ዐውደ ምሕረት

Description
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Advertising
We recommend to visit

★ሰውን በማዝናናት የብቃት ማረጋገጫ ያለው ብቸኛው ቻናል ሁሌም Telegram ላይ በጥበብ ደምቀን እናሸበርቃለን

💌 Contact us, @Modenyazbot

»የተመረጡ እና ማንም ያላያቸው የአማሪኛ ቀልዶች እንዲሁም የሚያስደንቁ ስዕሎችንና ቪዲዮ ያገኛሉ።

° ° [ ሙድ እንያዝ በእኛ የአራዶች መዝናኛ ] ° °

° ° Creator @Teke_Man ° °

Last updated 1 month, 1 week ago

☕ ስለ ኢትዮጲያ ቡና የሚወጡ ወቅታዊና ትክክለኛ የክለቡ መረጃዎች አዚህ ያገኛሉ!

➪የዝዉዉር ዜና
☞የአሰልጣኞች አስተያየት
➪ጎሎች እና ቪዲዮዎች
☞የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
➪ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት ከየስታድየሙ !

➡መወያያ ግሩፓችን @Ethiopia_coffee_Sc

📩ሀሳብ ወይም አስተያየት ካሎት
በዚህ 👉 @EthiopianCoffeeScBot ✍
BOT ማድረስ ይችላሉ!

Last updated 3 months, 2 weeks ago

ማንኛውንም የማስታወቂያ ስራ ለማሰራት የምትፈልጉ(only promotion) inbox @Eyyiba
ሌሎች ጥያቄዎችን ለማድረስ
@Ethiodailyvacbot

Last updated 1 day, 11 hours ago

1 month, 3 weeks ago

+++ እርሷ መድኃኒታችሁ ናትና!!" +++

ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ለኢየሱስ ክርስቶስ እናት ዓመታዊ በዓል (ብዙኃን ማርያም) እንኳን አደረሰን!!
(በትዕግሥት ሆነው ያንብቡት፣ ለሌላውም በማጋራት ሃይማኖታዊ ግዴታዎን ይወጡ)

ላለመማርና ላለማወቅ አእምሯቸውን አሳልፈው የሰጡ ኦርቶዶክሳዊነትንና ኦርቶዶክሳውያንን አምርረው የጠሉ ሰዎች "ድንግል ማርያም ምክንያተ ድኂን እንጂ መድኃኒት አትባልም" ሲሉ ለይቶላቸው የወጡቱ ደግሞ ጥቅሶችን ከዓውድና ከተነገሩበት ዓላማ ውጭ በመጥቀስ "ማርያምን መድኃኒት ቤዛ አድኝን" አትበሏት ብለው በአፍም በመጽሐፍም ይናገራሉ:: ኦርቶዶክሳውያን ድንግል ማርያምን "መድኃኒት፣ ቤዛ" ብለን ስንጠራት በውስጥም በአፋ ያሉ ብዙዎች ባልተረዱት ባላወቁት ባልመረመሩት ነገር እርሷን ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያተካከልናት በእርሱ የማዳን ዙፋን ያስቀመጥናት አድርገው ያስባሉ ይናገራሉም:: ከዚያም አልፈው በክርስቶስ የማዳን ሥራ ላይ የተንሸዋረረ እውቀትና እምነት እንዳለን አድርገው በሌሎች ዘንድ ያጠለሹናል:: ኦርቶዶክሳውያን ያዳነን ማን እንደሆነ ከምን እንዳዳነን ለምን እንዳዳነንና በማዳኑም ሥራ ውስጥ ማዳኑ የተፈጸመለት የሰው ልጅ ሱታፌና ድርሻ ምን መሆን እንደሚገባው ቤተክርስቲያን ታስተምረናለች:: ድንግል ማርያምና ቅዱሳኑን በመንቀፍና በመጥላት ስለ እነርሱም ላለመናገር ዳተኛ በመሆን ለክርስቶስ ያለኝን "ፍቅር" እገልጻለሁ ብሎ መድከም ምንኛ አለመታደል ነው? ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች የ"ፓስተሮቻቸውን የ"መጋቤዎቻቸውን" የ"ነቢያቶቻቸውን" የ"ያድናሉ" መልእክት በፖስተር በብሮሸርና በትላልቅ "ባነሮች" እየለጠፋ ወደ የመስብሰቢያ አዳራሾቻቸው ሰዎችን ይጋብዛሉ : በየጉባኤዎቻቸውም የሚያምኑበትን የራሳቸውን ትምህርት ከማስተማር ይልቅ ኦርቶዶክሳዊነትን እያጨለሙና እያጠለሹ የሌለ ስም እየሰጡ ይሰብካሉ:: ኢየሱስ ክርስቶስ ከምንና ለምን አዳነን? እርሱ ካዳነን ከእኛ ምን ይጠበቃል? የሚሉትን ሀሳቦች ማየቱ እጅግ ሰፊ በመሆኑ ለጊዜው አቆይተነው ወደ ነጥባችን እንመለስ :-

+++ ድንግል ማርያም መድኃኒት አትባልምን ? +++

መልሱ ግልጽ ነው::መድኃኒት ትባላለች:: እርሷ መድኃኒት ማለታችን ግን ከክርስቶስ ጋር አስተካከልናት ማለት አይደለም ሊሆንም አይችልም::በመጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ ብርሃን ተብሏል ቅዱሳንም ብርሃን ተብለዋል:: (ማቴ 5:14 ዮሐ 5:38፣ 8:12) እናስተውል እርሱን ብርሃን ስንለውና እነርሱን ብርሃናት ስንላቸው አንድ አይደለም:: እርሱን ብርሃን ስንለው ቃሉ እንደ አምላክነቱ ይረቃል ይመጥቃል ይረቃልም:: እነርሱን ብርሃናት ስንላቸውም እንደ ማዕረጋቸው እንደ ቅድስና ደረጃቸው ነው። (ማቴ 13: 8 1ቆሮ 15:41) ያ ባይሆን ቅዱስ መጽሐፍ ክርስቶስንም ብርሃን አገልጋዮቹንም ብርሃን በማለቱ እርሱንና ቅዱሳኑን አፎካከረ ያሰኝ ነበር:: ወዳጆቹን ብርሃናት ማለት የእርሱን ብርሃንነት መካድ አይደለም:: እርሱ እንደውም የብርሃናት (የቅዱሳን) አባት ተብሏል:: (ያዕ 1:17) ይህን እንደ መነሻ ካልን እርሷ መድኃኒት መባል እንደሚገባት መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገን በንጽጽር እንመልከት::

+++ ቤዛ እስራኤል ቤዛዊተ ዓለም +++

በብሉይ ኪዳን እስራኤል ዘሥጋን ከግብጽ ባርነት ነጻ ያወጣ በጸናች እጅ በተዘረጋችም ክንድ ለሕዝቡ ቤዛ የሆነ ጠላቶቻቸውን የጣለ እርሱ እግዚአብሔር ነው::እግዚአብሔር ሕዝቡን ከባርነት ነፃ ሲያወጣ ነፃ ካወጣቸውም በኋላ የነፃነት ጉዞ ሲያደርጉ መላእክት ቀን በደመና ሌሊት በብርሃን እንደሚመራቸው ተነግሯቸው ነበር:: (ዘጸ 14:19 ዘጸ 23:20) በዚህ ነጻ የመውጣት ጉዞ ውስጥ ታላቅ ሚናና ድርሻ የነበረው ሰው መስፍኑ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ነበር :: ሕዝቡን ይመራና ያስተዳድር ስለእነርሱም ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ ነበር:: (ዘጸ 32:32) በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር የሆኑት እስራኤላውያን "የሙሴ ሕዝብ" ሲባሉ ሙሴም በፈጣሪው "የሕዝቡ ነፃ አውጪ" ተብሏል:: (ዘጸ 32:7-8) እስራኤል እግዚአብሔርን ባሳዘኑት ጊዜ ሙሴ ስለ እነርሱ በእግዚአብሔር ፊት ባይቆም ኖሮ ያጠፋቸው ነበር:: (መዝ 105:23) ከዚህ ሁሉ የተነሳ እግዚአብሔር ሙሴን ምክንያት አድርጎ ሕዝቡን ከባርነት ነጻ ስላወጣቸው ሙሴ "የእስራኤል ነፃ አውጪና ቤዛ" ተብሏል:: (ዘጸ 32:7-8፣ የሐዋ 7:35) ይህንም መጽሐፍ ሲመሠክር " ይህ ሰው (ሙሴ) በግብጽ ምድርና በኤርትራ ባሕር በምድረ በዳም አርባ ዓመት ድንቅና ምልክት እያደረገ አወጣቸው" ብሏል :: (የሐዋ 7:36)

እስቲ ጥያቄ እናንሣ እስራኤልን ነፃ ያወጣ ማነው? ሙሴ እንዴት ነፃ አውጪ ተባለ? የእስራኤል ቤዛ ማነው? ሙሴ እንዴት የእስራኤል ቤዛ ተባለ? እስራኤል የማን ሕዝብ ናቸው? የእግዚአብሔር የሆኑት ሕዝቡ እንዴት የሙሴ ሕዝብ ተባሉ? ሙሴ በሕዝቡ መካከል ድንቅና ምልክት ካደረገ "ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ድንቅና ምልክቶችን አድርጋለች።" ተብሎ ሲነገር "ይህማ አይሆንም!" ብሎ ሽንጥ ገትሮ መከራከርን ምን አመጣው? (ማር 16:17 ዮሐ 14:15 ::) በሐዲስ ኪዳን ግብጽ የሲኦል እስራኤላውያን የምእመናነ ሐዲስ ጉዟቸው የጉዟችን የገጠሟቸው ፈተናዎች የፈተናዎቻችን ምሳሌዎች እንደሆኑ ተነግሮናል:: (1ቆሮ 10:1-5) በሙሴ ምስፍና እግዚአብሔር ሕዝቡን ከግብጽ ባርነት ነፃ እንዳወጣ ከእርሷ ከድንግል ማርያም በነሳው (በተዋሐደው) ሥጋ እኛን ከሰይጣን አገዛዝ ከሲኦል ባርነት ነፃ አውጥቶናል:: (ዕብ 2:14-16 1ጴጥ 3:19 ዮሐ 1:14-15) በሙሴ ተልእኮ እስራኤል ከግብጽ ወጡ ከድንግል በነሳው ሥጋ ዓለም ከሲኦል ነፃ ወጣ:: በሙሴ ተልእኮ ፈርኦን ተሸነፈ ከድንግል በተዋሐደው ሥጋ በፈጸመው የማዳን ሥራ ዲያብሎስ አፈረ በመስቀሉም ተጠረቀ:: (ቆላ 2:14-16) እስራኤል ከሥጋ ባርነት ከፈርኦን አገዛዝ ነፃ ከወጡበት መንገድ ዓለም ከነፍስ ባርነት ከሰይጣን አገዛዝ የዳነበት መንገድ ይበልጣል :: በእርሱ ምክንያት በተፈጸመው እስራኤልን ነጻ የማውጣት ጉዞ ሙሴ ቤዛ ነጻ አውጪ ከተባለ በድንግል ማርያም በተፈጸመው የማዳን ሥራ ቤዛዊተ ዓለም ብትባል ምን ያንስባታል? እራሷ " ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ ( ማዳኑን ) አድርጓልና።" እንዳለች (ሉቃ 1:49-50)

+++ እርሷ መድኃኒታችሁ ናት +++

በተአምረ ማርያም መቅድም ከሠፈሩ እመቤታችንን እንድንወዳት ከሚያስገነዝቡን ኃይለ ቃላት አንዱ "ውደዷት እርሷ መድኃኒታችሁ ናት" ይላል:: እንግዲህ ይህን አንብበው ነው ሰዎቹ ለምን እንዲህ ትላላችሁ ብለው እንደ ጥህሎ ሊውጡን እንደ እንቀት ሊጠጡን የሚነሥሡብን ሳይመረምሩና ሳይገነዘቡም የሚተቹን :: እነዚህ ክፍሎች እርሷን እንዴት መድኃኒት ትሏታላችሁ? ብለውም ጉንጭ አልፋ መከራከርያ ያነሣሉ:: እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት አዳኝ ነው:: ማዳን የባሕርይው የሆነ እርሱ የወደዳቸውን በፍጹም ልባቸው ያመለኩት ወዳጆቹን ምክንያት አድርጎ በልዩ ልዩ መንገድ ማዳኑን ስለገለጠባቸው መድኃኒት አዳኝ እንዲባሉ ፈቀደ ያድኑም ዘንድ የማዳኑን ጥበብ ገለጠላቸው ኃይሉንም አስታጠቃቸው መንገዳቸውንም አቃና:: እስቲ የሚከተሉትን ለግንዛቤ እንመልከት

👇-ይቀጥላል-👇

2 months, 1 week ago

#ምትረተ ርእሱ ለቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ#

#“እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል”(ማቴ 3፥11)ብሎ ስለ ክርስቶስ ትንቢት የተናገረ ታላቅ ነቢይ፤

#“በነቢዩ በኢሳይያስ፦ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት።”(ማቴ3፥3) ጸያሔ ፍኖት (የክርስቶስ መንገድ ጠራጊ)፤

#“ራሱም ዮሐንስ የግመል ጠጉር ልብስ ነበረው፥ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሀ ማር ነበረ።”(ማቴ3፥4) የተባለለት ታላቅ መናኝ ባሕታዊ፤

#ለንስሐ የሚሆን ጥምቀትን ያጠመቀ ሰባኬ ጥምቀት፤(ሉቃ 3፥6)

#“አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው።”(ዮሐንስ 1፥30) ሲል ስለ ጌታ የመሰከረ ስምዐ ጽድቅ (የእውነት ምስክር)፤

#ጌታችን “እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፥ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ።”(ዮሐ 5፥35) ብሎ የመሰከረለት ድንቅ የጸጋ ብርሃን፤

#“እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም።” ማቴ(11፥11) ተብሎ በጌታ የተነገረለት ታላቅ የሃይማኖት ኮከብ፤

#አምላክን በሥጋ ያጠመቀ መጥምቀ መለኮት፤(ማቴ 3:15-16፤ማር 1:9፤ሉቃ 3:21)

#“እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም።”(ማቴዎስ 14፥4 )
ሲል ሄሮድስን በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮዳድያ ምክንያት ያስተማረና የገሠፀ ሐዋርያ፤

#ሄሮድስ ስለ ክብሩ ተጨንቆ በገዛ መሐላው ተታሎ አንገቱን ያስቆረጠው ሰማዕት፤“ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው።”(ማቴ14፥10)
እንዲል፤

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ዛሬ ክብርት አንገቱ በግፍ የተቆረጠችበት ዕለት ነው።ሄሮድስ ለሄሮድያዳ ልጅ በወጭት የቅዱስ ዮሐንስን አንገት እንዲሰጧት አዘዘ።እግዚአብሔር ባወቀ በርኩስ እጇ የቅዱሱን አንገት እንዳትነካ ነው።

አባታችን ዛሬም እኛ ልጆችህን “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ።”ማቴ3፥1-2 እያልህ ወደ ንስሐ ምራን።ልባችን የደነደነ እኛን "እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ"(ማቴ 3፥7-8) እያልህ ዝለፈን!!!

የቅዱስ ዮሐንስ በረከቱ ይደርብን!!!

#መምህር_ኢዮብ_ክንፈ
ወርኃ መስከረም 2/2017 ዓ.ም

2 months, 3 weeks ago

"ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር"
"የጻድቅ ሞቱ በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።"
መዝ 115:6

- የዛሬው በዓል ደግሞ ልዩ ነው።የጻድቁ አባት የዓለም ብርሃን የኢትዮጵያ ፀሐይ የአቡነ ተክለሃይማኖት በዓለ ዕረፍት ነውና!!!

- ለጻድቁ ክብርም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ክብርት ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን፣15ቱ ነቢያትን፣12ቱ ሐዋርያትን ብዙዎች የሰማይ ሠራዊትን ይዞ አቡነ ተክለሃይማኖት ወደሚገኙበት የደብረ አስቦ ዋሻ ወርዶ ብዙ ቃልኪዳንን ሰጥቷቸዋል።

- የጻድቁስ ሐሳብ በሰማዕትነት አደባባይ ለክርስቶስ ፍቅር ደማቸውን አፍስሰው፣ሥጋቸው ተቆራርጦ፣አጥንታቸው ተከስክሶ ለማረፍ ነበር።በጣም የሚገርመው ይህንን ሐሳባቸውን ለጌታ የነገሩት የቀራቸው ምንም ዓይነት ተጋድሎ ሳይኖር ነበር።ነገር ግን ጌታ ጻድቁ ለእርሱ ያላቸውን ጽኑ ፍቅር ያውቃልና ምንም የቀራቸው እንደሌለና በከፍተኛ የሆድ ሕመም እንደሚያርፉ፤ይህንንም እንደ ስቅለቱና እንደ ሰማዕታት ደም እንደሚቆጥርላቸው ነግሯቸው በዚያ በክብር ዐርፈዋል።

- ዋሻዪቱን ሊነገርና ሊሰማ የማይችል ብርሃንና በዚህ ዓለም የሌለ የልዩ ልዩ የሽቱና የዕጣን መዓዛ ሞልቶባት፤ምድሪቱም እየተንቀጠቀጠች፤የሰማይ ሠራዊት ቅዱስ ዳዊት"ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ምስጋና መኖሪያ ስፍራ እገባለሁና፤ በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና ምስጋና ቃል አሰሙ።"ሲል እንደተናገረ (መዝ 41፥4) በክቡር ዳዊት ምስጋና“እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።”በማለት እያመሰኑ የጻድቁ ነፍስ ከሥጋቸው ተለየች።(መዝ 117፥24)

- ጌታችን የጻድቁን ነፍስ በክብር ተቀብሎ አቅፎ ሳማት።"የጸራሽ ንጽሕት ነፍስ ሆይ" ሲልም አመሰገናት።አባታችንን በሕይወተ ሥጋ ሳለ  እንደነገራቸው በ15ቱ የገነትና በ5ቱ የመንግሥተ ሰማያት አህጉር ላይ ሾመው።አስቀድሞ በቅዱስ ወንጌል
“በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤” ያለ አምላክ ለጻድቁ የመንፈስ ልጆች ይሆኑ ዘንድ በእነዚህ ሁሉ ላይ ሾመው።(ዮሐ 14፥2)

- በጻድቁ ስም ለተራበ ያበላ፤ለተጠማ ያጠጣ፤የየታረዘውን ያለበሰ፤ገድላቸውን የጻፈ ያጻፈ የሰማ፤ለቤተ ክርስቲያናቸው ዕጣን፣ዘቢብ፣ወይን፣ ሜሮን፣ንጹሕ ስንዴ ልዩ ልዩ መባዕ ያገባ፤ለበዓላቸው ለሚዘጋጀው ዝክር ውኃ በመቅዳት፣እንጨት በመፍለጥ፣ቅጠል በመቁረጥ የተራዳ፤በዓላቸውን ደስ ብሎት ያከበረ፤ከእነዚህ ሁሉ ባይቻለው በበዓላቸው ቀን የታመመ የጠየቀ ወይም ያዘነውን ያጽናና፤ በበዓላቸው ቀን ከ ቅዱስ ሥጋው ከክቡር ደሙ የተቀበለውን፤ይህንንም ባይችል ለበዓላቸው ከተዘጋጀው ዝክር የቀምሰ፤ከእነዚህ ሁሉ የተቻለውን አንዱን ቢፈጽም እንደሚምርላቸው ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል።

- ለቅዱሳኑ የሚሰጠውን ቃልኪዳን በተመለከተ ራሱ ጌታችን እንዲህ ሲል ተናግሯል"እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ዋጋው አይጠፋበትም።"(ማቴ 10:40-42)

- የእግዚአብሔር የምሕረቱ ብዛት እንዴት ብዙና ጥልቅ ነው።ጻድቁን የሰጠን አምላካችን እግዚአብሔር ስሙ ይክበር ይመስገን!!!

ጻድቁም በጸሎታቸው በበረከታቸው ይጎብኙን፤በፍጹም ሰማያዊ መስቀላቸውም ይባርኩን፤በፍጹም ሰማያዊ ሥልጣነ ክህነታቸውም ከኃጢአት ማሠሪያ የተፈታን ንጹሐን ለመንግሥተ ሰማያትም የተዘጋጀን ድልዋን ያድርጉን!!! አሜን!!!

#ኢዮብ ክንፈ
  ነሐሴ ተክለሃይማኖት/2016 ዓ.ም

4 months, 1 week ago

"ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሣራ ተመልከቱ።" (ኢሳ 51:2)

ነቢዩ ይህንን ቃል ቅዱስ አብርሃምንና ቅድስት ሣራን ምሰሏቸው ለማለት ተናግሮታል።

#አብርሃም አበ መናንያን (የመናንያን አባት) ነው።ሁሉን ትቶ እግዚአብሔርን ተከትሎአልና።(ዘፍ 12:1)

#አብርሃም የሙሽሮችም አባት ነው።ሚስቱ ምን መካን ብትሆን አልተዋትምና።

#አብርሃም ለሰብዓ ዓለም (በዓለም ለሚኖሩ ክርስቲያኖች) አባት ነው።በሕገ ልቡና ሁኖ ወንጌልን ፈጽሟልና።አረ ግሩም ነው !!! የእግዚአብሔር እንግዳ ቤቴ ሳይመጣ ግብር አላገባም፤እህል አልቀምስም ማለት እንዴት ያለ ብፅዕና ነው!? ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ እንዴት ቢጸኑለት ነው!?ደጉ አባታችን የእግዚአብሔር ሰው አብርሃም  ወንጌልን ሲፈጽማት ተመልከቱልኝማ!!!

#"በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና"(ማቴ 5:3) ትሑቱ አብርሃም ባለጠጋ ሆኖ ሳለ ለእኔ የሚስማማ ደህነትነው፤ባለጠግነትማ የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው በማለት መንፈሱን ዝቅ አድርጎ ራሱን እንዳሳላፊ ቆጥሮ እግዚአብሔር የሰጠውን ለሌሎች ያካፍል ነበር።በዚህም መንግሥተ ሰማያት (የሰማያት መንግሥት) የሆኑ ሥላሴን አስተናግዷል።መንግሥተ ሰማያት የሚባል ጌታም ከእርሱ ዘር ተወልዷል።"የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ።"ማቴ 1:1እንዲል

#“የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና።”
(ማቴ 5:4) ርኅሩኁ አብርሃም ለሦስት ቀናት ያህል ሰው ቤቱ ስላልመጣ እጅጉን አዝኗል።ሥላሴን በማግኘት ተጽናንቷል።

#"ስለ  ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።"(ማቴ 5:6) መፍቀሬ ሰብእ ደጉ አብርሃም ስለ ሰው ፍቅር ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት ተርቧል።ጽድቅ የሚባል እግዚአብሔርን በድንኳኑ ተቀብሎም ጠግቧል (ነፍሱ ተደስታለች) ።

#"ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።"(ማቴ 5:10) የሃይማኖት ሰው አብርሃም እግዚአብሔር "ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ።"(ዘፍ 12:1) ሲለው በፍጹም እምነት ወጥቷል።መንግሥቱንም ወርሷል።

"አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፤አየም ደስም አለው።" ዮሐ8:56 ማለት እንግዲህ  ይህ ነው።በጨለማው ዘመን ሆኖ ብርሃንን ማየት ወንጌልን መኖር!!!ቅድስት ሥላሴን በቤቱ ተቀብሎ"የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተእመለሳለሁ፤ሣራምልጅንታገኛለች።"ዘፍ18፤14 ባለው ቃል መሠረት ለጊዜው ይስሐቅን እንደሚወልድ ለፍጻሜው ክርስቶስ ከእርሱ እንደሚወለድ ኪዳንን ተቀብሏል።

#በሕገ ልቡና ሕገ ኦሪት በሕገ ኦሪት ሕገ ወንጌል በተሰጠን በእኛ ቅዱስ አብርሃም ይፈርዳል፤ከአብርሃም የሚከብር ጌታ በሥጋ አብርሃም ተወልዶ በጥምቀት ልጅነትን፣በልጅነት መንግሥተ ሰማያትን ሰጥቶን የአብርሃምን ሥራ አልሠራንምና።

የአብርሃሙ ሥላሴ በሁላችን ቤት ይደሩ!!!

ሐምሌ ሥላሴ/2016 ዓ.ም
#ኢዮብ ክንፈ

4 months, 3 weeks ago

+++ ተዋሕዶ አእተታ ለምንታዌ! +++

በፍጹም ተዋሕዶ አንድ የኾነ ክርስቶስን እየነጣጠለ በሰውነቱ እንዲህ በመለኮቱ እንዲያ እያለ ሊከፍል የሚሻ አስተሳሰብን ለመንቀፍ ሊቃውንቱ "ተዋሕዶ አእተታ ለምንታዌ" በማለት መጻሕፍትን መሠረት አድርገው ከፊደል ላይ ሳይሆን ትርጓሜን መነሻና መድረሻ አድርገው በስፋት ያስተምራሉ "ተዋሕዶ ኹለትነትን አጠፋ" ለማለት። ሥግው ቃል (Incarnated logos) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተዋሕዶ በኋላ አይነጣጠልም አይከፋፈልም!!

በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆኖ በሥጋ ማርያም የተገለጠ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከኹለት አካል አንድ አካል፤ ከኹለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ነው፡፡ ሥጋም ፍጹም በሆነው ተዋሕዶ የመለኮትን ገንዘብ (ግብረ ባሕርዩን፡- ሁሉን ዐዋቂነት ሁሉን ሰጪነት ልዕልና ምሉዕነት ሁሉን ቻይነት ….) ገንዘቡ አድርጓልና "ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው።" ብሎ ተናገረ፡፡ (ዮሐ 16፥15)

ለአብ ያለው ምንድነው? ለአብ ያለው ዕውቀት፣ ቸርነት፣ ከኃሊነት፣ ጥበብ ሁሉ ለወልድም አለውና የወልድም ጥበቡ፣ ዕውቀቱ፣ ቸርነቱ፣ ከኃሊነቱ ተቆጥሮ ተሠፍሮ አያልቅም ፡፡ ለእኛ ጸሎትን ምስጋናን ሊያስተምረን ሥጋም (ሰውነት) በተዋሕዶ መክበሩን በገለጠበት አንቀጹ "አባት ሆይ ያንተ የሆነ ሁሉ የእኔ ነው የእኔውም ያንተ ነው።" በማለት ተናግሯል፡፡ (ዮሐ 17፥10) ጌታችን ክብር ይግባውና ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር በሥልጣን በሕልውና በአገዛዝም በምልአትም አንድ እንደሆነ በሥጋዌው ወራት ዋና ምሥክርነቱ ነበር፡፡ (ዮሐ 14፥8-11) "የእኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ ባደርገው ግን እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደሆነ እኔም በአብ እንደሆንሁ (በሕልውና፣ በአኗኗር፣ በዕውቀት አንድ እንደሆንን) ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።" ብሎ እንደተናገረ፡፡ (ዮሐ10፥38)

ወልድን መካድ (በወልድ ላይ የክሕደት ንግግር መናገር ) አብን መካድ ነው፡፡ ወልድን በገደምዳሜ ወደ ንስጥሮሳዊ ትምህርት ማስጠጋት አብንም መካድ ነው። ሊቃውንቱ "አብ ሲነክ ወልድ ይነክ።" እንዲሉ። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ "ወልድን የሚክድ አብ እንኳን የለውም በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው።" ብሎ የመሠከረውም ይህን ያመለክተናል፡፡ (1ዮሐ 2፥23)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ
ሠኔ 26 ቀን 2016 ዓ ም
https://www.facebook.com/bitwoded.worku?mibextid=ZbWKwL

Facebook

Log in or sign up to view

See posts, photos and more on Facebook.

5 months ago

"ሕይወትን በሚሰጥ አዳኝ በሆነ ከአብ በሠረጸ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን" (ጸሎተ ሃይማኖት)

#እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በዛሬው ዕለት በእሳትና በነፋስ ተመስሎ ለቅዱሳን ሐዋርያት ወረደ።ይኸውም በቅዱስ ማርቆስ እናት በማርያም ቤት የደስታ መፍሰሻ ወላዲተ አምላክን ከብበው በአንድ ልብ ሲጸልዩ ነው።

#ፍስሕት (ደስተኛዪቱን) ይዘው ቢጸልዩ የደስታ መንፈስ የሆነ መንፈስቅዱስ ወረደላቸው።

#መዝገበ ምሥጢር ድንግል ማርያምን ይዘው ቢጸልዩ ከሣቴ ምሥጢር (ምሥጢርን የሚገልጥ) መንፈስ ቅዱስ ወረደላቸው።በዚህም በሚያውቁት አንድ ቋንቋ ላይ ሰባ አንድ ቋንቋ ተገልጦላቸው ቅዱስ ወንጌልን ሰብከዋል።

#ናዛዚት (የምታረጋጋ) ድንግል ማርያምን ይዘው ቢጸልዩ ናዛዚ (የሚያረጋጋ) መንፈስ ቅዱስ ተሰጥቷቸዋል።

#ንጽሕት ድንግል ማርያምን ይዘው ቢጸልዩ መንጽሒ (ከኃጢአት የሚያነጻ) መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።

#ጽንዕት (የጸናች) ድንግል ማርያምን ይዘው ቢጸልዩ መጽንሒ (የሚያጸና) መንፈስቅዱስን ተቀበሉ።

#መስተሥርዪ ኃጢአት (ኃጢአትን ይቅር የምታስብል) ርኅርኂተ ኅሊና ድንግል ማርያምን ይዘው ቢጸልዩ ኃጢአትን ይቅር የሚል መንፈስ ቅዱስ በእሳት ተመስሎ ወደ እነርሱ መጣ።

#እናታቸውን ይዘው ምን ሊያጡ ኖሯል?ጽዮንን (እመቤታችንን) ከብበው ቢጸልዩ በደብረ ጽዮን የሚኖር መንፈስ ቅዱስ አደረባቸው።

#ይህቺ ቀን የቅድስት ቤተክርስቲያን የልደት ቀን ናት።ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው እንደ ጌታቸው ሁሉ ጾሙ ጸለዩ።መንፈስ ቅዱስ ያደረበት እንደሚጾም እንደሚጸልይ ያጠይቃል።በዓለም ሁሉ ዞረው ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን ሰበኩ።

#አምላካችን መንፈስ ቅዱስ በቸርነቱ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት አማላጅነት ከመፍገምገም ወደ ጽናት ፣ ከኃዘን ወደ ደስታ ፣ ከኃጢአት ወደ ንጽሕና ፣ ከመቅበዝበዝ ወደ መረጋጋት ፣ ከድንቁርና ወደ ዕውቀት ይመልሰን!!! አሜን !!!

#በዓለ ጰራቅሊጦስ

ወርኃ ሰኔ 16 / 2016 ዓ.ም
#ኢዮብ ክንፈ

6 months, 2 weeks ago

ለክርስቶስ ልደት መንገድ የጠረገ ልደት:- ልደታ ለማርያም

እንኳን አደረሳችሁ!!

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ጥንተ አብሶ ካመጣው ፍዳና መርገም ጠብቋታል:: የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ዓለም በጥንተ አብሶ በነበረበት ዘመን በክርስቶስ ማዳን ዋዜማ ሲያበሥራት ቅድስት ኤልሳቤትም በፅንሰቷ ጊዜ ስታመሰግናት ደጋግመው "ጸጋን የሞላብሽ ሆይ" "አንቺ ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ።" እያሉ ይህን እውነት መስክረዋል። (ሉቃ፩:፳፮-፵ በጥንተ አብሶና ውጤቱ (origional sin and its effects) ምክንያት ሰዎች "የእግዚአብሔር ክብር ጎድሏቸዋል በተባሉበት ዘመን ጸጋን የተመላች ብቸኛ ልዩ እርሷ ነበረች:: ።" (ሮሜ ፫:፳፫) እግዚአብሔር እርሷ የዓለም መድኃኒት ክርስቶስን ለመውለድ ፈቃደኛ እንደምትሆን ስለሚያውቅ አስቀድሞ በአካል የሚመስለው በባሕርይ ከእርሱ ጋር አንድ የሆነ አንድያ ልጁን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንድትወልድ ቅድመ ዓለም መርጧታልና የእመቤታችን ልደት (ልደታ ለማርያም) የዓለም መዳን የማይቀር መሆኑ ለታወቀበት ለጌታችን ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት መንገድ የጠረገ ልደት ነው እንላለን። (The nativity of the blessed virgin Mary prepares the way for the birth of Jesus Christ) እንዳለ ሊቁ። (The book of the nativity of Virgin Mary ,) የጌታችን ሰው መሆን "ከዘላለምና (ቅድመ ዓለም) ከትውልዶች ጀምሮ (ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ) ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው።" (ቆላ፩:፳፮) መባሉም የአምላክ ሰው መሆን እንዲሁም የእርሷ እርሱን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለድ ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ሕሊና የሚታወቅ መሆኑን ያስረዳናል። (ኢሳ ፯:፲፬ ፱:፮) እርሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነገሥታት ንጉሥ የጌቶች ጌታ የአማልክት አምላክ ነው። (መዝ ፻፴፭:፩ ራእ፲፱:፲፮) እርሱ ፍጥረትን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ ፈጣሪ ነው:: "ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች ያለ እርሱ አልሆነም።" (ዮሐ ፩:፫) "መልካሙን ነገር ለማድረግ በክርስቶስ ተፈጠርን።" "የሚታዩትና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሁኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና።" እንደተባለ:: (ቆላ ፩:፲፭-፲፮፣ ኤፌ ፪:፲) እርሱ ለቅዱሳን የጸጋ አምላክነትን ክብር የሰጠ ሁሉን ፈጥሮ የሚገዛ የባሕርይ አምላክ ነው:: (ዘጸ ፯:፩፣ መዝ ፹፩:፩፣ ዮሐ፲÷፴፬፣ ሮሜ ፱:፭፣ ፩ተሰ ፫:፲፩፣ ቲቶ ፪:፲፩፣ ፩ዮሐ ፭:፳) እርሱ ቸር ከሆነ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአገዛዝ በሥልጣን በሕልውና በመለኮት አንድ ነው:: (ዮሐ ፲:፴፣ ፲፯:፲፣ ማቴ ፲፩:፳፯-፳፱፣ ዮሐ ፲፬:፮-፰) እርሱ ፀሐይ እናቱ ምሥራቅ ናት:: (ሕዝ ፵፬:፩፣ ዮሐ ፰:፲፪፣ ሚል ፬:፪) ምሥራቅ እናቱን ዘወትር መሻታችን የፀሐይ ክርስቶስን በረከት ፍቅርና ቸርነት ለማግኘት ነው:: እንኳንስ እናቱን ነቢዩ ዳዊት ስለ ወዳጆቹ "ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው ስለዚህም ነፍሴ ፈለገቻቸው።" ብሎ ዘምሯል:: (መዝ ፻፲፰:፻፳፭) እርሱ የባሕርይ አምላክ እርሷ ደግሞ ወላዲተ አምላክ ( Theotokos) ናት:: ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ከተፈጠረም በኋላ መቸም መች አምላክን "ልጄ ወዳጄ" ማለት ከቶ ለማን ተችሏል? እርሱ ፈጣሪ እርሷ ደግሞ ወላዲተ ፈጣሪ ኩሉ ዓለም ናት:: እርሱ እውነተኛ ደስታ እርሷ የደስታ መፍሰሻ ናት። (መዝ ፵፭:፭) እርሱ ሕይወት እርሷ ነቅዐ ሕይወት (የሕይወት ምንጭ) ናት። ይህች ብርሃን ሙዳየ መድኃኒት ቤዛዊተ ኩሉ ብርሃንን ትሰጠን ሕይወት ክርስቶስን ትወልድልን ዘንድ ከተቀደሱ ተራሮች ከአብርሃም ከዳዊት ቤት ተወለደች። (መዝ ፹፰(፹፱):፩)

+++ የልደቷ ቀን +++

አንተ የራስህን እንዲሁም የምትወዳቸውን ሰዎች ልደት ሻማ አብርተህ ኬክ አስጋግረህ ወዳጅ ዘመዶችህን ጠርተህ በዳንስ በጭፈራና እስክስታ በመውረግረግ ታከብራለህ የአምላክ እናት ድንግል ማርያም የተወለደችበትን ቀን በማሰብ በዓለ ልደቷን የሚያከብሩ ሰዎችን ግን ለምን ያከብራሉ ብለህ ትተቻለህ:: ለመሆኑ አንተ ያንተ የሆኑትን ሰዎች ልደት ተገቢ በሆነ መንገድ ብታከብር አምላክ እንደማያዝንብህ ካወቅህ የእናቱን ልደት እርሱን እያመሰገንን እያወደስን እናቱ "ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል።" (ሉቃ ፩:፵፱) እንዳለችም እርሷንም እያመሰገንን "ብርቱ የሆን እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጓልና።" ብላ እንደመሠከረችም በእርሷ ለሰው ዘር የተደረገውን ታላቅ ሥራ እያሰብን ብናከብር የሚያዝንብን ይመስላሃልን? ከማዳኑስ በላይ ምን ታላቅ ሥራ አለ? ዓለም:- የኤድስ ቀን፣ የጉበት ቀን፣ የኩላሊት ቀን፣ የላብ አደር ቀን፣ የውሃ ቀን፣ የአፈር ቀን፣ የእናቶች ቀን፣ የአባቶች ቀን እያለ በልዩ ልዩ መንገድ ሲያከብር ቅር አይለውም የእናቱ የእመቤታችንን ልደት ለማክበር ግን ያመዋል::
ልደታ ለማርያምን ስናከብር

☞ ቤተ ክርስቲያንን በሚያስነቅፍ አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት በዳንኪራና በአስረሽ ምስናከብር
ሆን በመንፈሳዊ ሥርዓት እናክብረው ያኔ የልጇ በረከት እጥፍ ድርብ ይሆንልናል። (ምሳ ፲:፯፣ ፩ጴጥ ፪:፲፪)
☞ የቤተክርስቲያን ባልሆነ የልደቷን ነገር በማይገልጥ በማይወክል መንገድ በአምልኮ ባዕድ ጨሌን በየዛፉ ዙርያ አረቄና ቡና በማፍሰስ የሚያከብሩትን ሰዎች በማስተማርና ትክክለኛውንና የክርስትናውን መንገድ በተከተለ መንገድ እንዲያከብሩት በማድረግ ድርሻችንን በመወጣት እናክብር ::
☞ ልደቷ "በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል።" ከተባለለት ከዮሐንስ ልደት የሚልቅ መሆኑን እንወቅ። እርሷ የዮሐንስ ፈጣሪ የክርስቶስ እናቱ ናትና። ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም " ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው እርሱም እናቱን ፈጠረ።" እንዳለ:: እርሱ ክርስቶስ "ሁሉን በስሜ አድርጉት" እንዳለን እርሷን በእርሱ ስም ወላዲተ አምላክ እመ ብርሃን ብለን ተቀብለን ልደቷን እንደምናከብር እንረዳ:: (ሉቃ ፩:፲፬)

+++ አድባር +++

አድባር የሚለው ቃል የግእዝ ሲሆን ትርጉሙም ተራሮች ማለት ነው:: እመቤታችን በሊባኖስ ተራሮች መሐል ተወልዳለችና የልደቷን ወቅት አድባር እንላለን። (መኃ ፬:፰)

?የእናቱን በዓለ ልደት ማክበር ማኅበራዊ ፋይዳ ?

በዚህ ቀን የአንድ ቀዬ ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው ጸሎት በማድረግ እግዚአብሔርን በማመስገን እናቱንም በማወደስ ማክበራቸው ከሃይማኖታዊው ፋይዳ ባለፈ በልዩ ልዩ ምክንያት እየደበዘዘና እንደ ዳይኖሰርና ዶዶ ድራሹ እየጠፋ የመጣውን አብሮነት ማኅበራዊ ትስስር የሚያጠነክር መልካም ባሕላችንም ጭምር ነውና አጥብቀን ልንይዘው ይገባናል:: የድንግል ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ የልደት ቀን በረከት ያሳትፈን!!!

©️ መምህር ቢትወደድ ወርቁ
ሚያዝያ ፴ ቀን ፳፲፮ ዓ ም

We recommend to visit

★ሰውን በማዝናናት የብቃት ማረጋገጫ ያለው ብቸኛው ቻናል ሁሌም Telegram ላይ በጥበብ ደምቀን እናሸበርቃለን

💌 Contact us, @Modenyazbot

»የተመረጡ እና ማንም ያላያቸው የአማሪኛ ቀልዶች እንዲሁም የሚያስደንቁ ስዕሎችንና ቪዲዮ ያገኛሉ።

° ° [ ሙድ እንያዝ በእኛ የአራዶች መዝናኛ ] ° °

° ° Creator @Teke_Man ° °

Last updated 1 month, 1 week ago

☕ ስለ ኢትዮጲያ ቡና የሚወጡ ወቅታዊና ትክክለኛ የክለቡ መረጃዎች አዚህ ያገኛሉ!

➪የዝዉዉር ዜና
☞የአሰልጣኞች አስተያየት
➪ጎሎች እና ቪዲዮዎች
☞የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
➪ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት ከየስታድየሙ !

➡መወያያ ግሩፓችን @Ethiopia_coffee_Sc

📩ሀሳብ ወይም አስተያየት ካሎት
በዚህ 👉 @EthiopianCoffeeScBot ✍
BOT ማድረስ ይችላሉ!

Last updated 3 months, 2 weeks ago

ማንኛውንም የማስታወቂያ ስራ ለማሰራት የምትፈልጉ(only promotion) inbox @Eyyiba
ሌሎች ጥያቄዎችን ለማድረስ
@Ethiodailyvacbot

Last updated 1 day, 11 hours ago