በርግጥም በስጋ በመወሰናችን ነው፤እዚህ ቁጭ ብለን ከጀርባችን ምን እየተደረገ እንደሆነ አለማየታችን በርግጥም ንቃታችን ስጋችን የቆመበትን ስፍራ ማዕከል አድርጎ የስሜት ህዋሶቻችን የተዘረጉበት አድማስ ድረስ ያህል ብቻ የተወሰነ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡

ንቃታችን በስሜት ህዋሶቻችን አድማስ ያህል የተወሰነ ቢሆንም ይሄ ግን የመጨረሻው እውነት አይደለም፡፡ ከስጋ ባርነት ነፃ የሚወጣ፣ ከስሜት ህዋሶቻችንም ድንበር የሚዘል ሌላ ንቃተ አካል እንዳለን የአንዳንድ ሰዎች ተደጋጋሚ ተሞክሮ ያሳየናል፡፡ ይህ ንቃተ አካል፣ ስጋዊ አካላችንና የስሜት ህዋሶቻችን ያሉባቸውን ድክመቶችና ውስንነቶች ሁሉ አካክሶ የሚገኝ ነው፡፡ በጊዜ አይወሰንም፤ ያለፈውን፣ የአሁኑንና የወደፊቱን ማየት ይችላል፡፡ በጠጣርና ብርሃን ማለፍ በማይችልባቸው ነገሮች ውስጥ ሁሉ በንቃት ማለፍ ይችላል፡፡ ከላይ የቀረበው የሎራ ተሞክሮም ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡

ስጋዊ አካል ከንቃተ አካል የተለየ ነው፡፡ ንቃተ አካል ስጋዊ አካል ውስጥ ገብቶ የሚኖር ቢሆንም በራሱም ግን ከቁሳዊ ባሕርይ በላይ የሆነ የተለየ ህልውና አለው፡፡ ስጋዊ አካል ቁሳዊ የሆነና በስሜት ህዋሳቶቹ አማካኝነት ከቁሳዊው ዓለም ጋር የሚግባባ ሲሆን፣ ንቃተ አካል ግን ስጋዊ ኣካልን እንደ ልብስ የሚጠቀምና ቁሳዊ ያልሆነ ህልውና ነው፡፡ ንቃተ አካል ከስጋዊ አካል ወጥቶ ሲሄድ ስጋዊ አካል በድን ሆኖ ይቆያል፤ በዚህ ወቅት በስጋዊ አካል ፈንታ ንቃተ አካላችን ብዙ ነገሮችን እየተከታተለ ይቆያል፡፡

ይህ ንቃተ አካል ነፍስ ብለን የምንጠራው ነገር ይሁን፣ አይሁን አላውቅም፡፡ ፕሌቶ ግን ከዛሬ 2300 ዓመት በፊ ስለ ነፍስ እንዲህ ብሎ ነበር፤

"የሰው ጥንተ ተፈጥሮ (ምንነት) ያለው ነፍሱ ላይ ነው፡፡ ነፍስ በስጋ ከመታሰሯ በፊት የራሷ ሕልውና የነበራትና ከስጋ መሞት በኋላም ሕያው ሆና የምትኖር ናት፡፡”

ይቺ ነፍስ እንደፈለገች ስጋችን ውስጥ ግብት ውጥት የምትል አይደለችም፡፡ አሁን እያወራን ያለነው ግን ሞት የሚባለውን ክስተት ሳያስከትል ወደስጋዊ አካላችን ግብት ውጥት ስለሚለው ንቃተ አካል ነው፡፡

እንደዚህ ዓይነት ክስተት በሩቅ ምሥራቅ ሀገሮች መንፈሳዊ ሕይወት(ተመስጦ) ውስጥ የተለመደ ቢሆንም በምዕራባውያን ሳይንቲስቶችም በተደጋጋሚ የተስተዋለ ክስተት ነው፡፡ መቀመጫውን ለንደን ያደረገውና በዚሁ በንቃተ አካል ላይ ትኩረት ያደረገው International Academy of Consciousness (IAC) የተባለው ተቋም አንድ ጥናት አድርጎ ነበር፡፡ የጥናቱ ዋነኛ ዓላማ ንቃተ አካል ከስጋዊ አካል ተለይቶ መሰብሰብ በሚችላቸው መረጃዎች ላይና መረጃዎቹንም ወደ ስጋዊ አካል (አእምሮ) የሚተላለፍባቸውን ሂደቶች ማጥናት ነው፡፡ አምስት የተለያዩ ምልክቶች ተዘጋጅተው ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ አሜሪካና እንግሊዝ እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡ ሙከራው ምን ያህል አዋጭ እንደሆነና የውጤቱን አስተማማኝነትም የሚያረጋግጡ ኦዲተሮችና ዳኞች ሁሉ ተሳትፈዋል፡፡

የጥናቱ ውጤት በ2002 ኒዮርክ በ3ኛው ዓለማቀፍ Projectiology ጉባኤ ላይ ይፋ ሆኗል፡፡ ለሙከራው ፈቃደኛ ሆነው ከተሳተፉ 105 ሰዎች መካከል 52ቱ 93 የተለያዩ መረጃዎችን ከስጋዊ አካላቸው በመውጣት በንቃተ አካላቸው መሰብሰብና ሪፖርት ማድረግ ችለዋል፡፡ በጥናቱ መሠረት ንቃተ አካል የነገሮችን ቅርፅና ቀለማት ኬሌሎች መረጃዎች በተሻለና በቀላሉ መለየት ይችላል፡፡

“ከስጋዊ አካሌ ውጭ ነበርኩ፤ ሁሉም ነገር አስደስቶኛል፡፡ በስጋ አልባው ንቃተ አካል ውስጥ ሆኜ መጀመሪያ የተገነዘብኩት ነገር የንቃተ ህሊናን በሁሉም ስፍራ የመገኘት እውነታ ነው፡፡ ሁሉንም ነገሮች በሁሉም ደረጃ መመልከት ችያለሁ፤ ሌላው ይቅርና ወደ ቢራቢሮነት ለመፈልፈል የተዘጋጀው ዕጭ (caterpillar) የሚሰማው ስሜት ሳይቀር ተሰምቶኛል፡፡ ሕይወት በሁሉም ደረጃ እኩል እንደሆነና በሁሉም ፍጥረቶች ውስጥ ያለው የንቃት ደረጃ ተመሳሳይ እንደሆነ ተመልክቻለሁ፤ ዋጋቸውም ከእኛ ከሰዎች ያላነሰና የከበረ ነው፡፡ የሁሉም ፍጥረቶች ምንነት ሞለኪዩል ጀምሮ የፍጥረት ተሰምቶኛል፤ከእያንዳንዷ የትየለሌነት፣ አስገራሚነትና ውበት ተሰምቶኛል፡፡ ከዚያም ወደ ህዋ ተጓዝኩ፤ በዚያም ማለቂያ የሌለው አውታር (dimension) እና ማቆሚያ የሌለው ፍጥረት እንዳለ ተመልክቻለሁ፡፡ በዚያ ከምናስበው በላይ የሆኑ እጅግ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡” (Aliece's Out of Body Experience associated with nitrous oxide at Dentist office, reported on 15 July 2007)

ይሄ የአሊስ ተሞክሮ ንቃተ አካል ከስጋዊ አካል ሲወጣ ወደ ሁለንተናነት ሊያድግና ሊዋሀድ እንደሚችል የሚያስገነዝበን አጋጣሚ ነው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ነገሮችና ክስተቶች ሁሉ እርስበርስ የተቆላለፈ መስተጋብር እንዳላቸው ሁላችንም የምናውቅ ቢሆንም፤ ይኼኛው ተሞክሮ ግን የፍጥረታትን ሁሉ የአንድነት ህልውና የሚያስገነዝበን ነው፡፡ አሊስ በዚህ ተሞክሮዋ የጠፈርን ሥርዓት፣ህግና ሚዛን ተገንዝባለች፤ እሷ ራሷም የዚህ ሥርዓት አካል እንደሆነች ተገንዝባለች፡፡ ኦሾ፤ ሰው ሰባት አካሎች እንዳሉት ይጠቅስና ስለ 6ኛው ፅንፈዓለማዊ አካል (cosmic body) ሲናገር እንዲህ ይላል፤

“እስከ 5ኛው አካል (physical body, etheric (emotion) body, astral body, mental & spiritual body) ድረስ ከ‹‹እኔነት›› ማዕከል መላቀቅ አይቻልም፤ ከ5ኛው ወደ 6ኛው አካል (cosmic body) ስንሸጋገር ግን የእኔነት ማዕከል ይጠፋል፤ ልዩነት ይጠፋል፤ ወሰን አልባና በሁሉም ነገር ውስጥ በንቃት የምትገኙ ውህድ ሁለንተና ትሆናላችሁ፡፡"

ይሄንን ሁለንተናዊ የሆነ ህልውና እንደ ውቅያኖስ ውሰዱት፤ ውቅያኖሱ በውስጡ የተናጠል ህልውና ያላቸው የሚመስሉ፣ ሆኖም ግን የእሱ አካል የሆኑ ብዙ ዓይነት ፍጥረቶችን ይዟል፡፡ በየአካባቢው ያሉ ወንዞች፣ ሀይቆች፣ ባህሮች፣ ዝናብና በሁሉም ነገር ውስጥ ያለው እርጥበት ሁሉ የውቅያኖሱ አካል ናቸው፡፡ እነዚህ በዓይነትና በህልውና የተለያዩ የሚመስሉ የውቅያኖሱ ክፍሎች ሁሉ ወደ ውቅያኖሱ ሲገቡ ፍፁም ውህድና አንድ ይሆናሉ፤ የህልውናቸው ልዩነት ይጠፋና ሁለንተናዊ የሆነ አንድ ህልውና ውስጥ ይጠቃለላሉ፡፡

ይቀጥላል

@zephilosophy
@zephilosophy

2 months, 4 weeks ago

የኛ ውብ ምድር

#ምድር የማንም ዘር ወይም ሀገር ንብረት አይደለችም። ይህች ምድር የሁላችንም ናት ግን የህይወትን ሃይል ጉልበት፣ የአዕምሮ ብቃታችን ለደስታችን ከመጠቀም ፈንታ እኛ በተራ ነገር ሞትን እያመረትን ነው ያለነው። የህይወት ብቸኛው ስራ ሞትን ማምረት አየመሰለ መጥቷል፤ ይህ ደግሞ ለምድራችን እንደማይበጃት ታሪክን የኃሊት መመልከት ብቻ በቂ ነው።

“ዩሪ ጋጋሪን የመጀመርያው ሩሲያዊ የጠፈር ተመራማሪ ጨረቃን በቅርብ ርቀት መመልከት እንዲሁም ምድርን ከርቀት መመልከት የቻለ የመጀመርያ ሰው ነው ከጠፈር ሲመለስ እንደተናገረው ከሆነ በጣም የሚገርመው ነገር ቢኖር የምድርን አንዱን ክፍል ሩሲያ ሌላውን ቻይና ብሎ ለያይቶ መመልከት አለመቻሉን ነው። ወደ ሞስኮ እንደ ተመለሰ ጋዜጠኞች ጠየቁት ጠፈር ላይ ሆነህ ምድርን ስትመለከታት መጀመርያ አእምሮህ ላይ የመጣው ሀሳብ ምንድን ነበር?” እሱም እንዲህ አለ ይቅርታ አድርጉልኝና #ሩሲያዊ መሆኔን በፍፀም ረስቼው ነበር እናም እንዲህ አልኩ ኦ የኔ ውብ ምድር የመጀመርያ ወደ አእምሮዬ የመጡት ቃላት እነዚህ ነበሩ እናም ዩሪ እንዳለው በርግጥም ምድራችን የኛ ውብ ምድር ናት።

ኦሾ

@zephilosophy

3 months ago

LIMITLESS
By JIM KWIK

UPGRADE YOUR BRAIN,LEARN ANYTHING FASTER AND UNLOCK YOUR EXCEPTIONAL LIFE

@Zephilosophy
@Zephilosophy

3 months ago

ቀላሉን ነገር አታካብደው
ደራሲ:- ዶክትር ሪቻርድ ካርሰን
ትርጉም:- ዶክትር ዮናስ ላቀው

@zephilosophy
@zephilosophy

We recommend to visit

Welcome To Amharic films

Best Place To find Amharic Movies

አዳዲስ እና የድሮ አማርኛ ፊልሞችን እና አማርኛ ተከታታይ ድራማዎችን ለማግኝት ቻናላችንን Join ይበሉ ።
Share:- @Amharic_Films

ለማስታወቂያ - @Abusheymc & @Alpha6249

Buy ads: https://telega.io/c/Amharic_films

Last updated 1 year, 5 months ago

ስለ መድፈኞቹ የሚወጡ መረጃዎች ለማግኘት የትም መሄድ አያስፈልግም

- የዝዉዉር ዜና
- የአሰልጣኞች አስተያየት
- የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
- ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት

ለማስታወቂያ ስራ  --> @MKHI7

Last updated 4 days, 15 hours ago

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

#ኢትዮጵያ

ያግኙን +251913134524

Last updated 1 week, 5 days ago