Infinite Entertainment, Zero Cost: Get Your Free Books, Music, and Videos Today!

ዮሐንስ ጌታቸው

Description
ርቱዕ ሐልዮ
ጥያቄና አስተያየት ካልዎት ይስጡ!
@tmhrte_tsdk_bot
Advertising
We recommend to visit

ከቅዳሜ በስተቀር በየዕለቱ፣ ከሰኞ እስከ ዓርብ ረፋድ ከ3:30 እስከ 5:00፣ እሁድ ከጠዋቱ 2:00 እስከ 4:00 በብስራት ኤፍ ኤም 101.1

Last updated 2 Wochen, 2 Tage her

የስራ ማስታወቂያ ከጋዜጣ ፣ ከቲቪና ራዲዮ ፣ ከማስታወቂያ ቦርድ ፣ ከድህረ-ገፅና ከማህበራዊ ሚዲያና ከመሳሰሉት ቦታዎች በአንድ ቦታ ተሰብስበው ያግኙ::

#Group t.me//Ethio_Jobs2000




#የመዝናኛ ቻናል https://t.me/+UPjrnHF6QzI0ZmQ0

https://t.me/+h0l2XzeI8RQyODlk

For promotion 📩 @Share_Home

Last updated 1 Tag, 13 Stunden her

Certified Professional Life Coaches
የቻናላችንን አነቃቂ ቪዲዮ መመልከት ለምትፈልጉ
https://www.youtube.com/@inspireethiopiamedia 👈 ይሄንን ሊንክ ይጫኑ

Last updated 4 Monate, 2 Wochen her

1 month ago

+++++++#በበጎነት_መጽናት#+++++++++

ማር ወግሪስ እንዲህ ይላል፦ "ዳግመኛም ስማኝ ልንገርህ! ለዘለዓለም ላንተ ይብስብሃልና ባደርክበት ኹሉ ቃልህን አትለውጥ። በሰዎች መካከል ጥልን አትዝራ፤ አነዋወርህ ኹሉ በሰላም ይኹን፤ ወደ ልቡናህም ቍጣን አታስገባ፤ ወንድምህ የበደለህን ከቶ አታስብ። የቍጡ ሰው ድካሙ ኹሉ በዐይን ጥቅሻ በከንፈር ንክሻ ፈጥኖ ያልፋልና። ቂምን በልቡናው የሚያኖር ሰው የሰይጣን ደቀ መዝሙሩ ነው፤ የዘለዓለም ሕይወትንም አያያትም። ማንንም ማንን አትማ፤ ከማንም ጋር አትከራከር፤ የባልጀራህን ንብረት አትመኝ የሌላውንም አትቀማ።

ሐሜተኛ ሰው የእግዚአብሔር ጠላቱ ነው። በጠላትህ ውድቀትና ሞት ደስ አይበልህ፤ ባዘኑት ላይ አትሣለቅ፤ ለዕውሩ መሰናክል አታኑርበት። ስትጸልይ ለመቀመጥ አትቸኩል፤ ለጸሎት ጽሙድ ኾነህ በቆምክበት ቦታ ኹሉ አትነቃነቅ፤ በመካነ ጸሎትህ ላይ አዘውትረህ ቆመህ ተገኝ። ለለመነህ ኹሉ ስጥ፤ ከሌለህ ደግሞ እግዚአብሔር ይስጥህ ካለው ያድርስህ ብለህ በለዘበ ቃል ተናገር። የምትሠራውን ሥራ ኹሉ ፊት አይተህ አድልተህ አትሥራ። የደረሰብህን ኹሉ እግዚአብሔርን አመስግነህ ተቀበል። ይህንን ያደረግህ እንደ ኾነ በእግዚአብሔር ትእዛዛትና ሕግጋት አንተ በእውነት ፍጹም ነህ። እኔስ በእውነት የእግዚአብሔርን ጥበብ አደንቃለሁ።" እንዲል። (ገብረ ኪዳን ግርማ (አባ፣ የአራቱ ጉባኤያት የምስክር መምህር)፣ መጽሐፈ ወግሪስ፣ 2013 ዓ.ም፣ ገጽ 51)።

የሕይወት መርሐችን ከላይ በተገለጸው መሠረት ቢኾን በበጎ መጽናት እንችላለን። ክፉ ነገር በሕሊናች ውስጥ በመጣ ጊዜ ወዲያው አስወግደን ብናስወጣው እና ሕሊናችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ኹል ጊዜ ብናስቀምጥ፥ በዚያም ቃል ብንመሰጥበት ሕይወታችን የተስተካከለ ይኾናል። ድንገት ስሜታዊ ኾነን ወደ ክፉ ልንሳብ ስንል ራሳችንን የምንቆጣጠርበት የእግዚአብሔር ቃል ውስጣችን ሊኖር ይገባል። በእርግጥም የሕይወት መርሐችንን በቃለ እግዚአብሔር እያደረግን ስንሄድ ስሜታችን በራሱ በቃለ እግዚአብሔር እየተገራ ይሄዳል። ውስጣችንም በቃለ እግዚአብሔር መመራትን እንደ ግዴታ መቀበል ይጀምራል። እንዲህ ሲኾን ብንጣላ ወዲያው ይቅር እንባባላለን፥ ቢበድሉን እንታገሳለን፥ ቢሰድቡን ስድብ የሚገባን ኃጥእ እንደ ኾን አድርገን እንቀበላለን፣ ቢንቁንም የክፉ ሥራችን ውጤት መኾኑን አምነን ያለተቃውሞ እንቀበላለን። እንዲህ በበጎ እየጸናን ስንሄድ የሚረብሸን ነገር በእኛ ላይ ኃይሉን እያጣ ይሄዳል፤ ሕይወታችንም በፍጹም ሰላምና ዕረፍት ይመላል።

እንግዲህ ምክንያታዊ ነኝ ብለን ከምናስበው አጸፋዊ መልስ ኹሉ እየራቅን እንሄዳለን። እንዲህ ያደረግኹት እንዲህ ስላደረገችኝ/ገኝ ነው እያሉ ከመናገር ኹሉ ነጻ እንወጣለን። በሕይወታችን የሚገጥሙንን ችግር የምንላቸውን ነገሮች ኹሉ የመጋፈጥና የማሸነፍ ብርታታችን ታላቅ ይኾናል። የብዙ ዓመታት ሕማም ቢኾን፣ ወይም የገንዘብ እጦት ችግር ቢኾን፣ ወይም ከሰዎች ዘንድ ፍቅር አጣኹኝ ብሎ የማሰብ ፈተናም ቢኾን እንሻገረዋለን። መጀመሪያ መስተካከል ያለበት አስተሳሰብ እና ነገሮችን የምንረዳበት መንገድ ነው። ሲቀጥልም የመኖር ትርጒሙና ዓላማው ግልጽ ኾኖ ሊገባን ያስፈልጋል። ይህ በትክክል ሲገባን ያን መፈጸም ዋና ዓላማችን እየኾነ ይመጣል። ስለዚህ ሰይጣን ሊጥለንና ጥቅም አልባ ሊያደርገን የሚፈጽምብን ጥቃት ኹሉ ይከሽፋል። በበጎነት ጽናታችንም ድል ይነሣል። ስለዚህ ስንኖር ለምንድን ነው የምኖረው? እንዴትስ እንድኖር ነው ፈጣሪ የሚፈልገው? ፈጣሪስ እንደሚፈልገው መኖር ያልቻልኩት ለምንድን ነው? ለመኾኑ በበጎነት ጸንቼ እንዳልኖር የሚከለክለኝ ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ለራሴ እየጠየኩ ሕይወቴን እያስተካከልኹኝ ልኖር ይገባኛል። በምን መመሪያ እንዳንል ከላይ ማር ወግሪስ ያስቀመጠልን ድንቅ የሕይወት መመሪያ አለልን።

https://t.me/phronema

Telegram

ዮሐንስ ጌታቸው

ርቱዕ ሐልዮ ጥያቄና አስተያየት ካልዎት ይስጡ! @tmhrte\_tsdk\_bot

+++++++#በበጎነት\_መጽናት#+++++++++
1 month ago

++++++#የምትወድቁ_አትደነቁ#+++++++

ዮሐንስ ዘሰዋስው "አንተ በየዕለቱ የምትወድቅ አትደነቅ፤ በቦታህ ላይ በርትተህ ቁም እንጂ አታቋርጥ። በርግጥም የሚጠብቅህ መልአክ ትዕግሥትህን (ጽናትህን) ያከብረዋል። ቍስል ገና ትኩስና አዲስ ኾኖ ሳለ ለማዳን ቀላል ነው፤ የቆየ፣ የተተወ፣ የሚመግልም እንደ ኾነ ግን ለማዳን የሚያስቸግር፣ ብዙ ክብካቤ፣ መቍረጥ፣ ማሸግ፣ መብጣትም የሚፈልግ ነው። ብዙዎች ከረዥም ቸልታ የተነሣ መዳን የማይችሉ ወደ መኾን መጥተዋል። ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ኹሉ ይቻላል። ማቴ 19፡26፤ ከመውደቃችን በፊት አጋንንት እግዚአብሔር ሰውን ወዳጅ ነው ይሉናል፣ ከወደቅን በኋላ ግን ጨካኝ ነው ይሉናል። ...

ሕሊናችን ከንጽሕና በመነጨ ሳይኾን በክፉ ከመስጠሙ (ከመዘፈቁ) የተነሣ እኛን መውቀስ አቍሞ እንደ ኾነ በጥንቃቄ ማጤን ይገባናል። ከውድቀት የመዳናችን ምልክቱ ያለማቋረጥ ራሳችንን እንደ ባለ ዕዳ አድርገን ማሰባችን ነው። የእግዚአብሔርን ምሕረቶች የሚተካከል ወይም የሚበልጥ ምንም ነገር የለም። በመኾኑም ተስፋ የሚቆርጥ ሰው ራሱን መግደል እየፈጸመ ነው።" ይላል። (ሳሙኤል ፍቃዱ (ተርጓሚ)፣ ምዕራግና ድርሳን፣ 2011 ዓ.ም፣ ገጽ146-147)።

ከመውደቅ በላይ ትልቁ ችግር ያለው ለመነሣት አለመጣር ላይ ነው። መውደቅ አዳማዊ ነው፤ ወድቆ መቅረት ግን ሰይጣናዊ ነው። ወንድሜ ሆይ አንድ ቀን ብቻ አይደለም! ብዙ ዕለታትን በተደጋጋሚ ልትወድቅ ትችላለህ ወይም አኹንም በተደጋጋሚ እየወደቅህ ይኾናል። ነገር ግን መነሣት እንዳለብህ እወቅ! ለመነሣት ከልብ በመነጨ ፍላጎት ስትፍጨረጨር እግዚአብሔር ኃይል ይኾንሃል ትነሣማለህ። ክርስትና የመነሣት ሕይወት መኾኑን ኹል ጊዜ በሕሊናህ ውስጥ አስቀምጠህ ያለ መሰልቸት ትጋ። የሰይጣን ትልቁ ትግልና ውጊና ያለው መነሣት አትችልም የሚለውን ሐሳብ በማሳሰብ ማደካከም ላይ መኾኑን ልብ ብለህ እንደ ብልህ ወታደር በጥንቃቄ ተዋጋ። በልብህም ውስጥ ወደ ቀቢጸ ተስፋ የሚወስዱ ምክንያትችን አታስቀምጥ፤ ይልቅስ የእግዚአብሔርን ምሕረት እያሰብክ ሳታቆርጥ ተጋደል። በክፉ ሕይወት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ እየገባው እንዴት እግዚአብሔር ፊት ቆሜ ይቅር በለኝ እለዋለሁኝ አትበል። እግዚአብሔር ካንተ የሚፈልገው የእውነት መጸጸትህን እና በእርሱ ይቅር ባይነት ማመንህ ነው። ይህንም እኮ አላደረኩም፤ ሌላው ቢቀር ንስሐም እኮ አልገባኹም ለመግባትም እፈራለሁኝ እያልክ ራስህን በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ አትክተት። አእምሮ እንዳለው ሰው አስበህ ኹል ጊዜም የእግዚአብሔርን ምሕረት ፈልግ። እስካኹን የንስሐ ሕይወት ባይኖርህም ከእንግዲህ እንዲኖርህ ማድረግ የምትችል መኾንህ አውቀህ ሳትሳነፍ ወደ እግዚአብሔር ቅረብ። እግዚአብሔር የኹላችንንም ዐይነ ልቡና ያብራልን።

https://t.me/phronema

Telegram

ዮሐንስ ጌታቸው

ርቱዕ ሐልዮ ጥያቄና አስተያየት ካልዎት ይስጡ! @tmhrte\_tsdk\_bot

++++++#የምትወድቁ\_አትደነቁ#+++++++
1 month ago

++++#ታላቍ_መቃርዮስ_እንዲህ_አሉ#+++++

ጥላቻ የሚመጣው ቂምን ወይም ክፉን ከመሰወር ነው፣ ክፉን መሰወር ደግሞ ከኩራት፣ ኩራት ከግብዝነት፣ ግብዝነት ከእምነት ጉድለት፣ የእምነት ጉድለት ከልብ ድንዛዜ፣ የልብ ድንዛዜ ከቸልተኝነት፣ ቸልተኝኀት ከስንፍና፣ ስንፍና ከተስፋ መቁረጥ፣ ተስፋ መቁረጥ ከትዕግሥት ማጣት፣ ትዕግሥት ማጣት ከትዕቢት ይመጣል። ጸሎት በፍቅር ላይ ይመሠረታል፣ ፍቅር ደግሞ በደስታ፣ ደስታ ደግሞ በቅንነት፣ ቅንነት በትሕትና፣ ትሕትና በአገልግሎት፣ አገልግሎት በተስፋ፣ ተስፋ በእምነት፣ እምነት በመታዘዝ፣ መታዘዝ በግልጸኝነት ወይም ራስን ቀለል በማድረግ ላይ ይመሠረታል። Ven. Macarius the Great

https://t.me/phronema

Telegram

ዮሐንስ ጌታቸው

ርቱዕ ሐልዮ ጥያቄና አስተያየት ካልዎት ይስጡ! @tmhrte\_tsdk\_bot

++++#ታላቍ\_መቃርዮስ\_እንዲህ\_አሉ#+++++
1 month, 1 week ago

ምስጢረ ትንሳኤ ሙታን I በመምህር ዲ/ን ዮሐንስ ጌታቸው I 2ተኛ ዙር የተልዕኮ ትምህርትI #አዲስ_ስብከት
https://youtube.com/watch?v=WgHQvYNIMLY&si=jkfHnO7OABq6VasH

YouTube

ምስጢረ ትንሳኤ ሙታን I በመምህር ዲ/ን ዮሐንስ ጌታቸው I 2ተኛ ዙር የተልዕኮ ትምህርትI #አዲስ_ስብከት

የሰንበት ት/ቤታችንን አገልግሎት ለመደገፍ እባክዎን #ሰብስክራይብ\_ያድርጉ ያድርጉ ቪድዮውን #ላይክ በማድረግ ይጀምሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትና ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት Facebook page:- / fbirhan Telegram Channel:-https://t.me/finotebirhan12 Website:-https://w…

1 month, 1 week ago

+++#መዳን_የምንችለው_እንዴት_ነው_?#+++

"በኦርቶዶክሳዊነት መጽናት፣ እርስ በእርሳችን የአረዳድ አንድነታችንን ስንጠብቅ፣ ግብዘነት የሌለው ፍቅር ሲኖረን፣ የነፍስንና የሥጋን ንጽሕና ስንጠብቅ፣ ክፉና ንጹሕ ያልኾኑ ሐሳቦችን ስናስወግድ፣ በትንሹ ስንበላና ስንጠጣ፣ ከኹሉ በላይ ራሳችንን በትሕትና ስናስጌጥ፣ እንግዳ መቀበልን ቸል ካላልን፣ ከግጭት ስንርቅ፣ በምድራዊ ሕይወት ለማንኛውም ነገር ክብርንና ከፍታን ካልሰጠን ነገር ግን በምትኩ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሽልማትንና የሰማያዊ መልካም ነገሮች ደስታን እናገኛለን።" እንዲል። (St. Sergius of Radonezh, Life, 32)

ቴኦፋን "ድኅነትን ማግኘት ከፈለክ፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውን በሙሉ ተማር፣ በልቡናህም ጠብቀው፤ ከቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትም ሰማያዊውን ኃይል ተቀበል፤ ክርስቶስ ባዘዘው የትእዛዝ መንገድ ሂድ፣ ይህን ካደረግህ ያለ ጥርጥር ሰማያዊቷን መግሥትም ታገኛለህ ትድንማለህ። ... ማንም ሰው ከዚህ መንገድ ያጎደለ ቢኖር አይድንም።" ይላል።  
(St. Theophan the Recluse, Five Teachings on the Path to Salvation, 3)

አባ እንጦንስ አንድ መነኩሴ ለመዳን ግድ ምን ላድርግ? አላቸው። አባ እንጦንስም፦ በራስህ ጽድቅ አትመካ፣ ስላለፈውም አትጨነቅ፣ ምላስህንና ሆድህን ግታ" አለው። (Ancient Patericon, 1.2)።

አንድ ወንድም አባ መቃርዮስን 'እንዴት ነው መዳን የምችለው? አላቸው። አባ መቃርስም "እንደ ሞተ ሰው ኹን፤ ከሰዎች የሚመጣብህን ስድብም ኾነ ክብርን አታስብ፣ እንዲህ ካደረግህ ትድናለህ" አሉት። (Ancient Patericon, 10.45)።

https://t.me/phronema

Telegram

ዮሐንስ ጌታቸው

ርቱዕ ሐልዮ ጥያቄና አስተያየት ካልዎት ይስጡ! @tmhrte\_tsdk\_bot

+++[#መዳን\_የምንችለው\_እንዴት\_ነው\_](?q=%23%E1%88%98%E1%8B%B3%E1%8A%95_%E1%8B%A8%E1%88%9D%E1%8A%95%E1%89%BD%E1%88%88%E1%8B%8D_%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8B%B4%E1%89%B5_%E1%8A%90%E1%8B%8D_)?#+++
1 month, 1 week ago

ዲያቆን ዮሐንስ ጌታቸው የሾላ ዛፍ ሉቃ 19፥ 1
https://youtube.com/watch?v=TNcbqNzihpI&si=KI7YaaCbXyv4waoo

YouTube

ዲያቆን ዮሐንስ ጌታቸው የሾላ ዛፍ ሉቃ 19፥ 1

***✝️******✝️******✝️***የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ በጸሎት ያግዙን***✝️******✝️******✝️***አዲሱን የማኅበራችንን የዩቱዩብ ቻናል +++SUBSCRIBE +++ እያደረጋችሁ ትምህርቶችን እና መዝሙሮችን እንዲደርሶት እና ለሌሎች እንዲደርሳቸው ሼር በማድረግም ይተባበሩን:: ከዚህ በፊት የተለቀቁ ትምህርቶችንና ዝማሬዎችን ለማግኘት ከስር የሚገኘውን ሊንክ ይጠቀሙ https://www.youtube.com/channel/UCol\_BHX6I…

3 months, 1 week ago

ድንቅ ስብከት| የዚህ ዓለም ጥበብ | በመ/ር ዲ/ን ዮሐንስ ጌታቸው
https://youtube.com/watch?v=1P0-JiBGU_k&si=CX0EweG8pV4-1Y4O

YouTube

ድንቅ ስብከት| የዚህ ዓለም ጥበብ | በመ/ር ዲ/ን ዮሐንስ ጌታቸው

ይህ የዩትዩብ ገጽ የመንበረ መንግሥት (ግቢ) ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ሲሆን የተለያዩ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው ቪዲዮዎችን ለምእመናን የምናደርስበት ነው፡፡ ቻናላችንን ሰብስክራይብ (Subscribe) በማድረግ እና የደውል ምልክቱን በመመንካት የምንለቃቸውን መልእክቶች እንዲደርሳችሁ እንጠይቃለን፡፡ አስተያየት ካላችሁ በኢሜይል አድራሻቸን amdehaymanot19@gmail.com…

3 months, 2 weeks ago

++++++ወይን እኮ የላቸውም++++++

የቃና ዘገሊላ ታሪክ ውስጥ አስደናቂ ከኾኑ ክስተቶች ውስጥ አንዱ የወይን ማለቅ ጉዳይ ነው። በእርግጥ ቃና ዘገሊላ ውስጥ የተፈጸመው የሰርግ ጉዳይ ጥልቅ መልእክቶችን የተሸከመ መኾኑ በብዙ የሚብራራ ነው። ታሪኩን በጥልቀት ለመረዳት ግን ወደ ታሪኩ ጥልቀት ውስጥ የምንገባበትን በር ማግኘት አለብን። የዮሐንስን ወንጌል ምሥጢራዊነት ወደ መረዳት ከፍታ እስካልወጣን ድረስ በወንጌሉ ውስጥ የተፈጸሙትን አስደናቂ ክስተቶች በአግባቡ መረዳት አንችልም። ማክሲመስ ተናዛዚው መጽሐፍ ቅዱስን በጥቅሉ በቤተ ክርስቲያን ይመስልና የዮሐንስን ወንጌል ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለችውን ቅድስተ ቅዱሳን ትመስላለች ይላል። ይህ የሚያመለክተው ወንጌሉ የተሸከመውን ጥልቅ ምሥጢር ነው። እንዲያውም ቀለሜንጦስ ዘእስክንድርያ ሦስቱን ወንጌላት በሥጋ የዮሐንስን ወንጌል ደግሞ በመንፈስ ይመስላል። የሌሎቹ ወንጌላት እስትንፋሳቸው የዮሐንስ ወንጌል ነውና!!

@@ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የዮሐንስን ወንጌል ለመረዳት ሊቁ ኦሪገን እንዳለው ወደ ጌታ ደረት ጋር ጠጋ ብሎ እንደ ዮሐንስ ከጌታ እመቤታችንን መቀበልን ይጠይቃል። ይህ ኹሉ የሚያመለክተው በወንጌሉ ላይ የተጻፉ ክስተቶችን በችኩልነትና በለብ ለብ ስሜት አልፈን እንዳንሄድና በጥልቀት እንድንመረምር ነው። ሰርግ የተፈጸመባት የገሊላዋ ቃና ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያምን በመያዟ ከሚመጣባት ጉድለት ስትድን እንመለከታለን። ከክርስቶስ ጋር ለምናደርገው ግንኙነት የእመቤታችን ልመና እጅግ አስፈላጊ ነው። እርሷ ቀድማን ጉድለታችንን ባታሰማልን ኖሮ መሽራው ክርስቶስ እንዴት ይቀበለን ነበር!!

@@እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከቤተ አይሁድ ወገን ስለ ኾነች የአይሁድን ጉድለት በእጅጉ ታውቀዋለች፤ ስለዚህ የሚጠቅማቸውን ወይን ይሰጣቸው ዘንድ ትለምናለች። በመጽሐፍ እንዲህ ተብሏል “እናንተ ሰካራሞች ንቁ ለመስከርም ወይን የምትጠጡ እናንተ ሁላችሁ! ተድላና ደስታ ከአፋችሁ ጠፍተዋልና አልቅሱ፤ እዘኑም።" ኢዩ 1፥5። በመኾኑም አይሁድ የድኅነትን ደስታ በማጣት በኀዘን ውስጥ ናቸው፤ ይህ ነውና የወይን ማጣት!! ወይን እኮ የላቸውም የድኅነት ደስታ ከደጃቸው ጠፍታለችና ስጣቸው ማለቷ ነበር። በተራው ምድራዊ ወይን ሰክረው የድኅነትን ወይን በማጣት ጨለማ ውስጥ ገብተው ነበርና ጉድለታቸውን የምታውቅ ፈጣኗ እናት ለመነችላቸው።

@@ወይን እኮ የላቸውም ርቱዕ እምነት የላቸውም። አኹንም በኦሪታቸው ውስጥ የምትታየውን አንተን ወደ ማወቅ አልመጡምና አይኖቻቸውን ከፍተህ ብርሃነ ወንጌልህን ግለጥላቸው። በጨለማ ውስጥ ያለን ነገር ለማየት የግድ ብርሃን እንዲያስፈልግ በእምነት ጨለማ ውስጥ ያሉትን ወይን ርቱዕ እምነትን ሰጥተህ አድናቸው ማለቷ ነው። ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው በሐዲስ ኪዳኗ ትክክለኛዋ እምነት በኩል ከእግዚአብሔር ጋር እስካልተገናኘን ድረስ በእርግጥም ወይን እኮ የለንም!!

##እመቤታችን ወይን እኮ የላቸውም ማለቷ ሰዎች ከፈሪሓ እግዚአብሔር በመራቃቸው ምክንያት የደረሱበትን መልከ ጥፉነት ለማመልከትና ከዚያ እንድንፈወስ ለማስደረግ ነው። መዝ 127 “ብፁዐን ኩሎሙ እለ ይፈርሕዎ ለእግዚአብሔር ወለ እለ የሐውሩ በፍናዊሁ። ፍሬ ጻማከ ተሴሰይ፣ ብፁዕ አንተ ወሠናይ ለከ፤ ብእሲትከ ከመ ወይን ሥሙር ውስተ ጽርዓ ቤትከ - እግዚአብሔርን የሚፈሩ ኹሉ የተመሰገኑ ናቸው፣ የድካምህን ዋጋ ትበላለህ፤ ምስጉን ነህ መልካምም ይኾንልሀል፤ ምስትህም በቤትህ ውስጥ እንደ ወይን የተወደደች ናት።" በማለት በብዙ አንቀጽ ጀምሮ በአንድ አንቀጽ ወደ ማውራት ይመጣል። ይህ የሚያመለክተው የክርስቶስንና የእርሱ የኾነችውን ቤተ ክርስቲያን ግንኙነት ነው። በቤትህ እንደ ወይን የተወደደች ናት በማለት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ውበት ያነሣል። ስለዚህ በፈሪሓ እግዚአብሔር ውስጥ የሚኖሩ የቤተ ክርስቲያን አካሎች የምግባር ውበታቸውን ሳያጡት እንደሚኖሩ፤ ወይን እኮ የላቸውም የተባሉት በዚህ ዓለም ፍልስፍናና ፍቅር የነጎዱትን ነው። የጠፉትን ወደ በረቱ ለመሰብሰብ የተደረገ የፍቅር ጥሪ ነው!!

##ወይን እኮ የላቸውም። ፍቅረ ቢጽ ወፍቅረ እግዚአብሔር የላቸውም። የራሳቸውን ስሜት በመውደድ የሠለጠኑ ናቸውና ወይን ፍቅር የላቸውም!! ወይን ጣዕሟ እንደሚያረካ ነፍሳቸው የምትረካባቸው ቃለ እግዚአብሔር የላቸውም!! ቃልህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው ተብሏል እነርሱ ግን ይህ በአንተ ቃል የመመራት ሐሳብ የላቸውምና በቃልህ የመመራት ኃይልን ሙላባቸው!! እንግዳ ክፉ ፈቃድ ተነሥቶባቸዋልና ይህን ድል የሚያደርጉበትን ወይን ትዕግሥትን ስጣቸው። መናፍቃን ለሚያቀርቡባቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተው ሰውነታቸውን በእውነት መሠረት ላይ ይገነቡት ዘንድ ወይን ማስተዋል የላቸውምና ማስተዋሉን አድላቸው!!

###ወይን ሕገ ወንጌል ናት። በሕገ ወንጌል ወይን ውስጥ ገብተው ይኖሩ ዘንድ ወይን የወንጌል ምሥጢራትን የሚረዱበት ሀብተ ትርጓሜ የላቸውም። በወንጌል ውስጥ የተዘገበው ሰላም ቀድሞ ባለበሳቸው ጥላቻ ምክንያት አልተገኘላቸውምና “ወይን እኮ የላቸውም" ። የሕይወት ወይን አንተን ራስህን በማጣት ሕማም ውስጥ ገብተው ቆስለዋልና አምላክነትህን ገልጠህ አሳያቸው። በሕይወት ውጣ ወረድ ውስጥ የሚገጥማቸውን መከራ በጽናት ይቀበሉ ዘንድ ወይን እኮ የላቸውም። በእርግጥ የእመቤታችን ድምጿ በልጇ ዘንድ ይሰማል። የእኛ ጉድለትም ስለ እርሷ ሲባል ይሟላል። ብቻ እናችን ቅድስት ኾይ ከመዝሙር ይልቅ ዘፈን ደስ የሚያሰኘንን እኛን ወይን እኮ የላቸውም በይልን!! ጌታ ሆይ ወይን ደምህን ጠጥተን ምሬተ ኃጢአታችንን ታስወግድ ዘንድ ስለ እናትህ ብለህ ወይንህን ስጠን!! አሜን።

https://t.me/phronema

Telegram

ዮሐንስ ጌታቸው

ርቱዕ ሐልዮ ጥያቄና አስተያየት ካልዎት ይስጡ! @tmhrte\_tsdk\_bot

++++++ወይን እኮ የላቸውም++++++
3 months, 2 weeks ago

ምኑን በኅበ ሰብእ ብሎ ራሱን የገለጠ ስሙን ያልገለጸው የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊ ጉዳዩን እንዲህ ይመልሳል፦ "የጌታችን መጠመቅ ስለ ኹለት ምክንያት ነው፤ አንዱ ምክንያት በእመቤታችን ማኅፀን የተፈጸመውን ሥራ ይገልጥ ዘንድ ነው፤ አንዱ ምክንያት ከሞቱ በኋላ የሚፈጸመውን ሥራ ለመግለጥ ነው።

በእመቤታችን ማኅፀን የተፈጸመው ሥራ ቃል ሥጋዋንና ደመ ድንግልናዋን መንሣቱ ነው፤ ደመ ድንግልናዋንም ከነሣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ማረፉ ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ባሕር ልብሱን አኑሮ ገብቶ ሦስት ጊዜ ተጠምቋልና፤ ከተጠመቀም በኋላ አካሉ በውኃ ረጥቦ ከውኃው ወጥቷል፤ ከውኃው ከወጣ በኋላም መንፈስ ቅዱስ ከሰማይ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀምጧልና። የጌታችን ወደ ውኃው መውረዱ ከሰማይ ወደ እመቤታችን ማኅፀን የመውረዱ ምሳሌ ነው፤ ከልብሱ መራቆቱም አብና መንፈስ ቅዱስ ሰው ላለመኾናቸው ምሳሌ ነው። ሦስት ጊዜ መጠመቁ ኀይለ ዘርዕን፥ ኀይለ ንባብን፣ ኀይለ እንስሳን፣ ለመንሣቱ ምሳሌ ነው፤ እነዚህም በእመቤታችን በባሕርይዋ ያሉ ሥጋ፣ ነፍስ፣ ደመ ነፍስ ናቸው። ከውኃው አካሉ ርጥብ ኾኖ መውጣቱ ደመ ድንግልናዋን ነሥቶ ለመጸነሱ ምሳሌ ነው። ከውኃው ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ መውረዱ ምእመናን ቅብዐ ትፍስሕት መንፈስ ቅዱስን ለመቀበላቸው ምሳሌ ነው፤ በዮሐንስ እጅ መጠመቁ በአብና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሰው ለመኾኑ ምሳሌ ነው። ይህ ኹሉ ምሥጢር የተደረገው በማኅፀን ነውና ስላልታየ ለሰው ለማሳየት በዮርዳኖስ ተጠመቀ።

ከሞቱ በኋላ የሚኾን ኹለተኛው ምክንያት ከልብሱ ተራቁቶ መጠመቁ በመስቀል ላይ ራቁቱን ለመሰቀሉ ምሳሌ ነው፤ ሦስት ጊዜ መጠመቁ ሦስት ቀን በመቃብር ለማደሩ ምሳሌ ነው፤ ከተጠመቀ በኋላ የመንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረድ በርሱ ሞት ልጅነትን ለማግኘታችን ምሳሌ ነው፤ በካህኑ በዮሐንስ እጅ መጠመቁ በካህናት በሐናና በቀያፋ ምክር ለመገደሉ ምሳሌ ነው፤ ከውኃው መውጣቱ ለመነሣቱ ምሳሌ ነው፤ የጎልማሳነት ዘመኑን ከፈጸመ በኋላ በሠላሳ ዓመቱ መጠመቁ የድኅነት ሥራ ከፈጸመ በኋላ ለመገደሉ ምሳሌ ነው። ጌታችን በወንጌል "የሰጠኸኝን ሥራ ጨረስኩ" ብሎ እንደተናገረው ከአዳምና ከሔዋን ዘመን ጀምሮ በእብነ ሩካቤ ተቀርጾ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጥሎ የነበረውን "አዳም የዲያብሎስ አገልጋይ ነው፤ ሔዋን የዲያብሎስ አገልጋይ ናት" የሚለውን የዕዳ ደብዳቤ አጠፋልን። ማጥፋቱም ከአዳም ከሔዋን ወገን የነበረ የሰይጣንን ባርነት ለማጥፋቱ ምሳሌ ነው። ይህን ኹሉ ምሥጢር ለማስረዳት ተጠመቀ።" በማለት በዝርዝር ያስረዳል። (ምኑን በኀበ ሰብእ፣ አምስቱ አዕማደ ምሥጢር፣ 2014 ዓ.ም፣ ገጽ 154-156)።

ሊቀ ጳጳስ አባ ገሪማ "ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ፣ በፈለገ ዮርዳኖስ ሊጠመቅ የመጣው፦ በነቢያት የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም፣ ውኃውን ለመቀደስ፣ ለጥምቀት ኃይልን ለመስጠት፣ ለእኛም አርአያና ምሳሌ ለመኾን እንጂ የንስሐ ጥምቀትን በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ የመጣ አይደለም።" ይላሉ። (አባ ገሪማ (ሊቀ ጳጳስ፣ ዶ/ር)፡ አርተር ዶር መርሻ አለኸኝ፣ ትምህርተ ሃይማኖት፣ 2006 ዓ.ም፣ ገጽ 123)። እንግዲህ በጌታችን መጠመቅ በኩል ብዙ ነገሮችን ማሰብ እንችላለን። የሥርዓት ባለቤት እርሱ ሥርዓቱን ፈጽሙ ብቻ ያለን ሳይኾን በተግባር ፈጽሞ እንድንፈጽም ነገረን እንጂ።

https://t.me/phronema

Telegram

ዮሐንስ ጌታቸው

ርቱዕ ሐልዮ ጥያቄና አስተያየት ካልዎት ይስጡ! @tmhrte\_tsdk\_bot

ምኑን በኅበ ሰብእ ብሎ ራሱን የገለጠ ስሙን ያልገለጸው የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊ ጉዳዩን እንዲህ ይመልሳል፦ "የጌታችን መጠመቅ ስለ ኹለት ምክንያት ነው፤ …
3 months, 2 weeks ago

+++#ጌታችን_ስለ_ምን_ተጠመቀ#+++

ቅዱስ ዮሐንስ አጥማቄ ሥግው ቃል፥ ያጠምቅ የነበረው ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት ነበር። ጊዜው ሲደርስ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮሐንስ ሄዶ ተጠመቀ። የቅዱስ ዮሐንስ ጥምቀት "የንስሐ ጥምቀት" ተብላ ነው የምትታወቀው። ቅዱስ አትናቴዎስ የዮሐንስ ጥምቀት ከኃጢአት ለመንጻት ብቻ የሚጠቅም መኾኑንና፥ የክርስቶስን መምጣት ለመጠባበበቅ የተሰጠ እንጂ ልጅነትን ለመስጠት ወይም የልጅነትን ጥምቀት የሚተካ የክርስቲያኖች ጥምቀት አለመኾኑን ገልጿል። (The Orthodox Study Bible, Athanasius Orthodox Academy 1993 G.C)። ይህን ያደረገው ኃጢአት ኖሮበት ከዚያ ለመንጻት ወይም ለመቀደስ አይደለም፥ እርሱ ራሱ የቅድስና ባለቤት ነውና። እንግዲያውስ ፍጹም አምላክ የኾነ እርሱ ስለ ምን ተጠመቀ የሚለውን የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ድንቅ መልሶችን አስቀምጠውልናል።

ቅዱስ ኤፍሬም፦ "... ስለዚህ ጌታ የጎደለው ስላለ አንዳች ነገር ሊሞላለት በዮሐንስ የተጠመቀ አይደለም። ነገር ግን የተዋረደውን የአዳምን ሥጋ ስለ መልበሱ ለማጠየቅ በዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ መጣ። ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀትን በማወጅ ኃጥአንን እያጠመቀ የመጣ ቢኾንም ስለ ጌታችን "እርሱ ኃጢአት አላደረገም" ተብሎ ተጽፏልና ጌታችን ንስሐ ከሚገቡት ጋር ወደ ጥምቀት መቅረቡ ኃጢአተኛ ኾኖ እንዳልኾነ በዚህ እንረዳለን። ... በተላይ በእርሱ ጥምቀት የዮሐንስ ጥምቀት ማብቃቱንና በዮሐንስ የተጠመቁ በእርሱ ድጋሚ መጠመቅ እንደሚያስፈልጋቸው ለማስረዳት ወደ ዮሐንስ መምጣት ተገባው። በእርሱ ጥምቀት የዮሐንስ ጥምቀት ሊያገለግል የሚችለው እርሱ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ብቻ እንደ ነበረ አሳወቀን። በሕጉ ምክንያት ከኾነው ርግማን ሊዋጀን አማናዊው ጥምቀት በጌታችን ተሰጠን።" ይላል። (ሽመልስ መርጊያ (መ/ር፣ ተርጓሚ)፣ ኅብረ ወንጌል፣ 2013 ዓ.ም፣ ገጽ 75)። ስለዚህ ጌታችን የተጠመቀው ፍጹም ሰው መኾኑን ለማስረዳት፣ የዮሐንስን ጥምቀት ለመፈጸም፣ አዲስ የልጅነትን ጥምቀት ለመስጠት መኾኑን ልብ ይሏል። እንግዲህ ጌታችን ሊጠመቅ ወደ ዮሐንስ መሄዱ የፍጹም ሰውነቱ ማረጋገጫ እንጂ ከቅዱስ ዮሐንስ የማነሱ ማስረጃ ሊኾን አይችልም። አምላክ ሰው የኾነው በምትሐት እንጂ በእውነት ሰውነትን ገንዘብ በማድረግ አይደለም የሚለውን ክሕደት የሚያፈርስ ተግባራዊ ከኾኑ መልሶች መካከል አንዱ ሊጠመቅ ወደ ዮሐንስ መሄዱና መጠመቁ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ የትሕትና ትምህርት ቤት ከመኾንም በላይ "ትሕትና ምንድን ናት?" ለሚለው ጥያቄ መልስ ነው። ትሕትና ማለት ክርስቶሳዊነት ነውና። ኹሉ ያለው እርሱ፡ በፈጠረው ፍጡር እጅ ሊጠመቅ ሄደ ብሎ መናገርን ማን ሊያብራራውና ሊጠነቅቀው ይችላል! ይህ ከአእምሮ የሚሻገር እጅግ በጣም አስደናቂ ነገር ነው። ትንሽዬ የዕውቀት ጨረፍታ ያለን ሲመስለን ኹሉን ነገር የምናዋርድና ራሳችንን ለምናዘማንን ሰዎች በሙሉ ሕይወት ጣዕም ያላት የምትኾነውና የኾነችው እኛ በያዝነው መንገድ አለመኾኑን "ጌታ እኮ በባሪያ እጅ ተጠመቀ" በሚለው መረዳት እንችላለን። የማያልቅ ለኹል ጊዜ የክርስትና ሕይወት ጥፍጥና የሚኾን አርአያነት ይሏል ይህ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የተከላትን ይህችን በጎ ፍኖት የሚያጣምም፥ ወይም ቸል የሚል ኹሉ የክርስቶስ ተከታይ ነኝ እንዴት ሊል ይችላል!

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፦ " ዮሐንስ ያጠምቅ የነበረው ጥምቀት "የንስሐ" ስለ ነበረ፣ ሰዎች ኹሉ ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ ይመጡ ስለ ነበረ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወደ ፈለገ ዮርዳኖስ የመጣው በዚህ አግባብ ነው ብሎ ማንም ሰው እንዳያስብ፥ መጥምቁ ዮሐንስ ይህ ኹሉ ከመኾኑ አስቀድሞ በግ እና ከኃጢአት ኹሉ የሚያድን ብሎ ጠራው። ... በተጠመቀ ጊዜም እንደዚሁ ለጥምቀተ አይሁድ ፍጻሜ ሰጠ፤ ጥምቀተ ቤተ ክርስቲያንንም መሠረተ። የብሉዩን ፋሲካ ፈጽሞ አሳልፎ የሐዲሱን ፋሲካ የጀመረው በመዓድ (በመብል በመጠጥ) እንዳደረገው ኹሉ፥ ጥምቀተ አይሁድን አሳልፎ ጥምቀተ ሐዲስን ደግሞ በውኃ አደረገው። በመዓዱም ኾነ በውኃው አስቀድሞ ምሳሌዎችን (ጥላ የነበሩትን) አመጣ፤ ቀጥሎም አማናውያኑን አጸና መሠረተ። ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የምታሰጥ ይህቺ ጥምቀተ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናትና፤ የዮሐንስም ጥምቀትም ብትኾን ይህን ጸጋ የመስጠት አቅም አልነበራትምና። ስለዚህ ዋና ምክንያትም በጥምቀተ አይሁድም ኾነ በጥምቀተ ዮሐንስ እንደዚህ ያሉ ምልክቶች ሳይታዩ፥ በእርሱ በጌታችን ልትሰጥ ባላት በጥምቀተ ቤተ ክርስቲያን ግን ታዩ።" ይላል። (ገብረ እግዚአብሔር ኪደ (መ/ር፡ ተርጓሚ)፣ የማቴዎስ ወንጌል በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 1-24፣ 2011 ዓ.ም፣ ገጽ 213-221)። ይህ የሊቁ ገለጻም ጌታችን የተጠመቀው ለእኛ የልጅነትን ጥምቀት ሊሰጠን መኾኑን የሚያመለክት ነው። የልጅነት ጥምቀታችሁ መሥራች እኔ ነኝ፥ ሲል ነው። በእርግጥ ጽድቅም እርሱ በሠራው ሕግና ሥርዓት መጓዝ ነው። ጌታችን በተግባር ፈጽሞ ካሳየን መንገድ ውጭ በመጓዝ ጽድቅን ገንዘብ ልናደርግ ፈጽሞ አንችልም። በማንኛውም የጽድቅ መሥመር እውነተኛው መሪ፥ ወይም አርአያ እርሱ ነውና። ክርስትና አምላካችን ክርስቶስ ባሳየው አኗኗር ላይ የተመሠረተ የተመስጦ ሕይወት ነው።

ቅዱስ ያሬድ ፦ "አውሥአ ኢየሱስ ለዮሐንስ ወይቤሎ አጥምቀኒ በማይ ከመ ይትቀደስ ማይ በዮርዳኖስ ቀላልይ፦ ኢየሱስ ዮሐንስን ውኃ ይቀደስ ዘንድ በዮርዳኖስ ወንዝ በውኃ አጥምቀኝ አለው።" ይላል። ( ድጓ ዘጥምቀት)። በቅዱስ ያሬድ አገላለጽ ጌታችን የተጠመቀው ውኃውን ይቀድስ ዘንድ ነው ማለት ነው። ይኸው ሊቅ በተጨማሪ "አኮ ዘረከበ ጸጋ በተጠምቆቱ አላ ከመ ያብርህ መካናት ወያኀይል ማያተ ለእለ ሀለወሙ ይጠመቁ ውስቴታ፦ በመጠመቁ ጸጋ አልተቀበለበትም ዮርዳኖስን ጽድልት ማኅፀን ለማድረግ፣ ጥምቀትን ለመቀደስ፣ ውኃዎችን ለመባረክ በውስጧ ይጠመቁ ዘንድ ላላቸው ኹሉ ነው እንጂ።" ይላል። (ጌታኹን ደምፀ (ሊቀ ጉባኤ)፣ ኆኅተ ስብከት ዘቅዱስ ያሬድ ቅጽ አንድ፣ 2010 ዓ.ም፣ ገጽ 559)። በዚህም መሠረታዊ ሐሳብ ምክንያት ጌታችን የተጠመቀው ስለ እኛ መኾኑን እንረዳለን።

ርቱዓ ሃይማኖት እንዲህ ይላል፦ "... እኔ ወደ ባሕር ካልወረድሁ የመድር ነገሥታት ይጠመቁ ዘንድ ወደ ባሕር አይወርዱምና። እኔ ካልተጠመቅሁ ውኃው አይቀደስምና፤ ዮሐንስ ሆይ፥ እኔ ካልተጠመቅሁ በውኃው ላይ መንፈስ ቅዱስ አይወርድም፤ ለሰዎችም ኹለተኛው ልጅነት አይሰጣቸውም፤ ..." እያለ ያስረዳል። (ተስፋ ሚካኤል ታከለ (መ/ር፡ ተርጓሚ)፣ ርቱዓ ሃይማኖት፣ 2004 ዓ.ም፣ ገጽ 77)። ይህም ማለት ጌታችን የተጠመቀው ውኃን ለመቀደስ፣ በውኃው ላይ መንፈስ ቅዱስ እንዲወርድ ለማድረግ፣ እኛ የምንጠመቃትን የልጅነት ጥምቀት ባርኮ ለመስጠት ነው። በበዓለ ጥምቀት ዕለት የምንረጨው የልጅነት ጥምቀትን ለመጠመቅ አይደለም። ኾኖም ግን የልጅነት ጥምቀት የተሰጠን በክርስቶስ መጠመቅ ምክንያት ነው። እርሱ ተጠምቆ ተጠመቁ ብሎናልና። እርሱ በዮርዳኖስ ተጠምቆ፥ ለእኛ የመጠመቂያ ገንዳውን ዮርዳኖስ አድርጎ፥ ውኃውን በመስቀል ላይ ከጎኑ ሰጠን። የልጅነት ጥምቀትን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ስንጠመቅ፡ የቅድስት ሥላሴ ልጅ የመኾን ጸጋ የሚሰጠን መኾኑን በእርሱ ጥምቀት በኩል እንድንመለከት አደረገን። በጥምቀቱ ምሥጢረ ሥላሴን የገለጠልን ሕሊናችንን ወደዚያ ድንቅ ምሥጢር እንድንወስድ ለማድረግ ነውና።

Telegram

ዮሐንስ ጌታቸው

ርቱዕ ሐልዮ ጥያቄና አስተያየት ካልዎት ይስጡ! @tmhrte\_tsdk\_bot

+++#ጌታችን\_ስለ\_ምን\_ተጠመቀ#+++
We recommend to visit

ከቅዳሜ በስተቀር በየዕለቱ፣ ከሰኞ እስከ ዓርብ ረፋድ ከ3:30 እስከ 5:00፣ እሁድ ከጠዋቱ 2:00 እስከ 4:00 በብስራት ኤፍ ኤም 101.1

Last updated 2 Wochen, 2 Tage her

የስራ ማስታወቂያ ከጋዜጣ ፣ ከቲቪና ራዲዮ ፣ ከማስታወቂያ ቦርድ ፣ ከድህረ-ገፅና ከማህበራዊ ሚዲያና ከመሳሰሉት ቦታዎች በአንድ ቦታ ተሰብስበው ያግኙ::

#Group t.me//Ethio_Jobs2000




#የመዝናኛ ቻናል https://t.me/+UPjrnHF6QzI0ZmQ0

https://t.me/+h0l2XzeI8RQyODlk

For promotion 📩 @Share_Home

Last updated 1 Tag, 13 Stunden her

Certified Professional Life Coaches
የቻናላችንን አነቃቂ ቪዲዮ መመልከት ለምትፈልጉ
https://www.youtube.com/@inspireethiopiamedia 👈 ይሄንን ሊንክ ይጫኑ

Last updated 4 Monate, 2 Wochen her