★ሰውን በማዝናናት የብቃት ማረጋገጫ ያለው ብቸኛው ቻናል ሁሌም Telegram ላይ በጥበብ ደምቀን እናሸበርቃለን
? Contact us, @Modenyazbot
»የተመረጡ እና ማንም ያላያቸው የአማሪኛ ቀልዶች እንዲሁም የሚያስደንቁ ስዕሎችንና ቪዲዮ ያገኛሉ።
° ° [ ሙድ እንያዝ በእኛ የአራዶች መዝናኛ ] ° °
° ° Creator @Teke_Man ° °
Last updated 1 month, 2 weeks ago
☕ ስለ ኢትዮጲያ ቡና የሚወጡ ወቅታዊና ትክክለኛ የክለቡ መረጃዎች አዚህ ያገኛሉ!
➪የዝዉዉር ዜና
☞የአሰልጣኞች አስተያየት
➪ጎሎች እና ቪዲዮዎች
☞የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
➪ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት ከየስታድየሙ !
➡መወያያ ግሩፓችን @Ethiopia_coffee_Sc
?ሀሳብ ወይም አስተያየት ካሎት
በዚህ ? @EthiopianCoffeeScBot ✍
BOT ማድረስ ይችላሉ!
Last updated 6 months, 3 weeks ago
ማንኛውንም የማስታወቂያ ስራ ለማሰራት የምትፈልጉ(only promotion) inbox @Eyyiba
ሌሎች ጥያቄዎችን ለማድረስ
@Ethiodailyvacbot
Last updated 3 weeks ago
"#እባክህን_ከእሳቱ_ላይ_አትውረድ"
አንድ ወንድም አባ ጴሜንን "ምከረኝ" ብሎ ጠየቀው። አባ ጴሜንም "ድስት በእሳት ላይ እያለ ምንም አይነት ተባይ ሊቀርበውና ሊያበላሸው አይችልም። ከእሳት ወጥቶ ሲቀዘቅዝ ግን ነፍሳት ሁሉ ለመግባትና ለማበላሸት ይቻላቸዋል። ክርስቲያንም ከመንፈሳዊ ተግባር ካልራቀ ጠላት የድቀት ምክንያት አያገኝበትም" አለው።
ወዳጄ ሆይ ሕይወት ቀዝቅዛብሃለችን? ከእሳቱ ወደ መሬት ወርደህ በርደሃልን? የሕያውነትህ ሙቀት እሳት በማጣት ተንዘፍዝፏልን? ድስት የተባለ ሰውነትህ ክረምት የሚያህል ጉድን ተሸክሟልን? ዙሪያ ገባህ ፀሐይ እንደማትወጣበት ምእራብ ጨለማን የሚጠራ ሆኗልን? ማንነትህ እሳት እንዳጣ ምግብ ጥቃቅን ነፍሳት በተባሉ ኃጢአቶች (ቁጣ፣ ቸልተኛነት፣ ስስት፣ አልታዘዝ ባይነት፣ ጭንቀት፣ ሁሉን የመናቅ ስሜት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ...) ተወርሮ፣ መዓዛ ቅድስና ተለይቶት እጅ እጅ ብሏልን? ሞቅ የሚያደርገው አጥቶ በዓለማዊነት ሻግቷልን? የተባዮች መጫወቻ፣ የተውሳኮች መቀለጃ ሆኗልን? እንግዲያውስ በቶሎ ወደ እሳቱ ውጣ፡፡
ወዳጄ ሆይ ሃይማኖት በተባለችና ከሰማይ በወረደች ልዩ እሳት (ሉቃ.12፥49) ላይ ተቀምጠህ የድስትነትህን ሙቀት መልስ፡፡ እምነት፣ ተስፋና ፍቅር (1ቆሮ.13፥13) በተባሉ ሦስት ጉልቻዎች ላይ በምቾት ተጥደህ የሕይወትህን የኃጢአት ብርድ አስወግድ፡፡ ንስሐ በተባለች ነበልባል ውበትነት የክረምትህን ጽልመት በምስራቃዊ በጋነት ድል ንሳ፡፡ በሥጋ ወደሙ ፍምነት ድስት የተባለ ሰውነትህን በከዊነ እሳትነት ቀድስ፡፡ እባክህን በቶሎ ወደ እሳቱ ውጣ፡፡
ሃይማኖት የተባለ እሳትን ተባይ አይቀርበውም፡፡ እምነት ተስፋና ፍቅር የተሰኙ ጉልቻዎችን ተውሳኮች ሽቅብ አይወጡአቸውም፡፡ የነበልባለ ንስሐን ብርሃንና ሙቀት ነፍሳተ ጽልመት መቋቋም አይችሉም፡፡ ስለዚህ በእሳቱ ላይ እስካለህ ድረስ (በመንፈሳዊ ተግባራት እስከጠነከርክ ድረስ) አንተ ሁሌም ከተባይና ከነፍሳት ብልሽት (ከአጋንንት) የራቅክ ነህ፡፡
ወዳጄ እባክህን ከእሳቱ ላይ አትውረድ፡፡ እሳቱ በደንብ ይነድ ዘንድ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት የተባሉ እንጨቶችንና ምጽዋት የተባለ ጋዝን መጨመርህን እንዳትዘነጋ፡፡ እንዲህ ከሆነ ዘንዳ ድስትነት ሁሌም የሞቀ ይሆናል፡፡ እጅ እጅ ከማለት፣ ከመሻገትና የተባይ መጫወቻ ከመሆን ትድናለህ፡፡
ወዳጄ ሆይ እባክህን ከእሳቱ ላይ አይትውረድ፡፡
በኃጢአት "እጅ እጅ '' ከማለትና በበደል ከመሻገት እግዚአብሔር ይሠውረን! አሜን!
(ሕሊና በለጠ ዘኆኅተብርሃን)
@beteafework @beteafework
@beteafework @beteafework
@beteafework @beteafework
ጥር12
እንኳን ቃና ዘገሊላ ታላቅ ክብር በዓል በሰላም አደርሳችሁ አደርሰን አሜን
#ቃና ዘገሊላ ምንድነው?
ቃና ዘገሊላ በቀጥታ ትርጉም የገሊላዋ ቃና ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት(ጥር 12) ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ ይህ በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ በድምቀት የሚከበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዳራ ያለው በዓል ነው፡፡ በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ሀገር ክፍል በምትሆን ቃና በተባለችው ቦታ በፈፀመው ተአምር መነሻነት ነው፡፡ የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ ወይም ታሪኩ የተፈፀመው የካቲት 23 ቀን ነው፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የየካቲቱን በዓል ወደ ጥር 12 አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማስተሣሠር ለማስኬድ ነው፡፡ በመሆኑም የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር 12 ቀን ይከበራል፡፡
በቃና ዘገሊላ ምን ተፈፀመ? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና በተደረገ ሠርግ ላይ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ተገኝቶ ነበር፡፡ ‹‹ወሀለወት ህየ እሙ ለእግዚእ ኢየሱስ›› ‹‹የጌታ የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች›› እንዳለ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ (ዮሐ 2÷1) እመቤታችን ለሠርገኞቹ ዘመድ ነበረችና ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሰርጉ ላይ ታድማ ነበር፡፡ እናትን ጠርቶ ልጅን መተው ሥርዓት ስላልሆነ፤ በተጨማሪ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ከጌታ ጋር በሰርጉ ታድመዋል፡፡ ይህም መምህርን ጠርቶ ደቀ መዛሙርቱን መተው ሥርዓት ስላልሆነ (ተገቢ ስላልሆነ) ነው፡፡ የሠርጉ ሥነ-ሥርዓት በሠመረ ባማረ ሁኔታ እየተከናወነ ሳለ ድንገት የወይን ጠጅ አለቀ፡፡ አስተናባሪዎቹ በጭንቀት ባሕር ሰጥመው ምን እንደሚያደርጉ ግራ በገባቸው በጠበባቸው ጊዜ የችግር ጊዜ ደራሽ የኃዘን ጊዜ አፅናኝ የሆነችው የአምላክ እናት ድንግል ማርያም ቅዱስ ገብርኤል እንደተናገረ በፀጋ የተሞላች ናትና (ሉቃ 1÷28) ማንም ሳይነግራት የልቦናቸውን ጭንቀት አይታ፣ ጎዶሎአቸውን ተመልክታ ወደ ልጃ_ ወደ ወዳጃ_ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወር ብላ ‹‹ወይንኬ አልቦሙ›› ‹‹ወይን ጠጅ እኮ አልቆባቸዋል›› አለችው፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› አላት፡፡ እመቤታችንም ለአገልጋዮቹ ‹‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ›› አለቻቸው፡፡ ጌታም በቦታው የነበሩ ስድስት ጋኖች ውኃ ሞልተው እንዲያመጡ አዘዛቸው፡፡ ውኃውንም ወደ ወይን ለውጦ ለሊቀ ምርፋቅ (ለአሳዳሪው) እንዲሠጡት አዘዘ፡፡ አሳዳሪውም ወደ ወይን የተለወጠውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ፡፡ ከወዴት እንደመጣ ስላላወቀ ሙሽራውን ‹‹ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል ከሰከሩም በኋላ መናኛውን ያቀርባል አንተ ግን መልካሙን እስከ አሁን አቆይተሃል›› አለው፡፡ ወይኑም በሰው እጅ ያይደለ በሠማያዊው አባት የተዘጋጀ ስለነበር ጣፋጭ እና ልብን የሚያስደስት ነበር፡፡ ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ይህንን የጌታችንን ንግግር ብዙዎች በዘመናችን ሲሣሣቱበት ይታያል ፡፡ ክብር ይግባውና አምላካችን ይህንን የተናገረው እናቱን ሊያቃልል ሽቶ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር ይህን አረፍተ ነገር መመልከቱ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በተናጠል ስንመለከት ‹‹አንቺ ሴት›› ሴት የሚል ቃል የፆታ መጠሪያ ነውና በፆታዋ አክብሮ ሲጠራት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሔዋን ከአዳም በተፈጠረች ጊዜ አዳም እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር ‹‹ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል›› (ዘፍ 2÷23) በመሆኑም ጌታ አንቺ ሴት ማለቱ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ መንሣቱን ለማጠየቅ ነው፡፡ ‹‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለውን ዐረፍተ ነገር የንቀት ስለመሰለን ብቻ ‘ የዳቦ መልክ የያዘ ድንጋይ፤ ዳቦ ነው እንደማይባል’ የንቀት ንግግር ነው ልንል አይገባም፡፡ ጌታም እንዲህ ሲል ውኃውን ወይን አድርግላቸው ብትይኝ አላደርግም እልሽ ዘንድ ከአንቺ ጋር ምን ፀብ አለኝ ማለቱ ነው፡፡ ይህ ንግግር በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ተጽፎ እንደሚገኘው በዕብራውያን ዘንድ የተለመደ የአነጋገር ዘይቤ ነው፡፡
አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በእናቱ በቅድስት ድንግል አማላጅነት ወኃውን ወደ ወይን እንደ ቀየር ዛሬም የተመሰቃለብን ህይወታችን በእናቱ አማላጅነት በመልካም ጎዳና ይቀርልን ።
ከወላዲት አምላክ ረድኤት በረከት ያሳትፈን አሜን
[እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ]
✍ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
♥ ጥምቀት ማለት ቃሉ የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “መነከር፣ መዘፈቅ፣ ውሃ ውስጥ ገብቶ መውጣት” ማለት ነው፡፡ ጥምቀት ማለት አንድ ሰው አንድ አምላክ በሆኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በተጸለየበትና በተባረከ ውሃ ሦስት ጊዜ ጠልቆ ዳግመኛ ከሥላሴ ተወልዶ የቤተ ክርስቲያን አባል የእግዚአብሔር ሕዝብ ወገን የሚሆንበት ቅዱስ ምስጢር ነው (ማቴ 28፡19-20)፡፡
♥ ምስጢረ ጥምቀት ምስጢር መባሉ ካህኑ ለጥምቀት የተመደበውን ጸሎት አድርሰው ለማጥመቅ የተዘጋጀውን ውሃ ሲባርኩት ውሃው ተለውጦ በዕለተ ዐርብ በመስቀል ላይ ከጌታ ጎን የፈሰሰውን ውሃ ስለሚሆንና ለተጠማቂው ሰው በሚፈጸምለት የሚታይ ሥርዐት የማይታይ የልጅነት ጸጋ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለሚሰጥ ነው (ዮሐ 3፡5)፡፡
♥ምስጢረ ጥምቀትን የመሰረተልን ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ሲመሰርትም በማዘዝ ብቻ ሳይሆን በሥራ በማሳየት ጭምር ነው (ማቴ 3፡17፤ ማር 1፡9፤ ሉቃ 3፡21፤ ዮሐ 1፡31)፡፡
♥ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እከብር አይል ክቡር የባሕርይ አምላክ ሆኖ ሳለ በዮርዳኖስ ወንዝ በአገልጋዩ (በፍጡሩ) በዮሐንስ የተጠመቀበት ምክንያት፦
1) አንድነቱን ሦስትነቱን ለመግለጽ
2) የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ
3) በእርሱ ጥምቀት የእኛን ጥምቀት ለመቀደስ
4)ለጥምቀታችን ኀይልን ለመስጠት
5) ለአብነት ርሱ ተጠምቆ እናንተም ተጠመቁ ብሎ አርአያና ምሳሌ ለመሆን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በ30 ዘመኑ ጥር 11 ከሌሊቱ በ10ኛው ሰዓት፤ ማግሰኞ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡
♥ ጌታችን በዮርዳኖስ እንደሚጠመቅና የዮርዳኖስ ወንዝ ጌታን ስታይ እንደምትሸሽ ነቢዩ ዳዊት በመዝ 113፡3-5 “ባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፤ ተራሮች እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ፤ አንቺ ባሕር የሸሸሽ፥ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ ምን ሆናችኋል?” በማለት ከ1000 ዓመት አስቀድሞ ትንቢት የተናገረ ሲሆን፤ ብዙ ምሳሌም አለው፨
♥ ምስጢሩ ግን ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን ላይ የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ መከራ አጸናባቸው፤ ከዚያም ለኔ የባርነት ስም ብትሰጡኝ መከራውን አቀልላችሁ ነበር አላቸው፤ እነሱም “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ” (አዳም የዲያብሎስ ወንድ አገልጋይ ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ) ብለው አሉ፤ ርሱም ይህንን በዕብነ ሩካም አድርጎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጥሎት ነበርና፤ ጌታም በዮርኖስ ጥልቅ ወንዝ የተጣለውን የሰው ልጆች ሁሉ የዕዳ ደብዳቤ በጥምቀቱ ለማጥፋት ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡
♥ ዮሐንስ ወደ ጌታችን መምጣት ሲገባው ጌታችን ወደ ዮሐንስ የሄደበት ምክንያት ትሕትናን ለማስተማር ሲሆን ሁለተኛው ለአብነት ለምሳሌ ነው፤ ይኸውም ዮሐንስ ሄዶ አጥምቆት ቢሆን ዛሬ ባለሥልጣናቱ ካህናትን ቤታችን ድረስ መጥታችሁ አጥምቁን ይሏቸው ነበርና ሄዳችሁ ቤተ ክርስቲያን ተጠመቁ ለማለት ሄዷል።
♥ ዮሐንስ ግን ወደርሱ በትሕትና የመጣው አምላኩ ክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ “እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን?” ሲል ጌታችንም “ጽድቅን ልንፈጽም” ይገባናል ብሎ ትንቢተ ነቢያትን ሊፈጽም እንደመጣ ሲነግረው ዮሐንስ እሺ አለ።
♥ ከዚያም ተያይዘው ወደ ዮርዳኖስ ሲወርዱ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት እንደሚያስተምሩት የዮርዳኖስ ወንዝ 40 ክንድ ወደ ኋላዋ ሸሽታለች በዚህም ዳዊት በመዝ 77፡16 ላይ “አቤቱ፥ ውኆች አዩህ ውሆችም አይተውህ ፈሩ ጥልቆች ተነዋወጡ፥ ውኆችም ጮኹ” ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ።
♥ ጌታችንም ተጠምቆ ከውሃው ከወጣ በኋላ አብ በሰማይ ኹኖ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ” (በርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይኽ ነው) ብሎ ሲመሰክር፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ፤ አካላዊ ቃል ክርስቶስም በጽንፈ ዮርዳኖስ ቁሞ ታየ፡፡
♥ ይኸውም በምስጢረ ሥላሴ ትምህርት እንደምንረዳው ከሰማይ ኾኖ የመሰከረው ክርስቶስ በቃልነት መንፈስ ቅዱስ በእስትንፋስነት ያሉበት (ሕልው የኾኑበት) አብ ነው፤ ወርዶ በወልድ ራስ የተቀመጠው አብ በልቡናነት ክርስቶስ በቃልነት ሕልው የኾኑበት መንፈስ ቅዱስ ነው፤ በጽንፈ ዮርዳኖስ ቆሞ የታየው አብ በልቡናነት መንፈስ ቅዱስ በእስትንፋስነት ሕልው የኾኑበት አካላዊ ቃል ክርስቶስ ነው፤ እንዲኽ አድርገው የአካል ሦስትነታቸውን የፈቃድ አንድነታቸውን ለማስረዳት አብ በደመና ኾኖ መሰከረ፤ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ ታየ፤ አካላዊ ቃል ክርስቶስ በጽንፈ ዮርዳኖስ ቆሞ ታየ።
♥ በዚኽም የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በሚገባ ሲታወቅ በተጨማሪም “በርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይኽ ነው” ብሎ እግዚአብሔር አብ በመመስከሩ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው በኋለኛው ዘመን ከእመቤታችን ያለ አባት በኅቱም ድንግልና የተወለደው እግዚአብሔር ወልድ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው አንድ ብቻ መኾኑ በሚገባ ተረጋግጧል፤ ዕለቱም በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋንያ ሲባል በግእዝ አስተርእዮ በዐማርኛም የመታየት የመገለጥ ጊዜ ተብሏል፡፡
♥ ኢትዮጵያ ሀገራችን ስለ ነገረ ጥምቀት የሰማችው ከሌላው ዓለም አስቀድማ ጌታችን ባረገ በጥቂት ወራት (በ34 ዓ.ም) ነው (የሐዋ 8፥26-39)፤ ይህም በዐል ከዘጠኙ ዐበይት በዐላት አንደኛው ሲሆን ጌታችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ስላመራ ይህንን ለማሰብ ታቦታቱ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ያመራሉ።
♥ ሊቀ ትጉኃን ኃይለ ጊዮርጊስ በጻፉት የነገረ ሃይማኖት መጽሐፍ ላይ በስፋት እንደጻፉት በኢትዮጵያ በዚህ መልኩ መከበር የተጀመረው ከ515-529 ዓ.ም ለ14 ዓመት ኢትዮጵያን በመሩት በአጼ ገብረ መስቀል ዘመን ሲሆን በጊዜው ቅዱስ ያሬድ የነበረበት ጊዜ በመሆኑ ከዝማሬው በመነሣት ታቦታቱ ጥር 11 ጠዋት ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው ወደ ባሕረ ጥምቀቱ አምርተው አመሻሹ ላይ ይመለሱ ነበር፡፡
♥ ከዚያም ከ1157-1197 ዓ.ም ድረስ ለ40 ዓመት ኢትዮጵያን በመራው በታላቱ ጻድቅ ንጉሥ በላሊበላ ዘመን በአንድ አካባቢ ያሉ አብያተ ክርስትያናት ታቦታቱ ባንድ ላይ እንዲያከብሩ ንጉሥ ላሊበላ ታላቅ መንፈሳዊ ዐዋጅን አሳውጆ በአንድ አካባቢ፣ ወረዳ፣ ያሉ በአንድ ላይ ማክበር ጀመሩ፤ በርሱ ዘመን የነበሩት ታላቁ ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአክሱም፣ በጎንደር፣ በሸዋ፣ በአንኮበር፣ በመርጡለ ማርያም እየሄዱ ባሕረ ጥምቀቱን ባርከዋል፡፡
♥ በመቀጠልም ከ1245-1268 ዓ.ም ለ23 ዓመት ኢትዮጵያን በመሩት በዐጼ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አሳሳቢነት ታቦታቱ በባሕረ ጥምቀት ሲውሉ ምእመናን በታላቅ ድምቀት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ እንዲውሉ መንፈሳዊ ዐዋጅ አሳወጁ፡፡
♥ በመቀጠል ከ1426-1460 ዓ.ም ለ34 ዓመት ኢትዮጵያን በመሩት በታላቁ ንጉሥ በዐጼ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥትም ንጉሡ ከሊቃውንት ጋር በመወያየት የበዐሉን ታሪክ ተከትሎ ታቦታቱ ጥር 10 ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው ወደ ባሕረ ጥምቀት እንዲወርዱና ጥር 11 እንዲመለሱ ተወሰነ።
?????
#እመቤቴ_ሆይ፤ ባትወለጂ እግዚአብሔርን በሥጋ ተገልጦ እናየው ነበርን? በፍጹም። አንቺ ባትወለጂ ፍቅር፣ ምሕረት እና ፍጹም መልካምነት በእውነት ሥጋን ነሥተው በክርስቶስ እናይ ነበርን? በፍጹም። አንቺ ባትወለጂ የእግዚአብሔርን ጸጋ እና ንጽሕና በሰውነት ተገልጦ እናይ ነበርን? በፍጹም። ይኸውም ያንቺ የቅድስና ሕይወት ነው። ከሊቃውንት አንዱ የአንቺ አንዲቷ ትንፋሽ ከቅዱሳን ሁሉ ገድል፣ ምስጋና እና ምልጃ ሁሉ የከበረች እንደሆነች ተናገረ። ይህ ሁሉ ከሰው ኅሊና ስለሆነው ንጽሕናሽ ነው። በዘወትር ቋንቋችን አንቺን "ንጽሕት" ብቻ ማለት ንጽሕናን ማጉደፍ ይሆናል እኮን። ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ያንቺ ንጽሕና እና ቅድስና በቃል ከመነገር ይልቅ፤ በዝምታ የልብ ለኆሳስ ቢመሰገን የተገባ ነው። አንቺ ባትወለጂ የእግዚአብሔር ትእዛዝ በምልዓት ሲፈጸም፤ ሕጉ ሲደረግ ምን እንደሚመስል በምን እናውቅ ነበር?
አንቺ ባትወለጂ የክህነት ንጽሕና በምን ይጠበቅ ነበር? አንቺ ባትወለጂ የንስሐ መንገዱን ማን ያመለክተን ነበር? አንቺ ባትወለጂ ያንቺ መታዘዝ፡ የእኛን ዐመጸኛነት እንዴት ይገስፀዋል? አንቺ ባትወለጂ ያንቺ ትሕትና፡ የኔን ትዕቢት ይሰብረው ዘንድ እንዴት ይቻለዋል? ስለ አምላካዊው ኀይሉ፤ ጠላት ሰይጣን ለልጅሽ ይገዛል። የልጅሽ የክርስቶስን ስም ሲሰማ ይንቀጠቀጣል። አንቺ ግን በትሕትናሽ ሰይጣንን አራድሽው። እርሱ መንፈስ ሲሆን "ሥጋ ለባሽ" ብሎ በሚንቃት "በአንዲት ሴት" መሸነፉ ሁልጊዜም ግራ ይገባዋል። ስምሽን የሚጠሩ ሰዎች ፊትም መቆም አይቻለውም። ስምሽን ሲጠሩ ኀይላቸውን ትተው ኀይልሽን ይይዛሉና። ይኸውም እግዚአብሔር ነው። ስምሽን ሲጠሩ ትዕቢታቸውን ጥለው በትሕትናሽ ይጋረዳሉና። ስምሽን ሲጠሩ ጥርጣሬያቸውን በሃይማኖትሽ ያሸንፋሉና። በንጽሕና ቀሚስሽ ስለ እድፈታቸው ከሚከሳቸው ይጋረዳሉና። ሰይጣን ከእነርሱ ዘንድ አይቀርብም። እመቤቴ ሆይ አንቺ ባትወለጂ ከመልካሙ ሁሉ በአፍአ በቀረን ነበር እኮን። አሁንም "መጥተን" ሳለን የቀረን አታድርጊን። እኛ ራሳችንን ብንተው፤ አንቺ አትተዪን። እኛ ብንርቅ፡ አንቺ አትራቂን። እኛ ብንዘነጋ፡ አንቺ አትዘንጊን። መሐርነ፡ ወተሣሃልነ!
ፀሀፊ Micky Asres
የወገኖቼም ኃጢአት እንዲሁ በታየኝ ጊዜ አለቅሳለሁ" አሉት፡፡ በሌላም ጊዜ ጌታችን በመሠዊያው ላይ ሆኖ ተገልጦላቸው የእያንዳንዱን ሰው ኃጢአት መላእክት ሲያቀርቡለት አሳያቸው፡፡ ቀጥሎም "ሕዝቡን አስተምረህ ከክፋታቸው መልሳቸው" አላቸው፡፡ እሳቸውም "አይሰሙኝም" ቢሉት ጌታችንም "አስተምረሃቸው ከክፋታቸው ባይመለሱ ደማቸው በራሳቸው ላይ ይሆናል" አላቸው፡፡
❤ መናፍቁ ንጉሥ መርቅያኖስና ተከታዮቹ ክብር ይግባውና ጌታችንን "ሁለት ባሕርይ" በማለታቸው ጉባዔ ሠርተው አባቶች ሲሰበሰቡ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ አባ መቃርስን አስከትሎ በጉባዔው ተገኘ፡፡ አባ ዲዮስቆሮስና አባ መቃርስም ሁለት ባሕርይ ባዮችን አስተምረዋቸው እምቢ ቢሏቸው አውግዘውና እረግመው ከቤተ ክርስቲያን ለዩአቸው፡፡ ለመከራም የተዘጋጁ ሆነው ራሳቸውን አሳልፈው ሰጧቸው፡፡ ከሃዲው ንጉሥም ወደ ጋግራ ደሴት አጋዛቸው፡፡ አባ ዲዮስቆሮስም ለአባ መቃርስ "አንተ በእስክንድርያ ሀገር ሰማዕትነት ትቀበላለህ" በማለት ትንቢት ነግረዋቸው ከአንድ ነጋዴ ጋር ወደ እስክንድርያ ላኳቸው፡፡ እዚያም ሲደርሱ መናፍቁ ንጉሥ መርቅያኖስ አባ መቃርስን ይዞ ብዙ ካሠቃያቸው በኋላ ኩላሊታቸውን ብሎ ገደላቸውና የሰማዕትነታቸው ፍጻሜ ጥቅምት 27 ቀን ሆነ፡፡ ክርስቲያኖችም ሥጋቸውን ወስደው ከነቢዩ ኤልሳዕና ከመጥምቁ ዮሐንስ ሥጋ ጋር በአንድነት አኖሩት፡፡ ከሥጋቸውም ብዙ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛን በአባ መቃርስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥቅምት27 ስንክሳርና መዝገበ ቅዱሳን።
❤ ጌታችን ለአቡነ መብዓ ጽዮን የወርቅ በትር ሰጥቷቸው በእርሷ ነፍሳትን ከሲኦል ያወጡባት ነበር፡፡ መቋሚያዋም እሳቸው ካረፉ በኋላ የሚሞተውን ሰው እየለየች ትናገር ነበር፡፡ አባታችን እንደ አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በመልአክ ተጥቀው ተወስደው የሥላሴን መንበር ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር አጥነዋል፡፡ ጌታችን ከተረገመችና ከተወገዘች ዕፅ ጋር በተገናኘ ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክና ለአቡነ መብዓ ጽዮን ልዩ ምሥጢር እንደነገራቸው በሁለቱም ቅዱሳን ገድላት ላይ በሰፊው ተጽፏል፡፡
❤ አቡነ መብዓ ጽዮን በይበልጥ የሚታወቁት ሁልጊዜ ወር በገባ በሃያ ሰባት መድኃኔዓለምን አብልጠው በመዘከራቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት "እንደ አንተም በየወሩ በሃያ ሰባት የሞቴ መታሰቢያ ለሚያደርግ ነፍሳትን ከሲኦል አወጣለታለሁ" የሚል ድንቅ ቃልኪዳን ከጌታችን ተቀብለውበታል፡፡ ይኸውም የመድኃኔዓለምን የሞቱን መታሰቢያ የሚያድርግ ቢኖር ነፍሳትን ከሲኦል እንደሚያወጣ ሲነግራቸው ነው፡፡ ቅዱስ አባታችን "ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ! በዓልህን አደርግ ዘንድ አንተ የምትወደውን ግለጥልኝ" ብለው ጌታችንን ሲጠይቁት እርሱም "የሞቴን መታሰቢያ ያደረገ እንደ እኔ ነፍሳትን ከደይን ያወጣል፣ "በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ይሠራል፣ ከዚያም የበለጠ ይሠራል" ብዬ በወንጌሌ እንደተናገርሁ" አላቸው"፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን ለልጆቻቸው እንዲህ ብለው መከሯቸው፡- "ክርስቲያኖች ሁሉ የፈጣሪያችንን የመድኃኔዓለም ክርስቶስን የመታሰቢያ በዓሉን እናድርግ፡፡ የአባቶቻችን የሐዋርያት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የመላእክት መታሰቢያቸው ባረፉበት በተሾሙበት ቀን ይከበራል፡፡ እነርሱን የፈጠራቸው እርሱ መድኃኔዓለም ነው፣ ያከበራቸው፣ ከፍ ከፍ ያደረጋቸው፣ ስማቸውን ለጠራ መታሰቢያቸውን ያደረገ እንደሚድን ቃልኪዳን የሰጣቸው እርሱ ነው፡፡ የመድኃኔዓለምን የሞቱን መታሰቢያ ያደረገ ግን የተኮነኑ ነፍሳትን ከደይን ያወጣል፣ በሞቱም ጊዜ ሥቃይን አያያትም"፡፡
❤ የአቡነ መብዓ ጽዮን በዓለ ዕረፍታቸውም እጅግ አብዝተው በሚዘክሩበትና ዓመታዊ ክብረ በዓሉ ታስቦ በሚውለው በመድኃኔዓለም ቀን ጥቅምት ሃያ ሰባት ነው፡፡ ከአባታችን አቡነ መብዓ ጽዮን እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን፣ በጸሎታቸው ይማረን!።
❤ አቡነ ጽጌ ድንግል ከደብረ ሐንታው ከአቡነ ገብረ ማርያም ጋር እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው እመቤታችንንና ፈጣሪ ልጇን በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየመሰለ የሚያመሰግነውን ድርሰቱን በመዝሙረ ዳዊት መጠን 150 አድገው ደርሰዋል፡፡ አቡነ ገብረ ማርያምና አቡነ ጽጌ ድንግል ማኅሌተ ጽጌን በጥምረት ሊደርሱት የቻሉት አቡነ ገብረ ማርያም በወሎ ክፍለ ሀገር በወረኢሉ አውራጃ ልዩ ስሙ ደብረ ሐንታ በሚባለው ገዳም የሕግ መምሕር ሆነው በተሾሙበት ወቅት ነው፡፡ እነዚህም ሁለት ቅዱሳን የዘመነ ጽጌ የማኅሌት አገልግሎትን ሳይለያዩ በሰላምና በፍቅር በአንድነት አግልግለዋል፡፡ ይኸውም የሆነው እንዲህ ነው፡-
አንድ ዓመት አቡነ ገብረ ማርያም የክረምት መውጫና የዘመነ ጽጌ ዋዜማ በሆነው መስከረም 25 ቀን ከደብረ ሐንታ መጥተው ደብረ ብሥራት አቡነ ጽጌ ድንግል ገዳም ገብተው ከመስከረም 25 ቀን እስከ ኅዳር 5 ቀን ያለውን የዘመነ ጽጌ የ40 ቀን አገልግሎት ከአቡነ ጽጌ ድንግል ጋር ፈጽመው ኅዳር 8 ቀን ወደ ደብራቸው ደብረ ሐንታ ይመለሳሉ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ አቡነ ጽጌ ድንግል ከገዳማቸው ከደብረ ብሥራት ተነሥተው ወደ ደብረ ሐንታ ሄደው እንዲሁ እንደ አቡነ ገብረ ማርያም 40ውን ቀን አግልግለው ይመለሳሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ቅዱሳን እንደዚህ እያደረጉ በየተራ አንደኛው ወደ ሌላኛው ገዳም እየሄዱ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ በፍጹም ፍቅርና በትሕትና አብረው እመቤታችንን ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡ ይኸውም በራሳቸው በአቡነ ገብረ ማርያም ገድል ላይ እና በአቡነ ዜና ማርቆስ ገድል ገጽ 72-73 ላይ በሰፊው ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ የሁለቱ ድርሰታቸው የሆነው "ማኅሌተ ጽጌ" ድርሰት የእመቤታችንንና የልጇን የጌታችንን ሥጋዊ ስደት የሚገልጽ ሲሆን በጨማሪም ስደት የማይገባው አምላካችን ወደ አህጉራችን አፍሪካ ተሰዶ የሠራቸውን ድንቅ ድንቅ ተአምራትና የእመቤታችንን ንጽሕናዋን ቅድስናዋን አማላጅነቷን የሚያስረዳ ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡
❤ አባ ጽጌ ድንግል ከማኅሌተ ጽጌ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ አስደናቂ ድርሰቶችን ደርሰዋል፡፡ የጻድቁ ቅዱስ ዐፅማቸው፣ ታቦታቸውና የደረሷቸው በርካታ ድርሰቶች በገዳማቸው ደብረ ጽጌ ውስጥ በክብር ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ አምሃራ ሳይንት ቦረና ከአቡነ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም የ5 ሰዓት የእግር መንገድ ከተሄደ በኋላ የሚገኘው ገዳማቸው "ደብረ ጽጌ" ከአንድ ወጥ ዓለት ተፈልፍሎ የተሠራው ሲሆን አሠራሩም እጅግ ድንቅ ነው፡፡
❤ የአቡነ ጽጌ ድንግል ገዳም ከአቡነ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ጋር የሚያገናኘው "የእግዜር ድልድይ" የተባለ አስገራሚ ታሪክ ያለው ድልድይ አለው፡፡ ሁለቱ ቅዱሳን በመንፈስ ተጠራርተው ለመገናኘት ቢያስቡም የወለቃ ወንዝ ሞልቶ በአካል ሳይገናኙ ቀሩ፡፡ በዚህም በጣም አዝነው ከወንዙ ወዲያና ወዲህ ሆነው ተላቅሰው አፈር ተራጭተው ወደየገዳማቸው ቢመለሱም ያ ተላቅሰው የተራጩት አፈር በተአምር ትልቅ ድልድይ ሆነ፡፡ ድልድዩን ሁለቱም በበዓታቸው ሆነው በመንፈስ አዩት፡፡ የበጎ ነገር ጠላት ሰይጣንም ይህንን ሲመለከት ድልድዩን
በትልቅ ሹል ድንጋይ በስቶ ሊያፈርሰው ሲል አቡነ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመንፈስ አዩትና ከጋስጫ ተነሥተው በደመና ተጭነው በመሄድ ሰይጣኑን በግዘፈ ሥጋ ገዝተው ያንን ድልድዩን አፈርስበታለሁ ያለውን ትልቅ ሹል ድንጋይ አሸክመውት በዓታቸው ጋስጫ ድረስ ወስደውታል፡፡ ያ ድንጋይ ዛሬ በጋስጫ አቡነ ጊዮርጊስ ገዳም ለመነኮሳቱ ደወል ሆኖ እያገለገለ ይኛል፡፡ ድልድዩም እስከ አሁን ድረስ ለአካባቢው ኢስላም ማኅበረሰብ ብቸኛው የወለቃ ወንዝ መሻገሪያቸው ሆኖ እያገለገላቸው ነው፡፡
ከአባታች አቡነ ጽጌ ድንግል እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከትን ይሳትፈን፣ በጸሎታቸው ይማረን! ምንጭ፦ገድለ አቡነ መባዓ ጽዮን፣ መዝገበ ቅዱሳን።
❤ ይህም አባ መቃርስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመጠበቅ በመክሊት ነግዶ ዕጥፍ አድርጎ አትርፎአልና እግዚአብሔርም በእጆቹ ያደረጋቸውን ታላላቆች ድንቆች ተአምራት ስንቱን እናገራለን። ስለርሱም እንዲህ ተባለ እርሱ በአገረ ቃው ተሾሞ በወንበር ተቀምጦ ሕዝቡን በሚያስተምራቸው ጊዜ ዘወትር ያለቅሳል ከደቀ መዛሙርቶቻቸውም አንዱ በእግዚአብሔር ስም ካማላቸው በኋላ ለምን ሁልጊዜ እንደሚያለቅሱ በመሐላው አምሎ ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም ስለመሐላቸው ፈርተው ነገሩት "ዘይት በብርሌ ውስጥ ጎልቶ እንደሚታይ
ፆመ ፍልሰታ የእመቤታችን እረፍት ትንሳኤና እርገት ሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡ እመቤታችን በተለያዩ ጊዜያት ሞትና ትንሣኤዋን ለሐዋርያት የገለጸችበትን ምስጢር ከነሐሴ 1-16 ድረስ ምእመናን በጾም በጸሎት ተወስነው የልጇን ቸርነት የእርሷን አማላጅነት በሱባኤ ይማጸናሉ፡፡ የሱባኤው ወቅት ሲፈጸም “እመቤታችን በእውነት ተነሥታለች” ብለው በደስታ የጾሙን ወቅት ይፈጽማሉ፡፡ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን ቅዱስ ያሬድ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የሐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው፡፡ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል” በማለት ገልጾታል፡፡
በኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ 64 ዓመታት ያህል ቆይታ አርፋ ተነሥታ በክብር አርጋለች፡፡ ይህንን የትንሣኤና ዕርገት ዐቢይ ምሥጢር ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ተንሥአ እግዚኦ” ውስተ ዕረፍትከ፡፡ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፡፡ አንተና የመቅደስህ ታቦት” /መዝ.131፡8/፤ እንዲሁም “ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” /መዝ.44፡9/ ሲል የተናገረው ቃለ ትንቢት በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና የጸናች የቅድስት ድንግል እመቤታችንን ዕረፍት፣ ትንሣኤ፣ ፍለሰት /ዕርገት/ ያስገነዝባል፡፡ /ራእ.11፡19/
እመቤታችን ታቦተ እግዚአብሔር መሆኗን አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ሲገልጽ “ከመ ታቦት ሥርጉት በወርቀ ዓረብ ወተርሴስ በድንግልና ማርያም ሥርጉተ ሥጋ ወነፍስ” ሲል አመስግኗታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በትርጓሜያቸው ይህንን ቃለ ትንቢት ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ከገለጣት “ንግሥተ ሰማይ፤ የሰማይ ንግሥት” /ራእ.12፡1/ ጋር በማገናዘብ የእመቤታችንን ሁለንተናዊ ክብርና ልዕልና አምልተውና አስፍተው ገልጸውታል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ “… በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው፡፡….. ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ሥራቸውም ይከተላቸዋል” /ራእ.14፡13/ ብሎ እንደመሰከረው እመቤታችን ከዕረፍቷና ዕርገቷ በኋላ የመጨረሻ ወደ ሆነው ክብር መሸጋገሯ ያስረዳል፡፡
ይህንን ክብርዋን በመረዳት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር “ወበእንተዝ ናዐብየኪ ኩልነ ኦ እግዝእትነ ወላዲተ አምላክ ንጽሕት ኩሎ ጊዜ፡፡ ንስአል ወናንቀዐዱ ኀቤኪ ከመ ንርከብ ሣህለ በኀበ መፍቀሬ ሰብእ፤ ሁልጊዜ ንጽሕት የምትሆኚ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ ስለዚህ ነገር እናከብርሻለን፣ እናገንሻለን፡፡ ሰውን ከሚወድ ልጅሽ ዘንድ የቅርታንና ምሕረትን እናገኝ ዘንድ ሁል ጊዜ ዓይነ ልቡናችንን ወደ አንቺ እናነሣለን፡፡ በማለት ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ሁል ጊዜ ዓይነ ልቡናችንን ወደ አንቺ እናነሣለን፡፡ በማለት ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣትን ልዩ የቃል ኪዳን ጸጋና አምላካዊ ክብር እያመሰጠሩ ያመሰግኗታል፡፡ ሊቁ “ቀስተ ደመና ማርያም ትእምርተ ኪዳኑ ለኖኅ፣ ዘእግዚአብሔር ሤመኪ ለተዝካረ ምሕረት ወፍትሕ፣ ህየንተ ቀስፋ ለምድር ወአማሰና በአይኅ፡፡ ብሎ እንዳመሰገናት፡፡
እመቤታችን በአጸደ ሥጋ ሳለች ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ በመዋዕለ ሥጋዌ ላደረገው የድኅነት ዓለም ጉዞ ምክንያት ነበረች፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ባርነትና ስደት ለማጥፋት ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ የሰው ልጆችን ያሳደደ ሠይጣን በሄሮድስ አድሮ ሲያሳድደው ልጇን ይዛ በመሰደድ ለድኅነታችን ምክንያት ነበረች፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ባርነትና ስደት ለማጥፋት ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ የሰው ልጆችን ያሳደደ ሠይጣን በሄሮድስ አድሮ ሲያሳድደው ልጇን ይዛ በመሰደድ ለድኅነታችን ምክንያት ነበረች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በራእዩ እንዳየው፤ “ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች፡፡ እርስዋም ፀንሳ ነበር፡፡ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጨንቃ ጮኸች፡፡ ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ፡፡ አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔር ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ፡፡ ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስልሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች ”/ራእ.12፡1-6/
#ፍልሰታ_መጣች ?
"ሕፃኑም ወጣቱም ወንዱም ሴቱም ዕድሜው የገፋውም ሁሉም በፍቅር የሚፆሟት፣ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድዔትና በረከት የሚታፈስባት፣ ፍቅረ እግዚአብሔር በሰው ልቡና የሚሰለጥንባት ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር የሚያይልባት #የንሰሐና_የምህረት_ጾም_ጾመ_ፍልሰታ_መጣች ?
❤ በዓለም ያሉ ወደ ቤተክርስቲያን በቤተክርስቲያን ያሉ ወደ ገዳማት የሚገሰግሱባት ጾመ ፍልሰታ መጣች?
የተዋህዶ ልጆች እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ ?
??❤️ ለሀገራችን ምህረትን ፣ ሰላም እና ፍቅርን የድንግል ማርያም ልጅ ያድልልን የበረከት የምህረት የይቅርታ ፆም ይሁንልን ??❤️
ሰውን የሚያረክሱትን ነገሮች የትኛዎቹ እንደኾኑ እንረዳ እና አንዴ ከተረዳንም በኋላ እንራቃቸው፡: በቤተ ክርስቲያን ውስጥ፤ አብዛኛዎቹ ሰዎች የውጫቸው ንጹህ ኾኖ መታየት እንደሚያሳስባቸው እናያለን፤ ነገር ግን ስለ ንጹህ ልብስ እንጂ በእግዚአብሔር ፊት ንጹህ ልባቸውን ስለማቅረብ አያስቡም፡፡ እጃችሁን ወይም አፋችሁን አትታጠቡ እያልኩ አይደለም ነገር ግን በትክክለኛው መንገድ በመልካም ተግባርና በጎነት ብትታጠቡ ይሻላል፡፡
ስለሌሎች መጥፎ መናገር፤ ጸያፍ ቋንቋ መጠቀም፤ ተገቢ ባልኾኑ ቀልዶች መሳቅ እነዚህ ነገሮች ልብን ያቆሽሹታል፡፡ እንግዲያው፣ ከእነዚህ ነገሮች አንዱንም ካላደረጋችሁ፤ በቅን ልብ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ትችላላችሁ፡፡ እነዚህን ነገሮች ካደረጋችሁ ግን ጸሎታችሁ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ርኩሰት የተሸከመ ምላስህንም በውኃ ማጠብህ ትርጉም አይኖረውም።
ይህን አስቡ በእጃችሁ ላይ ጭቃ ወይም እበት ቢኖርባችሁ ለመጸለይ ትደፍራላችሁ? በጭራሽ። ነገር ግን የእጅ መቆሸሽ ከልብ መቆሸሽ በላይ የሚያጸይፍ መሆን የለበትም፡፡ ለምንድነው አላስፈላጊ ለኾኑ ነገሮች ትኩረት የምትሰጡት እና አስፈላጊ የኾኑትን ችላ የምትሉት? “አትጸልዩ ነው ወይ የምትለን" ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። አይ፤ መጸለያችሁን ማቆም የለባችሁም፣ ግን በዚህ ቆሻሻ ሁኔታ ውስጥ መሆን የለበትም፡፡
“ሳላውቅ ኃጢአትን ብሰራ፣ ስህተት ካደረኩ ምን ማድረግ አለብኝ?" እራስህን አጽዳ፡፡ እንዴት? ተጸጸት፣ ለድሆች ስጥ፣ የሰደብከውን ስው ይቅርታ ጠይቅ፣ የበደሉህንም ይቅርታ አድርግላቸው፡፡ እግዚአብሔርን አብዝተህ እንዳታስቆጣ አንደበትህን አጽዳ፡፡
በእጆቹ ጭቃ የያዘ ሰው እግርህን ቢይዝና ገንዘብ ቢጠይቅህ፣ አትሰማውም፤ እንዲያውም ልትገፋው ትችላለህ፡፡ ታዲያ ለምን በዚህ መንገድ ወደ እግዚአብሔር ትቀርባለህ? የሚጸልዩ ሰዎች አንደበት የእግዚአብሔርን ጉልበት እንደሚነካ እጅ ነው፡፡ ስለዚህ አንደበታችሁን አታርክሱ፣ አለዚያ እግዚአብሔር ጸሎታችሁን አልሰማም ይላል፡፡ አንደበት የሕይወትና የሞት ኃይል አለው። ቃላትህ ሊያጸድቁህ ወይም ሊያስኮንኑህም ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ምላስህን ከዓይኖችህ የበለጠ በጥንቃቄ ጠብቅ።
አንደበት ለንጉሥ እንደ ፈረስ ነው፤ በእርሱም ላይ ልጓም ቢደረግበት፣ ከተቆጣጠሩት እና ከገሩት ለንጉሡ የታመነ ይኾናል፡፡ ነገር ግን እንዲሁ እንዲሮጥ ከፈቀድክ የዲያብሎስ መሳሪያ ይሆናል፡፡ አንደበትህን አታርክሰው፣ በየዋህነት እና በትህትናም አስጊጠው::
ለእግዚአብሔር የሚገባውን አድርጉ፣ አንደበታችሁ በመልካም ቃላት ይሞሉ፤ መልካም ቃል ከስጦታ ይሻላልና፡፡ ለድሆች በደግነትና በቅንነት መልሱ፡፡ የቀረውን ጊዚያችሁን ስለ እግዚአብሔር ሕግጋትና ትምህርቶች በማሰብ አሳልፉ፡፡ ንግግሮቻችሁ ኹሉ በልዑል እግዚአብሔር ህግጋት የተገሩ ይሁኑ፡፡ ራሳችንን አስጊጠን ወደ ንጉሡ እንውጣና በእግሩ ሥር እንውደቅ፣ በአካል ብቻ ሳይኾን በአዕምሯችንም፡፡ ወደ ማን እንደምንሄድ፣ ለምን ዓላማ እና ምን ማከናወን እንደምንፈልግ እንመርምር፡፡ ሱራፌልና ኪሩቤል በዓይናቸው የማያዩት፤ ግርማውን መሸከም ያቃታቸው፣ መዳረሻ አልባ ብርሃን ወደሆነው ወደ እግዚአብሔር እንሄዳለን፡፡ ከገሃነም ለማምለጥ፤ ለኃጢአታችን ይቅርታ ለመጠየቅ፤ ከቅጣት ለመራቅ እና ወደ መንግሥተ ሰማያት (እና በረከቶቿ ኹሉ) ለመግባት ወደ እርሱ እንሄዳለን፡፡
ምንጭ፦
(#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ - #የነፍስ_ምግብ ገጽ 60-62 #በፍሉይ_ዓለም_የተተረጎመ)
★ሰውን በማዝናናት የብቃት ማረጋገጫ ያለው ብቸኛው ቻናል ሁሌም Telegram ላይ በጥበብ ደምቀን እናሸበርቃለን
? Contact us, @Modenyazbot
»የተመረጡ እና ማንም ያላያቸው የአማሪኛ ቀልዶች እንዲሁም የሚያስደንቁ ስዕሎችንና ቪዲዮ ያገኛሉ።
° ° [ ሙድ እንያዝ በእኛ የአራዶች መዝናኛ ] ° °
° ° Creator @Teke_Man ° °
Last updated 1 month, 2 weeks ago
☕ ስለ ኢትዮጲያ ቡና የሚወጡ ወቅታዊና ትክክለኛ የክለቡ መረጃዎች አዚህ ያገኛሉ!
➪የዝዉዉር ዜና
☞የአሰልጣኞች አስተያየት
➪ጎሎች እና ቪዲዮዎች
☞የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
➪ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት ከየስታድየሙ !
➡መወያያ ግሩፓችን @Ethiopia_coffee_Sc
?ሀሳብ ወይም አስተያየት ካሎት
በዚህ ? @EthiopianCoffeeScBot ✍
BOT ማድረስ ይችላሉ!
Last updated 6 months, 3 weeks ago
ማንኛውንም የማስታወቂያ ስራ ለማሰራት የምትፈልጉ(only promotion) inbox @Eyyiba
ሌሎች ጥያቄዎችን ለማድረስ
@Ethiodailyvacbot
Last updated 3 weeks ago