ቅንጭብጭብ

Description
ካየሁት 👀 አስገራሚ
ከሠማሁት 👂 መሣጭ
ካነበብኩት 📖 አስተማሪ
ካሠብኩት ♀🅱 ልዩ ልዩ

እነሆ #ቅንጫቢ

ፅሁፎቻችሁን በ @bcrAzykid አካፍሉን።

ለማንኛውም አስተያየት ጥያቄ እና ጥቆማ @bcrAzykid ይጠቀሙ።
Advertising
We recommend to visit

★ሰውን በማዝናናት የብቃት ማረጋገጫ ያለው ብቸኛው ቻናል ሁሌም Telegram ላይ በጥበብ ደምቀን እናሸበርቃለን

💌 Contact us, @Modenyazbot

»የተመረጡ እና ማንም ያላያቸው የአማሪኛ ቀልዶች እንዲሁም የሚያስደንቁ ስዕሎችንና ቪዲዮ ያገኛሉ።

° ° [ ሙድ እንያዝ በእኛ የአራዶች መዝናኛ ] ° °

° ° Creator @Teke_Man ° °

Last updated 1 month, 1 week ago

☕ ስለ ኢትዮጲያ ቡና የሚወጡ ወቅታዊና ትክክለኛ የክለቡ መረጃዎች አዚህ ያገኛሉ!

➪የዝዉዉር ዜና
☞የአሰልጣኞች አስተያየት
➪ጎሎች እና ቪዲዮዎች
☞የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
➪ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት ከየስታድየሙ !

➡መወያያ ግሩፓችን @Ethiopia_coffee_Sc

📩ሀሳብ ወይም አስተያየት ካሎት
በዚህ 👉 @EthiopianCoffeeScBot ✍
BOT ማድረስ ይችላሉ!

Last updated 3 months, 2 weeks ago

ማንኛውንም የማስታወቂያ ስራ ለማሰራት የምትፈልጉ(only promotion) inbox @Eyyiba
ሌሎች ጥያቄዎችን ለማድረስ
@Ethiodailyvacbot

Last updated 1 day, 11 hours ago

2 months ago

ገላጣ
(በእውቀቱ ስዩም)

ዛሬ የተከበረውን የዓለም አቀፍ ራሰ በራዎች ቀን ሳልዘክር ወደ ምኝታየ ብሄድ የሶቅራጥስ አጽም ይወጋኛል፤

ሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “በራሕ”የሚለውን ቃል ሲተረጉሙት-“ በራ፥ መላጣ፥ ራሰ ገላጣ፥ ከቦታው የታጣ፥ የራሱ ቁርበት፥ ሳንባና ጉበት የሚመስል “ ይላሉ (መጽሀፈ ስዋሰው ወግስ ፥ ገጽ 287፤ በትርጉሙ ውስጥ ያሉትን አሉታዊ ቃላት ብዛት ለተመለከተ አለቃ ባለ ሙሉ ጠጉር እንደሆኑ መገመት አያቅተውም፤

አለቃ “ራሰ ገላጣ “ ቢሆኑ ኖሮ “ራሰ በራ ” የሚለውን ሲተረጉሙ “ራሱ የበራለት፤ ታጥቦ የተወለወለ የንጉስ ብርሌ የመሰለ፥ መላጣ፥ ከፎረፎርና ከቅማል ስጋት ነጻ የወጣ “ብለው ሊተረጉሙት ይችሉ ነበር፤

በታሪካችን ትልልቅ ራሰ በራ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ነበሩ፤ ከጌቶች መካከል ብንጠቅስ፥ ራስ ስኡል ሚካኤል፥ አጤ ምኒልክ፥ ራስ ዳርጌ፥ መለስ ዜናዊ፥ ከደራሲ ፥ሀዲስ አለማየሁ፥ ጃርሶ ኪሩቤል ሞትባይኖር፥ መንግስቱ ለማ፥ ሊጠቀሱ ይችላሉ፤ ( ሎሬት ጸጋየ ገብረመድህን ራሰ በራ ነው ወይስ የተሸጋሸገ ጎፈሬ ነው የሚለው በታሪክ ሲያከራክር ይኖራል )

“ለኔ እየሰጠችኝ ደረቁን እንጀራ
እስዋ በነካካው በራሰው ልትበላ"

የሚለውን ጥንታዊ ውስጠ ወይራ ዘፈን መናሻ አድርገን ብንናገር ፥ ሴቶች ከሚያበጥር ይልቅ የሚወለውል ወንድ የበለጠ እንደሚማርካቸው መረዳት አያቅትም፤

ስለ ጸጉር ጨዋታ በተነሳ ቁጥር ፈገግ የምታሰኝኝ ድምጻዊ አብነት አጎናፍር የተናገራት ናት፤ አብነት እንዲህ አለ፤

“ ከጥቂት ጊዜ በፊት ጸጉር ላስተክል ቱርክ ሄጄ ፤ ጸጉር የሚተከለው ሰውየ መላጣ መሆኑን ሳይ ትቸው ተመለስኩ"🙂

በዚህ አጀንዳ ላይ ሌሎች የከተማው ነዋሪዎች ያላቸውን አስተያየት ለመስማት ከፈለጉ ከታች የጫንኩትን ትረካ ያድምጡ።

2 months ago

የቱ ጋር መሰለህ…
(ሚካኤል አ)

መባቻ ጅምርህ
የነፍስህ ድባቴ
ውድቀት እንግልትህ
ያኔ …
ባሽትሪ መያዣ ፣ በሲጋራ ብናኝ
በርጋፊ ቅጠል ፣ ድባቧ የሚቃኝ
በዛች ጠባብ ክፍል
ምጥን መሰብሰቢያ
ዙሪያህን ሰው ሞልቶህ
ቀንህን ማጣፊያ
ለአፕላይ ግብዣ የተዘረጋች ጣት
በሚግተለተል ጢስ ፣ ሰንቃልህ እሳት
እሷን ለመቀበል ስትፈግግ ባ’ክብሮት
የሰበብ አስባብ ጢስ
ቀረ ቤትህን ወርሶት።
የቱ ጋር መሰለህ?
በቀይ መብራት ፍካት
በቅልቅል ሽቶ አዲስ አይነት ክርፋት
በጭላጭ ብርጭቆ ተላኮበት ድራፍት
ከስፒከር ማህፀን ሙዚቃ ተለቆ
ጭፈራ እና ዳንሱ አንድ ላይ ተዛንቆ
የቀይ ሴት ታፋ ዓይንህ በስስ ሰርቆ
በምራቅህ ድርቀት ጉሮሮህ ተጨንቆ
ጠቅሰህ ስትጠራት
ያቺን የሞት ብልቃጥ
ከባቷ ፈልቅቀህ ዕፅዋን ስትቀምሳት
በገላህ ፍሰሀ መቅደስህን ናድካት ።
የቱ ጋር መሰለህ?
የልጅነት ልምድህ
ከሰንበት ቤት ገዳም
ምልልስ ብርታትህ
በሀይኪንግ ሲቀየር
የያሬዱ ወረብ
በእስክስታ ሲዛወር
ሳትቆም ለፀሎት
ሳይንስ ከእምነት ልቆት
ኒቼ ቦታ ሲወርስ የየኔታን መንበር
የነፍስህ ቁዘማ መንደርደሪያ ነበር።
ትዝ አለህ?
ዘር መራጭ ስትሆን
የደም ሴል መንጣሪ
ጆሮህ ዳባ ሲለብስ
ለፍጥረት እንግልት
ለህፃናት ጥሪ…
መንገድህ ሲሳለጥ
በ V 8 መኪና
ዝርግ አስፓልት ሲመስልህ
ጉርብጥብጥ ጎዳና ፤
ስቆልኛል ስትል ጥርሱን የነከሰ
እንባው አንሸራሽሮህ ጌታ ዘንድ ደረሰ።
ምላሹስ የከፋው መቼ ላይ ሆነና?
ጥሬ እየቆረጥክ ሆድህ ሲመረመር
እስቲም ሳውና ገብተህ ፊትህ ሲጭበረበር
በድሎትህ መኃል
ገላን የሚያኮስስ የእሾህ ስንጥር ነበር።
ትዝ አለህ?
መኝታህ በምቾት ተሞልቶ በአጀብ
እንቅልፍህ ሲናጠብ?
ትዝ አለህ?
በውድ ቀለም ቤቶች ልጆችህ ሲማሩ
ከግብረገብ ታዛ ተናንሰው ሲቀሩ?
ትዝ አለህ?
የጉያህ መልካም ሴት
የአጥንትህ ፍላጭ
አሁን ከምን ጊዜው
ሆነችብኝ ምላጭ?
ብለህ ስትቆዝም …
እንዲያ ነው አይዋ
ግፍ ፅዋው ሲሞላ
በትሩን አይመርጥም።
ትዝ አለህ?
ታወሰህ?
የቱ ጋር መሰለህ?
የተፈታው ውሉ
የጎደልክ ከሙሉ
ኧረ ስከን ሲሉ
ከዕድሜ የተማሩ
የጋሽ ውቤን ምክር
የእመት ጉሌን ዝክር
ረግጠህ ስትበር…
ስትሻገር ፣ ስጥስ
የምስኪናን ድንበር
የዛሬ ውድቀትህ ፣ በግጥም ሊነገር
ክንፍህ የተመታው ይሄን ጊዜ ነበር።
ትዝ አለህ?

አዎን እሱ ጋር ነው!

2 months, 1 week ago

የአብዛኛው ፍልስፍና መፅሐፍ ቶቻችን የቃላት ውስንነት ይታይባቸዋል ከደራሲው የሚመነጩ አንዳንዱም ከዘርፉ ባህሪ አንባቢም ግር ላለማሰኘት ፀሐፊዎች በቅንፍ የእንግሊዘኛውን ቢያስቀምጡ መልከም ይመስለኛል
ይሄንን ከዘረያቆብ ገፅ ነው ያገኘሁት ተከተሏቸው አሪፎች ናቸው
የፍልስፍና መዝገበ ቃላት
=============
1. Pragmatic - ገቢራዊ
2. Statuesque - ነቢር
3. Hierarchy - የላዕላይነት ተዋረድ
4. Normative - የልኬት-ሚዛን
5. Theory - ህልዮት
6. Ideal - ተምኔታዊ-ስዕል
7. Moral sense - ግበረ-ገባዊ ህዋስ
8. Collective - ጋርዮሻዊ
9. Soul-Body dichotomy - የነፍስና ስጋ ኩፋሌ
10. Compromiser - አመቻማች
11. Ethos - የአኗኗር-ዘይቤ-መንፈስ
12. Aristocratic - ባላባታዊ/ጌትነታዊ
13. Moderation - ታጋሽነት
14. Courageous - ደፋርነት
15. Indulgence - ልልነትን
16. Passivity - ቀሰስተኛነት
17. Chaotic - ውጥንቅጥ
18. Master Morality - የጌትነት ምግባር
19. Slave Morality - የደካሞች ምግባር
20. Life-negating - ህይወትን የሚያማርር
21. Life-affirming - ህይወትን የሚያፈቅር
22. moral supremacy - ግብረገባዊ ልእልና
23. Contextual background - አውዳዊ ዳራ
24. Intuition - ውስጠተ-ስሜት
25. Oedipus Complex - የወንድ ህቡዕ ፆታዊ ምኞት
26. Electra Complex - የሴት ህቡዕ ፆታዊ ምኞት
27. Classics - ብሉያት
28. Humanists - ሥነ ሰብዓውያን
29. Renaissance - ዘመነ ትንሳኤ
30. Critical Thinking - ነቂሳዊ እሳቤ
31. Artificial Intelligence - ሰው ሰራሽ አስተውሎት
32. Sculpture - ኪነ ቅርፅ
33 Painting - ኪነ ቅብ
34. Premises - መነሻ ሐሳቦች
35. Argument - ነገረ ሐሳብ
36. Critical Social Theory - የማህበራዊ ነቀሳ ህልዮት
37. Thesis, Anti-thesis, Synthesis - አንብሮ፣ ተቃርኖ፣ አስተፃምሮ
38. Virtue - ምግባረ እሴት [ሰናይነት]
39. Altruism - ለሌላው ቅድሚያነት
40. Contemporary - ዘመነኛ
41. Existentialism - የአኗኗር ፍልስፍና
42. Authority - መሪ ሊቅ
43. Absurd - ወለፈንድ
44. Prejudice - ፅልማዊነት
45. The Problem of Evil - ነገረ እኩይ
46. Moral Evil - ክፋት
47. Scholastic - መጽሐፋዊ
48. Fallacy - ተፋልሶ
49. Historical Background - ታሪካዊ ዳራ
50. Being/Existence - ኑባሬ
51. Term - አኃዝ
52. Dialectic - ሕገ-ተቃርኖ

2 months, 1 week ago

#ሐዲስ ዓለማየሁ እና ፍቅር እስከ መቃብር
(Abrham Tsehaye)

ዘመኑን በልኩ የሚስሉት አሉ። የዘመን ልኮች፤ ፖለቲካው እነሱን የሚመስል፣ ራሳቸው ስነ ጽሑፍን የሚያክሉ፤ የጊዜውን ምጣኔ ሃብት ለማውራት ማጣቀሻ የሚሆኑ አሉ። የዘመን ዋርካዎች!

#ሐዲስ

ሩዶልፍ ኬ ሞልቪየር ጽፈው የሰነዱት የጥበብ ሰዎቻችንን የያዘው ዶሴ 'ጥቋቁር አናብስት' ተብሎ ወደኛ ቋንቋ ተመልሷል። እዚሁ ላይ ስለሐዲስና መጽሐፋቸው የተቀነጨበ ታሪክ አለ። ሁኔታውን ስናወሳ ልክ እንደ ድርሰቱ ደራሲውም ይታወሱ በሚል ሐቅ ነው! መጽሐፉ ወደቴሌቪዥንና አንተርኔት መስኮቶች ብቅ ማለቱን ተከትሎ መሆኑም ይታወቅ።

#ሐዲስ ዓለማየሁ የዛሬ 59 ዓመት በ1958 ዓመተ ምህረት ፍቅር እስከ መቃብርን ወለዱ። ይህ የመጀመሪያ ትልቁ ልብወለዳቸው መፃፍ የተጀመረው ግን በግምት ከ20 ዓመታት በፊት በዋሺንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዋና ፀሐፊ እያሉ ( ከ1939–1943 ) ነበር። በ1938 ማለት ነው! ሃያ ዓመታት የተማጠ ያልቸኮለ ጥበብ!

መጽሐፉ በመጀመርያ በእንግሊዝኛ ተሞክሮ ነበር፤ ኒውዮርክ ለሚገኝ አሳታሚ ልከውት ኅትመት ቤቱ ለማሳተም ፈቃደኛ አልሆን አለ እንጂ። መልሰው በአማርኛ መጻፍ ጻፉት።

ፍቅር እስከ መቃብር በየመሐሉ ለረዥም ጊዜ ተቋርጧል። ለምሳሌ ደራሲው በእንግሊዝ አምባሳደር ሳሉ ( 1953–1958) ባለቤታቸው አረፉ፤ በዚህ ሀዘናቸው የተነሳ ለአንድ ዓመት ያህል እርግፍ አድርገው ትተውት ቆይተዋል።

ከስራ ወደስራ በተዛወሩ ቁጥር ሌሎችም ረዣዥም መቆራረጦች ነበሩ። ሲጨርሱትም ጥሩ መጽሐፍ መስሎ እንዳልታያቸው ይነገራል። ያው ልከኛ የጥበብ ሰው አይረካም! ሐዲስ ያለምንም ማቋረጥ ሲጽፉ ፍሰቱ ጥሩ እንደሚሆን የሚያቋርጣቸው ሲኖር ግን እንደገና ካቆሙበት ለመቀጠል ሃሳባቸው ስለሚበታተን ፍሰቱን ለማስኬድ እንደሚቸገሩ ያስረዱ ነበር። በአጠቃላይ መጽሐፉ በአስቸጋሪ ጊዜያት የታጀቡ የብዙ ቅጥልጥል ውጤቶች ነው፡፡

ሞልቪየር ይህ አለመመጣጠን ባለቀው መጽሐፍ ላይ በጉልህ ይታያል ባይ ናቸው። መጽሐፉን ጽፎ ለመጨረስ ብዙ ጥረት ጠይቋል፤ ለማሳተምም ገንዘብ እስከመበደር ተደርሷል። ይህ ታልፎ ታትሞ የወጣው ፍቅር እስከ መቃብር በስተመጨረሻ በጥሩ ሁኔታ በመሸጡ ደራሲው እጅግ ተደስተውም ተገርመውም ነበር። የጻፉት ሲነበብ ራሱ ትልቅ ሽልማት ነው!

#ህትመትና ሽያጭ

በመጀመሪያው ዙር 5,000 ቅጂዎች ብቻ ነበር የታተመው። በሚቀጥለው 7,000 ቅጂዎች ደረሰ። እስከ 1978 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ በጥቅሉ ስድስት ጊዜ ያህል ተደጋግሞ ታትሟል። መጽሐፉ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ሲያገኝ ከታተመ ከጥቂት ዓመታት በኋላም በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ገብቶ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የማስተማሪያ መጽሐፍም ሆነ።

#ደራሲውና ገጸ ባሕሪያቱ!

በዛብህና ጉዱ ካሳ

በፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ ብዙ ክፍሎች ከደራሲው ሕይወት የተቀዱ ናቸው ። በጎጃም ደብረወርቅ እና ዲማ ያሉት ታሪኮች ደራሲው በቅኔ ተማሪነታቸው ያሳለፉት ሕይወት ግልባጭ ነው። በዛብህ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣና በከተማው ውስጥ የሚያጋጥሙት ሁነቶች ሐዲስ ራሳቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በ1918 ዓ.ም ከጎጃም ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የታዘቡት ገጠመኝ ጥርቅም ነው።

በአጠቃላይ ሐዲስ ልብወለዱ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ገፀ ባህሪያት ውስጥ ራሳቸውን በተወሰነ መልኩ እንደሚያዩ ይናገራሉ። የመጀመሪያው ወደ አዲስ አበባ ከመምጣቱ በፊት የቤተክርስቲያን ትምህርት የቀመሰው እና እንደ ሐዲስ ለቤተሰቡ ብቸኛ ልጅ የሆነው የልብወለዱ ዋና ገፀ ባህሪ በዛብህ ሲሆን ሌላው ደግሞ በማኅበረሰቡ ሳይሆን በራሱ ሀሳብ የሚመራው ይኼም ዘወትር ከራሱ ወገኖች እና ከመደብ ፍላጎቶቹ ጋር ቅራኔ ውስጥ የሚያስገባው ጉዱ ካሳ ነበር ።

#መቼት

የልብወለዱ መቼት ከሐዲስ የልጅነትና ወጣትነት ሕይወት ጋር በተወሰነ ደረጃ ይገጥማል (የተወለዱት በ 1902 ነበር )። በእርግጥ ልብወለዱ ከዚህ ትንሽ ቀደም ብሎ ይጀምራል። የልብወለዱን መቼት በሀያኛው ከፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ ወደ ኃይለሥላሴ የግዛት ዘመን የመጀመሪያ ዓመታት ( ስልጣን የያዙት በ 1923 ዓ.ም ነው ) ይጠጋል። ሞልቪየር ሲያክሉ "ከሐዲስ ጋር ይህንን የጊዜ ሰሌዳ አውጥተን ነበር ፤ ነገር ግን ሐዲስ በልብወለዱ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ልማድና ስርዓቶች የጥንት እንደነበሩ አንዳንዶቹም እስከ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ዘመን ( 1847- 1861 ) ወደኋላ እንደሚለጠጡ ነግረውኛል" ብለዋል።

#በስተመጨረሻ!

ሐዲሳችን በመጨረሻው የሕልፈት ሰዓታቸው ግን እንደተለመደው፣ እንደባሕላችን እሳቸውም እንደሌሎቹ ትጉኃን እጦት ጎብኝቷቸዋል። ደራሲ ዘነበ ወላ በአይፐሲዜ መጽሐፉ ላይ እንዳወጋን እንዴት ነው የፈረንካ ነገር ሲላቸው አሁን አሁን ይቸግረኝ ጀምሯል ብለውታል። ተደጋግሞ የሚታተመው የፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍዎስ አላቸው። "ማን ጠይቆን ይታተማል ብለህ ነው?!" ሲሉ መልሰው ነበር።

ሰዎቻችን አኑረውን የማይኖሩት ነገር የድግግሞሻችን የነውር ቀለም ይመስላል! ነጋዴዎችም ነግደው ያተርፉባቸዋል። እኛም ለምን አለማለት ለምዶብናል!

2 months, 2 weeks ago

ውድ የመዲና ዲጂታል መጽሔት ቤተሰቦች

እንኳን ለ2017 ዓ.ም በሰላም አደረሳችሁ! ለአዲስ ዓመት ገጸ በረከት እጅ መንሻ ይሆን ዘንድ የጳጉሜን ልዩ ዕትም ይዘንላችሁ ቀርበናል። የጳጉሜ ዕትም በመሆኗ ከወትሮ በተለየ በገጽ ከመመጠኗ በቀር ያጎደለችው ነገር የለም። ስለምታነቡን እናመሰግናለን።

መልካም አዲስ ዓመት!

2 months, 2 weeks ago
6 months, 2 weeks ago

ይህ ልብወለድ አይደለም፤ እውነተኛ ታሪክ ነው። ወዳጄ Nebiyu Bazezew "አንተ ብትተርከው ይሻላል" ብሎ የነገረኝን ታሪክ እጅጉን ስለደነቀኝ እኔ ፃፍኩላችሁ።


በሬው ጠፋ።
የሚተዋወቁ የሰፈሩ አባወራዎች ናቸው፤ ለቅርጫ ገንዘብ አዋጡ፦ ለፋሲካ። ተወካዮቹ የቅዳሜ ስዑር ዕለት ገበያ ወጡ። ዞር ዞር ብለው ገበያውን አዩ። ዋጋ ጠየቁ። ተከራከሩ። እንደአቅማቸው በሬ ገዙ፦ በ58 ሺህ ብር። ወደ ሰፈራቸው ፈረንሳይ ለጋሲዮን በሬውን ይዘው መጥተው አንድ ግቢ ውስጥ አሰሩ። አራጅ ቀጠሩ። ለሊት ሰባት ሰዓት ሊያርዱት ከአራጁ ጋር ተቀጣጥረው ተሰነባበቱ።


ለሊት ሰባት ሆነ።
ሰዎች ተሰባሰቡ፤ በሬውን ሊያርዱት ገመዱን ሲፈቱት አመለጠ። ተከተሉት። በዚያ ድቅድቅ ጨለማ የዕውር ድንብራቸውን ሮጡ። ሊደርሱበት አልቻሉም። ፈረጠጠ። ዳገት ወጡ፣ ወረዱ። ልባቸው ሊፈነዳ ደረሰ። ሩጫቸውን ገታ አድርገው ጨለማው ላይ አፈጠጡ። ከፊታቸው ጥቁር ጨለማ ብቻ ተዘርግቷል። ተስፋ ቆረጡ። በሐዘን ተውጠው ወደ ሰፈራቸው ተመለሱ።


አይነጋ የለም፤ ነጋ።
"እንግዲህ ለቅርጫ ማሕበርተኛው ምን ይባላል?" ተባባሉ። ቅርጫ የገቡት ሰዎች በሬው መገዛቱን አይተዋል፤ አንድ ግቢ ውስጥ መታሰሩንም አይተዋል፤ ለሊት በሬው ጠፋ ቢባል ማን ያምናል? ዓመት በዓሉስ እንዴት ዓመት በዓል ይሆናል?!
"ዕድል ቢቀናን ወደ ጫካ ወጥተን እንፈልግ" ተባባሉ። እናም ወፍ ሲንጫጫ ለሊት በሬው ወደፈረጠጠበት አቅጣጫ ጉዞ ጀመሩ።


በጉዞአቸው መሃል ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ታየቻቸው፤ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ኪዳነምህረት። ተሳለሙ።
"እመቤቴ አንቺ እርጂን" አሉ። ስዕለት ተሳሉ። እናም ፍለጋቸውን ቀጠሉ፦ ወደ አንቆርጫ። አንዱን ኮረብታ አልፈው፣ ወደ ሌላ ኮረብታ። "አይ በዚህ ምንም ዳና የለም" እየተባባሉ በሌላ መንገድ ፍለጋ ቀጠሉ፤ ያኛውንም መንገድ እየተው በሌላ አቅጣጫ ሲሄዱ፣ ሲሄዱ፣ እግራቸው እንዳመራቸው ሲሄዱ ቆይተው ደረሱ፦ አካኮ።


እዚያ ከአንድ የገጠር ጎጆ ፊት ለፊት ጫካ ውስጥ ሰዎች ተሰባስበዋል። ብዙ ናቸው፤ በሬ አርደው እዚያው የሚበላውን ሥጋ እየበሉ ነው። እየተጨዋወቱ፤ እየተጎራረሱ፣ መደብ እየመደቡ ወዘተ። የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው።

በሬ ፈላጊዎቹ ጠጋ ብለው ሰላምታ ሰጧቸው።
ከሠላምታ በኋላ፦ "ኑ! ምሰሉን፤ እዚህ ቁጭ በሉ" አሏቸው፤ ወደሚበሉት ሥጋ እየጠቆሙ ጋበዟቸው።
"አይ አንቀመጥም" አሏቸው የታረደው በሬ የእነሱ መሆኑን ለመለየት ወደ ቆዳው እያማተሩ።

"ኧረ ነውር ነው፤ በዓመት በዓል ሳትቀምሱ አትሄዱም"
"የለም፤ እንቸኩላለን"
"ብትቸኩሉስ፤ ቁጭ በሉ አፋችሁ ላይ ይቺን ጣል አድርጉ" አሏቸው ሥጋ በእጃቸው እያቀበሏቸው። በእጃቸው የዘረጉትን
ሥጋ ተቀብለው በሩቅ ሲያማትሩ አንዱ ሽማግሌ ሌላ ጥያቄ ሰነዘሩ።

"ምነው፤ ምን እግር ጣላችሁ? ምን ሆናችሁ ነው?"
ነገሯቸው፤ በሬ እንደጠፋባቸውና ፍለጋ ላይ እንደሆኑ።
ገበሬዎቹ መንደርተኞች እርስ በርስ ተያዩ።


አካኮ፤ ገበሬዎቹ በሬ የጣሉበት ጫካ ፊት ለፊት ያለው ጎጆ ውስጥ ያሉ አንድ እናት አልፈስክም ብለው አስቸግረዋል። ምክንያቱ የተሸጠው በሬ ነው።

ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ጨፌ አካባቢ የጠፋው በሬ ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በፊት "ቤቱ" ደርሷል። የበሬውን መድረስ ያዩት እናት አዝነዋል።

"ይኼንን በሬ የገዙት ሰዎች፤ ቤተሰቦቻቸው፣ ልጆቻቸው ሳያከፍሉ፤ እኔ አላከፍልም" ብለው እህል ሳይቀምሱ ፀሐይ ወገግ ብሏል። ገበሬዎቹ ይህንን ስለሚያውቁ ነው እርስ በርስ የተያዩት።


ገበሬዎቹ በዐይናቸው ተሳስቀው፤ እነዚህ ጥቁር እንግዶች ቁጭ እንዲሉ ወተወቷቸው። እና አረቄ በስኒ እየጋበዟቸው ጥያቄአቸውን ቀጠሉ።

"የት ነው የገዛችሁት?"
"የሸጠላችሁ ሰው መልክ ታውቁታላችሁ?"
"በስንት ገዛችሁ?"
ተጠያቂዎቹ ሁሉንም ጥያቄ በትክክል መለሱ። ይኼኔ አንዱ ወጣት "ልክ ናችሁ፤ እኔ ነኝ የሸጥኩላችሁ" አለ ራሱ ላይ የጠመጠመውን ነጠላ ቢጤ አንስቶ።

"ዐይናችንን የሆነ ነገር ጋርዶት እንጂ ሻጩ ፊት ለፊታችን ነበረ" አለኝ ይኼን ታሪክ የነገረኝ ገዢ።

ቀጠለ ወጣቱ ገበሬ፦
"...በሬው የእናታችን ነው፤ ቤቱ ገብቷል፤አዎ 58 ሺህ ብር ነው የገዛችሁኝ። አሁን ግን እጄ ላይ ያለው 55 ሺህ ነው። እንደገዛችሁኝ አንድ ሺህውን ብር ከጓደኞቼ ጋር ተገባብዘንበታል፤ 2 ሺህ ብር ደግሞ ለደላላ ከፍለናል። የቀረው 55 ሺህ ገንዘባችሁ ነው፤ ውሰዱ"

ተገረሙ።

"እኛ ግን በሬውን...."
አቋረጧቸው አንዱ አባት።
"አይ በሬውን አንሰጣችሁም፤ ይኼ በሬ ካለምክንያት ተመልሶ አልመጣም፤ ከአሁን በኋላ አይሸጥም፤ ከቤትም አይወጣም ብላለች ባለቤቴ"

"ወቸው ጉድ"
"ባይሆን"
"ባይሆን ምን?.."
"ብሩን አንወስድም ካላችሁ ሌላ በሬ እንቀይርላችሁ፤ ሁለት ሺህ ጨምራችሁ ሌላውን በሬ ውሰዱ"

በዚሁ ተስማሙ።
በሬ የጠፋባቸው ሰዎች ሌላ በሬ ይዘው እኩለ ቀን ላይ ወደ ሰፈራቸው ተመለሱ።

እውነተኛ ፋስካም ሆነላቸው።
---
Via ወሰንሰገድ ገብረኪዳን

7 months, 1 week ago

የማባልጋት ባለትዳር ነበረች ።

ዋና ተግባራችን ወሲብ ነው ። የምንቀጣጠረው ለወሲብ ብቻ ነው ። የምናወራው ስለ ወሲብ ነው ። አንዳችን አንዳችንን የምንፈልገው ወሲብ ሲያምረን ነው ።

አጠገቤ ሆና ባሏ ደውሎ ያውቃል: "ሰውዬሽ ደወለ" ብዬ ስልኳን አቀብያት አቃለሁ ። ምንም እንዳልተፈጠረ ስታወራው እርቃኗን አትመስልም ነበር። ይገርመኛል ድድብናችን ።

ነውራችን ስለተደጋገመ ተግባራችን ብልግና መሆኑ ተሰወረብን ።

ቢሮዋ እሄዳለሁ፣ ቢሮዬ ትመጣለች ። ጓደኛዬ ቤት፣ እኔ ቤት፣ የሆነ ኮስመን ያለ ሰዋራ ቦታ ፣የሆነ ድብቅ ፅድት ያለ ስፍራ ፣ መኪና ውስጥ ... ብዙ ብዙ ቦታ ትመጣለች እንዋሰባለን ። የታሪካችን መነሻ እና መድረሻው ወሲብ ነው ።
አንድ ቀን በደነገጠ: ተስፋ በቆረጠ ድምፅ "ባሌ አወቀብን" አለችኝ .....ደነገጥኩ ።

ጠፋሁኝ ...ጠፋች

ከአስራ ሰባት ቀን በኋላ ጓደኞቼ "ገኒ ሃዘን ላይ ነች፣ ሙሉ ከላይ እሰከታች ጥቁር ለብሳለች፣ ከስታለች" አሉኝ

"ምን ሆነች?" አልኩ

"ባሏ ሞቶባት ነው፤ ራሱን አጥፍቶ ነው የሞተው" አሉ።

ስደነግጥ፣ ፊቴ ሲቀያየር ፣ እምባዬ ሲያመልጠኝ አዝኜለት ነው የመሰላቸው ። እኔ እንደገደልኩት አልጠረጠሩም ።

የጥፋተኝነት ስሜት ሊገለኝ ሲል ማምለጫ መፅሃፍ ቅዱስ ገለጥኩ።

"ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል " የሚለው ከሁሉም ጎልቶ ተነበበኝ ።
..
ሰው ይዞ መውደቅ ፤ ማስተካከል የማይቻል አወዳደቅ ፣ ሲያስታውሱት የሚያስነክስ አይነት አወዳደቅ፣ እነሳለሁ የማይሉት አወዳደቅ ፣ ወድቄ ነበር የማይሉት አወዳደቅ። በግዜ ምክንያት የማይደበዘዝ አወዳደቅ ...
እንደዚህ አይነት መውደቅ ሲ..ያ...ስ..ጠ..ላ !! !

© አድኃኖም

7 months, 1 week ago

#Ethiopia | ታይታኒክ የተገነባችው ሰሜን አይርላንድ ውስጥ “White Star Line” በተባለ ካምፓኒ ነው፡፡

ታይታኒክ 269 ሜትር ርዝመት፣ 28 ሜትር ስፋት፣ 32 ሜትር ቁመት እንዲሁም ከ47 ሚሊዮን ኪ.ግራም በላይ ክብደት ነበራት፡፡

ታይታኒክ የተሰራችው በ7.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡ እ.አ.አ በ1997 ለእይታ የበቃው የጀምስ ካሜሮን ፊልም ታይታኒክ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጥቶበታል፡፡

ታይታኒክ በቀን 600 ሺህ ኪ.ግራም ከሰል ትጠቀም ነበር፡፡

ታይታኒክ ከእንግሊዝ ሳውዝ ሀምፕተን ከተማ ወደ ኒውዮርክ ጉዞ የጀመረችው እ.አ.አ ሚያዚያ 10 ቀን 1912 ነው፡፡

መርከቧ ለ4 ቀናት የተሳካ ጉዞ ካደረገች በኃላ 30 ሜትር ቁመት ካለው የበረዶ ግግር ጋር የተላተመችው ሚያዚያ 14 ቀን 1912 ከሌሊቱ 5 ሰዓት ከ40 አካባቢ ነው፡፡ መርከቧ ሙሉ በሙሉ ለመስጠም 2 ሰዓት ከ40 ደቂቃ ፈጅቶባታል፡፡

በአደጋው ወቅት ከ2 ሺህ 200 በላይ ሰዎች መርከቧ ውስጥ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በህይወት የተረፉት 706 ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡

ታይታኒክ ውስጥ 20 ህይወት አድን ጀልባዎች ነበሩ፡፡ ጀልባዎቹ እያንዳንዳቸው እስከ 64 ሰው የመያዝ አቅም ቢኖራቸውም መርከቧ ውስጥ በተፈጠረው ትርምስ ጥቂት ሰዎችን ብቻ ነበር እየያዙ የወረዱት፡፡

በታይታኒክ አደጋ የሞቱት አብዛኞቹ ወንዶች ናቸው፡፡ ይህም የሆነው ወደ ማምለጫ ጀልባዎች እንዲገቡ ቅድሚያ ለሴቶች እና ለህጻናት በመሰጠቱ ነው፡፡

ከሟቾች ውስጥ 26ቱ ጫጉላ ላይ የነበሩ ጥንዶች ናቸው፡፡

የታይታኒክ የሙዚቃ ባንድ አባላት መርከቧ እስክትሰጥም ድረስ ሙዚቃ መጫወት አላቆሙም ነበር፡፡

መርከቧ ውስጥ የነበሩ አንድ ቄስ ሁለት ጊዜ ወደ ህይወት አድን ጀልባዎች እንዲገቡ ተጠይቀው እሺ ሳይሉ ቀርተዋል፡፡ ቄሱ እስኪሰጥሙ ድረስ ከሞት ጋር የተፋጠጡ ክርስቲያኖችን ኑዛዜ (ንስሐ) ሲሰሙ እና ስርየት ሲለምኑ ነበር፡፡
የታይታኒክ ዋና ካፒቴን ኤድዋርድ ስሚዝ ለመርከቧ ሰራተኞች ያስተላለፉት የመጨረሻ መልዕክት እንዲህ የሚል ነበር፡፡ “ወድ ሰራተኞች የሚጠበቅባችሁን ሁሉ አድርጋችሁል፡፡ ከዚህ በላይ እንድታደርጉ የምጠይቃችሁ ምንም ነገር የለም፡፡ የባህር ላይ ህግን ታውቃላችሁ፡፡ አሁን ሁሉም ሰው ለራሱ ነው፡፡ ፈጣሪ ይባርካችሁ”፡፡

ታይታኒክ ከባህር በታች በ3 ሺህ 840 ሜትር ጥልቀት ነው የሰጠመችው፡፡

ታይታኒክ ከመስጠሟ ከ14 ዓመታት በፊት በ1898 ሞርጋን ሮበርትሰን የተባለ እውቅ ደራሲ ‘ሊሰጥም የማይችለው መርከብ (unsinkable ship) ከበረዶ ግግር ጋር ተላትሞ ሰጠመ’ የሚል ጭብጥ ያለው መጽሐፍ ለንባብ አብቅቶ ነበር፡፡ ደራሲው በምናብ ለፈጠራት መርከብ የሰጣት መጠሪያም “ታይታን” የሚል ነበር፡፡

የታይታኒክ መርከብ ፍርስራሽ የተገኘው አደጋው ከደረሰ ከ73 ዓመታት በኋላ ዶ/ር ሮበርት ባላርድ በተባለ አሜሪካዊ የስነ ውቅያኖስ ተመራማሪ ነበር፡፡ ጊዜውም እ.አ.አ 1985 ዓ.ም ነበር፡፡

የታይታኒክ ፊልም መሪ ተዋናይት ኬት ዊንስሌት “ማይ ኸርት ዊል ጎ ኦን” የተሰኘውን የፊልሙን ማጀቢያ ሙዚቃ እንደምትጠላው ተናግራ ነበር፡፡ ኬት “ሙዚቃውን ስሰማው ሊያስመልሰኝ ይደርሳል“ ነበር ያለችው፡፡

ታይታኒክ ፊልም በ11 ዘርፎች ኦስካር (አካዳሚ አዋርድ) አሸንፏል፡፡ ከሽልማቶቹ ውስጥ ግን አንዱም በተውኔት ዘርፍ የተገኘ አይደለም፡፡ የፊልሙ መሪ ተዋናዮች ኬት ዊንስሌት እና ሊዮናርዶ ዲ ካፔሪዮ በምርጥ ትወና አልተሸለሙም፡፡

© ኢዮብ መንግስቱ - በአብሮነት እንቆይ
@kinchebchabi

We recommend to visit

★ሰውን በማዝናናት የብቃት ማረጋገጫ ያለው ብቸኛው ቻናል ሁሌም Telegram ላይ በጥበብ ደምቀን እናሸበርቃለን

💌 Contact us, @Modenyazbot

»የተመረጡ እና ማንም ያላያቸው የአማሪኛ ቀልዶች እንዲሁም የሚያስደንቁ ስዕሎችንና ቪዲዮ ያገኛሉ።

° ° [ ሙድ እንያዝ በእኛ የአራዶች መዝናኛ ] ° °

° ° Creator @Teke_Man ° °

Last updated 1 month, 1 week ago

☕ ስለ ኢትዮጲያ ቡና የሚወጡ ወቅታዊና ትክክለኛ የክለቡ መረጃዎች አዚህ ያገኛሉ!

➪የዝዉዉር ዜና
☞የአሰልጣኞች አስተያየት
➪ጎሎች እና ቪዲዮዎች
☞የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
➪ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት ከየስታድየሙ !

➡መወያያ ግሩፓችን @Ethiopia_coffee_Sc

📩ሀሳብ ወይም አስተያየት ካሎት
በዚህ 👉 @EthiopianCoffeeScBot ✍
BOT ማድረስ ይችላሉ!

Last updated 3 months, 2 weeks ago

ማንኛውንም የማስታወቂያ ስራ ለማሰራት የምትፈልጉ(only promotion) inbox @Eyyiba
ሌሎች ጥያቄዎችን ለማድረስ
@Ethiodailyvacbot

Last updated 1 day, 11 hours ago