★ሰውን በማዝናናት የብቃት ማረጋገጫ ያለው ብቸኛው ቻናል ሁሌም Telegram ላይ በጥበብ ደምቀን እናሸበርቃለን
💌 Contact us, @Modenyazbot
»የተመረጡ እና ማንም ያላያቸው የአማሪኛ ቀልዶች እንዲሁም የሚያስደንቁ ስዕሎችንና ቪዲዮ ያገኛሉ።
° ° [ ሙድ እንያዝ በእኛ የአራዶች መዝናኛ ] ° °
° ° Creator @Teke_Man ° °
Last updated 1 month, 1 week ago
☕ ስለ ኢትዮጲያ ቡና የሚወጡ ወቅታዊና ትክክለኛ የክለቡ መረጃዎች አዚህ ያገኛሉ!
➪የዝዉዉር ዜና
☞የአሰልጣኞች አስተያየት
➪ጎሎች እና ቪዲዮዎች
☞የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
➪ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት ከየስታድየሙ !
➡መወያያ ግሩፓችን @Ethiopia_coffee_Sc
📩ሀሳብ ወይም አስተያየት ካሎት
በዚህ 👉 @EthiopianCoffeeScBot ✍
BOT ማድረስ ይችላሉ!
Last updated 3 months, 3 weeks ago
እንኳን ወደ # ሉሲ የቴሌግራም ቻናል በደህና መጡ
#የሉሲ /LUCY DINKINESH E/ቤተሰብ ሰለሆኑ ደስብሎናል።
መረጃ መስጠት የምትፈልጉ በዚ አድርሱን 👉 @CACA77
#ፋኖነት የአሸናፊነት መገለጫ አርማችን ነው!
ነፃነታችንን 💪በፈርጣማው ጡንቻችን ይረጋገጣል
👉 ፋኖነት /አማራነት /ኢትዬጵያዊነት አርበኝነት የማንነት አርማች ነው
🙏🙏🙏
Last updated 6 days, 14 hours ago
"ኃጢአት ከበጎ ነገር በተቃራኒ መስራት ብቻ አይደለም። በጎውን አውቆ አለመስራትም ኃጢአት ነው።"
ሮዝሜሪ/Rosemary/ - የማርያም አበባ
(ዲ/ን ሕሊና በለጠ)
ይህን ጽሑፍ ከምታነቡት ምናልባትም ብዙዎቻችሁ "ሮዝሜሪ ምንድን ነው?" ብላችሁ ደግማችሁ ሳታስቡ "የሥጋ መጥበሻ" ትሉኝ ይኾናል። ከዚህ በዘለለ የመረመሩት አሉና እነሆ!
ሮዝሜሪ መዓዛው የሚያስደስት፣ መልኩ ያማረና ቅጠሉን ለምግብ ማጣፈጫነት የምንጠቀመው ተወዳጅ የአበባ ተክል ነው። "ሮዝሜሪ/Rosemary" የሚለው ስም "ሮዝ/Rose/ - አበባ" እና "ሜሪ/Mary/ - ማርያም" ከሚሉት የተውጣጣ እንደ ኾነና ትርጉሙም "የማርያም አበባ" ማለት እንደ ኾነ የሚናገሩ ብዙ ኦርቶዶክሳውያንና ካቶሊካውያን አሉ። የዕፅዋት ሳይንስ ተመራማሪዎች ግን ስሙ "ros marinus" ከሚሉ የላቲን ቃላት የተገኘ መኾኑን ገልጠው ትርጉሙም "dew of the sea - የባሕሩ ጤዛ" ማለት እንደ ኾነ ያስረዳሉ። የእመቤታችን ወዳጆች ግን "የማርያም አበባ" ይሉታል።
ሮዝሜሪ ጥንታዊ ከሚባሉት ዕፅዋት አንዱ ነው። በተለይም በክርስቶስ ልደት ጊዜ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ነበሩት። አንዱ የሮዝሜሪ ጥቅም ትኋን፣ ቁንጫና የመሳሰሉትን ነፍሳት ለማስወገድ ማገልገሉ ነው። ስለዚህ የጥንት አይሁዳውያን በቤታቸው ውስጥ: በተለይም በፍራሻቸው ውስጥ ያደርጉታል። ጌታ በተወለደ ጊዜ: ቅዱስ ዮሴፍ ለሕፃኑ በግርግም ውስጥ የሚተኛበትን ፍራሽ ከሳር ሲያዘጋጅለት: ተባዮች እንዳያስቸግሩት ይህን ተክል እንደተጠቀመ ይታመናል።
የሮዝሜሪ ሌላኛው ጥቅሙ መዓዛው እንደ ሽቶ ማገልገሉ ነው። አይሁድ ልብስ ያጥቡና ሮዝሜሪ ላይ ያሰጡታል። ፀሐይዋ ስትወጣ ልብሱን ከማድረቅ ባሻገር የሮዝሜሪውን ዘይት እያተነነች ወደ ልብሱ ታመጣዋለች። ልብሱም የተክሉን መዓዛ ይይዛል። በዚያን ጊዜ የንጹሕ ልብስ መለኪያው ያንን መዓዛን መያዙም ጭምር ነበር። እመቤታችንም ጌታችንን የምትጠቀልልበትን ልብስ አጥባ በሮዝሜሪ ተክል ላይ ታሰጣው እንደ ነበር የታሪክ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
አይሁድ የሮዝሜሪን መልካም መዓዛ ለመቃብርም ይጠቀሙ ነበር። በመኾኑም የጌታችንን ትንሣኤ ያበሠሩት እነዚያ ሴቶች: በሌሊት ወደ መቃብሩ ሲገሰግሱ ሮዝሜሪን ይዘው እንደ ነበር ይነገራል።
እመቤታችን በስደቷ ጊዜ: ልጇን ከሄሮድስ ወታደሮች ለመሠወር ከሮዝሜሪ ቁጥቋጦ ሥር ተደብቃ እንደ ነበርም የሚገልጹ ብዙ ናቸው።
ተክሉን ከእመቤታችን ጋር እጅግ የሚያቆራኙት ሰዎች: ሮዝሜሪ ከስሙ ባሻገር የአበባውን ቀለምም ያገኘው በእመቤታችን ምክንያት እንደ ኾነ ይገልጻሉ። በአንድ ወቅት ድንግል እናታችን ካባዋን በአበባው ላይ ብትጥልበት: አበባው የካባዋን ቀለም ያዘ ይላሉ። ኾኖም: ይህን ገለጻ ለእመቤታችን ካለ ፍቅር አንጻር ለልጆች እንደሚተርኩት አፈታሪክ የሚወስዱት ብዙ ናቸው።
ዘመናዊ አጥኚዎች ሮዝሜሪ የማስታወስ ዐቅምን በ75 በመቶ እንደሚጨምር ይገልጻሉ። ለነገሩ አስቀድሞም ሼክስፒር በትራጄዲው ሐምሌት ድርሰቱ፣ በአራተኛው ትዕይንት፣ ኦፌሊያ (ጸጋዬ ገብረ መድኅን "ወፌ ይላ" ብለው ስሟን ተርጉመዋል) በተባለችው ገፀ ባሕርይ የታወቀ ንግግር ላይ "There’s rosemary, that’s for remembrance" ብሏል።
ሮዝሜሪን የኀዘንና የሞት መግለጫ ምሳሌ ተደርጎ እንደሚገለጽም የሚናገሩ የታሪክ ባለሙያዎች ደግሞ በራሱ በሼክስፒር የቀብር ሥርዓት ላይም የሮዝሜሪ የአበባ ጉንጉን የያዙ ኀዘንተኞች እንደነበሩም ይገልጻሉ።
ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስና ይህን የአበባ ዓይነት ብቻ ሳይኾን ብዙ አበቦችን ለእመቤታችንም ለጌታችንም በምሳሌነት ማንሣት በእኛም በሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት እጅግ የተለመደ ነው። በቀጣይ ሌሎችን ለማንሣት እንሞክራለን።
እስከዚያው ሮዝሜሪ ጥብስንና ምግብን ኹሉ እንደሚያጣፍጠው: እመቤታችንም ሕይወታችንን ታጣፍጥልን!
(ዘመነ ጽጌ፣ 2013 ዓ.ም.
hhilinabelete
ከገቢረ ኀጢአት ሳይወጡ አዲስ ዓመት ሲመጣ መደሰት፣ ብዙ መብልና መጠጥ ማዘጋጀት፣ አዲስ ልብስም መልበስ ጥቅም የለውም፡፡ ነፍሳችን በኀጢአት እየተጨነቀች፣ ነፍሳችን ተርባና ተጠምታ ሳለ፣ የተዳደፈ የኀጢአት ልብስም ተጆቡና ሳለ አዲስ ዓመት ማክበር ለእኛ ምን ጥቅም ይሰጠናል? እንዲህ ከገቢረ ኀጢአት ሳይወጡ አዲስ ዓመትን ማክበር ማለት ለእኔ እንደ ልጆች የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ነው፡፡
ክርስቶስ ከዚሁ ሥራ አውጥቶናል፡፡ ከሕፃንነት አዕምሮ ወደ ማወቅ አሸጋግሮናል፡፡ ከምድራውያን ለይቶ ከሰማያውያን ጋር ደባልቆናል፡፡ ስለዚህ “መልካሙን ሥራችሁን ዐይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” እንደ ተባለ አፍአዊ ሳይኾን መንፈሳዊውን ብርሃን ልናበራ ይገባናል (ማቴ.5፡16)፤ በአዲሱ ዓመት፡፡ ይህም ብርሃን ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን የሚያስገኝ ነው፡፡
ወዳጄ ሆይ! ቤቱ ቆሽሾ ሳለ ውጫዊ በሩን ብቻ ለማሽቀርቀር ለምን ትጨነቃለህ? ነፍስህ በኀጢአት ተዳድፋ ሳለ ሥጋህን ብቻ ለማስደሰት ለምን ትሮጣለህ? አስቀድመህ ቤቱን (ነፍስህን) ለማስዋብ አትሽቀዳደምምን? አስቀድመህ ለነፍስህ የምታስብ ከኾነ ከሰው እጅ ሳይኾን ከክርስቶስ እጅ ሹመት ሽልማት ትቀበላለህ፡፡ ኹል ጊዜ “የማደርገው ነገር እግዚአብሔር ይከብርበታልን?” ብለህ አስብ እንጂ እንዲሁ በዘልማድ የምትመላለስ አትኹን ብዬ እመክርኻለሁ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመክረን፡- “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትኾኑ ወይም ማናቸውም ነገር ብታደርጉ ኹሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ያለንም ስለዚሁ ነውና በአዲሱ ዓመት በድርጊቶቻችን ኹሉ እግዚአብሔርን ለማክበር እንዘጋጅ (1ኛ ቆሮ.10፡31)፤ አዲስ ዓመት ማክበር ማለት ይኼ ነውና፡፡
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
(ሰማዕትነት አያምልጣችሁ መጽሐፍ - #ገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ)
"አንተ ሐሳብህን ልትመራዉ እንጂ፤ ሐሳብህ አንተን ሊመራ ቦታ አትስጠዉ፥ እዉነተኛ ክርስቲያን ስሜቱ የሚመራዉ ሳይሆን ስሜቱን የሚመራ ነውና።"
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሸኖዳ ሣልሳዊ
‹‹አግርር ጸራ ታህተ እገረሃ እቀብ ህዝባ ወሰራዊታ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ›› ቤተክርስቲያን ለእምዬ ኢትዮጵያ ሰላም ዘወትር የምታቀርበው ጸሎት ነው፡፡ ጠላቶቿን ከእግሮቿ በታች አድርግላት ፤ ህዝብና ሰራዊቷንም ጠብቅ አሜን፡፡
አሁን አገራችን ከፖለቲከኞቿ ልታገኝ የሚገባት ነገር ሁሉ እንደ ጉም ተኖ ፤ እንደ ጢስ በኖ ጠፍቷልና ሰው ሲጨርስ፤ ተስፋ ሲቆርጥ እርሱ ገና ስራውን ወደሚጀምረው አምላክ የምናንጋጥጥበት ጊዜው አሁን ነውና ለጸሎት እንነሳ…
‹‹ተንሥኡ ለጸሎት››
የዚህ ቃል ትርጉም ለጸሎት ተነሱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥራዓተ አምልኮ ውስጥ ካሉ በርካታ ጸሎቶች ዋናውና ትልቁ በሆነው ጸሎተ ቅዳሴ ውስጥ ዲያቆኑ ደጋግሞ የሚያውጀው ቃል ነው … ተንሥኡ ለጸሎት፡፡
ይህ አዋጅ የሚያስታውሰን አንድ የረዥም ዘመን ታሪክ አለ፡፡ ወደኋላ እናነሳዋለን፡፡ አሁን ግን በቃሉ መነሻነት ስለ ጸሎት ጥቂት አንበል፡፡
ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነው፡፡ ስለ አምላክነቱ እና ቸርነቱ የሚቀርብ ምስጋና፤ እንዲህ አድርግልኝ ብሎ ልጅነትን አምኖ አባትነቱን ተቀብሎ የሚቀርብ ልመና ነው ጸሎት፡፡ ጸሎት ከእግዝአብሄር ጋር መነጋገር ነው ሲባል መምህራን የእመቤታችንን ነግር በአንክሮ ያነሳሉ፡፡ ከልጇ ጋር በምድር ላይ የኖረችው ሰላሳ ሦስት ዓመት ለካ ጸሎት ነበር፡፡ ምንም ልጄ ብላ ብታወራው ልጇ እግዚአብሔር ነውና ነገርየው ጸሎት ነበር፡፡ ጸሎት ብሂል ተናግሮተ ምስለ እግዚአብሔር እንዲሉ አበው፡፡
ይሄ ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገው ንግግር ማለትም ጸሎት ጥንቃቄ የሚፈልጉ ጉዳዮች የማያጡት ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ እንዴት መጸለይ እንደሚገባው አያውቅም ነበርና ብዙ ጊዜ ጸሎት ሲያበላሽ ታይቷል፡፡ ‹‹በነገስክ ጊዜ ልጆቼን በግራና ቀኝ አድርግልኝ ››ያለችውን እናት ምክንያት አድርጎ ክርስቶስ ሲገስጸን ‹‹የምትለምኑትን አታውቁም›› ብሎናል፡፡ ያቺ ምስኪን እናት የክርስቶስ መንግስት ምድራዊ መስሏት ለልጆቿ የለመነችው በግራና ቀኝ መሰቀልን ነበር፡፡ ታድያ ሐዋርያት እንዲህ አይነቱን ስህተት ላለመስራት ክርስቶስን ‹‹እንዴት ብለን እንጸል?›› ሲሉ ጠይቀውት ነበር፡፡
ክርስስቶስ ለዚህ ጥያቄ ከሰጠው መልስ በኋላ ግን እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አውቀናል፡፡
‹‹እናንተስ ስትጸልዩ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ›› ብሎ ክርስቶስ አባትችን ሆይ የሚለውን ጸሎት ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯቸዋል፡፡ ይሄ ጸሎት ቃል በቃል እንዲህ እያላችሁ ጸልዩ ከማለት ያለፈ አንድምታ እንዳለው አባቶች ያስተምሩናል፡፡ ጸሎቱን አስተውለን ካየነው ከጥያቄ ይልቅ ምስጋና ይበዛዋል፡፡ ክርስቶስ በዚህ ጸሎት ውስጥ ያስተማረን የጸሎት ቀመርን ጭምር ነው፡፡ የጸሎታችን መነሻና መድረሻ ምስጋና እንዲሆን ተናግሮናል፡፡ ይሄን ቀመር ይዘን ለጸሎት በምንቆምባቸው ሰዓታት ሁሉ እሱን በማመስገን እንጀምራለን፤ እሱን በማመስገንም እንጨርሳለን፡፡ ስለዚህ እንዴት መጸለይ እንዳለብን እናውቃለን፡፡
እንደ መጽሐፍ ልማድ የአንዱን ጸሎት ሌላው ሲጸልየው ማየት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ›› ብሎ የጸለየውን ጸሎት ከዕልፍ ዘመነት በፊት በአምላኩ እንደ ልቤ የተባለው ንጉስ ዳዊት ጸልዮት ነበር፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ በመከራው ሰዓት ዳዊት ይደግም ነበር ማለት ነው፡፡ እመቤታችንም ሃና እመ ሳሙኤል ጸልያ የነበረወን ጸሎት ተውሳ ‹‹ነብሴ እግዚአብሔርን ታላቅ ታደርገዋለች›› የሚል ቅኔን ተቀኝታ ነበር፡፡ አሁንም እኛ ልክ እንደ ክርስቶስ ዳዊት እንደግማለን፤ እንደ እመቤታችንም በየዘወትር ጸሎቱ ነብሴ እግዚአብሔርን ታላቅ ታደርገዋለች እንላለን፡፡ መጽሐፉና ፍሬአቸውን እየተመለከትን በእምነት የምንመስላቸው ዋኖች ስላሉን ጸሎታቸውን እንጸልያለን፡፡ ስለዚህ ጸሎት እናውቃለን፡፡
ዋናው ነገር ጸሎቱን ለምደነው መንፈሳዊነት የተለየው ማነብነብ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር መትጋቱ ላይ ነው፡፡ ይልቅስ በተሰላቸ መንፈስ ከሚጸለይ ጸሎት በላይ በተሰበረ ልብ የሚቀርብ ጎልዳፋ አንደበት ውጤት አለው፡፡
እዚህ ጋር አንድ ምሳሌ እናንሳማ፡፡
የአባቶቻችን የገዳም ታሪክ ነው፡፡ አንድ በገዳም ያለ ወጣኒ ጸሎት ሚያስተምረው ሰው አላገኘም ነበርና እንዲሁ የመሰለውን ሲጸልይ ይኖር ነበር፡፡ ጸሎቱም "ጌታ ሆይ አትማረኝ ጌታ ሆይ አትማረኝ" የሚል ነበር፡፡ ኋላ አንድ መንገደኛ አባት ገዳሙን ሲሳለሙ የዚህን ሰው ጸሎት ይሰሙና "የለም እንዲህ ብለህ ጸልይ" ብለው አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት አስተምረውት ጉዟቸውን በታንኳ ተሳፍረው ይቀጥላሉ፡፡
ይህ ምስኪን ሰው ግን ጸሎቱን በሚገባ አልያዘውም ነበርና በመሃል ሲጠፋበት ሮጦ ሄዶ ‹‹አባቴ ያስተማሩኝ ጸሎት ጠፋብኝ›› አላቸው፡፡ ይሄን ጊዜ ባህሩ ላይ እየሮጠ እንደመጣ ያስተዋሉት አባት ‹‹የለም ልጄ አንተ የቀድሞው ጸሎትህ አብቅቶሃል፡፡ እንደቀድሞው ጸልይ›› ብለው አሰናብተውታል፡፡ እንግዲህ የተሰበረ ልብ ካለህ፤ አምላክህንም በብርቱ መሻት ከፈለግህ ጎልዳፋ አንደበትህን ሳይንቅ ይቀበልሃል፡፡ ነገር ግን ስሌት ሰርተህ፤ መቼም እሱ መሃሪ ነው በሚል ለስንፍናህ በሚስማማ ቃል ተማምነህ ችላ ብትል ግን እንዴት መጸለይ እንደሚገባህ አስተምሮሃልና የመምህርነቱን ፍሬ ይጠብቅብሃል፡፡ ስለዚህ ለጸሎት ተነስ፡፡
የአገርህ ሰላም ማጣት ያስጨንቅሃል? የቤተሰብ ውሎ መግባት አሳስቦሃል? ሥራ ማጣት፣ የትዳር አለመስመር እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎችህ ናቸው? እንግዲያውስ አመስግነው ቀጥሎም ጽድቁን ብቻ ፈልግ ሌላው ሁሉ ይጨመርልኃል፡፡
ቀደም ሲል ያነሳነው ተንሥኡ ለጸሎት የሚለው አዋጅም ለዚህ ትጋት ነው የሚቀሰቅሰን፡፡ ያኔ አዳም እጸ በለስን በልቶ ባደረገው አመጽ በድቀት ይኖር ዘንድ ሲፈረድበት ጊዜ የአምላኩን ማዳን በተስፋ ይጠብቅ ነበርና ነብሳቱን ሁሉ ሰብስቦ ‹‹ለጸሎት ተነሱ›› እያለ ያበረታ ነበር፡፡ ዲያቆኑ አዳምን ነው የሚወክለው፡፡ ህዝቡም ‹‹እግዚኦ ተስአለነ››ይላል፡፡ አቤቱ ይቅር በለን፡፡ በዚህ መሃል ካህኑ በዚያ ልብን በሚማርከው ግሩም ዜማ ‹‹ሰላም ልኩልክሙ›› ይላሉ፡፡ ክርስቶስ ወደ ከርሰ መቃብር ወርዶ ነብሳትን ነጻ ያወጣበትን ጊዜ እያስታወሱ ነው ካህኑ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን የሚሉት፡፡ ህዝቡም በአንደም ድምጽ ‹‹ምስለ መንፈስከ›› ይላል ከመንፈስህ ጋራ፡፡ ዲያቆኑ በቅዳሴው ሰዓት እንዲህ ያለውን የመዳን ታሪክ እያስታወሰ ነው እንግዲህ ተንሥኡ ለጸሎት የሚለው፡፡
ታድያ አሁን የምንተኛበት ጊዜ ነው? በጭራሽ ሌላው ቢቀር የአገራችንን ጥፋት እንዳናይ የአቤሜሌክን እንቅልፍ ስጠን ለማለትም ቢሆን በርትተን ለጸሎት እንነሣ፡፡
ወዳጄ ሆይ! ኃጢአተኛ ከኾንህ በደልህን ትናዘዝ ዘንድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ና፤ ጻድቅም ከኾንህ ከጽድቅ (ጎዳና) እንዳትወድቅ ወደ ቤተ ክርስቲያን ና፤ ቤተ ክርስቲያን የኃጥኡም የጻድቁም ወደብ ናትና፡፡
ኃጢአተኛ ነህን? ተስፋ አትቁረጥ፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተህም ንስሐ ግባ፡፡ ኃጢአት ሠርተሃልን? እንግዲያውስ እግዚአብሔርን “በድያለሁ” በለው፡፡
እስኪ ንገረኝ! “በድያለሁ” ብለህ ለመናዘዝ ምን ውጣ ውረድ፣ ምን ዓይነት የሕይወት መርሕ፣ ምንስ መከራ አለው? “በድያለሁ” ብሎ አንዲት ቃል ለመናገር ክብደቱ ምኑ ላይ ነው? ምናልባት (ኃጢአት ሠርተህ ሳለ) በደለኛ አይደለሁም የምትል ከኾነ ዲያብሎስም አንተን አይወቅስህም፡፡ (በድያለሁ ብለህ ንስሐ የምትገባ ከኾነ ግን) ይህን (ዲያብሎስ ሊወቅስህ እንደሚችል) አስቀድመህ አስብ፡፡ …
ስለዚህ ክብርህን እንዳይወስድብህ ለምን አትከለክለውም? ለቅጽበት ያህልስ እንኳን የማይተኛ ከሳሽ እንዳለህ ዐውቀህ ለምን በደልህን ተናዝዘሃት አታስወግዳትም?
ኃጢአት ሠርተሃልን? እንግዲያውስ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተህ እግዚአብሔርን “በድያለሁ” ብለህ ንገረው፡፡ እኔ ከዚህ ውጪ ከአንተ የምፈልገው ሌላ ምንም ነገር የለኝም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስም፡- “ንግር አንተ ኃጣውኢከ ቅድመ ከመ ትጽደቅ - ትከብር ዘንድ አንተ አስቀድመህ ኃጢአትህን ተናገር” ይላል (ኢሳ.43፡26)፡፡ ስለዚህ ኃጢአትህን ታስወግዳት ዘንድ ተናዘዛት፡፡
ይህን ለማድረግ ውጣ ውረድ የለውም፤ ዙሪያ ጥምጥም የቃላት ድርደራም አያሻህም፤ ገንዘብ መክፈል አያስፈልግህም፤ ወይም እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ነገሮች አያስፈልጉህም፡፡ አንዲት ቃል ተናገር፤ በደልህን በአንቃዕድዎ አስባት፤ “በድያለሁ” ብለህም ተናዘዛት፡፡
(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)
ወርቅን የሚያነጥር ሰው አንዲትን የወርቅ ቅንጣት ወደ እሳት ውስጥ ጨምሮ እጅግ ንጹህ እስክትኾን ድረስ ይጠብቃታል፡፡ እግዚአብሔርም ልክ እንደዚሁ ሰዎች እስኪነጹ፣ እስኪለወጡና ባገኛቸው ነገር ጥቅም እስኪያገኙ ድረስ ፈተና ውስጥ እንዲቆዩ ይፈቅዳል፡፡ ይህ ደግሞ ከጥቅምም እጅግ ከፍ ያለ ጥቅም ነው፡፡
ስለዚህ ፈተና ሲገጥመን ውስጣችን ሊረበሽ ወይም ተስፋ ሊቈርጥ አይገባውም፡፡ ያ ወርቅን የሚያነጥር ሰው በእሳት ውስጥ የጨመራትን የወርቅ ቅንጣት እዚያ ውስጥ ምን ያኽል ጊዜ መቆየት እንዳለባት ያውቃል፤ መቼ ከእሳቱ ሊያወጣት እንደሚገባውም ያውቃል፡፡ እንዲሁ እስከ መጨረሻው በእሳቱ ውስጥ ተጥላ እንድትቀርና በዚያ እንድትቃጠል አይፈቅድም፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ይህን ከወርቅ አንጣሪው በላይ ያውቃል፡፡ መቼ ከርኵሰታችን እንደምንነጻ ያውቃል፡፡ በመኾኑም ራሳችንን በመጣልና ተስፋ በመቁረጥ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመርን እንዳንሔድ ሽቶ መቼ ከዚያ ፈተና እንደሚያወጣን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ድንገት ያላሰብነው ነገር ቢገጥመን በፍጹም የምናማርር፣ ወይም ተስፋ የምንቈርጥ ልንኾን አይገባንም፡፡ ከዚህ ይልቅ የእነዚህ ነገሮች ምንነትን የሚያውቅ እግዚአብሔርን መጠበቅ፣ እርሱ እስከ ፈቀደው ጊዜ ድረስም ልቡናችንን በእሳት እንዲፈተን ማድረግ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ይህ ነገር በእኛ ላይ እንዲኾን የፈቀደው ለእኛ ጥቅምና በዚያ ውስጥ ኾነን በምናሳየው ጥረት ይበልጥ ሊያከብረን ስለሚወድ ነው፡፡
ይህን በማስመልከትም ጠቢቡ ሰው እንደዚህ ሲል መክሮናል፡- “ልጄ ሆይ! ለእግዚአብሔር ትገዛ ዘንድ ብትሔድ ሰውነትህን ለመከራ አዘጋጅ፤ ልብህን አቅና፤ ኹልጊዜ ታገሥ፤ አታወላውልም፤ በመከራ ብትጨነቅም አትጠራጠር” /ሲራ.2፥1-2/፡፡ “ኹሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ስጠው፡፡” ለምን? እግዚአብሔር ከዚያ መከራ መቼ እኛን ማውጣት እንዳለበት ያውቃልና፡፡ ስለዚህ ኹሉንም ለእርሱ ልንሰጥ፣ ዘወትር እርሱን ልናመሰግን፣ ኹሉንም ነገር - ጥቅምም ይኹን ቅጣት - በአኰቴት ልንቀበል ይገባናል፤ ይህም ቢኾን ለእኛ ረብሕ የሚኾን ነውና፡፡ አንድ ሐኪም፥ ሐኪም የሚባለው ታካሚውን ገላዉን ሲያጥበውና ሲመግበው እንዲሁም ደስ ወደሚያሰኝ ስፍራ ሲወስደው ብቻ አይደለም፤ በእርሱ (በታማሚው) ሰውነት ላይ የቀዶ ጥገና ምላጭና ቢላ ሲያሳርፍም ጭምር ሐኪም ነው፡፡ አባትም አባት የሚባለው ልጁን ሲንከባከብ ብቻ አይደለም፤ የገዛ ልጁን ከቤት ሲያስወጣው፣ ሲገሥጸው፣ ሲገርፈውም ያው አባት ነው፡፡ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔር ከሐኪሞችም በላይ ሰውን ወዳጅ እንደ ኾነ በማወቅ፥ ምን ዓይነት የሕክምና ዓይነት እንደሚሰጠን በጥልቀት አንጠይቅ፤ ወይም ደግሞ ለደረሰብን መከራ እርሱን ተጠያቂ አናድርግ፡፡ ከዚህ ይልቅ እርሱ የወደደውን ነገር - ቅጣትም ይኹን ቅጣት የሌለው ነገር - ብቻ ምንም ይኹን ምን በአኰቴት ልንቀበል ይገባናል፡፡ በየትኛውም መንገድም ቢኾን የእርሱ ፈቃድ እኛ እንድንድንና ከእርሱ ጋር አንድ እንድንኾን ነውና፡፡ የትኛው መንገድ ለእኛ እንደሚጠቅምም እርሱ ያውቋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው የትኛው መንገድ ወደ እርሱ እንደሚመልሰው ያውቃል፡፡ ኹላችንም እንዴትና በምን ዓይነት መንገድ ልንድን እንደምንችል ያውቃል፡፡ በመኾኑም የሚመራን በዚህ እኛ በምንድንበት መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ወደየትኛውም መንገድ ቢወስደንም - ልክ እንደ መጻጉዑ - እርሱ እንደሚያዘ’ን ተከትለን መሔድ እንጂ ትልቁ ጉዳያችን በለስላሳና በቀላል አልያም ደግሞ በከባድና በሸካራ ጎዳና እንድንሔድ የሚያዘ’ንን ትእዛዝ መኾን የለበትም (ልንሔድበት የሚገባ’ው መንገድ እርሱ ስለሚያውቀው እንዲሁ መታዘዝ እንጂ የመንገዱን ከባድነት ወይም ቀላልነት የእኛ አጀንዳ ሊኾን አይገባውም፡፡)
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
#ወደ_ኦሎምፒያስ_የተላኩ_መልእክታት መጽሐፍ#በገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ ከተተረጎመው
አንድ ሰው መጥቶ ለአንድ ቅዱስ አባት ጥያቄ አቀረበለት "ተአምር መሥራት እፈልጋለሁ ፣ እንዴት ላድርግ?" ቅዱሱ አባት መለሰለት፦
"አንድን ሰው ወንጌል እንዲያነብ ካስተማርከው ዓይን አበራህ ማለት ነው፤ ድሆችን እንዲረዳ ካስተማርከው ሽባውን አዳንክ ማለት ነው፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔድ እንዲችል ካደረግህ አንካሳውን ፈውሰሃል፤ ሙት ማንሣት ከፈለግህ ደግሞ ንስሓ እንዲገባ አድርገው ያኔ የሞተ ሰውን አስነሥተሃል ማለት ነው።
በል ሒድና ተአምር ሥራ!"
እንኳን ለተራዳኢው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል አመታዊ በአለ ንግስ አደረሳችሁ❤
★ሰውን በማዝናናት የብቃት ማረጋገጫ ያለው ብቸኛው ቻናል ሁሌም Telegram ላይ በጥበብ ደምቀን እናሸበርቃለን
💌 Contact us, @Modenyazbot
»የተመረጡ እና ማንም ያላያቸው የአማሪኛ ቀልዶች እንዲሁም የሚያስደንቁ ስዕሎችንና ቪዲዮ ያገኛሉ።
° ° [ ሙድ እንያዝ በእኛ የአራዶች መዝናኛ ] ° °
° ° Creator @Teke_Man ° °
Last updated 1 month, 1 week ago
☕ ስለ ኢትዮጲያ ቡና የሚወጡ ወቅታዊና ትክክለኛ የክለቡ መረጃዎች አዚህ ያገኛሉ!
➪የዝዉዉር ዜና
☞የአሰልጣኞች አስተያየት
➪ጎሎች እና ቪዲዮዎች
☞የተጨዋቾች የህይወት ታሪክ
➪ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት ከየስታድየሙ !
➡መወያያ ግሩፓችን @Ethiopia_coffee_Sc
📩ሀሳብ ወይም አስተያየት ካሎት
በዚህ 👉 @EthiopianCoffeeScBot ✍
BOT ማድረስ ይችላሉ!
Last updated 3 months, 3 weeks ago
እንኳን ወደ # ሉሲ የቴሌግራም ቻናል በደህና መጡ
#የሉሲ /LUCY DINKINESH E/ቤተሰብ ሰለሆኑ ደስብሎናል።
መረጃ መስጠት የምትፈልጉ በዚ አድርሱን 👉 @CACA77
#ፋኖነት የአሸናፊነት መገለጫ አርማችን ነው!
ነፃነታችንን 💪በፈርጣማው ጡንቻችን ይረጋገጣል
👉 ፋኖነት /አማራነት /ኢትዬጵያዊነት አርበኝነት የማንነት አርማች ነው
🙏🙏🙏
Last updated 6 days, 14 hours ago