Dive into the Ultimate Free Library: Your One-Stop Hub for Entertainment!

የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

Description
ይህ ቻናል በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ፈቃድ ትምህርቶች የሚለቀቁበት ነው::
@deaconhenokhaile

"ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን"
2ኛ ቆሮ. 2:14
We recommend to visit

ከቅዳሜ በስተቀር በየዕለቱ፣ ከሰኞ እስከ ዓርብ ረፋድ ከ3:30 እስከ 5:00፣ እሁድ ከጠዋቱ 2:00 እስከ 4:00 በብስራት ኤፍ ኤም 101.1

Last updated 6 days, 8 hours ago

የስራ ማስታወቂያ ከጋዜጣ ፣ ከቲቪና ራዲዮ ፣ ከማስታወቂያ ቦርድ ፣ ከድህረ-ገፅና ከማህበራዊ ሚዲያና ከመሳሰሉት ቦታዎች በአንድ ቦታ ተሰብስበው ያግኙ::

#Group t.me//Ethio_Jobs2000




#የመዝናኛ ቻናል https://t.me/+UPjrnHF6QzI0ZmQ0

https://t.me/+h0l2XzeI8RQyODlk

For promotion 📩 @Share_Home

Last updated 1 week ago

Certified Professional Life Coaches
የቻናላችንን አነቃቂ ቪዲዮ መመልከት ለምትፈልጉ
https://www.youtube.com/@inspireethiopiamedia 👈 ይሄንን ሊንክ ይጫኑ

Last updated 4 months ago

1 month, 1 week ago

ቅትለተ መነኮሳት ከዝቋላ ወደ ደቡብ አፍሪቃ

አባ ተክለ ሃይማኖት (አባ ተክላ) ደቡብ አፍሪቃ ገጠር ውስጥ የሚያገለግሉ መነኩሴ ነበሩ:: ወላጆቻቸው ለኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ምልጃቸውን በመማጸን ተስለው ስለወለዱአቸው ስማቸውን በጻድቁ ስም ሰይመዋቸዋል:: ከባለጸጋ ቤተሰብ የተወለዱትና የሚተዳደሩበት የራሳቸው መርከብ የነበራቸው እኚህ ወጣት የእንጦንስ የመቃርስን መንገድ ተከትለው ሀብታቸውን ሸጠው ለድኆች ሠጥተው የቀረውን ለገዳም አውርሰው መነኮሱ:: ከዓመታት በፊት በገዳማቸው ተገኝቼ በረከት በተቀበልሁበት ወቅት እንዴት እንደመነኮሱ ፣ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ያላቸውን ፍቅርና አንዳንድ ነገሮችን አጫውተውኝ ነበር:: ለእኔም ያሳዩት ስስትና ፍቅር ከሕሊናዬ የማይጠፋ ነው:: ዛሬ በግፍ ሰማዕትነትን እንደተቀበሉ ቢቢሲ ዘግቦ አየሁ:: ሰይጣን የእውነተኛይቱን ቤተ ክርስቲያን አድራሻ መቼም አይሳሳትም::

በግብፃዊው ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ስም በተሰየመ ገዳም የመነኮሱ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት በሆኑ በሳምንቱ በኢትዮጵያዊው ጻድቅ ተክለ ሃይማኖት ስም የተሰየሙ መነኩሴ ከወንድሞቻቸው ጋር ሰማዕትነት ተቀበሉ:: ሰይጣን ከሃይማኖታችን እንጂ ከዘራችን ጠብ የለውም::

ሰአሉ ለነ አስተምሕሩ ለነ
እስመ በጸሎተ ጻድቅ ትድኅን ሀገር

“በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ" ማቴ. 24:9

https://www.facebook.com/share/U25yhRDtJaBojkjB/?mibextid=WC7FNe

Facebook

Log in or sign up to view

See posts, photos and more on Facebook.

2 months ago

ምንኩስና የተጀመረው እንዴት ነበር? ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻዎቹ ባሻገር የምንኩስናን ታሪክ ስናጠና በ4ኛው ክፍለ ዘመን እንደተጀመረ ይታወቃል:: ለሦስት መቶ ዓመታት በአሰቃቂው ዘመነ ሰማዕታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መከራ ስትቀበል ክርስቲያኖችም በየቀኑ ሲገደሉ የነበረበት ዘመን ድንገት አበቃ:: በደማቸው ለመጠመቅና በሞታቸው ክብር ለመቀዳጀት የተዘጋጁ ምእመናንን ድንገት "በቃ ከእንግዲህ አትሞቱም" የሚል አዋጅ ታወጀባቸው::

ዕረፍት አገኘን ብለው የተደሰቱ እንደነበሩ ሁሉ ለሰማዕትነት ቆርጠው ለክብር አክሊል ተዘጋጅተው የነበሩ ብዙዎች ግን ድንገት ሰማዕትነት ሲቆም አዘኑ:: ከሰማዕትነት ክብር ወርደው እንደማንኛውም ሰው መኖር ከበዳቸው:: ስለዚህም በሰይፍ ባይሞቱም በፈቃዳቸው ሞተው ለክርስቶስ ሕያው ሆነው ሊኖሩ ወደ ገዳማዊ ሕይወት ወደ ምንኩስና ጎረፉ:: ይህም ክስተት ለምንኩስናና ለገዳማዊ ሕይወት ምክንያት ሆነ::

ዝቋላን በመሳሰሉ ገዳማት የሚገኙ መነኮሳት በሥጋ የሚሞቱበት ቀን ሳይደርስ በክርስቶስ ፍቅር በፈቃዳቸው የሞቱ ሐዋርያው እንዳለው "ሥጋን ከክፉ ምኞቱና መሻቱ ጋር የሰቀሉት" ናቸው:: ሰማዕትነትም ቀድመው የተመኙት ክብር ነበር:: በእነርሱ መገደል የሞትነው በእነርሱ ጸሎት ብርሃንነት የምንኖር ፣ ስንጨነቅ ከእግራቸው ሥር የምናለቅስ ፣ በዓለም ማዕበል ስንላተም በመስቀላቸው መልሕቅ ወደ ጸጥታ ወደብ የምንደርስ እኛው ነን::

ባለቆቡ ሰማዕት አባቴ ሆይ እርስዎን የገደሉ የገደሉት የእኔን ተስፋ ነው:: ሰማዕቱ መነኩሴ ሆይ በእርስዎ ሞት የተቀደደው የዕንባዬ መሐረብ ነው:: አንጀታችን በኀዘን እርር የሚለው ለእናንተ ሳይሆን ለራሳችን ነው:: ከእናንተ ጸሎት በቀር ምርኩዝ የሌለን እኛ ይለቀስልን እንጂ ለእናንተ አናለቅስም:: ቀድማችሁ የጠላችኋት ዓለም ብትጠላችሁ አይገርምም:: በፍቅርዋ ለተሸነፍን ለእኛ ግን ዕንባ ያስፈልገናል:: እውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን የትኛዋ እንደሆነች ፣ ዘመነ ሰማዕታትን የምትደግመዋ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ማን እንደሆነች በደማችሁ ያሳያችሁ ምስክሮች ሆይ ለእኛ እንጂ ለእናንተ አናለቅስም:: የእኛን እግር ከማጠብ ፣ የእኛን ብሶት ከመስማት ፣ የእኛን የክርስትና ስም ዘወትር በጸሎት ከመጥራት ፣ እኛን ተቀብሎ ከማስተናገድ አረፍ ብላችሁ ከመነኮሳችሁለት አምላክ ዕቅፍ ስለገባችሁ አናዝንም:: የምናዝነው በተራራ ላይ ያለ መብራታችን ለጠፋብን ለእኛ ነው:: የእኛ ደብረ ታቦር ዝቋላ ሥሉስ ቅዱስ በደመና ይጋርድሽ እንጂ ምን እንላለን?

ገዳምንና ገዳማውያንን መንካት የንቡን ቀፎ ማፍረስ ነው:: ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ ዐቃቢት ያሉት ሁሉ በገዳም ቀፎነት የተሠሩ የማር እንጀራዎች ናቸው:: ማሩን የሚጋግሩት ንቦች ያሉት ከቀፎው ገዳም ውስጥ ነው:: የአቡየ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የቆብ ልጆች በአስኬማ ላይ የሰማዕትነት አክሊል የደረባችሁ ቅዱሳን መነኮሳት ጸልዩልን በዙፋኑ ፊት ቆማችሁ "ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?" ብላችሁ ስለ እኛ አማልዱ:: (ራእ. 6:10)

2 months ago

**"ይህችን ዓመት ተወኝ!"

ከዓመት እስከ ዓመት - ፍሬን ሳላፈራ - ደረቅ እንደሆንኩኝ
በራድ ወይም ትኩስ - ሁለቱንም ሳልሆን - እንዲያው ለብ እንዳልኩኝ
አለሁኝ በቤትህ - ለሙን መሬትህን - እያጎሳቆልኩኝ
አውቃለሁ አምላኬ - ፍሬዬን ለመልቀም - እንዳመላለስኩህ
ዛሬም ሳላፈራ - እሾህን አብቅዬ - ደርቄ ጠበቅሁህ
ያልተደረገልኝ - ያላፈሰሰክብኝ - ያልሰጠኸኝ የለም
ነገር ግን ይህ ሁሉ - አላርምህ አለኝ - አልለየኝም ከዓለም
የማትሰለቸኝ ሆይ - ተነሥቼ እስክቆም - እባክህ ታገሠኝ
የእኔን ክፋት ተወው - መልአክህን ሰምተህ - ይህችን ዓመት ተወኝ!

አውቃለሁ ታውቃለህ - ቀጠሮን ሰጥቼ - እንደማላከብር
ብዙ ጊዜ አቅጄ - ብዙ ጊዜ ዝቼ - በወሬ እንደምቀር
‹ዘንድሮስ…!› እንዳልኩኝ - አምና ይሄን ጊዜ - ሰምተኸኝ ነበረ
ምንም ሳልለወጥ - ‹ዘንድሮዬ› አልፎ - በአዲስ ተቀየረ
ፍሬ የማይወጣኝ - እኔን በመኮትኮት - እጆችህ ደከሙ
እኔ ግን አለሁኝ - ዛሬም አልበቃኝም - በኃጢአት መታመሙ
የቃልህን ውኃ - በድንጋይ ልጅህ ላይ - ሳትታክት ስታፈስስ -
ዘመን ተቆጠረ
ወደ ልቤ ሳይሰርግ - ሕይወቴን ሳይለውጥ - እንዲያው ፈስሶ ቀረ
ቃልህን ጠግቤ - እያገሳሁት ነው - ሌሎች እስኪሰሙ
በቃልህ መኖር ግን - አልያዝህ አለኝ - ከበደኝ ቀለሙ
ብዙ ጥቅስ አገኘሁ - ከቅዱስ መጽሐፍህ - ገልጬ አይቼ
ከራሴ ላይ ብቻ - አንድ ጥቅስ አጣሁኝ - በበደል ተኝቼ
ውጤቴ ደካማ - ትምህርት የማይሠርጸኝ - ተማሪ ብሆንም
ይህችን ዓመት ተወኝ - ደግሞ ትንሽ ልማር - ታገሠኝ አሁንም!

እባክህ አልቆረጥ - በቅዱስ መሬትህ - ልቆይ ፍቀድልኝ
ያፈሩት ቅዱሳን - የፍሬያቸው ሽታ - መዓዛ እንዲደርሰኝ
የተሸከምከኝ ሆይ - ዛሬም ተሸከመኝ - አትሰልቸኝ አደራ
ማን ይታገሠኛል - ጠላት እየሆንኩት - አይሠሩ ስሠራ!
አታውጣኝ ከቤትህ - ብዙ ቦታ አልይዝም - ፍሬ ስለሌለኝ
ስፍራ የማያሻኝ - ቤት የማላጣብብ - ፍሬ አልባ በለስ ነኝ!
ቦታስ የሚይዙት - ባለ ምግባሮቹ - ቅዱሳንህ ናቸው
ልክ እንደ ዘንባባ - የተንዠረገገ - ተጋድሎ ጽድቃቸው!
ከሊባኖስ ዝግባ - እጅጉን የበዛ - ገድል ትሩፋታቸው!
እኔ አይደለሁም - ቦታስ የምትይዘው - የአንተው እናት ናት
ሥሮቿ በምድር - ጫፎቿ በሰማይ - ሲደርሱ ያየናት
ይሀችን ዓመት ተወኝ - ከሥርዋ እሆናለሁ - ባፈራ ምናልባት!..
ይህችን ዓመት ተወኝ - እባክህ አምላኬ - አንድ ዓመት ምንህ ናት
ሺህ ዓመት አንድ ቀን - አይደለም ወይ ለአንተ - ዓመት ኢምንት ናት!
ይሄ ዓመት አልፎ - ዳግም ‹ዓመት ሥጠኝ› - እስከምልህ ድረስ
እባክህን ጌታ - ይህችን ዓመት ተወኝ - የወጉን እንዳደርስ!

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

---**

2 months, 3 weeks ago

https://youtu.be/Iua2noVYn9w?si=ULy1bGIyCyqDqx1Q

YouTube

🛑ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ || ኢየሱስ የሚሉት አዲስ ንጉሥ@arganon #የአእላፋትዝማሬ @janderebaw_media

#እንኳንአደረስዎ #like #Share #Subscribe @arganon @janderebaw\_media https://youtube.com/@arganon ይህንን ቻናል Subscribe በማድረግ አገልግሎቱን ይደግፉ።ለወዳጅዎም በማጋራት የእግዚአብሔር ቃል እንዲዳረስ የበኩልዎን ይወጡ። እግዚአብሔር ያክብርልን!! Any way of reproducing, reposting & reusing of this video is…

2 months, 3 weeks ago

በከበረች ጸሎቱ ይቅር ይበለንና ራሱን በትሕትና "ከጌቶች ልጆች የሚወድቀውን ፍርፋሪ የሚለምን ውሻ" ብሎ የሚጠራው ሶርያዊው ኮከብ ቅዱስ ኤፍሬም በየድርሰቶቹ መካከል እንዲህ እንዲህ አለ:-

"ጌታችን ከሣምራዊትዋ ሴት ጋር በተነጋገረ ጊዜ በንግግራቸው መጀመሪያ ማንነቱን አልገለጠላትም። መጀመሪያ ያየችው ውኃ የጠማውን ሰው ነበር ፣ ከዚያ አይሁዳዊ ፣ ከዚያ መምህር (ረቢ) ፣ ቀጥሎ ነቢይ ከሁሉም መጨረሻ መሲህ መሆኑን አየች።
ውኃ የተጠማውን ሰው በንግግር ልትረታ ስትሞክር በአይሁዳዊ ላይ ያላትን ጥላቻ አሳየች። ከመምህሩ ጋርም ተከራከረች ፣ ከነቢዩ እግር ስር ተንበረከከች ፣ መሲሁንም ወደደችው"
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (ስለ ሣምራዊቷ ሴት ዮሐ 4:1)

★ ★ ★

"ጌታ ሆይ ለእኛ ፊት ክብርን የሠጠ እንደ አንተ ያለ ማን አለ?
የዕውሩን ዓይን ባበራህለት ጊዜ ላድነው ነህ ብለህ በፊቱ ላይ አልተፋህበትም።
ነገር ግን አርኣያችንን አክብረህ በመሬት ላይ እንትፍ ብለው ፈወስከው።
ጌታዬ ሆይ በእኔ ላይ ግን በፊቴ ላይ እንትፍ በልብኝ ፣ በፈቃዴ ያጠፋሁትን ዓይኔን በፈቃድህ አብራልኝ"

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
(ዕውር ሆኖ ስለተወለደው ዮሐ 9:30)

★ ★ ★
"ጌታ ሆይ ዕውሩን ሂድ ብለህ ወደላክህበት ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ አሁን ልንሔድ አንችልም። ነገር ግን ሕይወትንና ብርሃንን የተሞላው የከበረ ደምህ ያለበት ጽዋ በእኛ ዘንድ አለ። ከእርሱ በተቀበልን ቁጥር እንነጻለን" ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ

★ ★ ★

"ጌታዬ ሆይ በሔድኩበት ውጣውረድ የተሞላ መንገድ እምነቴ ደከመ ፣ መንገዱ የሚወስደኝም በግራ ወደሚቆሙት ፣ በደጅ ቆመው ክፈትልን ሲሉህ "አላውቃችሁም" ከምትላቸው ወገን ልሆን ነው።
ጌታዬ ሆይ እኔ አውቅሃለሁ ፣ አንተ ግን አላውቅህም ትለኝ ይሆን? አቤቱ በአንተ ለማምን ለእኔ ለኃጢአተኛው ራራልኝ። ብበድልህም እንኳን አሁንም በርህን እያንኳኳሁ ነው። እየተጎተትኩም ቢሆን አሁንም የምጓዘው ወደ አንተ ለመምጣት ነው"

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (ማቴ 7:7)
★ ★ ★

"ጌታ ሆይ እነዚህን በዕድሜ ሕፃናት የሆኑ የመንፈስ ልጆቼን ይቅር በላቸው። ሕፃን የነበርከው ሆይ የሕፃንነትህን ጊዜ አስብ። ልጅነታቸው ያንተን ልጅነት እንዲመስል አድርግላቸውና በቸርነትህ አድናቸው"
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ከተለያዩ መዝሙራቱ (Hymns) በተርጓሚው ተለቃቅሞ የተሰበሰበ
ኅዳር 26 2011 ዓ ም
ክርስቲያን ሳንድ
Deacon Henok Haile

3 months, 1 week ago

የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ (ርእስ)

የአእላፋት ዝማሬን ዕውን ለማድረግ ላለፉት ሦስት ወራት እንቅልፍ ያጡ ፣ የታመሙ ፣ ልባቸው በስድብና በሽሙጥ ንግግር የቆሰለ ፣ በረዣዥም ስብሰባዎችና የጉልበት ሥራዎች የዛሉ ፣ ዝግጅቱን በዚህ ደረጃ ከፍ እንዲል ሰዎችን አሳምኖ ገንዘብ በማሰባሰብ የተንከራተቱ ፣ በአንድ ትንፋሽ ሠላሳ መዝሙር ሲያጠኑ የከረሙ ፣ መዝሙር ለማስቀረጽ ሥራ ትተው በስቱድዮ የዋሉ ፣ ሦስት ጊዜ revise የተደረገውን Stage design የሠሩ ፣ በመሐረነ አብ ጸሎት በየአድባራቱ ደጅ የጠኑ ፣ የዘማርያን ልብስና ልብሰ ተክህኖ ዲዛይን ሲያደርጉ ፣ ተነግሮ የማያልቅ ድካም የደከሙ ትሑታንና ታዛዦች የሆኑ የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ የቦርድና የሥራ አስፈጻሚ አባላት ፣ የጃን ያሬድ ኅብረ ዝማሬ መዘምራን ፣ የጃን አጋፋሪ event organizing ቡድንና በሥሩ የተቋቋሙ 15 ቡድኖች ፣ የጃን አግናጥዮስ የሕፃናትና አዳጊዎች project አባላት ፣ የጃን እስጢፋኖስ ዲያቆናት ፣ የጃንደረባው ሚድያ እሳት የላሱ የካሜራና ኤዲቲንግ የግራፊክስ ባለሙያዎችና የማኅበራዊ ሚድያ ዘመቻ ወጣቶች የአእላፋት ዝማሬን እውን ለማድረግ የከፈሉት መሥዋዕትነት እጅግ ብዙ ነው::

ለዚህ አገልግሎት ምስጋና የሚገባው ዕንባና ተማጽኖአችንን ያልናቀ ልዑል እግዚአብሔር ነው::

ዓለም ዘመኑ ጥሩ አይደለም ብላ ስካሩን ጭፈራውን ፈንጠዝያውን ግድያውን አላቆመችም:: እኛም ስብሐተ እግዚአብሔር የወቅቱን ሁኔታ እያየች የማታስታጉል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች እንደመሆናችን ሲከፋን የምንተወው ደስ ሲለን የምንቀጥለው መዝሙር የለም ብለው ለጸሎተ ምሕላና ለአእላፋት ዝማሬ የተሠጡ ወጣቶች ብዙ ናቸው:: "አርምሞ ጽርዓት በሌለበት ምስጋና ሳናቋርጥ ዘወትር እናመሰግንሃለን:: ይኸውም ሊቃነ መላእክት የሚያመሰግኑህ ምስጋና ነው" (ጸሎተ ኪዳን)

ምግብ ቤት ገብተን ጥሩ ስንበላ አስተናጋጁን እናመሰግናለን:: ቲፕ እንሠጠዋለን:: ማዕድ ቤት ውስጥ እሳት የበላቸውን ሼፎችና ተባባሪ ሠራተኞች ግን አናያቸውም:: የአእላፋት ዝማሬንም በተመለከተ ሊመሰገን የሚገባው እንቅልፉን የሠዋ ብዙ ወጣት ከጀርባ አለና አስተናጋጁን ለቀቅ አድርጋችሁ ሼፎቹ ላይ አተኩሩ::
ከዚያ ውጪ ግን ከታመነበት ተአምር መሥራት የሚችለውን ቅን 1/21ኛውን ጃን ያሬድ ብቻ ሳይሆን መላውን የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ በጸሎት በገንዘብ በሃሳብ ደግፉ::

የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድን ለመደገፍ

https://donate.janderebaw.org/

በቴሌ ብር
Merchant ID 777582
The Ethiopian Jandereba Generation

8261
Commercial Bank of Ethiopia

8261
Abyssina Bank

Janderebaw Media
የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ The Ethiopian Jandereba Generation

donate.janderebaw.org

የሚከለክለኝ ምንድን ነው

የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ ታኅሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ዋዜማ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን የሚሳተፉበት 'የአእላፋት ዝማሬ' የተሰኘ የአደባባይ ዝማሬ ዝግጅት ያከናውናል። ይህንን አገልግሎት ለመደገፍ የሚከተለውን ሊንክ በመጠቀም የበረከቱ ተካፋይ ይሁኑ።

4 months, 2 weeks ago

ነቢያት ጌታ "ይወርዳል ይወለዳል" ብለው የተናገሩት ትንቢት እንዲፈጸም ተመኝተው ጾሙ ጸለዩ:: እኛ ስለምን እንጾማለን? ክርስቶስ ተወልዶ ፣ ተጠምቆ ፣ አስተምሮ ፣ ተሰቅሎ ፣ ሞቶ ፣ ተነሥቶ ፣ ዐርጎ ፣ በአባቱ ቀኝ አይደለምን? አሁን ለምን እንጾማለን? ብለን እናስባለን::

ጌታ በእኔና አንተ ልብ ውስጥ እውነት ተወልዶአልን? እውነት የእኛ ልብ እንደ ቤተልሔም ግርግም ለክርስቶስ ማደሪያ ሆኖአል? ማደሪያ አሳጥተን ከእናቱ ጋር አልመለስነውም?

የጥምቀቱ ትሕትና በእኛ ልብ መቼ ደረሰ? የስቅለቱ ሕማም መች በእኛ ሕሊና ተጻፈ? የትንሣኤው ተስፋ የዕርገቱ ልዕልና በእኛ ልቡና መቼ ዐረፈ?

ስለዚህ ነቢያት "ውረድ ተወለድ" ብለው የጾሙትን ጾም እንጾማለን:: ጌታ ሆይ በእኔ ሕይወትም ውስጥ ውረድ ተወለድ የእኔን ሰውነት ማደሪያህ አድርገው:: ሕዋሳቶቼ ከኃጢአት አርፈው እንደ ቤተልሔም ግርግም ማደሪያህ ይሁኑ::

የቤተልሔም እንስሳት ትንፋሽ ገበሩልህ ፣ የቢታንያ ድንጋዮች ዘማሪ ቢጠፋ ሊዘምሩ ዝግጁ ነበሩ ፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለክብርህ ተቀደደ ፣ ጨረቃ ላንተ ደም ለበሰች ፣ ፀሐይ ስላንተ ጨለመች ፣ ከዋክብት ለስምህ ረገፉ ፣ ዓለቶች ለፍቅርህ ተሰነጠቁ::

ከቤተልሔም እንስሳት ፣ ከቢታንያ ድንጋዮች ፣ ከቤተ መቅደስ መጋረጃ እኔ እንዴት አንሼ ልገኝ? የቢታንያ ድንጋይ ያወቀህን ያህል ሳላውቅህ ፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ የተረዳህን ያህል ሳልረዳህ እንዴት ልኑር?

ዓለት ላንተ ሲሰነጠቅ የኔ ልብ ለምን ከዓለት ደነደነ? ጨረቃ ደም ስታለቅስ እኔ መከራህ ለምን አልተሰማኝም?
ሙታን በሞትህ ሲነሡ እኔ ምነው ከኃጢአት ሞት መነሣት ተሳነኝ?

ለዚህ ነው በእኔ ሕይወት ገና አልተወለድክም የምለው::

ስለዚህ ጌታ ሆይ የነቢያትህን ጾም ጸሎት ሰምተህ የወረድህ የተወለድህ ጌታ ሆይ በእኔም ሕይወት ውረድ ተወለድና እኔም ከመላእክት ጋር አብሬ ልዘምር ፣ ከሰብአ ሰገል ጋር ሥጦታህን ልቁጠር ፣ ከእረኞች ጋራ ልደነቅ:: ልደትህ ሳይገባኝ ምጽዓትህ እንዳይደርስብኝ እርዳኝ::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጾመ ነቢያት 2015 ዓ.ም. የተጻፈ

6 months ago

የትምህርት ዕድል ያመለጠህ መስሎህ ነው? ገና ሺህ የትምህርት ዕድሎች አሉህ:: ዕድሜህ ያመለጠህ መስሎህ ነው? ነገ የሚጠብቁህ ብሩሕ ዘመናት እኮ ቁጭ ብለው አሉ? የሚረዳኝ ሰው የሚያስብልኝ ሰው አጥቼያለሁ? ብለህ ከሆነም ካልሰሙህ ጥቂቶች በላይ ልንሰማህ የምንሻ "ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ"

መከራ ጸናብኝ ኑሮ ጨለመብኝ የሀገሪቱ ሁኔታ ተስፋ አሳጣኝ ብለህ ይሆን? እኛስ አብረንህ አይደልንም? አብረን ከገባንበት ችግር አብረን ብንወጣ አይሻልም? ከአንተ በባሰ ሁኔታ የታሰርንና የተገረፍን ጳውሎሶችና ሲላሶች "ሁላችን በዚህ አለንና በራስህ ክፉ አታድርግ" ስንልህ ስማን::

ይልቅ አንተም እንደ ወኅኒው ጠባቂ "እድን ዘንድ ምን ላድርግ ብለህ?"ነፍስህን የምታድንበትን መንገድ ወደ መቅደሱ ቀርበህ ጠይቅ::

ወዳጄ ይህንን ጽሑፍ ያነበብኸውም በሕይወት ስላለህ ነው:: የአንተን ዓይን የሚጠብቁ ብዙ ጽሑፎች ፣ የአንተን ጆሮ የሚፈልጉ ብዙ ድምፆች ፣ የአንተን መሐረብ የሚፈልጉ ብዙ ዕንባዎች ፣ የአንተን ሳቅ የሚፈልጉ ብዙ ቀልዶች ... ገና ብዙ ብዙ አሉ::

ስለዚህ ሰይጣንን አሳፍረው:: እንዲህ በለው :-

"ጠላቴ ሆይ፥ ብወድቅ እነሣለሁና፥ በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና በእኔ ላይ ደስ አይበልሽ" ሚክ. 7:8

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥቅምት 2016 ዓ.ም.
ሜልበርን አውስትራሊያ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

6 months ago
  • በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ +

ይድረስ ለተከፋኸው ወንድሜ
መኖር ለደከመህ ፣ ሕይወት ለታከተህ ፣ የሚሰማህ ላጣኸው ፣ የሚረዳህ ሰው ላላገኘኸው መከረኛው ወዳጄ!

ከሞት ውጪ ሌላ መፍትሔ አልታይ ካለህ የአንተ ቢጤ መከረኞቹ ጳውሎስና ሲላስ እስር ቤት ውስጥ ሆነው እንዲህ ይሉሃል::

"በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ" ሐዋ. 16:28

አውቃለሁ ዙሪያው ገደል ሆኖብሃል:: ምነው ባልተፈጠርሁ እስክትል ድረስ ተጨንቀሃል::
ግን ይህ ስሜት በአንተ አልተጀመረም:: ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ኑሮ ያልመረረው ማን አለ? መሞት ያልተመኘስ ማን አለ?

ሞት ያማረህ አንተን ብቻ መሰለህ?

" ስለ ምን ከማኅፀን አወጣኸኝ? ዓይን ሳያየኝ ምነው በሞትሁ" ያለውን ጻድቅ ኢዮብ አልሰማህም? (ኢዮ. 10:18)

"ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ" ብሎ እንዲሞት የለመነውን ኤልያስን አላየኸውም? 1ነገሥ. 19:4

ዮናስንስ "አሁንም፥ አቤቱ፥ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ፥ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ፡ አለው" ሲል አልሰማኸውም? (ዮናስ 4:3)

ወንድሜ እመነኝ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን መኖር ያላስጠላው ሰው በታሪክ ፈልገህ አታገኝም::

ሞት ሞት የሸተተው ልቡ የተሰበረ ብዙ ነው:: አንተ ላይ ብቻ የደረሰ ልዩ ፈተና የለም:: "ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል" ይላል መጽሐፍ:: 1ኛ ቆሮ. 10:13

ምናልባት የልብህን መሰበር የኀዘንህን ጥልቀት አይቶ ምቹ ጊዜ አገኘሁ ብሎ ራስህን እንድትጎዳ ሰይጣን ሊገፋፋህ ይችላል:: እንዴት እንዲህ ዓይነት ሃሳብ በልቤ ሊመጣ ቻለ ብለህ አትረበሽ:: ሰይጣን ይህንን ክፉ ሃሳብ ላንተ ብቻ ሳይሆን ለክርስቶስም አቅርቦለታል::

"የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር" ብሎ ክርስቶስን እንኳን [ማንነቱን ሳያውቅ] ራሱን እንዲወረውር ሊገፋፋው የሞከረ ደፋር ነው:: የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው ግን ራሱን አይጎዳም:: "ጌታ አምላክህን አትፈታተነው" "ሒድ አንተ ሰይጣን" ብለህ ሰይጣንን ገሠፀው::

ሰይጣን ክርስቶስን "ከሕንፃ ጫፍ በመወርወር የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አሳይ" ሲለው ክርስቶስ ሰይጣንን ሒድልኝ ብሎ በመገሠጹ በክብር ወደ ሰማይ ዐርጎ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ::
ወንድሜ ሆይ አንተም ሰይጣንን አትስማው ሃሳቡ ራስህን ጎድተህ ከፈጣሪህ እንድትጣላ ሊያደርግህ ነው:: ሰይጣንን ከገሠጽከው በእግዚአብሔር ቀኝ ከበጎቹ ጋር ትቆማለህ::

አሁን ያለህበት ችግር ያልፋል:: የሚሰማህ ክፉ ስሜት መቼም የማይለወጥ አይምሰልህ:: ኀዘኑም ፣ ብቸኝነቱም ፣ ተስፋ ቢስነቱም ያልፋል:: ጨለማው ይነጋል:: የተዘጋው በር ይከፈታል:: ችግሩ ሲፈታ አንተ ከሌለህ ግን ትርጉም የለውም::

ስለዚህ ለሚፈታ ችግር የማይቀለበስ ውሳኔ አትወስን:: ራስን ማጥፋት ከጊዜያዊ ችግር ለመሸሽ ሲሉ ዘላቂ ችግር ውስጥ መግባት ነው:: ጊዜያዊ ሕመምን ለማስታገስ የዘላለም ሕመምን ለምን ትመርጣለህ? "የሞተ ተገላገለ" ሲሉ ሰምተህ እንዳትታለል ሞት ዕረፍት የሚሆነው ራሱ እግዚአብሔር ሲጠራህ ብቻ ነው::
"እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ" ያለው ጌታ ሳይጠራህ ራስን ማጥፋት የዘላለም ስቃይ ያመጣል::

ወዳጄ "በራስህ አንዳች ክፉ አታድርግ"

የሕይወትህን ዋጋ ታውቅ ይሆን? አንተ እኮ የእግዚአብሔር ልጅ ለአንተ ሲል የሞተልህ ነህ:: ሊፈውስህ የቆሰለ ፣ ሊያከብርህ የተዋረደ ፣ ሊያረካህ የተጠማ ፣ ሊያለብስህ የተራቆተ ለአንተ እኮ ነው::
ክርስቶስ ስለ አንተ ሞቶአል:: አንተን ግን የጠየቀህ እንድትሞትለት ሳይሆን እንድትኖርለት ነው::
ለሞተልህ አምላክ እንዴት መኖር ያቅትሃል?

ወዳጄ ሆይ ሰውነትህ በአምላክ ደም የተገዛ ክቡር ሰውነት ነው:: አካልህ "አንተ" እንጂ "ያንተ" አይደለም:: "በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ" ይላል

ስለዚህ በከበረ የእግዚአብሔር ልጅ ደም የተገዛ ሰውነትህን ለሰይጣን በርካሽ አትሽጠው:: አትግደል የሚለው ሕግ ራስህንም ይጨምራል:: ቤተ መቅደስ የሆነ ሰውነትህን ለማፍረስ አታስብ::
"ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ" 1ኛ ቆሮ. 3:17

ሰዎች አስቀይመውህ ይሆን?

"አሳያቸዋለሁ ፤ ስሞት የእኔን ነገር ይገባቸዋል" ብለህ በሰዎች ተቀይመህ ራስህን አትጉዳ:: እመነኝ ብትሞት ሰዎች ከሳምንት በላይ አያስታውሱህም:: ለሕይወትህ ዋጋ ያልሠጡ ሰዎች ለሞትህ ዋጋ አይሠጡም:: ፈጥነውም ይረሱሃል:: ለሚረሱህ ሰዎች ብለህ የማይረሳህን አምላክ አታሳዝን:: ሰው ስለ አንተ ግድ የለውም እግዚአብሔር ግን የራስህን ቁጥር ሳይቀር በቁጥር ያውቀዋል :: እንኳንስ ራስህን ልትጎዳ አንዲት ጸጉር እንኳን ከአንተ እንድትወድቅ አይፈልግም::

እግዚአብሔርን በኃጢአት ብታሳዝነው እንኳን ኖረህ ንስሓ እንድትገባ እንጂ እንድትሞት አይፈልግም:: አባትህ ነውና ከእርሱ ጋር ባትሆንም እንድትኖር ይፈልጋል:: በምሳሌ ልንገርህ :-

ሁለት ሴቶች አንድን ሕፃን "የኔ ልጄ ነው" ብለው እየተከራከሩ ጠቢቡ ሰሎሞን ፊት ቀረቡ:: ጠቢቡ ሰሎሞን ሰይፍ አመጣና "ልጁን ቆርጬ ለሁለት ላካፍላችሁ" አላቸው:: አንደኛዋ ሴት "እሺ እንካፈል" ስትል እውነተኛዋ እናት ግን "ልጄ ከሚሞት እርስዋ ትውሰደው" አለች:: እናት መሆንዋም በዚህ ታወቀ::

ወዳጄ ያንተም ኑሮህ ከእግዚአብሔር ጋር ላይሆን ይችላል:: ዓለም የራስዋ አድርጋህም ይሆናል:: በሱስ ውስጥ ትዘፍቀህ ፣ እንደ ሶምሶን በደሊላ እቅፍ ፣ እንደ ዴማስ በተሰሎንቄ ውበት ተማርከህ ይሆናል:: እግዚአብሔር ግን አባትህ ነውና ሞትህን አይፈልግም::

"ልጄ ከሚሞት እርስዋ ትውሰደው" እንዳለችው እናት ፈጣሪህ ከነኃጢአትህም ቢሆን እንድትሞት አይፈልግም:: ከእርሱ ጋር ባትኖርም መኖርህን ይፈልጋል:: "የሟቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ" ሕዝ. 18:32

የይሁዳ ኃጢአቱ ጌታውን መሸጡ አልነበረም:: ራሱን መግደሉ ነው:: እግዚአብሔር የሚያዝነው ከበደልህ በላይ በእርሱ ተስፋ ቆርጠህ ራስህን ስትጎዳ ነው::

ወዳጄ የአንተን መኖር የሚፈልጉ ብዙ ናቸው:: ፈጣሪ ወደዚህች ዓለም ያለ ምክንያት አላመጣህም:: በአንተ አለመኖርም የሚጎድል ነገር አለ:: አንተን የሚመስል ሌላ ሰው አልፈጠረምና ለዚህ ዓለም አንተን የሚተካ የለም:: በክብር ወደዚህ ዓለም ያመጣህ አምላክ በክብር ወደራሱ እስኪወስድህ ድረስ "በራስህ ላይ ክፉ ነገር አታድርግ"

"የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ።
ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ፦ ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ፡ ብሎ ጮኸ" ሐዋ. 16:27-28

ይህ ሰው እስረኛ ያመለጠ መስሎት ራሱን ሊያጠፋ ሲል ጳውሎስ "ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ" አለው::

ወዳጄ አንተስ ተስፋ የቆረጥኸው ምን ያመለጠ መስሎህ ነው?

6 months, 2 weeks ago

"ውበት ሐሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ ነው:: እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች" ምሳ. 31:30

ቅድስት አርሴማን የምናመሰግናት ለዚህ ነው:: ቅድስት አርሴማ (St. Hripsime) በውበትዋ ምክንያት እስከ ሰማዕትነት ድረስ የደረሰች ቅድስት ናት:: በውበትዋ ከተማረከው ከንጉሥ ዲዮቅልጢያኖስ ሸሽታ ወደ አራራት ተራራ ስትሸሽ የአርማንያው ንጉሥ ድርጣድስ (Drtad) ያሳደዳትና እስከ ሰማዕትነት የበቃችው በሚያልፈው ውበት የማያልፈውን አምላክ ላለማጣት ነበር::

ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን

"ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም" ያለው ቃል ቅድስት አርሴማን አይመለከትም:: ዕብ. 12:4 እርስዋ ከኃጢአት ጋር ደም እስከማፍሰስ ተጋድላለች::
ውበት ሐሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ ነው እግዚአብሔር የምትፈራ አርሴማ ግን ትመሰገናለች::

We recommend to visit

ከቅዳሜ በስተቀር በየዕለቱ፣ ከሰኞ እስከ ዓርብ ረፋድ ከ3:30 እስከ 5:00፣ እሁድ ከጠዋቱ 2:00 እስከ 4:00 በብስራት ኤፍ ኤም 101.1

Last updated 6 days, 8 hours ago

የስራ ማስታወቂያ ከጋዜጣ ፣ ከቲቪና ራዲዮ ፣ ከማስታወቂያ ቦርድ ፣ ከድህረ-ገፅና ከማህበራዊ ሚዲያና ከመሳሰሉት ቦታዎች በአንድ ቦታ ተሰብስበው ያግኙ::

#Group t.me//Ethio_Jobs2000




#የመዝናኛ ቻናል https://t.me/+UPjrnHF6QzI0ZmQ0

https://t.me/+h0l2XzeI8RQyODlk

For promotion 📩 @Share_Home

Last updated 1 week ago

Certified Professional Life Coaches
የቻናላችንን አነቃቂ ቪዲዮ መመልከት ለምትፈልጉ
https://www.youtube.com/@inspireethiopiamedia 👈 ይሄንን ሊንክ ይጫኑ

Last updated 4 months ago