★ሰውን በማዝናናት የብቃት ማረጋገጫ ያለው ብቸኛው ቻናል ሁሌም Telegram ላይ በጥበብ ደምቀን እናሸበርቃለን
💌 Contact us, @Modenyazbot
»የተመረጡ እና ማንም ያላያቸው የአማሪኛ ቀልዶች እንዲሁም የሚያስደንቁ ስዕሎችንና ቪዲዮ ያገኛሉ።
° ° [ ሙድ እንያዝ በእኛ የአራዶች መዝናኛ ] ° °
° ° Creator @Teke_Man ° °
Last updated 2 months, 1 week ago
☕ ስለ ኢትዮጲያ ቡና የሚወጡ ወቅታዊና ትክክለኛ የክለቡ መረጃዎች አዚህ ያገኛሉ!
➪የዝዉዉር ዜና
☞የአሰልጣኞች አስተያየት
➪ጎሎች እና ቪዲዮዎች
☞የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
➪ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት ከየስታድየሙ !
➡መወያያ ግሩፓችን @Ethiopia_coffee_Sc
📩ሀሳብ ወይም አስተያየት ካሎት
በዚህ 👉 @EthiopianCoffeeScBot ✍
BOT ማድረስ ይችላሉ!
Last updated 4 months, 3 weeks ago
ማንኛውንም የማስታወቂያ ስራ ለማሰራት የምትፈልጉ(only promotion) inbox @Eyyiba
ሌሎች ጥያቄዎችን ለማድረስ
@Ethiodailyvacbot
Last updated 1 month ago
እንኳን ለጻድቁ አባታችን ለአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እረፍት ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
#ዋኖቻችሁን_አስቡ። ዕብ 13:7
ይህን ኃይለ ቃል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለጊዜው ለዕብራውያን ሰዎች የተናገረው ሲሆን ፍጻሜው ግን በክርስቶስ ክርስቲያን ለተሰኘን ለኛ ለምዕመናን ሁሉ ነው።
ዋኖቻችን እነማን ናቸው ቢሉ ሐዋርያው «የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁ» በማለት መልሶልናል። እነርሱም ከቀደምት አበው ጀምሮ ነቢያት ሐዋርያት ጻድቃን ሰማዕታት በሙሉ ቅዱሳን ናቸው።
ጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስም ገብረ ሕይወትም ይባላሉ።በ562 ዓመታት ሕይወታቸው እንደ ሐዋርያት ከምድረ ግብፅ እስከ ኢትዮዽያ ወንጌልን ሰብከዋል። በዚህም በሚሊየን (አእላፍ) ለሚቆጠሩ ነፍሳት የድኅነት ምክንያት ሆነዋል። “በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን።” ሮሜ 14፥8 እዳለው ቅዱስ ጳውሎስ ሕይወታቸውን ለክርስቶስ የሰጡ ወንጌልን(የእግዚአብሔርን ቃል) በቃላቸው የሰበኩት ብቻ ሳይሆን አካል አልብሰው ሚዳሰስ ሚታይ አድርገው የኖሩት የዕምነትን ፍሬ ያስመሰከሩ ታላቅ ቅዱስ የቤተክርስቲያናችን አባት ናቸው የንሒሳው ኮከብ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቀር አላቸው። ስለ ሃገሪቱና ሕዝቧ ፍቅር ሲሉ ለ100 ዓመታት በደብረ ዝቋላ መከራን ተቀብለዋል። ምሕረትን ሲለምኑ ሥጋቸው አልቆ በአጥንታቸው ቁመው ነበርና ሃገራችን አሥራት ሆና ተሰጠቻቸው። በ8ኛው ክ.ዘ አካባቢ የተወለዱት አባታችን ያረፉት በ14ኛው መቶ ክ.ዘ አካባቢ ነው። ፍጥረታትን ሁሉ አዘው መጋቢት 5 ቀን ሲያርፉ ግሩማን መላእክት ገንዘው አካላቸውን ሠውረዋል። ጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ እረፍታቸው መጋቢት 5 ቀን ነው ይህ ደግሞ በታላቁ ዓብይ ጾም ወቅት ነው ፍትሃ ነገስት አንቀጽ 15 ላይ በዓብይ ጾም በዓል ማክበር ይከለክላል የሀዘን ወቅት ነውና ከበሮ አይመታም እልልታና ጭብጨባ የለም ፍጹም ሀዘን እንጂ የመጋቢት 27 ስቅለት ጥቅምት 27 ቀን እንደሚከበረው ሁሉ ወደ ጥቅምት 5 ቀን ተዛውሮ እንዲከበር ተደረገ፡፡
በመጨረሻም ሐዋርያው እንዳለን ቅዱሳኑን አስበን የነርሱን አሰረ ፍኖት ተከትለን በምግባር በሃይማኖት እንድንመስላቸው አምላካችን በቸርነቱ ይርዳን። እመ አምላክ ወላዲተ አምላክ ሰዓሊተ ምሕረት ፍቅሯን በልባችን ጧዕሟን በአንደበታችን ታኑርልን። የጻድቁ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን።
መልካም በዓል🤗!
#ለሌሎች_ተደራሽእንዲሆን_ሼር_ማድረግ_አትዘንጉ👇👇
🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹
https://t.me/orthodoxzelalemawit
ሊንኳን ይጫኑ
🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹
+++++++#በበጎነት_መጽናት#+++++++++
ማር ወግሪስ እንዲህ ይላል፦ "ዳግመኛም ስማኝ ልንገርህ! ለዘለዓለም ላንተ ይብስብሃልና ባደርክበት ኹሉ ቃልህን አትለውጥ። በሰዎች መካከል ጥልን አትዝራ፤ አነዋወርህ ኹሉ በሰላም ይኹን፤ ወደ ልቡናህም ቍጣን አታስገባ፤ ወንድምህ የበደለህን ከቶ አታስብ። የቍጡ ሰው ድካሙ ኹሉ በዐይን ጥቅሻ በከንፈር ንክሻ ፈጥኖ ያልፋልና። ቂምን በልቡናው የሚያኖር ሰው የሰይጣን ደቀ መዝሙሩ ነው፤ የዘለዓለም ሕይወትንም አያያትም። ማንንም ማንን አትማ፤ ከማንም ጋር አትከራከር፤ የባልጀራህን ንብረት አትመኝ የሌላውንም አትቀማ።
ሐሜተኛ ሰው የእግዚአብሔር ጠላቱ ነው። በጠላትህ ውድቀትና ሞት ደስ አይበልህ፤ ባዘኑት ላይ አትሣለቅ፤ ለዕውሩ መሰናክል አታኑርበት። ስትጸልይ ለመቀመጥ አትቸኩል፤ ለጸሎት ዝግጁ ኾነህ በቆምክበት ቦታ ኹሉ አትነቃነቅ፤ በመካነ ጸሎትህ ላይ አዘውትረህ ቆመህ ተገኝ። ለለመነህ ኹሉ ስጥ፤ ከሌለህ ደግሞ እግዚአብሔር ይስጥህ ካለው ያድርስህ ብለህ በለዘበ ቃል ተናገር። የምትሠራውን ሥራ ኹሉ ፊት አይተህ አድልተህ አትሥራ። የደረሰብህን ኹሉ እግዚአብሔርን አመስግነህ ተቀበል። ይህንን ያደረግህ እንደ ኾነ በእግዚአብሔር ትእዛዛትና ሕግጋት አንተ በእውነት ፍጹም ነህ። እኔስ በእውነት የእግዚአብሔርን ጥበብ አደንቃለሁ።" እንዲል። (አባ ገብረ ኪዳን ግርማ ፣ የአራቱ ጉባኤያት የምስክር መምህር)፣ መጽሐፈ ወግሪስ፣ 2013 ዓ.ም፣ ገጽ 51)።
የሕይወት መርሐችን ከላይ በተገለጸው መሠረት ቢኾን በበጎ መጽናት እንችላለን። ክፉ ነገር በሕሊናች ውስጥ በመጣ ጊዜ ወዲያው አስወግደን ብናስወጣው እና ሕሊናችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ኹል ጊዜ ብናስቀምጥ፥ በዚያም ቃል ብንመሰጥበት ሕይወታችን የተስተካከለ ይኾናል። ድንገት ስሜታዊ ኾነን ወደ ክፉ ልንሳብ ስንል ራሳችንን የምንቆጣጠርበት የእግዚአብሔር ቃል ውስጣችን ሊኖር ይገባል። በእርግጥም የሕይወት መርሐችንን በቃለ እግዚአብሔር እያደረግን ስንሄድ ስሜታችን በራሱ በቃለ እግዚአብሔር እየተገራ ይሄዳል። ውስጣችንም በቃለ እግዚአብሔር መመራትን እንደ ግዴታ መቀበል ይጀምራል። እንዲህ ሲኾን ብንጣላ ወዲያው ይቅር እንባባላለን፥ ቢበድሉን እንታገሳለን፥ ቢሰድቡን ስድብ የሚገባን ኃጥእ እንደ ኾን አድርገን እንቀበላለን፣ ቢንቁንም የክፉ ሥራችን ውጤት መኾኑን አምነን ያለተቃውሞ እንቀበላለን። እንዲህ በበጎ እየጸናን ስንሄድ የሚረብሸን ነገር በእኛ ላይ ኃይሉን እያጣ ይሄዳል፤ ሕይወታችንም በፍጹም ሰላምና ዕረፍት ይመላል።
እንግዲህ ምክንያታዊ ነኝ ብለን ከምናስበው አጸፋዊ መልስ ኹሉ እየራቅን እንሄዳለን። እንዲህ ያደረግኹት እንዲህ ስላደረገችኝ/ገኝ ነው እያሉ ከመናገር ኹሉ ነጻ እንወጣለን። በሕይወታችን የሚገጥሙንን ችግር የምንላቸውን ነገሮች ኹሉ የመጋፈጥና የማሸነፍ ብርታታችን ታላቅ ይኾናል። የብዙ ዓመታት ሕማም ቢኾን፣ ወይም የገንዘብ እጦት ችግር ቢኾን፣ ወይም ከሰዎች ዘንድ ፍቅር አጣኹኝ ብሎ የማሰብ ፈተናም ቢኾን እንሻገረዋለን። መጀመሪያ መስተካከል ያለበት አስተሳሰብ እና ነገሮችን የምንረዳበት መንገድ ነው። ሲቀጥልም የመኖር ትርጒሙና ዓላማው ግልጽ ኾኖ ሊገባን ያስፈልጋል። ይህ በትክክል ሲገባን ያን መፈጸም ዋና ዓላማችን እየኾነ ይመጣል። ስለዚህ ሰይጣን ሊጥለንና ጥቅም አልባ ሊያደርገን የሚፈጽምብን ጥቃት ኹሉ ይከሽፋል። በበጎነት ጽናታችንም ድል ይነሣል። ስለዚህ ስንኖር ለምንድን ነው የምኖረው? እንዴትስ እንድኖር ነው ፈጣሪ የሚፈልገው? ፈጣሪስ እንደሚፈልገው መኖር ያልቻልኩት ለምንድን ነው? ለመኾኑ በበጎነት ጸንቼ እንዳልኖር የሚከለክለኝ ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ለራሴ እየጠየኩ ሕይወቴን እያስተካከልኹኝ ልኖር ይገባኛል። በምን መመሪያ እንዳንል ከላይ ማር ወግሪስ ያስቀመጠልን ድንቅ የሕይወት መመሪያ አለልን።
ዲ/ን ዮሐንስ ጌታቸው
ለመኖር የተፃፈ✍📜
#ለሌሎች_ተደራሽእንዲሆን_ሼር_ማድረግ_አትዘንጉ👇👇
🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹
https://t.me/orthodoxzelalemawit
ሊንኳን ይጫኑ
🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹
ስለ " ቅዳሴ" መሰረታዊ እና መታወቅ ያለባቸው ነገሮች
1⃣. ቅዳሴ ምንድነው ? What is "Liturgy"?
"ቅዳሴ" ማለት "ቀደሰ" ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ የምሥጋና ቃል ነው ። አመስጋኙ የሰው ልጅ ሲሆን ተመስጋኙ ፈጣሬ ዓለማት ( የዓለማት ፈጣሪ ) የሆነው ቅዱስ እግዚአብሔር ነው እርሱ የሚመሰገነው በሰው ብቻ ሳይሆን በፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ ነው ። ( ኢሳ 6:3 ፣ ራዕ 4:8 ፣ ሉቃ 2:13 - 14 ፣ ሐዋ 16:25 ..........)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን "ቅዳሴ" የሚለው ቃል ቅዱስ ቁርባን የሚከብርበትን አገልግሎት ሲያመለክት "ምስጋና" የሚለው ትርጉሙ ደግሞ (ጽርእ) ቃል "ኤቭኻሪስቲያ" (Thanksgiving) አቻ ነው ። ከምስጋና ባሻገር "ቅዳሴ" የሚለው ቃል "ቅድሳት" በመባል የሚታወቀውን የጌታን ሥጋውንና ደሙን ተቀብለው ካህናቱና ምእመናኑ የሚያገኙት የቅድስና ሕይወትን ያመለክታል ።
ቅዳሴ እና ቅዱስ ቁርባን ስለማይለያይ "ቁርባን" ምን ማለት እንደሆነ እንይ እና ወደሌላው እንቀጥላለን
⏺ቁርባን :- የሱርስት ቃል ሲሆን ፍቺውም መባእ እና ስጦታ አምሀ ማለት ነው ። በመስቀል ላይ የተሰጠን ሥጋና ደም ሳይገባን በነጻ በችሮታ የተሰጠን ስለሆነ ነው ስጦታ የተባለው ። ምሥጢረ ቁርባንን የመሰረተው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። የመሰረተውም በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ነው። በማስተማር ዘመኑም ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው ብሎ አስተምሯል ( ዮሐ 6:56 ፣ ማቴ 26:26 ) በዚሁ አምላካዊ ትምህርት ክርስትያን የሆነ ሁሉ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን መቀበል ይኖርበታል ። በዚህ አምኖ ያልተቀበለ ርስተ መንግሥተ ሰማያትን አያገኝም ፣ አይድንም ።
2⃣ . በቤተክርስቲያናችን ስንት አይነት ቅዳሴዎች አሉ ?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ለትምህርተ ሃይማኖትና ለጸሎት እንደዚሁም ለአምልኮተ እግዚአብሔር ከምትገለገልባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ አሥራ አራቱ መጻሕፍተ ቅዳሴ ነው ።
ይህ መጽሐፈ ቅዳሴ በቁጥር 1⃣4⃣ ሲሆን በሥርዓት አፈጻጸሙ ግን ሦስት ክፍሎች አሉት ።
እነሱም ⤵️⤵️⤵️
ሀ) ሥርዓተ ቅዳሴ (የዝግጅት ክፍል ወይም ግብዓተ መንጦላዕት ) :- Preparation service
"ኦ እኁየ ሀሉ በዝንቱ ልቡና....." ከሚለው ጀምሮ
" ሚ መጠን ግርምት ......." እስከሚለው ያለው ነው ።
ለ) ጸሎተ አኮቴት (የትምህርት ወይም የንባብ ክፍል) :- Didactic service
" ሚ መጠን ግርምት ....." ከሚለው ጀምሮ
" ፃኡ ንዑሰ ክርስትያን " እስከሚለው ድረስ ያለው ክፍል ነው ።
ሐ) አኮቴተ ቁርባን ( ፍሬ ቅዳሴ) :- Eucharistic service
"ፃኡ ንዑሰ ክርስትያን" ከተባለ በኋላ ያለውን ክፍል ነው።
👉 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥጋውና ደሙን የምታከብርባቸው 1⃣4⃣ ቅዳሴያት አሏት ።
እነሱም ⬇️⬇️⬇️
1⃣.ቅዳሴ ሐዋርያት ( Anaphora of the Apostles)
2⃣.ቅዳሴ እግዚእ (Anaphora of the Lord)
3⃣.ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ (Anaphora of st. John the son of thunder)
4⃣.ቅዳሴ ማርያም( Anaphora of st.mary)
5⃣.ቅዳሴ ሠለስቱ ምዕት(Anaphora of the 318 Orthodox fathers)
6⃣.ቅዳሴ አትናቴዎስ( Anaphora of Athanasius)
7⃣.ቅዳሴ ባስልዮስ(Anaphora of Basil)
8⃣.ቅዳሴ ጎርጎርዮስ(Anaphora of Gregory of Nyssa)
9⃣.ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ( Anaphora of Epiphanius)
🔟.ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ(Anaphora of John chrystosom)
1⃣1⃣.ቅዳሴ ቄርሎስ(Anaphora of Cyril)
1⃣2⃣.ቅዳሴ ያዕቆብ ዘሥሩግ(Anaphora of Jacob of sarug)
1⃣3⃣.ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ(Anaphora of Dioscoros)
1⃣4⃣.ቅዳሴ ጎርጎርዮስ ካልዕ(Anaphora of Gregory of Nazianzus )
ይህ ታላቅ ምሥጢር የሚፈጸምበት አገልግሎት ከልዑል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጠ የፍቅር ስጦታ ነው። ስለሆነም ቅዳሴ የክርስቶስን ሕማም ሞትና ትንሣኤ እያሰብን እግዚአብሔር አብ በአንድ ልጁ ሞት ላሳየን ዘለአለማዊ ፍቅር ምስጋና የምናቀርብበት አምልኮ ነው ።
#ቅዳሴ የአዲስ ኪዳን መሥዋዕት የሚቀርብበት ዐቢይ ሥርዓተ አምልኮ ነው ።
*ቅዳሴ የክርስቶስን የማዳን ሥራ እውን የሚያደርግልን የምስጋና አገልግሎት ነው።
*ቅዳሴ በምድር ላይ ያለ ሰማያዊ አገልግሎት (Heaven on earth service) ነው ።
*ቅዳሴ የሰማያዊው አምልኮ ነጸብራቅ ነው።
*ቅዳሴ በደስታና በሐሴት የሚከናወን አምልኮ ነው።
(አኮቴተ ቁርባን ፣ቀሲስ ዶ/ር መብራቱ ኪሮስ ፣ ገጽ 3)
➡️ዋቢ መጻሕፍት 👇
"አኮቴተ ቁርባን" በቀሲስ ዶ/ር መብራቱ
ፅጌም አይደል በአበባዎች እያሸበረቅን እናስባት🥰
🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹
https://t.me/orthodoxzelalemawit
ሊንኳን ይጫኑ
🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹
"በእርግጥ ሕዝቡ ለበዓላት ትርጓሜ ስንሰጥ ባየንበት መንገድ እግዚአብሔርን በሆታና በእልልታ የሚያመሰግንበት ፣ ደስታውንም የሚገልጽበት በዓል ነው። ስለዚህ እነዚህን በዓላት ከዚህ ባለፈ ማክበር እንዲገባ የጻፈ የለም። አንድ ሰው ይኸን ማድረግ ሳይችል ፣ ወደ ቤተክርስቲያን ሳይሄድ ፣ እግዚአብሔርን ሳያመሰግን ፣ ሳያስቀድስ ፣ ቃለ እግዚአብሔር ሳይማር እቤቱ በመቀመጡ ብቻ በዓሉን አክብሯል ሊባል አይችልም። ምክንያቱም በዓል ማክበር ሥራ ፈትቶ በሐሜት ፣ በጸብ ፣ በክርክርና በአሉባልታ የሚያሳልፉት ነገር አይደለምና ። ስለዚህ በዓላቱን እናከብራለን የሚሉ ሰዎች አስቀድመው ማድረግ ያለባቸውን ግዴታ አውቀውና ተረድተው መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ሥራ መተው የሚያስፈልገውም ለማስቀደስ ፣ ለመጸለይ ፣ ቃለ እግዚአብሔር ለመስማትና ፣ በማኅበር እግዚአብሔርን ለማመስገንና ለማገልገል እንጂ ለዋዛ ለፈዛዛ ጉዳይ አይደለም ።"
(በዓላት ምን? ለምን ? እንዴት? ፣ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ፣ ገጽ 169 -170)
#ለሌሎች_ተደራሽእንዲሆን_ሼር_ማድረግ_አትዘንጉ👇👇
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
https://t.me/orthodoxzelalemawit
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
"አንዳንድ ፍሩሃነ ንሥሐና እኩያነ ምግባር የሆኑ ሰዎች ከክፋታቸው ሳይመለሱና ንስሐ ሳይገቡ በድፍረትና በማን አለብኝነት መንፈስ አንድ ቀን በቅዱሱ በዓል ስለመጡ ፣ ቦታውን ስለረገጡና የተቻላቸውን ስላደረጉ "ቦታህን የረገጠውን ፣ እንዲህ ያደረገውን .....እምረዋለሁ" የሚለውን ብቻ በመስማት በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ እንዳይዘብቱ አስጠንቅቆ መንገሩና ወደ ንስሐ እንዲመለሱ ፣ በጎ ሥራ እንዲሰሩና ክፋታቸውን እንዲተው ማስተማር ያስፈልጋል ። እግዚአብሔር ለሰሎሞን ያለውን ማሰብ ያስፈልጋል ።
1ኛ ነገሥት 9
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³ እግዚአብሔርም አለው፦ በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ።
⁴ ዳዊትም አባትህ በየዋህ ልብና በቅንነት እንደ ሄደ አንተ ደግሞ በፊቴ ብትሄድ፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዓቴንም ፍርዴንም ብትጠብቅ፥
⁵ እኔ፦ ከእስራኤል ዙፋን ከዘርህ ሰው አታጣም ብዬ ለአባትህ ለዳዊት እንደ ተናገርሁ፥ የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።
ምክንያቱም እግዚአብሔር ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን ያጸናው ወይም የሚጠብቀውም ሰሎሞን በትእዛዘ እግዚአብሔር ሲኖር ነውና። "ዳዊትም አባትህ በየዋህ ልብና በቅንነት እንደሄደ አንተ ደግሞ ብትሔድ" የሚለው ይህን ያስረግጥልናል።
ስለዚህ በዓላትን እንደ ክርስትያን ማክበር የሚለው በቤተክርስቲያን ተሰባስቦ በመማር ፣ በመጸለይ ፣ በማስቀደስና ሥጋውን ደሙን በመቀበል ሊሆን እንደሚገባ ማስተዋል ያስፈልጋል ።
(በዓላት ምን ? ለምን ? እንዴት ? ፣ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ፣ ገጽ 162-163)
#ለሌሎች_ተደራሽእንዲሆን_ሼር_ማድረግ_አትዘንጉ👇👇
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
https://t.me/orthodoxzelalemawit
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
ዌል ትንሽ ማብራሪያ ዋቄፈታ ላይ..
ቅዱስ ጳውሎስ የአቴና ሰዎችን እንዲህ አላቸው:
“..የአቴና ሰዎች ሆይ፥ እናንተ በሁሉ ነገር #አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ። የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ፦ #ለማይታወቅ_አምላክ፡ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ።”
[ሐዋ 17: 22]
እነርሱ የማይታወቅ አምላክ ብለው የሚያመልኩት ጣኦትን ሊሆን ይችላል ግን እውነተኛው እርሱ ሳይሆን ይሄ ነው ብሎ ያሳያቸዋል ማለት ነው..
የዋቄፈታ ሰዎችም ደግሞ አይተውትም ሆኖ ድምጹን ሰምተውት የማያውቁት አምላክ አላቸው.. የሁሉ ፈጣሪ እንደሆነም ያስባሉ.. እንግዲያውስ ይህ ዓይነት ክብር የሚገባው ለእውነተኛው አምላክ የኢየሱስ አባት ነው.. ልጁ ኢየሱስም ከአባቱ እንደመገኘቱ ከእርሱ ጋር አንድ የሆነ ጌታ ነው..
እና በዚህ አምነው አምልኮዋቸውን እንዲያስተካክሉ እና ከፈጣሪያቸው ጋር እንዲገናኙ ጥሪ ማቅረብ ማለት ነው.. ያው በፍቅር እና በትህትና..
ኦርቶዶክሳዊ ልጆችን ማስተማር
በቤተ ክርስቲያን የኦርቶዶክሳውያን ልጆችን ማስተማር የተለመደ ነው። በተለይ በውጭው ዓለም ላሉ ኦርቶዶክሳውያን ልጆችን ስለ ሃይማኖታቸው ስለ ሀገራቸው ለማስተማር የወላጅ ትልቁ ፍላጎትና ስቃይ ነው። ይኹን እንጂ ኹለት ትልልቅ ፈተናዎች እንዳሉ እገነዘባለሁ።
አንደኛው ምእመኑም ካህናቱም ለልጆች የሚሰጡት ቦታ ዝቅተኛ ከመኾኑ ባሻገር ከእቅድና ወሬ ያለፈ አለመሆኑ ነው። እኔም ለመረጃ ስጠይቅ “ከተወራ ይበቃል” አይነት መልስም ሰምቻለሁ። ከልባቸው በትክክል እያስተማሩ ያሉ ጥቂት አጥቢያዎች ይኖራሉ።
ኹለተኛው ደግሞ የምናስተምርበት መንገድ ነው። በጥቂት አብያተ ክርስቲያናት ራሱን ችሎ በተመደቡ በብዛት ግን ወላጅ አልያ ፈቃደኛ በኾኑ ምእመናን የሚሰጥ የልጆች ትምህርት ነው። እኔ በጥቂቱ ለመታዘብ በሞከርኩት እንኳን ለማስተማር ቀርቶ የሚናገሩን ምን እንደኾነ እንካ የማያውቁ ብሎም ስህተት መረጃ ለልጆች የሚሰጡ “የልጆች አስተማሪዎች” እንዳሉ ታዝቤያለሁ።
ሌላው ልጆቹን የሚያስተምሩት ወላጅ እያስቀደሰ ልጆች እንዳይረብሹ አንድ ክፍል ውስጥ ዘግቶ ማንጫጫት ወይም ማስተማር ነው። ፊደል አልያ ዓረፍተ ነገር ማሰራት። ይኽ ትምህርት ሳይሆን ልጆቹ እንዳይረብሹ ማድረግ ነው ዓላማው።
በተጨማሪም ኦርቶዶክሳዊ የልጆች ትምህርት ምንድነው የሚለው በደንብ መለየት አለበት። በውጭው ዓለም እንዳየሁት ልጆች የሚማሩት በቅዳሴ ሰዓት ሲሆን ለቁርባን ተሰልፈው ይመጣሉ። ይኽ በብዙ ምክንያት እንደሆነ ብረዳም በጣም ጎጂ ከመሆኑ በላይ ስህተት ነው። የኦርቶዶክስ ትምህርት ከክርስቶስ ጋር የምንኖረው የሱታፌ ሕይወት እንጂ እውቀት ብቻ አይደለም። ስለሆነም የምንማረው በተሳትፎ በተግባር ነው። ልጆች ቢረብሹም ከወላጆች ስር ሆነው ማስቀደስ አለባቸው።
በቅዳሴ ወቅት በር ዘግተን ከምንማረው ትምህርት ይልቅ በቅዳሴ ተሳትፈው ሲያልቅ አንድ ሰዓት በትክክል ልጆችን ማስተማር የበለጠ ትክክለኛ ይሆናል።
መ/ር ንዋይ ካሳሁን
#ለሌሎች_ተደራሽእንዲሆን_ሼር_ማድረግ_አትዘንጉ👇👇
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
https://t.me/orthodoxzelalemawit
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
@TnshuaBetechrstian
የጽጌ ጾም
በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ንጉሥ ሄሮድስ ሥልጣኔን ይቀማኛል በሚል ቅናት ተነሣሥቶ እርሱን ለማስገደል አሰበ፡፡ ያንጊዜም ጌታችን በተአምራት መዳን ሲቻለው የትዕግሥት፣ የትሕትና አምላክ ነውና በለበሰው ሥጋ በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ በመልአኩ ተራዳኢነት፣ በአረጋዊው ዮሴፍ ጠባቂነትና በሰሎሜ ድጋፍ ከገሊላ ወደ ግብፅ ተሰዶ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቆይቷል፡፡ ሄሮድስም ጌታችንን ያገኘው መስሎት በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙ ሀለት ዓመት ከዚያ በታች የሆኑ አንድ መቶ ዐርባ አራት ሺሕ ሕፃናትን በግፍ አስፈጅቷል፡፡
በተአምረ ማርያምና በማኅሌተ ጽጌ ተጽፎ እንደሚገኘው ጌታችን በግብጽ ምድር በስደት ሳለ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ውሃ በጠማቸው ጊዜ ውሃ እያፈለቀ ማጠጣቱና ይህንን ውሃ ክፉዎች እንዳይጠጡት መራራ ማድረጉ፤ ለችግረኞችና ለበሽተኞች ግን ጣፋጭ መጠጥና ፈዋሽ ጠበል ማድረጉ፤ ‹‹የሄሮድስ ጭፍሮች ደርሰው ልጅሽን ሊገድሉብሽ ነው›› ብሎ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ እመቤታችንን በማስደንገጡ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ድንጋይ ሆኖ እንዲቆይ ማድረጉ፤ መንገድ ላይ የተራዳቸው ሽፍታ ሰይፉ በተሰበረች ጊዜ እንደ ቀድሞው ደኅና እንድትሆን ማድረጉ፤ እንደዚሁም የግብጽ ጣዖታትን ቀጥቅጦ ማጥፋቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የጌታችንና የእመቤታችን የስደት ወቅት በወርኃ ግንቦት ነው፤ ነገር ግን ዘመነ ጽጌ የአበባና የፍሬ ወቅት በመሆኑ እመቤታችንን በአበባ፣ ጌታችንን ደግሞ በፍሬ እየመሰሉ ለማመስገንና ለማወደስ በሚያስችል ምሥጢር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የስደቱ ጊዜ በዘመነ ጽጌ እንዲዘከር አድርገዋል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዘለዓለሙ የማይደርቀውን የሕይወት ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን ንጽሕት የማትጠወልግ አበባ ናትና፡፡ ይህ የእመቤታችን አበባነትና የጌታችን ፍሬነትም እንደ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫና አባ ጽጌ ድንግል ባሉ ሊቃውንት ድርሰቶች በሰፊው ተገልጧል፡፡
የጽጌ ጾም በቤተክርስቲያናችን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፭ ያሉት አርባ ቀናት ዘመነ ጽጌ (ወርኃ ጽጌ) እንደሚባሉ ይታወቃል። በነዚህም ቀናት በየቤተ ክርስቲያኑ የሚነበቡ ምንባቦች፣ የሚዘመሩ መዝሙሮች፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚቆመው ማኅሌት፣ በጠቅላላው የሚነገረው ስብሐተ እግዚአብሔር ሁሉ ሰማይ በከዋከብት ምድር በጽጊያት አሸብርቀው የሚታዩ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው። በወርኃ ጽጌ ለሚከናወነው መንፈሳዊ አገልግሎት መነሻው ‹‹መልአኩ ሕፃኑና እናቱን ወደ ግብጽ ይዘሃቸው ሽሽ፤ ሕፃኑን ሊገድሉት ይሻሉና›› ሲል ለዮሴፍ በሕልሙ በነገረው መሰረት ሕፃኑን እናቱን ድንግል ማርያምን ይዞ ዮሴፍ ወደ ግብፅ መሰደዱና እመቤታችንና ሕፃኑን ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በስደት ከኖሩ በኋላ ወደ አገራቸው ወደ ናዝሬት የመመለሳቸው መታሰቢያ ነው። (ራእይ ፲፪፥፲፮)
በዐሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሡ አባት አባ ጽጌ ብርሃን ‹‹የሮማን ሽቱ የቀናንም አበባ የምትሆኝ ማርያም ሆይ ፥ በረሃብ በጾም አበባ የመሰለ የመልክሽ ደም ግባት እስኪ ጠወልግ ድረስ በስደትና በለቅሶ የደረሰብሽን ችግርና ድካም መከራሽንም ሁሉ እንደ እኅትሽ እንደ ሶሎሜ አብሬሽ ብቀበል ምኞቴ ነበር፤ በዚህም ፍጻሜ የሌለውን ደስታሽን እሳተፍ ነበር።›› ብለዋታል፡፡ እንዲሁም አባ አርከ ሥሉስ በስደቷ የደረሰባትን ኀዘን፣ ልቅሶና ሰቆቃ አስመልክተው በደረሱት ‹‹ሰቆቃወ ድንግል›› በሚለው ድርሰታቸው እንዲህ አሉ፦ ‹‹ፀሐይን የምትለብሽ የብርሃን ልጅ ቅድስት ድንግል ማርያም ከክፉ ከሄሮድስ ዘንድ ልጅሽን ባሸሽ ጊዜ የደረሱብሽን ችግሮች ጨረቃን የሚጫሙ እግሮችሽ በመንገድ ብዛትና በአሸዋ ግለት እንዳጎበጎቡ ሲሰማ ሰው ይቅርና ድንጋዩም ባለቀሰ ነበር።››
በዚህ ወቅት በሚገኙ ሰንበታትም ሊቃውንቱ ሌሊቱን ሙሉ ስለ እመቤታችን አበባነትና ስለ ጌታችን ፍሬነት የሚያትት ትምህርት የያዙትን ማኅሌተ ጽጌና፣ ሰቆቃወ ድንግልን ከቅዱስ ያሬድ ዚቅ ጋር በማስማማት ሲዘምሩ፣ ሲያሸበሽቡ ያድራሉ፡፡ ቅዳሴውም በአባ ሕርያቆስ የተደረሰውና ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ሥላሴንና ነገረ ማርያምን የሚተነትነው ቅዳሴ ማርያም ነው፤ ምንባባቱም ከዚሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ናቸው፡፡
የማኅሌተ ጽጌና የጾመ ጽጌ አጀማመር የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር ነው። በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጥዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌተ ጽጌና ከሰቆቃወ ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው። ዝክሩም በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም፥ ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢው ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም የሚዘክሩት ነው። ዐቅመ ደካሞች ድሆችና መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል። ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው።
የጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ዜና ገድል የጽጌን ጾም አስመልክቶ የሚከተለውን ይተርካል፦ ‹‹አባ ጽጌ ብርሃን የተባለው አባት እንደ መዝሙረ ዳዊት መቶ ኀምሳ አድርጎ ማኅሌተ ጽጌን ደረሰ። አባ ጽጌ ብርሃን ይህንን በደረሰበት ጊዜ የወረኢሉ ተወላጅና የደብረ ሐንታው አባ ገብረ ማርያም አማካሪው ነበር። ድርሰቱንም ሲደርስ ቤት እየመታና በአምስት ስንኝ እየከፋፈለ ነው። አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያም ከመስከረም ፳፮ ቀን እስከ ኅዳር ፭ ቀን ማኅሌተ ጽጌን ለመቆምና የጽጌን ጾም ለመጾም በየዓመቱ በደብረ ብሥራት እየመጡ ይሰነብቱና ቁስቋምን ውለው ወደየ በአታቸው ይመለሱ ነበር።›› ከአባታችን የገድል ክፍል ለመረዳት እንደሚቻለው አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያም የጽጌን ማኅሌት መቆም ወቅቱንም በፈቃዳቸው መጾም የጀምሩበ ዘመን በዐሥራ አራተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።
ከዚያ ወዲህ ግን ጥቂት በጥቂት እያለ አብያተ ክርስቲያናት በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ጀመሩ። ጥቂት መነኩሳትና አንዳንድ ምእመናን በፈቃዳቸው ወቅቱን መጾም ጀመሩ። በዘመናችን በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ስለ ተለመደ ከማታው በሦስት ሰዓት ይደወላል። ሴት ወንዱ፥ ትንሹም ትልቁም ይሰባሰባል፤ ማኅሌተ ጽጌው እየተዜመ፤ አስፈላጊ የሆነው በጽናጽል በከበሮ እየተወረበና እየተሸበሸበ እስከ ጥዋቱ ፲፪ ሰዓት ድረስ ተቁሞ ይታደራል። የጽጌ ጾም የውዴታ (የፈቃድ) እንጂ የግዴታ አይደለም። የእመቤታችን ስደት በማሰብ ከትሩፋት ወገን የሚጾም ስለሆነ ምእመናን ሁሉ እንዲጾሙት አይገደዱም፤ የሚጾመው የማይጾመውን ለምን አልጾምክም ብሎ ሊፈርድበት ስለ ራሱም እየጾምኩ ነው ብሎ መናገር አይገባውም። የፈቃድ መሆኑንም የሚያሳየው ይኸው ነው፤ የማይጾመውም በልቡ ያመሰግናል፤ ስደቷን እያሰበ ማኅሌቷን እየዘመረ ያሳልፋል።
አምላካችን እግዚአብሔር የጽድቅ ፍሬን ሳናፈራ በሞት እንዳንወሰድ በቸርነቱ ይጠብቀን፤ አሜን፡፡
#ለሌሎች_ተደራሽእንዲሆን_ሼር_ማድረግ_አትዘንጉ👇👇
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
https://t.me/orthodoxzelalemawit
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት ወጥነትና ስምምነት
ሳይንስ እና ሃይማኖት ከሚለው አዲሱ የዲያቆን ያረጋል አበጋዝ መጽሐፍ ከገጽ 348-352 የተወሰደ
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በ1600 ዓመታት ውስጥ ነው። ይህም ማለት የመጀመሪያው መጽሐፍ ኦሪት ዘፍጥረት ከተጻፈበት ቅ.ል.ክ. 1500 ገደማ አንሥቶ የመጨረሻው መጽሐፍ ራእየ ዮሐንስ እስከ ተጻፈበት 98 ዓ.ም. ድረስ ያለው ዘመን 1600 ዓመት ያህል ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ለመጻፍ ይህን ያህል ረጂም ዘመን የሚሸፍን ሌላ የሃይማኖትም ሆነ መሰል መጽሐፍ የለም። ጸሐፊዎቹ ደግሞ ከ40 በላይ ናቸው። ጸሐፊዎቹ የኖሩበት ዘመን፣ የሥራቸው ዘርፍ፣ የትምህርትና የእውቀት ደረጃቸው ሁሉ አንድ ዓይነት አልነበረም።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በጣም የተማሩና ጠቢባን የነበሩ (ሊቀ ነቢያት ሙሴ፣ ጠቢቡ ሰሎሞን፣ ነቢዩ ዳንኤል፣ ቅዱስ ሉቃስ፣ ቅዱስ ጳውሎስ)፤ ከእረኝነትና ከዓሳ አጥማጅነት የተጠሩ (ነቢዩ አሞጽ፣ ንጉሥ ዳዊት፣ ቅዱስ ማቴዎስ፣ ቅዱስ ዮሐንስ . . )የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ነበሩ። ሆኖም እነዚህ በዘመን፣ በአኗኗር፣ ወዘተ የተለያዩ የነበሩ ከ40 በላይ ጸሐፊዎች በ1600 ዓመታት ውስጥ የጻፉት መጽሐፍ በይዘቱ ግን ወጥና እርስ በእርሱ የተስማማ ነው። አንዳችም የይዘት ተቃርኖ የለበትም።
ይህን ልብ ብሎ በጥሞና ለሚያስተውል ሰው፣ በእውነተኛው አምላክ ምሪት የተጻፈ ካልሆነ በስተቀር በሌላ በምንም መንገድ የሚቻል ነገር አይደለም። በአንድ ዘመን ያሉና ተመሳሳይ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሰዎች በአንድ ርእሰ ጉዳይ ላይ ተመካክረው የሚጽፉት ነገር እንኳ ወጥ ለመሆን ብዙ ፈተና አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ዘርፈ-ብዙ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን የይዘት ተቃርኖም ሆነ ተፋልሶ የለበትም።
ያውም መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ጥልቅና መሠረታዊ ስለሆኑ ጉዳዮች ነው። ስለ ፍጥረት አገኛኘት፣ ኃጢአት ስላስከተለው ውድቀት፣ ሞት ከየትና እንዴት እንደ መጣ፣ ዐለማችን አሁን ላለችበት ሁኔታ ያበቃት ምን እንደሆነ፣ ከዚህ መውጫው መንገድ ምን እንደሆነ፣ ከኦሪት ዘፍጥረት አንሥቶ እስከ ራእየ ዮሐንስ ድረስ ወጥ በሆነ ሁኔታ ያለ አንዳች ተቃርኖ የሚናገር መጽሐፍ ነው። በ10 እና 20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተጽፈው አለቁ የሚሏቸው፣ ሆኖም ግን ከይዘት ተቃርኖ መትረፍ ያልቻሉ የሃይማኖት መጻሕፍት አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን በ1600 ውስጥ ከ40 በላይ በሆኑ ሰዎች ተጽፎ እንደዚህ ያለ ነገር የለበትም።
እዚህ ላይ ማስታወስ የሚያስፈልገው አንድ ነገር ቢኖር ይዘቱን የማይረዱ አንዳንድ ጥራዝ ነጠቆች “መጽሐፍ ቅዱስ ይጋጫል” እያሉ የሚያወጧቸው ጥቅሶች ምንም የሐሳብ ተቃርኖ ያለባቸው አለመሆናቸው ነው። ተቃርኖዎች ሳይሆኑ አንድን ጉዳይ በተለያየ መንገድ የመግለጽ ወይም የአንድን ጉዳይ የተለያየ ገጽታ የመግለጽ ሁኔታዎች ብቻ ናቸው። ለዚህ ማሳያ ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ እንመልከት።
• “ዳዊትም ጋድን፣ እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ብዙ ነውና በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ፣ በሰው እጅ ግን አልውደቅ አለው።” 2 ሳሙኤል 24 ፡ 14
• “በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው።” ዕብራውያን 10፡31
መጽሐፍ ቅዱስን እንተቻለን የሚሉ ሰዎች ተቃርኖ እያሉ ከሚያቀርቧቸው መካከል አንዱ እነዚህን አገላለጾች ነው። ዳዊት በድሎ በነበረ ጊዜ ከሦስት ዓይነት የቅጣት አማራጮች መካከል አንዱን ምረጥ በተባለ ጊዜ በሰው እጅ ከምወድቅ በእግዚአብሔር እጅ ብወድቅ ይሻለኛል፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ምሕረቱ ብዙ ነውና ብሏል። ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ “በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው” ብሏል። ይህ የዳዊትና የጳውሎስ አገላለጽ የሚቃረን ሳይሆን የአንድን ጉዳይ የተለያየ ገጽታ የሚናገር ነው።
ዳዊት የተናገረው የዚህን ዐለም ሁኔታ ነው። በዚህ ዐለም በእግዚአብሔር እጅ ብንወድቅ ቅጣቱ የአባት ቅጣት ስለሆነ ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም። ስለዚህ “በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ” አለ። ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ደግሞ የዚያኛውን ዐለም ነው። በዚያኛው ዐለም በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ ዘለዓለማዊ ስለሆነ እጅግ አስፈሪ ነው።
ከዚህም ጋር ዳዊት በሰው እጅ ከመውደቅ በእግዚአብሔር እጅ መውደቅን በመምረጥ የእግዚአብሔርን መሐሪነት የሰውን ጨካኝነት አጉልቶ አስረዳ። ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ በዚህ ዘመን ያልፍልኛል ወይም ወደ ሌላ ቦታ ሄጄ አመልጠዋለሁ ሊሉት የማይቻል ከባድ ነገር መሆኑን አስረዳ። ስለዚህ እነዚህ የዳዊትና የቅዱስ ጳውሎስ አገላለጾች የሚቃረኑ ሳይሆኑ የአንድን ጉዳይ የተለያየ ገጽታ የሚያሳዩ ተመጋጋቢ አገላለጾች ናቸው።
• “ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው።” ማቴዎስ 17፡1
• “ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ።” ሉቃስ 9፡28
ጌታችን ወደ ደብረ ታቦር ሦስቱን ደቀ መዛሙርቱን ይዞ የወጣበትን ጊዜ ሲጽፍ ማቴዎስ “ከስድስት ቀንም በኋላ” ሲል ሉቃስ ደግሞ “ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ” ብሏል። ቅዱስ ማቴዎስ “ስድስት ቀን” ያለው፣ መጀመሪያ በፊልጶስ ቂሳርያ “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል” ብሎ ደቀ መዛሙርቱን የጠየቀበትን ቀንና ወደ ደብረ ታቦር የወጡበትን ቀን - ሁለቱን ቀኖች - ሳይቆጥር ነው። ቅዱስ ሉቃስ ስምንት ቀን ያለው ደግሞ፣ እነዚህን ሁለቱን ቀኖች (የመጀመሪያውና የኋለኛውን ቀን) ቆጥሮ ነው። ስለዚህ ይህ ተቃርኖ ሳይሆን ወንጌል ነጻ በሆኑ የተለያዩ ሰዎች መጻፉን የሚመሰክር ነው።
ጽሩይ የሆነ አልማዝ ከተለያየ አቅጣጫ ሲያዩት አንዴ ሰማያዊ፣ ሌላ ጊዜ ሐምራዊ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቢጫ መስሎ እንደሚታየው፣ የእግዚአብሔር ቃልም አንድን ነገር ከተለያየ አቅጣጫ ሲያሳየን እንዲህ ባሉ የተለያዩ በሚመስሉ አገላለጾች ይገልጻቸዋል። ስለዚህ ይህን የመሰሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጾች አሉ። ሆኖም እነዚህ ተቃርኖዎች ሳይሆኑ አንድን ነገር በተለያየ መንገድ የሚገልጹ ናቸው። እንዲያውም እነዚህ የተለያዩ የሚመስሉ አገላለጾች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኝነት የሚመሰክሩ ናቸው፤ ምክንያቱም ጸሐፊያኑ እነዚህ መኖራቸውን እያወቁ የተዋቸው ችግር ስላልሆኑ ነውና። በዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ንባብ የሚፈልጉ ሰዎች በዚህ ዙሪያ የተጻፉ ማብራሪያዎችን መመልከት ይችላሉ🤗
#ለሌሎች_ተደራሽእንዲሆን_ሼር_ማድረግ_አትዘንጉ👇👇
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
https://t.me/orthodoxzelalemawit
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
★ሰውን በማዝናናት የብቃት ማረጋገጫ ያለው ብቸኛው ቻናል ሁሌም Telegram ላይ በጥበብ ደምቀን እናሸበርቃለን
💌 Contact us, @Modenyazbot
»የተመረጡ እና ማንም ያላያቸው የአማሪኛ ቀልዶች እንዲሁም የሚያስደንቁ ስዕሎችንና ቪዲዮ ያገኛሉ።
° ° [ ሙድ እንያዝ በእኛ የአራዶች መዝናኛ ] ° °
° ° Creator @Teke_Man ° °
Last updated 2 months, 1 week ago
☕ ስለ ኢትዮጲያ ቡና የሚወጡ ወቅታዊና ትክክለኛ የክለቡ መረጃዎች አዚህ ያገኛሉ!
➪የዝዉዉር ዜና
☞የአሰልጣኞች አስተያየት
➪ጎሎች እና ቪዲዮዎች
☞የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
➪ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት ከየስታድየሙ !
➡መወያያ ግሩፓችን @Ethiopia_coffee_Sc
📩ሀሳብ ወይም አስተያየት ካሎት
በዚህ 👉 @EthiopianCoffeeScBot ✍
BOT ማድረስ ይችላሉ!
Last updated 4 months, 3 weeks ago
ማንኛውንም የማስታወቂያ ስራ ለማሰራት የምትፈልጉ(only promotion) inbox @Eyyiba
ሌሎች ጥያቄዎችን ለማድረስ
@Ethiodailyvacbot
Last updated 1 month ago