የስራ ማስታወቂያ ከጋዜጣ ፣ ከቲቪና ራዲዮ ፣ ከማስታወቂያ ቦርድ ፣ ከድህረ-ገፅና ከማህበራዊ ሚዲያና ከመሳሰሉት ቦታዎች በአንድ ቦታ ተሰብስበው ያግኙ::
#Group t.me//Ethio_Jobs2000
#የመዝናኛ ቻናል https://t.me/+UPjrnHF6QzI0ZmQ0
https://t.me/+h0l2XzeI8RQyODlk
For promotion 📩 @Share_Home
Last updated 1 month ago
ከቅዳሜ በስተቀር በየዕለቱ፣ ከሰኞ እስከ ዓርብ ረፋድ ከ3:30 እስከ 5:00፣ እሁድ ከጠዋቱ 2:00 እስከ 4:00 በብስራት ኤፍ ኤም 101.1
Last updated 4 months, 2 weeks ago
Certified Professional Life Coaches
የቻናላችንን አነቃቂ ቪዲዮ መመልከት ለምትፈልጉ
https://www.youtube.com/@inspireethiopiamedia 👈 ይሄንን ሊንክ ይጫኑ
Last updated 6 months, 2 weeks ago
++++#ወጣትነትን_ምንድን_ነው?++++
ወጣት የሚለው ቃል በግእዙ ወሬዛ ተብሎ ይጠራል። ይኸውም "ወሬዛ" ጎልማሳ፥ ጎበዝ፤ ለጋ፣ ወጣት፥ ካሥራምስት ዓመት በላይ ያለ፤ ለዘር የበቃ፥ ለማልሞ፤ " እንዲል አለቃ ክፍለ ወልድ። (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (አለቃ)፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ 2008 ዓ.ም፣ ገጽ 403)። ይህ ትርጒም ወጣትነት ምን እንደ ኾነ ዘርዘር አድርጎ ያስረዳል። ጎልማሳ የኾነ ማለትም በአንድ በኩል እንድገቱን ለማስረዳት የሚያግዝ ሲኾን በሌላ በኩል ከሕፃናት የተለየ ብስለትና አስተውሎት ያለው መኾኑን ይገልጻል። ዳዊት በጎልማሳነት ጊዜ መንገድን ቀና ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደ ኾነ ሲያስረዳ "በምንት ያረትዕ ወሬዛ ፍኖቶ። ወሬዛ (ጎልማሳ ወይም ወጣት) ግብሩን ጎዳናውን በምን ያቀናል ብትል፡ 'በዐቂበ ነቢብከ' (ቃልህን በመጠበቅ) ወይም ሕግህን በመጠበቅ ነዋ። አንድም እንዲህ ቢሉ ሕግህን በመጠበቅ አይደለምን? " ይላል። (ትንሣኤ ማተሚያ፣ መዝሙረ ዳዊት ትርጓሜ፣ 2005 ዓ.ም፣ ገጽ 572)። ስለዚህ ርቱዕና ጣዕም ያለው ወጣትነት የሚበቅለው በቃለ እግዚአብሔር የተጠበቀ ሕይወት ሲኖር ነው። በግል ስሜትና ፍላጎት የምንጓዝና ለእግዚአብሔር ቃል ቦታ የማንሰጥ ከኾነ መጠበቅ አንችልም። ወደ ብዙ የኀጢአት ሐሳቦች እየበረርን የመግባት ዕድላችንን እያጠፋን ነው የምንሄደው። ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ "ከክፉ የጎልማሳነት (የወጣትነት) ምኞት ግን ሽሽ" በማለት ጢሞቴዎስን ያስጠነቀቀው። 2ጢሞ 2፥22። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ይሄን ሲያብራራ "የዘመናዊነት ምኞት ብቻ አይደለም ማንኛውም ተገቢ ያልኾነ ምኞት የወጣትነት ምኞት ነው። የበሰሉ ሰዎች የወጣቶችን ምግባራት እንዳያደርጉ ይማሩ። አንድ ሰው ለስድነት ወይም ለብልግና የተሰጠ ቢኾን ወይም ሥልጣንን አፍቃሪ ቢኾን ወይም ሀብትን አልያም ሥጋዊ ደስታን የሚያፈቅር ቢኾን ይህ የወጣትነት ምኞት ነው። እናም ይህ ደግሞ ጅልነት ነው።" ይላል። (ኀይለ ኢየሱስ መርሻ (ተርጓሚ)፣ 2ጢሞቴዎስ በቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ 2009 ዓ.ም፣ ገጽ 100-1)። ስለዚህ የወጣትነት ፈተናው ከባድ መኾኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው።
መጋቤ ሐዲስ ስቡሕ አዳምጤ "ጎልማሳነት ወይም ወጣትነት ብዙ ፈተናዎች የሚያንዣብቡበት የሕይወት ጊዜ ነው። የወጣትነት ጊዜ ለመስማትም ለማየትም ለማድረግም ፈጣን የምንኾንበት ጊዜ ነው። ወጣትነት ሰዎች የሚያደርጉትን ሁሉ ለማድረግ ይገፋፋል። ጢሞቴዎስን በዚህ ወጥመድ ውስጥ እንዳይገባ ያስጠነቅቀዋል።" ይላሉ። (ስቡሕ አዳምጤ (መጋቤ ሐዲስ)፣ ከኤፌሶን እስከ ዕብራውያን ትርጓሜ፣ 2013 ዓ.ም፣ ገጽ 222)። እንግዲህ ወጣትነት ምን ያህል አስጨናቂ ጊዜ መኾኑን የምንረዳው ቅዱስ ጢሞቴዎስን ስንኳን ቅዱስ ጳውሎስ አስጠንቅቆ መምከሩን ስናስተውል ነው። በወጣትነት ጊዜ ወስጥ ለማንኛውም ድርጊታችን እጅግ በጣም ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ነገሮችን ቀለል አድርገን ከገባን በኋላ ስሕተት መኾኑን እንኳን ዐውቀን ለመውጣት ያስቸግረናልና። እንዲያውም ሊቁ ቅዱስ አምብሮስ "ወጣት ካህናት ባሏ ወደ ሞተባትና ድንግል ወደ ኾነች መሄድን ለተወሰነ ጉብኝት ካልኾነ በቀር መሄድን አይፈልግ። ይልቅ እንዲህ ላለው አገልግሎት ከፍ ያለ ካህን ወይም ጳጳስ ይሂድ። ዓለም እኛን እንዲተች እድል ለምን እንሰጠዋለን?" ይላል። (S.t Ambrose, On Duties of Clergy, 1፡20 (68, 87)። እንግዲህ በወጣትነት ውስጥ ያሉ አገልጋዮችም ቢኾኑ እኛ እኮ አገልጋይ ነኝ በማለት ራሳቸውን ማታለል የለባቸውም። አገልጋዮች አገልጋይ በመኾናቸው ምክንያት ራሳቸውን እያዘማነኑ መኖር ሳይኾን ያለባቸው የበለጠ ራሳቸውን እየጠበቁ ነው መኖር ያለባቸው። ቅዱስ ሄሬኔዎስ "ለደናግል ሴቶች ያለምንም ልዩነት ወይ እኩል ትኩረት ወይም እኩል ቸልታን ስጧቸው። ከእነርሱም ጋር በአንድ ጣራ (ቤት) ውስጥ አትቆዩ ወይም በቀደመው የንጽሕናችሁ ታሪክ አትመኩ። ከዳዊት በላይ ቅዱስ ከሰሎሞንም በላይ ጠቢብ አይደላችሁምና።" ይላል። (S.t Irenaeus, The author፡ pastoral love, p. 667 (in arabic) )።
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የወጣትነትን ክብደት ለመግለጥ እንዲህ ይላል፦ "የወጣትነት ዕድሜ የአውሬነት ጊዜ ነው። በመኾኑም ብዙ ተቆጣጣሪዎች፣ መምህራን ርእሳነ መምህራን፣ አገልጋዮችና የግል መምህራን ያስፈልጉታል። እነዚህ ሁሉ ተደርገውለት የአውሬነቱ ጠባይ ከቆመ ደስታ ነው። ያልተገራ ፈረስ ወይም ለማዳ ያልኾነ የዱር አውሬ ማለት ነው ወጣትነት። ነገር ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ ከልጅነት እድሜው አንሥቶ ከመልካም ሕግጋት ጋር እንዲጣበቅ ካደረግነው ብዙ ድካም ላይጠይቀን ይችላል። መልካም የኾኑት ልማዶቻቸው እንደ ሕግ ይቆጥራቸውና ጥሩነት የሕይወታቸው መመሪያ ና ሕግ ይኾናል።" በማለት ገልጾልናል። (ኀይለ ኢየሱስ መርሻ (ተርጓሚ)፣ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ወደ ጢሞቴዎስ አንደኛይቱ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንዳስተማረው፣ 2004 ዓ.ም፣ ገጽ 105)። ወጣትነት በራሱ በባሕርዩ ክፉ አይደለም ነገር ግን ክፉ ምኞቶች፣ ዘማዊነት፣ ዘፋኝነት፣ ትዕቢተኝነት፣ ሰካራምነት፣ ሱሰኝነተ የመሳሰሉ ክፉ ሥራዎችን እንድናደርጋቸው ውስጣችንን ዲያብሎስ በእጅጉ የሚፈትንበት ወቅት ነወ።
ስለዚህ ወጣቶች በዲያብሎስ ፈተና ከተሸነፉ ሰነፎች ናቸው ካሸነፉት ደግሞ ጎበዝ መባላቸው ይታወቃል ማለት ነው። ወጣትነትን አውሬ የሚያሰኘው ልክ እንደ አውሬ የሚያስፈሩ አስተሳሰቦች የሚመነጩበት አንድም ወጣቶች አውሬአዊ ሥራ ለመሥራት የሚወዱበት ወቅት ስለ ኾነ ነው። በተፈጥሮ አይደለም በራሳቸው ፈቃድና ፍላጎት ነው እንጂ። በዓይን አይታየንም እንጂ በዝሙት ሱስ በሌላም ከባድ ኃጢአት ውስጥ ያለ ወጣት የሚመስለው ዲያብሎስን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ክርስቶስን እንድንመስለው ነበር የሚነግረን። በወጣትነት ጊዜ ከሚመጡብን ክፉ ፍላጎቶች ኹሌም ቢኾን ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባል።
#ከትዕይንተ_ግብረ_ዝሙት_ለመውጣት_ምን_እናድርግ፦
1) ኃጢአትን ለንስሐ አባት በግልጽ መናዘዝ። ፈርተን ገና ለገና ምን እባላለሁኝ በሚል ከደበቅነው፡ ከትዕይንተ ግብረ ዝሙት ሳንላቀቅ ነው የምንቀረው። ስለዚህ ለንስሐ አባት እያንዳንዷን ነገር ዘርዝሮ ለንስሐ አባት መንገርና በምክረ ካህን መኖር በእጅጉ ጠቃሚ ነው። ከዚህ ርኲስ የኾነ ግብር እንድንወጣ ኀይል ይሰጠናል፥ ከእኛ በተጨማሪ የንስሐ አባታችን አባታዊ ጸሎት ይረዳናል።
2) እግዚአብሔር እንዲያነጻህ፣ እንዲያድስህ፣ አእምሮህን እንዲለውጥልህ በጸሎት መጠየቅ። በተለይ ልበ አምላክ ዳዊት ኃጢአቱን አምኖ በተማኅልሎ ኾኖ የዘመራትን መዝሙር 50 በእርሱ ቦታ ራሳችንን አስገብተን ጸሎትን በዝማሬ ለእግዚአብሔር እናቅርብ። "አቤቱ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት ኀጢአቴን ደምስስ። ከበደሌም ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኀጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ በደሌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁል ጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ። ... በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እኾናለሁ። ..." እያለ ልበ አምላክ ዳዊት ይዘምራል። መዝ 50፥1-7።
3) እግዚአብሔር አእምሮህን እውነት፣ የከበረ፣ ፍትሐዊ፣ ንጹሕ፣ የሚወደድ፣ ትእዛዛዊ በኾኑ ነገሮች እንዲሞላልህ በጸሎት መጠየቅ። ሰውነትን የሚቀድሱ ነገሮችን ለማድረግ በተግባር እየጣርን እግዚአብሔርን ደግሞ በጸሎት የምንጠይቀው ከኾነ ሕይወታችን እየቀናና እየተስተካከል ይሄዳል። ሰውነታችን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እንዲኾን "ሁለ ገብ የኾኑ የመንፈሳዊነት መገለጫዎችን በየቀኑ መለማመድ ወይም የሕይወታችን አካል ማድረግ፣ ለምሳሌ፦ የሥራ ፍቅር፣ ጥንቃቄ፣ ተስፋ፣ እምነት፣ ሐቀኝነት፣ ታማኝነት፣ ትሕትና፣ መነቃቃት፣ ወጥነት፣ ዓላማ ያለው፣ ፈጥኖ የመረዳት አቅም፣ የአመለካከት ከፍታ፣ አንድነት፣ ግልጽነት፣ ይቅር ባይነት፣ መረጋጋት፣ አገልጋይነት፣ ጥንካሬ፣ ሰላም፣ ታጋሽነት፣ አመስጋኝነት፣ ብስለት፣ ራእይ።" እነዚህን በደንብ እየተጉ ገንዘብ አድርጎ ለመንር መጋደል። (ስማቸው ንጋቱ (መጋቤ ምሥጢር)፣ የለውጥ አመራር ለቤተ ክርስቲያን፣ 2013 ዓ.ም፣ ገጽ 63)።
4) ሰውነታችን ቅድስናን ገንዘብ እንዲያደርግ መማር። ከልቡናችን ጥልቅ ሰውነታችን ቅድስናን ገንዘብ እንዲያደርግ መጣር። የሕይወት ዓላማ በቅድስና ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት መኾኑን ተረድተን በዚያ ውስጥ ለመኖር መጣር ያስፈልጋል።
5) የሩካቤ ሥጋን ትክክለኛ ትርጉሙን መረዳትና በተቀደሰ ጋብቻ ውስጥ ኾኖ ከባለቤት ጋር ብቻ ይህን በአግባቡ መፈጸም። የዝሙት ስሜት ሲያስቸግረንና ወደ ትዕይንተ ግብረ ዝሙት እየገፋፋ ሲያስቸግረን ወደ ቅዱስ ጋብቻ በቤተ ክርስቲያናዊ ሥርዓት ለመግባት ፈቃደ እግዚአብሔር በጾምና በጸሎት መጠየቅ። ምክንያቱም ፍትወት በእጅጉ አደገኛ እሳት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ "ፍትወት እሳት ነው፤ ያውም የማይጠፋና ዘወትር የሚኖር እሳት፤ ፍትወት ማለት እንደ ተበከለና ዕብድ ውሻ ነው። ምንም ያህል ከእርሱ እንሽሽ ብትሉም ኹል ጊዜ ወደ እናንተ ፈጥኖ ይመጣል፤ ይህን ማድረጉንም መቼም መች አያቆርጥም። የእቶን እሳት ክፉ ነው፤ የፍትወት እሳት ግን ከእቶን እሳት ይልቅ አረመኔ ነው። በዚህ ጦርነት ውስጥ የተኩስ ማቆም ስምምነት የሚታሰብ አይደለም። በሕይወተ ሥጋ እስካለን ድረስ ከዚያ ውጊያ ውጪ ኾኖ መኖር የሚገመት አይደለም። ዘወትር ውጊያ አለ። ይህ የሚኾነውም ሽልማቱም ታላቅ ይኾን ዘንድ ነው። ብፁዕ ጳውሎስ ኹል ጊዜ የሚያስታጥቀንም ለዚሁ ነው፤ ውጊያው ኹል ጊዜ ስለ ኾነ ጠላት ኹል ጊዜ ንቁ ስለ ኾነ።
ፍትወት ከእሳት ባልተናነሰ መልኩ እንደሚያቃጥል መማር ትወዳላችሁን? ሰሎሞንን አድምጡት፤ እንዲህ ያለውን "በፍም የሚሔድ እግሮቹ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወደ ሰው ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፤ የሚነካትም ኹሉ ሳይቃጠል አይቀርም" ምሳ 6፡28-29። እንግዲህ የፍትወት እሳት ከተፈጥሮ እሳት ጋር እንዴት እንደሚነጻጸር ታያላችሁን? እሳትን የሚነካ ሰው ሳይቃጠል መመለስ አይቻለውም። የቆነጃጅትን ፊት ዐይቶ የሚመኝ ሰውም ከዚያ እሳት በላይ ነፍሱን ያቃጥላል። አንድን ሰው በዝሙት ዐይን መመልከት ለሰውነት እንደ ላምባ ነው። ስለዚህ ምክንያት እኛም የዚህ ዓለም ነገሮችን በዚሁ መልኩ ልንመለከታቸው አይገባም፤ የፍትወት ነዳጆች ናቸውና።" በማለት ይገልጻል። (ገብረ እግዚአብሔር ኪደ (ተርጓሚ)፣ ወደ ቴዎድሮስ፡ ታኅሣሥ 2009 ዓም ገጽ 8-9)። እንግዲህ የጋብቻ አንዱ ጥቅም ሰይጣን በሰውነታችን የሚያነደውን የፍትወት እሳት ለማብረድ መኾኑን ልብ ይሏል።
6) በመንፈስ ቅዱስ ምሪት መሠረት መጓዝ። በመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ የምትመራ ከኾነ ወደዚህ ሐሳብ አትገባም። በእኛ ውስጥ ስሜት (Emotion)፣ ዕውቀት (Knowledge) እና መንፈሰ እግዚአብሔር (Holy Spirit) አለ። በዚህ መሠረት በስሜታችን ብቻ የምንመራ ከኾን ስሜታዊ ስለምንኾን ትዕይንተ ግብረ ዝሙትን የማየትን ዕድላችንን እናሰፋለን ማለት ነው። በዕውቀታችንም ሲኾን፡ ነገሮችን በእኛ አእምሮ ልክ የምንመጥንና የምንመዝን ከመኾንም አልፈን እኛ ልክ አይደለም ብለን ካሰብን ማንንም የማንሰማ እንኾናለን። እነዚህ ኹለቱ መንገዶች ጎጂዎች ናቸው። ስለዚህም በመንፈሰ እግዚአብሔር የምንመራና ስሜታችንንና ዕውቀታችንን ቅዱስ በኾነው በእግዚአብሔር መንፈስ ቁጥጥር ስር አድርገን የምንጓዝ ከኾነ፡ ትዕይንተ ግብረ ዝሙት ይቆጣጠረን ዘንድ አይቻለውም።
7) ወደ ትዕንተ ግብረ ዝሙት የሚወስዱህን ነገሮች በሙሉ ለመግታት መጣር። ፊልሙን፣ ማኅበራዊ ሚዲያውን ተወት ማድረግ ያስፈልጋል። ማኅበራዊ ሚዲያዎች በዋነኛነት ወደ ትዕይንተ ዝሙት እንድንሳብ ቅስቀሳ ስለሚያደርጉብን ከዚህ ስሜት እስክንወጣና በመንፈሳዊነት እስክናድግ ከሚዲያ ራሳችንን ራቅ ብናደርግና፥ ኃይል አግኝተን መንፈሳዊ ነገሮችን ብቻ እየመረጥን ለመጠቀም መትጋት አለብን።
8) ከትዕይንተ ግብረ ዝሙት የሚያስወጡ እርምጃዎችን ለመውሰድ አትዘገይ። ምክንያቱም 1000 Km ርቀት ያለውን መንገድ ከ1Km ተጀምሮ እንደሚደረስበት ቸል ማለት አይገባምና። ብዙ ጊዜ እየጎዳን ያለው ቁርጥ ውሳኔ አለመወሰናችን ነው። ውሳኔያችን ከጥልቅ የልቡናችን መሠረት ከኾነ፡ የማሸነፍ ኀይላችን ይጨምራል። ወስነን ማስወገድ ከጀመርን በኋላ ወደ ኋላ መመለስ የለብንም፡ ወደ ፊት እየገሠገሡ መሄድ እንጂ!
9) በትዕይንተ ግብረ ዝሙት የሚመጣውን አደጋ ለመፍታት ከመጣር ይልቅ ወደ ትዕይንተ ግብረ ዝሙት የሚወስደውን ምክንያት መፍታት ወይም ማጥፋት ላይ ማትኮር። ይህ አካሄድ ሥሩን ነቅለን እንድንጥለው ያደርጋል። ወደ ትዕይንተ ዝሙት የሚመራንን መሠረት ለመናድ በእጅጉ ይጠቅመናል። ስለዚህም ዋናውን መሠረት እስካላገኘን ድረስ እንደ ፓራስታሞል መፍትሔ ብለን የምናቀርባቸው ነገሮች ሁሉ ከተወሰነ ማስታገስ በቀር በሽታው ተመልሶ እንዳይነሣ ከማድረቅ በቀር ጥቅም የሌላቸው ሊኾኑብን ይችላሉ። ስለዚህም መሠረቱን ነቅሎ ለመጣል ወደ ትዕይንተ ግብረ ዝሙት የሚወስዱንን ነገሮች በሙሉ ነቅሶ ዘርዝሮ እነርሱን መከላከልና ማስወገድ ላይ መሥራት በእጅጉ ጠቃሚ ነው።
#እንደ_ግል_አዳኝህ_አድርገህ_ተቀበለው_ይባላልን?
መናፍቃን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኝህ አድርገህ ተቀበል ማለታቸው ትክክል ነውን? በፍጹም ትክክል አይደለም፡፡ ሲጀመር ይህ ዓይነቱ እምነት የሚመነጨው ትምህርቶችን በሙሉ “ብቻ” በምትል ቃል ውስጥ ከመክተት ነው። እምነት ብቻ፣ ጸጋ ብቻ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ፣ ኢየሱስ ብቻ የመሳሰሉትን ትምህርት በልቡ የጸነሰና በአፉ የወለደ ኹሉ ዞሮ ክርስቶስን በብቻ መርሕ ውስጥ ከትቶ እንደ ግል አዳኝ አድርገህ ተቀበለው ቢል ብርቅና ድንቅ አይደለም። ደግሞ አለማስተዋል ካልኾነና ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመረዳት አለመፈለግ ካልታከለበት በቀር ማዳንን ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መስጠት ትክክል አይደለም፡፡ ማዳን የአብ የወለድና የመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ውጤት ነውና፡፡ ቤዛነት ወይም መሥዋዕትነት ወይም የሰው ልጆችን ተክቶ (በተገብቶ) የተፈጸመው ሥራ ወልድ በሥጋዌው በተለየ አካሉ ያደረገው ነው፡፡ ይህንን ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ሰጥተን አንናገርም፡፡ ምክንያቱም በተለየ አካሉ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ በአዳም ቦታ ተገብቶ ራሱን ቤዛ አድርጎ ያቀረበው አማናዊው መሥዋዕት እርሱ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና። ይህን በተመለከተ ሩሲያዊው ቭላድሚር ሎስኪ የተናገረውን መ/ር ፀሐዬ ደዲማስ እንዲህ ተርጒሞልናል፡- "በእርግጠኝነት (የድኅነት) ሥራ የሚከናወነው ልዩ በኾነው ማንም በማይጋራው በሥላሴ ፈቃድ ነው፤ በእርግጠኝነትም የዓለም (የሰው ልጆች) ድኅነት የዚህ አንድና የጋራ የኾነው የሦስቱ አካላት ፈቃድ ውጤት ነው፡፡ … ነገር ግን ይህ አንድ ፈቃድ በድኅነት ሥራ ላይ የተፈጸመው በእያንዳንዱ አካል በተለያየ ኹኔታና አፈጻጸም ነው፤ አብ ላከ ወልድ ታዘዘ (ተላከ) መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ያከናውንና ይረዳ ነበር፤ በዚህም ወልድ ወደ ዓለም ገባ፡፡ የወልድ ፈቃድ ያው ራሱ የሥላሴ ፈቃድ ነው፤ ነገር ግን የተገለጠው በመታዘዝ ወይም በመላክ ነው፡፡ እኛን ያዳነን ሥላሴ ነው፤ ነገር ግን የድኅነትን ሥራ እውን ለማድረግ ሰው ኾኖ (በተለየ አካሉ) የተገተጠው ወልድ ነው፡፡" ይላል፡፡ ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን መናፍቃንን ይህን ጉዳይ ልብ እንዲሉ ትመክራለች፡፡
በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ክርስቶስ ዓለምን ያዳነው እያንዳንዱን ግለ ሰብእ እየዞረ በማዳን አይደለም፡፡ ማለትም 1000 ሰዎች ቢኖሩ ለሁሉም በየግል እየሄደ እየተሰቀለ ድኅነትን አልሰጠም፡፡ አንድ ጊዜ በመስቀል ላይ ለዓለም ሁሉ ተሰቅሎ፡ ራሱን ቤዛ አድርጎ ዓለምን አዳነ እንጂ፡፡ የተጸነሰውም፣ የተወለደውም፣ የተገረፈውም፣ የተሰቀለውም፣ ወደ መቃብር የገባውም፣ ሞትን ድል አድርጎ የተነሣውም፣ ያረገውም ለግለ ሰብእ ሳይኾን አንድ ጊዜ ለዓለም ሁሉ ነው፡፡ ዓለምን ሁሉ አንድ ጊዜ ስላዳነ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ አዳኝ መኾኑን ስንናገር ዓለም በተባለው ውስጥ የሰው ልጆች ሁሉ መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ የሰውን ልጆች በሙሉ ሲያድን እንዳንዱን ግለ ሰብእ ማዳኑን ልብ ይሏል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን የዓለም አዳን ስንል የሰውን ልጅ በሙል ከጽንስ እስከ ዕርገት በፈጸመው ቤዛነት በአንዴ ማዳኑን ለመግለጽ ነውና፡፡ ሁሉን በማዳን ውስጥ እያንዳንዱን አድኗል እንጂ እያንዳንዱን እያዳነ በመጨረሻም ሁሉን ወደ ማዳን የደረሰ አይደለም፡፡ እንግዲህ ሁላችንንም በየግላችን ሳይኾን በአንድነት ያዳነንን እንዴት በየግል ብቻ እንዳዳነን አደርገን የግል አዳኝ እንለዋለን?
በእኛ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት መሠረት እያንዳንዱ አማኝ ክርስቶስን መድኃኒቴ ማለት ቢችልም የግሌ መድኃኒት ግን አይልም፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ስትጸልይ "… ነፍሴ በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴትን ታደርጋለች …" በማለት አርአያ ኾናናለችና፡፡ ስለዚህ መድኃኒቴ፣ አምላኬ እንለዋለን ነገር ግን የግሌ መድኃኒት፣ የግሌ አምላክ አንለውም፡፡ ምክንያቱም የግሌ የሚለው አገላለጽ የሌሎችስ አይደለም እንዴ የሚል ጥያቄን ይፈጥራልና፡፡
በሌላ በኩል ካየነው ድኅነት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሚቻል እንደ ኾነ ያስመስላል፡፡ ምክንያቱም ከቅድስት ቤተ ክርስቲን ውጭ ኾኜ በግሌ ክርስቶስ ያድነኛል ማለት ፈጽሞ ስሕተት ነውና፡፡ ድኅነት ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ፈጽሞ የማይኾን ነውና፡፡ የመዳን መንገዶች በሙሉ ተዘርግተው የተቀመጡት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነውና፡፡ አንድ ሰው ሌላው ቀርቶ ቤተ ክርስቲያን አታስፈልገኝም ብሎ በግሉ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋዕት እና የመሳሱት አድርጎ እዳናለሁ ካለ እንኳን በፍጹም ተሳስቷል፡፡ ምክንያቱም በግል ብቻ ኾኖ መዳን አይቻልምና፡፡ ለመዳን የግድ ማመን፣ መጠመቅ፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል፣ ኃጢአት ሲሠራ ንስሐ እየገባ እንደ ገና ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል፣ መልካም ሥራዎችንም መሥራት አለበት፡፡ በዚህ መሠረት ለመጠመቅ፣ ለመቁረብ እና ንስሐ ለመግባት የግድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖር አለበት፡፡ እነዚህን ነገሮች በግሉ ብቻ ሊያደርጋቸው አይችልምና፡፡ ሌላው ቀርቶ በምንሠራው መልካም ሥራ እንኳን ብዙ ጉድለቶች ስለሚኖሩብን በቅዱሳን ቅድስና አምነን በስማቸው ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ የተጠሙትን ማጠጣት አለብን፡፡ ይህን ሁሉ መስመር የዘረጋው አምላካችን ክርስቶስ ነውና፡፡ እምነታችንም ቢኾን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረት ላይ ካለው ውጭ ከኾነ መዳን አይቻልም፡፡ ስለዚህ በምንም መንገድ ብናስብ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውጭ ኾነን በግል መዳን አንችልም፡፡ እንግዲህ "እንደ ግል አዳኝ አድርገህ ተቀበል" ማለት ከላይ ከተዘረዘሩት መሠረታዊ የመዳን መንገዶች ውጭ እድናለሁ ብሎ ማሰብ ነውና ፍጹም ስሕተት ነው፡፡ ያለ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ያለ ቤተ ክርስቲያን ጥምቀት፣ ያለ ቤተ ክርስቲያን ቁርባን እና ምሥጢረ ንስሐ መዳን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነውና፡፡
ከላይ የገለጽነውን ጉዳይ አጽንዖት ሰጥቶ ታላቁ ሊቅ ቆጵርያኖስ "ማንም ቢኾን ራሱን ከቤተክርስቲያን ለይቶ ከአመንዝራዎች ጋር ቢቀላቀል፤ ከቤተክርስቲያን ቃል ኪዳን ይለያል፤ ቤተክርስቲያንን ትቷት የሄደ የክርስቶስን የክብር አክሊል አያገኝም። እርሱ እንግዳ ነው፤ እርሱ የተቀደሱ ነገሮችን የሚያቃልል ነው፤ እርሱ ጠላት ነው። ቤተክርስቲያን እናቱ ያልኾነችለት እግዚአብሔር አባቱ አይኾንለትም። ማንም ከኖኅ መርከብ አምልጦ ውጭ ከኾነ ከቤተክርስቲያንም ውጭ ይኾናል በማለት የኖኅ መርከብ የተባለችውን ቅድስት ቤተክርስቲያንን ትቶ መሄድ ተገቢ አለመኾኑን ያስረዳል። በመኾኑም ድኅነት የሚገኘው የጸጋው ግምጃ ቤት በኾነች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በኩል መኾኑን ልብ እንበል፡፡ ስለዚህ እንደ ግል አዳኝህ አድርገህ ተቀበል የሚለውን ከላይ ያብራራነውን መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የሚንድ ክሕደታዊ ሐሳብ መኾን እንስተውል፡፡ ... !
ኢንስታግራም (Instagram) አድሬሴ ነው ስካን አድርጋችሁ ተቀላቀሉ።
++++#የአባትን_ምክር_እንስማ#++++
መልካም ወጣት የአባቶቹን ቃል ሰምቶ የሚተገብር፡ እነርሱን አርአያ የሚያደርግ እንጂ፡ ራሱን በግሉ ሐሳብ ብቻ የሚመራ አይደለም፡፡ ራእየ ኒፎን በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ የሚል አለ፡- “በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሳለን ዘወትር ከምሥጢራት ሊካፈል ወደ ቤተ ክርስቲያን በመገሥገሥ የሚተጋ ለጽድቁ ሥራ የሚጋደል አንድ ወጣት ወደ አባታቸን ቀርቦ “አባቴ ሆይ የዘለዓለም ሕይወት እንዳገኝ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው፡፡ “ልጄ ንጹሕ ነፍስ ያለችህ ኾነህ ሳለህ በኃጢአት ከተበላሸ አንድ ሽማግሌ ምን የሚጠቅም ነገር አለና ትጠይቀኛለህ?” አለው፡፡ “ምክንያቱም አባቴ የእግዚአብሔር ቃል “አባትህን ጠይቅ ይነግርሃል” ይላልና፤ ከአንተ የሚጠቅመኝን ቃል ለመስማት ጠየቅሁህ፡፡ እባክህ የማልጠቅም ከኾንሁ ከእኔ ፊትህን አትመልስብኝ፡፡”
“ለመመንኮስ አስበሃል ወይስ ለሰው ሁሉ የተፈቀደውን ሕይወት በመኖር ፈጣሪህን ደስ ለማሰኘት ነው ምኞትህ? በማለት ወጣቱን ጠየቀው፡፡ “አባቴ ለጊዜው በዚህ እየኖርሁ ለየትኛው ሕይወት የተገባሁ እንደ ኾንሁ ራሴን መፈተን እፈልጋለሁ፡፡ ከዚያ የእግዚአብሔር ፈቃድ ወደምትመራኝ እሄዳለሁ፡፡” አለው፡፡ እንግዲያውስ ልጄ በሰዎች መካከል የምትኖር ከኾነ በእነዚህ ነገሮች ዙሪያ ጥንቃቄ ልታደርግ ይገባሃል፡፡ በማንም ላይ ትችትን አትሰንዝር፤ በማንም አትሳለቅ፤ ለመቆጣት አትቸኩል፤ ማንንም አትናቅ፡፡ እገሌና እገሌ በቅድስና ይኖራሉ፤ እገሌና እገሌ ደግሞ በኃጢአት ተውጠዋል ብለህ ከመናገር ተጠንቀቅ፡፡ ምክንያቱም “በማንም አትፍረድ” ማለት ይህ ነውና፡፡ ሁሉንም ሰው በተመሳሳይ ሐሳብ በእኩል ወዳጅነት በንጹሕ ልቡና ተመልከት፡፡ እንደ ክርስቶስ አድርገህ ተቀበላቸው፡፡
በሰዎች ላይ የሚፈርድን ሰው ጆሮህን ከፍተህ አትስማው፡፡ የበለጠ ግን በሚሰጠው ሐሳብ ተስማምተህ ደስተኛ እንዳትኾን ተጠንቀቅ፤ አፍህንም ጠብቅ፡፡ በሌላ አነጋገር ለመናገር የዘገየህ ለጸሎት ግን የምትፋጠን ኹን፡፡ ምንም እንኳ እያደረገ ያለው ስሕተት ቢኾንም በሌሎች ሲፈርድ የሰማኸውን ሰውም በሕሊናህ እንዳትፈርድበት ተጠንቀቅ፡፡ ከዚያ ይልቅ የራስህን ድክመት እያሰብክ በራስህ ላይ የምትፈርድ ኹን፡፡” አለው፡፡
“አባቴ አኹን የነገርከኝ ዘወትር ሳያቋርጡ በተጋድሎ ለሚኖሩ ነው፡፡ የማልጠቅም እኔ እግዚአብሔርን እንዴት ደስ ማሰኘት እችላለሁ? በማለት የመከረውን ሁሉ በደንብ ከሰማ በኋላ ጠየቀው፡፡ “ልጄ በብዙ ምኞትና የሥጋ ፈቃድ ለሚቃጠል ወጣት ንጽሕናንና ትሕትናን ከያዘ ተስፋ ያለው ነው፡፡ በጸጋ እያደገ እስኪሄድም ጌታ እግዚአብሔር ከዚያ በላይ አይጠብቅበትም፡፡ ስለዚህ ወጣትነትህን በንጽሕናና በትሕትና አስጊጠው፡፡ ራስህን በትሕትና ከሁሉ በታች አዋርድ፡፡ ይህን ካደረግህ በእውነት ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ይኖርሃል፡፡
በሕሊናህም በቅድስና ታላላቅ ቅዱሳን የደረሱበት ከፍታ ላይ እንደ ወጣህ አታስብ፡፡ ይልቅስ ነፍሴ ሆይ በእግዚአብሔር ፊት የሚያቀርብሽ ምንም መልካም ሥራ የለሽም፡፡ ዕለት ዕለት በክፋት ከአጋንንት እንኳ እየባስሽ ሄደሻል፡፡ በፍርድ ቀን የሚጠብቅሽ ቅጣት ምን ያህል ይኾን? ወዮልሽ! በማለት ራስህን ውቀስ፡፡ ጸሎት ስትጸልይም በዓለም ካሉት ኃጢአተኞች ሁሉ የከፋው ሰው ጸሎት እንደ ኾነ ቊጠር፡፡ … አንድ ሰው ሲበድልህ ካየህ ስለ እርሱ ራስህን ውቀስ፡፡ አንተን ሰው ቢሰድብህ፣ ቢተችህ፣ ቢሳለቅብህ፣ ፈጽሞ ቢያዋርድህ እንኳ በሕሊናህ ራስህን አዋርደህ በሕይወት እንኳ ለመቆየት የማይገባህ መኾንህን እመን፡፡ ይቅርታና ድኅነት የሚመጡት እነዚህን ተከትሎ ነው፡፡” አለው፡፡ ( ታምራት ውቤ (ቀሲስ፣ ተርጓሚ)፣ ራእየ ኒፎን፣ 2013 ዓ.ም፣ ገጽ 222-228።
እንግዲህ የአበው ምክር እንዴት አድርጎ እንደሚቀርጽ ልብ እንበል፡፡ ይህን የመሰለ ወደ መልካምነት የሚመራ ምክር ልናገኝ የምንችለው በመልካምነት ሕይወት ውስጥ ካሉት አበው መኾኑን ልብ ማለት አለብን፡፡
++++++++++#ማኅበራዊ_መገናኛ#+++++++++
በዚህ ዘመን ወጣቶችን እያመከኑ ካሉ ሱሶች ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ የሚችለው የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ ነው። አብዛኛው ወጣት የማኅበራዊ ሚዲያ ባሪያ ወይም ተገዢ ኾኗል። ከምንም ነገር ቅድሚያም ሰጥቶ የሚጠቀመው ማኅበራዊ ሚዲያን ነው። የዚህ ጉዳት ከፍ የሚለው እስካለንበት ድረስ በማንኛው ሰዓት በእጃችን ባለው ስልክ ምክንያትነት መምጣቱ ነው።
ማኅበራዊ ሚዲያ የተሠራበት ዋጋ ዓላማ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች እርስ በእርስ የመገናኘት ዕድላቸው እያጠረ ሲሄድ ማኅበረ ሰብን ለማገናኘትና እንዳይራራቁ ለማድረግ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ መረጃምዎች፣ ሐሳቦችን፣ ፍላጎቶችን፣ ሌሎችንም የመረጃ ዓይነቶችን በኔትዎርክ እና እንደ መግባቢያ አድርጎ የሚያገናኝ ነው። https://en.m.wikipedia.org/wiki/Social_media። ማኅበረ ሰብን እርስ በእርሱ እንዲጠያየቅ፣ ለሐሳብ ለሐሳብ እንዲለዋወጥ፣ እርስ በእርስ እንዲረዳዳ፣ መረጃዎችንም እንዲለዋወጥ ማድረጉ በእጅጉ ጥሩ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ በአግባቡ የሚጠቀሙ ሰዎችን በብዙ ነገር ይጠቅማቸዋል። ለምሳሌ አንድ የኦርቶዶክሳዊት ተዋልዶ ቤተ ክርስቲያን አማኝ ስለ ቤተ ክርስቲያን ማወቅ ቢፈልግ፥ የተለያዩ ትምህርታዊ ስብከቶችን፣ ሥልጠናዎችን፣ ሥርዓቶችን ሌሎችንም በስብከትም ኾነ በጽሑፍ ማግኘትና መጠቀም ይችላል። መንፈሳዊ ሚዲያዎችን በመከታተል ከእነዚያ በሚያገኘው መልእክታት ሕይወቱን መለወጥና ማቅናት፥ ከጭንቀቱ መላቀቅ ይችላል። ኾኖም ግን በማኅበራዊ ሚዲያ ለመጠቀም ተጠቃሚው አካል አስቀድሞ ራሱን የገዛና መቆጣጠር የሚችል መኾን አለበት። ይህ የማይኾን ከኾነ በዚያ በኩል በሚወረወሩ ገዳይ ነገሮችም የመጠመድ እና ከክርስትና ሕይወት የመውጣት ዕድሉ ጉልህ ነው የሚኾነው።
በዚህ ጽሐፍ በዋነኛነት የምንመለከተው ከወጣቶች ሕይወት አንጻር እያስከተ ያለውን ጉዳት ነው። የአብዛኛው የከተሜው ወጣት በእጀጉ እየተጠቃ ካለባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ማኅበራዊ ሚዲያ መኾኑ ግልጽ ነው። ሰይጣን በእጃችን በያዝነው ስልክ በኩል ሕይወታችንን በእጅጉ እያረከሰው ነው። ይህ ማለት ግን ሰይጣን በማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል ያለ እኛ ፈቃድ አስገድዶ ያረክሰናል ማለት አይደለም። እኛ ግን ፈቃዳችንን ለእርሱ እንድናስገዛ ጽኑዕና ያልተቋረጠ ቅስቀሳ ያደርግብናል። የልቡናችንን የትኩረት አቅጣጫ በሙሉ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲሳብ ያነሣሣናል። ስለዚህ እጅግ በጣም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። እስኪ በዝርዝር የማኅበራዊ ሚዲያን ጉዳት እንመልከት፦
1) ወረኛ ማድረግ። አብዛኛዎቻችን ከምንም ነገር በላይ ወሬ እንድንወድና የወሬ ተከታታይ እንድንኾን ትልቅ ተጽዕኖ አድርጎብናል። አቡነ አትናስዮስ እስክንድር "ክርስቲያናዊ ፍጹምነትን ለማግኘት የምትፈልግ ከኾነ ሕሊናህን ለነፍስህ ከማይጠቅም ወሬ መጠበቅ አለብን።" ይላል። (ሄኖክ ኃይሌ (ዲን፣ ተርጓሚ)፣ ተግባራዊ ክርስትና፣ 2008 ዓ.ም፣ ገጽ 18)። ሚዲያ ለወሬ ፍቅር እንድንገዛ የሚያደርግ፥ በሕሊናችን ውስጥ ወረኛነትን የሚያትም ነው።
2) ጥገኛ መኾን። ማኅበራዊ ሚዲያዎች አእምሯችንን በአግባቡ እንዳንጠቀምና በሚዲያዎቹ ላይ ጥገኛ እንዲኾን ያደርጉታል። እውነት የኾነውን ነገር እንኳን በማኅበራዊ ሚዲያ አሳስቶ ቀርቦ ስናይ ሳንመረምር ወደ መቀበል እንፈጥናል። በራሳችን ማድረግ የምንችለውን እንኳን ለማድረግ እየሰነፍን እንሄዳለን። ሚዲያዎን የምንገዛና የምንቆጣጠር መኾን ሲገባን፥ ሚዲያው የሚቆጣጠረንና የሚመራን ይኾናል። መሪ መኾን የነበረብን እኛ በማኅበራዊ ሚዲያ ስንመራ ነገሮች ሁሉ ቀስ በቀስ ዝብርቅርቅ ማለታቸው አይቀርም። ብዙዎቻችን ያለ ማኅበራዊ ሚዲያ ምንም ማድረግ እንደ ማንችል አድርገን እስከ ማሰብ ሳንደርስ አንቀርም። ይህ ምን ያህል አእምሯችን እንደ ተጠቃ የሚያመለክት ነው።
3) ትዕግሥትን ማጣት። ትዕግሥት የሌለው ሰው ክርስቲያን ነኝ ይል ዘንድ አይገባውም። ትዕግሥት የሌለው ሰው ክርስቶስን ሊመስለውም አይችልምና። ማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎችን ችኩሎችና ረጋ ብለው የማያስቡ ያደርጋቸዋል። አንድ መልእክት በማኅበራዊ ሚዲያ ተለቆ ብናይ ወዲያውና ይህ መልእክት የማይስማማን መኾኑን በግርድፉ ብናስብ ወዲያው በግልጽ ተቃውሟችንን እናሰማለን። ነገሩን ከተጠቃ አእምሮ ነጻ ኾነን በእርጋታ መርምረን ተገቢ ሐሳብ ከማቅረብ ይልቅ ፈጥነን እንቃወማለን። አብዛኛውን ጊዜ የተለቀቁ መልእክታትን በእርጋታ ሳናነብ ወይም ሳናያቸው አሳስተን የምንረዳና ችኩልና ስሑት አስተያየት የምናቀርብ ብዙ ነን። አንዳንዴ የጽሐፍ ርእስ ብቻ አይተን እንዴት እንዲህ ይባላል እያልን የምንተች ሰዎችም አለን። አጫጭር ጽሑፍ ካልኾነ ወዲያው እናሳልፋለን፥ አጫጭር ቪዲዮ ካልኾነ መስማት አንፈልግም። እንግዲህ ይህ ሁሉ የሚያመለክተው የደረስንበትን የጉዳት መጠን ነው።
4) ግሩፓዊነትን መፍጠር። አንድ ሰው በኾነ ጉዳይ ላይ የተሳሳተ ሐሳብ ያለው ጽሑፍ ቢያቀርብ ያን ጽሑፍ like, share, comment የሚያደርጉ አካላት ቢደግፉት። በጸሐፊው ቀስቃሽነት ግሩፐኝነትን ይዘው አብረው ወደ ስሕተት ይፈጥናሉ። በተለይ ደግሞ ይህን የተሳሳተ ሐሳብ የተቀበሉት ሰዎች በርከት ካሉ በምንም መረጃ ስሕተት መኾናቸው ቢነገራቸው ውስጣቸው እሺህ ብሎ አይቀበልላቸውም። እንግዲህ ይህ የግሩፓዊነት መንገድ ወደ ጭፍን ደካፊነት ይወስዳል፥ ነገሮችን አጥርቶ የማየት ብቃትን ያደበዝዛል።
5) ራስን ማግነን ያመጣል። አብዛኛዎቻችን ራሳችንን የተሻልን እንደ ኾን አድርገን እናስባለን። የራሳችንን ጉድለት የማየት አቅም እናጣለን። ሰዎች በእኛ መልክ፣ አነጋገር፣ አለባበስ እና የመሳሰሉት እንዲማረኩና እንዲደነቁ በእጅጉ እንጨነቃለን። የሚያዩን የሚሰሙን ኹሉ እኛ ላይ ተለጥፈው እንዲቀሩ እንተጋለን። ይህ የማኅበራዊ ሚዲያ ትልቁ ችግር ነው። ሚዲያውን በመጠቀም ራሳችንን ለብዙዎች ጣዖት አድርገን እናቀርባለንና። አብዛኛዎቻችን በሚዲያዎች ፎቶዎቻችንን የምንለቀው ኾነ ብለን ለመደነቅ ለመወደድ ፈልገን ነው። ይህም ይታወቅ ዘንድ ሰዎች የለቀቅነውን ፎቶ አይተው ምንም ዓይነት like እና comment ባይሰጡን በእጅጉ እናዝናለን። በተለይ ሴቶች እኅቶች ደግሞ ኹሉም ወንድ እንዲወዳቸውና እንዲገዛላቸው ሊያደርግ በሚችል መንገድ ተጨንቀውና ተጠበው ፎቷቸውን ይለቃሉ።
#በኩረ_መዘምራን_ኪነ_ጥበብ_ወ/ቂርቆስ
ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብዙ አበርክቶዎችን ያደረጉ፤ በመዝሙራቸው ብዙዎችን ያጽናኑ፣ የብዙዎችንም ልቡና ወደ ንስሐ የመሩ፤ ከ50 ዓመታት በላይ ቤተ ክርስቲያንን ያገለገሉ። በዝማሬያቸው መሐል የሚመክሩ፣ የሚያጽናኑ አባታችን ቀድሞ ያማቸው በነበረው የጀርባ ሕማም ታመዋልና ለሕክምና ይኾናቸው ዘንድ እባክዎትን የበኩልዎትን ያድርርጉ ዘንድ ግዴታ እንዳለብዎት በመረዳት ከታች በተቀመጠው የእርሳቸው አካውንት ያስገቡ።
በእርግጥ እርሳቸውን ተለምነን አልነበረም ማሳከም የነበረብን፡ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ኹሉ አሟልተን ልንንከባከባቸው ይገባ ነበር። ግን ያው ብዙዎቻችን እውነተኛ አገልጋዮችን በአግባቡ ባለመከታተላችን በብዙ ችግር ውስጥ ኾነው ያገለግላሉ። አርአያ የሚኾኑንን ባናሳዝናቸውና በረከት ብናገኝባቸው መልካም ነው።
እንግዲህ የባንክ አካውንታቸው ይኸው እንረባረብ!
CBE
1000481007287
KINETIBEB W/KIRKOS W/MESKEL
CMC Michael Branch
የስራ ማስታወቂያ ከጋዜጣ ፣ ከቲቪና ራዲዮ ፣ ከማስታወቂያ ቦርድ ፣ ከድህረ-ገፅና ከማህበራዊ ሚዲያና ከመሳሰሉት ቦታዎች በአንድ ቦታ ተሰብስበው ያግኙ::
#Group t.me//Ethio_Jobs2000
#የመዝናኛ ቻናል https://t.me/+UPjrnHF6QzI0ZmQ0
https://t.me/+h0l2XzeI8RQyODlk
For promotion 📩 @Share_Home
Last updated 1 month ago
ከቅዳሜ በስተቀር በየዕለቱ፣ ከሰኞ እስከ ዓርብ ረፋድ ከ3:30 እስከ 5:00፣ እሁድ ከጠዋቱ 2:00 እስከ 4:00 በብስራት ኤፍ ኤም 101.1
Last updated 4 months, 2 weeks ago
Certified Professional Life Coaches
የቻናላችንን አነቃቂ ቪዲዮ መመልከት ለምትፈልጉ
https://www.youtube.com/@inspireethiopiamedia 👈 ይሄንን ሊንክ ይጫኑ
Last updated 6 months, 2 weeks ago